Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
24.8K subscribers
41.2K photos
343 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት እየተከናወነ ነው
*************^
(ኢ.ፕ.ድ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም የሚሾሙ ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት እየተከናወነ ነው።

ለእነዚሁ አባቶች ሥርዓተ ጸሎተ አስኬማ በዋዜማው ተከናውኗል።

በዓለ ሢመቱ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ምዕመናን በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

ሢመተ ኤጲስቆጶስነት እየተፈጸምላቸው ያሉት ዘጠኝ አባቶች በሥርዓተ ቤተክርስቲያን በተቀመጠው መሠረት በዘጠኝ አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት ‼️

ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው!

የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ ጉዳይ ነው። ታሪክ የመቀየር ጉዳይ ነው። ለትውልድ የመትረፍ ጉዳይ ነው።

ከማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባራት ነጻ የሆነ ቀን የመረጥነው ይህ ቀን ሊያልፈው የሚገባ ኢትዮጵያዊ ስለሌለ ነው። ሰኞን ስንመርጥ የሥራ መጀመሪያችንን ተፈጥሮን በመታደግ እንድንጀምር ነው።
ፉክክራችን ከራሳችን ጋር ነው። ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና መንደሮች ከአምናው የበለጠ በመትከል የየራሳቸውን ሪከርድ እንደሚሰብሩ እናምናለን። እያንዳንዳችንም የየራሳችንን ሪከርድ መስበር አለብን።

ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም። ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው። ችግርን የምናሸንፈው መጀመሪያ የራሳችንን ፣ ቀጥሎ የአካባቢያችንን፤ በመጨረሻም የዓለምን ሪከርድ ስንሰብር ነው።

እኔ ነገ በተደጋጋሚ ለመትከል ተዘጋጅቻለሁ። እናንተስ?

ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 የራሳችሁን ሪከርድ በብዙ መጠን እስክትሰባብሩ ድረስ ዛፎችን ለመትከል ተዘጋጁ።
#አረንጓዴዐሻራ

"የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ ጉዳይ ነው"
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በአሶሳ የሚገነባው የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ በመጪው መስከረም እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ
******************
(ኢ ፕ ድ)

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት 200 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተጀመረው የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ በመጪው መስከረም ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተገለጸ።

የፋብሪካውን የግንባታ ሂደት የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ጎብኝተዋል።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም አብዱራሂም በጉብኝቱ ወቅት ለአመራሮቹ በሰጡት ማብራሪያ፤ ፋብሪካው ሲጠናቀቅ በቀን 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

በቀን ከ400 ኩንታል በላይ የዱቄት ግብዓት እንደሚያስፈልገው አመልክተው፤ ግንባታው ከተጀመረ ከአራት ወራት በላይ እንደሆነውም ጠቁመዋል፡፡

ግንባታው በ2016 መስከረም ወር ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የገለጹት አቶ አብዱልከሪም፤ የከተማውን እና የአሶሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የአካባቢውን የዳቦ ፍላጎት የመሸፈን አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ዳቦ ፋብሪካው ወደ ማምረት ሲገባ ከ150 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

አስተዳደሩ የፋብሪካውን የኤሌክትሪክ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ የግንባታ ስራዎች ጥራት እና ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ አስፋላጊውን ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከንቲባውን ማብራሪያ የተከታተሉት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን፤ ባለፈው የበጋ ወቅት የለማውን የመስኖ ስንዴ ተሞክሮ በማጠናከር ለፋብሪካው በቂ ግብዓት እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
#አረንጓዴዐሻራ

"እኔ ነገ በተደጋጋሚ ለመትከል ተዘጋጅቻለሁ፤ እናንተስ? ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 የራሳችሁን ሪከርድ በብዙ መጠን እስክትሰባብሩ ድረስ ዛፎችን ለመትከል ተዘጋጁ"

- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የክልሉ ህዝብ ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በነቂስ እንዲሳተፍ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጥሪ አቀረቡ
*********************
(ኢ ፕ ድ)

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል በሚካሄደው ዘመቻ የክልሉ ህዝብ በነቂስ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ መሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እና ለትውልድ ለማስተላለፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር መሆኑን ጠቁመው በመርሃግብሩ ላለፉት አመታት እንዳደረግነው ሁሉ ነገም የሀይማኖት፣ የብሔርና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድበን በነቂስ በመውጣት ስለሀገራችን ብለን የምንሳተፍበት ተግባር ነው ብለዋል።

በክልላችንም በአንድ ጀምበር ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አስፈላጊውን ዝግጅት ያጠናቀቅን በመሆኑ ነገ ሐምሌ 10 ከማለዳው 12:00 ጀምሮ በተዘጋጁ የችግኝ የመትከያ ስፍራዎች እንዲሁም በየአካባቢው ችግኝ በመትከል ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም
ሙሽሮቹ የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸውን ችግኞችን በመትከል አከበሩ
*****
(ኢ ፕ ድ)

በሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ ጋብቻቸውን ዛሬ የፈፀሙት ጥንዶች የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸውን ችግኞችን በመትከል አሳልፈዋል።

ጥንዶቹ የችግኝ ተከላውን ከሚዜዎቻቸው ቤተሰቦቻቸውና አጃቢዎቻቸው ጋር "ነገን ዛሬ እንትከል" የሚለውን መርህ በመከተል መሆኑም ተገልጿል።

በሾኔ ከተማ ሊቻ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ሙሽራው አቶ ረታ ወልቃ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው ችግኝ መትከል የሰው ልጆችን ህይወት ጤናማ እንደሚያደርግ ነው።

“በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትግበራ የሀገሪቱን የግሪን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማሳደግ በተጨማሪ ሁለንተናዊ ጉዞዋን ለማሳለጥ የሚያግዝ በመሆኑ በተግባሩ በመሳተፍ ላይ ነኝ” ሲል ገልጿል።

ነገ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር የሚተከለውን አምስት መቶ ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርን በማሰብ ዛሬ የሰርግ ስነ-ስርዓቱን ችግኞችን በመትከል ለማሳለፍ መነሳሳቱን አብራርቷል።

ሙሽሪት ወይዘሮ ፍሬህይወት ብርሃኑ በበኩሏ የሀገርን ልዕልና አስጠብቆ ለማስቀጠል ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበትና የጊዜና የቦታ ወሰን ሊገድብ እንደማይገባ ተናግራለች።

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሀገራችንን ከፍታ ለማረጋገጥ ታቅዶ በመተግበር ላይ ያለ በመሆኑ የሰርግ ስነ-ስርዓታቸውን ከሚዜዎቻቸው፣ ከአጃቢዎቻቸውና ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ችግኝ በመትከል ለማሳለፍ ከባለቤቷ ጋር ቀድመው የተተስማሙበት መሆኑን ተናግራለች።

የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ ለታቀደው ዓላማ እንዲውል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የሾኔ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ በዶሬ በከተማው በአንድ ጀምበር ከ 100 ሺህ በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸውን የፈፀሙት ጥንዶች በሰርጋቸው ላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች በሾኔ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ በመትከል ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

የጥንዶቹ ድርጊት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ትግበራ የሰጡትን ትኩረት የሚያመላክት ከመሆኑ በተጨማሪ የጋራ ሃሳቡ ሊጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም