Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የትምህርት ቤቶች የፈረቃ ስርአት እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ2 እስከ 3 ሊሆን እንደሚችል ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ
************************
(ኢ ፕ ድ)
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለ 7 ወራት የተቋረጠውን መደበኛ ትምህርት ለማስቀጠል ትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ፡፡
መንግስት በትምህርት ቤቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የውሃ እና የእጅ ማፅጃ አቅርቦቶችን በማሟላት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን የማፅዳት ስራዎችን በማከናወን መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ተማሪዎች እንደየ ደረጃው ወደ ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የገለፁ ሲሆን ትምህርት ሲጀመርም በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚጀመር መሆኑን እና በቀጣይም ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ወደ መደበኛ ትምህርቱ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡ ጥንቃቄዎች ሙሉ በሙሉ የሚተገበሩ መሆኑን እና የትምህርት አሰጣጡ ሂደትም በፈረቃ የሚሰጥ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የፈረቃ ስርዕቱም እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ 2 እስከ 3 ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በትምህርት ቤት ውስጥ መምህራኖች ትልቁን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
መደበኛ ትምህርቱም መንግስት ውሳኔ እንዳሳለፈ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ሁለት የመዝናኛ ከተማዎችን ልትገነባ ነው
*********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡ - ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ የመሆን ግቧ አካል የሆኑ ሁለት የመዝናኛ (ሪዞርት) ከተማዎችን ልትገነባ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የቱሪዝም እቅድ ዘርፍ መሪ አቶ አህመድ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ከመዝናኛ ከተሞቹ አንዱ የሚገነባው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ 70 ገደማ ሰው ሰራሽ ደሴቶች ይኖራሉ። ግድቡ ሲጠናቀቅም በሀገሪቱ ዋነኛው የቱሪስት መዳረሻ ይሆናል።
ሁለተኛው የመዝናኛ ከተማ የሚገነባበት ቦታ የአዋጪነት ጥናት ከተካሄደ በኋላ ይወሰናል ያሉት አቶ አህመድ፤ የመዝናኛ ከተማ ግንባታ የሚከናወነው የግሉ ሴክተርን ጨምሮ በብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሪዞርቶችን በግል ባለሀብቶች እንደሚገነባ የተናገሩት አቶ አህመድ፤ የመዝናኛ ከተማዎቹ ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ከፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
እንደ አቶ አህመድ መሐመድ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በ2022 ኢትዮጵያን የቱሪስቶችን ቁጥር 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ የያዘች ሲሆን ፣ ከቱሪዝም ዘርፍ ብቻ የሚገኘውን ገቢ 23 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ አቅዳለች።
በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ በነባር 40 መዳረሻዎች ላይ እሴት በመጨመር በመላ አገሪቱ 59 አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማት እቅድ መያዟን የተናገሩት አቶ አህመድ፤ ሚኒስቴሩ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የፈጠራ ማዕከላት እና የስብሰባ ማዕከላት ግንባታ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
እንዲሁም እንደ ፣ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ባህላዊ ምግብ እና መጠጥ ቤቶች ያሉ የቱሪስት ለቱሪስት አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት ግንባታ በቀጣይ 10 ዓመታት ለማካሄድ በእቅዱ ላይ መያዙን አቶ አህመድ አመልክተዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፤ ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ ቅርሶችን እና ታሪካዊ ቦታዎችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ብሎም የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም በመላ አገሪቱ የሚገኙ በርካታ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን የማደስ ተግባር በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል ።
የሰው ኃይልን ፣ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን፣ የመስመር ላይ አገልግሎት አሰጣጥን ፣ ዲጂታል ማድረግን እና የቱሪስት ገበያዎች ብዝሃነትን በማሻሻል በዘርፉ የመዋቅር ሽግግርን ለማምጣት ተጨማሪ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ ሀገሪቱ በዘርፉ በቀጣይ 10 ዓመታት ለማሳካት ያቀደችውን እቅድ ለማሳካት በአገሪቱ ውስጥም ጥሩ ዕድሎች አሉ። እስካሁን በቱሪስት መዳረሻነት ያልታወቁ የመስህብ ስፍራዎች እና ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው ።
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም
የመስቀል በዓል በተወሰኑ ምዕመናን እንደሚከበር ተገለጸ
********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፦ የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከልን መሰረት አድርጎ በተወሰኑ ምዕመናን እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንዳስታወቁት ፣ የዘንድሮው የደመራ በዓል ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ አነስተኛ ምዕመናን በተገኙበት ይከበራል ።
በበዓሉ በአጠቃላይ እስከ 5 ሺህ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል ።
በዘንድሮ በዓል የተሳታፊ ሰዎች ቁጥር የተወሰነው ካለው ወቅታዊ የወረርሽኙ ሁኔታና መስቀል አደባባይ በአሁኑ ወቅት ማስተናገድ የሚችለውን የሰው ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም
"የፈለገ ጥሩ ሃሳብ፣ ጥሩ አመለካከት ይዘህ ብትመጣ አንተን ለመቃረን ብቻ ሌላ ኃይል ተደራጅቶ ይጠብቅሃል" - ዶክተር ደመቀ አጭሶ
***********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፦ “የፈለገ ጥሩ ሃሳብ፣ ጥሩ አመለካከት ይዘህ ብትመጣ አንተን ለመቃረን ብቻ ሌላ ኃይል ተደራጅቶ ይጠብቅሃል”። ይህ የሴራ ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ገዝፎ መውጣቱን ዶክተር ደመቀ አጭሶ አስታወቁ ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ግንኙነት ትብብር እና ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፣ በኢትዮጵያ የፈለገ ጥሩ ሃሳብ፣ ጥሩ አመለካከት ይዘህ ብትመጣ አንተን ለመቃረን ብቻ ሌላ ኃይል ተደራጅቶ ይጠብቅሃል። ይህ ማደም ፤ ሴራ ነው። ይህ የሴራ ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ገዝፎ ወጥቷል ።
መልካም ነገር ይዘህ ስትመጣ የአንተን መልካም ነገር የሚያኮላሹ፣ ከግብ እና ከዓላማህ የሚያጨናግፉ በርካታ ሕጋዊም ሆነ ሕገ ወጥ አደረጃጀቶች በሀገሪቱ እንዳሉ ያመለከቱት ዶክተር ደመቀ ፣ እነዚህ ነገሮች ሆን ተብለው የሚደረጉ ካልበላሁ ልድፋው ዓይነት የአስተሳሰብ መሰረት ያላቸው ናቸው ብለዋል። ካልበላሁ ልድፋው ለየትኛውም ችግር መፍትሔ አምጥቶ እንደማያውቅም አመልክተዋል።
መልካም አስተሳሰቦች ስር እንዲሰዱና ግባችንን ማሳካት እንድንችል የሁሉንም ሰው ቀና ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ የሁሉም ሰው አስተሳሰብ የአመለካከት መገራትን እንደሚፈልግ አስታውቀዋል። የተለያዩ አመለካከቶች ይኑሩ፣ እንከራከር፣ እንወያይ፣ በጥሩ መንፈስ መከራከር መልካም ነው ብለዋል ።
ክርክር ጥሩ የሚሆነው መልስ ለመሰጣጠት ብቻ ሳይሆን እራስን ለማነፅ፣ ክፍተቶችን ለመሙላት፤ የተከራካሪህንም ክፍተቶች ለመሙላት የምታደርገው ዴሞክራቲክ የሆነ እና የሰለጠነ ክርክር መሆን ሲችል እንደሆነ ጠቁመው ፣ ይህን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ለመገነባቢያ የሚረዳ የክርክር ባህል ማዳበር እንደሚገባ አመልክተዋል ። በእኛ ሀገር ግን እየሆነ ያለው ክርክር ለማጥቃት እና ለመከላከል እንደሆነም ገልጸዋል።
በኛ ሀገር የፖለቲካ ባህል ሀገር ሊገነባ የሚችል ሃሳብ ይዘህ ብትመጣ ከአንተ በተቃራኒ በመቆም ምንም ሳያዳምጥህ መልስ የሚሰጥህ ወይም ስትናገር የሚያዳምጥህ አንተን ለማጥቃት ወይም የአንተን ሃሳብ ለማኮላሸት ነው የሚሉት ዶክተር ደመቀ፣ ይህ ወደአሰብነው ግብ እንዳንደርስ እንደሚያደርገን ጠቁመዋል ። እከሌ በዚህ ጎራ ተሰልፏል።
ስለዚህ ከሱ ጋር ላለመሰለፍ በማለት ሆን ተብሎ ከሱ ጋር ላለመሆን የሆነ ስንጥር እየሰነጠረ በተቃራኒህ ይቆማል። አንድ ከምሆን ሞቼ እገኛለሁ ይልሃል ፤ ይህ የፖለቲካ ባህል የትም እንደማያደርሰን አመልክተዋል።
ይህ ዓይነት አካሄድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሁን እየበዛ እንደመጣ ያመለከቱት ዶክተር ደመቀ፣ ከዚህ የተነሳም ግባችን ላይ እንዳንደርስ ፅንፍ የረገጡ ኃይሎች የአንዱን መብት፣ የመኖር ህልውና፣ ባህል፣ ወግ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ከግንዛቤ ሳያስገቡ እኔ ብቻ በሚል አስተሳሰብ ከምንጊዜውም በላይ ጎልተው መምጣታቸውን አስታውቀዋል ።
“ይህን በዓለም ታሪክ ስንቃኝ የቡድን አስተሳሰብ (the we group, the they group) የእኛ ቡድን የእነሱ ቡድን፤ ከእኛ ለእኛ ወገን የእኛ ቡድን የሚጠቀመውን ነገር የእነሱ ቡድን እንዳይጠቀመው እናድርግ። የእኛ ቡድን የማያሳካውን ግብ የእነሱ ቡድን እንዳያሳካ እናድርግ የሚባል ሴራ በዓለማችን ላይ ከባባድ እልቂቶችን አስከትሏል” የሚሉት ዶክተር ደመቀ፣ የአንደኛውም ሆነ የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ውጤቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
“ለብዙ የአይሁድ ማህበረሰቦች በአውሮፓ እንዲታረዱ ምክንያት ሆኗል። ጭፍን በሆነ ጥላቻ መሰላል (ደረጃ) አስቀምጦ እነዚህ፣ እነዚህ ሰዎች መወገድ አለባቸው ብሎ ማሰብ በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አይተናል። በኢትዮጵያም ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አልገባም ማለት አይቻልም። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰዎች በእሳት ሲቃጠሉ አይተናል። ይህ በጣም አጸያፊ ተግባር ነው። ጭፍን ጥላቻ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ወደ እልቂት እንዳያመራን ዋልታ እረገጥ አመለካከቶችን ማስቀረት፣ መቁረጥ፣ መከራከርም ይኖርብናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም
889 ተጨማሪ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ 12 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል
*******************
(ኢ.ፕ.ድ)

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 8 ሺህ 115 የላቦራቶሪ ምርመራ 889 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 320 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 28 ሺህ 634 ሆኗል።

ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉ መረጋገጡን ተከትሎ በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 108 ደርሷል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 69 ሺህ 709 ደርሷል።
የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖቹ አዲሱን የብር ኖት እንዲያነቡ መደረጋቸውን ንግድ ባንክ አስታወቀ
*****************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- ነባሩን የብር ኖት ሲያነቡ የነበሩ የኤቲኤም ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንዲያስችላቸው የሚያደርግ ስራ መሰራቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ገለጹ። አዲሱ የብር ኖት በየቅርንጫፎቹ በመዳረስ ላይ እንደሆነም ተናገሩ።

ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ አቶ የአብስራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አዲሱን የብር ኖት መለወጥ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ደንበኞች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመምጣት እየለወጡ ይገኛሉ።አዲሱን የብር ኖት የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች ማንበብ እንዲችሉ ማድረግ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስራ በመሆኑ ነባሩን የብር ኖት ሲያነቡ የነበሩ ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንዲችሉ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ባሉት ኤ.ቲኤ.ም ማሽኖች አዲሱን ኖት መክፈል ተጀምሯል።እንደዚያም ሆኖ ነባሩን የብር ኖት መክፈል ባለማቆማችን ስራውን ጎን ለጎን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

እንደ አቶ የአብስራ ገለጻ፤ ደንበኞች ነባሩን የብር ኖት በመመለስ ላይ ሲሆኑ፣ በተለይ ከአምስት ሺህ ብር በላይ ከሆነ አዲስ ሒሳብ ከፍተው እያስቀመጡ ይገኛሉ።የብር ኖቱ ለውጥ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አዲስ አበባ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ብቻ ባሉት 320 ቅርንጫፎች ላይ አዲሱ የብር ኖት እንዲዳረስ ተደርጓል።ከዚህ ባሻገር ደግሞ በተመረጡ ስድስት የክልል ከተሞች ላይ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በትብብር አዲሱን ኖት የማድረስና የማሰራጨት ስራ ተጀምሯል።

የገንዘብ ኖቱ በበርካታ ቦታ ማለትም ገንዘብ የሚከፋፈልባቸው ቦታዎች ደርሷል ያሉት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ፣ ለአብነትም ጅግጂጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ አዳማና ሌሎችም ከተሞች ላይ በመዳረስ ላይ ይገኛል ብለዋል።በተጨማሪም ሌሎች ገጠራማ የሆኑ ስፍራዎችም በመጓጓዝ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።

በባንክ ደረጃ በችግር ያየናቸው ነገሮች እስካሁን የለም ሲሉ ጠቅሰው፤ ህዝቡ ደስተኛ ሆኖ እየለወጠ መሆኑን አስረድተዋል።ጊዜው አጭር ስለሆነ ደንበኞች ሳይዘናጉ እየመጡ እንዲለውጡም አበረታትተዋል። በኋላ ላይ ሩጫ ሳይፈጠርና ጊዜው ሳይጨናነቅ ቢለውጡ መልካም መሆኑንም ጠቅሰው እሁድንም ጨምረው በመስራት ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

እርሳቸው ደንበኞች ገንዘብ በኪስ ይዘው እንዳይሄዱ አበረታትተው፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ሲቢኤ ብር፣ ኤቲኤምና መሰል ቴክኖሎጂዎችን ህዝቡ ቢጠቀም የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል።በካርድ ግብይት መፈጸሚያ ማሽኖችንም መጠቀምን የሚደግፍ አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲሱ ብር ኖት ጠቀሜታው በርካታ ነው ያሉት አቶ የአብስራ፣ በተለይም ሀሰተኛ የብር ኖቶችን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።በተጨማሪም የዋጋ ግሽበትን የሚከላከል ሲሆን፣ ለአገሪቱም ጤናማ ኢኮኖሚ መሰረት ነው በማለት ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2013
አስቴር ኤልያስ
ምክር ቤቱ 6ኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰነ
*****************************
(ኢ ፕ ድ)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደው ባለው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛው አስቸኳይ ስብሰባው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰነ።
ምርጫው የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ ሀሳብ መሠረት ቫይረሱን በመከላከል ምርጫውን ማከናወን እንደሚቻል የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ የውሳኔ ሃሳብ እና ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የውሰኔ ሃሳቡም የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 16/2013 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ በ8 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ምክር ቤቱ መስከረም 8/2013 ባካሄድው 5ኛ ዙር 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥና ቀጣይ እርምጃዎች የቀረበውን ሪፖርትና ምክር ሃሳብ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል፡፡
በድሬዳዋ በበጀት ዓመቱ ከ23 ሺ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል
********************
(ኢፕድ)

የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከድሬዳዋ አስተዳደር እና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው፡፡

የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በድሬዳዋ የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በድሬዳዋ ዛሬ ባካሄደዉ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ በከተማ አስተዳደሩ በ2013 በጀት አመት ከ23 ሺ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ዘንድሮ ወደ ድሬ ዳዋ ኢንዲስቲሪ ፓርክ የሚገቡ የተለያዩ ኩባንያዎች በመኖራቸው እስከ 10ሺ ለሚሆኑ ዜጎች በቀጥታ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ሲሆን እንዲሁም ለኩባኒያዎቹ የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ እና አገልግሎቶችን የሚሰጡ ለተለያዩ የስራ መስኮችንም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራል ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኑጉሱ ጥላሁን በድሬዳዋ የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አደረጃጀቱን የማሻሻል ስራ በማከናወን በተሻለ የስራ ዕድል ፈጠራ የማመቻቸቱን ስራ ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋለ፡፡

በመድረኩ ላይ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የንግድ፣ ኢንደስቲሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ከዲር ጁሃር እንዲሁም በአስተዳደሩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በመተከል ዞን ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 13 ተጠርጣሪዎች እና 8 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 13 ተጠርጣሪዎችና 8 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል፡፡

በዞኑ ቡለን ወረዳ በቅርቡ የጸጥታ ችግር በተከሰተበት ኤጳር ቀበሌ በደረሰው ጉዳት ቀጥታ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበሩ የተባሉ 5 ተጠርጣሪዎች ከ1 ጂምስሪ እና 5 ክላሽ በድምሩ 6 የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ አመራሩ በሠራው የህዝብ ግንኙነት ሥራ በቀበሌ በደረሰው ጉዳት ቀጥታ ተሳትፎ የነበራቸው 5 ሽፍታዎች ከ2 ክላሽ የጦር ማሳሪያዎች ጋር የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ ርብርብ እና የተኩስ ልውውጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አበራ አስታውቀዋል፡፡

በመተከል ዞን ሁሉም አካባቢዎች የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በዞኑ እየተፈጠሩ ከሚገኙ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ በዳንጉር ወረዳ 2 በጉባ ወረዳ ደግሞ 1 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታዬ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አመራሩ፣ የፌዴራልና የክልሉ ጸጥታ አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ እየተሠሩት ያለውን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው አቶ አበራ የተናገሩት፡፡

በዞኑ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እየተሠራ ባለው የሕግ የበላይነት ማስከበር ሥራ ከዚህ ቀደም 358 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል ሲል የዘገበው የክልሉ የመንግስት ኮምንኬሽን ቢሮ ነው።
በሀገሪቱ የተከሰቱ ሁከቶችና ግጭቶች ከሙስና ወንጀል ጋር እንደሚያያዙ ኮሚሽኑ ገለጸ
*************************
(ኢፕድ)
አዳማ:- ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች እየደረሱ ያሉት ሁከቶች እና ግጭቶች ኢንዲሁም ከዚህ የመነጨው የዜጎች መፈናቀል ከሙስና ወንጀል ጋር የተያያዘ መሆኑን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ የ10 ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ፣ የ2013 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድና የስነ ምግባር መከታተያ መመሪያ ዙሪያ ሲሰጥ በቆየውና ዛሬ በሚጠናቀቀው ስልጠና ላይ የሥራ መመሪያ የሰጡት በኮሚሽኑ የክልል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መለስ ተገኝ፤ ሙስና አሁን በዓለም ደረጃ እጅግ አሳሳቢ የሆነ፣ የአደጉ አገራትንም የፈተነ፣ በተለይም የአረብ አገራትን እስከማፈራረስ የደረሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአረብ አገር ህዝቦች በአገራቸው መኖር ያልቻሉበትና ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ የተገደዱት ከዚሁ ችግር በመነጨ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች እንደመሆኗ አደጋው ቢከሰትባት እጅግ በጣም አስከፊ እንደሚሆን አመልክተዋል።

‹‹በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች በዛች አገር ሆነው የዘረፉትን ገንዘብ እየበሉ መኖር የሚችሉት አገር ሲበጠበጥና ሰላም ሲጠፋ ነው›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሰላም ከሰፈነ፣ አንድነት ከተፈጠረ እንደሚጠየቁ ያውቃሉ ብለዋል።

ዳይሬክተሩ በአገሪቱ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉት ሁከትና ግጭቶች በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች አጀንዳ መሆኑን ማሰብ ብልህነት ይሆናል ብለዋል፡፡

እንቅስቃሴው እውነት ለዘራቸው፣ ለብሄራቸው ወይም ለሃይማኖታቸው ተቆርቁረው አይደለም ያሉት አቶ መለስ፤ በሙስና የተዘፈቁ ዜጎችን ጠያቂ ህብረተሰብ እንዳይፈጠር አጀንዳ ለመቀየር እየተደረገ ያለ ጥረት አካል እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው ግጭትና ሁከት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ውስብስብ የሆነ፣ እጅግ በጣም በረቀቀ እና በቡድን የተሳሰረ መልኩ የሚከናወንን ሙስና ተበታትኖ መታገል እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል የተደረጉ ጥረቶች መልካም እንደነበሩ፣ ካለው የችግሩ ግዝፈት አንጻር በተሻለና ወጥነት ባለው አገራዊ መልክ በያዘ የእቅድ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ በመደጋገፍ ለመስራት ዕቅዱ ጸድቆ ወደ ትግበራ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል፡፡

ዕቅዱ ቀድሞ ከተከናወነው የላቀ በመተግበር፣ ያለውን የገዘፈ ችግር ያገናዘበና ወጥ የሆነ ትግል ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ያመለከቱት አቶ መለስ፤ ትግሉን የሚያንቀሳቅሱ በሁሉም የእርከን ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች እርስ በርስ በመናበብ፣ የተቀናጀና የተናበበ ተግባር በማከናወን ስኬታማ ተግባር ለማከናወን እንደሚያስችል አመልክተዋል።

በኮሚሽኑ የስልጠናና ጥናት ምርምር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ በበኩላቸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የጸረ ሙስና ትግሉ በተለያዩ ተቋማት የሚካሄድ በመሆኑ የሙስና ወንጀሎችን ለመታገል አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል። የሙስና ተጋላጭነትም እየጨመረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በተቋማት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭነት መበራከትም ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት መሆኑንም ያመለከቱት አቶ ተስፋዬ፣ የጸረ ሙስና ትግሉ በቴክኖሎጂ አለመደገፉ እና በተቋማት ውስጥ በሚፈጸሙ ኢ-ስነ ምግባራዊ ድርጊቶች ምክንያት በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ሮሮዎችና ቅሬታዎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል። ለተማሪዎች የስነ ምግባር ብልሽት መንስኤ የሚሆኑ በአቋራጭ የመበልጸግ ፍላጎት መጨመርንም እንደተግዳሮት አንስተዋል።

እቅዱ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የመከላከል አቅምን የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተው፤ የአገሪቱን የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የመከላከል ደረጃ እንደሚያሳድግ፣ በሙስና መከላከል ላይ የኮሚሽኑና የአገሪቱ ገጽታ ለመገንባት አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ጠንካራና ኃላፊነቱን በብቃት መፈጸም የሚችል ተቋም መገንባት፣ የተቋማትን የስነ ምግባር መከታተያ ክፍሎችን የመፈጸም አቅም ማሳደግ፣ በሀገሪቱ ሙስናና በብልሹ አሰራሮችን የመከላከል አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ፣ ተማሪዎች በመልካም ሽነ ምግባር ታንጸው ሙስና እንዲጠየፉ ማድረግ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተቋማት የሙስና ተጋላጭነት እንዲቀንስ በማድረግ በአፍሪካ ሙስናን በመከላከል ግንባር ቀደም ሆኖ መገኘት ከእቅዱ የሚጠበቁ ውጤቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

አገራዊ የስነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ስትራቴጂያዊ እቅዱ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ለ10 ዓመታት የሚተገበር ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 13/201
በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች ላይ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙ ተገለጸ
********************
(ኢ ፕ ድ)

በ2012 በጀመት ዓመት በ130 ሺህ የስልክ መስመሮች ላይ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል መፈጨሙን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ ላይ እንደገለጹት፤ ኩባንያው በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓትን በመዘርጋት ቀደም ሲል የነበሩትን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ስርቆቶችንና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎችን መቀነስ ችሏል፡፡

እንደ ዋና ስራ አሰፈጻሚዋ ገለጻ፤ አሁንም ቢሆን ህገ ወጦች በደንበኞች በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ተጠቅመው የሚፈጸሙት የወንጀል ደርጊቶችና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች ከጊዜው ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት አመትም በ130 ሺህ የኩባንያው ደንበኞች የመስመር ስልክ ላይ የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል።

ደንበኞቹ በተለያዩ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፍበት ወቅት ወዲያወኑ ባለማዘጋታቸው፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅም የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠት የተነሳ ወንጀለኞች የስልክ መስመሩን ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች እየተጠቀሙበት መሆኑን ወ/ሪት ፍሬህይወት አስታውቀዋል።

በተጠቀሰው የማጭበርበር ወንጀል የተነሳ ደንበኞች ለአንግልትና ለወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት እየተዳረጉ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ኩባንያውም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቀዋል።

የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል መከላከል እንዲቻል ደንበኞች በተለያየ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋበት ወቅት በአቅሪያባቸው በሚገኙ የሽያጭ ማዕከላት በመቅረብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸው ያሉት ዋና ስራ አሰፈጻሚዋ፤ የስልክ መስመራቸውን በማዘጋትም ምትክ ሲም ካርድ መውስድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ደንበኞች የስልክ መስመራቸውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ባለመስጠትና ለወንጀለኞች ተባባሪ ባለመሆን በስልክ መስመራቸው አማካኝነት ከሚፈጸም ወንጀል እንዲጠነቀቁም አሳስበዋል፡፡
በወንድማገኝ አሸብር
የትምህርት ቤቶች ትምህርት ማስጀመር ሂደት በሶስት ዙር እንደሚከናወን ተገለጸ
************************
(ኢ.ፕ.ድ)
የትምህርት ቤቶች ትምህርት ማስጀመር ሂደት በሶስት ዙር እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ማለትም ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ደግሞ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ነው ምክረ ሃሳብ የቀረበው።
በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው ውይይት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ የሚደረገው ውይይት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የ8ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ብሔራዊ ፈተና መውሰጃ ቀናት ይፋ ሆነ
******************
(ኢ.ፕ.ድ)
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተደረገ ባለው ውይይት ላይ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ገለፃ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም በምክረ ሀሳቡ ላይ ተጠቅሷል።
የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
የግል ትምህርት ቤቶች የምዝገባ ክፍያ በ2012 ዓ.ም በነበረው መጠንና የክፍያ ስርዓት መሆን እንዳለበትም ተገልጿል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የትምህርት ቤቶች የክፍያ ስርዓት በባንክ በኩል ብቻ መፈጸም እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
እነ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 18 ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዘዘ
*************
(ኢ.ፕ.ድ)

ፍርድ ቤቱ እነ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 18 ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ አዘዘ።

በጥበቃ በኩል ስጋት ካለ እንደሚከታተልም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱ በችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾች እንዲቀርቡ ትዛዝ ሰቷል።

በችሎት ያልቀረቡት ተከሳሾች ባሉበት ክስ ለማንበብ መስከረም 21 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኤፍቢሲ ዘግቧል።
በቀጣይ 10 ዓመታት የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ 82 ለማድረስ ታቅዷል
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

በቀጣይ 10 ዓመታት የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ ተደራሽነትን 82 ለማድረስ መታቀዱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የ10 ዓመት መሪ እቅድ እንዲሁም በሰላም ግንባታ የሚዲያ ሚና ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተቋሙን የ10 ዓመት መሪ እቅድ ያቀረቡት የተቋሙ አማካሪ አቶ ግዛው ተስፋዬ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት 60 የሀገሪቱ ቋንቋዎች የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ 10 ዓመታት ሁሉም የሀገሪቱ ቋንቋዎች የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ እንዲሆን ይሰራል።

በውይይት መድረኩ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሚስተዋሉ ጥንካሬዎች፣ ዕጥረቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና፣ ስጋቶችና አስቻይ ሁኔታዎች ተዳሰዋል።

በውይይት መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ቦርድ አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት እንዲሁም የፌዴራል የዲሞክራሲ ተቋማት የበላይ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በመላኩ ኤሮሴ
ለመስቀል ደመራ በዓል ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን ፖሊስ ይፋ አደረገ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሰከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የሚከበረው የደመራ በዓል ተጀምሮ አስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪዎች ዝግየሚደረጉ መንገዶችን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት፦
.ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ
.ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያ አካባቢ
.ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት
.ከቸርችል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አገር አስተዳደር መብራት ወይም ኢሚግሬሽን መ/ቤት አካባቢ
.ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ
.ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ
.ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ
.ከሳሪስ በጎተራ የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ
.ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ
.ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ፣ ሜክሲኮ ፣ ለገሀር መብራት የሚወስደውመንገድ ለገሃር መብራት አካባቢ ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ ሲሆን፣ ደመራው የሚደመርበት መስቀል አደባባይ እና ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ስታዲዬም እንዲሁም ከሃራምቤ ሆቴል ወደ ሴንጅ ዮሰፍ የሚያቋርጠው መስቀለኛ መንገድ ለበዓሉ በሚደረገው ዝግጅት ምክንያት ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ዝግ የሚደረግ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪውን አስተላልፏል፡
12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እና ምዝገባ በኦንላይን እንደሚካሄድ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
************************
(ኢ ፕ ድ)
ከኮቪድ ወረርሽን ጋር በተያያዘ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እና ምዝገባ በኦንላይን እንደሚካሄድ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቋል።

ተማሪዎች ለፈተና ከመቀመጣቸው በፊትም የ45 ቀን የማካካሻ እና የቴክኖሎጂ መለማመጃ ጊዜም እንደሚሰጣቸው በትምህርት ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት እና ፈተናም የሚሰጠው ትምህርት ቤቶች የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማሟላት ሲችሉ ብቻ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ መቅረቡን አስታውቋል።
አርቲስት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ) ከዚህ አለም በሞት ተለየች።
********************
(ኢ ፕ ድ)
በበርካታ የትያትርና ፊልም ስራዎች የምትታወቀው አርቲስት አልማዝ ኃይሌ (ማሚ) ከዚህ አለም በሞት ተለየች።
ለሳምንታት በህመም ላይ የነበረችው አርቲስቷ ዛሬ ማለዳ ነው ማረፏ የተሰማው።
የአርቲስቷ ስርዓተ ቀብር ነገ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈፀማል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ አርቲስቷ ከ40 ዓመት በላይ በኪነ ጥበቡ ዓለም በመቆየት በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አበርክታለች።