Ethio Fm 107.8
19.5K subscribers
6.22K photos
16 videos
4 files
2.27K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
በጋምቤላ በደረሰ ግጭት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ፡፡

በጋምቤላ ከተማ ትናንት ማምሻውን በተፈጠረ ግጭት የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አምስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት ለክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት እንደገለፁት በትላንትናው ዕለት ከጋምቤላ ከተማ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ አምስት ግለሰቦች በከፈቱት ተኩስ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ሁለት ሰው ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡

ጉዳቱን ተከትሎ በከተማው በተከሰተው ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉንና ሶስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ቢሮው አመላክቷል፡፡

በግጭቱ በአጠቃላይ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አምስት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ያመለከተው ፀጥታ ቢሮው ጥፋተኞቹን ወደ ህግ ለማቅረብ የፀጥታ አካላት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከግጭቱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ አስር የሚደርሱ ግለሰቦች ቀደም ብሎ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ተገቢውን ማጣራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ቢሮው አስታውቋል፡፡

ግጭቱ በተፈጠረበት በጋምቤላ ከተማ ያለው ሰላም ወደ ነበረበት እየተመለሰ መሆኑን የተገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥም በቢሮው ሃላፊ ተጠይቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም
የወንጀል መናኸሪያ እየሆኑ ነው የሚል ቅሬታ የሚነሳባቸው ጅምር ህንፃዎች ላይ ልዩ ክትትል እያደረኩ ነው ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ

በከተማዋ በጅምር ያሉ ያላለቁ እና ግንባታቸው አልቆም ሰው ያልገባባቸው ህንጻዎች የወንጀል መናኸሪያ እየሆኑ ነው የሚል ቅሬታ እየተነሳ ይገኛል።

በእነዚህ ህንጻዎች ተሰባስበው ያለ ስራ የሚቀመጡ ወጣቶች እንዳሉ ነዋሪው ጥቆማ እየሰጠን ነው ፤ ጥበቃም ይደረግልን ብለው ጥያቄ እያቀረቡ ነው ሲሉ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አረጋግጠዋል።

በጥቆማው መሰረትም ፖሊስ በተለይ ሰው ያልገባባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ጅምር ህንጻዎች ላይ የተለየ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ነግረውናል።

ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ ጎን ለጎን አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ሲያይ በአቅራቢያው ላለ የጸጥታ ሀይል እንዲያሳውቅም መልዕክት ተላልፏል።

መቅደላዊት ደረጄ
ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም
የአሜሪካ ተራድኦ ደርጅት (USAID) መጋዘኖችን በአሸባሪው ህወሓት መዘረፋቸው ተገለጸ

አሸባሪው ህወሓት የአሜሪካ ተራድኦ ደርጅት መጋዘኖችን እንደዘረፈ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ሚሽን ዳይሬክተር ሾን ጆንስ ተናገሩ፡፡

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የኢትዮጵያ ሚሽን ዳይሬክተር ሾን ጆንስ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ህወሓት ሁኔታውን ያለአግባብ እየተጠቀመበት እንደሆነ እናምናለን ብለዋል፡፡

ከተረጂዎች ላይ እርዳታን በሃይል እየነጠቀ እንደሆነ ይሰማናል ያሉት ዳይሬከተሩ እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ግን የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያሉትን የእርዳታ መጋዘኖቻችንን ዘርፈዋል፤ ይህ የምናውቀው ሀቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አሁን በግልጽ የምናውቀው ነገር የህወሓት ወታደሮች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል፣ መኪኖችን ሰርቀዋል በየመንደሮቹ ብዙ ውድመትን አድርሰዋልያሉት ዳይሬክተሩ ይህ ለተጎጂዎቹም ሆነ ለእኛ ለረጂዎቹ እጅግ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የኢትዮጵያ ሚሽን ዳይሬክተር ሾን ጆንስ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንቀሳቀሰው ሀገሪቱ አሁን ችግር ላይ ስላለች አይደለም ብለዋል፡፡

ይልቁንም ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አጋሮቻችን መካከል አንዷ ነች ያሉት ዳይሬክተሩ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለን አጋርነት በእጅጉ እንጨነቃለነ ነው ያሉት፡፡

አንዳንድ ጊዜ ህብረተሰቡ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩትን ያልተረጋጋጡ ወሬዎች በመያዝ የኢትዮ አሜሪካ ግንኙነት እንደሻከረ ያስባሉ ያሉት ዳይሬክተሩ ነገር ግን እንደአሁኑ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብረን የሰራንበት ጊዜ የለም ሲሉም ለኢብኮ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም
ቻይና ታዳጊዎች በጌሞች ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት ገደበች

ቻይና ታዳጊዎቿ በሳምንት ውስጥ በበይነ መረብ ጌሞች ላይ ማሳለፍ የሚችሉትን ጊዜ በሦስት ሰዓት ገደበች፡፡

ከአሁን በኋላ የሀገሪቱ ታዳጊዎች ጌሞችን መጫወት የሚችሉት አርብ እና የእረፍት ቀናት እንዲሁም በህዝባዊ በዓላት ወቅት ከምሽቱ 2 እስከ 3 ሰዓት ብቻ ይሆናል፡፡

ይህም ቀድሞ ወጥቶ ሲሰራበት ከቆየው ህፃናቱ በእያንዳንዱ ቀናት ለአንድ ሰዓት ተኩል እንዲሁም በህዝባዊ በዓላት ወቅት እስከ ሦስት ሰዓት ጌም በመጫወት እንዲያሳልፉ ይፈቅድ ከነበረው ሕግም ጠበቅ ያለ ነው፡፡

አዲሱ ሕግ በቻይና ያሉና በዓለም ዙርያም እውቅናን ያተረፉ አንዳንድ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን መነቅነቅ ጀምሯል፡፡

ለአብነት ውሳኔውን ተከትሎ ዝነኛው የጌም ኩባንያ ቴንሴንት የአክሲዎን ዋጋው በ0.6 በመቶ ሲወርድ የገበያ ዋጋውም ቀድሞ ጣርያ በነካበት ወቅት ከነበረው የ573 ቢሊዮን ዶላር አሁን ላይ ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡

ኔትኢዝ የተሰኘው ሌላኛው ኩባንያም እንዲሁ የአክሲዮን ዋጋው በ9 በመቶ ወርዷል፡፡

ሕጉ ቻይና ከጌም አንስቶ እስከ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቿ ተፅዕኖዋቸው ከሚገባው በላይ እንዳይሆን ለመቆጣጠር በማሰብ እየወሰደች ያለችው የቁጥጥር እርምጃ አካል ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ እድገት ሲያስመዘግቡ የቆዩትን የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና በበይነ መረብ ትምህርት ሰጪ ኩባንያዎች ከፍትሀዊ ተወዳዳሪነት ጋር በተያያዘ አደብ ያስገዙልኛል ያለቻቸውን ደንቦች አውጥታ ነበር፡፡

በዚህም በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰጥ የተጨማሪ ሰዓት ወይም ቱቶሪያል ትምህርን በቅርቡ በማገድ በዘርፉ የተሰማሩትን ኩባንያዎችንም መና አስቀቀርታቸዋለች፡፡

ከሳምንታት በፊት ቴንሴንት እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ጌሙን መጫወት እንዳይችሉና እንዲጫወቱ የሚፈቀደላቸውም በየቀኑ ከ1 ሰዓት በላይ በህዝባዊ በዓል ቀናት ደግሞ ከ2 ሰዓታት በላይ እንዳይጫወቱ መከልከሉን ቴክስፕሎር ዘግቧል፡፡

በዳዊት አስታጥቄ
ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም
ቅርሶች ከመፍረሳቸው በፊት እንዳንደርስ ያደረገን የመንግስት መስሪያ ቤቶች ምን ሊሰሩ እንደሆነ ቀድመን ባለማወቃችን ነው ሲል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ

የመንግስት መስሪያ ቤቶች ምን ሊሰሩ እንደሆነ ቀድመን አለማወቃችን ለቅርሶች እንዳንደርስ አድርጎናል ብሏል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በቅርሶች መፍረስ ብዙ ቅሬታዎች ተነስተዋል።

ከሰሞኑም የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽኑ የራስ ሀይሉ ተክለሀይማኖት መኖሪያ ቤት ፈርሷል በሚል የአዲስ አበባ ባህል ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው ይታወቃል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በበጀት አመቱ መጀመሪያ ላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ማን ምን ሊሰራ እንደሆነ ባለማወቃችን ለቅርሶች ልንደርስ አልቻልንም፣ የምናውቀው ማፍረስ ሲጀመር ነው ሲሉ የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

በተለያዩ የምክክር መድረኮች አብረውን ከሚሰሩ የመንግስት ቢሮዎች ጋር ለመገናኘት እንሞክራለን ያሉት ዳይሬክተሯ በእቅድ ዝርዝራቸው ላይ ቢያሳውቁን በጋራ ለመስራት እንችላለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ ቅርሶች የያዙት ቦታ ያጓጓል ነገር ግን የከተማ ልማት ቅርሶችንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሰራ ይገባል ሲሉም አጽኖት ሰጥተዋል።

በከተማዋ ያሉ ቅርሶች በእድሜ ብዛትና በግዴለሽነት ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተነግሯል።

የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው በአሁን ሰአት ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ የቅርስ አረዳድና አጠባበቅ የሚበረታታ ነው ያሉ ሲሆን አመራሩ ግን አውቆ ከማጥፋት ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል።

አክለውም በዚሁ ከቀጠለ ከተማዋን ቅርስ አልባ ወደማድረግ እየሄድን ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

መቅደላዊት ደረጄ
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
ሳፋሪኮም የሥራ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ለመንግሥት ማብራሪያ ሰጠ

በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ሳፋሪኮም፣ የሥራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዋና ሥራ አስፈጻሚው ፒተር ንዴግዋ የተማራው የሳፋሪኮም ልኡክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ እና ሚኒስቴር ዲኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚሁ በገንዘብ ሚኒስቴር ፍሬያማ በተባለው ውይይት ወቅት የሳፋሪኮም ኃላፊዎች ተቋማቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየሠራ የሚገኘውን እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል ነው የተባለው፡፡

ከመንግስት የሥራ ኃላፊዎቹ መካከል የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ መንግስት በቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎቶች ጥራት እና ስርጭት ጋር ተያይዞ ለሳፋሪኮም ድጋፍ እንደሚደርግም መግለጻቸው ተመላክቷል፡፡

ሳፋሪኮም የሚመራውና አምስት ኩባንያዎች እና ተቋማትን ያካተተው ‹‹ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ›› የተሰኘው ጥምረት የሚያቋቁመው ኩባንያ፤ በኢትዮጵያ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የማቅረብ ስራውን በጥር 2014 ለመጀመር እንዳቀደ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ሳፋሪኮም ፣ ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረት የኦፕሬሽን ፈቃድ የኦፕሬሽን ፈቃድ ለማግኘት 850 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ አቅርቦ ማሸነፉ ይታወቃል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
ፑቲን አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያገኘችው ውጤት ‹ዜሮ› ነው ብለዋል

የአፍጋኒስታን የ 20 ዓመት ዘመቻ በአሳዛኝ ሁኔታ አብቅቷል እናም ዋሽንግተን ምንም አላገኘችም ሲሉ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተችተዋል፡፡

የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን ውስጥ የነበረው ቆይታ ከንቱ ነበር ሲሉ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

ፕሬዝደንት ፑቲን ከወጣቶች ጋር ባደረጎት ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት “የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን ለ 20 ዓመታት ኖረዋል ፣ እና በእነዚህ 20 ዓመታት ውስጥ የአካባቢውን ህዝብ ሥልጣኔ ለማሳደግ ሳይሆን የኅብረተሰቡን የፖለቲካ አደረጃጀት ጨምሮ የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን ሞክረዋል ግን በእውነቱ አልተሳካላቸውም ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የትኛውንም ህብረተሰብ ላይ ቢሆን “ከውጭ ማንኛውንም ነገር መጫን አይቻልም” ነው ያሉት፡፡

የሩሲያው መሪ ምዕራባውያን አገሮችን እሴቶቻቸውን በምዕራባዊ ባልሆኑ ሀገሮች ላይ ለመጫን በመሞከራቸው ትልቅ ውድቀት ገጥሟዋል ሲሉ አጣጥለዋቸዋል፡፡

ያንን ለሚያደርጉት አሜሪካ እና በአፍጋኒስታን ለሚኖሩ ሰዎች የበለጠ ውጤቱ እጅግ አሳዛኝ ፣ ከባድ ኪሳራ፣ ድምር ውጤቱም ዜሮ ነው ”ብለዋል ፑቲን።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
“በዓለም ዙሪያ 35 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ ይሞታሉ ወይም የመሞት አደጋ ተጋርጦባቸዋል” ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠነቀቀ

በዓለም አቀፍ ደረጃ 150 ሚሊዮን በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ሲሆን 16 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት ደግሞ ለሞት ይጋለጣሉ ብሏል ድርጅቱ፡፡

አናዶሉ ኤጀንሲ የድርጅቱን ከፍተኛ ባለስልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት በ 55 ሀገሮች ወይም ክልሎች ውስጥ ቢያንስ 155 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ቀውስ ገጥሟቸዋል ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቁጥሩ አሁን ወደ 265 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የኢኮኖሚ ድቀት ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ፣ ወረርሽኞች እና ግጭቶች በዓለም ዙሪያ የሚጠበቀውን የምግብ ቀውስ ያባባሱ ምክንያቶች ሲሆን በአሁኑ ወቅት 821 ሚሊዮን ሰዎች ምግብ የማግኘት ችግር ገጥሟቸዋል ብለዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ የደን ቃጠሎ እና ጎርፍ የበለጠ አውዳሚ እየሆነ መምጣቷን ጠቅሶ ፣ ይህ በሚቀጥሉት ዓመታት የምግብ ቀውስ ከሚያስከትሉ በጣም አስፈላጊ ነገሮች አንዱ መሆኑን አፅንዖት ተሰጥቶታል።

በአለም ውስጥ ምግብ የማግኘት ዕድል የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከ 700 ሚሊዮን ወደ 821 ሚሊዮን ማደጉን ነው የተነገረው ፣ “በጣም ከባድ እርምጃዎች ቢወሰዱም ባለፉት አምስት ዓመታት የምግብ ዋስትና የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ ጨምሯል” ብለዋል ባለስልጣኑ።

የተባበሩት መንግስታት ባለሙያ የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ቀውስ ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎች የሚያስፈልጉ ዓለም አቀፍ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

በአህጉራችን በአፍሪካ ውስጥ 98 ሚሊዮን ሰዎች አጣዳፊ የምግብ ችግር እንደሚገጥማቸው ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

በ 2020 እጅግ አስከፊ የምግብ ቀውስ ካጋጠማቸው 10 አገሮች ውስጥ ደቡብ ሱዳን ፣ የመን ፣ ሶማሊያ ፣ አፍጋኒስታን ፣ ሶሪያ ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሄይቲ ይገኙበታል።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
ኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባት ልትሰጥ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ድረስ ለ22 ሚሊዮን ዜጎች ኮሮና ቫይረስ ክትባት ልትሰጥ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እስከ ፈረንጆቹ 2021 ድረስ 20 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ለመከተብ ታቅዷል ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ 2.4 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቿን የከተበች ሲሆን በኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት 22 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እስከ 2021 ድረስ ይከተባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በአንድ ሳምንት ብቻ እስከ 10ሺህ ያህል ዜጎች በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 308ሺህ 134 የደረሰ ሲሆን 276 ሺህ 842 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

እንደዚሁም 4 ሺህ 675 ያህል ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት በ 257 የፖሊስ መኮንኖች ይጠበቃሉ

የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በ257 የፖሊስ አባላት ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን መንግስት ይፋ አድርጓል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቢኔ ፀሐፊ ፍሬድ ማቲያንጊ ትላንት ለፓርላማው የደህንነት ኮሚቴ እንደገለፁት የምክትል ሩቶን መኖሪያ ቤት በሚጠብቁ የፖሊስ ክፍሎች ውስጥ የተደረጉ ለውጦች እንዳሉ ገልፀው ነገሩ ግን “መደበኛ” እና የተለመደ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ ሩቶን ከሚጠብቋቸው መኮንኖች መካከል 74 እጅግ ምርጥ የሚባሉ ፕሬዝደንታዊ ጠባቂዎች ናቸው ብለዋል።

ይህ ብቻ አይደለም የእኚህ ሰው ሁለት ሄሊኮፕተሮች በአውሮፕላን ማረፊያ ሆነው የሚጠብቁ ሌሉች የፖሊስ መኮኑኖች መኖራቸውን ሚቲያንጊ ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ አፍሪካ ዘግቧል።

በሀገሪቱ የምክትል ፕሬዝደንት ታሪክ እጅግ ጥበቃ የሚደረግላቸው ሰው ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡

ሰውዬው ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር ቅራኔ እንዳላቸው ይነገራል እንደውም በቀጣይ አመት ከስልጣናቸው ለማንሳት ኡሁራ አስበዋል ተብሏል፡፡

የምክትል ፕሬዝደንቱና ደጋፊዎቻቸው በእጅጉ በአይነ ቁራኛ የሚታዩ ናቸው ፡፡

ሰውዬው ከተቀናቃኙ ራይላ ኦዲንጋ ጋር የልብ ወዳጆች ናቸውም ይባላል፡፡

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
ታሊባን እና አሜሪካ ዳግም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የማይጀምሩበት ምንም ምክንያት የለውም አሉ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን

ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት የአሜሪካ የሕግ አውጪው ግሪጎሪ ሜይክስ ለታሊባን እውቅና መስጠት ይችላል ብለዋል

የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዴሞክራቲክ ሊቀመንበር ግሪጎሪ ሜይክስ ወደፊት በታሊባን የሚመራውን መንግስት ዕውቅና እንደማያገኝ መናገር ልክ አይደለም ብለዋል፡፡

ቡድኑ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የገባውን ቃል ማክበር እንዳለበት አሳስበዋል።

ሜይክስ ለኤም.ኤስ.ቢ.ሲ ሲናገሩ አሜሪካ ከቬትናም ከወጣች በኋላ ከቬትናም መንግስት ጋር የነበረው ግንኙነት በአንድ ወቅት የማይቻል መስሎ ነበር ፣ ነገር ግን ዋሽንግተን አሁን ከሃኖይ ጋር ሞቅ ያለ ግንኙነት አላት ብለዋል፡፡

ሜይክስ ሲያክሉ “ስለዚህ ከታሊባኑች ጋርም ይህ በጭራሽ አይሆንም አትሉም ፣ ግን ታሊባኖች በእውነት የሰብአዊ መብት መርሆዎች እንደሚጠብቁ ለማሳየት ብዙ ማድረግ አለባቸው ” ብለዋል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
"ሀገር አቀፍ የፆምና የፀሎት ምህላ አዋጅ"

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዲሱን አመት በሰላም ለመቀበል ያለመ ለ5 ቀናት የፀሎት መርሐግብር አወጀ።

የፀሎት መርሐ ግብሩ ከጷጉሜ 1 እሰከ 5 የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።

ጉባኤው አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ የሰላም ጥሪን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አገሪቱ ያጋጠማት ወቅታዊ ችግር በይቅርታና በፍቅር እንዲፈታ የተለያዩ እምነት የሚከተሉ ዜጎች በየሐይማኖታቸው የልዩ ፀሎቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በሁለቱም ወገኖች ያሉና በትግል ውስጥ ያሉ አካላት ለእርቅ ዝግጁ ሆነው አገሪቷን ማሻገር ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
“ሸኔ” በምእራብ ወለጋ ዞን 10 ሰዎችን ማገቱን መንግስት አስታወቀ

ባንክ እና ፍርድ ቤትን ጨምሮ ከ34 በላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይም ዝርፊያ ፈጽሟል።

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው “ሸኔ” በምእራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ በፈፀመው ጥቃት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን መንግስት አስታወቀ።

የቆንዳላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመረ በወረዳው “ሸኔ” በፈጸመው ጥቃት የንጹሃን የተገደሉ ሲሆን፣ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘርፈው በእሳት ተቃጥለዋል ማለታቸውን ኢዜአ በአፋን ኦሮሞ ገጽ አስነብቧል።

“በጥቃቱ ሸኔ 10 ሰዎችን አግቶ ወስዷል” ያሉት አቶ ቡላ ደመረ፤ 24 ንጹሃን ዜጎችን መግደሉንም አስታውቀዋል።

ቡድኑ የወረዳውን ፍርድ ቤት እና የአቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ሙሉ በሙሉ በእሳት ማጋየቱን በመጥቀስ፤ 4 የመንግስት አመራሮች መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆንዳላ ቅርንጫፍን አንዲሁም በ34 የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ያስታወቁት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በወረዳው የሚገኝ የ2ኛ ደረጃ ትምህት ቤት ንብረት እና የተማሪዎችን ማስረጃ ማውደሙንም ተናግረዋል።

የ“ሸኔ” ታጣቂዎች በአጠቃላይ በወረዳው ከነሃሴ 9፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በፈጸሙት ጥቃት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የቆንዳላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመረ ገልጸዋል።

“ህብረተሰቡ የሸኔ የሽብር ብድን የጥፋት ተግባርን ተረድቶ በአንድነት በመሆን የቡድኑን የጠላትነት ተግባር ሊያጋልጥ ይገባል” ሲሉም ዋና አስተዳዳው ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
ክላውድ ወርልድ ዋይድ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሄሎ ታክሲ ለብሄራዊ ፓርኮች 11 የቱሪስት አምቡላንሶችን ለመስጠት ቃል ገባ።


የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡት መካከል የሚገኘው ሄሎ ታክሲ በሀገራችን ለሚገኙ ብሄራዊ ፓርኮች 11 ቱሪስት አምቡላንሶችን ለመስጠት ቃል መግባቱ ተሰምቷል።

በዛሬው ዕለትም የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሀንስ የ3 አምቡላንሶችን ቁልፍ ማስረከባቸውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።


በዛሬው ዕለት የተረከቡት አምቡላንሶች ለሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ለባሌ ብሄራዊ ፓርክ እና ለነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።አክለውም ብሄራዊ ፓርኮችን የመረጥነው በብዛት ቱሪስቶች የሚጎበኟቸው ስለሆነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።


የሄሎ ታክሲ መስራች አቶ ዳንኤል ዮሀንስ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ አንዱ አምቡላንስ እስከ 600ሺ ብር እንደወጣበት ነግረውናል።
አምቡላንሶቹን ልንሰጥ የተነሳሳንበት ዋነኛው ምክንያትም በሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ቱሪስቶች ወሳኝ ሚና አላቸው ብሄራዊ ፓርኮቻችን ላይ የቱሪስት አምቡላንስ መኖሩ ቱሪስቶች እንደምናከብራቸው ማሳያ እንዲሆን አስበን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በመቅደላዊት ደረጀ

ነሃሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

“ተማር ልጄ” በሚለው ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኑ የብዙዎችን ቀልብ የማረከው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ነሐሴ 27፣2013 እኩለ ሌሊት በድንገት ማረፉ ነው የታወቀው።

"ተማር ልጄ ሌት ፀሀይ ነው ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው..." እያለ ሚሊየኖችን በዜማው መክሯል።

አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ 'ኤልቪስ ፕሪስሊ' የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶት ነበር።

ስቀሽ አታስቂኝ" ፣ " እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ"፣ " ማን ይሆን ትልቅ ሰው" ፣ " ምሽቱ ደመቀ"፣ "አዲስ አበባ ቤቴ" ፣ "የወይን ሃረጊቱ" ፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፤ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ" እና " ተማር ልጄ" ከአለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎች በዋናነት የሚጠቀሱለት ናቸው።

የድምፃዊው ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ ብሔራዊ ቴአትርን ጨምሮ አድናቂዎቹ ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም በድምፃዊው ህልፈት የተሰማውን ሀዘን አየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።
(FBC)
የአውሮፓ ህብረት ለታሊባን እውቅና እንደማይሰጥ አስታወቀ

የአውሮፓ ህብረት ታሊባንን እንደ አዲስ የአፍጋኒስታን መንግስት አልቀበልም ማለቱ ተሰምቷል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፕ ቦሬል ማንኛውም ተሳትፏችን ጥብቅ በሆኑ ሁኔታዎች የሚገዛ እና የአፍጋኒስታንን ህዝብ የሚደግፍ ብቻ ነው ብለዋል።

ዋሽንግተን ተመሳሳይ አቋም ወስዳለች ፣ ሩሲያ እና ቻይና ግን ለስላሳ አቋም ይዘዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በስሎቬኒያ በተካሄደው የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ “እኛ በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ወስነናል የፀጥታ ሁኔታው ከተሟላ” ብለዋል።

በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት በአፍጋኒስታን ላይ ከአሜሪካ ፣ ከቡድን 7 ፣ ከ ቡድን 20 እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን “በጥብቅ” ያስተባብራል ፣ እንዲሁም ከሀገሪቱ ጎረቤቶች ጋር “ክልላዊ የፖለቲካ የትብብር መድረክ” ይጀምራል ብለዋል።

ከቀናት በፊት አንድ የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዴሞክራቲክ ሊቀመንበር ግሪጎሪ ሜይክስ ወደፊት በታሊባን የሚመራውን መንግስት ዕውቅና እንደማያገኝ መናገር ልክ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሜይክስ ለኤም.ኤስ.ቢ.ሲ ሲናገሩ አሜሪካ ከቬትናም ከወጣች በኋላ ከቬትናም መንግስት ጋር የነበረው ግንኙነት በአንድ ወቅት የማይቻል መስሎ ነበር ፣ ነገር ግን ዋሽንግተን አሁን ከሃኖይ ጋር ሞቅ ያለ ግንኙነት አላት ብለዋል፡፡

ሜይክስ ሲያክሉ “ስለዚህ ከታሊባኖች ጋርም ይህ በጭራሽ አይሆንም አትሉም ፣ ግን ታሊባኖች በእውነት የሰብአዊ መብት መርሆዎች እንደሚጠብቁ ለማሳየት ብዙ ማድረግ አለባቸው ” ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም
መጭውን በዓላት ምክንያት በማድረግ 108 አማራጭ የገበያ ቦታዎች ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡

ቢሮዉ ቀጣዩን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ እየሰራ ካለው ስራ አንዱ ህብረተሰቡ አማራጭ እና ተደራሽ የገበያ ስፍራ እንዲያገኝና የሚፈልጋቸውን ምርቶች በቀጥታ ከአምራች ገበሬው ማግኘት እንዲችልና እየተስተዋለ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ቢሮዉ ለጣቢያችን በላከዉ መግለጫ አሳዉቋል፡፡


በአዲስ አበባ ከተማ 108 የመገበያያ ቦታዎችን እና ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ተጨማሪ የግብርና ምርት የተዘጋጀ መሆኑን ቦሮዉ ጠቁሟል፡፡

በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስራ የጀመሩት መሸጫዎቹ በከተማዋ የሚስተዋለዉን የኑሮ ዉድነት በማረጋጋት በተለይም የግብርና ውጤት የሆኑ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እንዲሁም ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ እንደ እንቁላል እና አይብ ያሉ የእንስሳት ተዋጽኦ አቅርቦትን ይበልጥ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

ከነዚህም ውስጥ 56 የቁም እንሰሳት የገበያ ስፍራዎች ሲሆኑ 52ቱ የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫዎች ናቸው ተብሏል፡፡

አዳዲስ የግብይት ቦታዎቹ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አገልሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን መሸጫ ስፍራዎቹ ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ተቀብለዉ ለሸማቹ ህብረተሰብ ምርት በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ከማቅረባቸው በተጨማሪ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንዲችሉ የተዘጋጁ አማራጭ የገበያ ስፍራዎች መሆናቸዉ ተነግሯል፡፡

በረድኤት ገበየሁ
ነሃሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም