የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
3.15K subscribers
3.97K photos
257 videos
95 files
459 links
ኢዜማ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች መብት የተከበረባት፣ ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ሰላማዊ እና የበለፀገች ሀገር እንድትሆን የሚሠራ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ነው።
Download Telegram
የሕግ የበላይነት ይከበር!!


አንፃራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሰፈነባቸው ሀገራት የመገናኛ ብዙኃን ዐራተኛ የመንግሥት አካል ተደርገው ይወሰዳሉ ይህንንም ተግባራቸውን የሚወጡት መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ እና በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ሕገወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ጭምር ነው።

በሀገራችን ግን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በቅጡ ባለመወጣታቸው እና አለአግባብ በሕግ ከተሰጣቸው መብት በላይ በመንቀሳቀሳቸው በታሪካችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማንበር እና መገናኛ ብዙኃን በነፃነት የዐራተኛ መንግሥትነት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ አልቻልንም።

አለአግባብ ከኃላፊነታቸው በላይ ከሚንቀሳቀሱ ወይም ሕግን ከሚጥሱ እና ይህንን የዴሞክራሲ ሥርዓት ከሚያቀጭጩት መካከል የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ አካላት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃንን፣ ሐሣባቸውን በዐደባባይ የሚገልፁ ግለሰቦችን እና ፖለቲከኞችን ከሕግ አግባብ ውጪ በተለያየ መንገድ ማዋከብ ዋናው ነው።

ባለፉት ዓመታት ይህ ዓይነት ተግባር በተደጋጋሚ ሲፈጸም ተመልክተናል፤ ባለፉት ጥቂት ወራትም ይኸው ተጠናክሮ ከመቀጠሉም በላይ ዜጎች የፀጥታ አካል ነን በሚሉ ግለሰቦች አንዳንዴም በማን እንደታፈኑ እና የት እንደታሰሩ እንኳን የማይታወቅበት ሁነት በተደጋጋሚ ሲያጋጥም እየታዘብን ነው። 

በመንግሥት በኩልም በተደጋጋሚ ያለአግባብ ያሠርኩት ጋዜጠኛም ሆነ ዜጋ የለም የሚል ምላሽ ሲሰጥም ተመልክተናል። የዚህ ምላሽ አሳሳቢነት አንድም መንግሥት ድርጊቱን እየፈፀመ ነገር ግን እየደበቀው ከሆነ መንግሥት ሕገወጥ ተግባራትን ሆነ ብሎ እየፈፀመ ነው የሚያስብል ሲሆን በሌላ መልኩ እነዚህ ተግባራት የሚፈፀሙት ከመንግሥት እውቅና ውጪ በሌሎች በተደራጁ አካላት ከሆነ መንግሥት በቅጡ የሀገሪቱን ፀጥታ እና የዜጎችን ደኽንነት እያስጠበቀ አይደለም የሚል ስጋት ዜጎች ላይ እንዲፈጠር ያደርጋል። 

እነዚህ ሁነቶች በዋነኝነት የሚያመሩት ዜጎች ጠባቂ የለኝም ከሚል ስጋት በገዛ እጃቸው ደኽንነታቸውን ለማስከበር መሞከር ሲሆን በተጨማሪም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚፈታተኑ ሕገወጦች እንዲበራከቱ በማድረግ የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ እና የዜጎች ደኽንነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚከት አስፈሪ ሁነት ነው።

በአሀዱ ራዲዮ ቅዳሜ ገበያ ፕሮግራም ላይ የሚሠራው አንጋፋው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ ከነሐሴ 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ደብዛው እንደጠፋ እና ባለፈው ሀሙስ የሚሰራበት ቢሮን ለማስፈተሽ ከፖሊስ ጋር መምጣቱን የሚሠራበት ተቋም ከትላንት በስቲያ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም. አሳውቋል።

በትናንትናው ዕለት ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም. ደግሞ የሪፖርተር ጋዜጠኛ የሆነው ዮናስ አማረ ጭምብል በለበሱ ግለሰቦች መወሰዱን ተቋሙ በይፋ አሳውቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥትን የመሠረተው ገዢው ፓርቲ በቅርቡ ማለትም ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እፈታቸዋለሁ ካላቸው ችግሮች መካከል በየደረጃው የሚነሡ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ ዐቅም ልክ በየደረጃው ለመመለስ እና ተገቢውንና እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ በየጊዜው ለመስጠትና ሐሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ ነው ቢልም በማግስቱ እንዲህ ዓይነት ተግባር መታየቱ የተገባው ቃል ከልብ አለመሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። 

ኢዜማ ይህ ነገር ትኩረት እንዲሠጠው እያሳሰበ ይህንን የሚያደርገው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን መንግሥት ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ወደከፋ ችግር ውስጥ ከመግባቷ በፊት ትኩረት ሰጥቶ ማረም እንዲችል ለመወትወት መሆኑን እየገለጽን ታፍነው የተሰወሩ ጋዜጠኞች ያሉበትን ሁኔታ በግልፅ እንዲያሳውቅ በመጠየቅ ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (#ኢዜማ)
ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም.
‹‹ኢዜማ በከረረ የጥላቻ መንፈስ ለሚቃወሙም፤ በጭፍን ድጋፍ ለሚነጉዱም ቤታቸው ሊሆን አይችልም››

ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (የኢዜማ ሊቀመንበር)

https://drive.google.com/file/d/1fs470Tnlo6aJTw5xl6DQf_x2NUKHWEsw/view?usp=drivesdk

በኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የምትዘጋጀው የዜጎች ልሳን መጽሔት ቅጽ 02_ቁ: 15 የወሩን እንግዳ ጨምሮ የተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮችን ታሥነብበናለች፤ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ሙሉውን ይዘት ያንብቡ።
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
#ኢዜማ የሕግ የበላይነት ይከበር!! ሲል ያወጣውን መግለጫ ሀገሬ ቴሌቭዥን እንደሚከተለው ዘግቦታል፤ ፓርቲያችን በጉዳዩ ላይ ያወጣውን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ተጭነው ያንብቡ።
https://www.facebook.com/share/p/19JFWb4Gny/
#ኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የምትዘጋጀው የዜጎች ልሳን መጽሔት በአምድነት ከምትይዛቸው መካከል ዜጎች ሐሣባቸውን የሚገልጹበት #አንድ_ዜጋ የሚል አምድ አንዱ ሲሆን በዚህ ወር ከእናንተ ከተላኩ ጽሁፎች መካከል
ብሔራዊ ጥቅም ከኢትዮጵያ አንፃር

የሚለው ጽሁፍ ለንባብ በቅቷል፤ እንዲያነቡት እየጋበዝን መሠል ጽሁፎችን ለማድረስ ፍላጎት ያላችሁ ዜጎች በስልክ ቁ 0944107661 የቴሌግራም/ዋትስአፕ መተግበሪያዎች ወይም በኢሜይል አድራሻችን ethzema@gmail.com ሊልኩልን እንደሚችሉ እናሣውቃለን።

መልካም ንባብ!!

https://drive.google.com/file/d/18DBTc9FYuOsHYAwaTX-a8FYfwdDy17rW/view?usp=drivesdk
#ኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የምትዘጋጀው የዜጎች ልሳን የነሐሴ ወር ዕትም የኢዜማ የውስጠ ዴሞክራሲ ባሕል ላይ የሚከተለውን ታስነብበናለች፤ በተጨማሪም በዚህች መጽሔት ዜጎች በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደኽንነት ጉዳይ ነፃ ሐሣብ የሚሰነዝሩበት #አንድ_ዜጋ የሚል አምድ ያለ ሲሆን ጽሁፎችን ለማድረስ ፍላጎት ያላችሁ ዜጎች በስልክ ቁ 0944107661 የቴሌግራም/ዋትስአፕ መተግበሪያዎች ወይም በኢሜይል አድራሻችን ethzema@gmail.com ሊልኩልን እንደሚችሉ እናሣውቃለን።

መልካም ንባብ!!

https://drive.google.com/file/d/1PGeL4Dt_igWUdEwWt2BzRhIiBMctxt5a/view?usp=drivesdk
#ኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የምትዘጋጀው የዜጎች ልሳን የነሐሴ ወር ዕትም የኢዜማ ሀገራዊ ራዕይ ላይ የሚከተለውን ታስነብበናለች፤ በተጨማሪም በዚህች መጽሔት ዜጎች በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደኽንነት ጉዳይ ነፃ ሐሣብ የሚሰነዝሩበት #አንድ_ዜጋ የሚል አምድ ያለ ሲሆን ጽሁፎችን ለማድረስ ፍላጎት ያላችሁ ዜጎች በስልክ ቁ 0944107661 የቴሌግራም/ዋትስአፕ መተግበሪያዎች ወይም በኢሜይል አድራሻችን ethzema@gmail.com ሊልኩልን እንደሚችሉ እናሣውቃለን።

መልካም ንባብ!!

https://drive.google.com/file/d/1izzEYVytQ6ZHV9TOb0wS0I0MTCf3lJyW/view?usp=drivesdk
አንድ ድርጅት እንዴት የፓርቲ መሪና የፓርቲ ሊቀ መንበር ይኖረዋል?


#ኢዜማ ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ የፓርቲ መሪ እና የፓርቲ ሊቀመንበር የሚባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ይገኛሉ። የፖርቲ መሪና ሊቀመንበር የሚል የኃላፊነት ቦታዎች በመዋቅሩ ላይ በማስቀመጥ ኢዜማ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አደረጃጀት ታርክ የመጀመሪያው ድርጅት ነው።

እነዚህ የኃላፊነት ቦታዎች በሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች መዋቅርና አሠራር ላይ የተለመዱ አይደሉም። ከዚህም የተነሳ “እንዴት አንድ ድርጅት የፓርቲ መሪና የፓርቲ ሊቀ መንበር ይኖረዋል?” የሚል ጥያቄ በተለያዩ የፖለቲካ አካላትና መገናኛ ብዙኃን ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ይነሳል።

የኢዜማ አመራሮች ይህ ጥያቄ በተነሳባቸው መድረኮች ሁሉ የኢዜማን አደረጃጀት በማስረዳት ጥያቄውን ለመመለስ ሞክረዋል።

የዚህም ጽሑፍ ዓላማ፣ ኢዜማ የፓርቲ መሪና ሊቀመንበር ያስፈለገበትን አደረጃጀት መሠረታዊ ምክንያቶች ከኢዜማም አልፈው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ምክንያቶች በመሆናቸው እነዚህን ምክንያቶች በበለጠ ለማስረዳት በሚደርገው ሙከራ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።

በተጨማሪም ይህንን ዓይነት መዋቅር ለምን አስፈለገ? ከሚሉት ምክንያቶች አንዱ የሆነውን “ኢዜማን እውነተኛ ሀገራዊ ፓርቲ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ይህ አወቃቀር ያለውን አስተዋጽኦ ማሳየት ነው”

በኢዜማ መዋቅር ውስጥ የመሪና የሊቀመንበር የኃላፊነት ቦታ እንዲኖር የተደረገበት ዋና ምክንያት በርግጥም ኢዜማን ሀገራዊ ፓርቲ ለማድረግ ከማሰብ የሚነሳ ነው። በኢዜማ ዕይታ የሀገራችን ፓርቲዎች አደረጃጀት ባህል አንድ የሚጎለው መሠረታዊ ጉዳይ አለ፤ ይህም የድርጅት ፍላጎትና ጥቅምን ከሀገር ፍላጎትና ጥቅም ለይቶ ያለማየት ችግር ነው።

ድርጅት (ቡድን) ሀገር ሊሆን አይችልም፤ ሀገር ከድርጅት በላይ ነው። በኢዜማ እምነት ከድርጅቶች የተለያዩ ፍላጎቶች በላይ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ በኢዜማ መሠረታዊ የመርህ ሰነድ ላይ ከቀረቡት የኢዜማ መርህ 10 ነጥቦች የመጀመሪያው “የኢትዮጵያና የሕዝቧ ጥቅም፣ ሰላምና ደህንነት፣ ምንግዜም ቅድሚያ ይኖረዋል” ይላል። ኢዜማ ለዚህ መርህ ተግባራዊነት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አላስቀመጠም። "ምንግዜም ቅድሚያ ይኖረዋል" ነው የሚለው። ይህ ማለት የሀገርና የሕዝብን ጥቅም፣ ሰላምና ደኽንነት ችግር ውስጥ የሚጨምር ሀገራዊ ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ እና በወቅቱ በሥልጣን ላይ ያለው ኢዜማ ከሆነና ኢዜማ ከሥልጣን መልቀቅ መፍትሔ ሆኖ ከተገኘ፣ ምንም ሳያቅማማ ከሥልጣን እንዲለቅ የሚያስገድድ መርህ ነው። በተቃራኒው ከኢዜማ ጋር መሠረታዊ የአመለካከት ልዩነት ያለው ድርጅት በሥልጣን እንዲቆይ የሚያስገድድ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚመጣ የደኅንነት አደጋ ካለ ኢዜማ እጅግ የማይስማማውን በሥልጣን ላይ ያለ ድርጅት ደግፎ ከመቆም ወደ ኋላ እንዳይል የሚያስገድድ መርህ ነው።

ሌላኛው በእርግጥም ኢዜማ ሀገራዊ ፓርቲ መሆን ካለበት በተለይ ሀገራችን ለረጅም ዘመን የተጓተቱ መጠነ ሰፊ ችግሮች ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ እነዚህን ችግሮች አጥንቶ፣ መፍትሔዎቹን ሊተገብሩ በሚችሉ ፖሊሲዎች ቀርጾ ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማሳየት፣ ከእነዚህ ፖሊሲዎች አኳያ የመንግሥትንና የሌሎች ድርጅቶች የተሳሳቱ ፖሊሲዎችን ማጋለጥ እጅግ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ተግባር እንደመሆኑ የተከተለው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በመሪው የሚመራ ድርጅታዊ አካል እንዲሁም ድርጅቱን በአባላት ቁጥር ከፍ ማድረግና ማብቃት፣ በፋይናንስ ማጠናከር እና መዋቅሩንማጠናከር የመሣሠሉትን የሚከታተል በሊቀመንበሩ የሚመራ የተለያየ አደረጃጀት መኖሩ አስፈላጊ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ ሀገራዊና ድርጅታዊ ጉዳዮችን የቀላቀለ አደረጃጀት ጉዳዮቹን በመቀላቀል በሥራ ላይ ከሚፈጥረው ችግር በላይ፣ በድርጅቱ አመራርና አባላት ዘንድ የሀገራዊ ጉዳዮች ሊሰጣቸው የሚገባውን ልዩ አትኩሮቶች ማደብዘዙ አይቀርም። ይህ ሁኔታ ኢዜማ መሠረታዊ መርኆዎቹን የማይከተል ሀገራዊ ኃላፊነት የማይሸከም ደካማ ድርጅት ያደርገዋል።

በመጨረሻም እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ እጅግ የተለያዩ አመለካከቶችና ፍላጎቶች ያሉባት ሀገር ቀርቶ የተቀራረበ ፍላጎቶችና አመለካካቶች ባሉባቸው ሀገሮች ምርጫዎች እውነተኛ የሕዝብ ፍላጎት መገለጫ እስኪሆኑ ድረስ በምርጫ ውስጥ የሚገቡ ድርጅቶች የሁሉንም ዜጎች ድጋፍ ሊያገኙ እንደማይችሉ ይታወቃል።

ለምሳሌ በአንድ የምርጫ ወረዳ በተደረገ የፓርላማ መቀመጫ ምርጫ አንዲት የኢዜማ እጩ 50.1% (ሃምሳ ነጥብ አንድ በመቶ) ድምጽ አግኝታ ልታሸንፍ ትችላለች። አሸናፊዋ እጩ እጅግ ጠባብ በሆነ አብላጫ ድምጽ ያሸነፈች ቢሆንም አንዴ ካሸነፈች በኋላ ተወካይነቷ ድምጽ ለሰጧትም ሆነ ላልሰጧት የምርጫ ወረዳው ዜጎች በሙሉ ጭምር መሆን አለበት። ድምጽ የሰጧትንም የነፈጓትንም ዜጎች በእኩልነት ችግራቸውን መፍታት፤ ፍላጎታቸውን ለማሳካት መጣር ይኖርባታል። በምንም ዓይነት ድምጽ በሰጡትና በነፈጉት መሀከል አድሎ ማድረግ አይኖርባትም።

ይህን ዓይነት የሕዝብ ተወካይ ድርጅታዊ ፍላጎትና ሀገራዊ ፍላጎትን ጠንቅቆ ባላወቀና አስፈላጊውን መዋቅራዊና አሠራራዊ ዝግጅት ባላደረገ ድርጅት ውስጥ ማፍራት አይቻልም። እንደውም የሀገራችን የገዥ ድርጅቶች ተሞክሮ የሚያሳየው በምርጫ ድምጽን ያልሰጣቸውን ዜጋ በጠላትነት መፈረጅና በተቻለው ሁሉ ማጥቃት ነው። ይህ ሁኔታ ዜጎችን፣ በመጉዳት፣ በማሸማቀቅና በማስፈራራት፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው።

በመሆኑም ከተለያዩ ምክንያቶቹ መካከል ኢዜማ የሀገራዊ ጉዳዮችን ከድርጅታዊ ጉዳዮች ሳይቀላቀልቡት በጥንቃቄ ለይቶ የሚመለከት አደረጃጀት መከተሉ አስፈላጊ ካደረጉት መካከል አንዱን በዚህ ጽሁፍ የተመለከትን ሲሆን በቀጣይ ተከታታይ ልጥፎች (Posts) የሚብራራ ይሆናል።
አንድ ድርጅት እንዴት የፓርቲ መሪና የፓርቲ ሊቀ መንበር ይኖረዋል?


ክፍል 2

#ኢዜማ የአደረጃጀት መርህ በሀገርና በድርጅት ፍላጎትና ጥቅም መሀከል ሊኖር የሚገባውን ጤናማ ግኙነት ከማረጋገጥ አንጻር፤

በሀገራችን በተለይ በምርጫ ስም ሥልጣን መያዝ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በአሸናፊነት እራሳቸውን ያስቀመጡ ድርጅቶች በሀገርና ሕዝብ ላይ ካደረሱት ከፍተኛ ጉዳቶች መሀከል አንዱ የድርጅትን ፍላጎትና ጥቅም ከሀገር ፍላጎትና ጥቅም ለይቶ ካለማየት የደረሰው ጉዳት ነው።

የመጀመሪያው የጉዳት ዓይነት በማናቸውም በተረጋጉ ሀገሮች የሚታየውን መንግሥትን ሳይሆን ሀገርን እንደ ሀገር የሚያስቀጥሉ ተቋማት ፈጽመው እንዳይፈጠሩ ያደረገው ጉዳት ነው። ይህ ሁኔታ በምርጫ በሥልጣን ላይ የፈለገው ዓይነት ድርጅት ይምጣ የአሸናፊውን ድርጅት ፖሊሲዎች የሚተገብር በየጊዜው እያደገና የበለጠ ውጤታማ እየሆነ የሚሄድ የሲቪል ሰርቪስ አካል ሀገሪቷ እንዳይኖራት አደርጓል። የዚህ ጉዳት ውጤት ወደፊት በትክክለኛ ምርጫ ሥልጣን ላይ ለሚመጡ እንደ ኢዜማ ላሉ ድርጅቶች ከፍተኛ ፈተና መሆኑ የሚቀር አይደለም።

እስካሁን ያለው ሁኔታ የሚያሳየው በተለያዩ መንግሥታዊ መሠረታዊ ተቋማት፣ እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ መለከላከያ፣ ደኅንነት፣ የፍትሕ አካላት ያሉ መሥሪያ ቤቶች ያላቸው ዝግጅት የተለያዩ ፖሊሲዎችን ለማስተናገድ የሚችል አይደለም። በመዋቅር፣ በአሠራርና በሰው ምደባ ደረጃ ያላቸው ዝግጅት የአንድ የፖለቲካ አመለካከትን ታማኝነት መመዘኛ ያደረገ ነው። በመሆኑም ከሌላ የፖለቲካ አመለካከት የሚነሳ ፖሊሲዎችን ይዞ የሚመጣ ድርጅት የእነዚህን ቁልፍ ተቋማት መዋቅር፣ አሠራርና የሰው ምደባ ከመሠረቱ እንዲለውጥ ያስገድደዋል። ለዚህ ለውጥ የሚወጣው የሀገርና የሕዝብ ሀብት እንኳን እንደ ሀገራችን ያለች ደሀ ሀገር ቀርቶ አቅም ባላቸውም ሀገራት የሚቻል አይደልም። ይሄም ብቻ አይደለም፣ እስካሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ እነዚህ ድርጅቶች ሀገራዊ ይዘትና አቋም እንዳይኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ኃይሎች ማፈኛ ሲያደርጋቸው ኖሯል።

በኢዜማ እምነት፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም የግድ የሀገርና የድርጅት ፍላጎቶችንና ጥቅሞች ባወቀና በለየ መልኩ መሥራት የሚያስችለው የአወቃቀርና የአሠራር ባህል ያለው ድርጅት ያስፈልጋል።

ለዚህም ነው ኢዜማ፣ ሀገራዊና መንግሥታዊ ጉዳዮችን ከድርጅታዊ ጉዳዮች ለይቶ ዝግጅት ማድረግ የሚያስችል የመዋቅርና የአሠራር መርህ የተከተለውና ተግባራዊ እያደረገ ያለው።

ሁለተኛው ጉዳት፣ በሀገር፣ መንግሥትና በድርጅት መሀከል ሊኖርው የሚገባው ልዩነት በአግባቡ አለመለየቱ የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ለድርጅት ጥቅምና ፍላጎት እንዲውል ያደረገው ሁኔታ ነው። ይህ ሁኔታ በሥልጣን ላይ ያለውን ድርጅት አላግባብ የሕዝብን ሀብትና ንብረት ለድርጅት ጥቅምና ፍላጎት በማዋል በቀጥታ ያደረሰው ጉዳት ነው።

በሌላ በኩል በሥልጣን ላይ ያለው ድርጅት በከፍተኛ ደረጃ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በሚያደርገው ፉክክር እጅግ አድሏዊ የመፎካከሪያ አቅም ሰጥቶታል። ይህ ሁኔታ በሀገራችን የሚደረጉ ምርጫዎች ሚዛናዊና ፍትሀዊ እንዳይሆኑ በማድረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዳይገነባ ከፍተኛ ችግር የሆነ ጉዳይ ነው።

ለዚህም ነው ኢዜማ፣ የሀገርንና የመንግሥትን ንብረት ለድርጅት ጥቅም አለመዋሉን የሚያረጋግጥ የመዋቅርና የአሠራር መርህ የተከተለውና ተግባራዊ እያደረገ ያለው።

ምስል: ዮሐንስ መኮንን (የኢዜማ ም/መሪ)
ማዕረጉ ግርማ (የኢዜማ ም/ ሊቀመንበር)
ግልጽ ማብራሪያ እንጠብቃለን!!


ፓርቲያችን ኢዜማ “የሕግ የበላይነት ይከበር” ሲል ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ዜጎች ላይ ከሚደርስ አለአግባብ እገታ በተለይም በወቅቱ ማንነታቸው በማይታወቁ አካላት የተወሰዱ ጋዜጠኞችን ጠቅሶ መንግሥት ጋዜጠኞቹ ያሉበትን ሁኔታ በግልጽ እንዲያሳውቅ ጠይቀን እንደነበረ ይታወሳል።

ጋዜጠኞቹ ከ 12 እና 10 ቀናት እገታ በኋላ በትላንትናው ዕለት መለቀቃቸውን የሚዲያ ተቋሞቹ አሳውቀዋል፤ ጋዜጠኞቹ ተለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀላቸውን ፓርቲያችን እንደ መልካም ዜና ተመልክቶታል። ጋዜጠኞቹን እና ቤተሰቦቻቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ማለትም ይወዳል።

ሆኖም ፓርቲያችን ይህንን  መልካም ዜና ሙሉ ሆኖ የማያገኝበት ምክንያት የተያዙበትም ሆነ የተለቀቁበት መንገድ አሁንም ግልጽነት የጎደለው መሆኑ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ዜጎችም በተመሳሳይ ቀይ ቦኔት እና የፀጥታ አካላትን ልብስ በለበሱ ሰዎች እየታፈኑ የመንግሥት ማረሚያ ቤትም ሆነ ፖሊስ ጣቢያ ባልሆኑ ቦታዎች ታግተው እየቆዩ እየተለቀቁ እንደሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየገለፁ መሆኑ በተለይም “ለመንግሥት ቅርብ ነን” ከሚሉ አካላት ጋር ባላቸው የግል አለመግባባት ይህንን ተግባር እንደተፈጸመባቸው መግለጻቸው እና ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የተሰወሩ ግለሰቦች እስካሁን የት እንደሚገኙ አለመታወቁ ነው።

ከጋዜጠኞቹ መለቀቅ ጋር በተያያዘ አሁንም በተመሳሳይ ብዥታ ውስጥ ሆነን በቁጥጥር ውስጥ ያዋላቸው አካል መንግሥት ከሆነ አስፈላጊውን የሕግ ሒደት አሟልቶ ተጠያቂ የሚያደርግበትን ማለትም በሕጉ መሠረት በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ሕግ አካል እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸውን መጥሪያ ለምን አልያዙም? በጭምብል መሸፈን ለምን አስፈለገ? በሕጉ መሠረት በ 48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ለምን አልቀረቡም? ለሚሉ ጥያቄዎቻችን አሁንም ምላሽ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።

ከመንግሥት ውጪ የሆነ አካል ይዟቸው ከነበረ ዜናው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንደሆኑ ጥርጣሬ ላይ በሚጥል መልኩ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ለምን ዝምታን መረጡ?  ይህ እንዳለ ሆኖ ሕግን ማስከበር እንዳለበት አካል መንግሥት ዜጎቹን በዚህ አግባብ ከተያዙበት ነጻ ለማውጣት እና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተጠያቂ ለማድረግ ምን አከናወነ? እና ከዚህ በኋላስ እንዲህ አይነት የዜጎች ሰላምን እና ደህንነት ከሚያውኩ ተግባራት ዜጎቹን ለመጠበቅ ምን እየሠራ ነው? የሚለው ላይ ከመንግሥት ማብራሪያ እንጠብቃለን።

በመጨረሻም መንግሥት አሁንም ትኩረት ሰጥቶ ሊመለከተው የሚገባው ጉዳይ ዜጎች ሕጉን በተገቢው የሚያስከብርልኝ አካል የለም ብለው ሲያምኑ ሊፈጠር የሚችለውን የጸጥታ ችግር የማንወጣበት ማጥ ውስጥ የሚከተን መሆኑን ተረድቶ በተለይም ዜጎች ከፍተኛውን እምነት ሊጥሉበት የሚገባውን መንግሥት እምነት በሚያሳጣ መልኩ የጸጥታ አካላትን ደንብ ለብሰው ወይም እውነትም የመንግሥት አካላት በሆኑ የሚፈጸም እንዲህ አይነት ተግባር ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ እያሳሰብን ፓርቲያችን መሠል ችግር የገጠማቸው ዜጎች መረጃዎች እንዲያደርሱን ጥሪ ያቀርባል። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም.
አንድ ድርጅት እንዴት የፓርቲ መሪና የፓርቲ ሊቀ መንበር ይኖረዋል?


ክፍል 3

#ኢዜማ ን ሰፊ ተቀባይነት ያለው ዘመን ተሻጋሪ
ፓርቲ ማድረግ፤

ኢዜማ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ለማድረግ የረጅም ጊዜ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። በመጀመሪያ የፓርቲው መርሆዎች ዘመን ተሻጋሪ፤ ለሀገር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሆን ይገባቸዋል። በመቀጠልም መርሆዎችን መሠረት ያደረገው ሀገራዊ ራዕይ ኢትዮጵያን የሠለጠነች ዴሞክራሲያዊ ሀገር ማድረግ መቻል ይኖበታል።

ኢዜማ ሀገራዊ ራዕዩን እውን ለማድረግ ሰፊ ተቀባይነት ያለው የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆን አለበት። ኢዜማ ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው ሀገራዊ ችግሮችን የተረዳ፣ ለችግሮቹ መፍትሄ ያለው፣ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል መዋቅር ዘርግቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት መሆን አለበት።

በሀገራችን ሁኔታ አሁን ባሉት 547 የምርጫ ወረዳዎች መዋቅር ዘርግቶ ሀገርን ለመለወጥ የሚያስችል እንቅቃሴ ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ድርጅታዊ ሥራ ይጠይቃል።በሌላ በኩል ኢዜማ የሰለጠነች ሀገር እውን ለማድረግ እራሱ መጀመሪያ የሰለጠነ ድርጅት መሆን አለበት። የሰለጠነ ድርጅት ማለት ዓባላቱ በመረጃና በምክንያት የሚመሩ፤ ምንም ጊዜ ልህቀት ላለው ሀሳብና ተግባር እራሣቸውን የሚያስገዛ ባህል ያዳበሩ፣ የዘመናዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጠቀሙ ዓባላት መሆን ይኖርባቸዋል።

ይህም በመሆኑ ኢዜማን ዘመናዊ ማድረግ እጅግ ከፍተኛ አትኩሮትና ጥረት የሚጠይቅ ተግባር ነው። ሌላው ኢዜማ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ተልዕኮውን ለመወጣት እራሱ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሆን አለበት። ይህ ማለት ኢዜማ አንድን ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ የሚያደርጉትን የግልጽነትን፣ የተጠያቂነትን፣ የብዙኃኑን ውሳኔን መቀበልና መተግበር፣ ሕግንና ደንብ የማክበርን መመዘኛዎች ማሟላት ይኖበታል።

ይሄን ዓይነቱን ዴሞክራሲያዊ ባህል በኢዜማ ውስጥ የበላይነት እንዲያገኝ ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል። ለዚህም ነው በዚህ ክፍል በቀረቡት ምክንያቶች የተነሳ፣ ኢዜማ፣ በሊቀመንበሩና በምክትሉ የሚመራ፣ ዋናው ትኩረቱ ኢዜማን ሰፊ ተቀባይነት ያለው ዘመን ተሻጋሪ፣ ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማድረግ የሚያስችል የመዋቅርና የአሠራር መርህ መከተልና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገው።

ክፍል 1: https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1304374781053271&id=100044422836699&mibextid=Nif5oz

ክፍል 2: https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1305159280974821&id=100044422836699&mibextid=Nif5oz
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
እንደ ኢዜማ ብልጽግናን እንዴት ትበይኑታላችሁ?

#ኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እዮብ መሣፍንት በቃለምልልሱ ላይ ከመለሱት የተወሰደውን አጭር መልስ ይመልከቱ። በተጨማሪም ሚያዚያ 2015 ኢዜማ ያለፉት 5 ዓመታት ግምገማ ሲል ካዘጋጀው ሰነድ "ብልፅግና በዜግነት እና ማንነት አጥር ላይ" ሲል የበየነበትን ትንታኔ ለማንበብ ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ

https://drive.google.com/file/d/13afzhNhoOCYYH1atddrFqpRCktjm7obt/view?usp=drivesdk

👉 ሙሉውን ቃለ ምልልስ ለመመልከት
https://youtu.be/XqYj7Uf1qmc?si=wtN8I9KO5JUraFE1