Ethio Fm 107.8
19.5K subscribers
6.24K photos
16 videos
4 files
2.27K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
ኢትዮጵያና ኬንያ የሞያሌን የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎትን ወደ ሥራ ለማስገባት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

የሁለቱን አገራት የንግድ ትስስር ያጠናክራል የተባለውን የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታና፣ የኬንያ የአገር ግዛት ደህንነት ኃላፊና የኬንያ ልዑክ መሪ ዊልሰን ጋቾከኪ በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የተካሄደው በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን ከሁለቱም አገራት የተወጣጡ የግል ዘርፍ ተወካዮች ተገኝተው ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት የጉምሩክ ኮሚሾነሩ አቶ ደበሌ ቀበታ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው፣ የሁለቱን አገራት የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር የሞያሌ አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

አገራቱን ድንበር ቢለያያቸውም ንግድ ያስተሳስራቸዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፣የሞያሌ የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት የንግድ ልውውጡን ከማጠንከሩ ባለፈ ለግሉም ዘርፍ ይበልጥ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

ስምምነቱ ፣የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ እና የዜጎችን እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፍ በመሆኑ ለኢትዮጵያና ለኬንያ የንግድ ልውውጥ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ዊልሰን ጋቾከኪ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የላፕሴት ኮሪደር መገንባት የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገውም ነው ኃላፊው ያነሱት።

ባለፈው አመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሃዋሳ ሞያሌ የጋራ ፍተሻ ጣቢያን መመረቃቸው የሚታወስ ነው።

በአባቱ መረቀ
መስከረም 05 ቀን 2014 ዓ.ም
በትግራይ ፤ በኤርትራ ስደተኞች ላይ የጦር ወንጀል እየተፈፀመ እንደሆነ የአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለፀ

የኤርትራ ስደተኞች ትግራይ ውስጥ ባለው ሀይል ታፍነው ይታሰራሉ፣ ይደፈራሉ፣ ይገደላሉ ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች፡፡

እንደ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት በኤርትራ ስደተኞች ላይ የሚፈፀሙት እነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በህወሀት ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ፌደራል ሀይል ጎን ቆመው በሚዋጉት የኤርትራ ሀይሎች ጭምር እንደሆነም አንስቷል፡

በሺዎች የሚቀጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች በትግራይ ካምፕ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የአፍረካ ቀንድ ዳይሬክተር እንደተናገሩት ፤ በትግራይ ዘግናኝ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈሮች እና ዘረፋዎች በኤርትራ ስደተኞች ላይ እየተፈፀሙ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ ግልፅ የጦርነት ወንጀሎች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኤርትራ ለዚህ ክስ እስካሁን ምንም አላለችም፤ ከዚህ ቀደም ግን ክሱን ውድቅ አድርጋ ነበር፡፡

ቢቢሲ ሮይተርስ የዜና ወኪልን ጠቅሶ እንደዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኤርትራ ጦር በትግራይ ይገኛል፡፡

ሔኖክ አስራት
መስከረም 06 ቀን 2014 ዓ.ም
በአባይ ግድብ ቀውስ ላይ ግብፅ ከወታደራዊ ግጭት መራቅ እንደምትፈልግ ገለጸች

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሾክሪ ከብሉምበርግ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀውስ ላይ ለመነጋገር ቁርጠኛ መሆኗን እና ከማንኛውም ወታደራዊ ግጭት መራቅ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

የግብፅ የውሃ ሀብቶች እና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ በበኩላቸው ግድቡን በተመለከተ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች እንደ ቀጠሉ ናቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ፍሬያማ እስኪሆኑ ድረስ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጥም ’’ በማለት ለአልጀዚራ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት አባል የሆኑት ራካ ሐሰን ለአል ሞኒተር ሲናገሩ “የወታደራዊ አማራጭ ለግብፅ የማይታሰብ እንደሆነ ገልፀው ከዚህ ይልቅ ፓለቲካዊ ጫና መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ’’ ተናግረዋ፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ግድቡን ከሚሰሩት ጀርመን እና ኢጣሊያን ኩባንያዎች ጋር መነጋገርን ጨምሮ ኢትዩጲያን ከሚደግፉት የአፍሪካ አገራት ጋርም መቀራረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በየአፍሪካ ህብረት ድርድሮች ይከሽፉ እንደሆነ የተጠየቁት ሀሰን “መደምደሚያውን መናገር አይቻልም ምክንያቱም ዲፕሎማሲ አይታወቅም” ብለዋል።

በሚያዚያ 6 ቀን በግብፅ ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል በኪንሻሳ ከተደረገው የመጨረሻ ዙር ድርድር በኃላ ለአምስት ወራት ድርድር ሳይደረግ መቆየቱን ተከትሎ ግብፅ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲመለከት ጠይቃለች።

ሐምሌ 8 የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ ኅብረት ሥር ድርድር እንዲጀመር ማሳሰቡ ይታወሳል።

በያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 07 ቀን 2014 ዓ.ም
ቻይና የአሜሪካ-እንግሊዝ-አውስትራሊያ ስምምነትን ኃላፊነት የጎደለው በማለት ኮንናለች

ቻይና በአሜሪካ ፣ በእንግሊዝ እና በአውስትራሊያ መካከል የተደረገውን ታሪካዊ የደህንነት ስምምነት “እጅግ ኃላፊነት የጎደለው” እና “ጠባብ አስተሳሰብ” በማለት ገልፃለች።

በስምምነቱ መሰረት አሜሪካ እና እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በኑክሌር ኃይል የሚሠሩ የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመሥራት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂን ለአውስትራሊያ ይሰጣሉ።

ሶስቱ ሀገራት ያደረጉት ስምምነት በደቡብ ቻይና ባህር ውስጥ የቻይናን ተፅእኖ ለመከላከል ያለመ መሆኑ ተሰምቷል።

ቀጠናው ለዓመታት የሀይል ሚዛን ማሳያ ሆኖ የቆየ ሲሆን እዚያ ያለው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው እንደ ቢቢሲ ዘገባ።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን እንዳሉት ህብረቱ “የአካባቢያዊ ሰላምን በእጅጉ ይጎዳል ... እና የመሳሪያ ውድድሩን ያጠናክራል” ብለዋል።

‹‹ ጊዜው ያለፈበት የቀዝቃዛው ጦርነት ... አስተሳሰብ ›› ብለው የጠሩትን ስምምነት ተችተው ሦስቱ አገሮች “የራሳቸውን ጥቅም እየጎዱ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቻይና መንግስታዊ ሚዲያዎች ስምምነቱን የሚያወግዙ ተመሳሳይ ርዕሶችን የያዙ ሲሆን በግሎባል ታይምስ ጋዜጣ ላይ አውስትራሊያ አሁን “እራሷን የቻይና ጠላት አድርጋለች” ብሏል።

በያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 07 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው ባሉት የሰብአዊ ቀውስ ምክንያት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ትእዛዝ ሰጡ።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከትግራይ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ ተጠያቂ ባደረጓቸው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ፣የአማራ ክልል ባለስልጣናት ፣ የህወሓት አመራሮች እና የኤርትራ መንግስት አመራሮች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በፈረሙት የስራ አስፈጻሚ አካል ትዕዛዝ (executive order) የትግራይ ክልል ግጭት እንዲራዘም ፤ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይቀርብ ያስተጓጎሉ እና የተክስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆነዋል ባሏቸው ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ወስነዋል።

ማዕቀቡ እንዲጣል ያዘዙትም ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና የአማራ ክልል መስተዳደር ባለስልጣናት ላይ፤ እንዲሁም በህወሓትና በኤርትራ መንግስት አመራሮች ላይ እንደሆነ የአሜሪካ መንግስት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

ተጠያቂ ናቸው የተባሉት የመንግስት ባለስልጣናት እና የህወሓት አመራሮች ማንነት ግን ይፋ አልተደረገም።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ የመንግስት ግምጃ ቤት ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን እየለየ ማዕቀቡን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ማዕቀቡ በተመረጡ ግለሰቦች ላይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ እና የኢትዮጵያ ህዝብን በማይጎዳ መልኩ እንደሚተገበር የአገሪቱ መንግስት ያወጣው መግለጫን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መስከረም 07 ቀን 2014 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

በደብዳቤያቸዉም ታዳጊ ሃገራት ከአሜሪካ የሚጠብቁት ከግለሰቦች ፍላጎት የጸዳና በዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማይገባ እንዲሆን ነዉ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በደብዳቤያቸዉ በህወሃት ምክንያት ህጻናትና እናቶችን ጭምሮ በርካታ ንፁሃን ዜጎች በስቃይ ላይ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከአብይ ግዛት መውጣታቸውን እንደማትቀበል አስታወቀች።


የደቡብ ሱዳን መንግስት በአብይ ግዛት በሰላም ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲወጡ ሱዳን ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አደረጓል።

የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ረዳት ሚኒስትር ዣን ፒዬር ላክሮይክስ ባለፈው ሳምንት ደቡብ ሱዳንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ መግለጫ ሰተዋል።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ልዑክ እና በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ፣ በአብይ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል እንደ ሱዳን ፖስት ዘገባ።

የደቡብ ሱዳን መንግስት መግለጫው በተጨማሪ በአወዛጋቢው ክልል ውስጥ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይልን ለመተካት ሱዳን ያቀረበችውን ጥሪ ውድቅ ማድረጎን አስታውቋል።

“በዚህ ሁኔታ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ይህ ኃይሉ የተሰጠውን ተልዕኮ በሙያ እና በገለልተኝነት እያከናወነ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ጦር እንዲወጣ በሚደረገው ጥሪ እንደማይስማማ ለመግለፅ እንወዳለን” ብሏል መግለጫው።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት የአብይን ግዛት ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝ ፓለቲካዊ ሂደት እንዲጀመር ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል ሲል አክሏል።

በያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 08 ቀን 2014 ዓ.ም
የሞሮኮ ትልቁ ኩባንያ፣ ኦሴፒ በድሬ ዳዋ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በመጀመሪያው ምዕራፍ 2.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም በድምሩ በሁለተኛው ምዕራፍ እስከ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ኢንቨስት ይደረጋል።

በድሬዳዋ የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ፕሮጀክት
በአመት 3.8 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ማምረት ይችላል ተብሏል።


በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በሞሮኮ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ኦሲፒ ከተባለው የሞሮኮ መንግስት ኩባንያ ጋር የተፈረመው ስምምነት በድሬዳዋ የማዳበሪያ ፕሮጀክት ለመተግበር የሚያስችል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፍላጎት እያደገ በመሄዱ በ2022 ከውጭ የሚገባው ማዳበሪያ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንዳለው ሲገመት ይህ መጠን በ2030 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 08 ቀን 2014 ዓ.ም
የጉጂ አባ ገዳዎች 'ሸኔ' የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አወጁ

የጉጂ አባ ገዳዎች በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው ታጣቂው ቡድን 'ሸኔ' የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አወጁ።

አባገዳዎቹ መንግሥት ሸኔ የሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን 'የኦሮሞ ጠላት ነው' ሲሉ የፈረጁት በቡድኑ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመገደላቸው ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ ታጣቂ ቡድኑን በተመሳሳይ 'የኦሮሞ ጠላት ነው' በማለት አውጀው ነበር።

የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ባለፈው ዓመት ይህንን ታጣቂ ቡድን 'ሸኔ'ን እና ህወሓትን አሸባሪ ድርጅቶች ሲል መፈረጁ ይታወሳል።

በቅርቡም እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን መንግሥትን ለመጣል ከህወሓት ጋር በትብብር እንደሚንቀሳቀስ ይፋ አድርጓል።

ባህላዊው መሪዎቹ፣ ታጣቂው ቡድን ላይ ውግዘት ያስተላለፉት "ኦሮሞ ሆኖ ኦሮሞን የሚገድል ጠላት ነው" በማለት እንደሆነ የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በጉጂ ሕይወት እጅጉን ፈታኝ ሆኗል የሚሉት አባ ገዳ ጂሎ፤ "የኦሮሞ ነጻነት ጦር ለኦሮሞ ሕዝብ ነው የምታገለው ይላል። ለኦሮሞ የሚታገል ከሆነ ኦሮሞን መግደል የለበትም" ብለዋል።

በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ማለትም በጉጂ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ2000 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ይናገራሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 08 ቀን 2014 ዓ.ም
"የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከአብዬ ግዛት መውጣታቸውን እንደማትቀበል ደቡብ ሱዳን አስታወቀች" በሚል ዜና "Sudans Post" ያወጣው ዘገባ ሀሰተኛ መሆኑን በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን ገልፀዋል።

አምባሳደሩ ይህንን ያሳወቁት ለኢትዮጵያ ቼክ የመረጃ አጣሪ ድረገፅ ነው።

ከዚሁ "SUDAN POST" ዘገባ ጋር በተያያዘ ፣ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከአብይ ግዛት መውጣታቸውን እንደማትቀበል አስታወቀች ብለን መዘገባችን ይታወሳል።

ነገር ግን አምባሳደሩ  " SUDAN POST "የተባለው ድረገፅ ሁልግዜ ሀሰተኛ መረጃ  ነው ፤ እንደዚህ አይነት ነገር አልተባለም" ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 09 ቀን 2014 ዓ.ም
የሱዳን የመንግስት ሚዲያዎች ‘ያልተሳካ’ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራን መደረጉን ዘገቡ

ከተፈጠረው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ከ 40 ያላነሱ ወታደራዊ መኮንኖች መታሰራቸው ተዘግቧል።

የሱዳን መንግስት ቲቪ ዛሬ ማለዳ ላይ “ያልተሳካ” መፈንቅለ መንግስት እንደነበረ አስታውቆ ፣ ከዋና ከተማዋ ካርቱም በአባይ ወንዝ ማዶ በኦምዱርማን የሚገኘውን የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ሕንፃ ለመቆጣጠር ሙከራ ተደርጓል ብሏል እንደ ዶቼቪሌ እንግሊዘኛው ዘገባ።

የሀገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሁኔታው በቁጥጥር ስር መዋሉን እና የህግ አስከባሪዎች ተጠርጣሪዎችን በአስቸኳይ በህግ መጠየቅ ይጀምራሉ ብለዋል።

ያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
የፖስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹን ወደ አስራ ሁለት ማሳደጉን የኢሚግሬሽን ፣ ዜግነትና ወሳኝ ሁነት ኤጀንሲ አስታወቀ

ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል ይህን የተናገሩት ለውጭ ጉዳይ ለዋናው መ/ቤት ሰራተኞች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ተጠሪ ተቋማት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ተጠሪ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ኤጀንሲው እየሰራ ስላለው የኦን ላይን አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና ሲሰጡ ነው።

ከመደበኛው አሰራር በተጨማሪ አሁን ላይ የኦን ላይን አገልግሎት ላይ ልዩ ትኩረቶ ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሙጅብ ባለፈው ዓመት ከ145ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች የኦን ላይን አገልግሎት ኤጀንሲው መስጠቱን ተናግረዋል ።

በሆሳእና፣ በጋምቤላ እና አሶሳ አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ቁጥር ወደ 12 ማድረሱን ለሰልጣኞች አብራርተዋል ።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከኤጀንሲው የሚፈልጉትን አገልግሎትን ለማግኘት የኦን ላይን አማራጩን በስፋት መጠቀም እንዳለባቸው መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
ቡና ባንክ ለጤና ባለሞያዎች እና ለመምህራን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው የሎተሪ እጣ በዛሬዉ እለት ወጥቷል፡፡

የሎተሪ እጣዎቹ በብሄራዊ ሎተሪ በዕድል አዳራሽ በህዝብ ፊት የወጡ ሲሆን የምእራብ መርካቶ ቅርንጫፍ ደንበኛ የሆኑት መምህር የ2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና አሸናፊ መሆናቸዉ ታዉቋል፡፡

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይም 12 ላፕቶፖች፣ 12 ዘመናዊ ታብሌቶች፣ 24 ስማርት የሞባይል ስልኮች እጣ ወጥቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ 6 የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች ለእድለኞች ደርሰዋል፡፡

የቡና ባንክ ስትራቴጂ ዋና ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ እንዳሉት፣የመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች የመጀመሪያው ዙር ፕሮግራም የሃገር ባለውለታዎችን ለማስታወስና የቁጠባ ባህልን ለማዳበር ታልሞ መዘጋጀቱን ገልጸዉ በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎችን ተሳታፊ ያደረገ የቁጠባ መርሃ ግብር መሆኑን አስታዉሰዋል፡፡

ለአንድ ሀገርና ብልጽግና የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ መንክር እነዚህ የሃገር ባለውለታዎች የቁጠባ ባህላቸውን ከማዳበርም በተጨማሪ ተሸላሚ የሚሆኑበትን አሰራር ቡና ባንክ መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

ቡና ባንክ አ.ማ ከተመሰረተ 12 ዓመታትን ያስቀጠረ ሲሆን ከ311 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት ከባንኩ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
የአግሮፉድና የፕላስቲክ ህትመት ማሸጊያ ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው፡፡

የንግድ ትርኢቱ በጀርመኑ ታዋቂ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ ፌር ትሬድ እና በኢትዮጵያው ፕራና ኢቨንትስ ትብብር ለ4ኛ ጊዜ እንደሚካሄድም ታውቋል።

ዝግጅቱ ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን፣ በአግሮ ፉድና እና እሴት ሰንሰለቱ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

ከተለያዩ አገራት የተዉጣጡ ዓለምአቀፋ የዘርፉ መሪዎች ለኢትዮጵያ የገበያ ፍላጎት የተዘጋጁ የግብርና፣የምግብ እና የመጠጥ ማቀናባበሪያ ቴክኖሎጂዎች እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈ የፕላስቲክ ህትመት እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂ እና መፍትሄዎችን በመያዝ፣ከ2ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች እንደሚያቀርቡም አዘጋጆቹ በሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል።

በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ፣ ከኢትዮጵያ ፣ከፈረንሳይ፣ከጀርመን ፣ከህንድ፣ከጣሊያን ፣ከኩዌት ፣ከናይጄሪያ ፣ከሩሲያ ፣ከደቡብ አፍሪካ ፣ከቱርክ እና ከአሜሪካ የተዉጣጡ ተሳታፊ ድርጅቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠብቃል ።

በአባቱ መረቀ

መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም
የሞያሌን አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ህገወጦችን ከመቀነሱም ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ የኢጋድ የጤና እና የማህበራዊ ልማት ዳይሬክተሯ ፋቲያ አልዋን ተናገሩ፡፡


ዳይሬክተሯ ይህን ያሉት ኢጋድ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሞያሌ ድንበር የጀመሩትን የንግድ ትስስር በሚያጠናክሩበትና በልማት ስራዎች ዙሪያ ከአባል አገራቱ ጋር እየመከረ በሚገኝበት ጉባኤ ላይ ነው።

የኢጋድ የጤና እና የማህበራዊ ልማት ዳይሬክተሯ ፋቲያ አልዋን፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሞያሌ ድንበር የጀመሩት ልማት በአካባቢው የሚገኙ ዜጎችን ህይወትን የሚሻሻል ነው ብለዋል ።
በተለይም በአካባቢውበህገወጥ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ከመቀነሱም ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

የዚህ ስብሰባ ዋነኛ አለማ በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር በተለይም በሞያሌ አካባቢ የሚገኙ ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም አገራት ድንበር አካባቢ የሚገኙ ከ1 ሺህ 6 መቶ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሯ ፋቲያ አልዋን አስታውቀዋል።

በቀጣይ፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በማስተሳሰር ረገድ ኢጋድ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለፁት ፋቲያ፣በተለይም የመተማ ጋለባት አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ኢትዮጵያና ሱዳንን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።
በመድረኩ፣ ከኢትዮጵያና ኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢጋድ፣ ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልል የተወጣጡ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ የሞያሌን አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ስምምነት ባለፈው ሳምንት መፈረማቸው የሚታወስ ነው።

በአባቱ መረቀ

መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡


በኮሮና ቫይረስ የማቾች ቁጥር ኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተነሳባት ቻይና መብለጧን ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኢትዮጵያ በኮቪድ19 የሞቱ ዜጎች ቁጥር ከ5ሺህ የበለጠ ሲሆን በቻይና በቫይረሱ የሞቱ ዜጎች ደግሞ 4ሺህ 636 ብቻ ነው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በሶስቱ ቀናት ብቻ 176 ያህል ዜጎች በቫይረሱ አማካኝነት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ይሕ ቁጥር ወደ ህክምና ጣቢያዎች መጥተው የሞቱትን ብቻ የሚያሳይ ሲሆን የህክምና ጣቢያ ሳይመጡ በቫይረሱ እንደተጠቁ ሳያውቁ በየቦታው በወረርሽኙ የሞቱ ወገኖች አጅጉን ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው፡፡

በትላንትናው እለትም የ43 ዜጎች ህይወት ሲያልፍ 700 ያህል ዜጎች ደግሞ በጽኑ ህሙማን ክፍል ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በሀገር ደረጃ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ተብሏል፡፡
በአሁኑ ሰአት የመተንፈሻ መሳሪያዎች እጥረት እያጋጠመ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማእከል ሲዲሲ ባስጠናው ጥናት መሰረት ያልተከተቡ ሰዎች ከተከተቡት ጋር ሲነጻጸር በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ከ4.5 እጥፍ በላይ ነው ይላል፡፡ ይህ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በዋነኝነት ክትባት መውሰድ አማራጭ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

እንደዚሁም ሆስፒታል የመግባት አድላቸው ከ10 እጥፍ በላይ እንደሆነ እና ታመው የመሞት እድላቸው ደግሞ 11 እጥፍ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም በማእከላዊ ሰሜን ሪጅን አካባቢዎች የ4G L.T.E.. ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት አስጀመረ

ኩባያንያው የሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎትን በላቀ ፍጥነት መጠቀም የሚያስችለውን የ4 ጂ አል.ቲ.ኢ.አድቫንስድ፣ በማእከላዊ ሰሜን ሪጅን በሆኑት በፍቼ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሱሉልታ፣ ገርበ ጉራቻ፣ ሰንዳፋ፣ በርኸ እና አካባቢዎች ተጠቃሚ የሚያደርገውን መርሃ ግብር በዛሬው እለት በደብረ ብርሃን ከተማ አስጀምረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሪት ፍሬህወት ታምሩ፣ አገልግሎቱ የላቀ ፍጥነትና ባንድዊድዝ እንዲሁም አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ይህም ደንበኞች አገልግሎታቸውን ዲጂታላዊ ለማድረግና ምርታማነታቸውን ለመጨመር ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

እስካሁን ድረስ ቴሌኮሙ ባደረጋቸው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ. አገልግሎት ማስፋፊያ ስራዎች የዛሬውን ጨምሮ በአዲስ አበባና በ15 ሪጅኖች የሚገኙ 86 ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

በጅብሪል ሙሃመድ
መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም