ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
980 subscribers
8.39K photos
102 videos
99 files
1.2K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ሚያዝያ ፴ ❖

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ሚያዝያ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

=>እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ
ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሃ ዕድሜ ናት::
እግዚአብሔር
ግን ደግ ነውና ይሔው ሚያዝያን አስፈጸመን::

+ባይገባን ነው እንጂ በዚሕች ወር ውስጥ:-
*ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል::
*ሚሊየኖችም ለንስሃ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል
(ሙተዋል)::

+እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪዋን ዘመን ደግሞ ለንስሃና
ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን::

+"+ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ +"+

+በዚሕች ዕለት ከ72ቱ አርድእት አንዱ የሆነ: ወንጌላዊ:
ሐዋርያ: ሰማዕት: ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ዻዻሳት የተባለ
ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ግብፅ ውስጥ ዐርፏል::

+ቅዱስ ማርቆስ እናቱ ማርያም: አባቱ አርስጥቦሎስ
ይባላሉ:: በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ
በሚገባ ተምሮ
ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል::

+የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከ120ው ቤተሰብ
በእድሜ በጣም ትንሹ (20 ዓመት) እርሱ ነበር:: ለ3
ዓመታት ከጌታ
እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን
ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል::

+በተለይ የግብፅና የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው::
ክህነትን ያገኘን ከርሱ ነውና:: ቅዱስ ማርቆስ 16 ምዕራፍ
ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ: ሊቀ
ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር::

+ቅዱሱ ክቅዱስ ዻውሎስ: ከበርናባስና ዼጥሮስ ጋር
ተጉዟል:: ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ
አካባቢ በዚህ ቀን [በ60 ዓ/ም አካባቢ]
አረማውያን ገድለውታል::

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን
እናስባቸው ዘንድ ይገባል::

❖ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ
የነበረ፡፡

❖ቅድስት ማርያም (እናቱ)
*ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ:
*ጌታችንን ያገለገለች:
*ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት
ናት::

+ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን
ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል::
የእመቤታችን ግንዘትም
ተከናውኖባታል::

❖እግዚአብሔር ከሐዋርያዊው ቅዱስ ቤተሰብ በረከትን
ያድለን::

=>ሚያዝያ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
3.ቅድስት ማርያም (እናቱ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

=>+"+ . . . እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ
ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ
ማርያም ቤት መጣ:: ዼጥሮስም የደጁን መዝጊያ
ባንኩዋኩዋ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ
ዘንድ ቀረበች:: የዼጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ
ከደስታዋ የተነሳ ደጁን አልከፈተችም:: ነገር ግን ወደ
ውስጥ ሮጣ ዼጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች::
+"+ (ሐዋ. 12:12-15)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" 🌷ልደታ ለማርያም ድንግል🌷 "*+

ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ:
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ::
" ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን:
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን) "

=>የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኩዋ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::

+ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::

+እመቤታችን ከአዳም ስሕተት በሁዋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9)

+ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ቀን: በሊባኖስ ተራራ ከ2,022 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::

"ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ" (መኃልይ. 4:8)

=>ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር::

+ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ::
እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

+የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

+ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን 2ቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::

+እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

+በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

+እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9)

+እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች::

=>የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-
*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=
*በእናቷ:-
-ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::
*በአባቷ በኩል:-
-ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::

+ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,026 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::

=>የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::

=>ግንቦት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ልደታ)
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቴክታና በጥሪቃ
4.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ (የእመቤታችንን ቅዳሴ የደረሰበት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

=>+"+ መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው::
ከያዕቆብ ድንኩዋኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::
በውስጧም ሰው ተወለደ::
እርሱም ራሱ ልዑል መሠረታት:: +"+ (መዝ. 86:1-6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት ክብረ በአል በደብረዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወደብረ ብስራ ቅዱስ ገብርኤል አብያተክርስትያናት በታላቅ ድምቀት ተከበረ፡፡
ግንቦት 1/2016 ዓ.ም
ፈለገ ጥበብ ሚዲያ
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት ፪ ❖

❖ ግንቦት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ ኢዮብ +"+

+የትዕግስት አባት ቅዱስ ኢዮብ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ
እንደተመለከትነው ያልተፈተነበት ነገር የለም:: ሐረገ
ትውልዱም
ከአባታችን አብርሃም ይመዘዛል::

*አብርሃም ይስሐቅን
*ይስሐቅ ኤሳውን
*ኤሳው ራጉኤልን
*ራጉኤል ዛራን
*ዛራ ኢዮብን ይወልዳሉ::

+ቅዱስ ኢዮብ የነበረው እሥራኤል በግብፅ በባርነት ሳሉ
ነበር:: ኢዮብ ይሕ ቀረህ የማይሉት ባለጠጋ: ደግና
እግዚአብሔርን
አምላኪ ነበር:: የኢዮብ ደግነት የተመሰከረው በሰው
(በፍጡር) አንደበት አልነበረም:: በራሱ በፈጣሪ አንደበት
እንጂ::

+በዚህ የቀና ጠላት ዲያብሎስ ግን ኢዮብን ይፈትነው
ዘንድ ከአምላክ አስፈቀደ:: ጌታችን የጻድቁን የትዕግስት
መጠን
ሊገልጥ ወዷልና ሰይጣን ኢዮብን በሐብቱ መጣበት::
በአንድ ጀምበርም ድሃ ሆነ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን ባረከ::

+ሰይጣን ቀጠለ:- የአብራኩን ክፋዮች (ልጆቹን)
አሳጣው:: ኢዮብ አሁንም አመሰገነ::

+በሦስተኛው ግን ሰውነቱን በቁስል መታው:: ቁስል ሲባል
በዘመኑ እንደምታዩት ዓይነት አልነበረም:: ከሰው ሕሊና
በላይ
የሆነ አሰጨናቂ ደዌ ነበር እንጂ:: ጻድቁ የአንድ ወጣት
እድሜ ያሕል በመከራው ጽናት እየተሰቃየ ገላውን በገል
ያከው
ነበር::ከአፉ ግን ተመስገን ማለትን አላቁዋረጠም::

+በመጨረሻም ሰይጣን በሚስቱ መጣበት::
"እግዚአብሔርን ተሳደብ" አለችው:: እርሱ ግን መለሰ:-
"እግዚአብሔር ሰጠ:
እግዚአብሔርም ነሣ: ስሙ የተባረከ ይሁን::"

+ከዚሕ ሁሉ ነገር በኋላ እግዚአብሔር ሰይጣንን ከጎዳናው
አስወገደው:: ጤናውን: ሐብቱን: ልጆቹን ለኢዮብ
መለሰለት::
ካለው እድሜ ላይ 140 ዓመት ጨመረለት:: ጻድቅና
የትዕግስት ሰው ቅዱስ ኢዮብ በ248 ዓመቱ በዚሕች ቀን
ዐረፈ::

=>እግዚአብሔር አምላክ ከጻድቁ ትዕግስትና በረከት
አይለየን::

❖ግንቦት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ (የትእግስት አባት)
2.አባ ቴዎድሮስ ሊቀ ምኔት (የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ
መዝሙርና የአቡነ አረጋዊ ጉዋደኛ)
3."22" ሰማዕታት (የአባ ኤሲ ማሕበር)

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
2፡ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
3፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
4፡ ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5፡ አባ ጳውሊ ገዳማዊ
6፡ አባ ሕርያቆስ ዘብሕንሳ

++"+ ወንድሞች ሆይ! የመከራና የትዕግስት ምሳሌ
የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ::
እነሆ
በትዕግስት የጸኑትን ብጹዓን እንላቸዋለን:: ኢዮብ እንደ
ታገሠ ሰምታቹሃል:: ጌታም እንደፈጸመለት አይታቹሃል::
ጌታ እጅግ የሚምር: የሚራራም ነውና:: +"+ (ያዕ.
5:10)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን::

🛑ግብረ-ሰላም 🛑

(ከአንድ ወንድም በደረሰኝ ጥያቄ መሠረት ለጊዜው እነዚህን ጉዳዮች ብቻ እንመልከት)

"ገብረ ሰላመ በመስቀሉ::
ትንሳኤሁ አግሃደ::"

1." ትርጉም "

=>"ግብረ-ሰላም" ማለት "የሰላም : የፍቅር : የአንድነት ተግባር" እንደ ማለት በጥሬው ሊተረጐም ይችላል::

2." ምንነት "

=>ግብረ-ሰላም የጌታን ትንሳኤ ተከትለው በሚመጡ 50 ቀናት የሚከናወን ተግባር ሲሆን መንፈሳዊና ሥጋዊ ድግሶች የሞሉበት ትውፊታዊ ክዋኔ ነው::

3." መነሻ "

=>ቤተ ክርስቲያናችን የሁሉ ነገሯ መሠረት መድኃኔ ዓለምና ትዕዛዛቱ ናቸው:: የግብረ ሰላምም መሠረቱ ቅዱስ መጽሐፍ ነው:: በብሉይ ኪዳን አገልጋይ ካህናትና ነቢያትን መመገብ በጐና የተለመደ ተግባር ነበር::

+ኦሪት ላይ እንደተጻፈው ቅዱስ ኢያሱ ርስትን ሲያካፍል ለካህናት አልሰጣቸውም:: ምክንያቱም የካህናቱ ርስት ሕዝቡ ነበርና:: (ኢያ. 21) በመጽሐፈ ነገሥት 2ኛ ያቺ ደግ ሱነማይት ሴት ለቅዱስ ኤልሳዕን ትመግበው : ታሳድረውም እንደ ነበርም ተጽፏል:: እንዲያውም ቤት ሁሉ ሠርታለታለች:: (2ነገ. 4:8)

+በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የክብር ባለቤት : አማናዊው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰዎች ቤት ገብቶ ግብር ሲያገቡለት (ሲጋበዝ) እንደ ነበር ቅዱስ ወንጌል ይናገራል:: እንደ ማሳያም ቤተ ማርታን (ሉቃ. 10:38) : ቤተ ስምዖን ዘለምጽን (ማቴ. 26:6) : ቤተ አልዓዛር ወኒቆዲሞስን (ዮሐ. 12:1) መጥቀስ እንችላለን::

<< ስለዚህ ካህናትን ወደ ቤት ጠርቶ መጋበዙ (ግብረ ሰላም ማድረጉ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው:: >>

+በተአምረ ኢየሱስ ላይ እንደተጠቀሰው ደግሞ በበዓለ ሃምሳ ካህናትን እንደ አቅሙ (ከ1 ጀምሮ) ያበላ በፍርድ ቀን ከመከራ እንደሚያመልጥ ጌታ መናገሩ ተዘግቧል::

+በተለይ ግን አበው ሐዋርያትን ጌታ እንዲህ ብሏቸዋል ሲል ቅዱስ ማቴዎስ ነግሮናል::

"በምትገቡባትም በማናቸውም ከተማ ወይም መንደር : በዚያ የሚገባው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ:: እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ:: ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ:: ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት:: (ይደርበት) ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ:: ከማይቀበላችሁም : ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ:: እውነት እላቹሃለሁ:: በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ፍርድ ይቀልላቸዋል::" (ማቴ. 10:11)

+በተጨማሪም "የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሠር" ያለውን የኦሪት ትዕዛዝ "ይደልዎ አስቦ ለዘይትቀነይ-ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል" ሲል ጌታ ተናግሮታል:: የአነጋገሩ ምሥጢር ብዙ ቢሆንም በጥሬው ግን የካህናት ደሞዝ ከምዕመናን መሆኑን ያሳያል:: (ዘዳ.25:4, 1ቆሮ.9:9, ማቴ.10:10

4." አፈጻጸም "

=>ግብረ-ሰላም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ (በቤተ ምርፋቅ) ሊከወን ቢችልም ብዙ ጊዜ የሚፈጸመው በምዕመናን ቤት ነው:: ለምን? . . . ቤታቸው በአበው ካህናት ይባረክ ዘንድ ይገባልና::

+ከትንሳኤ ማግስት ጀምሮ ምዕመናን እንደ አቅማቸው:-
1.መምህረ ንስሃ (የነፍስ አባታቸውን)
2.ከደብሩ ካህናት በቁጥር
3.የደብሩን ሁሉ አገልጋዮች
4.የአድባራትን ሊቃውንት . . . ሊጠሩ ይችላሉ:: ባለጠጐች ከሆኑ ብዙ ሊጠሩ ይችላሉ:: የኔ ብጤ የሆነ ደግሞ እንደ አቅሙ ማለት ነው::

+የተጠሩ ካህናት (ሊቃውንት) ወደ ቤት ሲደርሱ የቤቱ አባወራ አደግድጐ : እማወራዋ አገልድመው ከበር ላይ ይጠብቃሉ:: "እንኩዋን ደህና መጣችሁ" እያሉ አስገብተው በየማዕረጋቸው እንዲቀመጡ ይደረጋል::

+ከሁሉ የሚቀድም ጸሎት ነውና ማዕዱ ቀርቦ ጸሎት በርዕሰ ደብሩ ወይም በመምህሩ ይደረጋል:: ሲበላም በመስሪያ (6 ሆነው) ሲሆን ይህም ከ6ቱ ቃላተ ወንጌል ብዙዎቹ የሚከወኑበት መሆኑን ያጠይቃል:: በየመሥሪያው አበው እየቆረሱ "በእንተ ማርያም" ሰጥተው በሥርዓት ይበላል::

+መጠጥም (ወይን : ጠላ : ጠጅ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል) ጐን ለጐን ይቀርባል:: አጥንት ካለ እንደየ ማዕርጋቸው ለመምህራንና ለአበው ፍሪምባ : ቅልጥም ለምክትል መምህራን ወዘተ. ተሰጥቶ በቃለ ማኅዘኒ "ስብሐት ለአብ" ተብሎ እግዚአብሔር ይመሰገናል::

+መምህሩ አፉን አጥርቶ ትምህርት ከሰጠ በሁዋላ አበው እየተነሱ ይመርቃሉ:: የዜማ መምህራን በበኩላቸው የክርስቶስን ትንሳኤና የማዳን ሥራ የሚያዘክሩ ወረቦችን እየቃኙ ይወርባሉ:: ይቸበችባሉ:: በመጨረሻም ኑዛዜ ተሰጥቶ ስንብት ይሆናል::

+አበውና ካህናት "ስብሐት" ብለው ያተረፉትንም የቤቱ ባለቤቶች : ሕጻናትና ጐረቤት ሁሉ በደስታ ተካፍሎ ይበላዋል:: እጅግ ታላቅ በረከት ነውና::

5." ግብረ-ሰላም በትውፊት "

=>ይህ መንፈሳዊ ተግባር ምንም እንኩዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያንና በሃገራችን ታሪክም ተዘግቦ የሚገኝ : ለባለጠጐች : ለመሣፍንቱና ለነገሥታቱ ከነ ስሙም  "ግብር ማግባት" የሚባል ነበር::

+በዘመነ ሐዋርያትና ሰማዕታት አገልጋይ ካህናትን ሰብስቦ መጋበዙ የሚታሰብ አልነበረም:: ምክንያቱም ጊዜው የመከራና ክርስቲያኖች መብታቸው የተነፈገበት ነበርና::

+ከዘመነ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ወዲህ ግን ተመሳሳይ ግብር የማግባት (የግብረ ሰላም) ተግባራት እንደ ነበሩ ይታመናል:: እንደ ምሳሌም በ4ኛውና 5ኛው መቶ ክ/ዘ የነበሩ ደጋግ ነገሥታት (እነ ቴዎዶስዮስ 1ኛና 2ኛ : አርቃድዮስ : አኖሬዎስ : ዘይኑን እና አንስጣስዮስ) እንዲሁ ያደርጉ እንደ ነበር ገድላተ ቅዱሳን ያሳያሉ::

+በሃገራችን ኢትዮዽያም ከብሉይ ኪዳን ሲያያዝ የመጣው ተግባር በክርስትና ጸንቶ መቀጠሉን በነገሥታቱ ዜና መዋዕሎች ላይ መመልከት ይቻላል:: ሁሉም ነገሥታት ይህንን ያደርጉ ነበር ብሎ መናገር የሚቻልም ይመስለኛል:: በሕዝቡ ደረጃም አበው እና እማት ይህንን ሲከውኑ እዚህ ደርሰናል::
6." ዛሬስ "

=>ግብረ-ሰላም ዛሬም በትውፊታዊ ሥርዓቱ ቀጥሎ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ይከወናል:: በተለይ ደግሞ በሰሜኑ አካባቢ:: ነገር ግን አፈጻጸሙ ላይ ከሚታዩ ስሕተቶች የተነሳ ለጊዜውም ቢሆን እያስነቀፈን ይገኛል::

1.የተግባሩን መንፈሳዊነት ያልተረዱ አንዳንድ ምዕመናን . . . ሲጀመር "እንካ ብላ : አፈር ብላ" ዓይነት ግብዣ እያደረጉ አበው ካህናትን ሲያቀሉ ተመልክተናል::

2.በአንድ ጊዜ ጠጅ : ጠላ : አረቄ እና ውስኪን ቀላቅለው የሚጋብዙ እንዳሉም ሰምቻለሁ::

3.በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ "ማኅሌተ ገንቦ" በሚል ኃጢአት የሆነውን ዘፈን የሚሞክሩም አይጠፉምና "ቢታሰብበት!" ባይ ነኝ::
☞ዘንድሮ (በ2012) ደግሞ ባብዛኛው በኮሮና ቫይረስ ሰበብ ቀርቷል ብሎ ለመናገር በሚያስደፍር ደረጃ ላይ መድረሱን ታዝቤአለሁ፡፡ አንዳንድ ደጋግ ሰዎች ለበረከት ቢያደርጉትም፡፡

+ይህንን የመሰለ መጽሐፋዊ : ትውፊታዊና ታሪካዊ የበረከት ሃብታችንን በሥርዓቱ ማስቀጠል ብንችል . . . ወዲህ እንጠቀማለን:: ወዲያ ደግሞ ለትውልድ እናስተላልፋለን::
‹‹የእግዚአብሔር ሙላቱ በእርሱ እንዲኖር በእርሱ በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ያሉት ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና ›› (ቆላ. 1:19-20)