Ethiopia Check
26K subscribers
1.38K photos
180 videos
670 links
ኢትዮጵያ ቼክ በማህበራዊ ሚድያ እና በመደበኛ ሚድያዎች የሚቀርቡ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጣራት ስራዎቹን ለተከታታዮቹ ያቀርባል።
Download Telegram
⬆️
#MondayMessage #የሰኞመልዕክት

የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን፣ አካውንቶችን እንዲሁም ቻናሎችን እንዴት ቬሪፋይ ማስደረግ ይቻላል?

የማህበራዊ ሚዲያ ማረጋገጫ (verification) ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ሲደረግ ለታዋቂ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንዲሁም ከፍተኛ ተከታዮች ላሏቸው ሰዎች ብቻ ተጠብቆ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን በርከት ያሉ ኩባንያዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ አክቲቪስቶችን፣ የመንግስታት ሀላፊዎችን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ለማካተት ጥረት ተደርጓል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይህንን ማረጋገጫ (verification) ማግኘት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ከእነዚህም መሀል:

• ከተከታታዮች ጋር መተማመንን ለመገንባት
• ማህበራዊ ማስረጃን (social proof) ለማግኘት
• ተመሳስለው የሚከፈቱ አካውንቶችን፣ ገፆችን እና ቻናሎችን በቀላሉ ለመለየት፣ እንዲሁም
• የተከታታዮችን እድገት ለማግኘት ወዘተ ሊጠቀሱ ይችላሉ

በትዊተር ላይ ማረጋገጫን (verification) ማግኘት: በትዊተር ላይ ማረጋገጫን ለማግኘት በሚከተሉት ምድቦች ውስጥ መገኘት ያስፈልጋል:
• የመንግስት አካል
• የምርት ድርጅቶች፣ ኩባንያዎች እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች
• ጋዜጠኞች እና የዜና ድርጅቶች ባልደረባ
• የስፖርት ድርጅቶች እና ስፖርተኞች
• መዝናኛ ኢንደስትሪ ውስጥ ያሉ መሆን
• አክቲቪስቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆን

የትዊተርን ሰማያዊ ባጅ ለመቀበል ገጹ ትክክለኛ (authentic)፣ ታዋቂ (notable) እና ንቁ (active) መሆን አለበት።

ትክክለኛ(authentic): የትዊተርን ማረጋገጫ ለማግኘት ትዊተር ማንነትዎን ማረጋገጥ ይፈልጋል። ማንነትዎን ለማረጋገጥ ከሶስቱ ዘዴዎች ውስጥ አንዱን መምረጥ ይቻላል። እነሱም: የተረጋገጠ ድረ-ገፅ፣ መታወቂያ ወይም የኢሜል አድራሻን መጠቀም ይቻላል።

ታዋቂ (notable): አካውንቱ ከታወቀ ግለሰብ ወይም ድርጅት ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተያያዘ መሆን አለበት። ይህንንም ትስስር ትዊተር በራሱ ወይም አብረው በሚሰሩ ድርጅቶች ይረጋገጣል።

ንቁ (active): የትዊተር አካውንቱ የትዊተር ህጎችን ባከበረ መልኩ ንቁ መሆን አለበት። ይኼ ማለት የመገለጫ ስም እና የመገለጫ ምስል ሊኖረው ይገባል። ንቁ አጠቃቀም ማለት ባለፉት 6 ወራት ውስጥ አካውንቱን መጠቀም አለብዎት። ከዚህም በተጨማሪ አካውንቱ የተረጋገጠ የኢሜል አድራሻ ወይም የስልክ ቁጥር ሊኖረው ይገባል።

አንዴ የትዊተር ማረጋገጫ ከተሰጠ በኋላ የተጠቃሚ ስምዎን (username) ከቀየሩ፣ አካውንቱ እንቅስቃሴ አልባ ከሆነ፣ ወይም መጀመሪያ መረጋገጫው በተሰጠበት ቦታ ላይ ካልሆኑ የተሰጠው ማረጋገጫ ሊወርድ ይችላል። Note: ትዊተር ከቀናት በፊት የማረጋገጫ ጥያቄዎችን ለግዜው መቀበል እንዳቆመ አስታውቋል።

በፌስቡክ እንዴት ማረጋገጫ ይሰጣል?
• በመጀመርያ ወደ ፌስቡክ ሰማያዊ ማረጋገጫ ባጅ መጠየቂያ ገጽ (Blue Verification Badge Page) ይሂዱ። ሊንክ: https://www.facebook.com/business/learn/lessons/verify-facebook-instagram-account
• የማረጋገጫ ዓይነትዎን (ገጽ ወይም አካውንት) ይምረጡ
• ምድብ ይምረጡ፣ አገርዎን ይምረጡ፣ መታወቂያ ያስቀምጡ፣ የእርስዎ መለያ/አካውንት ለምን መረጋገጥ እንዳለበት ያብራሩ፣ ከዛም 'ላክ' የሚለውን ይጫኑ።

ለግለሰቦች የመንጃ ፈቃድ ወይም ሌላ በመንግስት የተሰጠ የመታወቂያ ካርድ ይበቃል። ለንግድ ገጽ ደግሞ የምስረታ የምስክር ወረቀትን፣ የኩባንያዎን ስልክ ወይም የፍጆታ ሂሳብ ወይም የግብር ሰነዶችን ማቅረብ ይችላሉ። ጥያቄዎን ከላኩ በኋላ የፌስቡክ ማረጋገጫ ቡድን መረጃዎን ይገመግምና እና ውሳኔ ይሰጣል።

ፌስቡክ ጥያቄውን ከተቀበለው በአካውንቱ ላይ ሰማያዊ ባጅ ይታያል። ሆኖም ጥያቄዎ ውድቅ ከተደረገ ከ30 ቀናት በኋላ እንደገና ማመልከት ይችላሉ። የፌስቡክ ማረጋገጫ የብቁነት መስፈርቶች ከኢንስታግራም (Instagram) ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

እንዲሁ በዩትዩብ (YouTube) ላይ ማረጋገጫ ማግኘት ይቻላል። የዩትዩብ ቻናሉ ለማረጋገጫ ባጅ ብቁ ከሆነ ግራጫ አመልካች ምልክቱን ለማግኘት በማረጋገጫ ባጅ ገጹ ላይ ማመልከት ይችላሉ።
ዩትዩብ መስፈርቶቹን የሚያሟላ መሆኑን ለማየት ቻናሉን ይገመግማል። የማረጋገጫ ባጅ ለመቀበል የዩትዩብ ቻናሉ ቢያንስ 100,000 ተመዝጋቢዎች ሊኖረው እና መስፈርቶችን ማሟላት አለበት።

ማስታወሻ: ሁሉም የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች ማረጋገጫ ለመስጠት ገንዘብ አያስከፍሉም፣ ስለዚህ "ማረጋገጫ እንዲሰጥዎት እናደርጋለን" ብለው ገንዘብ ከሚጠይቁ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ራስዎን ይጠብቁ።

@EthiopiaCheck
⬆️
#MondayMessage #የሰኞመልዕክት

በአዲስ ዓመት እንደ አዲስ እንጀምር!

ውሸት ስለራሳችንም ይሁን ስላለንበት ሁኔታ የተዛባ እና የተሳሳተ ግንዛቤን ይፈጥራል። በተፈጥሮው ሚዛኑን የሳተና የተንሻፈፈ እይታን መፍጠር ዋነኛ፣ ምናልባትም ብቸኛው ግቡ ነው። በዚህ በተሳሳተ ወይም በተዛባ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ የሚወሰድ ማንኛውም አቋም ወይም ውሳኔ ደግሞ መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የተጣላ፣ ውጤቱም ዘላቂነት የሌለው ይሆናል።

ባለፈው ዓመት ከተሰሩ ጥናቶች ውስጥ የአውሮፓ ህብረት የሰላም ኢንስቲትዩት በዓመቱ አጋማሽ አካባቢ “Fake News Misinformation and Hate Speech in Ethiopia: A Vulnerability Assessment” በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው ጽሑፍ እንደታዘበው ጥናቱ በተደረገበት የ6 ወር ጊዜ ውስጥ የተወሰዱ ናሙናዎች እንደሚያሳዩት የሚበዙት ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮች በጣም ውስን በሆኑ ርዕሶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።

እነዚህ ርዕሶች ብሔርን፣ ሀይማኖትን፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስርዓትን፣ የህዳሴ ግድቡን፣ ኮቪድ-19ን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የተመለከቱ እንደነበሩ ይህ ጥናት ያመለክታል። እነዚህ ርዕሶች እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከቱ፣ ህይወቱን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚነኩ ከሁሉም በላይ ግን ስሜትን የመኮርኮር አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ መሆናቸው አሳሳቢ ያደርገዋል።

ለዚህ ነው ሀሰተኛ መረጃን የመዋጋት ስራ እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል ጊዜ እና ቦታ ሳይወስነው ጉዳዬ ብሎ ሊይዘው ይገባል የምንለው። ባለፈው ሳምንት በሸኘነው አሮጌው አመትም ሊፈቱ የሚችሉ (እና የሚገቡ) ልዩነቶች በሀሰተኛ እና በአሳሳች መረጃዎች ምክንያት ያለልክ እንዲለጠጡ እና እንዲገዝፉ መሆናቸውን አስተውለናል።

ነገር ግን አሁን አዲስ ምዕራፍ ጀምረናል። የጊዜ አዲስ ምዕራፍ። ካለፈው አመት ተጎትተው የመጡት ሀገራዊ ጉዳዮች በቦታቸው እንዳሉ ቢሆኑም፣ ይህ አዲስ ጊዜ አዲስ ውጤት እንዲያመጣ ከቀደመው ጊዜ መማር ያስፈልጋል። ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃን ብቻ በመዋጋት ምትክ የሌለው ውጤት እና ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ኢትዮጵያ ቼክ በፅኑ ያምናል።

አሁን የጀመርነው አዲስ ዓመትም ከኋላ ትተነው ከመጣነው የተነጠለ፣ የተሻለ ለማድረግ ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃ ላይ እንዝመት። ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን ባለመፍጠር፣ ባለማጋራት እንዲሁም በማጋለጥ እንረባረብ።

መልካም ሰኞ! መልካም ዓመት!

@EthiopiaCheck
⬆️
#የሰኞመልዕክት ሁሉም ሰው ስለ ሚዲያ አጠቃቀም ያለው ንቃት ተመሳሳይ አይደለም። አንዳንዶቻችን ከፍ ያለ ንቃት ይኖረንና ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በቀላሉ መለየት እንችላለን። ሌሎቻችን ደግሞ ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች በቀላሉ እንጋለጣለን።

ብዙ ጊዜ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን የሚዲያ ንቃታቸው ዝቅ ያለ ይሆንና ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች ተጋልጠው እንመለከታለን። እውነታውን ለማስረዳት በምንሞክርበት ጊዜም የተግባቦት ችግር ይገጥምና መረጃውን ለማረም የምናደርገው ጥረት ያልተሳካ ሊሆን ይችላል።

ሆኖም የሚከተሉትን ቀለል ያሉ የተግባቦት ዘዴዎችን መጠቀም ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች የተጋለጡ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን ለማረም ብሎም ለማስተማር ሊረዱን ይቻላሉ:

1. በትዕግስት ማዳማጥ: የመረጃውን ሀሠተኛነት በማጋለጥ ለማሳመን ወይም ለማጣጣል አልያም ለማሸማቀቅ ከመሞከር ይልቅ መረጃውን በተመለከተ ያላቸውን መረዳት እንዲገልጹ በትዕግስት ማዳማጥ ማስቀደም ይመረጣል።

2. ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ: መረጃውን በተመለከተ ያላቸውን መረዳት ከሰማን በኋላ ወደ ዝርዝር የሚያመሩ ጥያቄዎችን ማስከተል ወደ መግባባት ለመድረስ ተመራጭ ዘዴ ይሆናል። በዚህም የመረጃ ምንጮቻቸው እነማን እንደሆኑ፤ ለምን እንዳመኗቸው ወዘተ ለማወቅ እንችላለን።

3. በትህትና ማስረዳት: ስለመረጃው ያላቸውን መረዳት በሙሉ በትዕግስት ካዳመጥን በኃላ መረጃው ሀሠተኛ መሆኑን ትህትና በተሞላበት መንገድ ማስረዳት እንችላለን። ለዚህም ሀሠተኛ መረጃውን የሚያጋልጡ ሀቆችን በዝርዝር ማቅረብ ይኖርብናል። የመረጃ ምንጮቻችንን መጥቀስና ለምን እንዳመናቸው ማስረዳትም ይጠበቅብናል። ይህን ስናደርግ ሀሠተኛ መረጃው ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ሰፋ ያለውን አውድ ማብራራት ተመራጭ ይሆናል።

4. በይደር ማቆየት: ሰዎች አንድ ጊዜ ያመኑትን ሀሳብ በቶሎ ለመቀየር ሊቸገሩ ስለሚችሉ የማስረዳት ሙከራችን ወደ ክርክር፣ ጭቅጭቅና አለመግባባት ሊያመራ ይችላል። ይህ የሚሆን ከሆነ ጉዳዩን በይደር ማቆየት ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት ያግዘናል።

5. ማስተማር: ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ስለ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ማስተማር ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ይረዳናል። ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን የመለየት ዘዴ፣ የመረጃ ምንጮችን የመገምገሚያ ነጥቦች፣ መረጃን ለማጣራት የሚረዱ መገልገያዎችን ወዘተ በዚህ ሊካተቱ ይችላሉ። የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃውች አሉታዊ ውጤቶችንም መግልጽ ጠቃሚ ይሆናል። ይህን ስናደርግም ቀለል ያለ ቋንቋ መጠቀም ይመረጣል።

የሚዲያ አጠቃቀም ንቃታችንን ከፍ በማድረግ እራሳችን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ ወዳጆቻችንና ማህበረሰባችንን ከሀሠተኛና ከተዛቡ መረጃዎች እንጠብቅ።

የኢትዮጵያ ቼክን ስራዎች በትዊተር: https://twitter.com/EthiopiaCheck?t=FsMKsm9TyYqMVn6gG9PXTA&s=09
⬆️
#EthiopiaCheck የአርብ ሳምንታዊ ዳሰሳ

1. ትዊተር የተጠቃሚዎቹ መለያ ስም (twitter handle) በሚጻፍበት መልክአ-ፊደል (font) ላይ ለውጥ ማድረጉን በቴክኖሎጅ ጉዳዮች ላይ የሚዘገበው ዘቨርጅ ድረ-ገጽ አስነብቧል። ለውጡ ተመሳስለው የሚከፈቱ አካውንቶችን በቀላሉ ለመለየት ያስችላል ተብሏል። በለውጡም ተጠቃሚዎች እንደ 'ዜሮ' (0)፣ 'ስሞል ኦ' (o)፣ 'ካፒታል ኦ' (O)፣ 'ስሞል ኤል' (l)፣ 'ካፒታል አይ' (I) ያሉ ፊደሎችን በቀላሉ መለየት ይችላሉ። የመልክአ-ፊደል ቅያሬው ለጊዜው ትዊተርን በድረ-ገጽ ለሚጠቀሙ ደንበኞች ብቻ ይታያል።

2. የቴሌግራም ቦት በመጠቀም የሚደረግ የማጭበርበር ድርጊት በፈረንጆች 2022 ዓ.ም የ800% ጭማሪ ማሳየቱን ኮፌንስ (Cofense) የተባለ የሳይበር ደህንነት ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናት አስነብቧል አሳይቷል። የማጭበርበር ድርጊቱ አይነትና ዘዴም እየረቀቀ መምጣቱንም ጥናቱ አስነብቧል።

3. ሜታ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፌስቡክና የኢንስታግራም አካውንቶች ላይ ጥሎት የነበረውን እግድ ማንሳቱን በትናንትናው ዕለት አስታውቋል። ሜታ እግዱን ያነሳው አሁናዊ ሁኔታዎችን ከገመገመ በኃላ መሆኑን የገለጸ ሲሆን የአሜሪካ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብትን ለማክበርም ነው ብሏል። አካውንቶቹም በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት እንደሚከፈቱ ሜታ በመግለጫው አስነብቧል። ሜታ በፕሬዝደንቱ አካውንቶች ላይ ዕግድ የጣላው መርሆቼንና ፖሊሲዎቼን ተጋፍተዋል በማለት ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበር ይታወሳል።

✅️ በዚህ ሳምንት ያቀረብናቸው መረጃዎች እና የቴሌግራም ሊንኮቻቸው:
- በሰኞ መልዕክታችን ከቤተሰቦቻችንና ከወዳጆቻችን ጋር ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በተመለከተ እንዴት መወያየት እንዳለብን ግንዛቤ የሚያሰጥ ጽሁፍ አስነብበናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1791

- እንዲሁም ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ተናገረቸው ተብሎ የተሰራጨ ሀሰተኛ መረጃን በአፋን ኦሮሞ አጋልጠናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1799

- የትምህርት ሚንስቴርን ስምና አርማ በመጠቀም ስለተከፈቱ ሀሠተኛ የቴሌግራም ቻናሎች መረጃ አድርሰናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1800

- በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ቼክ ስም ስለተከፈተ ሀሠተኛ የቴሌግራም ቻናል ጥቆማ ሰጥተናል: https://t.me/ethiopiacheck/1802

- በተጨማሪም የተለያዩ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃትን ከፍ የሚያደርጉ በርከት ያሉ በምስልና በቪዲዮ የተደገፉ መልዕክቶችን አጋርተናል።

@EthiopiaCheck
⬆️
#የሰኞመልዕክት ካሳለፍነው ሐሙስ ምሽት ጀምሮ በኢትዮጵያ በተወሰኑ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጭ መተግበሪያዎች ላይ ዕቀባ መጣሉ ይታወቃል። ይህንንም የኢንተርኔት ፍሰት መስተጓጎልን የሚከታተለው ዓለም አቀፍ ተቋም ኔትብሎክስ (NetBlocks) ያረጋገጠ ሲሆን ዕቀባውም ፌስቡክን፣ ቴሌግራምን፣ ቲክቶክን እንዲሁም ፌስቡክ ሜሴንጀርን ያካተተ መሆኑን ገልጿል።

እንዲህ ያለውን የኢንተርኔትንና የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎችን በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ የማቋረጥ ድርጊት የተለያዩ ሀገሮች መንግስታት አልፎ አልፎ ሲተገብሩት የሚታይ ቢሆንም በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰትና በተለይም አለመረጋጋትና ውጥረት በሚኖርባቸው ወቅቶች የሚጠበቅ (predictable) እየሆነ መጥቷል።

ሰፍርሻርክ (Surfshark) የተባለው የሳይበር ጉዳዮችን ተከታታይ ተቋም መረጃ እንደሚያሳየውም ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ቢያንስ አስራ አንድ ጊዜ የኢንተርኔትንና የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎችን በከፊልም ሆነ ሙሉለሙሉ የማቋረጥ ድርጊት ተፈጽሟል።

ይህም የዜጎችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘትና ከሳንሱር የመጠበቅ መብትን የሚጋፋ ሲሆን በኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 29 ላይ ከሰፈረው "የአመለካከት እና ሀሳብን በነጻ የመያዝ የመግለጽ መብት" ጋር የሚጣረስ ነው።

ዜጎች እውነተኛ፣ ታማኝና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ የሚያገኙበት በር ሲዘጋ የመረጃ ኦናነት (Information vacuum) መከሰቱም የሚጠበቅ ሲሆን ይህ ኦናነትም በሀሰተኛና በተዛቡ መረጃዎች፣ በሴራ ትንተና እንዲሁም በአሉባልታ የመሞላት ዕድሉም ከፍ ያለ ይሆናል። ይህም ውጅንብር በመፍጠር አለመረጋጋትንና ውጥረትን ያባብሳል።

የዜጎችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘት እንዲሁም ከሳንሱር የመጠበቅ መብቶችን ከሚጋፉ የኢንተርኔትንና የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎችን የማቋረጥ ድርጊቶች በመታቀብ የሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን፣ የሴራ ትንተናዎችን እንዲሁም አሉባልታዎችን እንግታ መልዕክታችን ነው።

@EthiopiaCheck
⬆️
#EthiopiaCheck የአርብ ሳምንታዊ ዳሰሳ

1. አንድ የእስራኤል ኩባንያ በሀሰተኛ መረጃ ማቀናጀት እና በምርጫዎችን ማዛባት አገልግሎቶች በክፍያ በማቅረብ አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ መገኘቱን ፎርቢድንስቶሪስ (forbiddenstories) በሚል መጠሪያ የሚንቀሳቀስ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ጥምረት በሳምንቱ መጀመሪያ በአስነበበው የምርመራ ውጤት አጋልጧል። "ቲም ጆርጌ" (Team Jorge) የሚል ስያሜ የተሰጠውና በሕቡዕ ይንቀሳቀሳል የተባለው ይህ የሳይበር ኩባንያ ሀሰተኛ መረጃን የሚያቀናጁ ሶፍትዌሮችን እና አድቫንስድ ኢምፓክት ሚዲያ ሶሉዊሽንስ (Advanced Impact Media Solutions) የተባለ ሀሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን የሚያመርት ሶፍትዌር ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብ ተነግሯል። በተጨማሪም አገር አቀፍ ምርጫዎችን የማዛባት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን እስካሁን በ30 ምርጫዎች ላይ መሳተፉም የምርመራ ውጤቱ አሳይቷል። ከኩባንያው ደንበኞች መካከልም የደህንነት ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኙበታል ተብሏል።ከጋርዲያን፣ ከሬዲዮ ፍራንስ፣ ከለሞንድ እና ከሌሎች እውቅ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡት ጋዜጠኞች ምርመራውን የሰሩት የኩባንያው ደንበኛ መስለው ከቀረቡና ሀላፊዎችን ካነጋገሩ በኃላ ነበር።

2. በመጭው ሳምንት በናይጀሪያ ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተገናኘ ሀሠተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ፖለቲከኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሀገሪቱ የደህንነት አገልግሎት Nigeria State Service) በትናንትናው ዕለት አስጠንቅቋል። አገልግሎቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው የናይጀሪያ ገዥ ፓርቲ ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ (All Progressive Congress) የምርጫ ዘመቻ ዳሬክተር የናይጀሪያን ጦርና አንድ የግል ተወዳዳሪን መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አሲረዋል በማለት መወንጀሉን ተከትሎ ነው። በናይጀሪያ የሚደረገው ምርጫ በሀሰተኛ መረጅና በጥላቻ መልዕክቶች እንዳይበረዝ በርከት ያሉ የመረጃ አጣሪ ተቋማትና የሲቪክ ድርጅቶች አበክረው እየሰሩ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተሰምቷል።

3. በፌስቡክና በኢንስታግራም ልጥፎች (posts) መነሳት ወይም አለመነሳትን የተመለከቱ ጉዳዩችን ላይ ውሳኔና ምክረሃሳቦችን የሚያቀርበው የሜታ የበላይ ተመልካች ቦርድ (Oversight Board) አሰራሩን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ለማስፋት ማሻሻያዎችን ማድረጉን በያዝነው ሳምንት አስታውቋል። በዚህም አፋጣኝ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ልጥፎች 48 ሰዐታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለመመልከት መወሰኑን አስታውቋል። ይህም የተቀላጠፈ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም በርከት ያሉ ጉዳዮችን ለመመልከት እንደሚያስችለው ገልጿል። የሜታ የበላይ ተመልካች ቦርድ መነሳት ሲኖርባቸው ያልተነሱ የጥላቻና ሌሎች አሉታዊ ይዘት ያላቸውን ልጥፎች እንዲሁም መነሳት ሳይኖርባቸው በፕላትፎርሙ አስተናባሪዎች (moderators) እንዲነሱ የተደረጉ ልጥፎችን ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ አካል መሆኑ ይታወቃል።

✅️ በዚህ ሳምንት ያቀረብናቸው መረጃዎች እና የቴሌግራም ሊንኮቻቸው:
- በሰኞ መልዕክታችን በኢንተርኔትና በዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚደረግ እቀባ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽኖ የተመለከተ ጽሁፍ አስነብበናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1848

- እንዲሁም በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶር አለሙ ስሜና በድምጻዊ አቡሽ ዘለቀ ስም ተመሳስለው የተከፈቱ የትዊተር አካውንቶችን በድጋሜ አጋልጠናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1850
https://t.me/ethiopiacheck/1853

- ቻትጂፒቲ (ChatGPT ) እያመጣቸው የሚገኙ ጥቅሞች እና ስጋቶችን የተመለከተ ጽሁፍም በአማርኛና በትግረኛ አጋርተናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1855
https://t.me/ethiopiacheck/1856

- በተጨማሪም የተለያዩ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃትን ከፍ የሚያደርጉ በቪዲዮ የተደገፉ መልዕክቶችን አጋርተናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1849
https://t.me/ethiopiacheck/1851
https://t.me/ethiopiacheck/1854

@EthiopiaCheck
⬆️
#የሰኞመልዕክት በማህበራዊ ሚዲያ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም የማታለልና የማጭበርበር ድርጊቶች ከሚሰራጩባቸውና ከሚፈጸምባቸው ዘዴዎች መካከል ተመሳስለው የሚከፈቱ ሀሠተኛ አካውንቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ይህን ችግር ለመቅረፍ የአካውንት ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት መስጠትን እንደቀዳሚ መፍትሄነት ሲጠቀሙበት መቆየታቸው ይታወቃል። በዚህ ረገድ ትዊተር ይህን አገልግሎት በቀዳሚነት በመጀመር የሚጠቀስ ነው።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም በአብዛኛው ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ትላልቅ ተቋማት ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል።

ሆኖም ባለጸጋው ኢሎን መስክ ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ ይህ አገልግሎት በክፍያ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን የመክፈል አቅም ያለው ማንኛውም የትዊተር ተጠቃሚ የአካውንት ማረጋገጫ ማግኘት የሚችልበት አሰራር ተዘርግቷል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነጻ የአካውንት ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት የተሰጣቸው ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ለማስቀጠል ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 1 ቀን 2023 ዓ.ም ቀደም ብለው ወደ ክፍያ ስርዐቱ መግባት እንዳለባቸው ኩባንያው ከቀናት በፊት አስታውቋል።

አዲሱ የትዊተር አካውንት ማረጋገጫ ስርዐት አካውንቶችን በሶስት የሚከፍል ሲሆን ለግለሰቦች ሰማያዊ (Blue)፣ ለተቋማት ወርቃማ (Golden) እና ለመንግስትና ለበይነ መንግስታት (multilateral organisations) ባለስልጣናትና ተቋማት ግራጫ (Grey) ቀለም ያለው ምልክት ያቀርባል።

ሰማያዊ የአካውንት ማረጋገጫ ምልክት የሚፈልጉ ግለሰቦች በየወሩ 8 የአሜሪካን ዶላር አካባቢ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ወርቃማ የአካውንት ማረጋገጫ ምልክት ለጊዜው በሙከራ ላይ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱን ለማግኘት በወር 1000 ዶላር መክፈል እንደሚያስፈልግ ትዊተር አስታውቋል። ግራጫ ምልክት የሚፈልጉ የመንግስትና የበይነ መንግስታት ባለስልጣናትና ተቋማት ትዊተር ያዘጋጀውን ቅጽ መሙላት ይጠበቅባቸዋል።

ምንም እንኳን አዲሱ የትዊተት አሰራር የመክፈል አቅምንና በውጭ ምንዛሬ ለመክፈል መቻልን የሚጠይቅ ቢሆንም የአካውንት ማረጋገጫ ምልክቶች ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን እንዲሁም የማታለልና የማጭበርበር ድርጊቶች ከመከላከል አንጻር ከሚኖራቸው አይተኬ ሚና አኳያ አቅም ያላቸው የትዊተር ተጠቃሚዎች ወደ ስርዐቱ ቢገቡ መልካም ነው እንላለን።

@EthiopiaCheck
#የሰኞመልዕክት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ከብሔር፣ ከሀይማኖት እንዲሁም ከሌሎች ሌሎች ማንነቶች አንጻር የሚሰነዘሩ የጥላቻ መልዕክቶች ከሚተላለፉባቸው ዘዴዎች መካከል ቀልዶች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ቀልዶች በጽሁፍ፣ በንግግር፣ በምስል፣ በቪድዮ ቅርጽ ሊቀርቡ ይችላሉ።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ያዘጋጀውን የሰኞ መልዕክት ያንብቡ: https://ethiopiacheck.org/home/tips-on-how-to-counter-hate-speech-on-tiktok-%e1%89%b2%e1%8a%ad%e1%89%b6%e1%8a%ad/
#የሰኞመልዕክት ከቅርብ አመታት ወዲህ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በሰፊው አነጋጋሪ እንዲሁም አሳሳቢ ሆኗል። ጊዜው የጠበቀ፣ የተሟላና ትክክለኛ መረጃ ለዜጎች ማቅረብ ደግሞ የጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት ተቀዳሚ ስራ ነው።

ይህን የየዕለት ተግባራቸውን ለመፈጸም ደግሞ በቅድሚያ ጊዜው የጠበቀ፣ የተሟላና ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም መረጃ ማግኘት መሰናክሉ ብዙ ነው። የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ሃላፊዎች በአብዛኛው ለጋዜጠኛና ለሚዲያ ተቋማት በራቸው ዝግ ነው።

ሙሉ የሰኞ መልዕክታችንን ለማንበብ: https://ethiopiacheck.org/home/providing-information-by-government-institutions-responsibility-can-prevent-the-spread-of-false-information-%e1%88%80%e1%88%a0%e1%89%b0%e1%8a%9b-%e1%88%98%e1%88%a8%e1%8c%83/