Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25.1K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የወልቃይት ጠገዴ እናቶች ሰቆቃ ሲታወስ
**************
(ኢ ፕ ድ)
”አንድ በሬ ሸጬ ስድስት ዓመት በመቀሌ የታሰረውን የልጅ ልጄን በደከመ አቅሜ ሄጄ አስፈትቻለሁ። ከተፈታ በኋላም አፋኙ የህወሓት ጁንታ በሚደረግበት ጫናና ክትትል ተማሮ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሄዷል። የልጅ ልጄ ያለበትን ቦታና ምን እንዳጋጠመው ስለማላውቅ የበረሃ ራት ሆኖ ይሆን ብዬ እየተጨነኩ ነበር። አምና ግን ሳውዲ መግባቱን ስለሰማሁ ደስታዬ ወደር የለውም” የሚሉት ወይዘሮ ከፍያለች በላይ ናቸው።

ቃፍታ ሁመራ ከተማ ከሀዲው የህወሓት ጁንታ ነጻ ከወጣች ሶስት
ሳምንት ሁኗታል። ከተማዋ ነጻነቷን በመቀናጀቷ እፎይታ ከተሰማቸው
ነዋሪዎች መካከል አንዷ ወይዘሮ ከፍያለች በላይ ናቸው። አፋኙ ቡድኑ
በማንነታቸው ምክንያት በእኚህ አዛውንት ላይ ከፍተኛ ማንገላታት፣
ሰቆቃና ግፍ ፈጽሞባቸዋል።

ማንነቴን አልሸጥም እኔ የወልቃይት አማራ ነኝ አባቴ፣ አጎቶቼ ይግባኝ ሲኖራቸው መቀሌ ሳይሆን ደባርቅና ዳባት ሄደው ሲያስፈጽሙ ነበር ብዬ በአደባባይ በመናገሬ እያረስኩና እያሳረስኩ ልጆቼን ያሳደኩበትን መሬቴን ተነጥቄያለሁ ይላሉ ።
https://www.press.et/Ama/?p=36795
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የመመስረትና መልሶ የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ
************************
(ኢ ፕ ድ)

መቀሌ፡- በትግራይ ክልል ህግን የማስከበር ሶስተኛው ምእራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር የመመስረትና መልሶ የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የትራይ ብሄራዊ ክልል ጊዜያዊ አስተዳር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ህግን የማስከበር ርምጃውን በጥንቃቄ በማከናወን ወደ ቀጣዩ ምእራፍ መሸጋገር ተችሏል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደር የመመስረትና መልሶ የማደራጀት ስራ ተጀምሯል።

እስካሁንም በሽሬ እና በአክሱም የተለያዩ ቀበሌዎችንና ወረዳ አስተዳደሮችን መልሶ የማደራጀት ስራ ተሰርቷል።

ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የተመረጡ ስራ አስፈጻሚዎች ስራ ጀምረዋል ያሉት ዶ/ር ሙሉ፤ በመቀሌ ከተማ ህዝቡ ወደ መደበኛው ስራው እንዲመለስ፣ የመንግስት ተቋማት ስራቸውን እንዲያከናውኑና የንግድ ተቋማትም ስራቸውን እንዲጀምሩ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች ተደራጅተው ከመከላከያ ጎን እንዲቆሙ የልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲሰጡም እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሙሉ፤ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የመንግስትን እገዛ ሲጠባበቁ እንደነበርና በከተሞች አልፎ አልፎ የሚታየውን ዘረፋ ለማስቆም ከጸጥታ ሃይሉ ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በጸጥታ ስጋት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ሸሽተው የሄዱ ሰዎችን ወደ ነበሩበት የመመለሱና የማረጋጋት ስራው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊት መቀሌንና ሌሎች ከተሞችን የተቆጣጠረ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ወደሚኖርበት አካባቢ በመምጣት ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህግ ማስከበሩ ስራ ለትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ጥቅም ይዞ የሚመጣ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ሙሉ፤ ህዝቡ ከነበረበት ጫና ወጥቶ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የክልሉን የካቢኔ አባላት የማዋቀር ስራ እንደሚሰራና እንደ ባንክ ፣ቴሎኮም፣ መብራት የመሳሉት አገልግሎት ሰጪ ቋማትን ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር የማስጀመሩ ስራ ትኩረት ተሰጥጦታል ብለዋል፡፡

የስራ እንቅስቃሴ ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ የምግብ እጥረት ሊፈጠር ስለሚችል አርዳታዎችን የማስተባበር ስራዎች እንደሚከናወኑ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡
በኢያሱ መሰለ
ከአላማጣ ወደ መቀሌ የሚሄደው የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፍያ መስመር እየተጠገነ ነው
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

ከአላማጣ ወደ መቀሌ የሚሄደው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፍያ መስመር እየተጠገነ ነው።

በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢ ተዟዙሮ እንደተመለከተው፤ በከሀዲው የህወሓት ታጣቂዎች ጉዳት ደርሶበት የነበረው ይሄው የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ጥገና በፍጥነት እየተከናወነ ነው።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ትግራይን መልሶ የመገንባቱ ሥራ የድኅረ ዘመቻ ዋናው ተግባራችን ነው ማለታቸውና ይህ ተግባር ሦስት መልኮች እንዳሉት ማስታወቃቸው ይታወቃል።

"ሰብአዊና ማኅበራዊ ድጋፍ፣ የተጎዳውን መሠረተ ልማት መልሶ መገንባት እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ማስጀመር። እነዚህ ሥራዎች በስፍራው በተገኙ ቡድኖች አማካኝነት ተጀምረዋል" ማለታቸውም ይታወሣል።
ባለ ከዘራው ኮሎኔል
*********
(ኢ ፕ ድ)
ፊታቸው ላይ የአልበገርም ባይነት ስሜት ጎልቶ ይነበባል፤ እያነከሱም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። መገናኛ ራዲዮናቸውን እና የምርኩዝ ከዘራቸውን ይዘው የጁንታው ቡድን አመራር ያለበት ቆላ ተንቤን አቅራቢያ በምትገኝ ሰዋራማ ስፍራ ላይ ጦሩን እየመሩ ይገኛል።
ኮሎኔል ሻምበል በየነ ይባላሉ። በቆሙበት የውጊያ ትዕዛዝ እየሰጡ ኮስታራ ፊታቸውን ወደእኛ ዘወር አደረጉ። ቆስለው አልታከምም በማለት በወኔ እየመሩ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራር መሆናቸውን ሰማንና ታሪካቸውን እንዲያካፍሉን ጠየቅናቸው።
ድንገተኛ ፈገግታ እያሳዩ ቀድሞም የጁንታው አባላት ውጊያ ሰራዊቱ ላይ ሊከፍቱ እንደሆነ ጥርጣሬ ነበረኝ በማለት በተረጋጋ ስሜት ትውስታቸውን ማጋራት ጀመሩ። እኔ የ31ኛ ክፍለጦር ምክትል የኦፕሬሽን አዛዥ ነበርኩ ዋና አዛዡ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ቀደም ብሎ የተወሰኑ አባላትን ሽሬ ድረስ ወስዶ ሲሰበስብ የሆነ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል አስበው እንደነበር።
ማታውኑ ችግር ሊኖር እንደሚችል በማመን በግሌ ዝግጅት አደረግኩ። ስዘጋጅ በባንክ አካውንቴ የነበረውን ጥቂት ገንዘብ በቤተሰብ አዞርኩ። ከዚያም ጥቃት ለማድረስ ከበባ ሲፈጽሙብኝ ተከብቤያለሁ በሚል ለበላይ አካላት ሪፖርት አደረኩ ።
በመከላከያ ላይ ጥቃት ሲፈጸምም የክፍለጦሩ አዛዡ ከድቶ የጁንታውን ቡድን ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ የክፍለጦር ኮሚቴ ወይም ከበታች አዛዦች አባላት ጋር በመሆን ግብግብ ፈጸምን። እኔም ከፊቴ ያለውን በጥይት መትቼ ጣልኩ። እኔ ጋር የተጀመረች የመከላከል ተኩስ እስከታችኛው የሻለቃ አመራር ድረስ እየተደማመጠ የመከላከል እርምጃውን ወሰደ።
በኋላም የካምፑን ከበባ አጠናቅቄ ስወጣ ደግሞ የልዩ ኃይል ከውጭ ጠበቀኝ የሚሉት ኮሎኔል፤ እነሱንም ጥሼ በመውጣት ከስምንተኛ ሜካናይዝድ ጦር ጋር ተቀላቀልኩ ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሱታል።
በወቅቱ እግራቸው ላይ በጥይት መመታታቸው እምብዛም ቁብ አልሰጡትም። በዚያ ሁኔታ ላይ እያሉ ወደኤርትራ በማፈግፈግ በዚያ ከሚገኘው እና በጁንታው ታጣቂ ጥቃት ደርሶበት ከሚገኘው ጦራቸው ጋር ተገናኙ። ጦሩን አደራጅተው በመመለስ ሽራሮ ፣ሽሬ፣ አዲ አደራይ፣ አዲነብሪ እና በርካታ ቦታዎች በማስለቀቅ የህግ ማስከበር እርምጃቸውን በብቃት መወጣትም ቻሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከታፋቸው የሚፈስ ደም እንደ ነበር በቅርበት የሚያውቋቸው ወታደሮች ይናገራሉ። ቁስሉን በየሶስት ቀኑ በጦር ሜዳ አካባቢ እየታከምኩ አንዷ ጥይት ወጣች የሚሉት ኮሎኔል ሻምበል፤ ምርኩዝ ይዘው ግዳጃቸውን መወጣታቸውን ነግረውናል። ዋና አዛዡ ግን የጁንታውን ቡድን በመቀላቀል ለጁንታው አመራር ሽፋን ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ቆላ ተንቤን ላይ ወንጀለኛ ለማስመለጥ እና ወንጀለኛ ለመያዝ ዋናው እና ምክትል አዛዡ ፊት ለፊት ተፋጠዋል። ምክትል አዛዥ ዋናውን ከነጀሌዎቹ እያባረረ እርምጃ እየወሰደበት ይገኛል። ከሚመሩት ጦር ጋር በርካታ ሀገር የከዱ ጄኔራሎችን እያባረሩ ቆላ ተምቤን ላይ ያደረሱት ኮሎኔል ሻምበል፤ እዚህ በመድረሴ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ሲሉ በኩራት ይናገራሉ።
ቆላ ተምቤን ላይ የመሸገውን የከሃዲው ቡድን አመራር አባላት ለህግ ሲቀርቡ በተሻለ ህክምና በጥይት የተመታውን እግራቸውን ሊታከሙት እንደሚችሉ እንደተወርዋሪ ኮኮብ መሳይ ብልጭታ ባለው ፈገግታቸው ታጅበው በለሆሳስ ነገረውናል። ቦታው ላይ ቆስለውም ቢሆን ጦሩን እየመሩ መገኘታቸው ለሰራዊቱም ብርታት መሆኑን አልሸሸጉንም።
በእጃቸው ከዘራቸውን ጨብጠው የሚንቀሳቀሱት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ በጉዳት እያሉም ቢሆን በህግ ማስከበር እርምጃ የጁንታውን አመራሮችን ለመያዝ ፀሐይ ውርጭ ሳይሉ በመታገል ላይ ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን በየጊዜው አታጣም የሚባለው ብሂል እውነት መሆኑን ያረጋገጠ ነው።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013 ዓ.ም
ጌታቸው ረዳና መሰል የህወሓት ጁንታዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎችና የግል ሰነዶቻቸው መያዛቸው ተገለጸ
*********************
(ኢፕ ድ)
ጌታቸው ረዳና መሰል የህወሓት ጁንታዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ከ40 በላይ ተሽከርካሪዎችና የግል ሰነዶቻቸው መያዛቸው ተገለጸ።
የጁንታው ቃል አቀባይ የሆነው ጌታቸው ረዳና መሰሎቹ ከመከላከያ ሰራዊት የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ለማምለጥ ሲጠቀሙባቸው የነበሩት እነዚሁ ተሽከርካሪዎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መግባታቸውን የ32ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ አስታውቀዋል።
እንደ ኮሎኔል ደጀኔ ገለጻ፤ ተሽከርካሪዎቹ የተያዙት ከማይጨው 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዴላ ወረዳ ነው።
ተሽከርካሪዎቹ ውስጥ በተደረገው ፍተሻም የከሀዲው ቡድን አመራር አባላት መታወቂያ፣ ፓስፖርትና የተለያዩ የግል ሰነዶቻቸው መገኘታቸውን ኮሎኔል ደጀኔ አስታውቀዋል።
የግል ሰነድ ከተገኘባቸው የጁንታው አባላት መካከል የቀድሞው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት እንደሚጠቀሱ ኮሎኔል ደጀኔ ተናግረዋል።
ከተያዙት ተሽከርካሪዎች ውስጥ እጅግ ዘመናዊና በአሻራ የሚከፈቱም እንዳሉበት ኮሎኔሉ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ፍተኛ ድጋፍ እንዳለው ገልጸው፤ በተለይም ከ10 ሺህ ህዝብ በላይ በማይጨው ስታዲየም ሰብስበው የማረጋጋት እና የማወያየት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚሁ ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ጁንታው በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲያደርገው ለነበረው መፍጨርጨር ከመንግስት ሰራተኞች የወር ደመወዝ ላይ በመቁረጥ ለሚሊሻውና ለታጣቂዎቹ ደመወዝ ይከፍል እንደነበር ህዝቡ በምሬት መናገሩን ኮሎኔሉ አስታውቀዋል።
ነዋሪዎቹ አሁን ይህ በመቅረቱ መደሰታቸውን እንደገለጹላቸው ኮሎኔሉ ተናግረዋል።
ህዝቡ እንደ ስልክና መብራት ያሉ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን መንግስት በፍጥነት እንዲመልስላቸው ማንሳታቸውን ገልጸው፤ በመንግስት በኩል እየተደረገ ባለው ርብርብ እስከ ኮረም ያለው ጥያቄ መልስ ማግኘቱንና በቀጣይም የተቀሩት ከተሞች ጥያቄ እንደሚመለስ አስታውቀዋል።
በእያሱ መሰለ
«መከላከያ ሰራዊታችን ያሳየን የኢትዮጵያዊነትን ልክ ነው» - ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ
**********************
(ኢ ፕ ድ)
መከላከያ ሰራዊታችን በሶስት ሳምንት ውስጥ በታላቅ ጀብዱ የኢትዮጵያዊነታችንን ልክ እንዳሳየን የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አስታወቁ ፡፡
ዶክተር ቢቂላ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፤ በትግራይ ክልል ተሸሽጎ የከረመው ጽንፈኛው የህወሓት ስግብግቡ ጁንታ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የሕግ ማስከበሩን ተግባር ባከናወነበት ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ ጀብድ በመፈጸም የኢትዮጵያዊነትን ልክ አሳይቶናል ።መከላከያ ሰራዊቱ በሶስት ሳምንት ውስጥ በሰራው ጀብዱ በእርግጥም ታላቅነቱንም አስመስክሯል ፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ፤ ‹በአገሬ ከመጣህማ እኔን ታርዳለህ እንጂ ትጥቄን አትፈታም፤ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና በአገሬ ማንነት ከመጣህ ትጨርሰኛለህ እንጂ በዘር አትከፋፍለንም የሚል የጀግንነት ጥግ አሳይቷል “ ያሉት ዶክተር ቢቂላ ፤ በተለይም ውስጥ ያሉ አመራሮች ትጥቃቸውን ፈተው ላለመስጠት ያደረጉት ተጋድሎ ታላቅ ነው ብለዋል።ሌላ ኃይል እስኪደርስላቸው ድረስ አንገት ለአንገት ተናንቀው የታገሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል ። ከድሉ ጀርባ ያለው የአገር አንድነት መለከያ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን እንደሆነም ጠቁመዋል ። https://www.press.et/Ama/?p=36927
ወደ ሕዝብ ባለመተኮስ የተገለጸ ቃል ኪዳንና ጽናት!
****************
(ኢ ፕ ድ)
ሻለቃ ዘላለም ብዙነህ በሰሜን አየር ምድብ የአየር መከላከል እቅድና ስልጠና ቡድን መሪ ነው።ዋናው የስራ ድርሻው ጠላት የአየር ጥቃት እንዳያደርስ መከላከል እና የምድር ኃይሉ እንዳይጎዳ ድጋፍ መስጠት ነው።ሰሜን አየር ምድብ ከመጣም ከ17 ዓመት በላይ ሆኖታል።ሻለቃ ቡዙነህ እንደሚያስረዳው ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ለውጡ ያልጣማቸው ኃይሎች አዳዲስ ባህሪ አምጥተዋል።
ከፌደራል መንግስት የሚተላለፉ መመሪያዎችን ያለመቀበልና ሰራዊቱን ከፋፍሎ የመመልከት ሁኔታዎችም ይስተዋሉ ነበር። የእነሱን ሀሳብ የማይቀበለውን የአየር ኃይል አባል የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊ ነው በማለት ያጥላላሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ምንም ባላሰቡት ሁኔታ መቀሌ በሚገኘው የሰሜን አየር ምድብ መኖሪያ ቤት የተኩስ ሩምታ ተከፈተ፤ ምንድ ነው ብለው ሲጠይቁም የሴራው ተባባሪ የሆኑና ጉዳዩን የሚያውቁ አባላት ልምምድ ነው እያሉ ያዘናጓቸው እንደነበር ያስታውሳል።
‹‹ሌሊቱን ሙሉ ሳንተኛ አድረን ልክ አስራ ሁለት ሰዓት ሲደርስ ልዩ ኃይሎች ወደ ግቢው መግባት ጀመሩ።በተለይም የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ አባላትን ከቤታችን እያወጡ እያመናጨቁና እየገረፉ ወሰዱን።ወደ ማጎሪያ ቤት ከወሰዱን በኋላ በብሔር ከፋፈሉን።ደቡብን ለብቻ ፤ አማራና ኦሮሞን በአንድ ላይ አድርገው አጎሩን። ሚሳኤል የመተኮስ ልምድና እውቀቱ እንዳለኝ ስለሚያውቁ እኔን ለብቻዬ ወሰዱኝና እንድተኩስላቸውና ከእነርሱ ወገን እንድቆም ጠየቁኝ።
https://www.press.et/Ama/?p=36926
«ጁንታው ሕጋዊ የንግድ ውድድርን ማዛባት ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪዎችን የማጥፋት አካሄድ ይከተል ነበር » - አቶ ውብሸት ሙላት የህግ ባለሙያ
***********************
(ኢ ፕ ድ)
ወንጀለኛው የህውሓት ጁንታ ሁሉንም የቢዝነስ ተቋማት በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ማንኛውም የንግድ ውድድር እንዳይኖር ከማድረግ በዘለለ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ የግልና የመንግስት የንግድ ተቋማትን እስከማጥፋት መሄዱን የሕግ ምሑሩ አቶ ውብሸት ሙላት አስታወቁ ።
አቶ ውብሸት በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ይህ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ አግላይ ብቻ ሳይሆን ሌላውንና ከሱ ውጭ የሆነውን የሚያስወግድ እና አፋኝ ነበር ። በኢኮኖሚውም መስክ በኢትዮጵያ ትልቁ ኢንቨስተር ይህ ቡድን ነበር ፤ከፌደራል መንግሥት በላይ የኢኮኖሚ አቅም የፈጠረ ነው ።
አንድ ቡድን በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው የበላይ ከሆነ እና በዚያ ላይ ያለው አስተሳሰብ አግላይ ከሆነ አገርን አደጋ ላይ ይጥላል የሚሉት አቶ ውብሸት፤ አገር ማፍረስን ጨምሮ የፈለገውን እንዲያደርግ እድል ይሰጠዋል፤ በወንጀለኛው ጁንታ የሆነው ይኸው ነው ብለዋል ።
https://www.press.et/Ama/?p=36925
"ጃንሜዳን ለጥምቀት በዓል ዝግጁ እናደርጋለን"
- አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ
**********************
(ኢ ፕ ድ)
ጃንሜዳን ለጥምቀት በዓል ዝግጁ እናደርጋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስተወቁ።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ተብሎ አትክልት ተራ ወደ ጃንሜዳ እንዲዘዋወር መደረጉን ያስታወሱት ወ/ሮ አዳነች፤ "አሁን ጃንሜዳን መልሶ ለጥምቀት በዓል እና ሌሎች ማሀበራዊ አገልግሎቶች ዝግጁ ላማድረግ ቦታውን ማጽዳት እና ማስተካከል ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ዛሬ ማለዳ በቦታው በመገኘት የጽዳት ስራ አስጀምረናል"ብለዋል።
በቦታው ያሉ ነጋዴዎችም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሃይሌ ጋርመንት እና በሌሎች አካባቢዎች ወደተዘጋጁ የገበያ ማዕከላት ይዘዋወራሉና ለዚህ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ከንቲባዋ አሳስበዋል።
"አዳዲሶቹ የአትክልት ገበያዎች የሚርቋቸው የከተማችን ነዋሪዎች ይቅርታ እየጠየኩ በገርጂ፣ ጀሞ፣ አቃቂ፣ ጉለሌ እና ሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ የገበያ ስፍራ እያዘጋጀን መሆኑን እና ችግሩ ጊዜአዊ እንደሆነ ማሳወቅ እወዳለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለበዓሉ አከባበር በኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ በመተባበር፣ በመቻቻል እና መተሳሰብ መንፈስ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“አስክሬን ማየት በጣም ቀላል ሊሆን ይችላል፤ እኔም አይቸዋለው፡፡ ከዚህ በፊት የአንድ አመት ልጄን ቀብሬያለሁ፤ አልከበደኝም ፡፡ ማይካድራ ላይ ግን መቆም አይቻልም፤ ያዩትን ሁሉ መመስከርም አይቻልም፤ ስሜቱ በጣም ከባድ ነው፡፡ ያንን ተቋቁመን ባንዘግበው፤ ቦታው ላይም ባንቆም ኖሮ ወንጀሉ ተዳፍኖ ይቀር ነበር” - ጋዜጠኛ ወንድአጥር መኮንን
*********************
(ኢ ፕ ድ)

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 80ኛ አመት የምስረታ በአሉን አመቱን ሙሉ በተለያቱ መድረኮች እያከበረ ይገኛል። የበአሉ አካል በማድረግም በህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ ለተሳተፉ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የምስጋና እና የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በዚሁ መርሀ ግብር ላይም ወደ ግንባር ከተላኩ ጋዜጠኞች መካከል የማይካድራውን ጭፍጨፋ በስፍራው ተገኝቶ የዘገበው የአማራ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ ወንድአጥር መኮንን የተመለከተውን ለእለቱ ታዳሚያን አጋርቷል።

አስክሬን ማየት በጣም ቀላል ሊሆን ይችላል፤ እኔም አይቸዋለው፡፡ ከዚህ በፊት የአንድ አመት ልጄን ቀብሬያለሁ፤ አልከበደኝም ፡፡ ማይካድራ ላይ ግን መቆም አይቻልም፤ ያዩትን ሁሉ መመስከርም አይቻልም፤ ስሜቱ በጣም ከባድ ነው፡፡ ያንን ተቋቁመን ባንዘግበው ቦታውም ላይ ባንቆም ኖሮ ወንጀሉ ተዳፍኖ ይቀር ነበር” ሲል ነው ጋዜጠኛ ወንድአጥር ምልከታውን ያጋራው።

የተመለከትኳቸው ነገሮች የሚያሙ ናቸው፤ እነዚህ ህመሞች እኛን አመው ባይቆሙ ኖሮ ኢትዮጵያም ኢትዮጵያ ሆና አትቀጥልም ነበር፤ እውነት ለመናገር የማይካድራ ህዝብ ህመሙን ባይችለው ኖሮ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና አትቀጥልም ነበር፡፡

ጋዜጠኛ ወንድአጥር በእለቱ በሰጠው የአይን ምስክርነት ላይም ያነሳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፤

👉በማይካድራ ላይ የሞተው በዋናነት አማራ ይሁን እንጂ ኦሮሞም ሞቷል፤
ወላይታም ሞቷል፤ ሶማሌም ሞቷል፤

👉ትህነግ ለማንኛውም ነገር እንደማይመለስ የስለት ጫፍ ድረስ ከመጨከን
ወደኋላ እንደማይል ያሳየበት ቦታ ማይካድራ ነው፤

👉የትህነግ ጥላቻ ከ1968 ማኔፌስቶውም በፊት ነው፤ ማንፌስቶው እኮ
የአስተሳሰቡ ውጤት ነው፤

👉የትህነግ የማይካድራ ጭካኔና ጭፍጨፋ በፊት ከመጋረጃ ጀርባ እንደሚፈጸም
በሀሜት ደረጃ ይሰማ የነበረው አሁን መጋረጃው የተገለጠበት ሰይጣንም
ያፈረበት ስራው ነው፤

👉የጁንታው ውሸት አስገራሚ ነበር፤ እኔ ሁመራ ሆኜ ዘገባ እየሰራሁ፤ በሬዲዮ
የሰማሁት የእነሱ ዜና ሁመራን ተቆጣጥረናል የሚል ነው፤ ደነገጥኩ የት ነው
ያለሁት እኔ ነኝ ወይንስ ሁመራ ነው ወደሌላ ቦታ የሄደው እስክል ድረስ
ተገረምኩ፤

👉እነሱ ቢዋሹም አይናቸውና እጃቸው አይዋሽም ነበር፤ በሚዲያዎቻቸው
እየቀረቡ ሲዋሹ ሁሉም ነገር ያስታውቅባቸው ነበር፤

👉የትህነግ ሀይል ገኖ ነበር የመጣው፤ በተለይ እኔ በነበርኩበት አብድራፊ በኩል
አብድራፊን ተቆጣጥሮ ወደ ጎንደር፤ ሶሮቃን በዳንሻ በኩል ተቆጣጥሮ ወደ
ጎንደር፤ በራያ በኩል ወደ ወልዲያ የመሄድ እቅድ ነበረው፤ 23ኛው ክፍለ ጦር
ተበትኖ ስለነበረ ምንም አያስቀረውም ነበር።

👉ነገር ግን የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ዝግጁ ስለነበረና የኮንትሮባንድ ስራን
ሲቆጣጠሩ በነበሩ ከተፈጸመባቸው ጥቃት ያመለጡ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም
ባደረጉት ተጋድሎና ጀግንነት ትህነግ ሊቆም ችሏል፤

👉ከፊት ለፊት በመሳሪያ ከጎናቸው በጓደኞቻቸው አስከሬን ሽታ ተፈትነው ድል
ነስተዋል፤ ይሄንን ድል ያደረጉት በኢትዮጵያ ፍቅር ነው፤ በኢትዮጵጽያዊነት ነው፤

👉የአማራ ልዩ ሀይል ወደማይካድረ ከመሄዱ በፊት ሁለት የግዴታ አማራጮች
ነበሩት፤ አንደኛው ያለውን ስንቅና ጥይት ለተበተኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት
እያጋራ መዝለቅ፤ የተማረከውን ሀይል ደግሞ ለመከላከያ እየሰጠ መሄድ
ነበረበት፤ ይሄንን አደረገ፤

👉ሁለተኛው አማራ ልዩ ኃይል ሌላኛው ጫና እነማይካድራን ማስለቀቅ፣ የሉግዲ
መሿለኪያን ማስለቀቅ ወደ ሱዳን የሚሄደውን የትህነግ ኃይል የሚሾልከበትን
በር መዝጋትና የሁመራን ቦታ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን የተከበቡ የመከላከያ
ሰራዊት አባላትን ከጓደኞቻቸው የአስክሬን ሽታ፣ ከተከበቡበትም ሕይወታቸውን
ማትረፍ ግዴታው ነበረ፤ ሀላዊና በረከት ላይ ይህንን አደረገ፤

👉ወደ ማይካድራ ስንደርስ ደም ፈሷል፤ ሁሉም አዝኗል፤ ሁሉም ይተኩሳል፤
ከመኪና ስንወርድ ሁሉም በእኛ ተቆጥቷል፤ ምክንያቱም እኛ ድሉን ስናበስር
ነው የቆየነው፤

👉እዛ ቦታ ላይ ደም ፈሷል፤ የራሳችንን ወገን ደም ረግጠናል፤ እዛ ቦታ ላይ በወደቀ
የአስክሬን ብዛት መካከል መቆም ምናልባትም ትንፋሽን መቁጠር እስከሚያክል
ድረስ የምንተነፍሰው አየር ያስጨንቀን ነበር፤

👉በእንደዚህ አይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ትንፋሽ ቅንጦት ነው፣ የልብ ምት
ቅንጦት፤ ሁሉም ጭንቅላታቸው ተከፍቷል፤ ሁሉም ሆዳቸው ተከፍቷል፤ ሁሉም
ደምተዋል፤ ሁሉም ወድቀዋል፤ አልጋ ያገኙት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ በእነዚህ
መሃል መቆም በጣም ከባድ ነበር፤

👉በጋራ ሆነን ይህንን ነገር ለዓለም ማሳወቅ ነበረብን፤ ይህንን ዘግተነው ካለፍን
አደገኛ ነበረ፤ መበርታት ነበረብን፣ ደም ረግጠን ነው የቆምነው፤ ሁላችንም
ደም ረግጠናል፡፡

👉ይህንን ለቅሶ እዛ አላለቀስኩትም፣ ሰላም ስለሆነ ነው፤ ማልቀስም ሰላም
በሆነበት ቦታ ነው የሚቻለው፣

👉ህዝብን አነጋገርን ወስደው እንደ ቀበሯቸው ነገሩን፤ ነገር ግን የተገደሉት እነዚህ
ብቻ አይደሉም አሉን፤

👉ከቢሮ መቀሌ ትገባላችሁ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶናል፤ መቀሌ መግባት ለእኛ
መዝናናት ነበር፤ ስለሆነም በየቦታው የተደፉ ሰዎችን ማሳየት ነበረብን፤ አሞራና
ዝንብ እየተከተለን በየቦታው የወደቁ አስከሬኖችን አሳየን፤

👉 ዓለም የትህነግን መጥፎነት ያየው ያን ቀን ነበር፤ ምክንያቱም በፕሮፓጋንዳ
ተሸፍኖ ነበረ፤ እኛ ገለጥነው፤

👉 ከአከባቢው ሰው ጋር ተባብረን በመጀመሪያው ቀን የ74 ሰዎችን አስከሬ
አገኘን፤ 74ቱም ስዎች በጋራ ነው የተቀበሩት፤ የህጻናት ጫማ ነበረ፣ የሴቶች
ነጠላ ነበረ፤

👉 አቡነ አረጋዊ በሚባለው ቦታ ላይ የተቀበሩት ሰዎች ቁጥራቸው አይታወቅም፤
በጣም የሚገርመው አስክሬኖቹን መቅበር የማይቻልበት ጊዜ ነው የተደረሰው፤
የአካባቢው ሰው የአስከሬኑን ሽታ ለመቋቋም ሲል ሽቶ ተጠቅመዋል፤

👉 ከሁለት ቀናት በኋላ ተመሳሳይ ጥቆማ ደረሰን፤ አሞራ አከባቢውን ይዞራል፤
ዝንቦች ወረውታል፤ 18 የደረቀ አስክሬን አንድ ላይ ሳይቀበሩ አገኘን፤ እንዲሁ
ነው የተደፉት፤

👉 እስከ መቼ ነው በዚህ ሁኔታ የምንቀጥለው አሁን ያለን አማራጭ ኢትዮጵያ
የሁላችንም ድምቀት መሆን አለባት፤ የሁላችንም ጌጥ ነው መሆን ያለባት፤

👉 ኢትዮጵያን ተጭኖ የተለያዩ ብሔሮችን ዘር እየለየ የሚያጭድ የተንኮል ገበሬ
ካለና እሱ ካልፀዳ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ መሆን አይችልም፤

👉 እያንዳንዱ ወታደር የተዋጋው በሸተተ ጓደኛው አስክሬ ጎን ሆኖ ነው፤ እዚህ
ቦታ ላይ መቆም አስክሬን ማየት በጣም ቀላል ሊሆን ይችላል፤ እኔ

አይቻለሁ ከዚህ በፊት ልጄን ቀብሬያለው፤ አልከበደኝም፤ ማይካድራ ላይ ግን
መቆም አይቻልም፤ ይሀንን መመስከር አይቻልም፤

👉 ሰው ካልሆንን ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም፤ እነዛ ሰዎች ሰውነታቸው
ስለካዳቸው ነው ኢትዮጵያዊ መሆን ያልቻሉት፤

👉 ከዚህ በኋላ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የመጨረሻውን የተንኮል ስለት የያዘው አካል
በመከላከያ ሰራዊት፣ በልዩ ኃይል አባላት፣ በአፋር ልዩ ኃይል አባላት፣ በሁሉም
ኢትዮጵያዊ ደጀንነት ተሰናብቷል፤
ወታደሮችን በሲኖ ትራክ እስከመጨፍለቅ የዘለቀው የጁንታው የክፋት ጥግ
******************************
(ኢ ፕ ድ)
ሃምሳ አለቃ ደረጀ አንበሳ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ የጥገና ባለሙያ ናቸው። በሙያቸው አገራቸውን ሌት ተቀን ከማገልገላቸውም በላይ እንደማንኛውም የመከላከያ አባል ለትግራይ ህዝብ በችግሩ ጊዜ ከጎኑ በመቆም አጋርነታቸውን ሲገልጹ ኖረዋል። የህዝብና የአገር ከለላና መከታ የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ አባል እንደመሆናቸው አንድም ቀን በአገር ልጅ የባንዳነት ተግባር ይፈጸምብኛል ብለው አስበውም አያውቁም።
ይሁንና በእናት ጡት ነካሾች ጥቅምት 24/2013 ዓ/ም ከምሽቱ አራት ሰዓት ያልታሰበ ጥቃት ተፈጸመባቸውና ያለምንም ጥፋታቸው ተይዘው ለእስር መዳረጋቸውንና ቀላሚኖ እሰርቤት መታሰራቸውን ይገልጻሉ።
"ከቀላሚኖ እስር ቤት ወደ አግቤ በመቀጠልም ከትንሽ ቀን በኋላ ወደ ተንቤን መምህራን ኮሌጅ ወሰዱን። የመከላከያ ሠራዊትን የከባድ መሳሪያ ድምፅ ሲሰሙ የ90 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ አስጀመሩን። ልክ 40 ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ሲኖ ትራክ መኪና ከኋላችን መጣ። ተጓዡ ወደ 1,200 ሰው ነበር። ከአስፋልት እንድንወጣ ካለመፈቀዱም በላይ ከአስፋልቱ መሀል ከወጣን ልዩ ሀይል ተኩሶ ይመታን ነበር። ከግራና ከቀኝ ገደላማ የሆነ ጠባብ ቦታ ላይ ስንደርስ ሲኖ ትራክ መኪና ልከው ከኋላችን ነዱብንና የሚገድለውን እየገደለ፣ ያቆሰለውን እያቆሰለ ሄደብን።
እኔንም አንድ እግሬን አገኘኝና እግሬ ከተሰበረ በኋላ ተንከባልዬ ጉድጒድ ውስጥ ገባሁ። እዚያው ጉድጓዱ ውስጥ ከተጎዱ ጓደኞቼ ጋር ተኝቼ አደርኩ። ሲኖ ትራኩ ቢያንስ እስከ 50 ሜትር የተጓዘው በሰዎች ላይ ነበር። በዚህም ግማሹ ሞተ፣ ግማሹ ቆሰለ የቀረውም ወደገደል ገባ። እንግዲህ የራሳችን ወገን ነው እንዲህ አይነት በደል የፈፀመብን። ይህ ደግሞ በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው። ስንት ዓመት ሙሉ አብረናቸው ኖረን በመኪና ሲጨፈልቁን በጣም ነው የተሰማኝ፤ በጥይት ቢገድሉኝ ይሻል ነበር" ይላል::
በወቅቱ ሴቶችም ህፃናትም አብረውን ነበሩ ማን እንደሞተ ማን እንደተረፈ አንኳን አላውቅም ያለው ወታደሩ "በወቅቱ በሕይወት የተረፋትም ተበታተኑ፤ አንዳንዶቹም ቆስለው ወደጫካው ገቡ፤ የሞቱትም እዛው ቀሩ አምስት የምንሆን ሰዎች እዛው አድረን ከሞቱት ሰዎች መሀል በሕይወት ወጣን። የሞቱ ልጆችን እንኳን ለመለየት አልቻልኩም፤ አጠገቤ ነው እየጮሁ የሞቱት፤ ምንም ልረዳቸው አልቻልኩም። በወቅቱ እኔም በሁለት እግሬ መቆም አልችልም ነበርና በጉልበቴ ዳዴ እያልኩ ነው የወጣሁት" ሲል የውቅቱን አሳዛኝ ሁኔታ ይገልፃል::
"እኛኮ ከሌሊቱ 11 ሰዓት እየተነሳን አጨዳ የምናጭድ፤ ኮረና ገባ ሲባል ብር እያዋጣን የምንደግፍና ከደሞዛችን እየቆረጥን የልማት ስራዎችን የምንሰራ ነን። እኛ ለትግራይ ህዝብ ልማት ወደኋላ ብለን አናውቅም። ይሁንና ጁንታውና የእሱ ተላላኪዎች በሰው ላይ የማይፈፀም ድርጊት ነው የፈፀሙብን። ሰብስበው በቦንብ ቢያቃጥሉን ወይም በጥይት ቢገድሉን ይሻል ነበር። የውጪ ጠላት እንኳን በመኪና ሰውን ደፍጥጦ አይገድልም። ድርጊቱ ከተፈፀመብን በኋላ በመኪና መንገድ ላይ ስንሄድ እየተሸማቀቅን ነው። ጭንቅላታችን ራሱ ተጎድቷል::
ሌላው ተመሳሳይ ድርጊት የተፈፀመበት አምሣ አለቃ ወንድማገኝ ወልደገብርኤል ነው። እሱ እንደሚገልፀው በልዩ ሀይል እና በሚሊሻ ታጅበን በእግር እየተጓዝን ሳለ ከአስፓልቱ እንዳትወጡ አሉን እኛም ፈንጂ ያለ መስሎን የአስፋልቱን መሀል ይዘን መጓዝ ጀመርን። ጨለምለም ሲል ከኋላችን ሲኖትራክ መኪና መጣ፤ ከፊት ለፊት ተኩስ ተከፈተብን፤ እንዳንመታ ብለን ሁላችንም ተኛን፤ በዚህ ወቅት ሲኖ ትራኩ እየጨፈለቀን ሄደ ።
ግማሹ እየተንከባለለ ወደገደል ገባ፤ ተገጭተን የተረፍነው በማግስቱ ተነሳን፤ ብዙዎች ግን በሚያሳዝን ሁኔታሞቱ፤ አንዳንዶቹም ቆሰሉ፤ አሽከርካሪው ለመትረፍ የሚሞክሩ ሰዎችንም ዚግዛግ እየነዳ ነበር ሲጨፈልቃቸው የነበረው። በእግራችን መሄድ አቅቶን ጅብ ይብላን ብለን እዛው ከተኛን በኋላ ታፍነው በመከላከያ ሰራዊት እርዳታ የተለቀቁ እስረኞች እየረዱን የተወሰነ ርቀት ከተጓዝን በኋላ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ደርሰው ወደዚህ አመጡን። ሲሉ ደረሰባቸውን ግፍ አስረድተዋል።
ኢያሱ መሰለ
ታማኙ ሳጅን!
*******************
(ኢ ፕ ድ)
ዋና ሳጅን ታከለ እሸቴ ይባላል። በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር መተማ ዮሀንስ የወንጀል መከላከል ኦፊሰር ነው። በስራው ባህሪ የተነሳ ብዙጊዜ ከወንጀለኞች ጋር ተናንቆ ለህግ ማቅረብ መለያ ባህሪው እንደሆነ ባልደረቦቹ ይናገራሉ። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ በወንጀለኞች ጉዳት ደርሶበታል።
በአንድ ወቅትም በዚሁ የህግ ማስከበር ስራ ላይ እያለ ኮንትሮባንዲስቶችን ለማስቆም በሚያደርገው ጥረት ቦንብ ተወርውሮበት ቆስሎ እንደነበር ነግሮናል።
ዋና ሳጅን ታከለ በተለመደው ስራው ላይ እንዳለ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በመተማ ከተማ ቀበሌ 3 መናኸሪያ አካባቢ ካለ አንድ ሆቴል ጥቆማ ይደርሰዋል፤ “የሆቴሎ እንግዶች የያዙትን ሻንጣ አላስፈትሽም አሉ” የሚል። ጊዜ አላጠፋም ወዲያውኑ ወደሆቴሉ አቀና። በስፍራው የነበሩ እንግዶች የዋና ሳጅኑን መምጣት ሲመለከቱ በባጃጅ ለማምለጥ ሞከሩ። ነገር ግን አልተሳካላቸውም ዋና ሳጅን ታከለ አስቆማቸው።
ግለሰቦቹ ወደህግ ቦታ እንዲሄዱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ሻንጣቸውን እንዲያስፈትሹ ቢታዘዙም በተመሳሳይ ለመተባባር ፈቃደኛ አልሆኑም። ይህን ጊዜ ዋና ሳጅን ታከለ ጥርጣሬው ከፍ አለ። ሰዎቹ ወንጀለኛ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት በመውሰድ ወደ ህግ ቦታ እንዲሄዱ ደጋግሞ ጠየቃቸው። ግለሰቦቹ ግን በቀደመው አቋማቸው በመጽናት እንቢታቸውን አጥብቀው ያዙ።
የዋና ሳጅኑን የከረረ አቋም የተመለከቱት ግለሰቦቹ የያዟቸው ሻንጣ ውስጡ ብር መሆኑን በመንገር እንዲለቃቸውና አንዱን ሻንጣ ብር እሱ እንዲወስደው ጠየቁት። ዋና ሳጅኑ ግለሰቦቹ ያንን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ያገኙት እንዳልሆነ አመነ። ምክንያቱ ደግሞ ማንም ሰው በህጋዊ መንገድ የያዘወን ገንዘብ ለማያውቀው ሰው ሊሰጥ አይችልም፤ ይሄንን ያህል ገንዘብም በአሁኑ ወቅት ከባንክ ውጭ ማንቀሳቀስ አይችልምና ነው።
ስለሆነም ያቀረቡለትን ገንዘብ እንደማይቀበል ይለቁንንም ወደ ህግ እንዲሄዱ በተደጋጋሚ ይጠይቃቸዋል። ግለሰቦቹ ግን አሁንም ሌላ አማራጭ አቀረቡለት። ገንዘቡን በሙሉ ውሰድ እኛን ልቀቀን የሚል። ዋና ሳጅን ታከለ በዚህም ሃሳብ አልተሰማማም። በጭራሽ እንደማይሆን በመንገር ወደህግ እንዲያቀኑ ይጠይቃቸዋል። ግለሰቦቹም በተመሳሳይ በእንቢታቸው ጸኑ። ለማምለጥም የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ጀመሩ።
በዚህ መካከል የሃሳብ ልውውጡ እየከረረ በመሄዱ ግለሰቦቹ ሃይለቃልና ዛቻ መሰንዘርም ጀመሩ። በአጋጣሚ በአካባቢው የሚያልፍ የመከላከያ ሰራዊት የዋና ሳጅንኑንና የግለሰቦቹን ጭቅጭቅ ተመልክቶ ቀርቦ ምን እንደሆነ ጠየቃቸው።
ዋና ሳጅን መልስ ሰጠ። ግለሰቦቹ በወንጀል ስለተጠረጠሩ ወደ ህግ እንዲሄዱ ቢጠየቁም ሊተባበሩ እንዳልቻሉ ለመከላከያ ሰራዊት አባሉ አስረዳው። ይህ የሰራዊት አባልም የዋና ሳጅን ሃሳብን በመደገፍ ግለሰቦቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄዱ ነገራቸው። አማራጭ ስላልነበራቸው የተባሉትን አደረጉ።
“ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰድናቸው፡፡ ሻንጣው ሲፈተሽ እንደተባለውም ውስጡ ገንዘብ ሆኖ ተገኘ። ሲቆጠርም አምስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር መሆኑ ተረጋገጠ። በአከባቢው ይሄን ያህል ብር ይዞ መሄድ የተለመደ አይደለም። ይሁንና በዛን ዕለት ሌሊቱን በአከባቢው የነበረ ባንክ መዘረፉን ስለሰማሁ ለማጣራት ሞከርኩ። በእርግጥም ባንከ መዘረፉ ታወቀ።” ይላል ዋና ሳጅን ታከለ።
“ብሩን እንስጥህ ልቀቀን ባሉኝ ሰዓት እኔ ምንም ስሜቱም አልነበረኝም። ምንም ልቤ አልተቀበለውም ወንጀለኞች ስለሆኑ በህግና በህግ ነው መቀጣት ያለባቸው” የሚለው ዋና ሳጅን፤ በ”ስራ ዘመኔ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ፤ ይህ በጣም ቀላል ነው። ከዚህም በላይ ከባድ ፈተናዎች አልፌያለሁ። ህግን ስታስከበር የሚገጥሙህ ነገሮች ብዙ ናቸው። ከዚህን ቀደም ጉምሩክ ላይ ህገወጥ እቃዎችን ለመያዝ እሰራ በነበረበት ወቅት በጣም ብዙ ነገሮችን ተጋፍጫለሁ። በቦንብ ጥቃት ደርሶብኝ ከሞት አፋፍ ነው የተመለስኩት። ይህንን ሁሉ ስላለፍኩ ተጠርጣሪዎቹ ላቀረቡልኝ የሻንጣ ሙሉ ገንዘብ አልጓጓሁም” ሲል እምነቱን ነግሮናል።
ዋና ሳጅን ታከለ፤ “ማንም ህግ አስከባሪ የዚህ አይነትም ይሁን ሌላ ወንጀል ላይ ተጠርጣሪዎች የሚያቀርቡትን አማላይ የጉቦ ስጦታ መቀበል የለባቸውም፤ ይልቁንም ህዝብና መንግስት የጣለብንን አደራ በሃላፊነት መወጣት ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ነው አገርም ህዝብመ የሚጠቀመው” ሲል መልዕክቱን ለሙያ መሰሎቹ መልዕክቱን አስተላልፏል።
በሀይማኖት ከበደ
“መከላከያ ውስጥ ያየኋት ኢትዮጵያ የሰርጓ ቀን የደረሰ ሙሽራን ትመስላለች፡፡ የሰራዊቱ አባላት ፊታቸው ላይ የሚታየው ስሜት ውጊያ አይደለም የሚመስለው፡፡ ሁሉም ለኢትዮጵያ ሲሉ በወኔና በደስታ ነው የሚዋጉት። በይበልጥ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ተወልደው ያደጉ ልጆች ይህ ስሜት እንዲጋባባቸው እፈልጋለሁ”
ጋዜጠኛ ኑረዲን አወል
የአዲስ ቲቪ ጋዜጠኛ
**********************
(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 80ኛ አመት የምስረታ በአሉን አመቱን ሙሉ በተለያቱ መድረኮች እያከበረ ይገኛል። የበአሉ አካል በማድረግም በህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ ለተሳተፉ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የምስጋና እና የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ መርሀ ግብር ላይም ወደ ግንባር ከተላኩ ጋዜጠኞች መካከል የአዲስ ቲቪው ጋዜጠኛ ኑረዲን አወል የተመለከተውን እንዲህ ተናግሯል።
👉 ከግንባር ከመጣሁ በኋላ ጓደኞቼ ተሰበሰቡ፤ እስኪ ስለአገራችን ስለኢትዮጵያ የገጠመህን ንገረን አሉኝ፡፡ ስለየትኛዋ ኢትዮጵያ፤ መከላከያ ውስጥ ስላለችው ነው? ወይንስ እዚህ ቁርስ ስላልበላን ትፈርሳለች ስለምትባለዋ ኢትዮጵያ ነው ’የምነግራችሁ? አልኳቸው፡፡
👉 መከላከያ ውስጥ ያየኋት ኢትዮጵያ የሰርጓ ቀን የደረሰ ሙሽራን ትመስላለች፡፡ የሰራዊቱ አባላት ፊታቸው ላይ የሚታየው ስሜት ውጊያ አይደለም የሚመስለው፡፡ ሁሉም ለኢትዮጵያ ሲሉ በወኔና በደስታ ነው የሚዋጉት። በይበልጥ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ተወልደው ያደጉ ልጆች ይህ ስሜት እንዲጋባባቸው እፈልጋለሁ፡፡
👉ኢትዮጵያ ስትባል ብዙ ነገር ነች፡፡ ግን ከምንናገረው በላይ በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የሚታየው ኢትዮጵያዊነት ለእኛ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ጥቅም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡
👉 በዚህ አጋጣሚ ለእኔ ትውልድ ለሆኑት ወጣቶች መምከር የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ለእኛ መኖር ትልቅ መስዕዋትነት የሚከፍሉልን የመከላከያ ሰራዊቶች አሉና እነሱን እንዲያመሰግኑልኝ፤ ማመስገን ብቻም ሳይሆን እንደ ግዴታ ሆኖ የትኛውም ወጣት መዝመት አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡
👉 የምንዘምተው ለምንድን ነው አንደኛ ፍቅርን የምናገኘው እዚያ ነው፡፡ ስርዓትን የምናገኘው እዛ ነው፡፡ ለሰው መኖር መቻል እንዳለብን የሚገባን እዚያ ነው፡፡ ከሚበሉት ነገር ቆርሰው እና በሐይላንድ ቁራጭ ከሚጠጡት ሻይ ከፍለው ለእንደእኔ አይነቱ እንግዳ አስቀድመው ይሰጣሉ፡፡
👉 እኔ እንደዛ ነወይ የምኖረው? አይደለም፡፡ እነሱ ግን እንደዚህ መተዛዘን በተሞላበት መንገድ ነው የሚኖሩት፡፡ ያ ነገር ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ ትርፍ የምናተርፍበትና ትልቅ ጥቅም የምናገኝበት ነው፡፡
👉 እኔ በሕይወቴ አሁን ብቻ አይደለም ወደፊትም ይሄን አይነት ትምህርት አገኛለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ኮሮና የገባ ጊዜ ምን እንል ነበር ‹‹ፈጣሪ ሆይ ይችን ኮሮና ያሳልፍልን እንጂ ወደ እምነት ተቋሜ ተመልሼ አንተን አገለግላለሁ›› ብለን ነበር፡፡ አለፈ ፤ እኛም አልሄድንም፤ በነበርንበት እንደቀጠልን እንገኛለን፡፡
👉 ይህ ደግሞ ሁለተኛ የመማሪያ እድል ነው የተሰጠን ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁሌም መጥፎ ነገሮች የምንማራቸው ስለሆኑ የእኔ ትውልድና በእኔ የእድሜ እኩያ የሚገኙ ወጣቶች አሁን ትልቅ ትምህርት የምናገኝበት ጊዜ ነው፡፡ ምንድን ነው ከአጠገባችን ያለ ሰው ጠላታችን ሊሆን ይችላል፡፡
👉እርግጠኞች አንሆንም፡፡ እኔን የማያውቁኝ ሰዎች ስለ እኔ እዚያ ጋ ይሞታሉ፡፡አያውቁኝም እኮ፡፡ እኔ ኑረዲን መኖሬን አያውቁም እኮ፡፡ ነገር ግን እዚያ ጋ ኢትዮጵያዊ የሚባል የሚጎዳ ዜጋ አለና መጎዳት የለበትም ብሎ ለእኔ የሚያስብና ሕይወቱን መስዕዋት የሚያደርግ ብዙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የመከላከያ ሰራዊቶች አሉና እኔ ከመቀመጫዬ ተነስቼ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
👉 ከዚህ በመቀጠል እኛ የነበርንበት አካባቢ ትንሽ መልክዓም ምድሩ ከባድ ነበር፡፡ መልክዓም ምድሩን ሳይ ለምን መጣሁ አልኩኝ፡፡ከዚያ በኅላ ግን ወታደሩ ፊት ላይ የሚታዬው ስሜት፣ፍቅር ጥልቅ ነው፡፡ አሁን እኔ ያንን በቃል ልግለጸው ብል ማርከስ ነው የሚሆንብኝ፡፡በቃል ባወራው ማሳነስ ነው የሚሆንብኝ፡፡
👉 ማውራት ያለብን ስለግለሰብ ጀብድ አይደለም ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄን ታሪክ የሰራው ሙሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው፡፡የዚያ ታሪክ ተጋሪ በመሆኔ እድለኛ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ያንን አስቸጋሪ መልክዓ ምድር በመኪና ነው የወጣሁት፡፡ ነገር ግን ሴት የመከላከያ ሰራዊት በእግራቸው የሚተኩሱትን መሳሪያ ተሸክመው ሲወጡት ሳይ ለእኔ ብለው መሆኑን አይቼ አዘንኩ፡፡
👉 እኔ ለዚህች ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር ምንድን ነው ያደረኩላት? እኛ እንጠይቅ ነበር፡፡ ደመወዝ ተጨመረልን ወይ ብለን፡፡ ቤት መንግስት ይሰጠን ይሆን ወይ ብለን፡፡ እዚያ ጋ ግን ደመወዝ የማይጠይቅ፣ ቤት ይሰጠኝ ይሆን ብሎ የማያስብ፣ ከፊት ለፊቱ ሞትን እያዬ ለአገሩ ክብር የሚገሰግሰውን የመከላከያ ሰራዊት አይቻለሁና ደስ ብሎኛል፡፡ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
👉 ከመደሰትም በላይ በእኔ ዙሪያ ያሉ ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡እነዚያ ወጣቶች ብዙ ሊማሩበት ይገባል፡፡ ይሄን የምለው ለፕሮፖጋንዳ ትርፍ አይደለም፡፡ በሕይወት የኖርንባት እያንዳንዷ ቀን ትልቅ ትርጉም እንዲኖራ ከፈለግን ኢትዮጵያን እንወቃት፡፡ ለማወቅ ከፈለግን ደግሞ አገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንግባ እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
“እናትና አባትህ ይክዱኛል ብለህ የማትጠብቅበት አይነት ሁኔታ ውስጥ በሰራዊቱ ላይ ክህደት ተፈጽሟል። ቤታችን ነው ሰላም ነው ባልንበት ቦታ በተደራጀ ሃይል አፈና ተካሂዶብናል”
👉 የጁንታው አመራሮች በቅርበት ይከታተሉን ስለነበር የአየር ሀይላችን እነርሱን ነጥሎ ጠባብ መንገድ ላይ በአየር ድብደባ ተሸከርካሪዎቻቸውን አቃጥሏል፤
👉 የጁንታው አመራሮች ወደኋላ ሲመለሱ ደግሞ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመምታት መንገዱ እንዲዘጋባቸው አድርጓል፤
👉 የጁንታው አመራሮች መሄጃ በማጣታቸው የነበራቸውን ተሽከረካሪዎች እና ንብረት እየጣሉና እያንጠባጠቡ ሲበታተኑ መከላከያ ሰራዊታችን ደርሶ አብረውኝ የነበሩትን ሁሉ ነጻ አውጥቷል፤
👉 ሰራዊቱ የታፈኑትን ነጻ ሲያወጣ ጠላትና ወገንን የለየ ምርጥ ኦፕሬሽን አከናውኗል፤
ብርጋዴር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ
የሰሜን ዕዝ ምክትል ኦፕሬሽን አዛዥ
******************************
(ኢ ፕ ድ)
ሽሬ:- መከላከያ ሰራዊት በጁንታው ታጣቂዎች አማካኝነት የታፈኑትን የሰራዊቱ አመራርና አባላትን ነጻ ሲያወጣ ጠላትና ወገንን የለየ ምርጥ ኦፕሬሽን አከናውኗል ሲሉ ከታጋቾቹ መካከል አንዱ የነበሩት የሰሜን ዕዝ ምክትል ኦፕሬሽን አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ተናገሩ።
የሰሜን ዕዝ ምክትል ኦፕሬሽን አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ እንደገለጹት፤ መከላከያ ሰራዊቱ ታጋቾችን እና የጁንታውን ታጣቂ ለመለየት የተጠቀመው እርምጃ የሚደነቅ ነው። የሰራዊቱ አመራርና አባላትን በማይጎዳ መልኩ ጥንቃቄ የተሞላበት ኦፕሬሽን በተሳካ ሁኔታ ፈጽሟል።
"መከላከያ ሰራዊታችን እኛ የታፈንነውን አመራርና አባላት ላይ አደጋ እንዳይደርስ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ እርምጃ ወስዷል። በተለይ የጁንታው አመራሮች በቅርበት ይከታተሉን ስለነበር እነርሱን በሚነጥል ሁኔታ በአየር ከፊት ጠባብ መንገድ ላይ ተሸከርካሪዎቻቸውን አቃጥሏል።
መከላከያ ሰራዊቱ የጁንታው አመራሮች ወደኋላ ሊመለሱ ሲሄዱ ከኋላ ተሸከርካሪዎቻቸውም በመምታት መንገዱ እንዲዘጋባቸው አድርጓል። በዚህ ወቅት የጁንታው አመራሮች መሄጃ በማጣታቸው የነበራቸውን ተሽከረካሪዎች እና ንብረት እየጣሉና እያንጠባጠቡ ሲበታተኑ መከላከያ ሰራዊታችን ደርሶ አብረውኝ የነበሩትን ሁሉ ታጋቾችን ነጻ አውጥቷል" በማለት የሰራዊቱን እርምጃ አወድሰዋል።
ሰራዊቱ የታፈኑትን ነጻ ሲያወጣ ጠላትና ወገንን የለየ ምርጥ ኦፕሬሽን አከናውኗል ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል አዳምነህ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ደስተኛ የሆነበት እና ጥሩ ስራ የተከናወነበት ነው በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። <<መከላከያ ሰራዊታችንን በግሌም ሆነ አብረውኝ በነበሩ አመራሮች ስም ላመሰግን እወዳለሁ። በመከላከያ ሰራዊታችን ኮርተንበታል>> ብለዋል።
በአፈናው ወቅት ስለነበረው ሁናቴ ሲያስረዱም “ስሜቱን መግለጽ ያጥረኛል። እናትና አባትህ ይክዱኛል ብለህ በማትጠብቅበት ሰዓት በሰራዊቱ ላይ ክህደት ተፈጽሟል። ቤታችን ነው ሰላም ነው ባልንበት ቦታ በተደራጀ ሃይል አፈና ተካሂዶብናል” ነው ያሉት።
የአፈናው ጊዜ በሙሉ በርካታ ውጣ ውረዶች ያሉት ነው፤ ረጅም የእግር ጉዞዎች በቀንም በሌሊትም ያለዕረፍት ነበረው። ዞሮ ዞሮ ህይወታችንን ካተረፉን የመከላከያ ሰራዊት ወንድሞቻችን ጋር ሆነን ታሪኩን በጽሁፍ በሰፊው የምናቀርበው ይሆናል በማለት ሁኔታውን በአጭሩ አስረድተዋል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በጁንታው ቡድን ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው የታፈኑት የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አመራሮች ሽሬ ከተማ ሲደርሱ በሰራዊቱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በርካታ የሰራዊቱ አባላት ታፍነው የሰነበቱ አመራሮቹን እና ጓደኞቻቸውን ሲያገኙም ወደሰማይ በተተኮሰ የጥይት ድምጽ እና በጭፈራ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ህዳር 30 ቀን ከሰዓት በኋላ የጁንታው ቡድን አጋቾች አዴት በተባለ አካባቢ በእግር ሲያጓጉዟቸው የነበሩትን ከ1ሺህ በላይ የሰራዊቱን መኮንኖች በመልቀቅ በየአቅጣጫው መበታተኑ ታውቋል። ታፍነው የሰነበቱ የሰራዊቱ አመራሮች መንግስት ላደረገው የህይወት አድን ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም