Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
ተጨማሪ 1 ሺህ 368 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የ 25 ሰዎች ሕይወትም አልፏል
********
(ኢ.ፕ.ድ)
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገው 19 ሺህ 776 የላቦራቶሪ ምርመራ 1 ሺህ 368 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በዚህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 39ሺህ 33 ደርሷል።

የተጨማሪ 25 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ፤በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 662 መድረሱ ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት 251ሰዎች በጽኑ ሕክምና ላይ ይገኛሉ፤ 23ሺህ 889 ደግሞ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር እንደሆነ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 567 ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 14ሺህ 480 ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስካዛሬ ድረስ 736ሺህ 904 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።
አዲስ የተጀመሩት ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ነባር የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማጉላት የታለሙ ናቸው - ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
***************
(ኢ.ፕ.ድ)

ሥነ-ምኅዳርን አማክለው አዲስ የተጀመሩት ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ነባር የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማጉላት፣ የአገልግሎት ዘርፍን ለማስጀመር እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚ ሥራን ለመፍጠር የታለሙ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ስለፕሮጀክቶቹ በሰጡት ገለጻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኮይሻ ስለሚሠራው ፕሮጀክት በሰጡት ገለጻ፣ “ሥነ ምኅዳርን ያማከለው አዲሱ ፕሮጀክታችን ነባር የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማጉላት፣ የአገልግሎት ዘርፍን ለማስጀመር እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ሥራን ለመፍጠር የታለመ ነው።” ብለዋል።

ኮይሻ በለምለም ኮረብታዎች፣ እንደ ምንጣፍ በተዘረጉ መስኮች እና በጥቅጥቅ ደን የታደለች መሆኗን እንዲሁም በመጠናቀቅ ላይ ያለው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ እና የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክም በአቅራቢያው እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

ወንጪ ላይ የሚከናወነውን ፕሮጀክት በተመለከተ ደግሞ፣ “ወንጪ ተጨማሪ የቱሪዝም መስሕብነት ዐቅም እንዲኖራት፣ ቋሚ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በቂ መተዳደሪያ ለማግኘት እንዲችሉ” የታለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ቆርጦ የተነሳውን የደፋሮቹን የ‘ገበታ ለሀገር’ ቤተሰብን በመቀላቀል ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ባንኩ በኮቪድ-19 ምክንያት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ሰጥቶት የነበረውን ወርሃዊ የክፍያ እፎይታ ጊዜ ማጠናቀቁን ገለጸ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርኝሽ ምክንያት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ተበዳሪዎች ሰጥቶት የነበረውን ወርሃዊ የክፍያ እፎይታ ጊዜ ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ጫና ታሳቢ በማድረግ ባንኩ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብድር ተበዳሪዎች ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም የቆየ የሶስት ወር የእፎይታ ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል።

በመሆኑም የእፎይታ ጊዜው በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም መጠናቀቁንና ደንበኞች ክፍያቸውን ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ መክፈል መጀመር እንዳለባቸው ባንኩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሶስት ወር የብድር እፎይታ ጊዜ መሰጠቱን አስመልክቶ አውጥቶት በነበረው መግለጫ የእፎይታ ጊዜ ቢሰጥም የብድር መክፈያ ጣሪያው እንደማይራዘም ገልጾ ነበር።

”ወርሃዊ ክፍያውን መክፈል አቅም ያላቸው ደንበኞች የወርሃዊ ብድር ክፍያቸውን እንዲከፍሉ ይበረታታሉ” ሲል ባንኩ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ባንኩ በሰጠው የእፎይታ ጊዜ ውስጥ 542 ሚሊዮን ብር ገንዘብ መሰብሰብ ይችል እንደነበር በመግለጽ፤ ”በወረርሽኙ ምክንያትም ወደቀጣይ ጊዜ አራዝሚያለሁ” ማለቱ የሚታወስ ነው።
ምንጭ ኢዜአ
የአማራ ክልል በ2012 በጀት ዓመት ከ158 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት መሳቡን አስታወቀ
***************************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- አማራ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት 158 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
ኢንቨስትመንቶችን ከጥፋት ቡድኖች ለመጠበቅም የኢንቨስትመንት ፖሊሶች ተመድበው ተገቢው ጥበቃ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በተመለከተ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2012 በጀት ዓመት ለሁለት ሺህ 222 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 158 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ካፒታል ላስመዘገቡ ሁለት ሺህ 908 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰጥቷል። ይህም ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። በ2012 በጀት ዓመት የኮቪድ -19 ተጽእኖ ቢኖርም በክልሉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት መመዝገቡን አመልክተዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባት ሲችሉም 395 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አመልክተው፣ ባለሀብቶቹ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በግብርና ዘርፎች መሰማራታቸውንና፤ የኢንቨስትመንት ፈቃዱን ከወሰዱት ከ70 በመቶ የሚሆኑት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።
በተለይ ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ እስካሁን ልማት ላይ ውሎ የማያውቅ 60ሺህ ሄክታር መሬት በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ዕድገት የተመዘገበ መሆኑን አመልክተው፤ የኢንቨስትመን ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች ከቁጥራቸው ብዛትና ባስመዘገቡት ካፒታል አንጻር ሲታይ ባህር ዳር ከተማ፤ ሰሜን ሸዋ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ አዊን ዞን ጨምሮ ምዕራብ ጎጃምና ጎንደር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ክልሉ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት በቂ የመሠረተ ልማቶች ያልተዘረጉለት መሆኑን አውስተው፣ በተለይ በክልሉ ውስጥ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫና ማከፋፈያ ጣቢያ ባለመኖራቸው ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለኢንቨስትመንትና ግንባታቸው
ለተጠናቀቁት ኢንዱስትሪዎች ቀዳሚ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱን ለመቅረፍም አሁንም ገና ብዙ ሥራዎችን የሚጠይቅ ቢሆንም በደብረ ብርሃን፣ በደብረ ታቦር ቋሚና ተንቀሳቃሽ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያና ማሰራጫ ጣቢያዎች መተከላቸውን አመልክተዋል።
በቡሬና ደብረማርቆስ ከተሞች ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ በፌዴራል መንግሥት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ (ሰብስቴሽን) ለመገንባት ዕቅድ ቢይዝም ቶሎ ወደ ተግባር አለመግባቱንአመልክተው ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ማምረት ቢገቡም በሙሉ አቅም ለማምረት የኃይል እጥረት ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል ብለዋል።
ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ስልታዊ በሆነ መንገድ በመፍታት፣ የመሬት አቅርቦት በማመቻቸትና ያልተንዛዛ አገልግሎት በመስጠት ረገድ አሁንም በክልሉ በሚገኙ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የአመለካከት ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ እነዚህን ችግሮች ማረም ከተቻለ የክልሉን የኢንቨስትመንት ፍሰት በእጅጉ መጨመር እንደሚቻል ተናግረዋል።
«ክልሉ ለኢንዱስትሪና ለኢንቨስትመንት ዋስትና የሚሰጥና የተመቸ እንዲሆን እየሰራን ነው» ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ በአጭር ጊዜ በኢንቨስትመንቶች ላይ የጥፋት ኃይሎች ጉዳት እንዳያደርሱ ለመጠበቅ ኢንቨስትመንቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሰለጠኑ የኢንቨስትመንት ፖሊሶችን መድበናል፣በረጅም ጊዜ ደግሞ ኅብረተሰቡም ሆነ አመራሩ ኢንቨስትመንት ዕድል መሆኑን ተገንዝቦ እንዲጠቀምበትና እንዲጠብቀው የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።
አቶ ተፈራ እንዳሉት የኢንቨስትመንት ፖሊስ የሚል መዋቅር ዘርግተን በኢንቨስትመንቶች ላይ ተገቢ ጥበቃ እየተደረገ ነው። ስለዚህ የክልሉ የኢንቨስትመንት ሥራ አስተማማኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም ኮቪድ-19 የሚያሳድረው ተጸእኖ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ዕቅድ መያዙን አመልክተው፤ እስካሁንም ሆነ ወደፊት በኢንቨስትመንት ስም መሬት አጥረው እንዳይቀመጡና በአግባቡ እንዲያለሙ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
«በክልሉ የልማት ሥራዎችን ለማደናቀፍና ከግራም ሆነ ከቀኝ ክልሉን ለማተራመስ፣ ግርግርና ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፤ » ያሉት አቶ ተፈራ፤ የክልሉን መልማት የማይፈልጉ አካላትን የአማራ ሕዝብ ጠንቅቆ ስላወቃቸው መቼም ቢሆን አይሳካላቸውም፤ በበጀት ዓመቱም የተመዘገበው ኢንቨስትመንትም በሕዝቡ፣በመንግሥትና በጸጥታ ኃይሉ የተገኘ የተቀናጀ ሥራ ውጤት መሆኑንና ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ የሚገኙት፤ ኮምቦልቻና አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ሥራ የጀመሩ መሆኑን አውስተው በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ሼድ ሥራ የጀመረ ሲሆን ቀሪዎቹ ሼዶችና የባህዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በአጭር ጊዜ የሚሟሉ ነገሮች ተሟልተው ወደ ሥራ እንደሚገቡ አብራርተዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ግንባታቻው ተጠናቆ ማምረት ሲጀምሩም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል። ክልሉን ሆነ አገሪቱን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር ድርሻቸው የጎላ ነው ያሉት አቶ ተፈራ፣ በቀጣይም ክልሉ ለልማት የተመቸና የኢንቨስተሮችን ቀልብ የሚስብ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 18/2012
በጌትነት ምህረቴ
የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ፀብ -ጫሪነትን በመሸሽ ወደ አማራ ክልል በመግባት ላይ መሆናቸው ተገለጸ
**********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ፀብ ጫሪነት በመሸሽ ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ አማራ ክልል የሚገቡ የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይሎች የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ፀባ ጫሪነት በመሸሽ ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ አማራ ክልል እየሸሹ ነው። ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።
ከሰሞኑ ብቻ በሰሜን ጎንደር ከሰላሳ የሚበልጡ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአጥፊነት መልዕክትን በመክዳት ወደ አማራ ክልል ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው መግባታቸውን ያስታወቁት ኃላፊው፤ ከነዚህ መካከል አንዳንዶች የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ያለባቸው የክልሉ ነዋሪዎች ልጆች መሆናቸውን አመልክተዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ የትግራይ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን ገልጸዋል።ይህም ክልሉልዩ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ መፈረካከስ እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል።
ከትግራይ ክልል መንግሥት ሸሽተው የሚመጡት ዜጎቻችን በመሆናቸው ክልላችን በሚታወቅበት እንግዳን በአክብሮት የመቀበል ባህላችን ተቀብሎ እንክብካቤ እያደረገላቸው ነው ብለዋል።
ህወሃት በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶችን በወታደርነት በመመልመል ለጦርነት እያዘጋጀች መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ የትግራይ ሕዝብ የክልሉ መንግሥት እያደረገ ያለው ትክክል አይደለም ብሎ እንደሚያምን በፈቃዳቸው ወደ አማራ ክልል ከገቡ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መረዳት መቻሉን አስታውቀዋል።
በግዳጅ የሚታጠቁ ወጣቶች ከእነትጥቃቸው በተደጋጋሚ ወደ አማራ ክልል እየገቡ ናቸው።በአማራ ክልል በኩል በእንደዚህ ዓይነት መልኩ ሰው እንዲመጣ አንፈልግም።ምክንያቱም ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ብለን እናምናለን ሲሉ ኃላፊው አመላክተዋል።
ከትግራይ ክልል ጋር በምንዋሰንበት አካባቢ ለእረጅም ጊዜ የቆየ የአማራ ክልል ጥያቄ የሆነ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ መኖሩን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የህወሃት የአድዋ ቡድን የጦርነት ዝግጅት ለሀገር እድገት እና አንድነት ተገቢ አይደለም ብለዋል። በድንበር አካባቢ ወደ ጦርነት ለመግባት የማኮብኮብ ዓይነት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል።
«የአማራ ክልል ወደ ጦርነት አይገባም። የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች ሁለት ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው።በግልፅ እንደሚታወቀው አብረው ተጋብተው እና ተዋልደው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው።ምንም ዓይነት ጉንተላ እና ፀብ-ጫሪነት በትግራይ ክልል መንግሥት በኩል ቢኖርም መቼም ቢሆን ሁለቱ ሕዝቦች ወደ ጦርነት ይገባሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው» ብለዋል ።
ከአማራ ክልል በኩል እስከዛሬ ድረስ ምንም ዓይነት ትንኮሳ የለም ወደፊትም አይኖርም የሚሉት ኃላፊው፤ በእኛ በኩል እየጠየቅነው ያለው የሕዝብ ጥያቄ የሆነውን የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ነው። ይህ ደግሞ ሕጋዊ ጥያቄ ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው የፌዴራሉ መንግሥት ሕጋዊ አሠራር ተከትሎ የራሱን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል እንጠብቃለን ሲሉም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 18/2012
ሙሉቀን ታደገ
ነባሮቹን መዝናኛ ስፍራዎች በአዲስ መልክ ለመስራት ታቅዷል
******************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማን ነባር የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ለማደስና ለህዝብ አገልግሎት ምቹ ለማድረግ መታቀዱን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛዎቹ ነባር መናፈሻ ቦታዎች ወንዝን ተከትለው የተሰሩ ናቸው።
ከአዲሶቹ መዝናኛ ስፍራዎች አንፃር ሲታይ ነባሮቹ መዝናኛ ስፍራዎች ሰዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉባቸው ነገሮች እንደሌሏቸው የሚናገሩት አቶ ዋለልኝ፤ በቂ ማረፊያ ቦታ፣ የመብራት አገልግሎት፣ ፈጣን የሆነ የምግብ አገልግሎትና ሌሎች አዝናኝ ነገሮች እንደሚጎድላቸው አመልክተዋል። መዝናኛ ስፍዎቹ በትክክለኛ መንገድ እንዲገነቡ የማድረግ እቅድ እንዳለም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ዋለልኝ ገለፃ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአረንጓዴ አካባቢ የማልማት ስራ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። በተለይ ከተማዋ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን አረንጓዴ የልማት ቦታዎች አስፈላጊ ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሁሉን ያማከሉ አረንጓዴ ቦታዎች አልነበሩም።
በተለያዩ ምክንያቶች ከተማዋ ተፈጥሮአዊ መስህቦ ቿን ሳትጠቀም መቆየቷንና የተፈጥሮ ሀብቶቿ እየባከኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይ ወንዞች ቀደም ባሉት ዘመናት አሳ ይለማባቸውና ሌሎች የግብርና ምርቶች ይመረቱባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ለመዋኛና ለመዝናኛነትም ይውሉ እንደነበርም ገልፀዋል። ባለፉት አስርት ዓመታት ወንዞች ወደ ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃነት ተቀይረው መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ዋለልኝ አባባል፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው ውጤታማ ስራ ለውጦች እየመጡ ነው። በቀጣይ ዓመታት የወንዝ ዳርቻዎችን ተከትሎ ሰፋፊ የአረንጓዴ ቦታ በመፍጠር ለከተማዋ ህዝብ ምቹ መዝናኛ እንዲሁም ጎብኚዎቿን ሳቢ እንድትሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው። አጠቃላይ 56 ኪሎ ሜትር በቀበና፣ ቁርጥሜ፣ በቀጨኔ እንዲሁም በሌሎች ወንዞች ላይ የአረንጓዴ ፕሮጀክት ተጀምሯል።
ከዚህም ውስጥ ለማሳያነት ከሸራተን እስከ እሪ በከንቱ ድረስ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ጠቅሰዋል። የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በፍጥነት እንደተሰራና መናፈሻ ቦታው ሰፊ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ በፍጥነት መሰራት ለሌሎች ስራዎች እንደ ተሞክሮ እየጠቀመ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ከእንጦጦ አናት ጀምሮ መጀመሩን አመልክተው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል የእንጦጦ ፓርክ ግንባታም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውኖ ለማየት መቻሉንም አመልክተዋል። በቀጣይ ዓመታትም በወንዝ መዳረሻ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ወንዞችን በማጣራት፣ ግራና ቀኝ የአረንጓዴ ቦታዎችን ሳቢ ማድረግ ሰዎች በስፍራዎቹ እንዲዝናኑ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናቀቁም አብራተዋል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2012
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል
**********************************
(ኢፕድ)
ቢሾፍቱ፡- ባለፈው በጀት ዓመት 2012ዓ.ም በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ከ 100ሺ በላይ ዜጎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስክም ውጤታማ ስራ መሰራቱን አመለከተ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንድአርጋቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎችና የሚሲዮን መሪዎች ዓመታዊ ስብሰባ ትናንት " ዲፕሎማሲ ተልዕኮችን ለአገራዊ ብልጸግናችን" በሚል መሪ ቃል በቢሾፍቱ ከተማ ኩሪፍቱ ሪዞርት ሲጀመር እንደገለጹት፤ በ2012 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማ ስራዎችን አከናውናለች። በተለይ በዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ስራዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ከ100ሺ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
መንግስት በውጭ ለሚኖሩት ዜጎች ክብር የሚሰጥና ለመብታቸው መከበርም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኘ የገለጹት አቶ ገዱ ፤ በ2012 በጀት ዓመትም በዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ በውጭ አገራት ለሚኖሩት ደግሞ መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር ውጤታማ ስራዎች እንደተሰሩ ተናግረዋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችም ያጋጠሟቸው የተለያዩ ችግሮች ለማቃላል ሰፊ ጥረት መደረጉን ገልጸው፤ በተሰሩት ውጤታማ ስራዎች የዜጎችን መብቶችና ጥቅሞች በተቻለ መጠን ለማስጠበቅ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ሊባል የሚችል መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በድርድር ሂደት የተገኘውን ድል በፐብሊክ ዲፕሎማሲ በማጀብ የሀገራችን አቋም የሆነውን ፍትሀዊና ምክንያታዊ የተጠቃሚነት መርህን ለማስረዳት እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለመሰብሰብ የረዳ ጠንካራ የገፅታ ግንባታ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በህዳሴ ግድብ የበኩላቸውን የገንዘብና የዲፕሎማሲ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የተሰራው ስራም ስኬታማ እንደነበር አመልክተው ፤ይህ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስክም ውጤታማ ስራ እንደተሰራ ጠቁመው፣ ለአብነትም ከ200 በላይ ከሚሆኑ የዓለም አቀፍ ኩባያዎችና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸው ለማፍስስ የቅድመ ስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል።
በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ከሚገኙ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት በማድረግ ነባር እና አዳዲስ ስትራቴጂክ አጋሮችን በማፍራት በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ድጋፎች እንዲያገኝ በማድረግ አወንታዊ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በኢጋድ ማዕቀፍ በክልሉ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርን በመፍጠር፣ በሀገራችን ሰላም፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲኖር፣ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረምና በቀጠናው ሰላም የማስከበር ስራዎች ረገድ የተሰሩ ስራዎች በበጎ የሚነሱ የዲፕሎማሲው ስራዎች ውጤቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በአሜሪካን የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ፍጹም አረጋና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ተሸመ ቶጋ እንደገለጹልን ስብሰባው የአገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሁም ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ለመሳብ እና ሌሎች የዲፕሎማሲ ስራዎችን በትጋትና በውጤት ለማሳካት ስንቅ ይሆናል።
በተለይ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አምባሳደሮቹና ከፍተኛ ሃላፊዎቹ የሚሰጡትን አስተያየት እንደ ተጨማሪ ግብዓት በማካተት በመጪው ዓመት ፖሊሲው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
በስብሰባው ላይ የለውጥ ሥራዎች እና የመደመር ፍልስፍና መሰረታዊ ሃሳቦች፣ የፖለቲካ ብልጽግና እና የመደመር ገጽ፣ የኢኮኖሚ ብልጽግና እና የመደመር ገጽ፣ የሀገሪቱ የቀጣይ የአስር ዓመታት መሪ የልማት እቅድ፣ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤዎች በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ፣ ስትራቴጂክ አመራር እና የውጤት ተኮር ዕቅድ አስተቃቀድ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።
እንዲሁም የእያንዳንዱ ኤምባሲ የ2012 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀምና ሪፖርት ግምገማና በልዩ ልዩ ሀገራዊ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ የውጭ ግንኙነት ፈታኝ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ እንደሚያዝ ይጠበቃል።
ዓመታዊ ስብስባው ለ15 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ160 በላይ የሚሲዮን መሪዎችና የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ኃላፊዎች ይሳተፉበታል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2012
ነባሮቹን መዝናኛ ስፍራዎች በአዲስ መልክ ለመስራት ታቅዷል
******************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማን ነባር የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ለማደስና ለህዝብ አገልግሎት ምቹ ለማድረግ መታቀዱን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛዎቹ ነባር መናፈሻ ቦታዎች ወንዝን ተከትለው የተሰሩ ናቸው።
ከአዲሶቹ መዝናኛ ስፍራዎች አንፃር ሲታይ ነባሮቹ መዝናኛ ስፍራዎች ሰዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉባቸው ነገሮች እንደሌሏቸው የሚናገሩት አቶ ዋለልኝ፤ በቂ ማረፊያ ቦታ፣ የመብራት አገልግሎት፣ ፈጣን የሆነ የምግብ አገልግሎትና ሌሎች አዝናኝ ነገሮች እንደሚጎድላቸው አመልክተዋል። መዝናኛ ስፍዎቹ በትክክለኛ መንገድ እንዲገነቡ የማድረግ እቅድ እንዳለም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ዋለልኝ ገለፃ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአረንጓዴ አካባቢ የማልማት ስራ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። በተለይ ከተማዋ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን አረንጓዴ የልማት ቦታዎች አስፈላጊ ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሁሉን ያማከሉ አረንጓዴ ቦታዎች አልነበሩም።
በተለያዩ ምክንያቶች ከተማዋ ተፈጥሮአዊ መስህቦ ቿን ሳትጠቀም መቆየቷንና የተፈጥሮ ሀብቶቿ እየባከኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይ ወንዞች ቀደም ባሉት ዘመናት አሳ ይለማባቸውና ሌሎች የግብርና ምርቶች ይመረቱባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ለመዋኛና ለመዝናኛነትም ይውሉ እንደነበርም ገልፀዋል። ባለፉት አስርት ዓመታት ወንዞች ወደ ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃነት ተቀይረው መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ዋለልኝ አባባል፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው ውጤታማ ስራ ለውጦች እየመጡ ነው። በቀጣይ ዓመታት የወንዝ ዳርቻዎችን ተከትሎ ሰፋፊ የአረንጓዴ ቦታ በመፍጠር ለከተማዋ ህዝብ ምቹ መዝናኛ እንዲሁም ጎብኚዎቿን ሳቢ እንድትሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው። አጠቃላይ 56 ኪሎ ሜትር በቀበና፣ ቁርጥሜ፣ በቀጨኔ እንዲሁም በሌሎች ወንዞች ላይ የአረንጓዴ ፕሮጀክት ተጀምሯል።
ከዚህም ውስጥ ለማሳያነት ከሸራተን እስከ እሪ በከንቱ ድረስ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ጠቅሰዋል። የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በፍጥነት እንደተሰራና መናፈሻ ቦታው ሰፊ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ በፍጥነት መሰራት ለሌሎች ስራዎች እንደ ተሞክሮ እየጠቀመ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ከእንጦጦ አናት ጀምሮ መጀመሩን አመልክተው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል የእንጦጦ ፓርክ ግንባታም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውኖ ለማየት መቻሉንም አመልክተዋል። በቀጣይ ዓመታትም በወንዝ መዳረሻ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ወንዞችን በማጣራት፣ ግራና ቀኝ የአረንጓዴ ቦታዎችን ሳቢ ማድረግ ሰዎች በስፍራዎቹ እንዲዝናኑ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናቀቁም አብራተዋል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2012
ላለፉት 27 አመታት የተዘነጋው የህገ-መንግስቱ ቅርስ
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በህዳር ወር 1987 ዓ.ም ከመጽደቁ በፊት የህገ መንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን ስብሰባውን ያካሄደበት ታሪካዊው የመብራት ሃይል አዳራሽ አስታዋሽ አጥቶ እንዲህ በሚያሳዝን መልኩ ታሪክ ሆኗል።
ከህገ መንግስቱ ባሻገር ታሪካዊነቱ የጎላው ይህ አዳራሽ ላለፉት 27 አመታት አስታዋሽ አጥቶ ታሪኮ ደብዝዞ በምስሉ ላይ በሚታየው መልኩ ፈራርሶ ይገኛል።
ላለፉት 27 አመታት ስለ ህገ መንግስት ሲዘምሩ የነበሩት አካላት ቅርሱን በዚህ ሁኔታ ስለምን ተውት?
አሁንም የሚመለከተው አካል ለዚሁ ታሪካዊ አዳራሽ ትኩረት ይስጥ እንላለን!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ተወያዩ
**********************
(ኢፕድ)
የሱዳን የሽግግር መንግሥት የተመሰረተበት አንደኛ ዓመት ክብረ በዓል ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በካርቱም ተገኝተዋል
ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስካሁን ድረስ የሱዳን መንግሥት በስኬት ያጠናቀቃቸውን ምዕራፎች እንዲሁም፣ የፖለቲካ ውይይቶች በቀጣይነት መከናወናቸውን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ግንኙነትም አስመልክተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ዕጣ የተሳሰረ መሆኑን እና የተመሰረተውም ለረዥም ጊዜ በዘለቀው ታሪካዊ እና ስትራተጂያዊ ግንኙነት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። “አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሀገር ነን” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፣ የሕዳሴውን ግድብ እና የድንበር ማካለል ሥራን ጨምሮ የትኛውም ጉዳይ ቀጣይነት ባለው እና በመተማመን ላይ በተመሰረተ ውይይት አማካኝነት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክም በበኩላቸው፣ የሁለቱ ሀገራት ተመጋጋቢ ተፈጥሮ ለጋራ ጥቅም በትብብር እንዲሰሩ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ትሥሥር በማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚ ማሳደጋቸው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን እንዲሁም አፍሪካን በኢኮኖሚ የማነቃቃት ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ሁለቱም አካላት አንዳቸው የአንዳቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በአጋርነት መቆማቸውን እንደሚቀጥሉ እና ማንኛውንም ጉዳይ በቀጣይ ውይይት እና ድርድር መፍታታቸውን እንድሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኮሮናቫይረስ እየተስፋፋ ቢሆንም ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ ነው - ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ
***********************
የኮሮናቫይረስ እየተስፋፋ ቢሆንም ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ በመሆኑ በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ገለጹ።
የቀጣዩ ዓመት ትምህርት ምዝገባ ከነገ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች እንደሚጀመር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ምዝገባ እንዲያከናውኑ ተፈቅዷል ብለዋል።
የበሽታው ሁኔታ እየተስፈፋ ቢሆንም የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ ሆኑ መገኘቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ወደ መማር ማስተማር ተግባር በሚገባበት ወቅት ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራ ገልጸው፣ ማስክ፣ የእጅ ማፅጃ እና መሰል አቅርቦቶችን ከባላድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ተማሪዎች ማስክ በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና እጅን በመታጠብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛ ሴሚስተር ያለፋቸውን ትምህርቶች ማካካሻ ለመስጠት መታሰቡንም ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ገልጸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል ።
በሀሰተኛ የብር ኖቶች 20 ኩንታል ጤፍ የገዙት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
********************************
(ኢፕድ)
በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ ሊቫኖስ ቀበሌ ልዩ ቦታው ሮቢት እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ነሐሴ 18/2012 ዓ.ም በሀሰተኛ የብር ኖት 20 ኩንታል ጤፍ ለመግዛት የሞከሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም 90ሺ 1 መቶ ሀሰተኛ የብር ኖት፤ 13ሺ 7 መቶ ህጋዊ የብር ኖት፤ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከ6 መሰል ጥይት፤ ስድስት ተንቀሳቃሽ ስልክ እንደተገኘባቸው የጎዛምን ወረዳ ፖሊስም ገልጿል።
የወረዳው የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ፀጋዬ ጋሹ እንደገለፁት በመጭው አዲስ ዓመት በዓል ወቅት ህብረተሰቡ ልዩ ልዩ ግብይቶችን ሲያከናውን ለእንዲህ አይነቱ የወንጀል ድርጊት ሰለባ እንዳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥምም ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን የመከላከል ተግባሩን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል ሲል ከጎዛምን ወረዳ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኔዘርላንድ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀዳሚ መዳረሻ አገር ሆነች
************************
(ኢ ፕ ድ)
በ2012 በጀት ዓመት ኔዘርላንድ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀዳሚ መዳረሻ አገር መሆኗ ተገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ በ2012 በጀት አመት አበባ ፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት የኤሌክትሪክ ውጤቶች፣ ጫማ ፣ ቆዳ ማርና ሰም፣ የቅባት እህሎች የአልኮል መጠጦች፣ ጫት፣ ሻይ ብረትና የመሳሰሉትን ወደ ኔዘርላንድስ ልካለች።
ከተላኩት የወጪ ንግዶችም ኢትዮጵያ 320 ሚሊዮን 162 ሺህ የአሜሪካን ዶላር አግኘታለች።
ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ቡና ጫማ፣ አበባ፣ የቆዳውጤቶችን፣ የቅባት እህሎችን እና ሌሎች ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸውም ምርቶች በመቀበል አሜሪካ በሁለተኛነት ስትቀመጥ፤ በተጠቀሰው በጀት አመት 295 ሚሊዮን 809 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ችላለች፡፡
ከሶማሊያ 291 ሚሊዮን 855 ሺህ ዶላር፣ ከሳውዲ አረቢያ 214 ሚሊዮን 652 ሺህ፣ ከጀርመን 174 ሚሊዮን 283 ሺህ ዶላር መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1545 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የ 17 ሰዎች ህይወት አለፈ
****************************
(ኢፕድ)
በ24 ሰዓታት ለ18 ሺህ 778 ሰዎች በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 1545 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተረጋግጧል።
17 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ሲያልፍ በቫይረሱ የሞቱት ቁጥር 709 ደርሷል።
በዛሬው እለት 534 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች
ቁጥር 15 ሺህ 796 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።
ሌሎች 290 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል።
አጠቃላይ እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 43 ሺህ 688ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ ያለባቸው
ሰዎች ቁጥር 27 ሺህ 181 ደርሷል።
ከነገ ጀምሮ የሚተገበር የኢንተርኔት እና የድምፅ ጥቅል ቅናሽ ተደረገ
***************************
(ኢፕድ)
ኢትዮ ቴሌኮም ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በኢንተርኔት ጥቅል እና በድምፅ ጥቅል አገልግሎቶቹ ላይ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የ3 አመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እና የ2013 በጀት አመትን ዋና የትኩረት አቅጣጫ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በኢንተርኔት ጥቅል ላይ 35 በመቶ እንዲሁም በድምፅ ጥቅል ላይ የ29 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ገልፀዋል።
የሞባይል ድምጽ እና ዳታ ጥምር አገልግሎት 28 በመቶ እንዲሁም በፕሪሚየም ያልተገደበ የድምጽ ጥቅል አገልግሎት 21 በመቶ ቅናሽ ተደርጓልም ብለዋል፡፡
በፕሪሚየም ያልተገደበ የዳታ ጥቅል አገልግሎት 21 በመቶ እንዲሁም በፕሪሚየም ያልተገደበ የድምጽ እና ዳታ ጥቅል አገልግሎት 20 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል፡፡
በፕሪሚየም ፕላስ ያልተገደበ የጥቅል አገልግሎት 16 በመቶ እንዲሁም በሳተላይት አገልግሎት ላይ እስከ 61 በመቶ ቅናሽ መደረጉም ተገልጿል፡፡
በቤትዎ ይቆዩ የጥቅል አገልግሎት ላይ የ59 በመቶ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ድረስ ባለበት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያውያንን አዲስ ዓመት ምክያት በማድረግ ለአዲስ አመት የአደይ አበባ ጥቅል አገልግሎት 53 በመቶ እና በዓለም አቀፍ አየር ሰአት አገልግሎት ላይ የ100 ፐርሰንት የአየር ስጦታ ለደንበኞች አቅርቧል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ባለሙያዎች በአፍሪካ አቪየሽን ታሪክ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል የአውሮፕላን ክንፍ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ አደረጉ
*********************************
(ኢፕድ)
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች በአፍሪካ አቪየሽን ታሪክ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል የአውሮፕላን ክንፍ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ /winglet modification/ አደረጉ።
ማሻሻያው የተደረገው አየር መንገዱ በሚያበራቸው የቦይንግ 767 አውሮፕላኖች ላይ ሲሆን፣ ይህም በአመት እስከ 500 ሺህ ጋሎን ነዳጅ እንዲቆጥብ ያስችለዋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ማሻሻያው 277 ሺህ ሜትሪክ ቶን የካርበን ልቀትንም የሚያስቀር በመሆመኑ አየር መንገዱ በአካባቢ ጥበቃ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።
69 የሚሆኑ የአየር መንገዱ የአውሮፕላን አካል ጥገና ባለሙያዎች ሌት ተቀን እና በእረፍት ቀናቸውም በመስራት ጭምር ፕሮጀክቱን በስኬት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።
የህወሓት/ ትህነግ አመራሮችና ጥቅመኞቻቸው በራያ ወረዳዎች የመሬት ወረራ እያካሄዱ ነው ሲል የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ
*********************
(ኢ ፕ ድ)
"የህወሓት/ ትህነግ አመራሮችና ጥቅመኞቻቸው በትግራይ ክልል በተካለሉት የራያ ወረዳዎች ላይ ስልታዊና ዓይን ያወጣ የመሬት ወረራ እያካሄዱ ነው" ሲል የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) አስታወቀ።
“መሬታችን ያለ ሕጋዊ መንገድ አንሰጥም” ያሉ ገበሬዎች እየታሰሩ ነው ያለው ፓርቲው፤ በዚህ ምክንያትም በወፍላ ወረዳ 50፣ በራያ ዓዘቦ ወረዳ በወራባዬ ቀበሌ 13 ገበሬዎች መታሰራቸውን፤ በራያ-አላማጣ ወረዳም 110 ገበሬዎችን ያለ ካሳ ክፍያ መፈናቀላቸውን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ይህን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና የሕዝባችን እስርና እንግልት አጥብቆ ያወግዛል ያለው ፓርቲው፤ የፌዴራል መንግሥትና የሚመለከታቸው የሰዓአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም መፍትሔ እንዲሰጡ፤ የሚዲያ ተቋትም ተግባሩን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል።
በሃገራችን የሰሜን ምሥራቁ ክፍል በተደጋጋሚ የአንበጣ መንጋ መከሰት በራያ አከባቢዎች በሰብልና በአዝርእት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ያለው ፓርቲው፤ የክልሉ መንግሥት/ትህነግ እንደ ኮሮናው ሁሉ ይህን የተፈጥሮ አደጋ ከመከላከል ይልቅ በዝምታ እየተመለከተው ይገኛል። ይባስ ብሎም ገበሬዎችና ወጣቶች በጋራ በመሆን በሰው ኃይል የአንበጣ መንጋውን መከላከል እንዳይችሉ በምርጫ ምዝገባና ካርድ ማውጣት ሰበብ በተስፋና በጉጉት የሚጠበቁ የሰብልና የአዝርዕት ቡቃያዎች ለከፍተኛ ውድመት እንዲጋለጡ አድርጓል ብሏል።
“ይህ የትህነግ ተግባር በራያ ሕዝብ ላይ ያለውን የጠላትነትና የማደህየት ደባ በግልጽ ያሳየ ሆኖ አግኝተነዋል። ስለሆነም ሕዝባችን ይህ ሕገ_ወጥ ድርጅት መቸም ጊዜ ቢሆን ለደኅንነቱና ለዕድገቱ በየማያግዝ መሆኑን ዐውቆ እስከመጨረሻው እንዲቃወመውና ለመብቱና ማንነቱ መከበር ከሚታገለው ፓርቲያችን ጎን ይቁም” ሲል ጠይቋል።
እንደ ፓርቲው መግለጫም፤ የክልሉ መንግሥት/ትህነግ ለሥራ አጦች የሚሰጥ ሥልጠና በሚል ማታለያ መዝግቦ ለውትድርና ወጣቶችን በአስገዳጅ ሁኔታ እየመለመለ ይገኛል። እንዲሁም በየቀበሌው ከ300 እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎችን፣ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ታዳጊ ወጣቶችን ጭምር ለአስገዳጅ ውትድርና በቀበሌ አስተዳዳሪዎች አማካኝነት በመመልመል ወደ እርስበርስ ጦርነት ለመማገድ እያዘጋጃቸው ይገኛል።
የልማት ተግባራትን በመተው ቁጥር ስፍር የሌላቸው የክልል ልዩ ኃይሎችንና ሚሊሻዎችን አስታጥቀው የሚሰጧቸው ሬሽን ቢያጡ በግድ ገንዘብ፣ ዱቄት፣ ምግብ፣ እህል ወዘተ አዋጡ እያሉ ሕዝባችንን ለቀውስ መዳረጋቸው አጥብቀን እናወግዛለን ያለው ፓርቲው፤ “የሕዝባችንን ያለ አግባብ መጨቆንና መንገላታት በመገንዘብ የፌደራል መንግሥት እንዲደርስለትና ከሚደርስበት ብዝበዛ እና አስገዳጅ ውትድርና እንዲታደገው” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች የበሽታ የመከላከል አቅማቸው ስለሚቀንስ ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራል፡፡
በመሆኑም:-
1. ወደ ጤና ተቋም የሚያደርጉትን ምልልስ በመቀነስ የቀጠሮ ጊዜ እንዲረዝም ማድረግ
2. መድሃኒታቸውን በትክክልና ሳያቋርጡ መውሰድ
3. ከአደገኛ ሱሶች መራቅ
4. እራስን አለማጨናነቅ፣ የአካልብቃትእንቅስቃሴ ማድረግ
5. ሌሎች ለኮቪድ 19 መከላከያዎችን መተግበር
6. ህመም ከተሰማ ወዲያውኑ ወደ አቅራቢያ ጤና ተቋም መሄድ እና ሪፖርት ማድረግ፡፡
7. የጸረ-ኤችአይቪ ህክምና የምናገኝበትንና መድሃኒት የምንወስድበትን ጤና ተቋም እንዲሁም የባለሙያ ስልክ ቁጥር መያዝ፣ በስልክ የጤና ባለሙያዎችን ምክር መጠየቅ፣ ማማከር ተገቢ ነው።
የጤና ሚኒስቴር
በአዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታንያ ኤምባሲ፣ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ዲፕሎማቶች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ይቅርታ ጠየቀ
************************************
(ኢፕድ)
በአዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታንያ ኤምባሲ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ዲፕሎማቶች ላይ በቅርቡ ለተፈጸመው አግባብ ያልሆነ ድርጊት ይቅርታ ጠየቀ።
የኤምባሲው ከፍተኛ ባለስልጣን አሌክስ ካሜሮን እንዳሉት በቅርቡ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተፈጠረው ሁከትና በዲፕሎማት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ይቅርታ ጠይቀው፣ በቀጣይ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እንደማይደገሙ፤ የእንግሊዝ መንግስትም በቬናው ስምምነት መሰረት ለኤምባሲውም ሆነ ለዲፕሎማቶች ተገቢውን ጥበቃ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው በቬና ኮንቬንሽን መሰረት ማንኛውም አገር ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶችን ከሁከት፣ ጣልቃ ገብነት ወይም የአመጽ ተግባር የመከላከል ሃላፊነት እንዳለበት አስታውሰው፤ በቅርቡ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ዲፕሎማቶች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቅሬታ አሳድሯል። በመሆኑም ይላሉ አምባሳደሩ በቀጣይ እንዲህ ያለ ነገር እንዳይከሰት የእንግሊዝ መንግስት ተገቢውን ጥበቃ የማድረግ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።
በትግራይ ይካሄዳል በተባለው ህገ-ወጥ ምርጫ አንሳተፍም ያለው የራያ ሕዝብ እየታሰረና እየተሰደደ ነው ሲል የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) አስታወቀ
***********************
(ኢ ፕ ድ)
በትግራይ በሚካሄደው ህገ-ወጥ ምርጫ ላይ አንሳተፍም ያሉ የራያ ሕዝቦች እየታሰሩና እየተሰደዱ መሆናቸውን የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) አስታወቀ።
ፓርቲው ወቅታዊ የራያ አካባቢና ሃገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ህወሓት/ትህነግ ሊያካሂድ ላሰበው ህገ ወጥ ምርጫ ካርድ እያደለ ይገኛል። በዚህ ህገ-ወጥ ክልላዊ ምርጫ ላይ መብቴ/ማንነቴ ሳይከበርና ጥያቄዎቼ ሳይመለሱ አልሳተፍም ያለው የራያ ሕዝብ እንዲሁም ለውጡን የሚደግፉ ሰዎች፣ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እየታሰሩና እየተሰደዱ ይግኛሉ።
“ለምርጫ አንመዘገብም፣ የምርጫ ካርድም አንወስድም ያሉ ነዋሪዎች እስር፣ እንግልትና ድብደባ ጭምር እየደረሰባቸው ነው” ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ በዚሁ ምክንያትም በራያ- መኾኒ፣ በራያ-ኮረምና በራያ-ጨርጨር እስከ ዛሬው ቀን ድረስ 105 ወጣቶችና አዛውንቶች መታሰራቸውን አመልክቷል ።
የራያ ወገኖቻችንን ላይ ድብደባና ከፍተና የአካልና የሥነ-ልቡና ጉዳት እየደረሰ ነው ያለው ፓርቲው፤ “የራዴፓ አባል ናችሁ” እንዲሁም “ስበር ራያ”ን ትደግፋላችሁ እያሉ ወጣቶችንና አዛውንቶችንም ጭምር ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ መኖረያ ቤቶቻቸውን ይበረብራሉ፤ ያሸማቅቋቸዋል ነው ያለው። ለአብነት ያህልም በዚህ ሳምንት ብቻ በአላማጣ በ6 ወጣቶች ላይ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ፓርቲው አስታውቋል።
ከዚህ በከፋ መንገድ በማንነታቸው ምክንያት ጥያቄ ሊያነሡ ይችላሉ በሚል መሠረተ ቢስ ሰበብ በራያ አላማጣ ብቻ 20 የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል ያለው ፓርቲው፤ እነዚህ ተግባሮች በሕገ-መንግሥቱ የተደነገጉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚፃረሩ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሳስቧል።
“ሕዝባችን የመንግሥት ውሳኔን አክብሮ፣ በዚህ ሕገ-ወጥ ምርጫ አልሳተፍም፣ አልመርጥም በማለቱ ከፍተኛ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እየደረሰበት ነው” ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ “የፌዴራል መንግሥት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ ደኅንነቱና ህልውናው እንዲጠብቅልን፤ ከኮሮና በሽታ እልቂት እንዲታደግልን እንዲሁም ሕጋዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ መላው የራያ አካባቢ በገለልተኛ አካል ወይም በሃገር መከላከያ ሠራዊት ጥበቃ ሥር እንዲቆይ” ሲል ጠይቋል።
በትግራይ ይካሄዳል የተባለው ክልላዊ ምርጫ ህጋዊ እንዳልሆነና እንደማያውቀው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ፤ በተመሳሳይም የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ምርጫው ህገ ወጥና ተቀባይነት እንደሌላው መግለጹ ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ ፡ 'የአናብስቱ አባት' በሚንከባከቧቸው አንበሶች ተበሉ

ዌስት ማቲውሰን ይባላሉ። እውቅ የአካባቢ ተንከባካቢ ነበሩ። በተለይም ከደቦሎች ጋር ባላቸው ቅርበት 'የደቦል አንበሶች አባት' የሚል ቅጽል አስገኝቶላቸዋል።
እኚህ እውቅ የደቡብ አፍሪካ የዱር እንሰሳት ተንከባከባቢ የነበሩት ሰው ታዲያ በሚንከባከቧቸው አንበሶች መበላታቸው ተሰምቷል።
ክስተቱ ያልተመለደና ያልተጠበቀ ነበር።
ሚስተር ማቲውሰን በአናብስቱ ሲበሉ ባለቤታቸው አብረዋቸው በቅርብ ርቀት ነበሩ።
ሚስተር ማቲውሰን ነጫጭ አናብስቱን ለማለዳ የእግር ጉዞ ነበር ከጥበቃ ጎሬያቸው ይዘዋቸው የወጡት። ትንሽ እግራችንን አፍታተን እንመለስ ብለው።
ሆኖም ሳይመለሱ ቅርተዋል።
ባላቸውንና ለእግር ጉዞ ይዘዋቸው የወጡትን አናብስት በመኪና ከኋላ ኋላ ሲከተሏቸው የነበሩት የሟች ሚስት ነገሮች መልካቸውን እየለወጡ እንደሆነ ሲረዱ አንበሶችን ትኩረት ለማስቀየር ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
የ68 ዓመት ባላቸውንም ከመበላት አላስጣሏቸውም።
ዌስት ማቲውሰን በደቡብ አፍሪካ ታዋቂውን የሳፋሪ ሎጁ ያስተዳድሩ ነበር። ስሙም ላየን ትሪ ቶፕ ሎጅ ተብሎ ነው የሚጠራው። የሚገኘውም በደቡብ አፍሪካ፣ ምዕራብ ጆሐንስበርግ፣ ሊምፖፖ ግዛት አካባቢ ነው።
አንበሶቹ ከዚህ ቀደም ወደ አንድ ሌላ ሎጅ ተወስደው የነበረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ወደ ዱር ተመልሰው ሊወሰዱ እንደነበር ተዘግቧል።
አንዷ ሴት አንበሳ ያልተጠበቀ ባህሪ ማሳየቷ ነው ነገሮችን የለወጣቸው።
በወቅቱ ሴቷ አንበሳ ባልተለመደ መልኩ በሌላኛዋ አንበሳ ላይ ጨከን የማለት ባህሪ ታይቶባት ነበር።
ከዚያ ወዲያው ደግሞ ፊቷን መልሳ ከእኚህ ከተጠባቂያቸው ጋር ልፍያ ጀመረች። ሳይታሰብ ጠባቂዋን መቦጫጨቅ እንደጀመረች ተነግሯል።
የሟች ዘመዶች እንደሚሉት የሰውየው ለሞት መዳረግ ምናልባት አንበሶቹ እርስበርስ መቦጫጨቅና ኃይል የተቀላቀለበት ልፍያ ማድረጋቸው ያመጣው መጥፎ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።
የሚገርመው ሰውየው አናብስቱን ከሚታደኑበት ስፍራ አውጥተው በሕይወት እንዲቆዩ ማድረጋቸው ነው።
መካነ አደን (canned hunting) እንሰሳት በአንድ ክልል ሆነው ሰዎች በሕጋዊ አደን እንዲገድሏቸው የሚደረግበት ክልል ነው።
እነዚሁ አናብስት በ2017 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ክልላቸውን ጥሰው በመውጣት አንድ በአካባቢው የሚጎራበታቸውን ሰው ገድለዋል።
እኚህን ጠባቂያቸውን ሲገድሉ ታዲያ ይህ ሁለተኛ ጊዜያቸው መሆኑ ነው።
ሚስተር ማቲውሰን አናብስቱን ያሳደጓቸው ገና ደቦል ሳሉ ነበር። ሰውየው ከአናብስቱ ጋር አብረዋቸው ሲላፉና ሲጫወቱ በርከት ያሉ ዘጋቢ ፊልሞች አሏቸው።

ምንጭ ቢቢሲ