Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ የድርጅቱን ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ
**********************-
(ኢ.ፕ.ድ)

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ የድርጅቱን ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ።

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ዛሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አቶ ዳውድ በፓርቲው አንድነትና ሰላማዊ ትግል ላይ እየፈጠሩት የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም ያሉባቸውን ችግሮች ከማስተካከል ይልቅ ፓርቲውን የመከፋፈልና አንጃ የመፍጠር አካሄዶችን ሲከተሉ ቆይተዋል። በመሆኑም ለፓርቲው ህልውናና ጥንካሬ ሲባል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው አግዷቸዋል።

በቀጣይ በፓርቲው ህገ ደንብና አሰራር መሰረት የሚከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን ያስታወቁት አቶ ቀጃላ፤ ሁሉንም ሂደቶች በተመለከተ ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ሰነድና መረጃ ማስገባቱን አስታውቀዋል።

አቶ ዳውድ ላለፉት 20 አመታት በፓርቲው ላይ ተደጋጋሚ አደጋ መደቀናቸውን የተናገሩት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው፤ ቀደም ባሉት አመታት ሶስት ጊዜ ለፓርቲው መከፋፈል ዋናው ምክንያት እርሳቸው እንደነበሩና አሁንም ለአራተኛ ጊዜ ፓርቲውን ለመከፋፈል አንጃ ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ይተዋል። ይህንን ለማስተካከል ጥረት ሲደረግም በተጨባጭ የፓርቲውን ንብረትና ገንዘብ ወደግላቸው የማዘዋወር እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። ስለሆነም ፓርቲውን ለመታደግ ሲባል እርምጃው ተወስዶባቸዋል።

አቶ ዳውድ በፓርቲው ውስጥ ችግር መፍጠር የጀመሩት ከሀምሌ ወር ጀምሮ እንደነበር የተናገሩት አቶ ቀጀላ፤ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በእርሳቸው በኩል ችግሩን ለመፍታት ባለመተባበራቸው ፓርቲው ህጋዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ቀጀላ ገለጻ፤ ፓርቲ ከአቶ ዳውድ ጋር ያለው ትልቅ ልዩነት በትግል አካሄድ ላይ ነው። ኦነግ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ ሰራዊቱ በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት ወደ መንግስት የጸጥታ አካላት እንዲቀላቀል ስምምነት ቢደረግም፤ አቶ ዳውድ ግን በዚህ ላይ ግልጽ አቋም አልነበራቸውም፤ በአንድ በኩል ሰላማዊ ትግሉን ይፈልጋሉ፤ የትጥቅ ትግሉንም በኪስ አድርገው በድብቅ መሄድ ይፈልጋሉ።

በተጨባጭም በምዕራብና በደቡብ ጫካ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሄ አካሄድ አግባብ አይደለም በሚል ስራ አስፈጻሚው ሲነጋገርበት ቆይቷል። ምክንያቱም የትጥቅና ሰላማዊ ትግል ድንበር ሊበጅለት ይገባልና ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጎ አዲስ መሪ ኣስኪመረጥ ድረስ የድርጅቱ ተወካይና መሪ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ እንደሆኑ አቶ ቀጀላ ጠቅሰው፤ በአቶ ዳውድ በኩል እስከዛሬ የነበሩ የዲስፕሊን ጥሰቶችን በተመለከተ ፓርቲው ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ ለወጠች
**********
(ኢ.ፕ.ድ)
ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ መለውጧን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አስታወቁ።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ነባሮቹን የገንዘብ ኖቶች በመተካት ለግብይት የሚሆን አዲስ የገንዘብ ዓይነት መጠቀም እንደምትጀምር በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።

አዲስ የ200 ብር ገንዘብ ኖትም ተጨማሪ ሆኖ መምጣቱን ገልጸዋል።

እነዚህ አዲስ የገንዘብ ዓይነቶች ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግን ድጋፍ፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ ይረዳሉ ብለዋል።

በአዲሶቹ የገንዘብ ዓይነቶች ላይ የተካተቱ መለያዎች አመሳስሎ ገንዘብ ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት ያግዛሉ ነው ያሉት።
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ግብርና እና አርሶ አደሮች የሚውል የ80 ሚሊየን ዶላር እርዳታ አጸደቀ
*************
(ኢ.ፕ.ድ)
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ግብርና እና ለአርሶ አደሮች ድጋፍ የሚውል የ80 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ማጽደቁን አስታወቀ።
ባንኩ በድረ ገጹ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፤ እርዳታው የኢትዮጵያን ግብርና ምርት ለማሰደግ እና በእፕነስተኛ ማሳ ለሚተዳደሩ ለአርሶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚውል ነው።
የዓለም ባንክ የ 2019 የድህነት ምዘና በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት አስርት ዓመታት ለድህነት ቅነሳው ቁልፍ አንቀሳቃሽ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሶ ለሁለተኛው የግብርና ልማት ፕሮጀክት (AGPII) ተግባራዊነት የሚያግዝ ተጨማሪ ፋይናንስ ማጽደቅ ለአገሪቱን የግብርናው ኢኮኖሚ ማሳደግ አቅም ይፈጥራል ብሏል።
በአለም ባንክ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያ የሆኑት ቪካስ ቹድሃሪ እንዳሉት “ሁለተኛው የግብርና ልማት ፕሮጀክት (AGPII) በኢትዮጵያ ድህነት ቅነሳ ላይ የጎላ አስተዋፅዖ አድርጓል ፡፡ ፕሮጀክቱ በተጨባጭ በተለይም ምርታማነትን በማሳደግ እና የንግድ ሥራን በማጎልበት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል ፡፡ በተጨማሪም የመስኖ አጠቃቀምን በማስተዋወቅ አርሶ አደሩ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አስችሎታል ፡፡ አርሶ አደሩ ዝናብ ላይ ጥገኝነት በመላቀቅ እሴት የሚጨምሩ የአትክልት ፍራፍሬዎችን ማምረት ጀምሯል።
በተለይም AGPII ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ አነስተኛ አርሶ አደሮች (37% ሴቶች የሆኑ ) የግብርና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማሳደግ ረድቷል ፡፡ እንዲሁም በ 254 አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች መጠቀም በመቻሉ በሰብል ምርታማነትን በማሳደግና በአየር ንብረት-ዘመናዊ ጥበቃ ላይ ውጤታማ መሆን ተችሏል ነው ያለው ባንኩ።
ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንዲላመዱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን 2 ሺህ 299 አዳዲስ አነስተኛ የመስኖ እቅዶችን በማጠናቀቅ እና ነባር የመስኖ መሠረተ ልማቶችን በማሳደግ 23,290 ሄክታር የእርሻ መሬት በመስኖ እንዲለማ አስችሏል ተብሏል ፡፡
በፕሮጀክቱ ስር የተካሄዱት የገበያ መሰረተ ልማት እና የእሴት ሰንሰለት ኢንቬስትመንቶች አርሶ አደሮችን ከገበያዎች ጋር በማስተሳሰር እና ንግድን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል ፡፡ እነዚህ ተግባራት በሄክታር ከፍተኛ የምርት መጠን እንዲጨምር በማገዛቸው የአርሶ አደሮችን ገቢ እንዲያድግ አግዘዋል፡፡ እንዲሁም ለአርሶ አደሮች የተሻሻሉ የአመጋገብ ውጤቶችን አስገኝተዋል፡፡
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ለሱዳን ዳይሬክተር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ለጠቅላላ ምርቱ 45 ከመቶውን እንዲሁም 80 በመቶ የሚሆነውን የሰራተኛ ኃይል የሚቀጥር በመሆኑ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ ዘርፍ ነው ፡፡ በዘርፉ እስካሁን ድረስ አበረታች ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም ቀሪ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና የምርታማነት ግኝቶችን ለማፋጠን ፣ ለተዛባ የአየር ንብረት ሁኔታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ፣ የመሬት መበላሸትን ለመቅረፍ እና በዘርፉ ላይ የተመረኮዘ የተፈጥሮ ሃብት መሰረትን ለማሳደግ ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህ ተጨማሪ ፋይናንስ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ሙሉ አቅሙን መጠቀም እንዲችል ይረዳዋል ብለዋል። ገንዘቡ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን ለማሳደግ እና የተለያዩ ተጨማሪ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ለማሳደግ የተመደበ መሆኑን ተጠቅሷል ፡፡
በተጨማሪም ገንዘቡ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የተፈጠሩትን ያልተጠበቁ የፋይናንስ ክፍተቶችን የሚሞላ እና ከፍተኛ ወጪ በመጠየቃቸው ምክንያት የዘገዩ የፕሮጀክት ሥራዎች አፈፃፀም ያፋጥናል ተብሏል፡፡
ለሁለተኛው የግብርና ልማት ፕሮጀክት በ 167 ወረዳዎች በአማራ ፣ በኦሮሚያ ፣ በደቡብ ፣ በትግራይ ፣ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ፣ በጋምቤላ እና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ይተገበራል ፡፡ ፕሮጀክቱ በቀጥታ ለግብርና ዕድገት ከፍተኛ አቅም ባላቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ 1.6 ሚሊዮን አነስተኛ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል ፡፡
“የፓርቲዎች የውይይት ባህል እየጎለበት ከሄደ ቀጣዩን ምርጫ በተሻለ መግባባት ማካሄድ እንችላለን “ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ
**************************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- የፓርቲዎች የውይይት ባህል እየጎለበት ከሄደ ቀጣዩን ምርጫ በተሻለ መግባባት ማካሄድ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ ። ፓርቲዎች ተቀራርበው መወያየታቸውን ተከትሎ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም ተገለጸ ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተካሄዱትን ውይይቶች ትናንት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በጋራ በገመገሙበት ወቅት ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄደው የውይይት ባህል እየተጠናከረ የሚሄድ ከሆነ ለብዙ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ ይሆናል።
ይበልጥ ስንተዋወቅ፣ ስንደጋገፍ ቀጣዩን ምርጫ በተሻለ መግባባት ማካሄድ ያስችላል ብለዋል ።
“ምን አልባት ምርጫውን የሚያሸንፈው ሀይል በርከት ያለ ከሆነ ይህንኑ የትብብር መንፈስ ካስቀጠልነው በጋራ ሆኖ አገር መምራት የሚያስችል አውድ ይፈጥራል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአገራዊ አጀንዳዎች የሚካሄዱ ውይይቶች በጋራ መግባባት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ቀጣይ መንገዶችን ለማበጀት የታለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት የሚካሄዱ ውይይቶች ፍሬያማ እንደነበሩ አስታውቀዋል። በተለይ ብሄራዊ መግባባት ዙሪያ በምክር ቤቱ አማካኝነት የተካሄደው ውይይትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እያካሄዱት ያሏቸው ውይይቶች ቅርርብንና መግባባትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለጹት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተወክለው የመጡት አቶ ኡመር መሃመድ፤ መሰል ውይይቶች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
ትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ፤ “የፖለቲካ ባህላችን ኋላ ቀር ነው” ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት በብሄራዊ መግባባቱ ዙሪያ የተደረጉና በቀጣይ የሚካሄዱ ውይይቶች በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዘንድ ጥሩ መንፈስና መቀራረብ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በወቅቱም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የጋራ መድረክ አማካኝነት የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት፣ የኢትዮጵያ ትልቁ የቅራኔ ምንጭ ምንድነው? ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊነት፣ ጥሩ ምርጫ ምን ማለት ነው? የሚሏቸው አጀንዳዎች ዙሪያ በቀጣይ ውይይት ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተመረጡ አራት ሰዎች ከ10 ወይም ከ15 ቀናት በኋላ በሚያካሂዱት ውይይት መድረኮች ላይ ጹሁፋቸውን አቅርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።ፓርቲዎች ተቀራርበው መወያየታቸውን ተከትሎ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም በውይይት መድረኩ ላይ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013
ጌትነት ምህረቴ
በኦሮሚያ ክልል ከ32 ሺህ በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸው ተገለፀ
***********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፦ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ትምህርትን ለማስቀጠል እንዲቻል 32 ሺህ 108 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ተጨማሪ 30 ሺህ ክፍሎችን ለመገንባት ታቅዶ ከእቅዱ በላይ 32 ሺህ 108 መገንባቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ የውሃ እና የመፀዳጃ ቤት ግንባታዎችም መከናወኑንም አመልክተዋል።
ከመፅሃፍት ጋር በተያያዘም 1 ሚሊየን መጽሃፍት ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የተለያዩ አይነት መጽሃፍቶችን መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የ2013 የትምህርት ዘመን ትምህርት ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ያመለከቱት ዶክተር ቶላ፤ የተማሪዎች ምዝገባም እየተካሄደ ነው ብለዋል ። በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታትም ምዝገባው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
መምህራንን በተመለከተ በክልሉ ከሚገኙ 13 የመምህራን ኮሌጆች 25 ሺ 300 የ3ኛ ዓመት ተማሪዎችን የማጠቃለያ ቲቶሪያል በመስጠት ወደ ቅጥር ይገባሉ ብለዋል።
በክልሉ በዚህ የትምህርት ዘመን 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በወቅቱም የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሰራተኞች ለገበታ ለሀገር የአንድ ወር ደመወዛቸውን 1 ሚሊየን 249 ሺህ ብር መለገሳቸው ተገልጿል በመግለጫው።
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013
325 አዳዲስ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ተቻለ
*************************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- በ2012 ዓ.ም ብቻ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ ሃይል አግኝተው የማያውቁ 325 አዳዲስ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ተቋሙን በማዘመን ነባሩ ደንበኛ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ከማስቻል በተጨማሪ ከኤሌክትሪክ ጋር ምንም አይነት ትውውቅ የሌላቸውን አካባቢዎች ኤሌክትሪክ በማዳረስ ትልልቅ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት 168ሺህ 751 አባወራዎች አዲስ ቆጣሪ እንዲያገኙ ተደርጓል።
የገጠር ኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም ሲጀመር 667 ከተሞች ብቻ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ መላኩ፤ አንዳንድ የዞን ከተሞች ሳይቀሩ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ተናግረዋል። እስከ አሁን በገጠር ኤሌክትርፍኬሽን 6 ሺህ 759 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።
እንደ አቶ መላኩ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአጠቃላይ የደንበኛው ቁጥር ከ3 ሚሊየን የዘለለ አይደለም። ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥም 44 በመቶ ብቻ ነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኘው። 66 በመቶው ህዝብ ማለትም ብዛት ያላቸው ከተሞች አሁንም ከኤሌክትሪክ ሃይል ጋር እንደማይተዋወቁም ጠቁመዋል። ተቋሙ ይህን ሁኔታ ለመቀየር አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያልነበሩ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በከፍተኛ መዋለ ነዋይ ፕሮጀክቶች ነድፎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲዳረሰው ተቋማቸው ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑን ተናግረው፣ ኤሌክትሪክ ሀይል ማስፋፋት ቢቻልም አሁንም ተጠቃሚ ያልሆኑ በርካታ የገጠር ከተሞች አሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪ ነባሩ ደንበኛ በተለያዩ ምክንያቶች የሚዋዥቅ እና የሚቆራረጥ አገልግሎት ሲያገኝ ቆይቷል ያሉት አቶ መላኩ፤ አሁን ግን ኔትወርኩን በማሻሻል ነባሮቹ ደንበኞች በመደበኛነት ሃይል እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ለእዚህ ማሳያውም በዚህ ዓመት ክረምት ከፍተኛ ዝናብ ቢጥልም ሃይል የሚቆረጥበት ክስተት ውስን እንደነበር ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013
ምህረት ሞገስ
የብር ኖቶች መቀየራቸው ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ፖለቲከኞች አመለከቱ
***********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ ፦ መንግስት ነባሮቹን የገንዘብ ኖት በአዲስ መቀየሩ ህገወጥነትን የሚከላከል ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ፖለቲከኞች ገለጹ።
የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ መንግስት የገንዘብ ኖት መቀየሩ ትክክለኛ እርምጃ ነው። ምክንያቱም የቆየው የህወሀት አገዛዝ አገሪቷን የኮንትሮባንድ መናኸሪያ የደላላና የቀማኛ አገር አድርጓት ነበር።
እንደ ዶክተር አረጋዊ ገለጻ፤ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ በአንድ ጀምበር ሚሊየነር የሚሆኑ ፣ ከምንም ተነስተው ባለ በርካታ ህንጻ ባለቤቶች የሆኑ ህገወጦች የበዙባት ሆና ነበር፤ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና ህጋዊ መንገድን ለመፍጠር የገንዘብ ኖት መቀየር ትክክለኛ እርምጃ ነው ብለዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ኮንትሮባንድና ማጭበርበርን የማያውቁ በላባቸውና በወዛቸው የሚያድሩ ሰዎች ችግር ውስጥ ነበሩ ያሉት ዶክተር አረጋዊ ፤ አሁን የተፈጠረው እድል ህጋዊ ሆኖ የሰራ ሁሉ የሚያገኝበትና የሚለወጥበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩልም ዘርፈው ባስቀመጡት ገንዘብ መሳሪያ በመግዛት የተለያዩ አደንዛዥ እጾችን በማመላለስና ህገወጥ በሆኑ ተግባራት ላይ በመሰማራት አገሪቱ እንድትተራመስ ሲሰሩ የነበሩ አካላት የገንዘብ ለውጡ አደብ እንደሚያስገዛቸው አመልክተዋል።
መንግስት እንደከዚህ ቀደሙ ህጋዊ ያልሆኑ የመበልጸግ ሂደቶችን የሚቆጣጠርበት ህጋዊ ሳይሆኑ ወደ አገር የሚገቡ መድሀኒቶችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና የኮንትሮባንድ እቃዎች እይታ ውስጥ የሚያስገባበት ሁኔታ ስለሚፈጥር ፤ የገንዘብ ለውጥ ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም የሚሰጥና የኢኮኖሚ መረጋጋትን የሚያመጣ እንደሆነ አመልክተዋል።
ገንዘብን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲያከማቹ የቆዩ ሰዎች መውጫ መንገዳቸውን እራሳቸው የሚያውቁት ቢሆንም ፤ እየተተገበሩ ያሉ አሰራሮች የሰራ ሰው የሚያገኝበት፣ በሀቅ ገንዘቡን በአገር ልማትና እድገት ላይ የሚያውልበት ነው ብለዋል ።በጠቅላላው ህግን የተከተለ ተጠቃሚ የሚሆንበት መሆኑንም አብራርተዋል።
በአገሪቱ ላይ ያለውን ያልተመጣጠነና ለሌባና ለቀማኛ የተመቸ አካሄድን በማስቀረት ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ፣ የዋጋ ግሽበትም በቁጥጥር ስር እንዲውል፣ የተደበቁ ገንዘቦችም እንዲመክኑ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና ያለው እንደሆነም አስታውቀዋል።
አንድ አገር ደላላ የሚቆጣጠራት ከሆነ ፍትህ አይኖርም ዘራፊ ይበራከታል ፤ይህ ሲሆን ደግሞ እድገት አይደለም ወጥቶ መግባትም ይናፍቃል፤ በመሆኑም መንግስትም የሚሰራቸውን መሰረተ ልማቶች ተረጋግቶ እንዲሰራ አገርን የማልማት ስራውም የተሳለጠ እንዲሆን በጣም ጠቃሚ እረምጃ ነው ብለዋል ።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤መንግስት ጥናት አስጠንቶ መረጃ ሰብስቦ የፋይናንስ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ውይይት እንዲያደርጉበት አድርጎ የወሰነው ውሳኔ በመሆኑ ጥሩ እርምጃ ነው።
ህገ ወጥ ገንዘቦች በአገሪቱ ላይ መዘራታቸው አፍራሽ ሚና ያለው ነው፤ ግማሹም ፖለቲካውን ተገን በማድረግ ብዙ የብር ኖቶችን በየስርቻው ደብቆ ለእኩይ ተግባሩ ማስፈጸሚያነት ሲጠቀምበት የቆየ በመሆኑ ይህ ውሳኔ በመንግስት በኩል መወሰኑ ለኢኮኖሚያዊም ይሁን ፖለቲካዊ ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን አስታውቀዋል።
“ብዙ ኩንታል መቶ ብሮች አስቀምጠህ ከሆነና በፍጥነት ሄደህ ባንክ ካልቀየርክ ወረቀት ሆኖ ይቀራል ማለት እኮ በቂ ቁጥጥር ነው” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ አሁን ሁሉም ወደ ህጋዊነት የሚመጣበት ጊዜ ስለመሆኑም ጠቁመዋል ።
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013
እፀገነት አክሊሉ
“ለተቋሙ ሰራተኞችና አመራር አባላት ይህ መጽሀፍ እንዲወለድ ለነበራችሁ ጉልህ አስተዋጾ ከምስጋና ጋር የተበረከተ”
- የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

አገራዊ ሁነቶችን በየዕለቱ በዜና እየዘገበ ለታሪክ በመሰነድ 80 አመታትን የተጓዘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፤ ባለፉት ሁለት አመታትም የነበሩ አገራዊ ሁነቶችን ከመዘገብና ታሪክ ከመሰነድ ባሻገር አገራዊ ለውጡን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና መንግስታቸውን እለታዊ የስራ እንቅስቃሴ በዜና እየዘገበ “በለውጡ ጎዳና ላይ” በሚል ርዕሰ ለንባብ ለበቃው መጽሀፍ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም ለዚሁ አስተዋፆ ለተቋሙ የአመራር አባላትና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የምስጋና መልዕክታቸውም፤ “ለተቋሙ ሰራተኞችና አመራር አባላት ይህ መጽሀፍ እንዲወለድ ለነበራችሁ ጉልህ አስተዋጾ ከምስጋና ጋር የተበረከተ” ብለዋል።

“በለውጡ ጎዳና ላይ” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሀፍ የለውጡን ጉዞ ስኬት፣ተግዳሮት እና ተግዳሮቶቹ የታለፉባቸውን መንገዶች በዝርዝር የሚያስቃኝ ሲሆን፤ ይሄው መጽሀፍ ለአጥኝዎች፣ ለተመራማሪዎችና ለጋዜጠኞች ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።
አዲሱን የብር ኖት በኤቲኤም አገልግሎት መስጠት ተጀመረ
***********************
(ኢፕድ)
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነባሮቹን የብር ኖቶች በአዲሶቹ የመቀየር አገልግሎት በቅርንጫፎች ከመስጠቱ ጎን ለጎን የኤቲኤም ማሽኖች በአዲሶቹ የብር ኖቶች አገልግሎት እንዲሠጡ እያደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርጫፍ የሚገኙት ኤቲኤም ማሽኖች በአዲሶቹ የብር ኖቶች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም የባንኩ ኤቲኤም ማሽኖች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብሏል፡፡
በሶስት ቀናት ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 10.6 ሚሊዬን ብርና 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ዋለ
**************************
(ኢፕድ)

በሶስት ቀናት የኦፕሬሽን ስራዉ በጥቁር ገበያ እና በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 10.6 ሚሊዬን ብር እና 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበበ ፖሊሰ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ አዲስ የብር ኖቶችን ማስተዋወቋን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝዉዉር እየተስተዋለ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የብር ኖት ለዉጥ መደረጉን ተከትሎ ባደረገዉ የኦፕሬሽን እና የድንገተኛ ፍተሻ ስራ በርካታ ቁጥር ያለዉ ገንዘብ በቁጥጥር ስር አዉሏል፡፡

በጥቁር ገበያ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ5 ሚሊዬን ብር በላይ እንዲሁም በየኬላዎች በተደረገዉ ድንገተኛ ፍተሻ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 1.6 ሚሊዬን ብርን ጨምሮ 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በድምሩ 10.6 ሚሊዬን የኢትጵያ ብር በላይ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በኮሚሽኑ የሙስና ፣ ገቢዎች እና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ግርማ ተሰማ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝዉዉሩን ለመቆጣጠር ከሌሎች የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን በመግለጽ ህብረተሰቡም ከጸጥታ አካሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎች ሁለት ወራት 42 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ
******************
(ኢ.ፕ.ድ)

የገቢዎች ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች የ2013 በጀት አመት የገቢ አሰባሰብ እቅድ እና በበጀት ዓመቱ የሁለት ወራት አፈፃፀም ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በዉይይቱ ወቅት እንደተገለፀው በሀምሌና በነሀሴ ወር 39 ቢሊዮን 430 ሚሊዮን 954ሺ 692 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 42 ቢሊዮን 204 ሚሊዮን 26 ሺብር በመሰብሰብ የእቅዱን 107 በመቶ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ሁለት ወር ጋር ሲነጻጸር የ10.7 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በ2013 በጀት አመት ከሀገር ውስጥ ታክስ ብቻ 164.29 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን ይህም በ2012 ከሀገር ውስጥ ታክስ ከተሰበሰበው 128.67 ቢሊዮን አንጻር የ28 በመቶ ወይም የ35.62 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ነው የተገለጸው፡፡

እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል የተረጋጋ እና ጥሩ አቅም ያለው ሰራተኛ መኖሩና በሰራተኛውና በአመራሩ መካከል ያለው ተቀራርቦ መስራት ከምንጊዜውም በላይ እያደገ በመሆኑና ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በፈቃደኝነት የመክፈል ባህል እዳበረ በመምጣቱ ለዕቅዱ መሳካት አስተዋፅኦ አበርክቷል ነው የተባለው፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው “ያቀድነውን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ለመሰብሰብ መስራት አለብን፡፡ለዚህም ሰው ይቻላል ብሎ ከተነሳ የሚቻልበትን መንገድ ስለሚቀይስ ይቻላል፤በአንጻሩ አይቻልም ብሎ ከተነሳ የማይችልበትን መንገድ ብቻ ስለሚያይ ስለማይሳካለት ያቀድነውን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ለመሰብሰብ ‹ይቻላል!› የሚል መርህ አንግበን ልንሰራ ይገባል” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 602 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የ 12 ሰዎች ህይወት አለፈ
****************************
(ኢፕድ)
ባለፉት 24 ሰዓታት ለ8 ሺህ 221 ሰዎች በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 602 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተረጋግጧል።

12 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ሲያልፍ በቫይረሱ የሞቱት ቁጥር 1072 ደርሷል።

በዛሬው እለት 553 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 27 ሺህ 638 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።

ሌሎች 289 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል።
አጠቃላይ እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 67ሺህ 515 ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 38 ሺህ 803 ደርሷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቡለን ወረዳ ተከስቶ በነበረው ግጭት ከተፈናቀሉ ዜጎች ጋር ተወያዩ
*****************************
(ኢፕድ)
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከሳምንት በፊት ተከስቶ በነበረው ግጭት ከተፈናቀሉ ዜጎች ጋር ተወያዩ።

በወረዳው ኤዻር ቀበሌ በታጠቁ ሃይሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በመገደላቸው ተከትሎ በአካባቢው ሰላምን ለማስፈንና ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አደም መሃመድ እና የሰላም ሚኒስተር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በቦታው ተገኝተው ነዋሪዎችን አነጋግረዋል ።

ውይይቱ የተካሄደው ከአይጋሊ፣ሞዛንቢስ፣ኤዻር እና ዶቢ ቀበሌዎች ሲኖሩ ከነበሩ ተፈናቃዮች ጋር ነው።

በቀጠናው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በአጥፊዎች ላይ አስፈላጊውን ሁሉ ርምጃ በመውሰድ እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

ጉዳቱ የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው መንግስት በአካባቢው በዘላቂነት መፍትሄ በመስጠት ደህንነታቸውን እንዲያስጠብቅና ሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ምንጭ የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ የብር ኖት ስርጭት መጀመርን
በማስመልከት በነገው ዕለት እሁድ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች በተመረጡ የባንኩ ቅርንጫፎች የባንክ አግልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።
በእነ አቶ ጁሀር መሀመድ አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ
*******************^
(ኢ ፕ ድ)

በእነ አቶ ጁሀር ሲራጅ መሀመድ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ አድናን፤ እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN)፤ አቶ ደጀኔ ጉተማ ፤ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና አቶ ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስር የክስ መዝገቦች ከፈተ።

በ24ቱ ሰዎች ላይ እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድግ፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል የፌደራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215 አስር ተደራራቢ ክሶች ያስከፈተ ሲሆን፤ ተከሳሾቹም መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡