Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
25K subscribers
41K photos
338 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት አመት 47 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ገቢው ከእቅዱ 105 ነጥ ብ 1 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
ይህም ከባለፈው አመትም ጋር ሲነጻጸር በ31 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ መኖሩን ጠቁመው ÷ ተቋሙ ከውጭ የስልክ ጥሪ 147 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን ገልጸዋል። ከዚያም ባለፈ 10 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብድር መመለስ ተችሏልም ነው ያሉት።
የዚምባብዌ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው አለፈ
----------------------------------------------------
የዚምባብዌ የግብርና ሚኒስትር ፔሬንስ ሺሪ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ በኮሮናቫይረስ መሞታቸው የተረጋገጠው በምርመራ መሆኑንም የአገሪቱ መንግሥታዊ ጋዜጣ ሄራልድ ፕሬዚዳንቱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ሚኒስትሩ የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት በሚያዘው በኮሮናቫይረስ ለሞቱ ሰዎች የሚደረገው የቀብር ስነ ስርዓት መመሪያ መሰረት በነገው እለት እንደሚቀበሩም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የ65 አመቱ ሚኒስትር በመዲናዋ ሃራሬ በሚገኝ የግል ሆስፒታል ረቡዕ እለት ሕይወታቸው ማለፉ BBC
#አረንጓዴአሻራ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት በመገኘት ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ጋር ችግኝ ተክለዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሊት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው
*****************
(ኢ.ፕ.ድ)
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሊት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን እየገለጹ ለግድቡ ያላቸውንም ድጋፍ እየገለጹ ነው።
በከተማዋ የተለያዩ መኖሪያ ሰፈሮች ህዝቡ በየቤቱ በራፍ በመሆን፤ በጋራ መኖሪያ ቤት ያሉ ደግሞ በየብሎኮቻቸው በረንዳ ላይ በመውጣት ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በተመሣሣይም ተሽከርካሪዎች ጡሩንባዎቻቸውን በማሰማት በግድቡ የመጀመሪያ ሙሊት የተሠማቸውን ደስታ እየገለጹ ነው።
በአፍሪካ ህብረት የሚመራውና ለጊዜው ተቋርጦ የነበረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ዛሬ ይቀጥላል
**************************
(ኢ ፕ ድ)
በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ከሁለት ሳምንታት በፊት እ.አ.አ ሐምሌ 13/2020 የተቋረጠው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ዛሬ ከሰአት ይቀጥላል።
ድርድሩ ከሳምንት በፊት ሊቀጥል የነበረ ቢሆንም በሱዳን በኩል በቀረበው ለአንድ ሳምንት የይዘግይልኝ ጥያቄ መሠረት ለአንድ ሳምንት መዘግየቱን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሶስትዮሽ ድርድሩ ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ለቀጣዩ አንድ ሳምንት ይቀጥላል ተብሏል፡፡
የዚህ ሳምንቱ ድርድር ቀደም ሲል ከተካሄደው የ11 ቀናቱ ድርድር በኋላ ለመሪዎች በቀረበው ሰነድ መሠረት መሪዎቹ ባስቀመጠጡት አቅጣጫ የሚቀጥል ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ፍትሓዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ድርድሩን ለመቋጨት ትሠራለች ሲል ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስታውቋል።
ከነሃሴ መጨረሻ ሳምንት በፊት ምንም አይነት የቀጣይ አመት የትምህርት ምዝገባ ማካሄድ የተከለከለ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
********************************
(ኢ ፕ ድ)
ከነሃሴ መጨረሻ ሳምንት በፊት ምንም አይነት የቀጣይ አመት የትምህርት ምዝገባ ማካሄድ የተከለከለ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ለማድረግ ወላጆችን እያስገደዱ መሆኑ እና ምዝገባ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
ይህንን በተመለከተም የትምህርት ሚኒስቴር የኮምኒኬሽን ጉዳዬች ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ማንኛውም ትምህርት ቤት ከነሀሴ መጨረሻ በፊት ምንም አይነት ምዝገባ ማካሄድ እንማይቻል እና ይህንን ወሳኔ አልፈው ምዝገባ በሚያካሂዱ ትምህርት ቤቶች ላይም አስፈላጊው የዕርምት እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።
የምዝገባው የግዜ ሰሌዳ እንዲራዘም የተፈለገው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ ወላጆች እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የሚያደርጉትን ጉዞ በመግታት የ ቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ወላጆች ከተሳሳተ መረጃ እራሳቸውን በመጠበቅ እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልእና መንግስት ትምህርት እንዲጀመር ሲያሳውቅ ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አውቀው ልጆቻቸውን በእጃቸው ላይ የሚገኙትን የመማሪያ ቁሳቁሶች እንዲያነቡና እንዲያጠኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን "የፌደራል መንግስት፣ ኤርትራ እና አማራ ሊወረን ነው ታገሉ” በማለት የወጅራት ነዋሪዎችን ቢቀሰቅሱም ህዝቡ አሳፍሮ እንደመለሳቸው ተገለጸ
*************************
(ኢ ፕ ድ)
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን "የፌደራል መንግስት፣ ኤርትራ እና አማራ ሊወረን ነው ታገሉ” በማለት የወጅራት ነዋሪዎችን ቢቀሰቅሱም ህዝቡ አሳፍሮ እንደመለሳቸው ተገለጸ።
ትናንት በትግራይ ክልል የወጅራት ልዩ ስሙ ዓዲ ቀይሕ ነዋሪዎች የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ያስተባበሩትና ስማቸው ሊገለጽ ያልፈለጉ ወጣቶች ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ በበቅርቡ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ስዩም መስፍን የዋጅራት ህዝብን ህዝብ ሰብስበው፤ “ከድሮ ጀምሮ የወጅራት ህዝብ ጀግና ነው፤ አልገዛም ባይ ነው፤ ስለዚህ አሁንም የፌደራል መንግስት፣ ኤርትራ እና አማራ ሊወረን ነው ታገሉ” በማለት ቀስቅሰዋል።
የሰልፉ አስተባባሪዎች እንደገለጹትም፤ አቶ ስዩም የወረዳዋ ነዋሪዎች ያቀረበውን ጥያቄ ለማለባበስና ሌላ ውዥንብር ሊፈጥሩባቸው ቢሞክሩም
ህዝቡ ግን “እኛ የተሰበሰብነው ጥያቄያችን ልትመልሱልን መስሎን እንጂ ከማንም ጋር አንዋጋም በውጊያ ያተረፍነው ነገር የለም፤ ከሁሉም ጋር ተባብረን መልማት ነው የምንፈልገው” በማለት ለአቶ ስዩም መልስ እንደሰጧቸው የሰልፉ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።
ትናንት የተካሄደው ሰልፍም የህወሓት አመራሮች ጥያቄያችንን ከመመለስ ይልቅ የማፈንና ጥያቄውንም የማዳፈን አካሄዳቸው እየበዛ በመምጣቱ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሰልፉ ከነበሩ መፈክሮች ውስጥ “ወረዳችን ይመለስልን፤ ለዛችን ባህላችን ይከበርልን፤ ወጣቱ እየተሰደደ ነውና ስራ ይፈጠርልን፤ ለውጥ እንፈልጋለን” የሚሉ እንደሚገኙበት አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ወረዳችን ይመለስልን የሚል ሰለማዊ ሰልፎች ቢደረጉም መንግስት ይሄን ከመመለስ ይልቅ ሌላ ስም በመለጠፍ እያሸማቃቸው እንደሆነ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
ጥያቄ ያቀረቡ ወጣቶችን እየመረጡ ማሰቃየት እስርና ድብደባም በህዝቡ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ የሰልፉ አስተባባሪዎች ሳይገልጹ አላለፉም።
ተቋሙ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መዘረፉን አስታወቀ
********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2012 በጀት ዓመት በአራት ክልሎች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዘረፋ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ በመላ አገሪቱ በተቋሙ ልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ዝርፊያዎች ተባብሶ መቀጠሉን ጠቁመው፤ በበጀት ዓመቱ በአራት ክልሎች ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዘረፋ ብቻ ተቋሙ 35 ሚሊዮን 621 ሺ 688 ብር ኪሳራ ደርሶበታል።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ አንድ ትራንስፎርመር በአማካኝ 400 ሺ ብር የሚያወጣ ሲሆን፣ ከ20 እስከ 25 ዓመት አገልግሎት ይሰጣል። እንዲሁም አንዱ ትራንስፎርመር በትንሹ እስከ 200 አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በመላ አገሪቱ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች ላይ በሚደርሱ ስርቆቶች ተቋሙ አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ፈታኝ ከማድረጉ ባሻገር በአገሪቱ ለሚታየው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ መላኩ በበጀት ዓመቱ በኦሮሚያ ክልል 14 ሚሊዮን 130ሺ 314 ብር፣ በአማራ ክልል ሦስት ሚሊዮን 977ሺ ሦስት ብር፣ በአፋር ክልል 514 ሺ 370 ብር በደቡብ 17 ሚሊዮን ብር በድምሩ በአራቱ ክልሎች ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዘረፋ ብቻ ተቋሙ 35 ሚሊዮን 621 ሺ 688 ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ተቋሙ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ዘረፋ የፈጸሙና በኃይል ስርቆት ላይ በተሰማሩ 195 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ዘረፋ የፈጸሙ 30 ግለሰቦች ከ3 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2012
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞች አነስተኛ ደመወዝ ላላቸው ባልደረቦቻቸው ድጋፍ አደረጉ
****************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞች እና አመራሮች በተቋሙ ውስጥ ለሚሰሩና የወር ደመወዛቸው አነስተኛ ለሆኑ የስራ ባልደረቦቻቸው የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
“እኛው ለእኛው” በሚል መርህ የተደረገው ይሄው ድጋፍ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ከወር ደሞዛቸው በመቀነስ ከለገሱት የተገኘ መሆኑን የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድም ተክሉ አስታውቀዋል።
እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ይህ ድጋፍ ትልቅ ስራ ነው ተብሎ የታሰበ አይደለም፤ ነገር ግን በአንድ ተቋም ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የእርስ በእርስ መተሳሰብን ለማጠናከር ታስቦ የተደረገና ሌሎች መሰል ተቋማትም ይሄንኑ ተግባር እንዲያከናውኑ ለማነሳሳት ነው።
የዚህ አይነቱ እርስ በእርስ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልን በተቋም ውስጥ መገንባት ከተቻለ ተቋሙ ሊያሳከው የሚፈልገውን ግብ ከዳር ለማድረስ እንደ አንድ ግብአት የሚረዳ ይሆናል ያሉት አቶ ወንድም፤ በሰራተኞች መካከልም መዋደድና መተሳሰብን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በቀጣይም በተቋሙ የሚታሰበው ትልቁ ስራ እነዚህ ሰራተኞች እራሳቸውን በኢኮኖሚ የሚጠቅሙበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድም፤ የሰራተኛውን ችግር በቋሚነት ሊፈቱ የሚችሉ ስራዎች በተቋሙ እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰራተኞቹ የተደረገውን ድጋፍ ያስተባበሩት ወ/ሮ ብርሃኔ ደመቀ እንደተናጉት፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫናው በርትቶባቸዋል፤ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ የሚገኙና የወር ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ሰራተኞችን መደገፍ አስፈላጊ ሆኗል።
ይህንን የተቀደሰ ተግባር ከዳር ለማድረስም የድርጅቱ ሰራተኞችና አመራሮች ከወር ደመወዛቸው የሚቀነስ ገንዘብ በማዋጣት ለ43 የስራ ባልደረቦቻቸው ከጎናቸው መቆማቸውን በተግባር ማሳየት መቻላቸውን ወ/ሮ ብርሃኔ አብራርተዋል።
እንደ ወ/ሮ ብርሃኔ ገለፃ፤ እርስበርስ መረዳዳቱ በጣም አስፈላጊና ፈጣሪም የሚወደው ስራ ስለሆነ ድጋፍ የተደረገላቸውም ብቻ ሳይሆኑ ድጋፍ ያደረጉ ሰራተኞችም ደስተኛ ሆነዋል።
በእለቱ ድጋፍ ከተደረገላቸው ሰራተኞች መካከል የሆኑት ወ/ሮ ፀሀይ ደበሌ እና ወ/ሮ አበበች አስፋው እንደተናገሩት፤ የድርጅቱ ሰራተኞች ይህን መልካም ተግባር አስበው ድጋፍ በማድረጋቸው በእጅጉ ተደስተዋል። ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ እርስ በርስ እየተረዳዱ ማለፉን ፈጣሪ የሚወደው ተግባር ነው በሚል የስራ ባልደረቦቻቸው ያደረጉላቸው ድጋፍ ያልጠበቁት በመሆኑ ትልቅ ደስታን ፈጥሮላቸዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞችና አመራሮች ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ የወር ደመወዛቸው አነስተኛ ለሆኑ ሰራተኞች ተመሳሳይ ድጋፎችን ማድረጉ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2012
« የወንጀለኞች ቡድን በአገር ጥቅም ከመደራደር ወደ ኋላ አይልም » - ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ
****************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- የለውጡ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ወንጀል እየሰራ ያለው የወንጀለኞች ቡድን ወደ ሕግ የሚያቀርበው በመጥፋቱ ሥልጣን ይዞ እንደፈለገው ለመሆን ምንጊዜም በአገር ጥቅም ከመደራደር ወደ ኋላ እንደማይል ተገለጸ፡፡
ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ የለውጡ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ወንጀል እየሰራ ያለው የወንጀለኞች ቡድን ወደ ሕግ የሚያቀርበው በመጥፋቱ ሥልጣን ይዞ እንደፈልገው ለመሆን በአገር ጥቅም ከመደራደር ምንጊዜም ወደ ኋላ የሚል አይደለም።ሁሉም ወንጀለኞች የአገርን ጥቅም አሳልፈው አይሰጡም።የአገርን ጥቅም አሳልፈው የሚሸጡ ግን ሁሌም ወንጀለኞች ናቸው፡፡
መፈንቅለ መንግሥት የማድረግ ፍላጎት ያለው ይህ የወንጀለኞች ቡድን የለውጡ መንግሥት ሥልጣን ላይ እንዲቆይ እንደማይፈልግ አመልክተው፤ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል የደንቆሮዎች ፖሊሲ የአገርን ሉዓላዊነትና ነፃነት ለግብጽ አሳልፈው መስጠት የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በሚጀመርበት ጊዜ ሀጫሉን በመግደል ለዜጎች ሞትና ለንብረት ውድመት እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል።
ይህ የወንጀለኞች ቡድን ኦሮሞና አማራን ማጋጨት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ መቀልበስ ይቻላል ብሎ እንደሚያምን አመልክተው፤ ለዚህም ሲባል ሀጫሉ እንዲገደል ማድረጉ የቡድኑ የሴራ ፖለቲካ ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል።
በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች በጸረ ለውጡ ቡድን የተቀነባበሩ መሆናቸውን አውስተው፤ ከሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት መፈንቀለ መንግሥት ተሞከረ፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ቦምብ ተወረወረ፣ ቡራዮ በተከሰተው ችግር መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ኮማንዶ ቤተ መንግሥት መግባት፣በጥቅምትና ኅዳር ወራቶች 2011 ዓ.ም አካባቢ በኦሮሚያና በጌዲዮ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል፣ በአማራ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራና በቅማንት ግጭቶች ተከስተው በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸው አመልክተዋል።
እንዲሁም የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችን እንዲጋጩ መደረጉን፣ ቤተ ክርስቲያንና መስኪዶች መቃጠላቸውና ይህ መፈንቅለ መንግሥት መደረግ አለበት ብሎ ሲጎተጉት በነበረውና በተለያየ መንገድ ለውጡን እየመራ ያለ መንግሥት ደካማ ነው፤ ጸጥታ ማስከበር አይችልም የሚለውን ነገር ለማስረገጥ በማሰብም ሴት ልጆችን መጥለፉንና ጠለፍኩ ብሎ መናገር ያልቻለው በሕጋዊነት በአገር ላይ ስለሚኖር መሆኑንም ተናግረዋል።
ጸረ ለውጥ ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖለቲካ ተቀባይነት እንዳያገኙ ብዙ ሴራዎች መፈጸሙን አመልክተው፤ ይህ ጸረ ለውጥ ቡድን ህዳሴ ግድብ ተሸጠ አለ፣ ሌላም ሌላም የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ነዛ ያቀደው ግን ሊሳካለት አለመቻሉና ወደፊትም እንደማይሳካት ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የወንጀለኛውን ቡድን አባላት የትም ይሁን የትም የገቡበት ገብቶ ይዞ ፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተው፤ እስካሁንም መንግሥት በጣም ትዕግስት አድርጓል፤ ትዕግስት ማድረጉ ትክክል ቢሆንም ወንጀል በተለይም ልታልፈው በማይገባ ወንጀል ላይ ትዕግስት ማድረግ የለበትም፤ ምክንያቱም የኔት ወርክ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጀል የሚፈጸመው በተመሳሳይ ቡድን ነው ብለዋል፡፡
የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመጥለፍ የተከሰሱ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ
***************************
በእነ ከሊፋ አብዱረህማን የክስ መዝገብ የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ህዳር 24 እና 25/2012 ዓ.ም በመጥለፍ በሽብር ወንጀል ከተከሰሱት 17 ግለሰቦች መካከል ዘጠኙ በዛሬው ዕለት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በሦስት የሽብር ወንጀል የተከሰሱት ተከሳሾቹ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የተከሰሱበት ወንጀል ተነቦላቸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ተከሳሾቹ በበኩላቸው ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቃወሚያ በጽሁፍ አቅርበዋል።
ከሳሽ ዐቃቤ ህግ በመቃወሚያው ላይ ምላሽ እንዲሰጥና ትእዛዝ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 25/2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። EBC
“ቄሮ የለውጥ እንጂ የጥፋት ኃይል አይደለም” - ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር
********************************
(ኢፕድ)
አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ክልል ወጣት(ቄሮ) የለውጥ እንጂ የጥፋት ኃይል እንዳልሆነ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ አስታወቁ፡፡ ለዚህም የታገለለትንና ዋጋ የከፈለበትን ለውጥ ወደኋላ የሚመልሱ አክራሪ ጽንፈኞችን የሁከት ጥሪ በእምቢታ በማክሸፍ የለውጥ ኃይል መሆኑን በድጋሚ በግልጽ ማረጋገጡን አመልክተዋል።
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ቄሮ ለውጡን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣው መሆኑን በማስታወስ ጽንፈኛ ኃይሎች ይህንን ኃይል የከንቱ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ የሁከትና የአመጽ ጥሪዎችን በተለያዩ ጊዜያት ቢያስተላልፉለትም ለጥሪያቸው እምቢተኝነቱን በመግለጽ የለውጥ ኃይልነቱን በአደባባይ በተጨባጭ አስመስክሯል ብለዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ ገለጻ፤ አሁን የሚደረጉ የሁከትና የአመጽ ጥሪዎች ባለፈው የተፈጠረውን ችግር ማስቀጠል የሚፈልጉ ኃይሎች ጥሪ ነው፤ ሰዎቹ የቀደመውን ሁከት ያቀነባበሩ ናቸው፡፡ በሕዝብ የተተፉ፣ ሌሎችም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደረጉ ናቸው፡፡
እነዚህ ኃይሎች አንድ እግራቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ፤ አንድ እግራቸውን ደግሞ ውጪ አድርገው የሚጫወቱ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥፋቶች እንዲቀጥሉ የሚፈልጉና ይሄንን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑም አስታውቀዋል ።
ከዚህ በፊት ወጣቱ ለለውጥ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ በእነሱ የተፈጠረ አጀንዳ እንደሆነ በማስመሰል እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቁመው፣ እነዚህ ሰዎች ዛሬ ላይ የሚያደርጉት ጥሪ እና እንቅስቃሴ፤ ትናንት ወጣቱ ሲያደርገው ከነበረው ትግልና እንቅስቃሴ ጋር በጣም የተለያየ ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ የማይገናኝ ሆድና ጀርባ መሆኑን አመልክተዋል ።
ለዚህ እኩይ ተግባራቸው መሳካት እነሱ ቄሮ እያሉ የሚጣሩ ቢሆንም፤ ቄሮ የተፈጠረው ለእኩልነት ነው፣ ለፍትህ ነው የታገለው፤ ሕይወትም የከፈለው ለዚህ ነው ብለዋል ። ለሕዝቦች እኩልነትና ለፍትህ የታገለው ቄሮ ለእኩይ አላማቸው ጆሮውን በመንፈግ በኦሮሚያ ያለው ቄሮ የለውጥ ኃይል እንጂ የጥፋት ኃይል አለመሆኑን አሳይቷቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ እንደሚሉት፤ ቄሮ የታገለው የኦሮሞን ህዝብ ከሌላ ብሔር ጋር እኩል እንዲኖር፤ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ነው። ሁሉም ሃይማኖት እኩል እንዲሆንና በእኩል እንዲከበር ነው። ከዚህ በተቃራኒው አንዱ የበላይ፣ ሌላው የበታች እንዲሆን፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ እንዲኖር አይደለም።
ከውጪም ከውስጥም ሆነው ለእኩይ አላማ የሚንቀሳቀሱ እነዚህ ኃይሎች ትናንትና ቄሮ ጠይቆና ታግሎ ያመጣው ለውጥ በእነርሱ አጀንዳ እንደተፈጠረ አድርገው ለመሳል የሚያደርጉት ጥረት ከጅምሩም ትክክል አልነበረም፤ አሁን ደግሞ በተጨባጭ ትክክል እንዳልሆነ ከተግባራቸው ተረጋግጧል። ጉዞው ለየቅል መሆኑን ማየት ተችሏል፤ አሁንም መመልከት ይቻላል።
እነዚህ ኃይሎች እየተደረጉ ያሉት ቅስቀሳ ሆነ ጥሪ አገር የሚያጠፉ ነው ፤ ይሄን ለውጥ ወደኋላ እንዲመለስ የሚያደርግ ነው ፤ ይሄን የሚያደርጉ ቅጥረኞች ናቸው፤ ትናንትና እኛ ሞተን ያመጣነውን ለውጥ፣ ያመጣነውን እኩልነት ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው። ይሄን ጥረታቸውን ለማሳካትም በወጣቱ ስም የሚነግዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
“አሁንም የሚደረጉ ጥሪዎች እንዲከሽፉ፤ ሲቀሰቅሱ የነበሩት የጥፋት አጀንዳዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ያደረገው ወጣቱ ራሱ ነው። በመሆኑም ይሄ ቅስቀሳና ጥሪ የወጣቱ አጀንዳ አይደለም። የጥቂት አክራሪዎች አጀንዳ ነው። ኦሮሚያ ውስጥ ደግሞ ወጣቱ የአክራሪነት ዝንባሌ የለውም። ጥያቄው ለሁሉም ሕዝቦች የእኩልነት፣ የፍትህና የማንነት ጥያቄ እንዲረጋገጥ ነው። ኦሮሚያ ውስጥ ቄሮ ትግል ሲጀምር ለኦሮሞ ብቻ አይደለም፤ ለሁሉም ነው የታገለው። ለሁሉም ነው የሞተው። አሁንም ይሄው አስተሳሰብ ነው ወጣቱ ውስጥ ያለው” ብለዋል ።
አሁን ያለው የብሔር አክራሪነትና የሃይማኖት አክራሪነት ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ቄሮ አመለካከት አይደለም። ይሄንን የሚገልጽም አይደለም። አሁን የተደረገው ጥሪ የወደቀውም ከዚህ አንጻር ነው። አጀንዳቸውን የወጣቱ አጀንዳ ማድረግ ያልቻሉትም ከዚህ አንጻር ነው።
አሁን ወጣቱና የጸጥታ ኃይሉ አብሮ እየሰራ ነው። በዚህም በቅርቡ በተፈጠረው ግርግር ምንም ውስጥ የሌሉ ወጣቶች ችግሩን ለማስቀረት ሲሰሩ አካላቸውን ሕይወታቸውን ከፍለዋል። የብሔር ግጭት እንዳይፈጠር፤ የሃይማኖት ግጭት እንዳይፈጠር ከማድረግ አኳያ፤ አሁን እየሆነ ያለው ነገር ክፋት ነው በማለት ከፖሊስ ጎን ሆነው እንደ መንግስት ምንም ኃላፊነት ሳይኖራቸው ሕይወታቸውን የገበሩ ጥቂት እንዳልሆኑ አስታውቀዋል ።
ይሄ ደግሞ ትናንት የታገለለት የፍትህና ለእኩልነትና ዓላማ ወደኋላ እንዳይመለስ የከፈለው መስዋዕትነት ነው። ሌሎች ጓደኞቻቸው ቀድመው የሞቱለት ዓላማ ወደኋላ እንዳይቀለበስ ለማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል። እዚም እዛም የሚታየውም ጥቂት ቅጥረኞች የሚያደርጉት እንጂ የወጣቱ አጀንዳና ተግባር አይደለም ብለዋል።
ለምሳሌ፣ ድንጋይ የሚያስቀምጡ ቅጥረኛ ኃይሎች አሉ፤ ወያኔም አሰልጥኖ የሚልካቸው ኃይሎች አሉ። እነዚህን ደግሞ ከጸጥታ ኃይሉ በተጓዳኝ ወጣቶች ናቸው ይዘው ለህግ እያቀረቧቸው ያሉት። በዚህም አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሰላም እንደሆነ አስታውቀዋል።
👍1
ከ8ኛና 12ኛ ክፍል ውጭ ላሉ ተማሪዎች የነፃ ዝውውር መደረጉ ትምህርት ጥራት ላይ የሚፈጥረው ችግር እንደማይኖር የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
*************************
የትምህርት ሚኒስቴር ከ8ኛ እና 12 ኛ ክፍል ውጭ ያሉ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል ካለፈተና እንዲዛወሩ መወሰኑን ተከትሎ የትምህርት ጥራት ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ) የነፃ ዝውውር መደረጉ ተማሪዎች ላይ የሚፈጠረውን ጫና መንግስት እንዲሸከም በማድረግ ከትምህርት ውጭ የቆዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ለማድረግ ታስቦ ነው ብለዋል።
አሁን በምንከተለው ስርዓተ ትምህርት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ አንችልም ያሉት ሚኒስትሩ 2014 ላይ ወደ ተግባር የሚገባ ስረዓተ ትምህርት የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
የትምህርት ጥራት ችግርን በዘላቂነት የሚፈታው ይህ ስርዓተ ትምህርት እንጂ ፈተና በመፈተንና ባለመፈተን የሚረጋገት የትምህርት ጥራት አይኖርም ነው ያሉት።
የትምህርት ሚኒስቴር የነፃ ዝውውር ውሳኔን ሲወስን የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድና በተለያየ ምክንያት
የኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝን ተከትሎ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ስለቆዩ በዚያው እንዳይቀሩ ለማድረግ ታስቦም ጭምር ነው።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
ለ12ኛ ክፍል አይነ ስውራን ተማሪዎች እየተሰጠ ያለው የተስማሚ ቴክኖሎጂ ስልጠና በታሰበለት ደረጃ እየሄደ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
----------------------------------------------------
ሚኒስቴሩ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሁሉም አይነሰውራን ተማሪዎች በኦንላይን እንዲፈተኑ ለማድረግ በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑን አስታወቋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ ዓሊ ተማሪዎቹ ፈተናውን በኦንላይን ለመፈተን የሚያስችላቸውን መሰረታዊ እውቀት እየያዙ መሆኑን ተናግረዋል።
ገና ስልጠናው ሳይጀመር ለፈተና ብቁ ሊሆኑ አይችሉም ብሎ መገመት ለተማሪዎቹ ዝቅ ያለ ግምት መስጠት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በተቻለ መጠን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ አስፈላጊነቱ አጋዥ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችም ለመመደብ እቅድ መያዙን አብራርተዋል።
ተማሪዎቹ እንደየ አካባቢያቸው ሁኔታ ከዚህ ቀደም የኮምፒውተር እውቀት ያላቸውና የሌላቸው በመሆናቸው ተመሳሳይ አቀባበል የላቸውም ያሉት የተስማሚ ቴክኖሎጂ ለአይነስውራን በኢትዮጵያ ዳይሬክተርና አሰልጣኝ ታምሩ እውነቱ (ዶ/ር) ይህንን ታሳቢ በማድረግ ተማሪዎችን በመለየት ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
ተማሪዎቹ በበኩላቸው አብዛኞቻችን ከዚህ ቀደም የኮምፒውተር እውቀት ስለሌለን የስልጠናው ጊዜ ቢራዘም የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ 250 ዓይነስውራን ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተስማሚ ቴክኖሎጂ ስልጠና እየወሰዱ ነው።
ስልጠናው ለፈተና ዝግጁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ለሚኖራቸው የስራ ጊዜ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።
በየካ ክፍለ ከተማ የጎረቤቷን የኤቲኤም ካርድ በመስረቅ ከ5መቶ 80 ሺ ብር በላይ ወጪ አድርጋ ለግል ጥቅሟ ያዋለች ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ገለፀ፡፡
***
የግልተበዳይ ወ/ሮ ሰናይ ቦጋለ እና ወንጀሉን ፈፅማለች የተባለችው ግለሰብ የቅርብ ግንኙነት እና ጉርብትና አላቸው፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮተቤ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መርማሪ ረዳት ሳጅን እስጢፋኖስ ገ/ታቲዎስ እንደገለፁት ተጠርጣሪዋ ከግል ተበዳይ ጋር ያላትን ቅርበት ተጠቅማ ወደ ወ/ሮ ሰናይ ቦጋለ መኝታ ክፍል በመግባት ቁም ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ የነበረ የዘመን ባንክ ኤቲኤም ካርድ ከነ ሚስጥር ቁጥሩ ሰርቃ በመውሰድ እና በተለያዩ ጊዜያት ከ5መቶ 80 ሺ ብር በላይ ከባንኩ ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅሟ አውላች፡፡
የግል ተበዳይ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ መሆናቸውን የገለፁት ተወካያቸው አቶ ወርቁ ለገሰ ወ/ሮ ሰናይ ቦጋለ የኤቲኤም ካርዱን ከባንኩ ከወሰዱበት ጊዜ ጀምሮ ተጠቅመውበት እንደማያውቁ እና ባላወቁት ሁኔታ ገንዘቡ ከባንክ ወጪ መደረጉን ባወቁ ጊዜ ለፖሊስ ማመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን ግለሰቧ የፈፀመችው ተግባር በመተማመን መካከል መልካም ግንኙነትን የሚያጠለሽ ክስተት ሊፈጠር እንደሚችል በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡
ፖሊስ ከባንኩ ባገኘው መረጃ መሰረት በተጠርጣሪዋ ላይ ክትትል በማድረግ በየካ ክፍለ ከተማ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ስር እንዳዋላት እና በአሁኑ ወቅትም ምርመራ እየተጣራባት እንደሚገኝ ያስረዱት ረዳት ሳጅን እስጢፋኖስ ገ/ታቲዎስ የኤቲኤም ካርድ የሚጠቀሙ ግለሰቦች የሚስጥር ቁጥራቸውን ከተቻለ በቃላቸው መዝግበው በመያዝ ወረቀቱን ማስወገድ ይህ ካልተቻለም ሚስጥራዊ ቦታ በማስቀመጥ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኳታር ዶሃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል ገቡ
*********^

በኳታር ዶሃ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ሰሞኑን በኤምባሲው በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በመገኘት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል ገብተዋል።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት በኳታር የኢፌዲሪ አምባሳደር አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በእለቱ ባደረጉት ንግግር አገራችን ይህንን ታሪካዊ ድል ማስመዝገብ በመቻሏ ለሁሉም የአገራችን ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።

አምባሳደሯ አገራችን የውሃ ሃብቷን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ለፈለገችው ልማት የመጠቀም ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብቷን በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪመ የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ እስኪደርስ ድረስ እያንዳንዱ ዜጋ የአቅሙን ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በፕሮግራሙ የታደሙ የዳያስፖራ ተወካዮች እና የሚሲዮኑ የሥራ ባልደረቦችም የግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ለአገራችን እና ለመላው ኢትዮጵያዊያን አኩሪ ድል እንደሆነ እና የዚህ አኩሪ ታሪካዊ ስኬት አካል በመሆናቸውም ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። የግድቡ የግንባታ ስራ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ የበለጠ አጠናክረው ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ (575,000 ብር) ዋጋ ያለው የቦንድ ግዥ ለመፈጸምም ቃል ገብተዋል። ሌሎችንም የየማህበር አባሎቻቸውን እንዲሁም መላ የዳያስፖራ አባላትን ለመቀስቀስና ቦንድ ለማስገዛት እንደሚንቀሳቀሱም ቃል ገብተዋል።

በዶሃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ወዳጆች የግድብ ግንባታው ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል::

ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈም በግድቡ ዙሪያ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ለመስራት ያለመ እና ከአስራ አምስት በላይ አባላት ያሉት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንም ተመስርቶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህው በርካታ የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው አማካኝነት ስለ ህዳሴው ግድባችን በአርብኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን በመጠቀም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።
"ኢትዮጵያዊያን ዳግመኛ ለትውልድ ውርስ የሚሆን አረንጓዴ አሻራቸውን ተባብረው አሳርፈዋል፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላሳካው ለዚህ እቅድ አስደማሚ ውጤት ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፤ አመሰግናለሁ"
👉 ዶ/ር ዐብይ አህመድ
"አንድ ክልል ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት እገጥማለሁ ብሎ ለጦርነት ቢነሳ መጀመሪያ ከራሱ ክልል ጋር ነው የሚጋጨው፤ ሁለተኛ ከመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይጋጫል" - ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ
• አንድ ክልል ከፌዴራል መንግስቱ ጋር በስምምነት ነው መስራት ያለበት። ህገ መንግስቱን በመጣስ ከህግ ውጭ የሚሄድ ከሆነ ደግሞ በህገ መንግስቱ ውስጥ መፍትሄ አለው።
• አንድ ክልል ተነስቶ የፌዴራል መንግስትን በጦርነት አፈሙዝ አሸንፌ የሆነ ነገር አደርጋለሁ የሚል ካለ የእሳት ራት ነው የሚሆነው። ጦርነት ይመጣል ብዬ አንድ ቀንም ሰግቼ አላውቅም።
• ክላሽን አሸክመህ ከታንክና ከሚሳኤሎች ጋር የምታጋጥመው ሰው አይኖርም። እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ የሚገባ ወጣትም ያለም አይመስለኝም።
• የፌዴራል መንግስቱን አስተሳሰብ አውቃለሁ፣ የክልሎችንም አቅም አውቃለሁ፤ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ውስጣዊ አቋም አውቃለሁ።
• ግብጾች የመጨረሻ ርብርብ ያደረጉት፣ መፈንቀለ መንግስት አድራጊው ወንጀለኛ ቡድን የተኮሰው የመጨረሻዋ ጥይት ሀጫሉን የገደለበትና ያን ተከትሎ የመጣውን ግጭት ነው
• ይህ ማለት ግን ትንኮሳ ያቆማሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን ስጋቱ በግብጽ በኩልም በእኛ በኩልም ውሃ መያዝ ስለጀመርን እየቀነሰ ይሄዳል።
• የህዳሴው ግድብን ፈጥነን ስራችንን በጨረስን ቁጥር ስጋታችን ይቀንሳል። ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ስጋቱ መቶ በመቶ ባይጠፋም ትርጉም ያለው አይሆንም። ግብጾችም ፋይናንስ አያደርጉትም።
• አሁን ያለውን የለውጥ አመራር ቤተ መንግስት ያስገባው ማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።
• ለውጡ ከመጣ በኋላ ፖለቲከኛ፣ ተንታኝ፣ ያልሆነ የለም። ያልተከፈተ የሚዲያ አይነት የለም።
• መንግስት ትግስት ማድረጉ ትክክል ቢሆንም የሚታገሰውና የማይታገሰውን ነገር መምረጥ አለበት። ወንጀልን በፍጹም መታገስ የለበትም። ወንጀል ከሆነ የወንጀል ትንሽ የለውም።
• የኔት ወርክ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጀል የሚፈጸመው ተመሳሳይ ቡድን ነው።
• ምንጊዜም ቢሆን ለውጥ ካለ ጸረ ለውጥ አለ። ሀጫሉ ለውጡን ካመጡት፤ ለውጡ እንዲመጣ ካቀነቀኑት፣ከታገሉት ሰዎች የመጀመሪያው ረድፋ ላይ የሚሰለፍ ነው።
• ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖለቲካ ተቀባይነት እንዳያገኙ ብዙ ሴራዎች ተፈጽመዋል። ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶችን ለመገንዘብ ሶስቱን ሰኔዎችንና ሌሎች ክስተቶችን ወደ ኋላ ማየት ነው።
• በየአካባቢው ግጭት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ግድብ ተሸጠ፣ ሌላም ሌላም የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተነዛ ፤
• ይህን ሁሉ ከሞከረ በኋላ ከተላላኪዎቹ ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጦርነቱን አዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሳለን ብለው ወሰኑ።
• አዲስ አበባ ጀምረው አዲስ አበባ ለመጨረስ ትስስር ተፈጠረ።
• ኦሮሞና አማራን ማጋጨት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ መቀልበስም፤ አሁን ያለውን የለውጥ መንግስትም ከስልጣን ማስወገድ ይቻላል የሚል መደምደሚያ ላይ ስለተደረሰ ለሀጫሉ በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ተዘጋጀለት።
• ለሀጫሉ የሚዘጋጅለት ጥያቄ የኦሮሞንና የአማራን ግንኙነት የሚበጥስና የሚያጋጭ እንዲሆን ታስቦ ነው።
• ሀጫሉ የተገደለው የአማራና የኦሮሞ ግጭት ለማምጣት ነው። የሴራ ዕቅድ የለውጡን አመራሮች በቀላሉና በሰከንድ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብተን እናስወጣለን በሚል ስሌት ነው።
• ሀጫሉ ስለ አጼ ምኒልክ ተናገረ ፤ በምኒልክ ጉዳይ ደግሞ አማራ ይነሳል። ሀጫሉን አማራ ነው የገደለው የሚል አስተሳሰብ በኦሮሞ ይፈጠራል። ኦሮሞ በአማራ ላይ ይነሳል።
• አጼ ምኒልክ የአንድ ኢትዮጵያን የመሩ መሆኑ ቀርቶ የአማራ ንጉስ ተደርገዋል። ልክ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው ኢትዮጵያን ህዝብ የሚያገለግሉ እንጂ ለኦሮሞ ብቻ የቆሙ አይደሉም።
• ሀጫሉ በኦነግ ሸኔ ዛቻ እየመጣበት እንዳለና ለምን ያ ዛቻ እንደሚመጣበትም በግልጸ የተናገረው ነገር ግን ተቆርጦ ሳይተላለፍ ቀርቷል።
• ሀጫሉ የተመረጠው ምክንያት በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ታዋቂና የትግል ምልክት ተደርጎ የሚቆጠር ስለሆነ ነው።
• የሚገርመው ሀጫሉን እነሱ ገለውት መልሰው ያዝኑለታል። ስለዚህ አሁንም ለውጥ አለ፤ ጸረ ለውጥም አለ።
• እነዚህ ቡድኖች አዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሳለን የሚለው መርሀ ግብርና ዕቅድ ሲቀርጹ በተለያየ ቦታ መዋቅር አላቸው። በየቦታው የሚያስተባብሩ ሰዎች አሏቸው።
• ለማስተባበር ደግሞ የግድ የዚያ አካባቢ ነዋሪ ሊሆንም፤ ላይሆንም ይችላል። የሚያስፈልገው ገንዘብ ብቻ ነው።
• የሀጫሉን ሞት ተከትሎ ሰዎች ሞተዋል። ዜጎች 30ና 40 ዓመታት የለፉበት ንብረት ወድሟል። ሻሸመኔና መስል ከተሞች እንዳልነበሩ ሆነዋል። ግን እነሱ እንደፈለጉት ኦሮሞና አማራ ተነስቶ አልተዋጋም። ሁሉም ህዝብ ለምን እንደተደረገ ገብቶታል።
• ወቅቱ የህዳሴው ግድብ ሙሌት የተጀመረበት ነው። የግብጽ መንግስት እነዚህን ቡድኖች ፋይናንስ ያደርጋል።
• ሁሌም በወንጀል ውስጥ የሚኖር የአገርን ጥቅም አሳልፎ ይሻጣል። ምክንያቱም እነዚህ የወንጀለኛ ቡድኖች ምንጊዜም ወደ ህግ ፊት የሚያቀርባቸውን ሀይል በማጥፋት ስልጣን ይዘው እንደፈለጉት ለመሆን በአገር ጥቅም ከመደራደር ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም።
• ግብጾችን ወክለው የሚዋጉ ተላላኪዎች ስላሏቸው ለእነሱ ፋይናንስ ማድረግ ብቻ ይጠበቅባቸዋል።
• የህዳሴው ግድብ የስጋት ምንጫችን ሆኖ የሚቀጥለው ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ነው። ይህ ደግሞ በእኛ የመገደብ ፍጥነት ላይ ይወሰናል። ከዚያ በኋላ ነገሩ ይቀየራል።
• በትግራይ ክልል ምርጫ እናደርጋለን የሚለው ነገር ከጸጥታም ከህግም አኳያ በአግባቡ መታየት አለበት የሚል እምነት አለኝ።
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 30/2012 ዓ.ም ዕትም ጋር ከደደረጉት ቃለምልልስ የተወሰደ
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1 ሺህ 86 ሰዎች የኮኖና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ16 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

ባለፉት 24 ሰዓታት በኢትዮጵያ በተደረገ 14 ሺህ 688 የላቦራቶሪ ምርመራ 1 ሺህ 86 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም 26 ሺህ 204 ደርሷል።

በሌላ በኩል ትናንት 394 ሰዎች በማገገማቸው በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 428 ሆኗል።

ባለፉት 24 ሰዓታት የ16 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ይህም በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር 479 አድርሶታል።

በአሁኑ ጊዜ 14 ሺህ 295 ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሕክምና እየተከታተሉ ነው፤ 193 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕክምና ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስካዛሬ ድረስ 550 ሺህ 119 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1,038 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው
------------------------------
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 17ሺህ 323 የላቦራቶሪ ምርመራ 1038 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 27 ሺህ 242 ደርሷል።

በትናንትናው ዕለት 232 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 660 ሆኗል።

ካለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በኮሮናቫይረስ የተነሣ የሟቾች ቁጥር 492 ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት 195 ሰዎች በጽኑ ሕክምና ላይ ሲገኙ፣ 15 ሺህ 088 ደግሞ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስካዛሬ ድረስ 567 ሺህ 442 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።