Gazette Plus / ጋዜጣ ፕላስ/
24.8K subscribers
41.2K photos
343 videos
7 files
5.81K links
Ethiopian Press Agency, established in 1940 , is a public printing media enterprise operating in Ethiopia.
Download Telegram
የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወለጋ ከኅብረተሰቡ ጋር ያደረጉት ውይይት የተሳካ እንደነበር ተገለጸ
*****************
(ኢ ፕ ድ)
በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተካተቱበት ቡድን በምስራቅ እና በምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በቄለም ወለጋ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረገው ውይይት የተሳካ እንደነበር ተገለጸ።
የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ በዚህ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ አዱኛ በመግለጫቸው እንዳሉት፤ በውይይቱ ወቅት የሕብረተሰቡ የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ የጣሉ አደጋዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ያነሱት ኃላፊው፤ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡን ከጥቃት ለመታደግ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።
በዞኖቹ ከጸጥታ በተጨማሪ የመሰረተ ልማትና የሥራ አጥነት ችግር አንገብጋቢ መሆኑን በውይይቱ ወቅት መነሳቱን የተናገሩት አቶ ሀይሉ፤ መንግስት ጥያቄዎቹ ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት የተሳካ እንዲሆን ሕብረተሰቡ ሰላም አዋኪዎች ለመታገል ብርቱ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በዋቅሹም ፈቃዱ
የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በግማሽ በጀት ዓመት 42 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
***************
(ኢ ፕ ድ)
በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት 39 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 42 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር የገመገመ ነው።
በስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ የቢሮው ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወነው ስራ 39 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 42 ነጥብ 29 ቢሊዮን ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር የ10 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ብለዋል።
ቢሮው በበጀት አመቱ 70 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሞገስ ተስፋ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የትዊተር ገጽ ይከተሉ‼️
https://twitter.com/PressEthio
ኢትዮጵያ በዚህ አመት የ13 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አይ ኤም ኤፍ ገለጸ

👉የኢትዮጵያና የአንጎላ ኢኮኖሚ የመሪነቱን ደረጃ ከኬኒያ ይረከባልም ብሏል
********************
(ኢ ፕ ድ)

ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆች አመት (2023) የ13 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ( አይኤምኤፍ) ገለጸ።

ቢዝነስ ዴይሊ የተባለው ድረ ገጽ የኤይኤምኤፍን መረጃ መሰረት አድርጎ ባስነበበው መረጃ መሰረት፤ በዚህ አመት ከሰሀራ በታች ካሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ እና አንጎላ የኢኮኖሚ መሪነቱን ከኬንያን ይረከባሉ።

አይኤም ኤፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ መአት በ13 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የአንጎላ በ8 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ትንበያውን አስቀምጧል።

በአንጻሩ በኮቪድ 19፣ በድርቅ፣ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነትና በአገሪቱ በነበረው ምርጫ ችገሮች ምክንያት የኬኒያ የኢኮኖሚ እድገት በ2 ነጥበ 4 በመቶ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል ተቋሙ።

አይኤምኤፍ በዚሁ ትንበያው በዚህ አመት የኬንያ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 117 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር፣ የናይጄሪያ 574 ቢሊዮን ዶላር፣ የደቡብ አፍሪካ 422 ቢሊዮን ዶላር፣ የአንጎላ 135 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቀሰ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ደግሞ 126 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በተለይ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ የኢኮኖሚ እድገቱ ያንሰራራል የሚል ተስፋ እንዳለ የጠቀሰው አይኤምኤፍ፤ ከአፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከኬኒያ በተሻለ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን እየሳበች ትገኛለች ብሏል።

በመሀመድ ሁሴን
በአፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ ልዑክ ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ ቤቶችን ለማስረከብ ጅግጅጋ ገባ
****************
(ኢ ፕ ድ)
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የምክር ቤት እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ ቤቶችን ለማስረከብ ጅግጅጋ ከተማ ገብተዋል።

ለአፈጉባኤውና አመራሮቹ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ አቀባበል አድርገዋል።

አፈጉባኤው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመቀናጀት በጅግጅጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች እድሳትና ጥገና የተደረገላቸውን 31 መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች እንደሚያስተላልፉ ተመላክቷል።

ከሶማሌ ክልል መንግስት ጋር በመቀናጀት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ በጅግጅጋ ከተማ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ምቹ መኖሪያ እንዲያገኙ የተሰራ ስራ መሆኑም ተጠቅሷል።

በበጎ ፍቃድ ስራው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ተጠሪ ተቋማት በሆኑ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ፣የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መሆኑም ተመልክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በኦሮሚያ በ6 ወራት 37 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ
**************
(ኢ ፕ ድ)
በ2015 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት 37 ቢሊዮን 104 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደበበ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በግማሽ ዓመቱ በአጠቃላይ 38 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ አፈጻጸሙም 97 ነጥብ 26 በመቶ ሆኗል።

እንደ ወይዘሮ መስከረም ገለጻ፤ የስድስት ወራት ገቢው በመደበኛ መልኩ ከሚሰበሰብ ታክስ እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የተገኘ ነው። ከመደበኛ የታክስ ገቢ 31 ቢሊዮን 374 ሚሊዮን ብር በላይ የተገኘ ሲሆን፤ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ደግሞ 5 ቢሊዮን 730 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል።

የክልሉ አጠቃላይ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ12 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን የገለጹት ኃላፊዋ፤ በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ የበጀት ዓመቱን...
ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
https://www.press.et/?p=90863
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ
*****
(ኢ.ፕ.ድ)

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ እድገት፣ ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ አሳታፊ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ክልላችን ቀድሞ ከነበረበት የጦርነት ዳፋ ፈጥኖ ለመውጣት የሚያስችሉ የመልሶ ግንባታ፣ ወትሯዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በአንጻራዊ ውጤታማነት ለማከናወን ተችሏል፡፡

የክልሉን ነዋሪ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት ሁኔታ በማረጋገጥ ረገድ እና በልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች መስክ ከተከናወኑት ውጤታማ ተግባራት ባሻገር ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ በክልላችን ውስጥ በተከታታይነት የተከበሩትና እየተከበሩ ባሉ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን እንደ አብነት መውሰድ ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ከድህረ ጦርነት በኋላ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት በተረጋጋ ሁኔታ ላይ መገኘትን የማይሹ የቀውስ አምባሳደሮች የክልሉን ሕዝብና መንግሥት በግጭት አዙሪት ውስጥ መልሶ ለመዝፈቅ ከመቅበዝበዝ፤ በንጹሃን ዜጎችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘር አልቦዘኑም፡፡

በፀረ ሰላም ኃይሎች አማካይነት ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 9፡ 00 ሠዓት አካባቢ ጀምሮ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ጀውሃ ቀበሌ በሚገኘው የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ እና በፌደራል ፖሊስ አባላቶቻችን ላይ የተፈጸመው ጥቃት የጥፋት ኃይሎች በክልሉ ሕዝብ ላይ የደቀኑት የጥፋት መጠን ለከት አልባነት ያረጋግጣል፡፡

የፀረ ሰላም ኃይሎች በጸጥታ ኃይሎቻችን ላይ የከፈቱትን የአፈሙዝ ላንቃ ወደ ንጹሃን ዜጎች በማዞር በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ እያደረሱም ይገኛል።

በተለይም በኤፍራታ ግድም፣ አጣየ፣ ሰንበቴ፤ ጀውሃ እና በሸዋሮቢት ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ቀበሌዎች የፈጸሟቸውን ጥቃቶች የብሔር መልክ ያለው እንዲመስል በማድረግ በሁለቱ ዞኖች ነዋሪ ሕዝብ መካከል የብሔር ግጭት ለማስነሳት ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን እየፈጸሙ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ በዚህ የፀረ ሰላም ቡድን እና ተባባሪዎቹ ላይ ሕጋዊ፣ የተጠና፣ በማያዳግም መልኩ የህግ የበላይነትን በማስከበር የክልሉን ሕዝብ ሠላም፣ ደህንነትና አንድነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡

መንግስት ፀረ ሰላም ኃይሎች የከፈቱትን ጥቃት በአጭር ግዜ ውስጥ ለመቆጣጠርና ጥፋተኞችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌድራል ፖሊስና የአማራ ልዩ ኃይል ፓሊሶችን በስፍራው በማሰማራት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ያከናውናል፤ እያከናወነም ይገኛል፡፡

ስለሆነም ጥቃቱ በተከፈተባቸው አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝባችን በአካባቢው ከሚገኘው የመንግስት የፀጥታ ኃይሎቻችን የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ አዎንታዊ ሚናውን እንዲወጣ እንጠይቃለን።

በጥፋት ቡድኖች የተከፈተውን ጥቃት የብሔር መልክ በመስጠት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማድረግና መንግሥት ጥቃቱን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት የማደናቀፍ ተልዕኮ ያነገቡ የአሉባልታ ወሬዎችን የሚያሰራጩ አካላትን በመከላከል ረገድ ሁሉም ነዋሪ ለሰላም ሲባል የድርሻውን አስተዋጽዖ ሊያበረክት ይገባል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ጥቃቱ በተፈጸመባቸው በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ውስጥ በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ጥቃቱን ለማስቆም፤ አጥፊዎችንም ለህግ ለማቅረብ እና አካባቢውን ቀድሞ ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ የሚደረገውን ጥረትና ዝርዝር ሁነቶች በተመለከተ በተገቢው ወቅት መረጃ የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።

በመጨረሻም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሕዝብን ሰላም፤ ደህንነትና አንድነት ለማስጠበቅ ቀንና ሌሊት በሚደክሙ የፀጥታ ኃይሎቻችን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰዉ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎቻችን እና ጥቃጣቸውን በማስፋት በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ በደረሰው ክቡር የሆነ የሰው ህይወት መጥፋትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ምክንያት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለተሰውት የፀጥታ ኃይሎች አባላትና ንጹሃን ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጆች ልባዊ መጽናናትን ይመኛል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር
ለሀገራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 40 የዲያስፖራ አባላት እውቅና ሊሰጣቸው ነው
**********
(ኢ ፕ ድ)
ሀገር ሊያድግ የሚችለው እውቀትና ቴክኖሎጂን በማሸጋገር በሀገር ቤት ያሉ ተቋማትን አቅም ለመገንባት በሚያስችል መልኩ ዲያስፖራውን በመደበኛነት ማሳተፍ ሲቻል መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።

ለሀገራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 40 የዲያስፖራ አባላት እውቅና እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል።

የአገልግሎቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን ግርማ ለኢፕድ እንደገለፁት፤ ሀገርን ማሳደግ ከተፈለገ ዲያስፖራውን ወደ መደበኛ ተሳትፎ ማምጣት ያስፈልጋል።

እንደ አቶ ወንደሰን ገለጻ፤ ዲያስፖራው በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት ላይ በመሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ በማስተዋወቅ በኩል ሰፊ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ይህንን እንዲያሳካ መደበኛ በሆነ መልኩ ተሳትፎውን የሚገልጽበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ዲያስፖራው የማይዋዥቅና በሀገር ቤት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ተሳትፎን ሊያደርግ ይገባል ያሉት አቶ ወንደሰን፤ ይህ ደግሞ በእኛ ሀገር ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ..
ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
https://www.press.et/?p=90860
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የትዊተር ገጽ ይከተሉ‼️
https://twitter.com/PressEthio
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮፐንሀገን ከተማ በድጋሚ በረራ ሊጀምር ነው
***************
(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተማ በድጋሚ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

አየር መንገዱ በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ ከተማዋ የመንገደኞች በረራ እንደሚያደርግ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር በነበራቸው ውይይት‼️

👉 መምህራን ያነሷቸውን ጥያቄዎች በመለየት በሂደት ተገቢውን መልስ እንዲያገኙ ይደረጋል፣

👉 ምሁራን ለሀገራቸው ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግም ከሰፈር ፖለቲካ ወጥተው ሀገራዊ ዕይታቸውን ሊያሰፉ ይገባል፣

👉 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በራሳቸው የኢኮኖሚ አቅም እንዲተዳደሩ ማድረግ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብን ኢኮኖሚያዊ አቅም በዘለቄታዊነት ያጠናክራል፣

👉 ራስ ገዝ ይሁኑ ማለት ግን መንግስት ለዩኒቨርሲቲዎች በጀት አይመድብም ማለት አይደለም ፣

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ምሁራኑ የደመወዝ፣ የጥቅማጥቅምና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከሀገሪቷ የጸጥታ ሁኔታ፣ ለትምህርት ጥራት ከሚያግዙ ጉዳዮች፣ ስለአካል ጉዳተኞችና የሴቶች ተሳትፎ፣ ጉዳት ስለደረሰባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እንዲሁም ከሀገራዊ አንድነት ጋር የተቆራኙ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበዋል።
ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ
https://www.press.et/?p=90834
ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ
********************
(ኢ ፕ ድ)

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተጠናከረ መልኩ ወደ አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትንም የማስፋፋት እና የማጠናከር ተግባራት እየተከናወነ ነው። በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኀበር ኮሚቴ እስካሁን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭትና በድርቅ ምክንያት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልፀዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር በበኩላቸው ማኅበሩ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጭ መሆኑን የገለጸው የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የወልዲያ ከተማና አካባቢው የ24 ስዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ጀመረ
*****************
(ኢ ፕ ድ)

የወልዲያ ከተማና አካባቢው ከጥር 17 ቀን 2015 ጀምሮ የ24 ስዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ጀምሯል፡፡

ከደሴ ማከፋፈያ ጣቢያ በጊዜያዊነተ ኃይል ስታገኝ የቆየችው የወልዲያ ከተማ በአዲስ መልክ የተገነባው የወልዲያ ዶሮ ግብር ባለ230/33/15 የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተጠናቆ በከፊል አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ነው ተብሏል።

በአሁኑነ ወቅት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ሶስት ባለ15 ኪ.ቮ ወጪ መስመሮች አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው የወልዲያ ከተማና አካባቢው የ24 ሰዓት አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል፡፡

በዚህም በከተማው የሚገኙ ጎንደር በር፣ በቅሎ ማነቂያ፣ ፒያሳ፣ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳጎ፣ ገብርኤል አካባቢ፣ ሆስፒታል እና ሌሎች የገጠር አካባቢዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ቀሪ 15 ኪ.ቮ እና 33 ኪ.ቮ ወጪ መስመሮች አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ቀድሞ ከወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት ያገኙ የነበሩ የሰሜን ወሎና አፋር አካባቢዎች ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያገኘ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የትዊተር ገጽ ይከተሉ‼️
https://twitter.com/PressEthio