Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
889 ተጨማሪ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ 12 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል
*******************
(ኢ.ፕ.ድ)

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 8 ሺህ 115 የላቦራቶሪ ምርመራ 889 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 320 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 28 ሺህ 634 ሆኗል።

ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉ መረጋገጡን ተከትሎ በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 108 ደርሷል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 69 ሺህ 709 ደርሷል።
የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖቹ አዲሱን የብር ኖት እንዲያነቡ መደረጋቸውን ንግድ ባንክ አስታወቀ
*****************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- ነባሩን የብር ኖት ሲያነቡ የነበሩ የኤቲኤም ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንዲያስችላቸው የሚያደርግ ስራ መሰራቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ገለጹ። አዲሱ የብር ኖት በየቅርንጫፎቹ በመዳረስ ላይ እንደሆነም ተናገሩ።

ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ አቶ የአብስራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አዲሱን የብር ኖት መለወጥ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ደንበኞች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመምጣት እየለወጡ ይገኛሉ።አዲሱን የብር ኖት የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች ማንበብ እንዲችሉ ማድረግ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስራ በመሆኑ ነባሩን የብር ኖት ሲያነቡ የነበሩ ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንዲችሉ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ባሉት ኤ.ቲኤ.ም ማሽኖች አዲሱን ኖት መክፈል ተጀምሯል።እንደዚያም ሆኖ ነባሩን የብር ኖት መክፈል ባለማቆማችን ስራውን ጎን ለጎን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

እንደ አቶ የአብስራ ገለጻ፤ ደንበኞች ነባሩን የብር ኖት በመመለስ ላይ ሲሆኑ፣ በተለይ ከአምስት ሺህ ብር በላይ ከሆነ አዲስ ሒሳብ ከፍተው እያስቀመጡ ይገኛሉ።የብር ኖቱ ለውጥ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አዲስ አበባ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ብቻ ባሉት 320 ቅርንጫፎች ላይ አዲሱ የብር ኖት እንዲዳረስ ተደርጓል።ከዚህ ባሻገር ደግሞ በተመረጡ ስድስት የክልል ከተሞች ላይ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በትብብር አዲሱን ኖት የማድረስና የማሰራጨት ስራ ተጀምሯል።

የገንዘብ ኖቱ በበርካታ ቦታ ማለትም ገንዘብ የሚከፋፈልባቸው ቦታዎች ደርሷል ያሉት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ፣ ለአብነትም ጅግጂጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ አዳማና ሌሎችም ከተሞች ላይ በመዳረስ ላይ ይገኛል ብለዋል።በተጨማሪም ሌሎች ገጠራማ የሆኑ ስፍራዎችም በመጓጓዝ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።

በባንክ ደረጃ በችግር ያየናቸው ነገሮች እስካሁን የለም ሲሉ ጠቅሰው፤ ህዝቡ ደስተኛ ሆኖ እየለወጠ መሆኑን አስረድተዋል።ጊዜው አጭር ስለሆነ ደንበኞች ሳይዘናጉ እየመጡ እንዲለውጡም አበረታትተዋል። በኋላ ላይ ሩጫ ሳይፈጠርና ጊዜው ሳይጨናነቅ ቢለውጡ መልካም መሆኑንም ጠቅሰው እሁድንም ጨምረው በመስራት ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

እርሳቸው ደንበኞች ገንዘብ በኪስ ይዘው እንዳይሄዱ አበረታትተው፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ሲቢኤ ብር፣ ኤቲኤምና መሰል ቴክኖሎጂዎችን ህዝቡ ቢጠቀም የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል።በካርድ ግብይት መፈጸሚያ ማሽኖችንም መጠቀምን የሚደግፍ አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲሱ ብር ኖት ጠቀሜታው በርካታ ነው ያሉት አቶ የአብስራ፣ በተለይም ሀሰተኛ የብር ኖቶችን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።በተጨማሪም የዋጋ ግሽበትን የሚከላከል ሲሆን፣ ለአገሪቱም ጤናማ ኢኮኖሚ መሰረት ነው በማለት ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2013
አስቴር ኤልያስ
ምክር ቤቱ 6ኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰነ
*****************************
(ኢ ፕ ድ)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደው ባለው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛው አስቸኳይ ስብሰባው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰነ።
ምርጫው የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ ሀሳብ መሠረት ቫይረሱን በመከላከል ምርጫውን ማከናወን እንደሚቻል የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ የውሳኔ ሃሳብ እና ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የውሰኔ ሃሳቡም የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 16/2013 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ በ8 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ምክር ቤቱ መስከረም 8/2013 ባካሄድው 5ኛ ዙር 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥና ቀጣይ እርምጃዎች የቀረበውን ሪፖርትና ምክር ሃሳብ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል፡፡
በድሬዳዋ በበጀት ዓመቱ ከ23 ሺ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል
********************
(ኢፕድ)

የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከድሬዳዋ አስተዳደር እና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው፡፡

የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በድሬዳዋ የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በድሬዳዋ ዛሬ ባካሄደዉ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ በከተማ አስተዳደሩ በ2013 በጀት አመት ከ23 ሺ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ዘንድሮ ወደ ድሬ ዳዋ ኢንዲስቲሪ ፓርክ የሚገቡ የተለያዩ ኩባንያዎች በመኖራቸው እስከ 10ሺ ለሚሆኑ ዜጎች በቀጥታ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ሲሆን እንዲሁም ለኩባኒያዎቹ የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ እና አገልግሎቶችን የሚሰጡ ለተለያዩ የስራ መስኮችንም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራል ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኑጉሱ ጥላሁን በድሬዳዋ የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አደረጃጀቱን የማሻሻል ስራ በማከናወን በተሻለ የስራ ዕድል ፈጠራ የማመቻቸቱን ስራ ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋለ፡፡

በመድረኩ ላይ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የንግድ፣ ኢንደስቲሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ከዲር ጁሃር እንዲሁም በአስተዳደሩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በመተከል ዞን ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 13 ተጠርጣሪዎች እና 8 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 13 ተጠርጣሪዎችና 8 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል፡፡

በዞኑ ቡለን ወረዳ በቅርቡ የጸጥታ ችግር በተከሰተበት ኤጳር ቀበሌ በደረሰው ጉዳት ቀጥታ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበሩ የተባሉ 5 ተጠርጣሪዎች ከ1 ጂምስሪ እና 5 ክላሽ በድምሩ 6 የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ አመራሩ በሠራው የህዝብ ግንኙነት ሥራ በቀበሌ በደረሰው ጉዳት ቀጥታ ተሳትፎ የነበራቸው 5 ሽፍታዎች ከ2 ክላሽ የጦር ማሳሪያዎች ጋር የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ ርብርብ እና የተኩስ ልውውጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አበራ አስታውቀዋል፡፡

በመተከል ዞን ሁሉም አካባቢዎች የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በዞኑ እየተፈጠሩ ከሚገኙ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ በዳንጉር ወረዳ 2 በጉባ ወረዳ ደግሞ 1 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታዬ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አመራሩ፣ የፌዴራልና የክልሉ ጸጥታ አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ እየተሠሩት ያለውን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው አቶ አበራ የተናገሩት፡፡

በዞኑ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እየተሠራ ባለው የሕግ የበላይነት ማስከበር ሥራ ከዚህ ቀደም 358 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል ሲል የዘገበው የክልሉ የመንግስት ኮምንኬሽን ቢሮ ነው።
በሀገሪቱ የተከሰቱ ሁከቶችና ግጭቶች ከሙስና ወንጀል ጋር እንደሚያያዙ ኮሚሽኑ ገለጸ
*************************
(ኢፕድ)
አዳማ:- ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች እየደረሱ ያሉት ሁከቶች እና ግጭቶች ኢንዲሁም ከዚህ የመነጨው የዜጎች መፈናቀል ከሙስና ወንጀል ጋር የተያያዘ መሆኑን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ የ10 ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ፣ የ2013 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድና የስነ ምግባር መከታተያ መመሪያ ዙሪያ ሲሰጥ በቆየውና ዛሬ በሚጠናቀቀው ስልጠና ላይ የሥራ መመሪያ የሰጡት በኮሚሽኑ የክልል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መለስ ተገኝ፤ ሙስና አሁን በዓለም ደረጃ እጅግ አሳሳቢ የሆነ፣ የአደጉ አገራትንም የፈተነ፣ በተለይም የአረብ አገራትን እስከማፈራረስ የደረሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአረብ አገር ህዝቦች በአገራቸው መኖር ያልቻሉበትና ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ የተገደዱት ከዚሁ ችግር በመነጨ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች እንደመሆኗ አደጋው ቢከሰትባት እጅግ በጣም አስከፊ እንደሚሆን አመልክተዋል።

‹‹በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች በዛች አገር ሆነው የዘረፉትን ገንዘብ እየበሉ መኖር የሚችሉት አገር ሲበጠበጥና ሰላም ሲጠፋ ነው›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሰላም ከሰፈነ፣ አንድነት ከተፈጠረ እንደሚጠየቁ ያውቃሉ ብለዋል።

ዳይሬክተሩ በአገሪቱ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉት ሁከትና ግጭቶች በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች አጀንዳ መሆኑን ማሰብ ብልህነት ይሆናል ብለዋል፡፡

እንቅስቃሴው እውነት ለዘራቸው፣ ለብሄራቸው ወይም ለሃይማኖታቸው ተቆርቁረው አይደለም ያሉት አቶ መለስ፤ በሙስና የተዘፈቁ ዜጎችን ጠያቂ ህብረተሰብ እንዳይፈጠር አጀንዳ ለመቀየር እየተደረገ ያለ ጥረት አካል እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው ግጭትና ሁከት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ውስብስብ የሆነ፣ እጅግ በጣም በረቀቀ እና በቡድን የተሳሰረ መልኩ የሚከናወንን ሙስና ተበታትኖ መታገል እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል የተደረጉ ጥረቶች መልካም እንደነበሩ፣ ካለው የችግሩ ግዝፈት አንጻር በተሻለና ወጥነት ባለው አገራዊ መልክ በያዘ የእቅድ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ በመደጋገፍ ለመስራት ዕቅዱ ጸድቆ ወደ ትግበራ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል፡፡

ዕቅዱ ቀድሞ ከተከናወነው የላቀ በመተግበር፣ ያለውን የገዘፈ ችግር ያገናዘበና ወጥ የሆነ ትግል ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ያመለከቱት አቶ መለስ፤ ትግሉን የሚያንቀሳቅሱ በሁሉም የእርከን ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች እርስ በርስ በመናበብ፣ የተቀናጀና የተናበበ ተግባር በማከናወን ስኬታማ ተግባር ለማከናወን እንደሚያስችል አመልክተዋል።

በኮሚሽኑ የስልጠናና ጥናት ምርምር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ በበኩላቸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የጸረ ሙስና ትግሉ በተለያዩ ተቋማት የሚካሄድ በመሆኑ የሙስና ወንጀሎችን ለመታገል አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል። የሙስና ተጋላጭነትም እየጨመረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በተቋማት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭነት መበራከትም ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት መሆኑንም ያመለከቱት አቶ ተስፋዬ፣ የጸረ ሙስና ትግሉ በቴክኖሎጂ አለመደገፉ እና በተቋማት ውስጥ በሚፈጸሙ ኢ-ስነ ምግባራዊ ድርጊቶች ምክንያት በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ሮሮዎችና ቅሬታዎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል። ለተማሪዎች የስነ ምግባር ብልሽት መንስኤ የሚሆኑ በአቋራጭ የመበልጸግ ፍላጎት መጨመርንም እንደተግዳሮት አንስተዋል።

እቅዱ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የመከላከል አቅምን የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተው፤ የአገሪቱን የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የመከላከል ደረጃ እንደሚያሳድግ፣ በሙስና መከላከል ላይ የኮሚሽኑና የአገሪቱ ገጽታ ለመገንባት አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ጠንካራና ኃላፊነቱን በብቃት መፈጸም የሚችል ተቋም መገንባት፣ የተቋማትን የስነ ምግባር መከታተያ ክፍሎችን የመፈጸም አቅም ማሳደግ፣ በሀገሪቱ ሙስናና በብልሹ አሰራሮችን የመከላከል አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ፣ ተማሪዎች በመልካም ሽነ ምግባር ታንጸው ሙስና እንዲጠየፉ ማድረግ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተቋማት የሙስና ተጋላጭነት እንዲቀንስ በማድረግ በአፍሪካ ሙስናን በመከላከል ግንባር ቀደም ሆኖ መገኘት ከእቅዱ የሚጠበቁ ውጤቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

አገራዊ የስነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ስትራቴጂያዊ እቅዱ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ለ10 ዓመታት የሚተገበር ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 13/201
በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች ላይ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙ ተገለጸ
********************
(ኢ ፕ ድ)

በ2012 በጀመት ዓመት በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች ላይ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል መፈጨሙን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ ላይ እንደገለጹት፤ ኩባንያው በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓትን በመዘርጋት ቀደም ሲል የነበሩትን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ስርቆቶችንና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎችን መቀነስ ችሏል፡፡

እንደ ዋና ስራ አሰፈጻሚዋ ገለጻ፤ አሁንም ቢሆን ህገ ወጦች በደንበኞች በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ተጠቅመው የሚፈጸሙት የወንጀል ደርጊቶችና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች ከጊዜው ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት አመትም በ130 ሺህ የኩባንያው ደንበኞች የመስመር ስልክ ላይ የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል።

ደንበኞቹ በተለያዩ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፍበት ወቅት ወዲያወኑ ባለማዘጋታቸው፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅም የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠት የተነሳ ወንጀለኞች የስልክ መስመሩን ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች እየተጠቀሙበት መሆኑን ወ/ሪት ፍሬህይወት አስታውቀዋል።

በተጠቀሰው የማጭበርበር ወንጀል የተነሳ ደንበኞች ለአንግልትና ለወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት እየተዳረጉ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ኩባንያውም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቀዋል።

የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል መከላከል እንዲቻል ደንበኞች በተለያየ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋበት ወቅት በአቅሪያባቸው በሚገኙ የሽያጭ ማዕከላት በመቅረብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸው ያሉት ዋና ስራ አሰፈጻሚዋ፤ የስልክ መስመራቸውን በማዘጋትም ምትክ ሲም ካርድ መውስድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ደንበኞች የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ባለመስጠትና ለወንጀለኞች ተባባሪ ባለመሆን በስልክ መስመራቸው አማካኝነት ከሚፈጸም ወንጀል እንዲጠነቀቁም አሳስበዋል፡፡
በወንድማገኝ አሸብር
የትምህርት ቤቶች ትምህርት ማስጀመር ሂደት በሶስት ዙር እንደሚከናወን ተገለጸ
************************
(ኢ.ፕ.ድ)
የትምህርት ቤቶች ትምህርት ማስጀመር ሂደት በሶስት ዙር እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ማለትም ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ደግሞ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ነው ምክረ ሃሳብ የቀረበው።
በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው ውይይት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ የሚደረገው ውይይት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የ8ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ብሔራዊ ፈተና መውሰጃ ቀናት ይፋ ሆነ
******************
(ኢ.ፕ.ድ)
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተደረገ ባለው ውይይት ላይ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ገለፃ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም በምክረ ሀሳቡ ላይ ተጠቅሷል።
የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
የግል ትምህርት ቤቶች የምዝገባ ክፍያ በ2012 ዓ.ም በነበረው መጠንና የክፍያ ስርዓት መሆን እንዳለበትም ተገልጿል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የትምህርት ቤቶች የክፍያ ስርዓት በባንክ በኩል ብቻ መፈጸም እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
እነ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 18 ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዘዘ
*************
(ኢ.ፕ.ድ)

ፍርድ ቤቱ እነ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 18 ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ አዘዘ።

በጥበቃ በኩል ስጋት ካለ እንደሚከታተልም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱ በችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾች እንዲቀርቡ ትዛዝ ሰቷል።

በችሎት ያልቀረቡት ተከሳሾች ባሉበት ክስ ለማንበብ መስከረም 21 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኤፍቢሲ ዘግቧል።
በቀጣይ 10 ዓመታት የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ 82 ለማድረስ ታቅዷል
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

በቀጣይ 10 ዓመታት የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ ተደራሽነትን 82 ለማድረስ መታቀዱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የ10 ዓመት መሪ እቅድ እንዲሁም በሰላም ግንባታ የሚዲያ ሚና ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተቋሙን የ10 ዓመት መሪ እቅድ ያቀረቡት የተቋሙ አማካሪ አቶ ግዛው ተስፋዬ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት 60 የሀገሪቱ ቋንቋዎች የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ 10 ዓመታት ሁሉም የሀገሪቱ ቋንቋዎች የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ እንዲሆን ይሰራል።

በውይይት መድረኩ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሚስተዋሉ ጥንካሬዎች፣ ዕጥረቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና፣ ስጋቶችና አስቻይ ሁኔታዎች ተዳሰዋል።

በውይይት መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ቦርድ አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት እንዲሁም የፌዴራል የዲሞክራሲ ተቋማት የበላይ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በመላኩ ኤሮሴ
ለመስቀል ደመራ በዓል ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን ፖሊስ ይፋ አደረገ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሰከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የሚከበረው የደመራ በዓል ተጀምሮ አስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪዎች ዝግየሚደረጉ መንገዶችን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት፦
.ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ
.ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያ አካባቢ
.ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት
.ከቸርችል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አገር አስተዳደር መብራት ወይም ኢሚግሬሽን መ/ቤት አካባቢ
.ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ
.ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ
.ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ
.ከሳሪስ በጎተራ የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ
.ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ
.ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ፣ ሜክሲኮ ፣ ለገሀር መብራት የሚወስደውመንገድ ለገሃር መብራት አካባቢ ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ ሲሆን፣ ደመራው የሚደመርበት መስቀል አደባባይ እና ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ስታዲዬም እንዲሁም ከሃራምቤ ሆቴል ወደ ሴንጅ ዮሰፍ የሚያቋርጠው መስቀለኛ መንገድ ለበዓሉ በሚደረገው ዝግጅት ምክንያት ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ዝግ የሚደረግ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪውን አስተላልፏል፡
12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እና ምዝገባ በኦንላይን እንደሚካሄድ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
************************
(ኢ ፕ ድ)
ከኮቪድ ወረርሽን ጋር በተያያዘ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እና ምዝገባ በኦንላይን እንደሚካሄድ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቋል።

ተማሪዎች ለፈተና ከመቀመጣቸው በፊትም የ45 ቀን የማካካሻ እና የቴክኖሎጂ መለማመጃ ጊዜም እንደሚሰጣቸው በትምህርት ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት እና ፈተናም የሚሰጠው ትምህርት ቤቶች የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማሟላት ሲችሉ ብቻ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ መቅረቡን አስታውቋል።
አርቲስት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ) ከዚህ አለም በሞት ተለየች።
********************
(ኢ ፕ ድ)
በበርካታ የትያትርና ፊልም ስራዎች የምትታወቀው አርቲስት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ) ከዚህ አለም በሞት ተለየች።
ለሳምንታት በህመም ላይ የነበረችው አርቲስቷ ዛሬ ማለዳ ነው ማረፏ የተሰማው።
የአርቲስቷ ስርዓተ ቀብር ነገ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈፀማል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ አርቲስቷ ከ40 ዓመት በላይ በኪነ ጥበቡ ዓለም በመቆየት በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አበርክታለች።
በለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 7,227 የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ 486 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 72,173 ደርሷል።

በሌላ በኩል 402 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ስሆን በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ 29,863 ሰዎች ከበሽታው ማገገም ችለዋል።
“በህገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ ነው“ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር
******************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ:- በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ በመጎዳቱ ምክንያት በህገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳሰበ።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ክፉኛ ኢኮኖሚዋ ተጎድቷል።
በርካታ ሰዎች በቫይረሱ በመያዛቸውም የስራ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋል። ሀገሪቷ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ደግሞ ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ቢያስቡ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የከፋ ችግር ያጋጥማቸዋልና ባይሞክሩት ይበጃል።
እንደ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ከሆነ፤ በደቡብ አፍሪካ ያለው የኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ የውጭ ሀገራት ዜጎች የነዋሪውን ስራ እየተሻሙ ነው የሚል ቅሬታ በየጊዜው መቅረብ ጀምሯል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲደርስ ቆይቷል። መጤ ጠል አስተሳሰብ እየተስፋፋ በመሆኑ በህገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት የሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አደጋ ላይ ከመጣል ሊጠነቁቁ ይገባል።
በ2012 ዓም ሁለት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ደቡብ አፍሪካን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን፤ ቀድሞ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ብቻ እያሉ የነበረው የስራ አማራጭ አሁን ላይ እምብዛም በመሆኑ በህገወጥ መንገድ ወደሀገሪቷ መግባት ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ የከፋ አደጋን ያስከትላል።
የመንግሥት ለመንግሥት የሚደረጉ ስምምነቶች እስኪከናወኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሀገወጥ መንገድ መሄድ አደጋው የበዛ እንደሚሆን የገለጹት ዶክተር ሸፈራው፤ በህገወጥ መንገድ በእግር እና በተሽከርካሪ ሀገራትን እያቋረጡ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ማሰብ ግን ህይወትን መጥላት እና ቤተሰብንም ለሰቀቀን የሚዳርግ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ በኩል አቋርጠው ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሉ በቅረቡ ህይወታቸውን ያጡ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን ዶክተር ሽፈራው አስታውሰው፤ በህገወጥ መንገድ የሚጓዙ ዜጎችም አብዛኛዎቹ ተይዘው በእስር ቤት እንደሚያሳልፉ እና ወደኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ገልጸዋል። በቅርቡ እንኳን ከታንዛኒያ እስር ቤት የነበሩ ከሁለት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከብዙ መከራ በኋላ ወደሀገራቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል።
በየመንገዱ ያሉ ህገወጥ ደላሎች የሚያደርሱትን መከራ አልፈው በህይወት እና በሞት መካከል ሆነው ደቡብ አፍሪካ የሚደርሱ ጥቂት ኢትዮጵያውያንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስራ ለማግኘት ከባድ ፈተና እየገጠማቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ በኩል በጣምራ ሀገወጥ የሰዎችን ዝውውር ሊቀንስ የሚችል የአሰሪና ሰራተኛ ስምምነት ለማድረግ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፤ ስምምነቱ ሲከናወን ኢትዮጵያውያን በህጋዊ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው የሚሰሩበት መንገድ በቀጣይ እንደሚመቻች አስረድተዋል። ማንኛውም ሰርቶ መለወጥ የሚችል ሰው ህገወጥ ስደት ከመምረጡ በፊት ሀገሩ ላይ በሚመረጠው ዘርፍ ለመስራት ማሰብ እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በአካባቢው የሚገኙ ስድስት ሀገራት ማለትም ናሚቢያ ፣ ቦትስዋና፣ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር፣ ስዋቲኒ እና ሌሴቶ ላይ ስራውን እያከናወነ ይገኛል። በደቡብ አፍሪካ ብቻ ሁለት መቶ ሺህ ኢትዮጵያወያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2013
ከመስከረም 25 በኋላ “ህጋዊ መንግስት የለም” በሚል ትርምስ ለመፍጠር የሚጥሩ ሃይሎችን እንደማይታገስ ፖሊስ አስጠነቀቀ
*************************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ ፦ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከመስከረም 25 በኋላ “ህጋዊ መንግስት የለም” በሚል አገራዊ ትርምስ ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ገለጸ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው የመስቀል እና የኢሬቻ በዓል ቅድመ ዝግጅትን እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከመስከረም 25 በኋላ “መንግስት የለም” በሚል አገራዊ ትርምስ ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ ፖሊስ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል።
‹‹ከመስከረም 25 በኋላ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች›› የሚሉ ጥሪዎች በማህበራዊ ገጾች እየተላለፉ መሆኑን አመልክተው ፣ የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በአመጽ ጥሪው በሚሳተፉ አካላት ላይ ፖሊስና የፀጥታ አካሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል፡፡
ህዝቡን ለአመፅ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ መልዕክቶችን በስፋት የሚያሰራጩ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ ፣ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል ህገ መንግስቱን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብእንደሚኖርበት የጠቆሙት ኮሚሽነር ጀነራሉ ፣ ከሰላማዊ እንቅስቃሴ ውጪ ያሉ ተግባራትን ለማምከን ፖሊስ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
አያይዘውም ፖሊስ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ያስታወቁት ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ፣ የበዓሉን እንቅስቃሴ ለማደፍረስ ዕቅድ ያላቸው ሃይሎች እንዳሉ ፖሊስ በምርመራ የደረሰበት መሆኑን ጠቁመዋል። የበዓሉ አከባበር ወግና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጭ በዓሉን ለመረበሽ የሚፈልጉ ኃይሎች መለየታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በዓላቱ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እንዴት መከበር እንዳለበት አስቀድሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያት ከስምምነት መደረሱን ገልፀው፣ በበዓሉ ለመታደም የሚመጡ ምዕምናንና እንግዶች የይለፍ ባጅ ማድርጋቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ይህን ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም አካል ላይ ፖሊስ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳሰቡት ኮሚሽነር ጀነራሉ፣ ተመሳሳይ የይለፍ ባጅ አሰርተው ለመግባት የሚሞክሩ አካላት መለየት የሚያስችል አሰራር መኖሩን አስታውቀዋል። ተመሳሳይ ባጅ ይዞ የሚገኝ አካል በአገሪቱ የወንጀል መቅጫ ህጎች መሰረት ለህግ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡
በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ መግቢያ በሮች በሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ ቡራዩ፣ ገላንና ሰበታ ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚከበረው የመስቀል በዓል የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን ያስታወቁት ኮሚሽነር ጀነራሉ፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚከበረው የመስቀል በዓል የፀጥታ ሃይሉ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በዓላቱን ተገን አድርገው ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠርም ሆነ ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ፖሊስ እንደማይታገስም አሳስበዋል።
የመስቀልም ሆነ የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎች ቁጥራቸው ውስን እንዲሆን የተደረገው ከፀጥታ ሥጋት ጋር ሳይሆን ከኮቪድ-19 መከላከል ጋር ተያይዞ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2013