Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1 ሺህ 86 ሰዎች የኮኖና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ16 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

ባለፉት 24 ሰዓታት በኢትዮጵያ በተደረገ 14 ሺህ 688 የላቦራቶሪ ምርመራ 1 ሺህ 86 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም 26 ሺህ 204 ደርሷል።

በሌላ በኩል ትናንት 394 ሰዎች በማገገማቸው በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 428 ሆኗል።

ባለፉት 24 ሰዓታት የ16 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ይህም በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር 479 አድርሶታል።

በአሁኑ ጊዜ 14 ሺህ 295 ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሕክምና እየተከታተሉ ነው፤ 193 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕክምና ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስካዛሬ ድረስ 550 ሺህ 119 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1,038 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው
------------------------------
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 17ሺህ 323 የላቦራቶሪ ምርመራ 1038 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 27 ሺህ 242 ደርሷል።

በትናንትናው ዕለት 232 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 660 ሆኗል።

ካለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በኮሮናቫይረስ የተነሣ የሟቾች ቁጥር 492 ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት 195 ሰዎች በጽኑ ሕክምና ላይ ሲገኙ፣ 15 ሺህ 088 ደግሞ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስካዛሬ ድረስ 567 ሺህ 442 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።
መቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከሁለት ሺህ በላይ በጎዳና የወደቁ አረጋዊያንን አዕምሮ ህሙማን ለማንሳት ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጠው ጥሪ አቀረበ።

ማዕከሉን ለመርዳት ቃል የገቡ ወገኖችም ቃላቸውን እንዲፈጽሙ ጠይቋል።

ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ወር ውስጥ በጀመረው አረጋዊያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና እያነሳ መሆኑን ገልጿል።

የማዕከሉ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ራጁ ዲንሳ ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ በአዲስ አበባና ሐረር ከተሞች ከሁለት ሺህ በላይ አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማንን ከጎዳና ለማንሳት እየሰራ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ ከሁለት ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማንን ለማንሳት ማቀዱንና እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ከጎዳና መነሳታቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሐረር ከተማ ለማንሳት ከታቀደው 110 አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማን መካከል 60ዎቹን ማንሳቱን አስታውቀዋል።

በመሆኑም በከተሞቹ ዕድሚያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋዊያንንና ጎዳና ላይ የወደቁ ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን ጥቆማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ጥቆማ ለመስጠት በ90-49-49-49-49 ወይንም በ90-70-70-70-70 ስልክ ቁጥሮች ደውሎ ማሳወቅ እንደሚቻል አቶ ራጁ አስረድተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ማዕከሉን መጎብኘት ባለመቻሉ የሚደረገለት ድጋፍ ተቀዛቅዟል።

በወረርሽኙ ምክንያት መጋቢት 6 ቀን 2012 በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ቃል የገቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቃላቸውን እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል።

በወቅቱ ቃል ከተገባው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን እስካሁን የተሰበሰበው ከ15 ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ ነው የተናገሩት።

በመሆኑም በተሰጡት የስልክ ቁጥሮች በመደወል ቃል የገቡበትን ገልጸው ሕጋዊ በሆነ ደረሰኝ ያሉበት ድረስ በመሄድ መቀበል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በማዕከሉ የአረጋዊያን ተጠሪ መምህር ሳሙኤል ከበደ በማዕከሉ የሚገኙ አረጋዊያን የሚጦሩት ድጋፍ በሚያደርጉ ወገኖች በመሆኑ ቃል የገቡ አካላት ቃላቸውን አክብረው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት አረጋዊያንን መጎብኘት ባይቻልም፤ የማዕከሉ መግቢያ በር ላይ በሚገኘው ገንዘብ ቤት ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።

አልባሳትና ሌሎች ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖች በማዕከሉ ተገኝተው መለገስ ካልቻሉ፥ ያሉበት ድረስ በመሄድ መቀበል እንደሚቻልም ተጠቁሟል።

መቄዶኒያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከሶስት ሺህ ለሚበልጡ አረጋዊያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና በማንሳት የምግብ፣ የሕክምና፣ መጠለያና ሌሎች አገልግሎት ይሰጣል።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖች ቁጥር 10 ሺህ ለማድረስ እየሰራ ነው።

ማዕከሉ በአዲስ አበባ አያት አካባቢ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ ሆስፒታልና ለአረጋዊያን መኖሪያ የሚውል ባለ 11 ወለል ህንጻ እያስገነባ መሆኑም ታውቋል። ምንጭ...ኢዜአ
"ኢትዮጵያውያን ዳግመኛ ለትውልድ ውርስ የሚሆን አረንጓዴ አሻራቸውን ተባብረው አሳርፈዋል"

👉 ዐብይ አህመድ (ደ/ር)
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
“የትግራይ ህዝብ በታሪኩ የተዋረደበት፣ ባህሉ የጠፋበት፣ ቤተእምነቱ የተደፈረበት ያለፉት 27 ዓመታት ናቸው” አቶ ሊላይ ኃይለማርያም የህወሓት ነባር ታጋይ
*********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፦ የትግራይ ህዝብ በታሪኩ የተዋረደበት፣ ባህሉ የጠፋበት፣ ቤተ ክርስቲያኑ እና መስጂዱ የተደፈረበት ጊዜ ቢኖር ያለፉት 27 ዓመታት መሆናቸውን የህወሓት ነባር ታጋይ አቶ ሊላይ ኃይለማርያም አመለከቱ። ህወሓትን እየመሩ ያሉ አመራሮች ምን ያህል የወደቁ መሆናቸውን የሚያሳየው ተሳዳቢ ቡድን በማህበራዊ ሚዲያው ውስጥ ማደራጀታቸው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሊላይ ኃይለማርያም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ ተነግሮም፣ ተሰምቶም የማይታወቅ ነው። በትግራይ ታሪክም እንዲህ አይነት ክፉ ጊዜ አጋጥሞ አያውቅም። የትግራይ ህዝብ የተዋረደበት፣ ባህሉ የጠፋበት፣ ቤተ ክርስቲያኑ እና መስጂዱ የተደፈረበት ጊዜ ቢኖር ያለፈው 27 ዓመታት ናቸው።
“የትግራይ ህዝብ ከ1967 ትግል ከመውጣቱ በፊት ነጭ ጋቢ ይለብስ ነበር። አሁን ጆንያ ለብሶ ነው የሚያድረው። ቀድሞ ነጭ ማር፣ ነጭ ወተት፣ ነጭ አምባሻ ይመገብ ነበር። አሁን ግን በእርዳታ ስንዴ ነው የሚኖረው። የትግራይ ህዝብ አሁን ምኒሊክና ኃይለስላሴን ቀርቶ ደርግን ረስቷል። እነዛ ሥርዓቶች ካደረሱበት በላይ ፍጹም ድህነትና ፍጹም ባርነት ውስጥ ነው ያለው” ብለዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በትግራይ ታሪክ የተሰደዱበት፣ ሰው የታሰረበት፣ የተገደለበት ዘመን ቢኖር ያለፉት 27 ዓመታት ናቸው ያሉት አቶ ሊላይ፤ የህውሃት ሰዎች እንደ ገቡ አስር ትልልቅ እስር ቤቶች እና ሰባት የዜሮ ስድስት የድብቅ እስር ቤት እንደሰሩም አመልክተዋል።
የሰማዕታት እናቶች በረሃብ የሞቱበት፣ ህዝቡ በፍጹም ድህነት እንዲኖር የተፈረደበት ዘመን እንደነበረም አመልክተዋል። በዚህ ዘመን የትግራይ ህዝብ በልመና ኑሮውን እንዲገፋ፣ እንዳይሰራና ከ50 በመቶ በላይ ሴፍቲኔት ጠባቂ እንዲሆንም መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ህውሀት ይህን ሁሉ የሚያደርገው ‹‹ወደ ስልጣን ያመጣው የትግራይ ህዝብ እንደሆነ ሁሉ ከስልጣን የሚያወረደውም የትግራይ ህዝብ እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው›› ያሉት ነባር ታጋዩ፤ ህዝቡ ካመጸ የሚሰጠውን ድጋፍ በማቋረጥ ዝም ለማስባል የተደረገ ሴራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ስልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ ትግራይን ወደ ፍጹም ድህነት አስገብተውታል ብለዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ ተነግሮም፣ ተሰምቶም የማይታወቅ ነው። በትግራይ ታሪክም እንዲህ አይነት ክፉ ጊዜ አጋጥሞን አያውቅም። አሁን እኮ ስለ ደርግ፣ ኃይለስላሴ እና ምኒልክ የሚያወራ የለም። ምክንያቱም እነዚህ ሶስቱ ያጠፉት ተጨምቆ የስብሃት ነጋ ኔትዎርክ የሚሰራውን በደል አንድ መቶኛ ቢሆን ነው።
አሁን በትግራይ ያለው ፍጹም ባርነት ነው። ስራ ለመቀጠርና የትምህርት እድል ለማግኘት እንኳን የእነርሱ ኔትወርክ መሆን ወይም ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት መማር ዋና መመዘኛ ሆኖ እንደሚቀርብ አቶ ሊላይ አመልክተዋል፡፡
“ወያኔ የጀግኖች ስም እንጂ የተሳዳቢዎች ስም አይደለም። በጣም የሚያሳዝነው በአሁኑ ሰዓት ህወሓትን እየመሩ ያሉ አመራሮች ምን ያህል የወደቁ መሆናቸውን የሚያሳየው ተሳዳቢ ቡድን በማህበራዊ ሚዲያው ውስጥ ማደራጀታቸው ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ማህበራዊ ሥነ ልቡና እና ከትግራይ ባህል ውጪ ነው። ለምሳሌ፣ አሁን አንተ ከእኔ ጋር አውርተህ የምትጽፈውን ስታይ አንድ ሚሊዮን ተሳዳቢ ይወጣል። እናም በጣም የሚያሳዝነው መሪዎቹ ሚዲያ ላይ ወጥተው ላደረጋችሁት ተጋድሎ እናመሰግናለን ሲሉ ነው የምትሰማው” ብለዋል፡፡
ይሄ የሚያሳየው አመራሩ ብቃት እንደሌለው ነው።
የምትሳደበው ጉልበትና ሃሳብ ስታጣ ነው። ትግራይ ውስጥ ስድብ ጸያፍም ነውርም ነው። አይደለም መሳደብ ጮኾ መናገር ነውር ነው። ይህም እነዚህ ሃይሎች ከትግራይ ህዝብ ሥነልቡና ውጪ መሆናቸውን አመላካች እንደሆነም አስታውቀዋል።
“ለህወሓቶች ይሄን አይነት ማደናገሪያ ባህላቸው እንደሆነ ጠቁመው ፣ ባለፉት 27 ዓመታት በክልሉ ውስጥ ልማት አልተሰራም። ለምን ብትላቸው ሻዕቢያ መጥቶ ያፈርሰዋል ይሉሀል። ይህ ደግሞ ህዝቡ ደህንነት እንዳይሰማው ለማድረግ ነው። በዚህ መልኩ የትግራይን ህዝብ እየፈሩ ግን ሳያስቡት ቄሮ አባረራቸው። ምንም እንኳን ትግራይ ድረስ ሄደው ነጻ ባያወጡንም ዱላ ይዞ ታግሎ ላባረራቸው ለቄሮ የወጣት ንቅናቄ ትልቅ ክብር አለኝ። እናም ህወሓት አሁን ያለው የመጨረሻ አማራጭ ያለበትን ቦታ ላለማጣት እንደለመደው ህዝቡን የደህንነት ስጋት እንዳለበት አድርጎ ለማሳመን መስራት ነው” ብለዋል፡፡
ሰሞኑን ወታደራዊ ሰልፍ ሲያሳዩ ነበር። የሚገርመው አር.ቢጂ ክላሽ እናቶችን አሸክመው ነበር። እነዚህ ሰዎች በዚህ መልኩ ጦር በሰልፍ ለማሳየት መጣራቸው ምን ያህል ወደ ኋላ የቀሩና አንድ ቦታ ተተክለው የቀሩ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው። አር.ቢጂ ክላሽ ይዘህ የምታሸንፈው ጦርነት አሁን ዓለም ላይ አለመኖሩን እንኳን አልተገነዘቡትም። ይህ ይቅር፣ ለመሆኑ ያንን ጦርነት ከማን ጋር ነው የሚያደርጉት? ሲሉም ጠይቀዋል።
ማዕከላዊ መንግስት ይሄን እንዲያደርጉ የሚደግፋቸው ነው የሚመስለው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይሄ ሁሉ ጥፋት እንዲጠፋ በአሁኑ ሰዓት የኤርትራን ተቃዋሚ ትግራይ ውስጥ እያሰለጠኑ ነው። አማራን ለመውጋት ቅማንትን እያሰለጠኑ ነው። አርዱፍ አፋርን ለመውጋት እያሰለጠኑ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ በጀት እየጨመረ እየሰጠ ነው። ማዕከላዊ መንግስቱ ከሰባት ቢሊዮን አስር ቢሊዮን ጨምሬላችኋለሁ ይላል። በዚህ ደግሞ ማዕከላዊ መንግስት ወደፊት በታሪክ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል ፡፡
አሁንም ሌላ 200 ሺህ ጦር እንዲያሰለጥኑ ባጀቱን ከሰባት ቢሊዮን ወደ አስር ቢሊዮን አሳድጌያለሁ ብሎ ይነግረናል። ከአዲስ አበባ ሸሽተው የሄዱት ግን በዓመት ውስጥ እኮ ሶስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ነው ለሆቴልና ለሌላም ወጪ የወጣላቸው። ከግማሽ ሚሊዮን ወጣት ግን እዛ ስራ የለውም። ከዚህ ባለፈ ከኤርትራ ጋር የመጣውን ሰላም በቀላል ማየት የለብንም። ያንን ሰላም እኮ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የትግራይ ህዝብ አብዝቶ የሚፈልገውና አብዝቶ ሲናፍቀው የነበረ ነው።
ከሰላሙ በአንደኝነት የሚጠቀመው የትግራይ ህዝብ ነው። ሆኖም ያ ሰላም ከተፈጠረ እነዚህ ህወሓቶች መኖር ስለማይችሉ፤ አሁን ላይ ስትራቴጂያቸው ሻቢያ ወረረህ፣ አማራ ሊወርህ ነው፣ ዐብይ ሊወርህ ነው የሚል እንደሆነም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2012
በአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ሰመራ ገባ
**********************
(ኢ ፕ ድ)
በአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለመድረግ ዛሬ ጠዋት ሰመራ-አፋር ገብቷል፡፡
የልዑኩ አባላት ሰመራ-ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፍሬ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በጉዞው የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን አመብድ ዘግቧል፡፡
በርዕሰ መሥተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የተመራው ልዑክ ትናንት በኦሮሚያ ክልል ጉዳት ለደረሳባቸው ዜጎች ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ዘንድሮ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ 520 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ደርሰዋል
. በአደጋው የ 105 ሰዎች ህይወት አልፏል
******************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- እየተጠናቀቀ ባለው የ2012 ዓመት በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች 520 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መድረሳቸውንና የ 105 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ .አቶ ጉልላት ጌታነህ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በዘንድሮው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች 520 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ደርሰዋል፡፡
በዓመቱ በደረሱት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የ105 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን 132 የሚሆኑ ሰዎችም የመቁሰል ጉዳት አጋጥሟቸዋል። ከደረሱት 520 አደጋዎች ውስጥ 335 የእሳትና 185 የድንገተኛ አደጋዎች
ሲሆኑ 479ኙ በአዲስ አበባና 41 ያህሉ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተመዘገቡ ናቸው ።
በአደጋዎቹ የደረሰው የንብረት ውድመት በገንዘብ ሲተመን 342 ሚሊዮን 236 ሺ 660 ብር መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው በተመሳሳይ ሁኔታ በተደረገው ከፍተኛ የመከላከል ጥረት ከ7 ቢሊዮን 796 ሚሊዮን 284 ሺ 500 ብር በላይ የሚገመት ንብረትን ለመታደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የደረሱ አደጋዎችን ለመቆጣጠር 150 የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና 440 አምቡላንሶች ከ 6 ሺ 635 የአደጋ መከላከል ሠራተኞች ጋር መሰማራታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመት 335 የእሳት አደጋዎች የደረሱ ሲሆን በቃጠሎው ያጋጠመው ጉዳትም ከሌሎች አደጋዎች ይበልጥ ከፍተኛው ቁጥር እንደተመዘገበበት ተናግረዋል፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ 180 ድንገተኛ አደጋዎች መድረሳቸውን የጠቀሱት ባለሙያው በነዚህ አደጋዎችም ጉድጓድ ውስጥ መግባት፣ራስን ከፎቅ ላይ መወርወር ፣ታንቆ መሞትና መሰል ክስተቶች እንደሚያጋጥሙ ተናግረዋል ፡፡
ባለፈው ዓመት በእሳት ቃጠሎ የደረሱ አደጋዎች ቁጥር 397 እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጉልላት የዘንድሮው ዓመት ከአምናው ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በ62 መቀነሱን ተናግረዋል ፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ በ2011 ዓ.ም በድንገተኛ አደጋዎች የተመዘገበው ቁጥር 177 የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ባለው ተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ቁጥሩ በስምንት ጨምሮ 185 ሆኖ ተመዝግቧል። ዘንድሮ በተጠቀሱት አካባቢዎች የደረሱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸርም በ54 ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረውን የክረምት ተጽዕኖ ለመቀነስ አስቀድሞ ዝግጅት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ጉልላት በከተማዋ ያሉ 261 የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎችን በመለየት በተሰጠው ህብረተሰብ አቀፍ ግንዛቤ ውጤታማ ሥራ መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡
በኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በየጊዜው የሚሰጠው አደጋን የመቀነስ ጥንቃቄ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር አስተዋጽኦ አድርጓል ያሉት ባለሙያው ዘንድሮም ይህ ጥረት መቀጠሉ ችግሩን ለመቀነስ ድርሻ ነበረው ብለዋል።
ህብረተሰቡ ራሱንና ንብረቱን ለአደጋ ከሚያጋልጡ አደጋዎች ሊጠበቅ ይገባል ያሉት አቶ ጉልላት ከኮሚሽኑ በየጊዜው የሚሰጠውን ምክርና ማሳሰቢያን በመተግበርም ጥንቃቄን ባህል ማድረግ ግድ ይላል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2012
የቤት ውስጥ ራስን ለይቶ ህክምና (ውሸባ) እና እንክብካቤ በኢትዮጵያ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ
****************
(ኢ.ፕ.ድ)

የቤት ውስጥ ራስን ለይቶ ህክምና (ውሸባ) እና እንክብካቤ (Home Based Isolation and Care) በኢትዮጵያ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በተደረጉ 567,442 የኮሮና ቫይረስ የላብራቶሪ ምርመራዎች 27,242 በቫይረሱ የተያዙ ታማሚዎች ሲገኙ ከዚህም ውስጥ እስከ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም ከነበሩት 5,000 ታማሚዎች 76 በመቶ ምንም ምልክት የሌለባቸው እና 21 በመቶ መለስተኛ ህመም ያላቸው እና ቀሪውቹ ከባድ እና በፅኑ ህመም ውስጥ ያሉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል ፡፡

በብሔራዊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 ምላሽ ማስተባበሪያ የቤት ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ ክፍል ሀላፊ ዶ/ር ታይካ አለሙ እንደገለጹት በአሁኑ ሠአት 2000 በላይ የቤት ውስጥ የውሸባ እና እንክብካቤ የሚደረግላቸው ታካሚዎች እንደሚገኙ እና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ፡፡በዚህም ከ400 በላይ የሚሆኑት አገግመው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በቤት ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ ጊዜ ከታካሚው ጋር በሚኖር ግንኙነት ንክኪን ማስወገድ፣ እጅን ከአልኮል በተሰራ የእጅ ንፅህና መጠበቂያ ማፅዳት፣ ከታካሚው ጋር በሚገናኙበት ጊዜ የህክምና የአፍና የአፍንጫ ጭንብል በአግባቡ እንዲደረግ ዶ/ር ታይካ አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም ታካሚዎቹ ማንኛውም የህመም መባባስ ሲኖራቸው ወደ 8335/952 ወይም ለሚከታተላቸው ክፍል በመደወል ማሳወቅ ወይም አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ህክምና ማግኝት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

በቅድሚያ የቤት ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ ለማግኘት ስለታካሚው ተገቢውን መረጃ መስጠት የሚችል የቤት ውስጥ ተንከባካቢ ወይም የማህበረሰብ በጎ ፍቃደኛ መኖር፣ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ ቤቱ በተገቢው ሁኔታ የተዋቀረ መሆን፣ ለታካሚው ቤተሰብ በቂ የአፍና አፍንጫ ጭንብል፣ ጓንት መኖሩን ማረጋረጥ የምግብ እና መሰረታዊ አቅርቦቶች ሞሟላት በተጨማሪም ተንከባካቢው እንዲሁም ታማሚው ተጓዳኝ በሽታ እንደሌለበት ማረጋገጥ ይኖርብናል ተብሏል፡፡

ህብረተሰቡ የቤት ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ መጀመሩን አውቆ ከጤና ባለሞያዎች የሚሰጠውን ምክር በሚገባ መተግበር እንዳለበት እና ለቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ባለመሆን እንዲጠነቀቁ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

የቤት ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ ማለት አንድ የኮቪድ-19 ታማሚ መሆኑ በላብራቶሪ ምርመራ የተረጋገጠ ሰው የህመም ምልክት ሳያሳይ ወይም ቀለል ያሉ የህመም ምልክቶች ያሉት እንዲሁም በቤት ውስጥ መሞላት ያለበትን መስፈርቶች የሚያሞሉ የህብረተሰብ ክፍል የቤት ውስጥ እንክብካቤ ማድረግ ሲጀምር በቤት ውስጥ ውሸባ እንክብካቤ ማድረግ ማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በምሽቱ የዲያመንድሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተወዳደሩ ሲሆን አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ5ሺ ሜ ሴቶች 14:26.57 በሆነ ጊዜ ኬንያዊቷን ሄለን ኦቢሪን ተከትላ 2ኛ በመሆን ድሏን አጣጥማለች።

በ1,500 ሜ የተወዳደረው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ 5ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ የ3,000 ሜ መሠናክል ተሰላፊዎች አትሌት ለሜቻ ግርማ 8ኛ እና አትሌት ጌትነት ዋለ ደግሞ 10ኛ በመሆን እኤአ የ2020ን ዲያመንድሊግ ውድድር ሀ ብለው ጀምረዋል።

በ5ሺ ሜ ኡጋንዳዊው ጆሽዋ ቸፕተጌ 12:35.36 በሆነ ጊዜ ቀዳሚ ሲሆን በጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የነበረውን የ16 አመት የ5ሺ ሜ ሪከርድ 12:37.35 በመስበር ማሸነፍ ችሏል።

ቀጣዩ የዲያመንድሊግ ውድድር ከ9ቀናት በኋላ በስዊድን ስቶኮልም ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ግምገማ መጀመሩ ተገለጸ
***********
(ኢ.ፕ.ድ)

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ በየክልሉ ሥራ አስፈጻሚዎች የቀረቡትን ሪፖርቶች ለመገምገም ስብሰባ መጀመሩ ተገለጸ።

ሥራ አስፈጻሚው ዛሬ በጀመረው በዚሁ ስብሠባው በተጨማሪም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ጠቅላይ ሚኒስር ዶ/ር አብይ አህመድ በፌሥቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
በጋምቤላ ክልል የሚገነባው የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 74 ከመቶ ደረሰ
******************
(ኢ.ፕ.ድ)

በጋምቤላ ክልል በአኝዋ ዞን ጆር ወረዳ እንጎጊ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ 74 ከመቶ አፈፃፀም ላይ መድረሱን የጋምቤላ ክልል የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፅ/ቤት አስታወቀ፡፡

በ5ሺ 950 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ የሶላር ፕሮጀክት፤ በ425 ሺህ 746 የአሜሪካን ዶላር ወጪ "CET & NR Consotrium" በተባለ የቻይና ኩባንያ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የግንባታው ሥራ ክትትል የሚያደርገው ደግሞ የሪጅኑ አገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ፅ/ቤት ነው፡፡

እስካሁን 5.9 ኪሜ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ የተከናወነ ሲሆን፤ የሶላር ፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ175KW በላይ ኃይል ማመንጨት የሚችል ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ከ150 እስከ 200 ለሚጠጉ ደንበኞች እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጠት ይችላል፡፡

የሶላር ኃይል ማመንጫው ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሲል ያስታወቀው የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ መግለጫ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቀዳሚ ምርመራ ሂደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
**************************************************************
በዛሬው እለት አቶ ጃዋር መሃመድ ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ አቶ ጃዋር መሃመድ አሞኛል በማለታቸው ተሰተጓጉላል። ከዚህም የተነሳ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን የመስማት ሂደቱን ለማካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶዋል።

በዚህ አጋጣሚ ለህዝብ እና ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ለማድረግ የምንፈልገው እነ አቶ ጃዋር መሃመድ በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ስር እንደመሆናቸው ጤናቸውን ለመጠበቅ ባለው አሰራር አስፈላጊውን የጤና ክትትል እና አገልግሎት የሚያገኙ እና እያገኙ ያሉ ሲሆን ጤናቸውም በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ለዚህም ማሳያ ከተደረገላቸው የህክምና በተጨማሪ ዛሬ በዋለው ችሎት ምስክር መሰማት እንዳይጀምር የተለያዩ ምክንያቶችን እያነሱ ለረጀም ሰዓት ሲከራከሩ ከቆዩ በኃላ በክርክሩ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ ምስክር መሰሚያ ሰዓት ሲደርስ ወጣ ገባ ማለታቸው የሚፈለገው የምስክሮችን የማሰማት ሂደቱን ለማስተጓጎል እና በግብረአበሮቻቸው ሁከት እና አመጽ ለመቀስቀስ ነው።

የተጠርጣሪው ግብረ አበሮች በተለያየ መንገድ ምስክሮችን በማስፈራራት የፍትህ ሂደቱ እንዲስተጓጎል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቆዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፍጹም አግባብነት በሌላቸው መነሻዎች እና በተለያየ ሰበቦች ምስክሮች በቀዳሚ ምርመራ የሚሰሙበተ ሂደት እንዲራዘም እና እንዲሰናከል ለማድረግ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ እንደ ወትሮም ሁሉ ተቋማችን ለምስክሮች ተገቢውን የህግ ጥበቃና ከለላ የሚያደረግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንፈልጋለን።

ከምንም በላይ በተለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች አላግባብ ከሚቀርቡ አቤቱታ እና ይግባኞች ጀምሮ፣ አልተዘጋጀንም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን፣ ዳኛው ፌገግ ብሏል እና ይቀየርልን በማለት በሰበብ አስባቡ የፍርድ ሂደቱን ለማደናቀፍ በተጠርጣሪዎቹ በኩል የሚደረግ ጥረት እንዳለ ግልጽ ሆኖዋል። ይህን እውነታ ህዝቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡ እና በአፋጣኝ ፍትህ እንዲረጋገጥ ከምናደርገው ጥረት ጎን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እያቀረብን ማንም ይሁን ማን ከህግ በላይ መሆን የማይቻል መሆኑን በአጽኖት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ኢትዮጵያን በተመለከተ ያሰራጨው ዜና ስህተት መሆኑን አምኖ ይቅርታ ጠየቀ
***************
(ኢ.ፕ.ድ)
አምንስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት የታዋቂውን አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኢትዮጵያ በተከሰተው ቀውስ ሳቢያ "መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል" በሚል ያሰራጨው ዘገባ ስህተት መሆኑን በይፋዊ የቲዊተር ገጹ ላይ አምኖ ይቅርታ ጠየቀ።

ድርጅቱ በይፋዊ የቲዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው አምንስቲ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊ መብት እኩል እንዲከበር ድጋፉን ያደርጋል። አሁን ያለውን የአገሪቱን ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታም ድርጅቱ ይረዳል ብሏል።

የታዋቂውን አርቲስት ግድያ ተከትሎ በአገሪቱ በተነሳው ሁከት ሳቢያ "መንግስት የሰብዓዊ ምብት ጥሰት ፈጽሟል፤ በርካቶች ለተቃውሞ ወጥተዋል" የሚል ይዘት ያለው ዘገባ በአምኒስቲ በኩል መሠራጨቱ ስህተት ነው ሲል በይፋ አምኗል።

አምንስቲ አክሎም በተሰራጨው የተሳሳተ መረጃ ሳቢያ ለተከሰተው አሉታዊ ውጤት ይቅርታ እንጠይቃለን ብሏል።

አምንስቲ በወቅቱ የለቀቀውን መረጃ ከትዊተር ገጹ ላይ ማጥፋቱ ታውቋል።
የተወሰኑ የምግብ ሸቀጦች ሙሉ ለሙሉ ከቀረጥ ነፃ እየገቡ መሆናቸው ተገለጸ
************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- መንግሥት የሸቀጦችን ዋጋ በማረጋጋት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በአምስት መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረውን ቀረጥ ሙሉ ለሙሉ ማንሳቱ ተገለጸ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በምግብ ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ የዳቦ ስንዴ፣ ሩዝና የታሸጉ የሕፃናት ምግቦችን ሙሉ ለሙሉ ከቀረጥና ታክስ ነፃ አድርጓል፡፡

መንግሥት ከእነዚህ ምርቶች ያገኝ የነበረውን ገቢ ሙሉ ለሙሉ በመሰረዝ ምግቦቹን ከውጭ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች ቀረጥና ታክሱን ነፃ አድርጎ ኅብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ማግኘት ያለበትን መሠረታዊ የምግብ ሸቀጥ በቀላሉ እንዲያገኝ እገዛ እያደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም አቅርቦቱ እንዲሻሻልና ጥራቱ እንዲጨምር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የምግብ ዘይትን በተመለከተ ከዚህ በፊት በመንግሥት ድጎማ ይገባ የነበረው ፓልም ወይም በተለምዶ የሚረጋው ዘይት መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ይዘታቸው ፈሳሽ የሆኑ እና በቫይታሚን ኤ እና ዲ የበለፀጉ የዘይት ምርቶች ከዚህ በፊት በተመረጡ 24 አስመጪዎች እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ማንኛውም አስመጪና የግል ነጋዴ እነዚህን ምርቶች ከውጭ ሲያስገባ ከቀረጥ ነፃ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ስርጭቱንና ዋጋውን በተመለከተ መንግሥት የሚቆጣጠራቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑና የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በሚል በመንግሥት ድጎማ ብቻ ይገቡ የነበሩ ምርቶች በግል ነጋዴዎች ጭምር እንዲገቡ ተደርጓል።ይህ የሆነው አቅርቦቱ እንዳይቋረጥና ነጋዴውም ተገቢውን ትርፍ እንዲያገኝ ለማስቻል ነው።

ነገር ግን ከዚህ ባለፈ ነጋዴው ባልተገባ መንገድ እንዳይጠቀምና ምርቱ ወደ ግለሰቦች እጅ እንዳይገባ መንግሥት ጥብቅ ክትትል ያደርጋል።
በአገሪቱ ከሚያስፈልገው የምግብ ዘይት ስድስት በመቶ በአገር ውስጥ የሚመረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀሪው ከውጭ የሚገባ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በአጠቃላይ በአገር ውስጥ የሚመረተውን የምግብ ዘይት ጨምሮ በግለሰብ ነጋዴዎችና በአስመጪዎች በየወሩ እስከ 42 ሚሊዮን ሌትር የምግብ ዘይት እየገባ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2012
ተጨማሪ 1 ሺህ 386 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተገለጸ
**********
(ኢ.ፕ.ድ)

በለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 22,101 የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ 1,386 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 32,722 ደርሷል።

በሌላ በኩል 414 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ስሆን በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ 12,938 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
”የአመጽ ጥሪ አቅራቢዎች ቅጥረኛና ከሀዲዎች በመሆናቸው ህዝቡ ጆሮ ነስቷቸዋል" - ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን
********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ:- የአመጽ ጥሪ አቅራቢዎች ቅጥረኛ እና ከሀዲዎች መሆናቸው ስለሚታወቅ ህዝቡ በተደጋጋሚ ጆሮ እንደነሳቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አስታወቁ። ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ለጸረ ሰላም ሃይሎች ጥሪ ጆሮ ባለመስጠት ላሳየው የሰላም አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል ።

ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ለትናንት ተላልፎ የነበረው አይነት ተመሳሳይ የአመጽ ጥሪዎች በተደጋጋሚ አልተሳኩም ፣ ያልተሳኩት ደግሞ የአመጹ ጥሪ አቅራቢዎች ቅጥረኛ እና ከሀዲዎች መሆናቸው ህዝቡ ስለሚያውቅ እንደሆነ አስታውቀዋል ።

እንደ ኮሚሽነር አራርሳ ገለጻ፤ ህዝቡ ትላንት ሲታገል ለምን አደባባይ ይወጣ እንደነበር በደንብ ስለሚያውቅና ዛሬ የሚተላለፈው ተመሳሳይ ጥሪ ደግሞ ለምንና ለማን ፍጆታ እንደሆነ ይረዳል። በመሆኑም ትናንት በኦሮሚያ ክልል የተጠራው የአመጽ ጥሪ ከሽፎ ህዝቡ በተለመደው የእለት ተእለት ስራው ላይ ውሏል።

“በጸጥታው መዋቅር ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በገንዘብ ድጋፍ የአመጽ ጥሪን ለማስፈጸም የሚጥሩ የጸጥታ ኃይል አካላት ነበሩ። እነዚህ ወገኖች ከስልጣን በተባረረው ከጥፋት ኃይል ጋር ሆነው ችግር ሲፈጽሙ ቢቆዩም ተለይተውና ተጣርቶ እርምጃ በመወሰዱ አሁን እየታየ ላለው የሰላምና የጸጥታ ለውጥ የራሱን አስተዋጾ አበርክቷል። ለትናንቱ ጥሪ አለመሳካትም የተወሰደው እርምጃ ትልቅ አስተዋጾ አድርጓል”ብለዋል ፡፡

ሰኞ እለት በምዕራብ አርሲ እና በምዕራብ ሀረርጌ አካባቢ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ወዲያውኑ መቆጣጠር ተችሏል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አመጹ በተጠራበት እለት ትናንት ግን በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ከተሞች ምንም አይነት የጸጥታ ችግር አልታየባቸውም፤ በአንጻሩ መደበኛ ሥራ ሲከናወን መዋሉን አመልክተዋል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲደረግ የነበረው የአመጽ ጥሪ የወደቀ ሃሳብ በመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተደጋጋሚ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደረጉ ጥሪዎች ተቀባይነት እያገኙ አይደለም፤ ይህም ህዝቡ “ለሽፍታ እና ለተላላኪ እጅ አንሰጥም” የማለቱ አብይ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

“እነዚህ ሃይሎች ጥሪውን ለምን እንደሚያደርጉት በግልጽ ይታወቃል፡፡ ከስልጣን የተባረረው ኃይል በሚሰጠው ገንዘብ የሚከናወን ሥራ ነው፤ ጥሪውን የሚያደርጉት አካላት ገንዘቡን ተቀብለው ሂሳቡን ለማወራረድ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች ናቸው” ብለዋል።

ከሰኞ እለት ማታ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ እንደተነሳ ግጭት እንደተፈጠረ በማስመስል ከዚህ በፊት የነበሩ የተቃውሞ ምስሎችን በመጠቀም ቅስቀሳ ለማድረግ መሞከሩን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ነገር ግን በክልሉ ትናንት ምንም አይነት ግጭት እንዳልነበረና የተጎዳ ሰውም እንደሌለ ገልፀዋል።

ችግር ቢኖር ኖሮ የክልሉ መንግስት ከዚህ በፊት በአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ወቅት የተፈጠረውን ሳይደብቅ በሙሉ እንዳሳወቀው ሁሉ ያሳውቅ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት ችግር ከተፈጠረ የምንደብቅበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፤ ከተፈጠረም ወንጀለኞችን ፈልገን ለህግ እናቀርባለን እንጂ የምንደብቀው ጉዳይ አይኖርም ብለዋል።

የአመጽ ጥሪ በተደረገበት እለት በተቃራኒው በአምቦ፣ በጎባ እና በሌሎች ከተሞች ላይ ወጣቶች በጽዳትና መሰል የልማት ስራዎች ላይ ተሰማርተው መዋላቸውን ጠቁመዋል።

ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ለጸረ ሰላም ሃይሎች ጥሪ ጆሮ ባለመስጠት ላሳየው የሰላም አጋርነት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀጣይም በተመሳሳይ ለሰላምና ለልማት ያለውን አቋምና ጽኑ ፍላጎት አጠናክሮ እንዲቀጥል ፤ ከጸጥታ ሃይሉ ጋርም ተባብሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ13/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስካሁን 120 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ
********************************
- የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸሙም 78 በመቶ ደርሷል
(ኢ ፕ ድ)
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስካሁን 120 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ። የግድቡ አጠቃላይ ግንባታም 75 በመቶ መድረሱ ተጠቁሟል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ ከህዳሴው ግድብ የቦርድ አመራሮች እና ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ እንደተገለጸው የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 75 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የአሌሌክትሮ ሜካኒካል ስራው 46 ነጥብ 5 በመቶ፤ የሲቪል ስራው ደግሞ 88 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል።
ከወጪም አኳያ ለግድቡ በኮንትራት ደረጃ የተያዘው አጠቃላይ በጀት 78 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ 120 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የግድቡ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ አስታውቀዋል።
ግድቡን ለማጠናቀቅም 160 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ኢንጅነሩ ተናግረዋል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ግድቡ በመጪው አመት አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ሁሉ ተደርጎለት ነሀሴ 2013 ላይ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ በመያዝ ለህዝቡ ይበሰራል ብለዋል።
ከመስከረም እስከ ነሀሴ 2013 የሚሰሩ ስራዎች ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት ወሳኝ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ አግባብ መስራት ከተቻለ “በ2015 ዓ.ም የግደቡን የምረቃ ሪባን እንቆርጣለን” ብለዋል።
በጌትነት ምህረቴ
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1778 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የ 20 ሰዎች ህይወት አለፈ
****************************
(ኢፕድ)
በ24 ሰዓታት ለ21 ሺህ 456 ሰዎች በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 1778ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተረጋግጧል።
20 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ሲያልፍ በቫይረሱ የሞቱት ቁጥር 620 ደርሷል።
በዛሬው እለትም 228 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች
ቁጥር 13 ሺህ 536 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።
ሌሎች 248 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል።
አጠቃላይ እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 35 ሺህ 836 ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ ያለባቸው
ሰዎች ቁጥር 21 ሺህ 678ደርሷል።