Ethio Fm 107.8
20.4K subscribers
7.52K photos
16 videos
4 files
2.3K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
ጆ ባይደን በደቡብ ምስራቅ ኤዢያ ሀገራት ስብሰባ ላይ ሊሳተፉ ነው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በደቡብ ምስራቅ ኤዢያ ሀገራት ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡

ሮይተርስ ዜና ወኪል እንዳስነበበው በደቡብ ምስራቅ ኤዢያ ሀገራት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ አትቷል፡፡

በፕሬዝዳንቱ የተመራ ሉኡክ እና ባለስልጣኖቻቸው በነገው እለት ስብሰባው ወደ ሚከናወንበት ስፍራ ያቀናሉም ሲል ነው ሮይተርስ ያስነበበው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ከስብሰባው በተጨማሪም ከተለያዩ የምስራቁ ሀገራት መሪዎች ጋር የተናጥል ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በተለይም በሰሜን ኮርያ የባልስቲክ ምሳኤል ጉዳይ እንደዚሁም በቻይናና በሀገራቸው ያለውን የንግድ ሽኩቻ በሚፈቱበት መንገድ ዙርያ ሰፊ የሆነ ምክክር ሊያደርጉ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩን የዜና ወኪሉ ያስነበበው፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሰሜኑን ጦርነት በተመለከተ በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠሩ

በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበላቸው።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤትን የተቀላቀሉ አራት የፓርላማ አባላት ናቸው።

የፓርላማ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠሩላቸው የሚጠይቀውን ደብዳቤ ለተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ያስገቡት ባለፈው ዓርብ ጥቅምት12/ 2014 ዓ.ም. መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ምክር ቤት ቀርበው ምላሽ እንዲሰጡባቸው ከተጠየቁ ጉዳዮች መካከል፤ የኢፌዲሪ መንግስት “በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በምን ያህል ጊዜ የማጠናቀቅ” እቅድ እንዳለው ነው።

የፌደራል መንግስት ጦርነቱን ካጠናቀቀ በኋላ "በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን በምን ያህል ጊዜ ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ" ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያብራሩላቸው እንደሚፈልጉ የኢዜማ የፓርላማ ተመራጮች በደብዳቤያቸው በተጨማሪነት ጠይቀዋል።
አራቱ የፓርላማ አባላት የጦርነቱን “ዘለቄታዊ መፍትሔ” የተመለከተ ጥያቄም በደብዳቤያቸው ማንሳታቸውን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሓላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለጣቢያችን አረጋግጠውልናል ።

ጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ መፈታታቸው ተገለፀ።

በአገሪቱ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የተለያዩ አገራት እና ኅብረቶች ካወገዙት በኋላ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዱክ ከአንድ ቀን እስር በኋላ ከእስር መፈታታቸው ፍራንስ 24 ዘግቧል

የሱዳን የሽግግር ሉኣላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሀን በትላንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለደኅንነታቸው ሲባል መታሰራቸውን ገልፀው ነገሮች ሲረጋጉ እንደሚፈቱ ተናግረው ነበር።

አልቡርሃን ፥ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እኔ ቤት ነው ያሉት” ያሉ ሲሆን “ይህ የሆነው ለደኅንነታቸው ሲባል ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ወታደራዊ ኃይሉ እስከ ሐምሌ 2015 የሲቪሉን አስተዳደር ሥልጣን ቀምቶ ለመቆየት የወሰነ ሲሆን በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር እንዲመለስ በመጠየቅ ተቃውሟቸው ቀጥለዋል

በትላንትናው እለት እንደተለቀቁ የተነገረው ሃምዱክ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ብሊንከን ጋር በስልክ መነጋጋራቸውንም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመጪው ቅዳሜ አስቸኳይ ስብሰባን ጠራ

በስድስተኛው የፖርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት የስራ ጊዜውን የጀመረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ጠራ፡፡

አስቸኳይ ስብሰባው በምክር ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ እንደሚካሄድ የገለጸው ምክር ቤቱ የስብሰባ አጀንዳዎቹን አላስታወቀም፡፡

የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) በትግራይ ክልል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ፤ ለማሳለጥ የነዳጅ ፍላጎታቸው እንዲሟላላቸው የመንግስትን ድጋፍ ጠየቁ

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ፕሬዚዳንት ፒተር ሞረር በዛሬው እለት ከምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በጽህፈት ቤታቸው መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል፡፡

የተቋሙ ፕሬዝዳንት በውይይታቸው ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ ባለው የረጅም ጊዜ አገልግሎት በመንግስት በኩል እየተደረገለት ስላላው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ ተቀቋሙ በትግራይ ክልል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የነዳጅ ፍላጎታቸው እንዲሟላላቸው፣ የጥሬ ገንዘብ መጠን እንዲጨመር እና የአየር በረራ ፈቃድ እንዲሰጣቸው መንግስትን መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ICRC በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ ፤ በሰብዓዊነት መርህ ተልዕኮውን ለመወጣት እየሰጠ ስላለው አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ድርጅቱ በትግራይ ክልል እያደረገ ካለው የሰብዓዊ ድጋፍ ጋር ተያይዞ በትክክለኛ ፍላጎት ላይ በመመስረት የነዳጅ ሆነ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት እንዲሟላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ደመቀ ፤ " ህወሓት በከፈተው ወረራ ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎችን ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነውም" ሲሉ አስረድተዋል።

በተጨማሪ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ያሉትን የጦር እስረኞች በተመለከተ "ታሳሪዎቹ ዜጎቻችን ከመሆናቸውም ባሻገር የዓለም አቀፍ ህግን ታሳቢ በማድረግ ተገቢው አያያዝ ይደረግላቸዋል " ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 17 ቀን 2014
በመዋዕለ ህጻናት ግቢ ውስጥ በሚገኝ ትራንስፎርመር ምክንያት ስጋት እንደገባቸው የተማሪ ወላጆች ተናገሩ

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ እናት አጸደ ህጻናት ት/ቤት ግቢ ውስጥ በተተከለ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር የተነሳ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስጋት ላይ እንደወደቁ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

መዋዕለ ህጻናቱ በ1989 ዓ.ም የተቋቋመ እንደሆነ እና የዛሬ 5 አመት ለመንገድ ስራ ሲባል የመዋዕለ ህጻናቱ የቅጥር ግቢ እንደፈረሰና በግቢው ውስጥ ለጊዜው በሚል ትራንስፎርመሩ እንዲተከል መደረጉን የትምህርት ቤቱ ባለቤት ነግረውናል።

ጣቢያችን በቦታው ተገኝቶ እንዳረጋገጠው ትራንስፎርመሩ ካሁን አሁን አደጋ ሊያደርስ ይችላል በማለት ትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን መገንዘብ ችለናል።

መምህራንም በግቢው ውስጥ ልጆችን ለማጫወት እየተሳቀቁ እንደሆነና አልፎ አልፎ የእሳት ብልጭታእና የፍንዳታ ድምጽ ስለሚወጣ አደጋ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሀት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ባለቤት በተደጋጋሚ ትራንስፎርመሩ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጪ እንዲሆንላቸው ቢጠይቁም ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጣቸው አካል አለመገኘቱን በምሬት ገልጻዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰሜን ሪጅን ዲስትሪክት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገላን ተሊላ ጉዳዩን እንደሰሙ የጥናት ቡድን ልከው እንዴት ወደ ግቢው ሊተከል እንደቻለ አጣርተን ፣ ሀላፊነት የሚወስደው አካል ካጣሩ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

መቅደላዊት ደረጀ
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም
Ethio Fm 107.8 pinned Deleted message
የአፍሪካ ህብረት ሱዳንን በየትኞቹም የአፍሪካ ህብረት የድርጊት መርሃ ግብሮቹ ላይ እንዳትሳተፍ አገደ፡፡

ህብረቱ እገዳው የጣለው በጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዱክ የሚመራው የሲቪል አስተዳደር ወደ ቦታው እስከሚመለስ ድረስ የሚቀጥል እንደሚቀጥል ህብረቱ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው ኮሚንኬ ማታወቁን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

በመግለጫው እገዳው ሀገሪቱን ወደ ምርጫ የሚመራውን የሽግግር ባለስልጣን " ወደነበረበት እስከሚመለስ" ድረስ እንደሚቆይ ተናግሯል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም
በኤሌክትሪክ እና በአነስተኛ የነዳጅ ፍጆታ የሚሰሩ 25 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ላቀርብ ነው አለ

አቤት ትራንስፖርት በሚቀጥሉት 5 አመታት 25 ሺህ በኤሌክትሪክ እና አነስተኛ የነዳጅ ፍጆታ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ የ2021 የጀርመንና የሩሲያ ስሪት መሆናቸውን የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሙሉ ደሜ ተናግረዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ባለ 5 ፤7 እና 26 መቀመጫ ያላቸውና ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ናቸው ተብሏል፡፡

መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች ከ 30 ሺህ ብር ጀምሮ የወረፋ መጠበቂያ ክፍያ በመክፈል ይስተናገዳሉ፡፡

ድርጅቱ በ7.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ስራውን እንደጀመረ የተገልጸ ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎቹ የሚገጣጠሙት ደግሞ በኮምቦልቻ ከተማ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

60 ሺህ ዜጎች በቀጣዮቹ 5 አመታት በአቤት ትራንስፖርት በኩል የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም
እራሱን በገንዘብ ለመሸጥ ጨረታ ያቀረበው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘ

በሀገረ ናይጀሪያ ባለፉት እሁድና ቅዳሜ እራሱን ለመሸጥ በማህበራዊ ሚዲያ ሲቀሰቅስ የነበረው ግለሰብ በፖሊስ መያዙ ተሰምቷል፡፡

የሀገሪቱ እስላማዊ ፖሊስ ለቢቢሲ እንዳስታወቀው ከሆነ የ26 አመት እድሜ ያለው አልዩ ኢድሪስ የተባለ ግለሰብ፤ ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ እኔን መግዛት የሚችልና የሚፈልግ ካለ እራሴን ለመሸጥ ዝግጁ ነኝ እያለ ሲቀሰቅስ ነው የያዝነው ብሏል፡፡

ግለሰቡ እራሱን ለመሸጥ ያቀረበው ገንዘብ ደግሞ 20 ሚሊዮን ናይራ ወይም 49 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡

እንደግለሰቡ አባባል ከሆነ ደግሞ እራሱን ለመሸጥ የወሰነው በከባድ ድህነት ውስጥ እንደሚኖር ከገለጸ በኋላ አማራጮችን ብዙ ፈለኩ ነገር ግን ለጊዜው የመጣልኝ ሃሳብ ይሄው ብቻ ነበር ብሏል፡፡

በምትኩ ደግሞ የጠየኩትን ገንዘብ ከፍሎ እኔን ለሚገዛኝ ሰው ሰራተኛው በመሆን አገለግለዋለሁ ሲል ይናገራል ግለሰቡ፡፡

ምናልባት እኔ ለራሴ የገመትኩትን ወይም የጠየኩትን 20 ሚሊዮን ናይራ ዋጋ ከፍሎ የሚገዛኝ ሰው ካገኘሁ፤ 10 ሚሊዮን ናይራ የሚሆነውን ለወላጆቼ እሰጣለሁ፤ 5 ሚሊዮን ናይራ ለመንግስት ግብር እከፍላለሁ፤ 2 ሚሊዮን ናይራ የሚሆነውን ደግሞ እኔን ሊገዛኝ የሚችለውን ሰው ላገናኘኝ ደላላ ወይም ማንኛም ሰው እሰጣለሁ፤ የተቀረውን ግን ለራሴ የኪስ ገንዘብ አደረርገዋለሁ የሚል እቅድ እንደነበረውም ለጋዜጠኞች አንድ በአንድ አስረድቷል፡፡

ነገር ግን የሀገሪቱ እስላማዊ ፖሊስ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር እራሱን በገንዘብ ለክቶ ወይም መዝኖ መሸጥም ይሁን መግዛት ፈጽሞ የተከለከለ በመሆኑ ግለሰቡ እንዲያዝ ተደርጓል ብሏል፡፡

ጂብሪል መሐመድ
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም
ወጋገን ባንክ ለልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

ባንኩ ድጋፉን ያደረገው የ25ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ይፋዊ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ወቅት ሲሆን ድጋፉ በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ህፃናት ህክምና እንዲያገኙ ለማስቻል መሆኑን የባንኩ የዳሬክተሮች የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብድሹ ሁሴን ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በባንኩ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የፈጠረበት ቢሆንም፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን ባንኩ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም የቦርድ ሰብሳቢዉ ተናግረዋል፡፡

የልብ ህሙማን ማእከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ ባንኩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዉ ሌሎች ተቋማትና ማህበረሰቡ ለማዕከሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የልብ ማእከሉ አምባሳደር አርቲስት መሰረት መብራቴ የ1 ሚሊየን ብር ቼኩን ከባንኩ የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አብዲሹ ሁሴን ተረክባለች።

ባንኩ ከዛሬ 25 አመት በፊት በ16 ባለሀብቶችና የተከፈለ 30 ሚሊየን ብር እንዲሁም 60 ሚሊዮን ብር የተፈረመ መነሻ ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን በአሁን ወቅት በመላው ሀገሪቱ 398 ቅርጫፎች አሉት፡፡

ወጋገን ባንክ የተከፈለ ካፒታሉ 3.2 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉን ደግሞ ወደ 5.5 ቢሊየን ብር አሳድጓል፡፡

በዮርዳኖስ ተሾመ
ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም
የፌስቡክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ አዲሱ የድርጅታቸው ስም ሜታ እንደሚሆን አስታውቋል።

"ለመገናኘት ቴክኖሎጂን የምንገነባ ኩባንያ ነን" ሲል ዙከርበርግ ተናግሯል።

ሜታ ፌስቡክን እና የፎቶ አፕ ኢንስታግራምን ፣ የመልእክት መላላኪያ መተግበሪያን ዋትስአፕን እና ምናባዊ እና የተጨመሩ የእውነታ ጥረቶችን ጨምሮ አገልግሎቶቹን የሚመራ አዲስ  ኩባንያ ይሆናልም ተብሏል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል ድረ ገጻችንን https://ethiofm107.com/ ይጎብኙ::

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ ቦታዎች በየሣምንቱ እሁድ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ባዛር ሊዘጋጅ እንደሆነ ተነገረ።

በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር እንዲሁም በምርት አቅርቦትና ስርጭት የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመቀነስ እንዲያስችል ባዛር ማዘጋጀት ማስፈለጉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታውቋል ፡፡

ባዛሩ በአቅራቢውና በሸማቹ መካከል የሚገኘውን የአቅርቦት ሰንሰለት ለማሳጠርና የገበያ አማራጮችን ለማስፋት ያለመ መሆኑን የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ገልጸዋል።

ለንግድ ባዛሩ የመጀመሪያ ዙር 20 ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተዘጋጁ ሲሆን የፊታችን እሁድም የትራንስፖርት መዳረሻ እና የሕዝብ ብዛትን መሠረት በማድረግ በመገናኛ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ቃሊቲ መናኸሪያ እና ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ የሙከራ ስራ ይጀመራል ብለዋል።

በባዛሩም ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ ምርቶች መካከል የጤፍና የስንዴ ዱቄት፣ የባልትና ውጤቶች፣ ጥራጥሬና፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በተጨማሪ ዘይት፣ ማካሮኒና ፓስታ ይቀርባሉ ብለዋል ኃላፊው፡፡

በዚህ ባዛር ትኩስ የግብርና ምርቶችን ለሸማቹ ማድረስ፣ በአምራችና በሸማቹ መካከል ያለውን የአቅርቦት ትስስር በማሳጠር አማራጭ የግብይት ስፍራን መፍጠር እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና መቀነስ መሆኑን አቶ አደም ተናግረዋል፡፡

በባዛሩ አቅርቦት ላይም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራትና አርሶ አደሮች፣ የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ ማኅበራት፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሰብልና አትክልት አቅራቢዎች ወይም የጅምላ ነጋዴዎች እና በምግብ ማቀነባበር የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንደሚሳተፉ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ክልሎች የደም እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ፡፡

የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት እንዳስታወቀው አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሌ ክልሎች በህክምና ተቋማት የደም እጥረት አጋጥሟል፡፡

በአዲስ አበባ ከዚህ በፊት በቀን እስከ 450 ከረጢት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ይሰበሰብ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እየተሰበሰበ ያለው ግን ከ300 ከረጢት ደም በታች ነው እንደ ባንኩ ገለጻ፡፡

አዲስ አበባ ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ከባድ የሚባሉ የህክምና አገልግሎቶች የሚሰጡበት ቦታ መሆኑ የደም እጥረቱን ከፍተኛ አድርጎታል፡፡

ባንኩ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ደም በመሰብሰብ ለህክምና ተቋማት በነጻ የሚሰጥ ሲሆን ህክምና ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት ለሚመጡ ታካሚዎችም ይሰጣል፡፡

ይሁንና በአራቱ ክልሎች በተለይም የካንሰር ህሙማንን፣ ወላድ እናቶችን፣ የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎችን እና ሌሎች ህክምና ፈላጊዎችን ለማከም የደም እጥረት እንዳጋጠመ በባንኩ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ተመስገን አበጀ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተመስገን መረጃ ከሆነ ከካንሰር እና ሌሎች ታማሚዎች የሚፈስን ደም ማስቆም የሚችለውን ደም (ፕላት ሴል) ለመስጠት በአዲስ አበባ ብቻ በቀን 200 ፕላት ሴል ያስፈልጋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተመስገን ገለጻ በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የደም እጥረት ያጋጠመው ትምህርት ቤቶች ዘግይተው በመከፈታቸው እና ክረምት ወራት ላይ ደም ይለግሱ የነበሩ በጎ ፈቃደኞች አሁን ላይ መልሰው ደም ለመለገስ ሶስት ወራትን መጠበቅ ስላለባቸው ነው፡፡

የጦርነት ቀጠና በሆነው በሰሜን ኢትዮጵያ የደም እጥረት አላጋጠመም ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “አካባቢው የጦርነት ቀጠና እንደመሆኑ መጠን የተጎጂዎች ቁጥር ስለሚጨምር የደም ፍላጎት ይጨምራል ይሁንና በአፋር እና በአማራ ክልሎች በጎ ፈቃደኞች በፍላጎቱ ልክ ደም እየለገሱ በመሆኑ እስካሁን የደም እጥረት አላጋጠመም” ብለዋል ዶ/ር ተመስገን፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘዉ ሃና ማሪያም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በምግብ መበከል ምክንያት መታመማቸው የተነገረው ተማሪዎች የከፋ ኬዝ አለመኖሩንና የሆስፒታል ምንጮች ገለጹ

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዉስጥ በሚገኘዉ ጡሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ለህክምና 98 ተማሪዎች የመጡ ሲሆን ምርመራ ከተደረገላቸዉ ሴት 47 እና 51 ወንድ በአጠቃላይ 98 ተማሪዎች የመደንገጥና ከመጠነኛ ማስታወክ ስሜት ዉጭ የከፋ ኬዝ አለመኖሩን ነገር ግን ሁለት ተማሪዎች ብቻ መጠነኛ ህመም እንዳጋጠመው ከሆስፒታሉ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳምሶን ጉዱ እንደገለፁልን ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ አለመሆኑን እና የሞተ ተማሪ አለመኖሩን ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልፀዉልናል።

ኃላፊዉ ተጨማሪ ተማሪዎችም ምርመራ እየተደረገላቸዉ መሆኑን ሁሉም ተማሪዎች ነጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በመግለፅ በምግቡ ላይ የተከሰተዉን ሁኔታ በባለሙያ ጥናት በማድረግ የሚረጋገጥና ለህብረተሰቡ ይፋ ይደረጋል ያሉ ሲሆን ወላጆች እንዲረጋጉ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።

ያይኔአበባ ሻምበል
ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የወር አበባ ከሚያዩ ሴቶች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት የንጽህና መጠበቂያ እንደማያገኙ ተሰምቷል፡፡

በኢትዮጵያ 51 ሚሊዮን ከሚጠጉ ሴቶች መካከል 31 ሚሊየን የሚሆኑት የወር አበባ የሚያዩ ናቸው ተብሏል፡፡

የወር አበባ ከሚያዩ 31 ሚሊየን ሴቶች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ምንም አይነት የንጽህና መጠበቂያ አያገኙም ሲል አይ ኬር የተሰኝ ድርጅት አስታውቋል፡፡

በሴቶች ጉዳይ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ የሚገኝው አይ ኬር በኢትዮጵያ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ በርካታ ሴቶች ክትምህርት ገበታ ውጭ እየሆኑ ይገኛሉ ሲል አስታውቋል፡፡

የአይ ኬር መስራች የሆነችው ወጣት ሀና ላሌም እንደምትለው ከሆነ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ሴቶች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ ናቸው ብላለች፡፡

የወር አበባ ከአስር እስከ 14 ዓመት አንስቶ ከ45 እስከ 50 ዓመት የሚዘልቅ ዑደት ነው የምትለው ሀና ሴቶች በዚህ ምክንያት ሊሸማቀቁ አይገባም ትላለች፡፡

በገጠሪቱ ክፍል የሚገኙ በርካታ ሴቶች እንኳንስ የንጽህና መጠበቂያ ሊያገኙ ይቅርና ስለ ወር አበባ የሚያውቁት አንዳችም ነገር እንደሌለ ወጣት ሀና ተናግራለች፡፡

በደቡብ ክልል በአንድ ዞን ሴት ልጅ የወር አበባዋ በሚመጣባት ሰአት ውጭ እስከ ማደር ያደርሳታል ስትልም ነው የነገሩን ክብደት የገለጸችው፡፡

ይህ የሚያሳየው በሀገር ደረጃ ስለ ወር አበባ ምንም እንዳልተሰራ ነው ብላለች፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ የሚያመርቱ ስምንት ብቻ ድርጅቶች እንደሆኑ የተናገረችው ወጣት ሀና ካለው ፍላጎት አንጻር ሲታይ ውስን መሆኑን ተናግራለች፡፡

ከዋጋው አንጻርም የሴቶች የመግዛት አቅም ጋር የተመጣጠነ እንዳልሆነ ተናግራ በዋጋው እና በጥራቱ ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብላለች፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በ2022 የወተት ምርቷ 11.8 ቢሊየን ሊትር ለማድረስ በእቅድ መያዟ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚነገረው፡፡

ፍላጎቱ እየጨመረ ቢመጣም የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦት ግን በሚፈለገው መጠንና ጥራቱን ማዳረስ አለመቻሉም ይነገራል፡፡

እንደ አለም አቀፍ የግብርና ድርጅት መረጃ ከሆነ በፈረንጆቹ 2030 ላይ የወተት ምርቷ 231 ቶን ሊትር ወተት ትጠቀማለች ይላል፡፡

እንደዚሁም በ2022 አመት ደግሞ የወተት ምርቷን 11.8 ቢሊየን ሊትር ለማምረት እቅድ መያዟንም ነው መረጃው የሚጠቁመው፡፡

ሀገሪቷ በዚሁ አመት 1.7 ሚሊየን ኪሎግራም የስጋ ምርት ለማምረት ያቀደች ሲሆን 5.5 ቢሊየን የእንቁላል ምርት ለማግኝት እንዳሰበችም ያመላክታል፡፡

ሀገሪቷ በአስር አመት የልማት እቅዷ ላይ እነዳስቀመጠችው 247ሺህ ቶን የአሳ ምርት እንደዚሁም 106ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ ለማምረት አቅዳለች፡፡

በአፍሪካ በ2030 2.6 ሚሊየን ቶን የአሳ ምርት በምግብነት ሊውል እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የዶሮ እና የእንስሳት ሀብት አውደ ርእይ በይፋ በተከፈተበት ሰአት የሀገር ወስጥ እና የውጭ ሀገር በዶሮ እርባታ እና እንስሳት ሀብት ላይ የተሳተፉ አካለት ምርቶቻቸውን ለጎብኝዎች አቅርበዋል፡፡

አውደ ርእዩ ለሶስት ቀናት ለሚቆይ ሲሆን ከጀርመን፣ ከሀንጋሪ፣ ከዮርዳኖስ፣ ኔዘርላንድ እና ስኮትላንድ ያደረጉ ከ50 በላይ አለም አቀፍ ዘርፉ መሪዎች ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም
በሩስያ ምግብ ቤቶች እና ሱቆች እየተዘጉ ነው፡፡

በሩስያ የኮቪድ19 እንደ ገና ማገርሸቱን ተከትሎ ሱቆች እና ምግብ ቤቶች እየተዘጉ ይገኛሉ፡፡

በሞስኮ የሚገኙ በርካታ ምግብ ቤቶች እና ሱቆች እንዲዘጉ መንግስት ያስታወቀ ሲሆን አላስፈላጊ የሆኑ ምርቶች እንዳይሸጡ አስጠንቅቋል፡፡

ሀገሪታ በትላንትናው እለት ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር እና የማቾች ቁጥር ማስመዝገቧ ተከትሎ ነው ውሳኔው ያስተላለፈችው፡፡

በትላንትናው እለት በሀገሪቱ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከ1ሺህ በላይ ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉን ተሰምቷል፡፡

ከአውሮፓ ሀገራት ሩስያ ከፍተኛ የማቾች እና የተጠቂዎች ቁጥር ያስመዘገበች ሀገር ስትሆን አሁንም የቫይረሱ ስርጭት አይሎ ነው የሚገኝው፡፡

ይህ በመሆኑም ለሚቀጥሉት 11 ቀናት ምግብ ቤቶች ሱቆች እና ሌሎችም አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ውሳኔ አስተላልፋለች፡፡

እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ 8.4 ሚሊየን ዜጎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 235 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፋል ሲል የሀገሪቱ የዜና ወኪል የሆነው አር ቲቪ አስታውቋል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም
ሃና ማሪያም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ባልታወቀ ምክንያት ታመው ነበር የተባሉ ተማሪዎች በደህና ወደ ቤተሰቦቻቸው ተቀላቀሉ

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘዉ ሃና ማሪያም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ምክንያቱ በውል ባልተገለፀ ሁኔታ ሆስፒታል ገብተው የነበሩ ተማሪዎች ትላንት ማምሻውን በደህና ሁኔታ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተነግሯል።

ወደ ቤተሰቦቻቸው በሰላም የተቀላቀሉት ተማሪዎች 153 እንደሆነ የጡሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ይታያል አባተ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አረጋግጠዋል።

ተማሪዎቹ ያጋጠማቸውን ሁኔታ ኢትዮ ኤፍ ኤም የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳምሶን ጉዱ የጠየቀ ሲሆን በሰዓቱ ተማሪዎቹ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ ነገር እንዳልገጠማቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሀና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች የምግብ መመረዝ አጋጥሟቸዋል በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብሏል።

እርግጥ ተማሪዎቹ በትክክልም ያጋጠማቸው ምን ነበር ሲል ኢትዮ ኤፍ ኤም የጡሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ይታያል አባተን የጠየቀ ሲሆን አሁን ላይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው የተማሪዎቹ ደህንነት እንጂ በርግጥም ተማሪዎቹ ምን እንዳጋጠማቸው ለማረጋገጥ አስፈላጊ ምርመራና መረጃ እንደሚያስፈልግ ነግረውናል፡፡

የውልሰው ገዝሙ
ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም
23ኛው የጤና ጉባኤ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀመረ

ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት በአዲስ ምዕራፍ በሚል መሪ ቃል 23ኛው የጤና ጉባኤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ኡስማን፣ ክልሉ አርብቶ አደር ማህበረሰብ የሚኖሩበትና ኋላ ቀር በመሆኑ በጤናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል መንግስት የአርብቶ አደሩን የጤና ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የጤና አገልግሎት ማስጀመሩንም አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ልዩ ፍላጎት ለሚሹ አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት በተለይም የህፃናትና የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ አኳያ በአገር አቀፍ ደረጃ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሥርዓተ ምግብን በተመለከተም ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሰቆጣ ቃል ኪዳን በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን መቶ 10 ሺህ ህፃናት ከመቀንጨር ችግር ማላቀቅ እንደቻለም ዶክተር ሊያ አንስተዋል።

የፌደራሉ መንግስት ከአጠቃላይ አመታዊ በጀቱ 13.3 በመቶ የሚሆነውን ለጤናው ዘርፍ ባለፈው አመት መመደቡም ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ የጤና ፋይናንስን ለማሳደግ በተሠራው ስራ 3መቶ 80ሚሊዮን ዶላር ከአጋር ተቋማት እንደተገኘም ሚኒስትሯ ገልፀዋል ።

የኮቪድ ወረርሽኝና ግጭቶች የጤናውን ዘርፍ ገቢ መሻማታቸውን የጤና ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያቀደውን ዕቅድ እንዳያሳካ ችግር ፈጥሮበታል ተብሏል።

23ኛው የጤና ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የክልል የቢሮ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የአለም አቀፋ አጋር ተቋማት በመሣተፍ ላይ ናቸው።

አባቱ መረቀ
ጥቅምት 20 ቀን 2014
በቅኝ ግዛት ዘመን ምእራባዊያን ሀገራት 90 ከመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ባህላዊ ቅርስ መዝረፋቸውን የቅርስ ተመራማሪዎች ተናገሩ፡፡

ይህ የተገለፀው ከሰሞኑ በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ የሚገኙ የአፍሪካ ቅርሶች በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ነው።

የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የባህላዊ ቅርሶች ተመራማሪ ሶኒታ አሊየን በጥናቱ እንዳረጋገጠው በአፍሪካ በተለይም በናይጄርያ እና በቤኒን በርካታ ታሪካዊ እንደዚሁም ባህላዊ ቅርሶች መዘረፋቸውን አትቷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የጥናት ማእከል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው በቀኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉት ቅርሶች በተገቢው መንገድ ለሀገራቱ መመለስ ያስፈልጋል ሲሉ ተመራማሪዎች ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት እና ሶስት አስርት አመታት የተዘረፉትን ቅርሶቼ ይመለሱልኝ እያሉ የነበሩት የአፍሪካ ሀገራት እስካሁን ከሀጉሪቱ የተዘረፉትን ቅርሶች ማስመለስ አቅቷቸዋል፡፡

በቀኝ ግዛት ዘመን ከቤኒን በርካታ ቁጥር ያላቸው ባህላዊ ቅርሶች በፈረንሳይ እና በእንግሊዝ ወታደሮች እንደተዘረፉም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

ከ15ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ቤኒን በምዕራብ አፍሪካ ከሚገኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃገራት መካከል አንዷ ነበረች።

በአውሮፓዊያኑ 1897 ቤኒን በእንግሊዝ ዲፕሎማቶችን ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ በብሪታንያ ጥቃት ደርሶባታል። በዚህም ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ተቃጥላለች።

ከዚህ ተልዕኮ መጠናቀቅ በኋላ ከነሐስ ቅርጻ ቅርጾች በተጨማሪ ሌሎችም የንጉሳዊ ቤተሰቡ ቅርሶች ተዘርፈዋል።

አንዳንዶቹ የተዘረፉት ቅርሶች በወታደሮች እጅ ሲገቡ ሌሎቹ ደግሞ ተሽጠው ወታደራዊው ተልዕኮን ለማስፈፀም የወጣውን ወጪ እንዲሸፍን ተደርጓል።

የነሐስ ቅርሶቹ በመላው ዓለም ተበትነው ይገኛሉ።

ከኢትዮጵያም ከ188 አመታት በፊት በርካታ የንጉሳውያን ካባዎች የወርቅ አክሊሎች የብራና ጹሁፎች እና ሌሎችም ቅርሶች በእንግሊዝ ወታደሮች መዘረፋቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን ባደረገችው ጥረት የአጼ ቴወድሮስ የጸጉር ሹርባ ማስመለሷ አይዘነጋም፡፡ አልጀዚራ

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም