ፍሬ ሀይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት (mana dilbata firee amentaa)
187 subscribers
228 photos
8 videos
19 files
38 links
በዚህ መንፈሳዊ ቻናል የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሐይማኖታችንን እንድናውቅ የሚረዱ :-

፨ ከተለያዩ መንፈሳዊ ቻናሎች የምናገኛቸውን መረጃዎች አናጋራቹሃለን።

፨ ጥያቄ አና መልስ አንጠያየቃለን።


፨ መንፈሳዊ መፃህፍትን በ አማርኛ ፣ Afaan oromoo አና English language እናካፍላቹሃለን።

ሐሳብ አስተያየት ካላቹ @ye_gebriel ላይ አሳውቁን።
Download Telegram
Forwarded from መምህር ዘበነ ለማ (◦•●Yaredo●•◦)
#አንጨነቅ

በርግጥም ተፈጥሮአችንን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣው እርሱ ነውና፥ የሚያስፈልገን ምን እንደ ኾነም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለዚህ፡- “ርግጥ ነው፥ እርሱ አባታችን ነው፡፡ የምንሻቸው ነገሮችም እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን እንደሚያስፈልጉን አያውቅም” ማለት እንደ ምን ይቻልሃል? የገዛ ተፈጥሮአችንን እንኳን የሚያውቅ እርሱ፣ ማወቅ ብቻም ያይደለ ይህን ተፈጥሮአችንን የፈጠረ እርሱ፣ የፈጠረ ብቻ ያይደለ እንዲህ [ያስፈልጋል የምንለው ነገር እንደሚያስፈልገው] አድርጎ የፈጠረው እርሱ፥ አንተ ራስህ ለራስህ ያስፈልገኛል ከምትለው በላይ ምን እንደሚያስፈልግህ ያውቃል፡፡ ተፈጥሮአችን እንደዚህ ያለ ነገር እንዲያስፈልገው አድርጎ የፈጠረው እርሱ ራሱ ነውና፡፡ ስለዚህ እርሱ አስቀድሞ ያስፈልገዋል ብሎ ፈቅዶ ለፈጠረው፣ እንደሚያስፈልገው አድርጎ ፍላጎት ለሰጠው ተፈጥሮህ አያስፈልገውም ብሎ እንደ ገና ራሱን መቃወም አይቻለውምና፥ ተፈጥሮህ የሚሻውንና አጽንቶ የሚያስፈልግህን ነገር አይነሳህም፡፡

ስለዚህ አንጨነቅ፡፡ በመጨነቃችን ራሳችንን ከመጉዳት የዘለለ ሌላ የምናተርፈው ወይም የምናገኘው ነገር የለምና፡፡ እግዚአብሔር ብንጨነቅም ባንጨነቅም የሚያስፈልገንን ነገር ይሰጠናልና፡፡ በተለይ ደግሞ የማንጨነቅ ስንኾን የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያስፈልገን ዐውቆ ይሰጠናል፡፡ እንደዚህ ከኾነ ታዲያ እንዲያውም “አትጨነቅ” የሚለውን ትእዛዝ በመተላለፍህ ተጨማሪ ቅጣት በራስህ ላይ ከማምጣት በቀር፥ ተጨንቀህ የምታተርፈው ነገር ምንድን ነው? አንድ ሰው ወደ ባለጠጋ ሰው ቤት ለግብዣ እየኼደ “ምን እበላለሁ?” ብሎ አይጨነቅም፤ ወደ ምንጭ ውኃ እየኼደም “ምን እጠጣለሁ?” ብሎ አይብከነከንም፡፡ እንግዲያውስ እኛም ከየትኛውም ዓይነት ምድራዊ ምንጭ በላይ የተትረፈረፈ ውኃ ወይም ቊጥር የሌለው የተሰናዳ ማዕድ አለንና እርሱን እያየን ነዳያን ወይም በአእምሮ ሕፃናት አንኹን፡፡ ይኸውም መግቦተ እግዚአብሔርን ማለቴ ነው፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ፣ የማቴዎስ ወንጌል፣ ድርሳን ፳፪፥፫)

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመት ሲመጣ መደሰት፣ ብዙ መብልና መጠጥ ማዘጋጀት፣ አዲስ ልብስም መልበስ ጥቅም የለውም፡፡ ነፍሳችን በኀጢአት እየተጨነቀች፣ ነፍሳችን ተርባና ተጠምታ ሳለ፣ የተዳደፈ የኀጢአት ልብስም ተጆቡና ሳለ አዲስ ዓመት ማክበር ለእኛ ምን ጥቅም ይሰጠናል? እንዲህ ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት ለእኔ እንደ ልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡

ክርስቶስ ከዚሁ ሥራ አውጥቶናል፡፡ ከሕፃንነት አዕምሮ ወደ ማወቅ አሸጋግሮናል፡፡ ከምድራውያን ለይቶ ከሰማያውያን ጋር ደባልቆናል፡፡ ስለዚህ “መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” እንደ ተባለ አፍአዊ ሳይኾን መንፈሳዊውን ብርሃን ልናበራ ይገባናል (ማቴ.5፡16)፤ በአዲሱ ዓመት፡፡ ይህም ብርሃን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሚያስገኝ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለህ? ነፍስህ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋህን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለህ? አስቀድመህ ቤቱን (ነፍስህን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመህ ለነፍስህ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለህ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለህ አስብ እንጂ እንዲሁ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለሁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚሁ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ (1ኛ ቆሮ.10፡31)፤ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ይኼ ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

@fire_hymanot
@fire_hymanot
ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔርን ከማሳዘን ውጪ ምንም ይኹን ምን [አንፍራ፡፡] ሠለስቱ ደቂቅ የሚንበለበል እሳት በፊታቸው ቢያዩም ናቁት፤ ኃጢአትንም ብቻ ፈሩ፡፡ በእሳቱ ቢቃጠሉ ምንም የሚያስፈራቸው ነገር እንደሌለ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ባይገኝባቸው ግን እጅግ የከፋ ጉስቁልና እንደሚያገኛቸው ያውቃሉና፡፡ ምንም ሳንቀጣ ብንቀርም እንኳን እጅግ ትልቁ ቅጣት ግን ኃጢአት መሥራት ነው፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ምንም ያህል ቅጣት ቢያገኘንም እጅግ ትልቁ ክብርና ጸጥታ ግን በተጋድሎና በምግባር ሕይወት መኖር ነው፡፡

እግዚአብሔር ራሱ፡- “በደላችሁ በእናንተና በእኔ መካከል አልለየችምን?” ብሎ እንደ ተናገረ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ይለየናል (ኢሳ.59፡2)፡፡ ቅጣት ግን “እግዚኦ አምላክነ ሰላመ ሀበነ እስመ ኵሎ ወሀብከነ - አቤቱ አምላካችን ኹሉን ሰጥተኸናልና ሰላምን ስጠን” እንደ ተባለ ዳግመኛ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ ያደርገናል (ኢሳ.26፡12)፡፡

እንበልና አንድ ሰው ቁስል ወጣበት፡፡ የሚያስፈራው የትኛው ነው - የሚሰፋው ቁስል ወይስ የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ቢላ? ብረቱ ወይስ እጅግ እየባሰበት ያለው ቁስል? ኃጢአት የሚሰፋ ቁስል (Gangrene) ነው፤ ቅጣት ደግሞ የቀዶ ጥገናው ሐኪም ቢላ ነው፡፡ ያልፈረጠ የሚሰፋ ቁስል ያለው ሰው ሕመሙ እንዳለበትና ለወደፊቱም የማያፈርጠው ከኾነ ሥቃዩ እየባሰበት እንደሚኼድ ኹሉ፥ ቅጣት ያላገኘው ኃጢአተኛ ሰውም ከሰዎች ኹሉ ይልቅ ጎስቋላው ሰው እርሱ ነው፤ ለወደፊቱ ጭራሽ ቅጣትና መከራ የማያገኘው ከኾነ ደግሞ ከአሁኑ ይልቅ እጅግ ጎስቋላው ሰው እርሱ ነው፡፡ የጣፊያ ወይም የሆድ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ብዙ መብል ቢበሉ፣ ቀዝቃዛ መጠጦችን ቢጠጡ፣ የተለያዩ ዓይነት ጣፋጭና ቅመማ ቅመም የበዛባቸው መብሎችንም ቢወስዱ ይህ ድሎት ሕመማቸው እንደሚጨምረውና እንደ ሕክምናው ሕግ ራሳቸውን ከመብሉም ከመጠጡም በመጠኑ ቢወስዱ ግን የመዳን ተስፋ ሊኖራቸው እንደሚችል ኹሉ፥ በክፋት ዓዘቅት የሚኖሩ ሰዎችም ቅጣት ካገኛቸው በጎ ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል፤ ከክፋታቸው ጋር አብረው ዝንጋዔንና ድሎትን የሚጨምሩበት ከኾነ ግን ሆዳቸውን ከሚያማቸው ሰዎች በላይ እጅግ ጐስቋሎች ሰዎች ናቸው - ደዌ ዘነፍስ ከደዌ ዘሥጋ ይልቅ የከፋ ነውና፡፡ ተመሳሳይ ኃጢአት እያላቸው አንዳንዶቹ በማጣትና በብዙ ሕመም ሲሠቃዩ፣ ሌሎቹ ግን እስኪበቃቸው ድረስ እየጠጡና እየተስገበገቡ የሚበሉ እየተመቻቸውም በደስታ የሚኖሩ ሰዎችን ብትመለከት እነዚያ መከራ የሚቀበሉት የተሻሉ እንደ ኾኑ አስተውል፡፡ በእነዚህ መከራዎች የተወገደላቸው የፈንጠዝያ ሕይወት እሳት ብቻ ሳይኾን ሊመጣ ወዳለው ፍርድና አስፈሪ ዙፋን ሲኼዱም ከቀላል ዕረፍት ጋር አይደለምና፤ ስለኾነም እዚያ ሲኼዱ ከኃጢአታቸው የሚበዛውን በዚህ ዓለም ባገኛቸው ሥቃይ አስወግደው ነው፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
አንድ ሰው መጥቶ እናንተ የምትለብሱትን አንዲት ቁራጭ ልብስ እንኳ ሳይሰጣችሁና ሰውነታችሁ በብርድና በዋዕየ ፀሐይ እየተቆራመደ ሳለ ቤታችሁን በወርቅና በተንቆጠቆጠ የመጋረጃ ዓይነት ቢያስጌጥላችሁ ምን ጥቅም አለው? እኛስ ነፍሳችን ዕራቁቷን ሳለች ሥጋችንን ወርቅ ብናለብሰው በወርቅ ብናስተኛው ምን ትርጉም አለው? ነፍሳችን በመሬት ላይ እየተንፏቀቀች ሳለ ሥጋችን በከበሩ ሠረገላዎችና የተለያዩ ማጓጓዣዎች ብትንፈላሰስ ምን ጥቅም አለው?

ልጆቼ ! እውነተኛውን ልብስ ልበሱ ብዬ እመክራችኋለሁ። እዚህ የሚቀረውን ሳይኾን ዘለዓማዊውን ልብስ ልበሱ። የሰርጉን ልብስ ልበሱ።

እስኪ በየገዳማቱ ሒዱና ይህን ከቅዱሳን አበው ወእማት ተማሩ። እነዚህ ቅዱሳን በእልፍ ወትእልፊት ዕንቁ የተሽቆጠቆጠ ልብስ ብትሰጥዋቸው አይቀበሏችሁም። ለምን? እነርሱ ጋር ያለው ልብስ እናንተ ይዛችሁት ከሔዳችሁት ይልቅ በእጅጉ እንደሚበልጥ ስለሚያውቁ! ይኸውም የነፍሳቸው ልብስ ማለቴ ነው።

ለእነርሱ ይዛችሁት የሔዳችሁት ልብስ ለአንድ ምድራዊ ንጉሥ ብትሰጡት እጅግ ያመሰግናችኋል። እነርሱ ግን ከዚህ ንጉሥ በላይ በከበረ ልብሱ ያጌጡ ናቸውና አይቀበሏችሁም። ወርቃቸውን ወደሚያስቀምጡበት መዝገብ (ልቡናቸው) ገብታችሁ ስታዩ'ማ ራሳችሁን ስታችሁ ትወድቃላችሁ ። የሀብታቸውን (ምግባር ትሩፋታቸውን) ብዛት የወርቃቸውን ንጻት እንዲህ ነው ተብሎ የሚነገር አይደለም ። እናንተም ከእነርሱ ተማሩና እውነተኛውን ልብስ ለመልበስ ተሽቀዳደሙ ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

(ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ)
ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡

ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡

በሌላ አገላለጽ ብነግራችኁ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

@fire_hymanot
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ስለ_ቤተክርስቲያን

"አንድ ሰው ቤተ ክርስቲያን ከኖኅ መርከብ ትበልጣለች ቢል አልተሳሳተም፡፡ የኖኅ መርከብ እንስሳትን ወደ ውስጥዋ ብታስገባም እንስሳት አድርጋ ጠበቀቻቸው እንጂ አልለወጠቻቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን እንስሳትን ትቀበላለች፤ ትለውጣቸውማለች፡፡ ለምሳሌ ወደ ኖኅ መርከብ ቁራ ገባ፤ የወጣውም ግን ቁራ ኾኖ ነው፡፡ ተኵላ ገባ፤ የወጣውም ግን ያው ተኵላ ኾኖ ነው፡፡ እዚህ ቤተ ክርስቲያን ግን አንድ ሰው እንደ ቁራ ኾኖ ቢገባ የሚወጣው እንደ ርግብ ኾኖ ነው፡፡ ተኵላ ኾኖ ቢገባ የሚወጣው እንደ በግ ኾኖ ነው፡፡ እንደ እባብ ኾኖ ቢመጣ የሚወጣው እንደ ጠቦት በግ ኾኖ ነው፡፡ ተፈጥሮው ወደዚያ ስለሚለወጥ ግን አይደለም፤ ክፋቱ ስለሚርቅለት እንጂ፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ (ንስሐና ምጽዋት)

✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟

"ኃጢአት ሠርተሃልን? ወደ ቤተ ክርስቲያን ግባ ኃጢአትህንም አርቃት፡፡ በአደባባይ የምትወድቀው ቊጥሩ ከምትነሣው ጋር እኩል ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በደል ኃጢአት የምትሠራውን ያህልም ፍጹም ተስፋ ሳትቈርጥ ንስሐ ግባ፡፡ ኹለተኛ ብትበድል ኹለተኛ ንስሐ ግባ፡፡ በስንፍና ተይዘህ በፍጹም ምግባር ትሩፋት መሥራት አይቻለኝም አትበል፡፡ በእርግና ዘመን ብትኾንና ብትበድልም እንኳን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህ ንስሐ ግባ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሆስፒታል እንጂ ፍርድ ቤት አይደለችምና፡፡ እዚህ ስትመጣ ካህናት [“እግዚአብሔር ይፍታሕ” ብለው] ከኃጢአት እስራት ፈትተው ይቅርታ ይሰጡሃል እንጂ “ለምን በደልህ?” ብለው አይፈርዱብህምና፡፡ ስለዚህ፡- “አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ” ብለህ ለእግዚአብሔር ንገረው፤ ኃጢአትህም ይቀርልሃል (መዝ.50፡4)፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
"እየጾማችሁ ነውን?"
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

እንግዲያስ መጾማችሁን በተግባር አሳዩኝ፡፡ "እንዴት
አድርገን እናሳይህ?" ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፡- ድኻው እርዳታችሁን ፈልጎ እንደሆነ ቸርነትን አድርጉለት፤ የጠላችሁትን ሰው ካያችሁት ከእርሱ ጋር ፈጥናችሁ ታረቁ፤ ባልጀራችሁ ተሳክቶለት ስታዩት በእርሱ ላይ ቅናት አትያዙ፤ ቆነጃጅትን በመንገድ ሲያልፉ ስታዩ በዝሙት ዓይን አትመኙ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያደረጋችሁ በትክክል መጾማችሁን አሳዩኝ፡፡

በሌላ አገላለጽ አፋችሁ ብቻ ሳይሆን ዐይናችሁ፣ እግራችሁ፣ እጃችሁ፣ በአጠቃላይ የሰውነታችሁ ሕዋሳቶች በሙሉ መጾም አለባቸው፡፡
       + እጆቻችሁ ከመስረቅና የእናንተ ያልሆነውን
          ከመውሰድ ይጹሙ፤
       + እግሮቻችሁ የኃጢአት ሥራን ለመፈፀም
           ከመፋጠን ይጹሙ፤
       + ዐይኖቻችሁ ውጫዊ በሆነ ውበት ምክንያት
          ከመቅበዝበዝ ይጹሙ፡፡

ጥሉላትን (የፍስክ ምግብ) እየበላችሁ አይደለም አይደል? እንግዲያስ በዐይኖቻችሁም ክፉ ነገርን አትብሉ፡፡ የሚታዩ ነገሮች ለዐይን ምግቦች ናቸውና፡፡ ጀሮዎቻችሁም ይጹሙ፡፡ የጀሮ ጾም ሐሰተኛ ወሬንና ሐሜትን አለመስማትና ይህን የመሳሰለ ነው አንደበታችሁም ከከንቱ ንግግር ይጹም፡፡ ዓሣንና ሌሎች ጥሉላትን ከመብላት ተከልክለን ሳለ ነገር ግን ወንድሞቻችንን በሐሜት የምናኝካቸውና የምንበላቸው ከሆነ ምን ጥቅም አለው?

ወንድሙን የሚያማና የሚነቅፍ ሰው እርሱ የወንድሙን አካል ያቆስላል፤ ሥጋውንም ይበላል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ይህን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- "እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" /ገላ.5፡15/፡፡ ስታሙ በጥርሳችሁ የወንድማችሁን ሥጋ አትነክሱም፡፡ በክፉ ንግግራችሁ ግን የወንድማችሁን ነፍስ ትነክሳላችሁ፤ ታቆስሉትማላችሁ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ራሳችሁን፣ ወንድማችሁንና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ትጎዳላችሁ፡፡

አንደበታችሁ ክፉ ነገርን ከመናገር ካልጾመ ጉዳቱ
በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሐሜታችሁ እናንተን የሚሰማ ወንድማችሁም የሐሜታችሁ ተባባሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት እርሱንም በደለኛ ታደርጉታላችሁ ማለት ነው፡፡ እርሱም የራሱን ኃጢአት እንዳይመለከት ስላደረጋችሁት ሳያውቅ ከሐሜተኞች ጎራ ይቀላቀላል፡፡ በዚህም የሌሎች ወንድሞቹን ድካም እየተመለከተ እርሱ ግን በመጾሙ ትልቅ የጽድቅ ሥራን እንደፈጸመ ቆጥሮ ይኩራራል ስለዚህ አንደበታችሁም ክፉ ከመናገር ይጹም፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"ወዳጄ ሆይ ! መንፈሳዊ ተጋድሎን አትፍራ፥ ከእርሱም አትሽሽ፡፡ ተጋድሎ ከሌለ ምግባር ትሩፋትም የለምና፡፡ እምነትና ፍቅርም ካልተፈተኑ በእውን ከአንተ ጋር ስለ መኖራቸው ርግጠኛ መኾን አይቻልምና፡፡ እነዚህ በርግጥ አንተ ገንዘብ አድርገሃቸው እንደ ኾነ የሚታወቀው መከራ ሲገጥምህ ነውና፡፡ ስለዚህ ተጋድሎን አትፍራ፥ ከእርሱም አትሽሽ፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
"እግዚአብሔር የሚጠይቀው ጥቂት፣ የሚሰጠው ግን ብዙ ነው"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ይህን ያህል ቀን ጾምኩ አትበሉኝ፡፡ ይህን አልበላሁም ወይም ያንን አልበላሁም፣ የወይን ጠጅ አልጠጣሁም አትበሉኝ።

ይልቁንስ ከግልፍተኝነት ወደ ገርነት፣ ከጭካኔ ወደ ደግነት የተሸጋገርኽ እንደሆነ አሳየኝ፡፡ በአንተ ውስጥ ጥላቻና ቂም ቢኖሩ፣ በወይን ፋንታ ውኃ ብትጠጣ ምን ይጠቅማል? ጾም ብቻውን ስማያዊ ምንዳ አያስገኝምና፤ ትርጉም በሌለው በባዶ የፆም ሥርአት ራስህን አታስገዛ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#እግዚአብሔርን_መፍራት

ከፍርሃታችን የሚመጡትን ጥቅሞች ታያላችሁ? ፍርሃት ባይጠቅም ኖሮ አባቶች ለልጆቻቸው ሞግዚቶችን አይቀጥሩም፤ ሕግ አውጪዎችም በከተሞች ላይ ዳኞችን አይሾሙም ነበር። ከገሃነም የበለጠ የሚያስፈራስ ምን አለ? እናም ገሃነምን ከመፍራት የበለጠ የሚጠቅም ነገር የለም:: ገሃነምን መፍራት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይመራናልና፡፡ ይህ ፍርሃት ባለበት ምቀኝነት ቦታ የለውም፤ ይህ ፍርሃት ባለበት የገንዘብ ፍቅር ቦታ የለውም፤ ቁጣ ይጠፋል፣ ክፉ ምኞቶች ይወገዳሉ፡፡

አንድ ዘብ ሁልጊዜ ነቅቶ በሚጠብቅበት ቤት ውስጥ ሌባ፣ ዘራፊ ወይም ክፉ አድራጊ ሊመጣ እንደማይችል ኹሉ ፍርሃት አዕምሯችንን ሲይዝ፣ ልቅ ምኞቶች በቀላሉ አያጠቁንም፡፡ ይልቁንም ሸሽተው በየአቅጣጫው፣ በፍርሀት ምክንያት ይባረራሉ፡፡

ነገር ግን ፍርሃት ማባረር ብቻ አይደለም ጥቅሙ፤ ክፉ ፍላጎቶቻችንን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን በጎነት ወደ ነፍሳችን ለማምጣትም ይጠቅማል፡፡ ፍርሃት ባለበት ለጋስ መሆን አለ፤ የጸሎት ብርታት፣ ትኩስ የሚደጋገም እንባ እና ለንስሃ የነቃች ነፍስ አለች። ኃጢአትን የሚሸፍን በጎነትን የሚያብበው በማያቋርጥ የፍርሃት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ነው:: ስለዚህ በፍርሃት የማይኖር ሰው ልቡ ደንድኖ የሰይጣን ባርያ እንደሚሆን ኹሉ፣ በፍርሃት የሚኖር ሰው በማያውቀው ጎዳና እንደማይጓዝ ኹሉ፣ እግዚአብሔርን መፍራት በትክክለኛው የጥበብ መንገድ ይወስደናል፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ - #የነፍስ_ምግብ ገጽ 20 #በፍሉይ_ዓለም_የተተረጎመ)
ፈረስ የሚጋልብ ሰው ልጓሙን በአግባቡ ካልያዘው በቀር ፈረሱም ጋላቢውም ይጎዳሉ፡፡ አንድ እባብ የነደፈው ሰው ባለመድኃኒቶችን አግኝቶ መርዙ ወደ ሰውነቱ ኹሉ እንዳይሰራጭ ካላደረገ በቀር ወደ ሞት ሊደርስ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ትንሽ ቁስል በጊዜው ጊዜ ካልታከሙት በቀር ሰፍቶና ተስፋፍቶ ትልቅ ቁስል ወደ መኾን ያድጋል፡፡

በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድም እንደዚህ ነው፡፡ የኃጢአት ቁስል የሚሰፋው ችላ ሲባል ነው፡፡ ገና ትንሽ ነው በሚባልበት ደረጃ ካላራቅነው በቀር ነገ ከነገ ወዲያ ትልቅ ቁስለ ነፍስ ይኾናል፡፡

ተመልከቱ! ዛሬ ላለመቈጣት የሚታገል ሰው ነገ ሰዎችን የሚጎዳበት ዘዴን አይዘይድም፡፡ ሰዎችን የሚጎዳበት ዘዴ ካልዘየደም ብዙ ባልንጀሮች ይኖሩታል፡፡ ብዙ ባልንጀሮች ካሉት የሚጠላቸውም የሚጠሉትም ሰዎች አይኖሩም፡፡ ባልንጀራ እንጂ ጠላት የሌለው ሰውም የምግባር ኹሉ ፍጻሜ የኾነውን ፍቅር ገንዘብ ያደርጋል፡፡

ስለዚህ ተወዳጅ ሆይ! ወደዚህ ምግባር ታድግ ዘንድ ወደዚህ እንዳታድግ የሚያደርጉህን ጥቃቅን ኃጢአቶችን ከአንተ አርቅ፡፡ ሰፍቶ ተስፋፍቶ ነገ እንዳይቸግርህ ዛሬ በእንጭጩ እያለ ችላ አትበለው፡፡

ይሁዳ ገና የገንዘብ ፍቅር ደረጃ ላይ እያለ ራሱን ቢመረምርና ይህን ለማራቅ ቢጥር ኖሮ በኋላ ከተሰበሰበው ገንዘብ ወደ መስረቅ ባላደገ ነበር፡፡ ገና ከመጀመሪያው ደረጃ እያለ ችላ ባይል ኖሮ የኃጢአት ኹሉ ራስ የኾነው ኃጢአት ወደ መፈጸም ባልደረሰ ነበር፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደዚህ ልናደርግ እንደሚገባን ሲያስተምረን ከዝሙት ብቻ እንድርቅ ሳይኾን የእርሱ ሥር የኾነውንና አይቶ መመኘትን ችላ ልንለው እንደማይገባን ነገረን (ማቴ.5፡28)፡፡ ኃጢአት ሥር ሰዳና ሰፍታ ከመቸገራችን በፊት በችግኝ ደረጃ ላይ እያለች ነቅለን መጣል ቀላል ነውና፡፡ 

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ከቅዱሳን_ባሕታውያ_ጋር

በአንድ ወቅት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለ፡-ከዕለታት አንድ ቀን በሀገረ ስብከቴ ሥር በነበሩ በሜዲትራኒያን ባሕር በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩ ምእመናንን  ለመጎብኘት አሰብሁ፡፡ ከእኔ ጋር ቀሳውስትንና ዲያቆናትን አስከትዬ በጀልባ ተሳፍሬ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ተጓዝሁ፡፡ በደሴቱ ውስጥ ስንዘዋወር የሰው ዱካ ብንመለከትም  ምንም ሰው ማየት አልቻልንም ነበር፡፡ በአሸዋው ላይ ታትሞ የነበረውን የሰው ዱካ ተከትለን ስንጓዝ ካልተፈለፈሉ ዐለቶች የተሠራ ቤተ ክርስቲያን የሚመስል ዋሻ ላይ ደረስን፡፡

ዋሻው በርም ሆነ መስኮት የለውም፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ ልክ እንደ ሰባቱ ደማቅ ከዋክብት እጅግ በጣም አንጸባራቂ ብርሃን ቆመው ከሚጸልዩ ሰባት አባቶች ዘንድ ሲወጣ ተመለከትን፡፡ እኛም ከእነርሱ ጋር ለመጸለይ ባለንበት ቆምን። አባቶች ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ እኛ ዞሩና በፊቴ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሰገዱ። በመቀጠልም ሰላምታ ሰጡን፡፡ እኔ ዮሐንስም ‘እኔ አባታችሁና ፓትርያርካችሁ ዮሐንስ ነኝ’ አልኳቸው፡፡ ቅዱሳኑ እንደገና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በፊቴ ሰገዱ እና እኔን ደካማውን እንዲህ አሉኝ፡- “የምንወደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድትባርከንና እኛም አንተን በማየት እንድንበረታ ወደዚህ አመጣህ” አሉ። እኔም “እባካችሁ ታሪካችሁን ንገሩኝ” አልኋቸው፡፡

ሰባቱ አባቶችም “ከብዙ ዓመታት በፊት ሰባታችንም ከቍስጥንጥንያ ወጥተን በአንድነት ተሰባስበን ሕይወታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና በአምልኮ ብቻ ለማሳለፍ ወደዚህ ደሴት መጣን፡፡ ከዚህ ደሴት በደረስንበት ዕለት ከባሕሩ ከሚመጣው አስቸጋሪ ነፋስ ራሳችንን ለመከላከል ዋሻዎችን ለመገንባት ዐለቶችን ሰበሰብን፤ በሁለተኛው ቀን ደግሞ ይህን ቤተ ክርስቲያን መሥራት ጀመርን፡፡  በዐለቶች መካከል ከሚበቅለው ሣር እንበላለን፤ ውኃም ከባሕሩ እንጠጣለን፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን የከበቡትን እነዚህን የአሸዋ ክምሮች ለማስወገድ ፈልገን ነበር፤ ግን አእምሯችንና አሳባችን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስለተያዘ ጊዜ አጣን” በማለት ታሪካቸውን ነገሩኝ።

እኔም “መንፈሳዊ አባታችሁ የት ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ ይህን ጥያቄ ከመጠየቄ ወዲያውኑ አንድ ሽማግሌ በትሩን ተደግፎ ወደ እኔ ቀረብ አለና “እኔ የአንተ አገልጋይ ነኝ” አለኝ፡፡ አረጋዊው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ ራቁቱን ነበረና “ሰውነትህን የምትሸፍንበት ትንሽ ልብስ ትፈልጋለህ?” ስለው እሱም “ጌታ ከክረምቱ ቅዝቃዜ፣ ከበጋው ሙቀት ይከላከልልናል፤ ይጠብቀናልም” በማለት መለሰልኝ፡፡ “ምግብ ያስፈልጋችኋል?” ብዬ ስጠይቀው እርሱም “የሚበቃንን ያህል ከእነዚህ ዕፅዋት እንመገባለን ከዓለም የሆነ ምንም ነገር አያስፈልገንም” በማለት መለሰልኝ፡፡

እኔም “አባቶቼ እባካችሁ ለእኔ እና ስለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ጸልዩ” አልሁት። የእነዚያን ቅዱሳን ባሕታውያን አባቶች በረከት ከተቀበልን በኋላ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለም ምሥጋና የሚገባውን የምንወደውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያመሰገንን ወደ መጣንበት ተመለስን” ይለናል ቅዱሱ አባታችን ዮሐንስ አፈ ወርቅ።

ምንጭ፦ ግሑሣን አበው
#ወንድሞቼ!
ከእናንተ መካከል አንድ አይነ ሥውር ሰው ወደ ጉድጓድ ገብቶ ሊወድቅ ሲል እጁን ዘርግቶ የማይደግፈው ማን ነው? ታድያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በልቡናቸው ታውረው ወደ ሲዖል ጉድጓድ ለዘለዓለም ሲወድቁ እንደ ምን እጃችንን የበለጠ አይዘረጋም?ወገኖቼ!በነፍስም በሥጋም የታመመ ሰውን ስታዩ "ይህ የእኔ ሥራ አይደለም: የቀሳውስትና የመነኮሳት ሥራ እንጂ፡፡ ምክንያቱም ሚስት አለችኝ: ልጆችንም አሳድጋለሁ" አትበሉ፡፡

እስኪ ምሳሌ መስዬ ልጠይቃችሁ እናንተም መልሱልኝ፡፡ አንድ ትልቅ በወርቅ የተሞላ ሳጥን ወድቆ ብታዩ "ይህ እኔን አይመለከተኝም፡ ሌሎች መጥተው ያንሡት እንጂ" ትላላችሁን? ግራ ቀኛችሁን አይታችሁ በፍጥነት የምታነሡት አይደለምን?

ይህ ወደ ዘለዓለም ጉድጓድ እየወደቀ ያለው ወንድማችሁም ከዚያ ወርቅ በላይ ውድ የእግዚአብሔር ሀብት ነውና አንሡት እንጂ የበለጠ  እንዲወድቅ አትግፋት፡፡ እግዚአብሔር ይህን በተመለከተ በአፈ ያዕቆብ እንዲህ ብሏልና፡- "ወንድሞቻችን ሆይ! ከእናንተ ወገን ከጽድቅ ወጥቶ የበደለ ቢኖር መክሮ አስተምሮ ከበደሉ የመለሰው ቢኖር ራሱን አንድም ወንድሙን ከሞት እንዳዳነ ይወቅ፡፡ የራሱን አንድም የወንድሙን ብዙ ኃጢአቱን እንዳስተሠረየ ይወቅ፡፡ አንድም የወንድሙን ነፍስ እንዳዳነ ይወቅ"(ያዕ.5:19-20)፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ይህን ያህል ቀን ጾምኩ አትበሉኝ፡፡ ይህን አልበላሁም ወይም ያንን አልበላሁም፣ የወይን ጠጅ አልጠጣሁም አትበሉኝ።

ይልቁንስ ከግልፍተኝነት ወደ ገርነት፣ ከጭካኔ ወደ ደግነት የተሸጋገርኽ እንደሆነ አሳየኝ፡፡ በአንተ ውስጥ ጥላቻና ቂም ቢኖሩ፣ በወይን ፋንታ ውኃ ብትጠጣ ምን ይጠቅማል? ጾም ብቻውን ስማያዊ ምንዳ አያስገኝምና፤ ትርጉም በሌለው በባዶ የፆም ሥርአት ራስህን አታስገዛ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ