ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
650 subscribers
4.74K photos
5 videos
96 files
315 links
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :-
ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Download Telegram
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

            #ግንቦት ፲፱ (19) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ንጉሥ_ክህነት_ከንግሥና ጋር አስተባብሮ ለያዘው 40 ዓመት ሙሉ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ ከሰማይ እየወረደለት ለቀደሰው #ለጻድቁ_ለቅዱስ_ለይምርሐነ_ክርስቶስ ለልደት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።

                            
#ጻድቁ_ንጉሥ_ቅዱስ_ይምርሃነ_ክርስቶስ፡- ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ 14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስና አገልግለው አልፈዋል፡፡ በንግሥናቸው ሀገርን በመልካም ሥራና በቅድስና ከማስተዳደራቸው በተጨማሪ ቅዱሳን ጻድቃን ሆነው እግዚአብሔርን በብዙ ድካም በመልካም ተጋድሎአቸው ያገለገሉና አገልግሎታቸውም ሆነ ቅድስናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡

ከእነርሱም ውስጥ ሞትን ሳያይ እንደነ ሄኖክና ኤልያስ የተሰወረ አለ፤ ከእነርሱም ውስጥ በባሕር ላይ ቤተ መቅደሱን ያነጸ አለ፤ ከእነርሱም ውስጥ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር ራሱ ጌታችን በቃሉ ያስረዳው አለ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ በክህነቱ ሲቀድስ 40 ዓመት ሙሉ ቅዱስ ቁርባኑን መላእክት ከሰማይ እያመጡለት የነበረ አለ፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ነገሥታት ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ ምግባር ሃይማኖታቸው እጅግ ድንቅ ነው፡፡ የእነዚህ ቅዱሳን ነገሥታቱን የዘር ሐረጋቸው ከሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ "የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት" ወይም "የላስታ መንግሥት" በመባል ይታወቃል፡፡ ከዛጉዌ ነገሥታት ውስጥ የመጀመሪያው ንጉሥ መራ ተክለሃይማኖት የዐፄ ድልነአድን ልጅ መሶበወርቅን አግብቶ አራት ልጆችን ወልዷል፡፡ ሦስቱ ወንዶች ጠንጠውድም፣ ግርማ ስዩምና ዣን ስዩም ይባላሉ፡፡ ጠንጠውድም ገብረ መስቀልን ወለደ፣ ግርማ ስዩም ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ወለደ፣ ዣን ስዩም ደግሞ ቅዱስ ገብረማርያምንና ቅዱስ ላሊበላን ወለደ፡፡ ገብረ መስቀልም ጣራው ክፍት ሆኖ ዝናብ የማያስገባውን ገዳም የመሠረቱትን የመቄቱን ታላቁን አባት አቡነ አሮንን ወለደ፡፡ ቅዱስ ገብረማርያም ደግሞ ቅዱስ ነዓኵለአብን ወለደ፡፡

ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሳለ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል "ከጠንጠውድም በኋላ የምትነግሠው አንተ ነህ" በማለት ከነገረው በኋላ በመንገዱ ሁሉ እየተራዳው ወደ ኢትዮጵያ ይዞት መጥቷል፡፡ በቤተ መቅደስ ገብቶ ሲቀድስ መላእክት ሰማያዊ ኅብስትንና ጽዋን አምጥተው እየሰጡት እርሱም ለሕዝቡ ሁሉ ያቆርባቸው ነበር፡፡ ሕዝቡን የሚባርክበትም መስቀል ከሰማይ ነው የወረደለት፡፡ ዛሬም ድረስ አለ፣ በዓል ሲሆን ካህናት አባቶች እያወጡ ሕዝበ ክርስቲያኑን ይባርኩበታል፡፡ ጌታችን ለይምርሃነ ክርስቶስ በአካል ተገልጦለት እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ አካሉ እንደማይፈርስ ቃልኪዳን የሰጠውንና አሁን በላስታ ላሊበላ ያለውን ቤተመቅደሱን በባሕር ላይ እንዲሠራ ነግሮት በኋላም በቦታው ላይ እጅግ አስደናቂ ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ግንቦት 19 ቀን ሲወለድ እንደነ አቡነ ተክለሃይማኖትና እንደነ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ምሥራቅ ዞሮ አምላኩን ያመሰገነ ሲሆን ቤቱም በብርሃን ተሞልቶ ታይቶ አዋላጆቹን ሁሉ አስገርሟል፡፡ እርሱ ገና ሳይወለድ በፊት አጎቱ ጠንጠውድም በንግሥና ላይ ሳለ "ከአንተ በኋላ የሚነግሠው ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል ሰው ነው" ተብሎ ሲነገረው "እንዲህ የሚባል ሰው በቤተ መንግሥቴ አለን?" በማለት ቢጠይቅም እንደነቢዩ ኤርሚያስ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ የተመረጠ ሕፃን እንደሚወለድ ነግረውታል፡፡ አርባ ዓመት የነገሠው ጠንጠውድም ቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው "ይምርሃነ ክርስቶስ" የሚባል የወንድሙ ልጅ መወለዱን ሲሰማ "የወንድሜን ልጅ አየው ዘንድ አምጡልኝ" ብሎ ላከ፡፡ ባየውም ጊዜ ደም ግባቱ እጅግ ያምር ስለነበር "ይህስ መንግሥቴን ይውረስ፣ በእውነት ልጄ ነው" ብሎ ባረከው፡፡ ሆኖም ከእርሱ ጋር ስምንት ቀን ተቀምጦ በወለዳቸው ልጆቹ መካከል በተመለከተው ጊዜ በልቡ ሰይጣን አደረበትና በቅናት ሆኖ "እርሱ ነግሦ ልጆቼ ወታደሮቹ ሊሆኑ ነው" በማለት ይገድለው ዘንድ አሰበ፡፡ሆኖም ግን "ለጊዜው ምንም አያውቅም ለወደፊቱም የንግሥና ምሥጢር እንዳያውቅ ወደ እናቱና አባቱ ዘንድ መልሰው በዚያ ከብት ሲያግድ ያድጋል እንጂ ሥርዓተ ንግሥናን አያውቅም" በማለት ስለተመከረ ወደ እናቱ ላከው፡፡ በኋላም በጥበብና በብልሃት አስተዋይ ሆኖ ማደጉን በሰማ ጊዜ ሊገድለው አሽከሮቹን ላከ፡፡ እናቱም ለተላኩት አሽከሮች ምግብ አቅርባ እርሷ ግን ነገሩን እንዲገልጽላት እግዚአብሔርን በስውር አልቅሳ ስትለምን የንጉሡ ተንኮል ስለተገለጠላት ልጇን ደበቀችው፡፡ በስውርም ወስዳ ከጳጳሱ ዘንድ ዲቁና እንዲቀበል ካደረገችው በኋላ "ልጄ ሆይ! አጎትህ ሊገድልህ ይፈልግሃልና በፊቴ ከሚገድልህ ርቀህ ብትሄድ ይሻላል፣ ያዕቆብን ከኤሳው የጠበቀ አንተንም ይጠብቅህ" ብላ ሸኘችው፡፡

ንጉሡ አጎቱም "ይምርሃነ ክርስቶስን ፈልጎ ላገኘልኝ የመንግሥቴን እኩሌታ እሰጣለሁ" ብሎ ቢያውጅም ይምርሃነ ክርስቶስ ግን ወደ ኢየሩሳሌም ተሰደደ፡፡ በዚያም የሌዋውያን ወገን የምትሆን ቅድስት ሕዝባን አግብቶ ቅስናም ተቀብሎ ሥጋዊውንና መንፈሳዊውን ጥበብ ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ ወንጌልን እየሰበከ፣ በተአምራቱም ሕመምተኞችን እየፈወሰ እግዚአብሔር እያገለገለ ኖረ፡፡ እግዚአብሔርም አጎቱ ንጉሥ መሞቱንና በንጉሡም ዙፋን እርሱ እንደሚነግሥ ነግሮት በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መጥቶ በላስታ ወረዳ ሳይ (ዛሬ ሸጐላ ማርያም) ከምትባል ሀገር ደርሶ በዚያ ወንጌልን እያስተማረ፣ ድውያንን እየፈወሰ ተቀመጠ፡፡ ትምህርቱንና ተአምራቱን ያዩት የአካባቢው ሰዎች "ነፃነትና ፍቅር የሚገኝብህ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እኛ ሰላማዊ ብርሃናዊ ብለን ስም አወጣንልህ፣ ያንተ ግን ስምህ ማን ይባላል ንገረን" አሉት፡፡ እርሱም "ስሜ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው" ባላቸው ሰዓት ሕዝቡ ሁሉ በሹክሹክታ "ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል ሲነግሥ ሃይማኖት ይቀናል፣ ፍርድ ይስተካከላል፣ በዘመኑም የሮም ሰዎች ለኢትዮጵያ ይገዛሉ" ሲሉ አባቶቻችን ሰምተናል አሉ፡፡

ከጠንጠውድምም ሞት በኋላ ማንም እንዳልነገሠ ሲያረጋግጡ የማን ልጅ እንደሆነ እንዲነግራቸው በእግዚአብሔር ስም ለመኑትና "የጠንጠውድም የታናሽ ወንድምና የዣን ስዩም ታላቅ ወንድም የሆነው የግርማ ስዩም ልጅ ነኝ" አላቸው፡፡ እነርሱም "የተነገረው ትንቢት ደርሷልና ሳንዘገይ እናንግሠው" ብለው ሥርዓተ መንግሥቱን ፈጽመው በዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡ ለቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀልና ሰማያዊውን ኅብስት ከሰማይ ይወርድለት ነበር፡፡
ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ በትረ መንግሥቱንም ከያዘ በኋላ ሁሉም ሰው እንደወንጌሉ ቃል በአንድ ለአንድ ጋብቻ ብቻ ተወስኖ እንዲኖር በግዛቱ ሁሉ አወጀ፡፡ እግዚአብሔርም የሚመሰገንበት ቤት መሥራት አሰበና የተፈቀደለትን ቦታ እንኪያገኝ ድረስ ዛዚያ በምትባል ልዩ በሆነች ስፍራ ድንኳን ተክሎ እንደሙሴ እግዚአብሔርን ማገልገል ጀመረ፡፡ ዘጸ 33፡7። ሰኔ 21 ቀንም ቀድሶ ሕዝቡን ከማቁረቡ በፊት ኅብስቱንና ጽዋውን የእግዚአብሔር መልአክ ሕዝቡን ከሚባርክበት ሰማያዊ መስቀል ጋር ከሰማይ አምጥቶለታል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሕዝቡን ከሰማይ በወረደለት መስቀል እየባረከና ሰማያዊውን ኅብስትና ጽዋ እያቆረበ ለ22 ዓመት በድንኳኗ ውስጥ ኖሯል፡፡ ዛሬም ድረስ ያንን ሰማያዊው መስቀል በቤተመቅደሱ የሚያገለግሉት ካህናት አባቶች ቤተመቅደሱን ለመሳለም የሚመጣውን ሕዝበ ክርስቲያን በበዓል ቀን
ይባርኩበታል፡፡

ለቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ጌታችን ተገልጦለት ቤተ መቅደሱን በባሕር ላይ እንዲሠራ ነግሮታል፡፡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ እየወረደለት ለ22 ዓመት በድንኳኗ ውስጥ ካገለገለ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ተገልጦለት እንዲህ አለው፡- "ወዳጄ ይምርሃነ ክርስቶስ ይህን ሥፍራ (ዛዚያን) ልቀቅ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ቦታ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ አይወርድልህም፡፡ ወደማሳይህ ቦታ ተነሥተህ ሂድ፣ በዚያም እስከ ዕረፍትህ ቀን ድረስ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ ይወርድልሀል፡፡ ይህን ዓለም ለማሳለፍ እስከምመጣበት እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ የእኔ ጌትነት የአንተም የቅድስና ሕይወት የሚነገርበት፣ የሥጋህ የዕረፍት ቦታ የሚሆንበት፣ ለምትሠራው መቅደስ ክዳን የሚሆን ሣር የማይፈልግ ሰፊ ዋሻ አለ፣ በዚያ ቤተ መቅደሴን ሥራ፣ እኔም በምትሠራው ቤተ መቅደስ ከአንተ ጋር ለዘለዓለም ቃልኪዳኔን አቆማለሁ፡፡ በምታንጸው ቤተ መቅደስ ውስጥ "አቤቱ የይምርሃነ ክርስቶስ አምላክ ሆይ! ስለወዳጅህ ስለ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ብለህ ይቅር በለኝ" እያለ "አባታችን ሆይ!" የሚለውን ጸሎት የሚጸልይ ዕለቱን እንደተጠመቀ አደርገዋለሁ፡፡ ነገ ማለዳ ተነሥተህ ወግረ ስሂን ወደሚባለው የዕረፍትህ ቦታ ወደሚሆነው ዋሻ ሕዝብህን አስከትለህ ሂድ፤ በዚያም ቤተ መቅደሴን ሥራ" ብሎ ጌታችን ቃልኪዳን ከሰጠው በኋላ ሰላምታ ሰጥቶት በክብር ወደ ሰማይ ዐርገ፡፡ በዚች ቦታ እስከመጫረሻው በገድል ተጠምዶ ኖሮ ከእግዚአብሔር አምላኩ ብዙ ቃል ኪዳንን ተቀብሎ ጥቅምት 19 ቀን በክብር ዐረፈ። ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከቱ ያሳትፈን፣ በጸሎቱ ይማረን!።  ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

             #ግንቦት ፲፱ (19 ) ቀን።

እንኳን #ለኃይለኛ_ተጋዳይ ጌታችን አምስት ጊዜ ከሞት ላስነሣው ከዐሥራ ሁለት ዓመቱ ጀምሮ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ሲጋደል ለነበረ #ለቅዱስ_ኤስድሮስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና #ከአባ_መቃርስ ገዳም ለሆነ ከምግቡም የማዕጠንት አመድ ጨምሮ እየበላ ብዙ ዘመናት ለኖረ ለቅዱስ አባት #ለቀሲስ_ይስሐቅ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #ከቅዱስ_ኤስድሮስ እናት #ቅድስት_ሶፍያ_ከአባቱ_ቅዱስ_በድላዖን፣ ከእህቱ #ቅድስት_አፎምያ ከመታሰቢያቸውና #ከቅዱስ_ኤስድሮስ_ጋራ_ስምንት_መቶ_አምስት_ሺህ_ሰባት ሰዎች በሰማዕትነት ከዐረፉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                           
#ቅዱስ_ኤስድሮስ፦ ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር ከከበሩ ከቤተ መንግሥት ወገኖች ውስጥ ነው አባቱም በብዙ ሠራዊት ላይ የተሾመ መኰንን ነው። ስሙም በደላዖን ነው የእናቱም ስም ሶፍያ ነው ሁለቱም ከክርስቲያን ወገን ናቸው ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ ኤስድሮስ ብለው ሰየሙት።

ከብዙ ወራት በኋላም ከሀዲ ንጉሥ ከዲዮቅልጥያኖስ የሚያደርገውን የኃጢአትና የበደልን ብዛት በአየ ጊዜ እርሱ ከመንግሥት ታላላቆች ውስጥ ስለሆነ ምስፍናውን ትቶ ከሚስቱና ከልጁ ጋራ ገለል አለ። ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጻተኞች በመሆን ከዚህ ዐላዊ ንጉሥ ፊት ሸሽተው ሳሙኤል ከሚባል ሰው ዘንድ ተሰብስበው በገዳም ተቀመጡ።

ከዚህ በኋላ ለጣዖታት እንዳይሰግዱ ከንጉሡ ሸሽተው ስለተሠወሩ ከሀድያን መጥተው በንጉሡ ዘንድ ነገር ሠሩባቸው። ወዲያውኑ አምስት መቶ ጭፍራ ልኮ ከፊቱ አስቀረባቸው። ከእርሱ ዘንድ በመገለላቸውም ንጉሥ ጠየቃቸው እነርሱም እንዲህ አሉት "የክብር ባለቤት ክርስቶስን በካድከው ጊዜ ተውንህ ታላቅ ስንፍና አድርገህ ስተሃልና"። በሰማ ጊዜም ተቆጥቶ የበደላዖንን አንገት ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልን አገኘ። ቅዱስ ኤስድሮስን ግን ይመከር እንደሆነ ብሎ አሠረው ያንጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር።

ከጥቂት ቀን በኋላም በአንገቱ የብረት ዛንጅርና ገመድ አስገብተው ከንጉሥ ፊት አቀረቡት። ንጉሡም "አልፈራህምን ልብህስ ለመመለስ አልመከረምን" ብሎ ጠየቀው። እርሱም "እኔ የቀናች ሃይማኖቴን ትቼ ወደ ስሕተት አልመለስም" አለው። ያን ጊዜ አራቁተው ከምሰሶ ላይ ሰቅለው ደሙ እንደ ውሃ እስቲወርድ እንዲጨምቁት ንጉሥ አዘዘ። እናቱ ሶፍያም ከደሙ ወስዳ በንጉሥ ፊት ላይ ረጨች እንዲህም አለችው "ከሰው ሁሉ አንተ የተረገምክ ነህ" እንዲሁ እኅቱ አፎምያም ደንጋዮችን አንሥታ ንጉሡንና መኳንንቶቹን ወረወረችባቸው። ንጉሥም ተቆጣና ከወገባቸው መካከል እንዲቆርጧቸው አዘዘ ቆርጥዋቸውም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ አክሊልንም አገኙ።

ቅዱስ ኤስድሮስም ተሰቅሎ ሳለ በእናቱና በእኅቱ ላይ የሆነውን ይመለከት ነበር በወገቡም ላይ እሳት ፍም ደፋበት ደግሞም ሆዱን ሠንጥቀው አንጀቱን አወጡ። በተራራ ላይም ጣሉት የሰማይ ወፎችና የዱር አራዊት አልቀረቡትም። መድኃኒታችንም ከሞት አስነሥቶ እንደ ቀድሞ ሕያው አደረገው። ከዚያም ሔዶ በንጉሡ ፊት ቆመ ንጉሡም ከብረት ዐልጋ ላይ አውጥተው ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። ሁለተኛም በብረት ላይ አስተኝተው አንጀቱ እስቲፈስ ድረስ ፈጩት ከዚህም መድኃኒታችን አስነሣው።

ደግሞም ሁለተኛ ከስምንት መቶ ነፍስ ጋራ ሰቀሉት ያንጊዜም መድኃኒታችን አድኖ አስነሣው። ንጉሡም አይቶ በበሬ ቅርጽ በተሠራ ብረት ውስጥ አሥረው በላዩ ድኝና ዝፋት ጨምረው ከበታቹ እሳት እንዲአነዱ አዘዘ። ከጥቂት ቀን በኋላ ራሱን እንዲቆርጡት አዝዞ ቆረጡት ያንጊዜም ጌታችን ከሞት አነሣው እነሆ ሲያስነሣው ሦስተኛው ነው።

ደግሞ ከዚህ በኋላ እጅግ ከባድ የሆነ ደንጋይ በአንገቱ አሥረው ወደ ባሕር ጣሉት ወዲያውኑ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አውጥቶ ከንጉሥ ፊት አደረሰው። ንጉሡም በከተማ መካከል እንዲሰቅሉት አዘዘ እንደዚህም ተሰቅሎ ሞተ። የክብር ባለቤት ጌታችንም አስነሣው ይህም ሲያሥነሣው አራተኛ ጊዜ ነው። ከዚህም ለአንበሶች ጣሉት እግዚአብሔር ነቢዩ ዳንኤልን እንዳዳነ አዳነው።

ከዚህም በኋላ በየጥቂቱ ቆራርጠው እንዲከትፉትና በእንቅብ ሰብስበው ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ አሽከሮቹም እንዲሁ አደረጉ። ያን ጊዜም የክብር ባለቤት ጌታችን ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ጋራ መጥቶ በባሕሩ ዳር ቆመ ከዚያም አውጥቶ አስነሣው። ያለ ምንም ጉዳት ይህም ከሞት ሲያስነሣው አምስተኛ ነው።

ንጉሡም በአፈረና የሚያደርገውም በተሰናው ጊዜ ከወገኖቹ ጋራ ተማክሮ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ እጅና እግሩን አሥሮ ወደ ሰሎንቅያ አገር ላከው። የሰሎንቅያ አገረ ገዥም አስቀድሞ ስለ ሚያውቀው ከቅዱስ ኤስድሮስ ጋራ ቸርነትን ርኅራኄን አደረገ። ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ያንን መኰንንም እንዲአመጡት አዘዘ። ቅዱስ ኤስድሮስንም ወደ ርሱ መልሶ በእሥር ቤት በረኃብና በጽምዕ አኖረው ቅዱሱም በእሥራቱ መጠን ታላላቅ ድንቆች ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችን ሁሉ አዳነ።

በዚችም በግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በስድስት ሰዓት ከከተማ ውጭ እንዲሰቅሉት ንጉሥ አዘዘ። አየርም መላእክትን ተመላች የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙዎች ቃል ኪዳኖችን ከእርሱ ጋራ አደረገ። ያን ጊዜም ነፍሱን አሳለፈ። በማይጠፋ መንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊላትን ተቀበለ በተጋድሎ የኖረባቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመታቶች ናቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ኤስድሮስ በአማላጅነቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                           
#ቀሲስ_ቅዱስ_ይስሐቅ፦ ይህም አባት ከምሥር ከታናናሽ ቦታዎች ከአንዲት ቦታ ነው ወላጆቹም ድኆች ሲሆኑ ግን በበጎ ሥራ ባለጸጎች ናቸው። አረጋውያን መነኰሳትም የእጅ ሥራቸውን ሊሸጡ ወደ ምሥር በሔዱ ጊዜ ተከትሏቸው ወደ አስቄጥስ ገዳም መጥቶ ሲአገለግላቸው ኖረ። በቀንበራቸውም ተጠምዶ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ በዘመኑም ሁሉ ከቶ ምንም ጥሪት አላደረገም። እንደ አባቶቻችን ሁሉ ልብሶችን ለምን አልገዛህም ሲሉት እርሱም "እኔ እስከ ዛሬ ሕዝባዊ ነኝ በዓለም ሳለሁም ሁለት ልብስ የለኝም ነበር" ብሎ ይመልስላቸዋል። ሁለተኛም "አባቶቻችን እኮ ሰሌንና ማቅ ይለብሳሉ ለእኛም አንድ ልብስ ይገባናል ይህ አይበቃንምን" አላቸው።

ሁሉ ጊዜ የሚያለቅስ ሆነ "ለምን ታለቅሳለህ?" ብለው በጠየቁ ጊዜ "ወላጆቼ ሙተውብኝ ድኃ አደግ አድርገውኛልና" ይላቸዋል። ከምግቡም የማዕጠንት አመድ ጨምሮ እየበላ ብዙ ዘመናት ኖረ።

ከዚህ በኋላ ጭንቅ በሆነ ደዌ ተይዞ በታመመ ጊዜ ከወንድሞች አንዱ ምግብ ሠርቶ አመጣለት። እርሱም ከቶ አልቀምሰም ያም ወንድም "ይህ ጥሩ ምግብ ነው ለበሽታህም መድኃኒትነት አለውና ብላ" ብሎ ብዙ ለመነው። እርሱም "ወንድሜ ሆይ እመነኝ እኔ በዚህ ደዌ ውስጥ ሠላሳ ዓመት እኖር ዘንድ እወዳለሁ" ብሎ መለሰለት።
በዕድሜውም በሸመገለ ጊዜ ትሩፋቱና ጽድቁም በበዛ ጊዜ ቅስና ይሾሙት ዘንድ አረጋውያን ተሰብስበው ተማከሩ። እርሱም ከእርሳቸው ሸሽቶ ከተዘራ ማሳ ውስጥ ገብቶ ተሠወረ። እርሱንም እየፈለጉ ዞሩት አላገኙትም ያቺንም ማሳ አልፈው ከዳርዋ ተቀመጡ ጥቂት ሊያርፉ። ከእርሳቸው ጋራ አህያ ነበረ ወደ ማሳውም ሩጦ ገብቶ ይህ አባት በተሸሸገበት ቦታ ቆመ። አህያውን ሊያስወጡትም በገቡ ጊዜ ያንን አባት አገኙት። ደግሞ እንዳይሸሽ ሊአሥሩት ፈለጉ "አሁንስ ዐውቄዋለሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ" አላቸው ከዚያም አብሮአቸው ሒዶ ቅስና ሾሙት።

ከዚህ በኋላም ተጋድሎውንና ለአረጋውያን መታዘዙን ጨመረ ወጣቶችንም በጎ ሥራ ያስተምራቸዋል "ሰምትችሁ የምትታዘዙ ሁኑ ከትሩፋት ሁሉ ይህ ይበልጣልና" አላቸው።

የሚያርፍበት ጊዜ ሲደርስ ከእርሱ በኋላ የሚሠሩትን እንዲአስተምራቸው በዚያ ገዳም ያሉ ጐልማሶች በጠየቁት ጊዜ እንዲህ አላቸው "በገዳሙ ውስጥ ጸንታችሁ እንድትኖሩ እኔ ስሠራ ስታዩኝ እንደነበረ እናንተም እንዲሁ በፈቃዳችሁ ሥሩ። እኛ አባቶቻችን በዐረፉ ጊዜ አዝነን አልቅሰን ነበር እንደሚሠሩትም በሠራን ጊዜ ከእነርሱ በኋላ ተጽናንተን በገዳም የምንኖር ሆን"። ይህንንም እያለ በፍቅር በሰላም ግንቦት19 ቀን ዐረፈ የሕይወት አክሊልንም አገኘ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ይስሐቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የግንቦት19 ስንክሳር።

                          
"#ሰላም_ለኤስድሮስ_ንጹሕ እምሕብልያ። #ወልደ_በድላዖን_ዘአንጾኪያ። ድኅረ ኰነንዎ ሎቱ በዘዚአሁ አርአያ። ምስለ እኅቱ አፎምያ ወምስለ እሙ ሶፍያ። በእንተ ስሙ ተሰቅለ ለክርስቶስ ኬንያ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ(አርኬ) #የግንቦት_19

                          
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወበመንፈስከ ቅዱስ ይምርሐኒ በምድረ ጽድቅ። በእንተ ስምከ እግዚኦ አሕይወኒ በጽድቅከ። ወአውጽአ እምንዳቤ ለነፍስየ"። መዝ 142፥10-11። የሚነበበው ወንጌል 14፥25-ፍ.ም።

                           
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኃይለ። ኢይመውት ዘእንበለ ዘአሐዩ። ወእነግር ግብሮ ለእግዚአብሔር"። መዝ 117፥16-17። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 1፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 1፥6-10 እና የሐዋ ሥራ 8፥1-9። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 3፥10-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ወይም የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ዓቢየ እግዚእ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘንጂፋት፣ የአቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም፣ የአቡነ ብስጣውሮስ የዕረፍታቸው በዓል፣ የቅዱስ ኤስድሮስ፣ የአባ ይስሐቅ የዕረፍት በዓልና የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ግንቦት ፳ (20) ቀን።

እንኳን #ለጻድቁ_ለኢትዮጵያዊው_ንጉሥ የመን አገር ድረስ ዘምቶ በናግራን ያሉ ክርስቲያኖችን ከአይሁዳዊው ንጉሥ ከፊንሐስ ነጻ ላወጣቸው፤ የነገሠበት ዘውድ በጌታ መቃብር በጎልጎታ አስቀምጦ ንግሥናውን ትቶ ለመነነ #ለዐፄ_ለቅዱስ_ለካሌብ ለዕረፍት በዓልና #ለደብረ_ሊባኖስ ዐሥራ ስድስተኛ #አበ_ምኔት (እጨጌ) #ለአባ_ዘትረ_ወንጌል ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን።

                          
#ኢትዮጵያዊው_ጻድቁ_ንጉሥ_ዐፄ_ቅዱስ_ካሌብ፦ ይህም ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚፈራውና በፍጹም ልቡ የሚወደው ሃይማኖቱም የቀና ነው።

ናግራን አገር ያሉ ክርስቲያኖች አይሁድ እንደሚገድሏቸው በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ መንፈሳዊ ቅናትንም ቀና። ከዚህም በኋላ ተነሣ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገብቶ በመሠዊያው ፊት ቆመ ዐይኖቹንም ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ ጸለየ "ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ሆይ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠርህ መላእክት ሁሉ አእላፈ አእላፋት አንተን የሚያመሰግኑህ ለአንተም የሚገዙ ዐይኖቻቸው ብዙ የሆነ ኪሩቤል ክንፎቻቸው ስድስት የሆኑ ሱራፎልም ጽዕኑ ክቡር ልዩ ፍጹም አሸናፊ እግዚአብሔር በቅዱሳን የሚመሰገን እያሉ ያለማቋረጥ የሚያመሰግኑህ ብርሃን እንደ ልብስ የሚጐናጸፍ የክብር ባለቤት ለሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር ሆይ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ። የጠፋ በጎችን ይመለሳቸው ዘንድ ልጅህን ይኸውም ቃልህ ነው ፈቃድህ የላክኸው አንተ ነህ። ተናጋሪ በግ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳትለይ ከሰማይ የወረድክና ስለ እኛ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው የሆንክ ከጨለማም ከድንቁርናም አውጥተህ ወደ ብርሃን ወደ ሕይወት ወደ ዕውቀት የመራኸን። አሁንም ከሀዲ ወንጀለኛ ፊንሐስ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች እንደ በጎች በማረድ እንደ ገደላቸው እሳትም አቃጥሎ የወገኖችህንና የርስትህን ልጆች እንዳጠፋቸው እይ። እነሆ አብ ሆይ እኔ አመንሁብህ በአንድ ልጅህም በሕያው ቅዱስ መንፈስህም በመሠዊያህ ክብርም ተማፅኛለሁ በሃይማኖትህም ጸንቼአለሁ እንሆ ስለ አምልኮትህና ስለ ምዕመናን ወንድሞቼ ስለ ቀናሁ በአንድ ልጅህ መስቀል ጠላቶችህን ልዋጋቸው እወጣለሁና ከአለኝታዬ እንዳታሳፍረኝ የሚያውቁህም አምላካቸው ወዴት ነው እንዳይሉ። ስለ በደሌና ስለ ኃጢአቴም ጸሎቴን የማትሰማ ልመናዬንም ንቀህ የምትተው ከሆነ በዚህ ቦታ ብትገድለኝ ይሻለኛል። አቤቱ መሐሪ ይቅር ባይ ርኅሩህ ርስትህ የሆኑ ምዕመናንን በከሀድያን ጠላቶችህ እጅ አሳልፈህ አትስጥ። እኛ ወገኖችህና የርስትህ መንጋዎች ስለሆን ለአንተም ምስጋና እናቀርባለን ምስጋና ገንዘብህ ነውና ለዘላለሙ"።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ካሌብ ከአገረ መንግሥቱ ወጥቶ ሔደ የናግራንን አገር ያጠፋአት አይሁድን ገደላቸው ብዙ ተአምራትም አድርጎ ስለ አደረገለት ሁሉ እግዚአብሔር እያመሰገነ ወደ አገረ መንግሥቱ በታላቅ ክብር በታላቅም ደስታ ተመለሰ። "ለእግዚአብሔር ምን ዋጋ እከፍለዋለሁ ለጌትነቱና ፍጹም ለሆነ ገናናነቱ መባ አድርጌ ነፍሴንና ሥጋዬን ከማቀርብለት በቀር" አለ።

ከዚህም በኋላ ይህን ዓለም ንቆ መንግሥቱንም ትቶ ወጣ ደጋጎች መነኰሳት ወደ ሚኖሩበት ወደ አባ ጰንጠሌዎን በተራራ ላይ ወደ አለ ገዳም እስከ ደረሰ በእግሩ ሔደ። ወደ ዋሻ ውስጥም ገብቶ ሰውም እንዳያየው የዋሻውን በር ዘግቶ በዚያ ውስጥ ኖረ ከዚያችም ወጥቶ ዳግመኛ ዓለምን እንዳያይ ማለ። ከእርሱ ጋራም ያገባው ዕቃ የለም ከምንጣፍ ከሸክላ ጽዋ ከለበሳት የምንኵስና ልብስ በቀር ምግቡም አምባሻና ጨው የሚጠጣውም ውኃ ነው።

የክብር ባለቤት ከሆነ እግዚአብሔር ቃል መቃብር መስኮት ላይ ይሰቅልለት ዘንድ የኢየሩሳሌሙን ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስን እየለመነው ወጋው ብዙ የሆነ የነገሠበትን ዘውድ ላከ። ወደ ዋሻውም ከገባ በኋላ ከማንም ጋራ አልተነጋገረም እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶ በፍቅር አንድነት ግንቦት 20 ቀን ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ዐፄ ካሌብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                          
#አባ_ዘትረ_ወንጌል፦ ይህም ቅዱስ የደብረ ሊባኖስ ዐሥራ ስድስተኛ አበ ምኔት የሆነ ነው። ከታናሽነቱ ጀምሮ እንደ መላእክት ንጽሕናን የለበሰ ትሕትናን ቅንነትን የሚወድ ነበረ። የምንኵስናንም ልብስ ከለበሰ በኋላ መልካም ገድልን ተጋደለ በክርስቶስ መንጋ ላይም ጠባቂ ሁኖ ተሾመ ከዚያም በኋላ በበጎ እርጅና ግንቦት 20 ቀን ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የአባ ዘትረ ወንጌል በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦ #የግንቦት_20 ስንክሳር።
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

          #ግንቦት ፳ (20) ቀን።

እንኳን #ለሀገረ_ቶና ለከበረ ልታስተው የመጣችውን ሴት በማስተማር ለቅድስና ላበቃ #ለአባ_አሞንዮስ ለዕረፍት በዓል መታሰቢያ እግዚአብሔር ከምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚህ ቀን ከሚታሰብት፦#አባ_አሞንዮስ ለቅድስና ካበቃት #ከቅድስት_ሳድዥ ከመታሰቢያዋ፣ #ከቅዱስ_አሞኒ ረድእ #አባ_ዳርማ ከዕረፍት፣ #ከአባ_ኄሮዳና #ከአባ_ዘካርያስ ጋር በሰማዕትነት ከዐረፉበት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                          
#አባ_አሞንዮስ፦ ይህም ቅዱስ ጐልማሳ ሁኖ ሳለ አባ እንጦንዮስ ወደ ምንኵስና ሲጠራው ራእይን አየ። በነቃም ጊዜ ተነሥቶ ወዲያውኑ ወደ አባ ኤስድሮስ ሔደ ከእርሱም አስኬማን ለብሶ እያገለገለውም በእርሱ ዘንድ ኖረ።

ከዚህ በኋላ ወደ ደብረ ቶና ተመልሶ ለራሱ በዓትን ሠራ በታላቅ ገድልም ተጠምዶ በቀንና በሌሊትም ተጋደለ። ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ በሴት መነኵሲት አምሳል ወደርሱ መጣ የበዓቱን ደጃፍ በአንኳኳ ጊዜ ከፈተለትና ገባ "ቅዱሱም ተነሥተን እንጸልይ" አለው ያን ጊዜ ተንኰሉን ገለጠ መልኩም እንደ እሳት ላቦት ሆነ ቅዱሱንም "እኔ ታላቅ ጦርነት አመጣብሃለሁ" አለው።

ከዚህም በኋላ መልኳ ውብ ወደ ሆነ ወደ አንዲት ወጣት ሴት ሰይጣን ሒዶ አነሣሣት። ቅዱስ አሞንዮስን እርሷ ጋራ በኃጢአት ልትጥለው ቀጭን ልብሶችን ለብሳ ወደ ርሱ በምሽት ጊዜ ደረሰች። እንዲህም እያለች ደጃፉን አንኳኳች "እኔ መጻተኛ ሴት ነኝ መንገድንም ስቼ በምሽት ጊዜ ከዚህ ደረስኩ አራዊትም እንዳይበሉኝ በውጭ አትተወኝ እግዚአብሔርም ስለ እኔ ደም እንዳይመራመርህ" አለችው። በከፈተላትም ጊዜ የሰይጣን ማጥመጃው እንደ ሆነች የላካትም እርሱ እንደሆነ አወቀ በአምላካውያት መጻሕፍት ቃልም ገሠጻት ለኃጥአን ስለ ተዘጋጀ የሲዖል እሳትም አስገነዘባት ሁለተኛም ለጻድቃን ስለ ተዘጋጀ ፍጹም ተድላ ደስታ ነገራት። ያን ጊዜም የሚላትን ታስተውለው ዘንድ እግዚአብሔር ልቧን ከፈተላት። መልካሙንም ልብስ ከላይዋ አውጥታ ጣለች ከእግሮቹ በታችም ሰግደች ነፍሷንም ያድን ዘንድ በማልቀስ ለመነችው። የጠጉር ልብስም አለበሳት ራስዋንም ተላጭታ በገድል ሁሉ በብዙ ትሩፋትም ተጠመደች በቀንም በሌሊትም ዐሥራ ሁለት ጊዜ የምትጸልይ ሁናለችና በየሁለትና በየሦስት ቀንም ትጾማለች።

ሰይጣንም በአፈረ ጊዜ በመነኵሴ ተመስሎ በየአንዳንዱ ገዳም ሁሉ በመግባት እያለቀሰና እያዘነ እንዲህ አላቸው "በአባ አሞንዮስ ቤት ሴት አለችና እርሱ ታላቅ ገድል በኋላ የአንዲትን ሴት ፍቅር ወዶአልና እርሷም በእርሱ ዘንድ በበዓቱ ውስጥ ትኖራለች እነህ መነኰሳትን አሳፈራቸው እስኬማውንም አጐሳቈለ"።

የመላእክት አምሳል የሆነ ጻድቅ አባ ዕብሎ ያን ጊዜ ተነሣ አባ ዮሴፍንና አባ ቦሂንም ከእሱ ጋራ ወሰዳቸው። ወደ ቅዱስ አሞንዮስ ገዳም ደብረ ቶና ደረሱ ደጃፋንም በአንኳኩ ጊዜ ያቺ ሴት ወደ እርሳቸው ወጣች እርስ በርሳቸውም "ያ መነኵሴ የነገረን እውነት ነው ተባባሉ። የከበረ አሞንዮስም ሳድዥ ብሎ ስም አውጥቶላታል ይህም የዋሂት ማለት ነው። ገብተውም ጸሎት አድርገው የእግዚአብሔርንም ገናናነት እየተነጋገሩ እስከ ምሽት ተቀመጡ። አባ አሞንዮስም "አምበሻ እየጋገረችልን ነውና ተነሡ ሳድዥን እንያት" አላቸው። በገቡም ጊዜ በሚነድ የእሳት ምድጃ ውስጥ ቁማ እጆቿም ወደ ሰማይ ተዘርግተው ስትጸልይ አገኙዋት። አይተውም ስለዚህ ድንቅ ሥራ እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርም አመሰገኑ።

ከዚህ በኋላም አቅርባላቸው በሉ። በዚያችም ሌሊት መልአክ ስለ አባ አሞንዮስና ስለ ሳድዥ ገድላቸውን ለአባ ዕብሎ ነገረው "ወደዚህም ዛሬ ያደረሳችሁ እግዚአብሔር ነው የሳድዥን ዕረፍት እንድታዩ" አላቸው። ሦስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ የሚያስጨንቅ የሆድ ዝማ ታመመች በእግዚአብሔር ፊት አንዲት ስግደትን ሰገደችና በዚያም ነፍሷን ሰጠች መልካም አገናነዝም ገንዘው ቀበሩዋት።

አባ አሞንዮስም ትሩፋቷን ሊነግራቸው ጀመረ እርሷ በእርሱ ዘንድ ዐሥራ ስምንት ዓመት ስትኖር ከቶ ፊቷን እንዳላያት ምግባቸውም አምባሻና ጨው እንደሆነ። ከጥቂ ቀን በኋላም አባ አሞንዮስ ግንቦት 20 ቀን ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን በአባ አሞንዮስና በቅድስት ሳድዥ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የግንቦት 20 ስንክሳር።

                           
#"ሰላም_ሰላም_ለረዳኢተ_አሞንዮስ ሳድዥ። ዝ ብሂል የዋሂተ ግዕዝ። በሑረታቲሃ አዳም ወበምግባራ ሐዋዝ። ኢውዕየት ቀዊማ ከመ ዘመጥልል ውኂዝ። ማዕከለ ውዑይ ወርሱን ማሕበዝ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የግንቦት_20

                          
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ዝርዎሙ ለአሕዛብ እለ ይፈቅዱ ቀትለ። ይምጽኡ ተናብልት እምግብፅ። ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር"። መዝ 67፥30-31 ወይም መዝ 74፥2-3፡፡ የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 13፥1-11፣ 1ኛ ጼጥ 2፥11-20 እና የሐዋ ሥራ 13፥44-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ16፥24-28። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ወይም የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጻድቁ ንጉሥ ዐፄ ቅዱስ ካሌብ የዕረፍት በዓልና የበዓለ ዕርገቱ ሰሞን ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ግንቦት ፳፩ (21) ቀን።

እንኳን #አምላክ_ለወለደች_ለእናታች ለእመቤታችን #ለቅድስት_ድንግል_ማርያም #በደብረ_ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስትያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ #ለአምስት_ተካታታይ_ቀን_ለታየችበት ዓመታዊ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
                         

                         
#በዚች_ዕለት_አምላክን_የወለደች #እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም_በደብረ_ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስመታየቱ የክርስቲያ ወገኖች ሁሉም በታላቅ በዓልን ያደርጋሉ።

እርሷም በልጅዋ የመለኮት ብርሃን የተጐናጸፈች ናት በዙሪያዋም የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕርጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር ይጋርዷታልም። ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥናዋ ገናናነት ይሰግዳሉ ስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታል "አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ"።

ሁለተኛም ሰማዕታትም በየማረጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው እየመጡ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል እንዲሁም ባልጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል። ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጠው ይህ ቅዱስ መርቆሬዎስ ነው። ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል ምስጋና ያቀርብላታል።

ሁለተኛም ደግሞ የጻድቃን አንድነታቸው መጥተው በፊቷ ሰግደው ይመላለሳሉ። ኄሮድስ የገደላቸው ሕፃናትም መጥተው ይሰግዱላታል በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመታቃቀፍም ይጫወታሉ የተሰበሰብትም በአዩ ጊዜ ደስታ ይመላቸዋል በሰማይም ያሉ ይመስላቸው ነበር።

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹ ወይም ባልጀራው "ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳዪኝ ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች። ደግሞ መሀረባቸውን ወደላይ ይወረውሩላታል የወደደችውንም በእጅዋ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል።

እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም እስላሞችም አረማውያንም ያይዋታል። ወደ ቤታቸውም ለመሔድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል እርሷም ትባርካቸውና ይመለሳሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም አምላክ በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የግንቦት 21 ስንክሳር።

                          
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን። በዘአዝፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥12-13። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57።

                          
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ሰወረከኒ በዕለተ ቀትል መልዕልተ ርእስየ። ኢትመጥወኒ እግዚኦ እምፍትወትየ ለኃጥአን። ተማከሩ ላዕሌየ ኢትኅድገኒ ከመ ኢይዘኀሩ"። መዝ 139፥7-8 ወይም መዝ 140፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 7፥9-ፍ.ም፣ ራእ.ዮሐ 12፥1-5 እና የሐዋ ሥራ 7፥44-51። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥6-12። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የደብረ ምጥማቅ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ግንቦት ፳፪ (22) ቀን።

እንኳን ##ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት ለአንዱ ለከበረና ለተመሰገነ #ለሐዋርያው_ቅዱስ_እንድራኒቆስ ለዕረፍቱ በዓል፣ #በደብረ_ምጥማቅ_ለእመቤታችን መገለጥ #ለሁለተኛ_ቀን መታሰቢያ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከምሥራቃዊ_ከቅዱስ_ያዕቆብ ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።


                            
#ቅዱስ_እንድራኒቆስ፦ ይህንንም ሐዋርያ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መረጠው። እርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲሰብኩ ጌታ ከመከራው በፊት ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው።

በጽርሐ ጽዮንም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ መንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብሎ በብዙ አገሮች ውስጥ ሰበከ። በኒውብያ አገር ላይም ሐዋርያት በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት በውስጧም ሰበከ በጨለማ በድንቁርና የሚኖሩ ብዙዎች አረማውያንንም የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት አስገባቸው።

ከዚህም በኋላ ሐዋርያ ቅዱስ ዮልዮስን ወሰደው በአንድነትም በብዙ አገሮች ዙረው አስተማሩ። ብዙ ሰዎችንም አጠመቁ ተአምራትንም በማድረግ ከሰዎች ላይ አጋንንትን አባረሩ። ብዙዎች በሽተኞችንም ፈወሱአቸው የጣዖታትንም ቤቶች አፍርሰው የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናትን አነፁ። አገልገሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ ጌታችን ከድካም ወደ ዕረፍት ከኀዘንም ወደ ደስታ ሊወስዳቸው ወደደ።

ከዚህም በኋላ ሐዋርያ ቅዱስ እንድራኒቆስ ታመመና በዚች ቀን ግንቦት 22 ቀን ዐረፈ ቅዱስ ዮልዮስም ገንዞ በመቃብር አኖረው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የግንቦት 22 ስንክሳር።

                         
                          
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "በትርከ ወቀስታምከ አማንቱ ገሠፀኒ። ወሠራዕከ ማእደ በቅሜየ። በአንፃሪሆሙ ለእለ ይሣቅዩኒ"። መዝ 22፥4-5 የሚነበበው ወንጌል 27፥27-31።

                           
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 16፥6-10፣ 1ኛ ዮሐ 2፥27-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 21-15-21። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-12። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ እንድራኒቆስ የዕረፍት በዓልና የበዓለ ደብረ ምጥማቅ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"።

            #ግንቦት ፳፫ 23 ቀን

እንኳን #ለኢትዮጵያኑ_ጻድቅ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ላሾለኩ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ_ለልደታቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                          + + +
#አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ፡- አባታቸው ካህኑ ሮማንዮስ የደብረ ሊባኖሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ሲሆኑ እናታቸው ማርታ ይባላሉ፡፡ የትውልድ ቦታቸው ጽላልሽ ዞረሬ ነው፡፡ ሲወለዱ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ የታየ ሲሆን እርሳቸውም በብርሃን ልብስ ተጠቅልለው ታይተዋል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ በጽዮን ተሰጥተው ሃይማኖትን በሚገባ ተምረዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት ተሻግረው ሞተሎሚን አስተምረው ካሳመኑት በኋላ አቡነ ታዴዎስን ወደ እርሳቸው እንዲመጡ ልከውባቸው ሄደው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እያገለገሉ ዘጠኝ ዓመት ተቀመጡ፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ግን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ አቡነ ታዴዎስም ወደ ጽላልሽ ተመልሰዋል፡፡ ሁለቱም ከ32ዓመት በኋላ ተመልሰው በጽላልሽ ተገናኘተው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለአቡነ ታዴዎስ ማዕረገ ምንኩስናን ሰጥተዋቸዋል፡፡

አቡነ ታዴዎስም በሥጋ ዕድሜ ታላቅ ቢሆኑም እንደታናሽ ብላቴና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እያገለገሉ በደብረ ሊባኖስ ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ታዴዎስን ወደ ጽጋጋ እንዲሄዱ ነገሯቸው ምክንያቱም አቡነ አኖሬዎስ በዚያ ሲያስተምሩ ከሃዲያን ደብድበው አስረዋቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ታስረው ሳለ ወደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ የሚላካቸው ሲያስቡ ቁራ መጥቶ "እኔ እላክሃለሁ" ቢላቸው "ክፋትህ እንደ መልክህ ነው"ብለው እምቢ አሉት፡፡ ፀአዳ ኦፍ መጥቶ እኔ ከሀገራችሁ ኮዞረሬ የመጣሁ ነኝ "እኔ እላክሃለሁ" ብትላቸው "መጥተህ አድነኝ" ብለው በክንፏ ላይ ጽፈው ልከዋት እርሷም መልእክቱን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት አድሳ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው አቡነ ታዴዎስን ሕዝቡን ከኃጢአት ግዞት አኖሬዎስን ከእስራት እንንዲያስፈቱ የላኳቸው፡፡

አቡነ ታዴዎስም ከደብረ ሊባኖስ ወደ ደብረ ማርያም በሠረገላ ነፋስ ተጭነው በአንድ ሰዓት ደርሰው መዩጥ ከተባለውና አኖርዮስን ካሰራቸው ንጉሥ ፊት ቢደርሱ ንጉሡ በግንጋጤ መልአክ የመጣበት መስሎት ሲፈራ ከሰው ወገን መሆናቸውን ነግረው ክርስትናን አስተማሩት፡፡ ጋኔን ከእሳት ጥሎት ሲሠቃይ የሚኖርና ሊሞት የደረሰ ልጁን ቢፈውሱለት በትምህርታቸውና በተአምራታቸው አምኖ ሕዝቡ ክርስትናን እንዲቀበል በአዋጅ አስነገረ፡፡ አፍጃል የሚባለው ባለጸጋ ወደ አቡነ ታዴዎስ ቀርቦ ሲማር "ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል" ማቴ 19፥24፣ ማር10፥25፣ ሉቃ18፥25) የሚለውን የወንጌል ቃል ሲሰማ ለአእምሮው ረቆበት "እስቲ አድርገህ አሳየኝ?" አላቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስም እናቲቱን ግመል ከነጇ ቀጥሎም 28ግመሎችን በየተራ በመርፌ ቀዳዳ እያሾለኩ አሳይተውታል፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በእጅጉ ሲገረምና "በአምላከ ታዴዎስ ስም አምናለሁ" ሲል የባለጸጋው ልጅ ሙሳ ግን "በምትሀት አሳይቶን ነው እንጂ የእውነት አይደለም" በማለት አባቱንም እንዳያምን ይናገር ጀመር፡፡ ይህንንም ሲናገር በመጀመሪያ ያለፈችው እናቲቱ ግመል እረግጣ ገደለችው፡፡

አቡነ ታዴዎስም ንጉሡን፣ አባቱን አፍጃልንና ሕዝቡን የሞተ እንደሚነሣ ሲያስምሯቸው "የሞተ ይነሣልን? እስኪ ይህ የሞተው ልጅ ይነሳና ሁሉም አይቶ ይመን" አሏቸው፡፡ እሳቸውም "ዛሬ ተቀብሮ ይዋልና ነገ በሦስተኛው ቀን ይነሣል" ብለዋቸው ተቀብሮ ዋለ፡፡ በማግሥቱም አፍጃልን ጠርተው "አልዓዛርን ከሞት ባስነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ሆይ ና ውጣ" ብለህ ከልጅህ መቃብር ላይ አኑረው" ብለው ዘንጋቸውን ሰጡት፡፡ ሄዶም እንዳሉት ቢያደርግ ልጁ አፈፍ ብሎ ተነሥቷል፡፡ ይህንን ያዩ የአገሩ ሰዎች ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል፡፡ እሳቸውም 12አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸው ሞቶ የተነሳውን ሙሳን ሙሴ ብለው ሰይመው አስተምረው ሊቀ ካህናት አድርገው ሾመውት አቡነ አኖሬዮስን ይዘው ወደ ጽላልሽ ዞረሬ ተመልሰዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ አባ ያዕቆብ የተባሉ ጳጳስ ከግብፅ መጡ፡፡ የአቡነ ታዴዎስን ዜና ሲሰሙ ተደስተው ከአቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው አስጠርተዋቸው "የአባታችሁን ዜና ገድል ንገሩኝ" አላቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስም ጨዋታ በአስተርጓሚ አይሰምርም" ብለው ወደ ጌታችን ቢጸልዩ የጳጳሱ ቋንቋ ለአቡነ ታዴዎስ፣ የአቡነ ታዴዎስም ቋንቋ ለጳጳሱ ተገልጦላቸው የመሸ የነጋ ሳይመስላቸው40 ጾምን ሲጨዋወቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ጳጳሱ ከንጉሡ ተማክረው "ሊቀ ካህናት ዘጽላልሽ" ብለው ሾመዋቸዋል፡፡

በነግህና በሰርክ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ፣ ቀን ወንጌልን እየሰበኩ፣ ሌሊት ከባሕር ገብተው ሲጸልዩ እያደሩ በታላቅ ተጋድሎ እየኖሩ ሳለ ከ10ዓመት በኋላ ሰይጣን በንጉሡ በዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አሳድሮበት በክፉዎችም ምክር አታሎት የአባቱን ቅምጥ አገባ አቡነ ታዴዎስም ይህን ሲሰሙ እንደ ነቢዩ ኤልያስና እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ገሥጸው አወገዙት፡፡ ገሥጸውና አውግዘው አቡነ ማትያስን አስከትለው ሲመለሱ ቅምጧ የንጉሡ ሚስት በፈረስ ተከትላ ደርሳ የኋሊት አሳስራ ዛሬ "ማርያም ገዳም" ከሚባለው ቦታ ፊት ለፊት ካለው ትልቅ ገደል ውስጥ ሁለቱንም ጣለቻቸውና ጥር29 ቀን በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡

በሰማዕትነት ዐርፈው ደማቸው ከፈሰሰበት ከገደሉ ስር በፈለቀው ጸበላቸው "ታዴዎስ ወማትያስ" እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያለ የተጠመቀ ሰ እንደ 40 ቀን ሕፃን እንደሚሆን ጌታችን ቃል ኪዳን ገብቶላቷቸዋል፡፡ ይህ ሰማዕትነት በተቀበሉበት አካባቢ የተሠራው ቤተ ክርስቲያናቸው በጠላት ወረራ ጊዜ ፈርሶ ቦታው ጠፍ ሆኖ የኖረ ቢሆንም የአካባቢው ሕዝብ ቦታውን ከልሎ በክብር ሲጠብቀው ስለኖረ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ የአቡነ ታዴዎስ ታቦታቸው በ2005ዓ.ም ከኢቲሣ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ወጥቶ ጻድቁ ሰማዕትነት በተቀበሉበት አካባቢ በተሠራው መቃኞ ቤተ ክርስቲያናቸው በታላቅ ክብር ገብቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም ከኢቲሣ በእግር የአንድ ሰዓት ተኩል ርቀት ላይ ይገኛል። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም አጭር ታሪክ ከምትላው መጸሐፍ።
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

             #ግንቦት ፳፫ (23) ቀን።

እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት ለሆኑ #ለሐዋርያው_ቅዱስ_ዮልዮስ ለዕረፍት በዓል፣ #ለሐዋርያው_ቅዱስ_አፍሮዲጡ ለመታሰቢያ በዓሉና #በደብረ_ምጥማቅ_ለእመቤታችን_መገለጥ_ለሦስተኛ ቀን መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤነሠ አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ ሰማዕታት ከሆኑ #ከአንስያ_ከዮልያና_ከቀሲስ_ታኦድራጦስ#ከጳጳስ_ታድሮስ_ከዮልያኖስና_ከእናቱ_ከእስክንድርያ#ከኤስድሮስ#ከሚስቱና_ከሁለት ወር ልጅዋ እኔ ከእናቴ ጋራ ክርስቲያን ነኝ ብሎ ከተናገረና ዲዮቅልጥያኖስ ከገደላቸው ለእነርሱም ማኅበር ከመታሰቢያቸው ከሆነ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                           
#ቅዱስ-ዮልዮስ፦ የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ከይሁዳ ነገድ ከእስራኤል ልጆች ከቤተ ገብርኤል ነው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መረጠው። ከሰባ ሁለቱ አርድእትም የተቆጠረ ሆነ የመንፈስ ቅዱስንም ሀብት ከሐዋርያት ጋራ ተቀበለ ከእርሳቸውም ጋራ ታላቅ መከራ ደርሶበታል።

ከዚህ በኋላ ሐዋርያት በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሹመው ከቅዱስ እንድራኒቆስ ጋራ በአገሮች ውስጥ እንዲሰብክ ላኩት። ቅዱስ እንድራኒቆስም በአለፈው ዕለት በዐረፈ ጊዜ ይህ ቅዱስ ዮልዮስ ገንዞ ቀበረው። ከዚህ በኋላ ከርሱ እንዳይለይ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በማግሥቱ ዛሬ ግንቦት 23 ቀን ዐረፈ።

እንሆ የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም እሊህን ሐዋርያ በሮሜ ክታቡ ቅዱስ እንድራኒቆስንና ቅዱስ ዮልዮስን ሰላም በሏቸው ሲል አስታውሷቸዋል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የግንቦት 23 ስንክሳር።

                        
"#ሰላም_ለዮልዮስ እምቤተ ገብርኤል ልደቱ። ዘተወክፈ ጸጋ ለመንፈስ ቅዱስ ጊዜ ርደቱ። ለእንድራኒቆስ ረድእ ሳኒታ ዕረፍቱ። እግዚአብሔር አግዐዞ እምቅኔ ዓለም ዝንቱ። በከመ ሰአለ ኢይፍልጦ ሎቱ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ(አርኬ) #የግንቦት_23

                        
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን። በዘአዝፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥12-13። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥16፥19።

                          
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ44፥9-10። የሚነበበው መልዕክታት ሮሜ 16፥7-10፣ ይሁ 1፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 21፥15-21። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ10፥17-25። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ዮልዮስና የእመቤታች የደብረ ምጥማቅ በዓል ሰሞን። ለሁላችንም ይሁንልን።