Ethio Fm 107.8
20.5K subscribers
7.8K photos
16 videos
4 files
2.31K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
የመስቀል በአልን ምክንያት በማድረግ ከታሪፍ በላይ በጠየቁ 50 አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከመስቀል በአል አከባበር ጋር በተያያዘ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰድኩ እገኛለሁ ሲል አስታውቋል፡፡

በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመለስተኛ እና አነስተኛ መናሃሪያ የአዲስ ክፍለ ከተማ መናሃሪያ የቡድን መሪ አቶ ውብሸት ደመላሽ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት የመስቀልን በዓል ለማክበር ከመዲናዋ ውደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚንቀሳቀሱ ተጓዞች ላይ የሚደረግን የታሪፍ ጭማሪ ለመቆጣጠር አዲስ አሰራር ዘርገተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ከቁጥጥር ስራው ጋር በተያያዘ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ከታሪፍ በላይ በጠየቁ 50 ያህል አሽከርካሪዎች ላይ የቅጣት እርምጃ እንደተወሰደባቸው አቶ ውብሸት ነግረውናል፡፡

እንደ ዚሁም በሁለት ቀናት ውስጥ 110 ብር የነበረው የወልቄጤ መደበኛ የታሪፍ ዋጋ ላይ 300 በጠየቁ 5 ያህል አሽከርካሪዎች እስከ 2ሺህ ብር የሚደረስ ቅጣት ተላልፎባቸዋል ብለውናል፡፡

በበአሉ የተሸከርካሪ እጥረት እንዳይከሰት ባለስልጣን መስራቤቱ እንደ ርቀታቸው እና እንደ አካባቢው ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ከ35 ከመቶ እስከ 50 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ተደርጎ የህብረተሰቡን እንግልት ለማስቀረት እየሰሩ እንደሆነም አቶ ውብሸት ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በየቀኑ እስከ 1ሺህ ተሽከርካሪዎች ለስምሪት እንደሚወጡም ነው ሀላፊው ለጣቢያችን የተናገሩት፡፡

ከህጻናት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው አለምግባባት በተመለከተም እድሜያቸው 7 አመት የሆኑ ህጻናት በእናቶቻቸው ወይም በሞግዚቶቻቸው አማካኝነት ሳይከፍሉ ሊጓዙ እንደሚችሉ ተናግረው እድሜያቸው 12 የሆናቸው ደግሞ በግማሽ ከፍለው መጓዝ ይችላሉ ሲሉ አቶ ውብሸት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም
የኦሮሚያ ክልል እያካሄደ ባለው የአዲስ መንግስት ምስርታ አቶ ሽመልስ አብዲሳን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል ።
የኮቪድ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የአደባባይ  ክብረ በአላትን በከፍተኛ ጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባ ተጠቆመ

የአደባባይ ክብረ በአላትን ስናከብር  የኮቪድ-19 መከላከያ ጥንቃቄዎችን መፈፀም ስለሚገባ በአዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የጥንቃቄ መልእክቶች እየተላለፉ እንደሆነ ታውቋል።

መልእክቱን እያስተላለፉ የሚገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ፣ አፍሪ ኢቬንትስ እና ዩኤስ አይ ዲ ናቸው።

ህብረተሰቡ ማስክ ማድረግ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም እና  አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ከማክበር በተጨማሪ የኮቪድ ክተባትን በመከተብ ራሱን እና ቤተሰቡን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚገባው ዶ/ር ሜሎን በቀለ የአፍሪ ኢቨንትስ አስተባባሪ ተናግረዋል።

እንደ ዶ/ር ሜሎን ማብራርያ ከሆነ አሁን ላይ በብዛት በኮቪድ እየሞቱ ያሉ ዜጎች ክትባቱን ያልወሰዱ ዜጎች በመሆናቸው በክትባቱ ዙሪያ የሚናፈሱ ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን ቸል ብሎ ክትባቱን መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም በመስቀል አደባባይ የኮቪድ-19 የክትባት መርሃ ግብር እየተሰጠ እንደሆነ ተነግሯል።

በቀጣይም በኢሬቻ ክብረ በአል ተመሳሳይ ስራ እንደሚሰራ ከአዘጋጆቹ ሰምተናል።

መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ በመሆን ተመርጠዋል።

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የከተማው ምክር ቤት ምስረታ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር በ 138 ድምጽ በማግኘት ተመርጠዋል።

ወ/ሮ ቡዜና ከዚህ ቀደም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በሃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ሰኣት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

በመቅደላዊት ደረጄ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
ወ/ሮ ፋይዛ መሃመድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ተሾሙ

አዲስ አበባ ከተማ አዲስ ምክር ቤት ምስረታ ስነ-ስርአት እየተካሄደ ነው።

በማዘጋጃ ቤት ቴአትር እና ባህል አዳራሽ እየተካሄደ ባለው አዲስ ምክር ቤት ምስረታ ስነ-ስርአት በቀጣይ አምስት ዓመታት ምክር ቤቱን በአፈጉባኤነት እና በምክትል አፈጉባኤ እንዲሁም የከንቲባ ሹመት እና የካቢኔ አባላት ሹመት በቅደም ተከተል ለማካሄድ ባቀደው መሰረት በእጩነት አቅርቧቸው የነበሩት ወ/ሮ ፋይዛ ሞሃመድ 138 ድጋፍ አግኝተው ተሹመዋል፡፡

ወ/ሮ ፈይዛ መሐመድ ዑመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ነበሩ፡፡

በቀጣይም ምክር ቤቱን በአፈ ጉባኤነት ለአምስት ዓመታት እንዲያገለግሉ ተሹመዋል፡፡

በረድኤት ገበየሁ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትም ወይዘሮ አዳነች አቤቤን የከተማው ከንቲባ በማድረግ መርጧል፡፡

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከነሀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን አሁንም በድጋሚ ከተማዋን በከንቲባነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች ከተማዋን ከ 12 ወራት በላይ በምክትል ከንቲባ ማእረግ እየመሩ የሚገኙ ሲሆን ፣ ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው ጉባዔም ከንቲባ አድርጎ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በከንቲባነት ሾሟል፡፡

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዳማ ከተማ ከንቲባ፤ የገቢዎች ሚኒስትር፤ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በጅብሪል ሙሃመድ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
በከተማችን የምናካሄዳቸው ሁሉም የልማት ስራዎች በሂደታቸውም ሆነ በውጤታቸው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ለማድረግ በትኩረት እንሰራን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

በዛሬው እለት እየተካሄደ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምስረታ ስነ ስርዓት ላይ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ በከተማዋ የምንሰራቸው ሁሉም ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች በከታማችን ነዋሪዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥን እንዲያመጡ እንሰራን ብለዋል፡፡

በከተማችን ላይ ምርትና አገልግሎት አቅርቦቶችን ለማሻሻል ሲባል በጥናት ለመለየት ይሰራል ያሉት ወ/ሮ አዳነች የከተማዋን የመልማት አቅም ለማጎልበት በትብብር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች ይህንን የከተማዋን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጣን ደግሞ የመንግስት የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ የማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡

በተለይም ደግሞ የከተማዋ የመሰረተ ልማቶች ተደራሽነት ላይ በትኩረት የሚሰሩባቸው ዘርፎች መኖራቸውንም እንዲሁ ጠቁመዋል፡፡

ከነዚህም መካከል፤ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል፤ የውሃ፤ የመብራትና የኮምንዩኬሽን እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፎችን ለማሳለጥ በልዩ ትኩረት የምንሰራባቸው ዘርፎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች አክለውም ደሃ ተኮር መርሃ ግብሮቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ወጣቶችና ሴቶች ላይ የስራ እድል እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ የኢንዱስትሪን ልማት እድገትና የሰራ ፈጠራ ዘርፎችን ለመደገፍ ሲባል አንዱ የትኩረት አቅጣጫችን ይሆናል ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወሮ አዳነች የሌብነትና የዝርፊያ ስራዎችን ለመከላከል ሲባልም አዳዲስ የስነ ምግባር እንዲሁም ተጠያቂ ለመሆን የሚያስችሉ ደንቦችን እንዲወጡ እናደርጋንም ብለዋል፡፡

በጅብሪል ሙሃመድ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በአሁን ሰአት የከተማ አስተዳደሩን አስፈፃሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት በተዘጋጀው 101 አንቀፆች ባሉት ረቂቅ አዋጅ ላይ እየተወያየ ነው፡፡

በረቂቅ አዋጁ መሰረት ካለፈው ምክር ቤት 61 የነበሩት አጠቃላይ የአስፈፃሚ አካላት በአዲሱ ምክር ቤት 46 ሆኖ ሲቀርብ፣ የካቢኔ አባላት ደግሞ 24 እና በከንቲባ እንደ አስፈላጊነታቸው የሚሰየሙ ሌሎች ተቋማትን ጨምሮ አዳዲስ የካቢኔ አባላት የሆኑ ተቋማትን መያዙን ፋና ዘግቧል፡፡

በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ በካቢኔ ደረጃ የተደራጁ ተቋማት ከተች የተዘረዘሩትን እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ፦

1. ከንቲባ
2. ምክትል ከንቲባ
3. የከተማ ስራ አስኪያጅ
4. የስራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ
5. የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ
6. የፋይናንስ ቢሮ
7. የሰላም ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ
8. የፍትህ ቢሮ
9. የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ
10. የትራንስፖርት ቢሮ
11. የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ
12. የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ
13. የስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ
14. የንግድ ቢሮ
15. የጤና ቢሮ
16. የትምህርት ቢሮ
17. የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ
18. የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ
19. የገቢዎች ቢሮ
20. የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ
21. የኮሚኒኬሽን ቢሮ
22. የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ
23. የፕላንና ልማት ኮሚሽን
24. የኢንቨስትመንት ኮሚሽን
25. እንደ አስፈላጊነቱ በከንቲባ የሚሰየሙ ሌሎች የካቢኔ አባላት ይኖሩታል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ከ7 ሺህ በላይ ህጻናት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ሰማን

በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ከ7ሺህ በላይ ህጻናት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የሰማነው ከልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማእከል ነው፡፡

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማእከል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ በየአመቱ እስከ 500 የሚደርሱ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ እና ቀዶ ህክምና የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር በየቀኑ እንደሚጨምር ኢትዮ ኤፍ ኤም ከሃላፊው ሰምቷል፡፡

ይህ ቁጥር ግን ካለው ወረፋ አንጻር ሲታይ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

በማእከሉ አላቂ እቃዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው የተነሳ ወረፋ የሚጠብቁ ህጻናት ህክምና እያገኙ አለመሆናቸውን እና መድሀኒትም ቢሆን በሚፈለገው መጠን አለመገኝቱ በስራው ላይ እንቅፋት እንደሆነበት ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

እንደ አላቂ እቃዎች እና መድሀኒቶች በበቂ መጠን ቢሟሉ ኖሮ ግን በአመት እስከ 1 ሺህ 500 ያህል ቀዶ ጥገና ማድረግ ይቻል እንደነበር አንስተዋል፡፡

“ወረፋ አስይዘው ቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው ከማእከሉ ሲደወልላቸው ህይወታቸው እንዳለፈ የሚነገረን ጊዜ አለ” ፣ ይህ ሁኔታ ልብ የሚሰብር ነው” ሲሉ አቶ ህሩይ አሊ ተናግረዋል፡፡

ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙትን ህጻናት ለመታደግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉ ሀላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው 6710 ላይ ከአንድ ብር አንስቶ እስከ መቶ ብር ድረስ እገዛ ማድረግ ይችላል፡፡

የልብ ህመም አሁን ላይ በአለም ዋነኛ ገዳይ በሽታ እየሆነ መምጣቱን አለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያለመክቱ አቶ ህሩይ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጸዋል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም
ራሱን የስብከት እና የትግል ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው አዲስ ጅሃዳዊ ቡድን የሱዳን ሰላዮችን መግደሉ ተነግሯል

እምብዛም እውቅና የሌለው ራሱን የጅሃዲስት ቡድን በሚል የሚጠራው አዲስ ሃይል ስድስት የሱዳን የስለላ መኮንኖችን መግደሉን በትላንትናው እለት አስታውቋል።

እንደ ቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ መንግስት ጥቃቱ ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ ከሚጠራው (አይ ኤስ) ቡድን ታጣቂዎች ጋር እንደሚገናኝ ገልጻል ፡፡

ይህንን የመንግስት ወንጀላ ያጣጣለው ራሱን የስብከት እና የትግል ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ጅሃዲስት ቡድን ከአይ ኤስ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ቢያሳውቅም ጉዳዩን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ባለስልጣኖቹ በማክሰኞ ጥቃት አምስት አባሎቻቸው እንደተገደሉባቸው አምነው 11 የቡድኑን ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አሳውቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የሱዳን ጦር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ማክሸፉን ተከትሎ በሽግግር መንግስቱ በሲቪል አስተዳዳሮች እና በወታደራዊ ክንፎች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ በይበልጥ መካረሩ እየተነገረ ነው።

ያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም
ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኝ ድሮኖችን ሲያበር የተገኘ በሕግ ይጠየቃል ሲል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስጠነቀቀ

ለዜጎች ሰላም መረጋገጥ እንዲሁም የቁልፍ መሰረት ልማቶችን ደህንነት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመጠበቅና ስጋቶችን ለመከላከል ሲባል ድሮኖችን ያለምንም ህጋዊ ፈቃድ ለቀረፃ መጠቀምም ሆነ ማብረር እንደማይቻል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አሳሰበ፡፡

የሀገሪቱን ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም የመጠበቅ ተልዕኮ የተሰጠው መሆኑን የጠቀሰው ተቋሙ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚመለከተው አካል ህጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ ድሮኖችን በሀገሪቱ በሚካሄዱ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ህዝባዊ ሁነቶች ላይ ለቀረፃ ሲጠቀሙ እና ሲያበሩ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጿል፡፡

እነዚህ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጉዳዩ በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን አውቀው ከህገ ወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል፡፡

ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኝ ድሮኖችን ለቀረፃ ሲጠቀም እና ሲያበር የተገኘ ማንኛውም አካል ወይም ግለሰብ በህግ እንደሚጠየቅ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስጠንቅቋል።


ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም
ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አስረስ አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመረጡ

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አስረስ የክልሉ ርዕሠ-መስተዳድር አድርጎ መርጧል፡፡

ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በተለያዩ ትምህርት ኮሌጆች በመምህርነት፣ ዲን በመሆንና በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዝዳንትና ፕሬዝዳንት በመሆን ውጤታማ ሀላፊነትን የተወጡ አመራር መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም
የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ካቀረቧቸው እጩዎች መካከል አቶ ጣሂር ሙሃመድ ይገኙበታል።

አቶ ጣሂር ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች መካከል ሲሆኑ በአማራ ክልል የቱሪዝም ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ ነው የቀረቡት።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መንግስት 7 የተመድ ሰራተኞች በ72 ሰአታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላለፈ::


የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በተለያዩ ኤጀንሲዎች ውስጥ የሚሰሩ 7 የውጭ አገር ዜጎች በ72 ሰዓት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ማስተላለፉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት የመንግሥታቱ ድርጅት ባልደረቦች በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ ሥራ ሲሠሩ የተገኙ መሆናቸውም ነው የተገለፀው።


የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት የውጭ አገር ዜጎች የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ አዴል ኮርድ፣ የተራድኦ ምክትል አስተባባሪ ግራንት ሊያቲ፣ የተራድኦ ምክትል አስተባባሪ ተወካይ ሚስ ጋዳ ኤልታሂር ሙዳዊ እና የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ምክትል አስተባባሪ ሰኢድ መሀመድ ሀርሲ ናቸው።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም
ነገ መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ ከፀጥታ ስራ ጋር በተያያዘ ለሚከናወን ተግባር በመስቀል አደባባይ እና በዙሪያው የሚገኙ መንገዶች ለተወሰነ ሰዓት ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት፦

• ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒዬም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ወሎ ሰፈር አደባባይ

• ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ የሚውስደው መንገድ 22 ማዞሪያ

• ከ4ኪሎ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ፓርላማ መብራት

• በቸርችር ጎዳና ፒያሳ ወደ መስቀል የሚወስደው መንገድ ቴዎድሮስ አደባባይ

• ከጦር ሃይሎች በለገሃር ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት

• ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሳር ቤት አደባባይ

• ከሳሪስ ፣ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አጎና ሲኒማ

• ከቦሌ ፣ አትላስ ቅዱስ ዑራኤል ቤ/ከርስቲያን የሚወስደው መንገድ ኤድናሞል አደባባይ

• ከአዋሬ ወደ ካሳንቺስ የሚወስደው መንገድ ሴቶች አደባባይ

• ከልደታ በጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ የሚወስደው መንገድ አብነት ፈረሰኛ አካባቢ

ከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ ለጊዜው መንገዶቹ ለተሽከርካሪ ዝግ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የጉሙዝ ታጣቂዎች በሴዳል ወረዳ 145 ሰዎች ማገታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከልና ካማሺ ዞኖች የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ መፍጠን እንዳለበት አሳሳበ።

ኢሰመኮ በቤኒንሻንጉል ካማሺ ዞን የሚገኘው የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጾ፣ በክልሉ መተከል እና ካማሺ ዞኖች ያለውን የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግስቱና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሴዳል ወረዳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሸሽተው የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

በዚህ ችግር ምክንያትም ከመጋቢት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን የኢሰመኮ መግለጫ ያስረዳል።

ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ብለው የሚጠሯቸው ኃይሎች በወረዳው የሚኖሩ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አባወራዎችን (ቤተሰቦችን) ማገታቸውን ከዚሁ ሁኔታ የሸሹ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።

ታጣቂዎቹ “ዓላማችንን አልደገፋችሁም” በሚል ምክንያት አፍሰው እንደወሰዷቸውና በተለምዶ “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንዳገቷቸው አክለው አስረድተዋል።

ከታጋቾቹ መካከል “ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና” ቀሪው “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የተያዙ” መሆናቸውንም ከነዋሪዎቹ ማረጋገጡን ኢሰመኮ ገልጿል።

በመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በደረሰው ጥቃት ምክንያት 5 ሺህ የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉም ብሏል።

ኢሰመኮ አደረኩት ባለው ክትትል፣ ከመስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል “ውጊያ” በመካሄድ ላይ ነው ብሏል።

እንዲሁም ከመስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የሴዳል ወረዳ አመራሮችም ሆነ ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ አለመሆኑን ከነዋሪዎቹ ሰምቻለሁ ብሏል።

በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ የሲቪል ሰዎችን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ የጣሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ በፌዴራል እና ክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች አደጋውን ለመቀልበስ እና የሲቪል ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በቂ አለመሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም
አቶ ታገሰ ጫፎ ለ6ኛው ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአፈ ጉባኤነት ተመርጠዋል፡፡

አቶ ታገሰ ጫፎ ላለፉት ሶስት አመታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በአፈ ጉባኤነት መርተዋል፡፡

በ419 ድምጽ በስድስት ድምፅ ተዐቅቦ ተመርጠዋል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም