Ethio Fm 107.8
20.6K subscribers
7.98K photos
16 videos
4 files
2.31K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
የሞሮኮ ትልቁ ኩባንያ፣ ኦሴፒ በድሬ ዳዋ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በመጀመሪያው ምዕራፍ 2.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም በድምሩ በሁለተኛው ምዕራፍ እስከ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ኢንቨስት ይደረጋል።

በድሬዳዋ የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ፕሮጀክት
በአመት 3.8 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ማምረት ይችላል ተብሏል።


በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በሞሮኮ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ኦሲፒ ከተባለው የሞሮኮ መንግስት ኩባንያ ጋር የተፈረመው ስምምነት በድሬዳዋ የማዳበሪያ ፕሮጀክት ለመተግበር የሚያስችል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፍላጎት እያደገ በመሄዱ በ2022 ከውጭ የሚገባው ማዳበሪያ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንዳለው ሲገመት ይህ መጠን በ2030 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 08 ቀን 2014 ዓ.ም
የጉጂ አባ ገዳዎች 'ሸኔ' የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አወጁ

የጉጂ አባ ገዳዎች በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው ታጣቂው ቡድን 'ሸኔ' የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አወጁ።

አባገዳዎቹ መንግሥት ሸኔ የሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን 'የኦሮሞ ጠላት ነው' ሲሉ የፈረጁት በቡድኑ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመገደላቸው ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ ታጣቂ ቡድኑን በተመሳሳይ 'የኦሮሞ ጠላት ነው' በማለት አውጀው ነበር።

የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ባለፈው ዓመት ይህንን ታጣቂ ቡድን 'ሸኔ'ን እና ህወሓትን አሸባሪ ድርጅቶች ሲል መፈረጁ ይታወሳል።

በቅርቡም እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን መንግሥትን ለመጣል ከህወሓት ጋር በትብብር እንደሚንቀሳቀስ ይፋ አድርጓል።

ባህላዊው መሪዎቹ፣ ታጣቂው ቡድን ላይ ውግዘት ያስተላለፉት "ኦሮሞ ሆኖ ኦሮሞን የሚገድል ጠላት ነው" በማለት እንደሆነ የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በጉጂ ሕይወት እጅጉን ፈታኝ ሆኗል የሚሉት አባ ገዳ ጂሎ፤ "የኦሮሞ ነጻነት ጦር ለኦሮሞ ሕዝብ ነው የምታገለው ይላል። ለኦሮሞ የሚታገል ከሆነ ኦሮሞን መግደል የለበትም" ብለዋል።

በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ማለትም በጉጂ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ2000 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ይናገራሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 08 ቀን 2014 ዓ.ም
"የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከአብዬ ግዛት መውጣታቸውን እንደማትቀበል ደቡብ ሱዳን አስታወቀች" በሚል ዜና "Sudans Post" ያወጣው ዘገባ ሀሰተኛ መሆኑን በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን ገልፀዋል።

አምባሳደሩ ይህንን ያሳወቁት ለኢትዮጵያ ቼክ የመረጃ አጣሪ ድረገፅ ነው።

ከዚሁ "SUDAN POST" ዘገባ ጋር በተያያዘ ፣ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከአብይ ግዛት መውጣታቸውን እንደማትቀበል አስታወቀች ብለን መዘገባችን ይታወሳል።

ነገር ግን አምባሳደሩ  " SUDAN POST "የተባለው ድረገፅ ሁልግዜ ሀሰተኛ መረጃ  ነው ፤ እንደዚህ አይነት ነገር አልተባለም" ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 09 ቀን 2014 ዓ.ም
የሱዳን የመንግስት ሚዲያዎች ‘ያልተሳካ’ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራን መደረጉን ዘገቡ

ከተፈጠረው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ከ 40 ያላነሱ ወታደራዊ መኮንኖች መታሰራቸው ተዘግቧል።

የሱዳን መንግስት ቲቪ ዛሬ ማለዳ ላይ “ያልተሳካ” መፈንቅለ መንግስት እንደነበረ አስታውቆ ፣ ከዋና ከተማዋ ካርቱም በአባይ ወንዝ ማዶ በኦምዱርማን የሚገኘውን የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ሕንፃ ለመቆጣጠር ሙከራ ተደርጓል ብሏል እንደ ዶቼቪሌ እንግሊዘኛው ዘገባ።

የሀገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሁኔታው በቁጥጥር ስር መዋሉን እና የህግ አስከባሪዎች ተጠርጣሪዎችን በአስቸኳይ በህግ መጠየቅ ይጀምራሉ ብለዋል።

ያይኔአበባ ሻምበል
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
የፖስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹን ወደ አስራ ሁለት ማሳደጉን የኢሚግሬሽን ፣ ዜግነትና ወሳኝ ሁነት ኤጀንሲ አስታወቀ

ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል ይህን የተናገሩት ለውጭ ጉዳይ ለዋናው መ/ቤት ሰራተኞች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ተጠሪ ተቋማት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ተጠሪ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ኤጀንሲው እየሰራ ስላለው የኦን ላይን አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና ሲሰጡ ነው።

ከመደበኛው አሰራር በተጨማሪ አሁን ላይ የኦን ላይን አገልግሎት ላይ ልዩ ትኩረቶ ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሙጅብ ባለፈው ዓመት ከ145ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች የኦን ላይን አገልግሎት ኤጀንሲው መስጠቱን ተናግረዋል ።

በሆሳእና፣ በጋምቤላ እና አሶሳ አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ቁጥር ወደ 12 ማድረሱን ለሰልጣኞች አብራርተዋል ።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከኤጀንሲው የሚፈልጉትን አገልግሎትን ለማግኘት የኦን ላይን አማራጩን በስፋት መጠቀም እንዳለባቸው መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
ቡና ባንክ ለጤና ባለሞያዎች እና ለመምህራን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው የሎተሪ እጣ በዛሬዉ እለት ወጥቷል፡፡

የሎተሪ እጣዎቹ በብሄራዊ ሎተሪ በዕድል አዳራሽ በህዝብ ፊት የወጡ ሲሆን የምእራብ መርካቶ ቅርንጫፍ ደንበኛ የሆኑት መምህር የ2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና አሸናፊ መሆናቸዉ ታዉቋል፡፡

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይም 12 ላፕቶፖች፣ 12 ዘመናዊ ታብሌቶች፣ 24 ስማርት የሞባይል ስልኮች እጣ ወጥቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ 6 የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች ለእድለኞች ደርሰዋል፡፡

የቡና ባንክ ስትራቴጂ ዋና ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ እንዳሉት፣የመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች የመጀመሪያው ዙር ፕሮግራም የሃገር ባለውለታዎችን ለማስታወስና የቁጠባ ባህልን ለማዳበር ታልሞ መዘጋጀቱን ገልጸዉ በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎችን ተሳታፊ ያደረገ የቁጠባ መርሃ ግብር መሆኑን አስታዉሰዋል፡፡

ለአንድ ሀገርና ብልጽግና የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ መንክር እነዚህ የሃገር ባለውለታዎች የቁጠባ ባህላቸውን ከማዳበርም በተጨማሪ ተሸላሚ የሚሆኑበትን አሰራር ቡና ባንክ መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

ቡና ባንክ አ.ማ ከተመሰረተ 12 ዓመታትን ያስቀጠረ ሲሆን ከ311 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት ከባንኩ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
የአግሮፉድና የፕላስቲክ ህትመት ማሸጊያ ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው፡፡

የንግድ ትርኢቱ በጀርመኑ ታዋቂ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ ፌር ትሬድ እና በኢትዮጵያው ፕራና ኢቨንትስ ትብብር ለ4ኛ ጊዜ እንደሚካሄድም ታውቋል።

ዝግጅቱ ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን፣ በአግሮ ፉድና እና እሴት ሰንሰለቱ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

ከተለያዩ አገራት የተዉጣጡ ዓለምአቀፋ የዘርፉ መሪዎች ለኢትዮጵያ የገበያ ፍላጎት የተዘጋጁ የግብርና፣የምግብ እና የመጠጥ ማቀናባበሪያ ቴክኖሎጂዎች እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈ የፕላስቲክ ህትመት እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂ እና መፍትሄዎችን በመያዝ፣ከ2ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች እንደሚያቀርቡም አዘጋጆቹ በሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል።

በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ፣ ከኢትዮጵያ ፣ከፈረንሳይ፣ከጀርመን ፣ከህንድ፣ከጣሊያን ፣ከኩዌት ፣ከናይጄሪያ ፣ከሩሲያ ፣ከደቡብ አፍሪካ ፣ከቱርክ እና ከአሜሪካ የተዉጣጡ ተሳታፊ ድርጅቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠብቃል ።

በአባቱ መረቀ

መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም
የሞያሌን አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ህገወጦችን ከመቀነሱም ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ የኢጋድ የጤና እና የማህበራዊ ልማት ዳይሬክተሯ ፋቲያ አልዋን ተናገሩ፡፡


ዳይሬክተሯ ይህን ያሉት ኢጋድ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሞያሌ ድንበር የጀመሩትን የንግድ ትስስር በሚያጠናክሩበትና በልማት ስራዎች ዙሪያ ከአባል አገራቱ ጋር እየመከረ በሚገኝበት ጉባኤ ላይ ነው።

የኢጋድ የጤና እና የማህበራዊ ልማት ዳይሬክተሯ ፋቲያ አልዋን፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሞያሌ ድንበር የጀመሩት ልማት በአካባቢው የሚገኙ ዜጎችን ህይወትን የሚሻሻል ነው ብለዋል ።
በተለይም በአካባቢውበህገወጥ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ከመቀነሱም ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

የዚህ ስብሰባ ዋነኛ አለማ በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር በተለይም በሞያሌ አካባቢ የሚገኙ ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም አገራት ድንበር አካባቢ የሚገኙ ከ1 ሺህ 6 መቶ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሯ ፋቲያ አልዋን አስታውቀዋል።

በቀጣይ፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በማስተሳሰር ረገድ ኢጋድ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለፁት ፋቲያ፣በተለይም የመተማ ጋለባት አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ኢትዮጵያና ሱዳንን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።
በመድረኩ፣ ከኢትዮጵያና ኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢጋድ፣ ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልል የተወጣጡ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ የሞያሌን አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ስምምነት ባለፈው ሳምንት መፈረማቸው የሚታወስ ነው።

በአባቱ መረቀ

መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡


በኮሮና ቫይረስ የማቾች ቁጥር ኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተነሳባት ቻይና መብለጧን ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኢትዮጵያ በኮቪድ19 የሞቱ ዜጎች ቁጥር ከ5ሺህ የበለጠ ሲሆን በቻይና በቫይረሱ የሞቱ ዜጎች ደግሞ 4ሺህ 636 ብቻ ነው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በሶስቱ ቀናት ብቻ 176 ያህል ዜጎች በቫይረሱ አማካኝነት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ይሕ ቁጥር ወደ ህክምና ጣቢያዎች መጥተው የሞቱትን ብቻ የሚያሳይ ሲሆን የህክምና ጣቢያ ሳይመጡ በቫይረሱ እንደተጠቁ ሳያውቁ በየቦታው በወረርሽኙ የሞቱ ወገኖች አጅጉን ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው፡፡

በትላንትናው እለትም የ43 ዜጎች ህይወት ሲያልፍ 700 ያህል ዜጎች ደግሞ በጽኑ ህሙማን ክፍል ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በሀገር ደረጃ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ተብሏል፡፡
በአሁኑ ሰአት የመተንፈሻ መሳሪያዎች እጥረት እያጋጠመ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማእከል ሲዲሲ ባስጠናው ጥናት መሰረት ያልተከተቡ ሰዎች ከተከተቡት ጋር ሲነጻጸር በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ከ4.5 እጥፍ በላይ ነው ይላል፡፡ ይህ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በዋነኝነት ክትባት መውሰድ አማራጭ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

እንደዚሁም ሆስፒታል የመግባት አድላቸው ከ10 እጥፍ በላይ እንደሆነ እና ታመው የመሞት እድላቸው ደግሞ 11 እጥፍ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም በማእከላዊ ሰሜን ሪጅን አካባቢዎች የ4G L.T.E.. ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት አስጀመረ

ኩባያንያው የሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎትን በላቀ ፍጥነት መጠቀም የሚያስችለውን የ4 ጂ አል.ቲ.ኢ.አድቫንስድ፣ በማእከላዊ ሰሜን ሪጅን በሆኑት በፍቼ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሱሉልታ፣ ገርበ ጉራቻ፣ ሰንዳፋ፣ በርኸ እና አካባቢዎች ተጠቃሚ የሚያደርገውን መርሃ ግብር በዛሬው እለት በደብረ ብርሃን ከተማ አስጀምረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሪት ፍሬህወት ታምሩ፣ አገልግሎቱ የላቀ ፍጥነትና ባንድዊድዝ እንዲሁም አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ይህም ደንበኞች አገልግሎታቸውን ዲጂታላዊ ለማድረግና ምርታማነታቸውን ለመጨመር ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

እስካሁን ድረስ ቴሌኮሙ ባደረጋቸው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ. አገልግሎት ማስፋፊያ ስራዎች የዛሬውን ጨምሮ በአዲስ አበባና በ15 ሪጅኖች የሚገኙ 86 ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።

በጅብሪል ሙሃመድ
መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም
ራሚስ ባንክ ከ700ሚሊየን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

በምስረታ ላይ የሚገኘው ራሚስ ባንክ እስካሁን ባለው ሂደት 724 ሚሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል ሰብስቢያለሁ ብሏል፡፡

ባንኩ የእስላማዊ ፋይናንስ አገልግሎት ዘመናዊ የፋይናንስ አስተሳሰብ ከቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር ውጤታማ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱል ጀዋት መሀመድ እንደተናገሩት በምስረታ ሂደት 2 አመታትን ያስቆጠረው ራሚስ ባንክ ብሄራዊ ባንክ ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ ባገናዘበ መልኩ ወደ ምስረታ ሂደት መሸጋገሩን አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ሚያዝያ ብሄራዊ ባንክ ባስተላለፈው መመሪያ በምስረታ ላይ የሚገኙ ባንኮች 500 ሚሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዘው እና የመስራች ጉባኤ አድርገው እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ለፈቃድ እንዲያመለክቱ ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ይታወሳል።

ራሚስ ባንክ በሚቀጥለው መስከረም 22 የምስረታ ጉባኤውን እንደሚያደርም አስታውቋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ውስጥ ከ6ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች አክሲዮን መግዛታቸውን ነው አቶ አብዱል ጀዋት የተናገሩት፡፡

ባንኩ ወደ ስራ ሲገባ ሰፊ የኢንቨስትመንት ክፍተት በሚታይበት የግብርናው ዘረፍ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም
የመስቀል በአልን ምክንያት በማድረግ ከታሪፍ በላይ በጠየቁ 50 አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከመስቀል በአል አከባበር ጋር በተያያዘ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰድኩ እገኛለሁ ሲል አስታውቋል፡፡

በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመለስተኛ እና አነስተኛ መናሃሪያ የአዲስ ክፍለ ከተማ መናሃሪያ የቡድን መሪ አቶ ውብሸት ደመላሽ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት የመስቀልን በዓል ለማክበር ከመዲናዋ ውደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚንቀሳቀሱ ተጓዞች ላይ የሚደረግን የታሪፍ ጭማሪ ለመቆጣጠር አዲስ አሰራር ዘርገተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ከቁጥጥር ስራው ጋር በተያያዘ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ከታሪፍ በላይ በጠየቁ 50 ያህል አሽከርካሪዎች ላይ የቅጣት እርምጃ እንደተወሰደባቸው አቶ ውብሸት ነግረውናል፡፡

እንደ ዚሁም በሁለት ቀናት ውስጥ 110 ብር የነበረው የወልቄጤ መደበኛ የታሪፍ ዋጋ ላይ 300 በጠየቁ 5 ያህል አሽከርካሪዎች እስከ 2ሺህ ብር የሚደረስ ቅጣት ተላልፎባቸዋል ብለውናል፡፡

በበአሉ የተሸከርካሪ እጥረት እንዳይከሰት ባለስልጣን መስራቤቱ እንደ ርቀታቸው እና እንደ አካባቢው ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ከ35 ከመቶ እስከ 50 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ተደርጎ የህብረተሰቡን እንግልት ለማስቀረት እየሰሩ እንደሆነም አቶ ውብሸት ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በየቀኑ እስከ 1ሺህ ተሽከርካሪዎች ለስምሪት እንደሚወጡም ነው ሀላፊው ለጣቢያችን የተናገሩት፡፡

ከህጻናት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው አለምግባባት በተመለከተም እድሜያቸው 7 አመት የሆኑ ህጻናት በእናቶቻቸው ወይም በሞግዚቶቻቸው አማካኝነት ሳይከፍሉ ሊጓዙ እንደሚችሉ ተናግረው እድሜያቸው 12 የሆናቸው ደግሞ በግማሽ ከፍለው መጓዝ ይችላሉ ሲሉ አቶ ውብሸት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም
የኦሮሚያ ክልል እያካሄደ ባለው የአዲስ መንግስት ምስርታ አቶ ሽመልስ አብዲሳን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል ።
የኮቪድ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የአደባባይ  ክብረ በአላትን በከፍተኛ ጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባ ተጠቆመ

የአደባባይ ክብረ በአላትን ስናከብር  የኮቪድ-19 መከላከያ ጥንቃቄዎችን መፈፀም ስለሚገባ በአዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የጥንቃቄ መልእክቶች እየተላለፉ እንደሆነ ታውቋል።

መልእክቱን እያስተላለፉ የሚገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ፣ አፍሪ ኢቬንትስ እና ዩኤስ አይ ዲ ናቸው።

ህብረተሰቡ ማስክ ማድረግ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም እና  አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ከማክበር በተጨማሪ የኮቪድ ክተባትን በመከተብ ራሱን እና ቤተሰቡን ከቫይረሱ መከላከል እንደሚገባው ዶ/ር ሜሎን በቀለ የአፍሪ ኢቨንትስ አስተባባሪ ተናግረዋል።

እንደ ዶ/ር ሜሎን ማብራርያ ከሆነ አሁን ላይ በብዛት በኮቪድ እየሞቱ ያሉ ዜጎች ክትባቱን ያልወሰዱ ዜጎች በመሆናቸው በክትባቱ ዙሪያ የሚናፈሱ ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን ቸል ብሎ ክትባቱን መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም በመስቀል አደባባይ የኮቪድ-19 የክትባት መርሃ ግብር እየተሰጠ እንደሆነ ተነግሯል።

በቀጣይም በኢሬቻ ክብረ በአል ተመሳሳይ ስራ እንደሚሰራ ከአዘጋጆቹ ሰምተናል።

መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ በመሆን ተመርጠዋል።

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የከተማው ምክር ቤት ምስረታ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር በ 138 ድምጽ በማግኘት ተመርጠዋል።

ወ/ሮ ቡዜና ከዚህ ቀደም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በሃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ሰኣት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

በመቅደላዊት ደረጄ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
ወ/ሮ ፋይዛ መሃመድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ተሾሙ

አዲስ አበባ ከተማ አዲስ ምክር ቤት ምስረታ ስነ-ስርአት እየተካሄደ ነው።

በማዘጋጃ ቤት ቴአትር እና ባህል አዳራሽ እየተካሄደ ባለው አዲስ ምክር ቤት ምስረታ ስነ-ስርአት በቀጣይ አምስት ዓመታት ምክር ቤቱን በአፈጉባኤነት እና በምክትል አፈጉባኤ እንዲሁም የከንቲባ ሹመት እና የካቢኔ አባላት ሹመት በቅደም ተከተል ለማካሄድ ባቀደው መሰረት በእጩነት አቅርቧቸው የነበሩት ወ/ሮ ፋይዛ ሞሃመድ 138 ድጋፍ አግኝተው ተሹመዋል፡፡

ወ/ሮ ፈይዛ መሐመድ ዑመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ነበሩ፡፡

በቀጣይም ምክር ቤቱን በአፈ ጉባኤነት ለአምስት ዓመታት እንዲያገለግሉ ተሹመዋል፡፡

በረድኤት ገበየሁ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትም ወይዘሮ አዳነች አቤቤን የከተማው ከንቲባ በማድረግ መርጧል፡፡

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከነሀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን አሁንም በድጋሚ ከተማዋን በከንቲባነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች ከተማዋን ከ 12 ወራት በላይ በምክትል ከንቲባ ማእረግ እየመሩ የሚገኙ ሲሆን ፣ ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው ጉባዔም ከንቲባ አድርጎ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በከንቲባነት ሾሟል፡፡

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዳማ ከተማ ከንቲባ፤ የገቢዎች ሚኒስትር፤ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በጅብሪል ሙሃመድ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም
በከተማችን የምናካሄዳቸው ሁሉም የልማት ስራዎች በሂደታቸውም ሆነ በውጤታቸው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ለማድረግ በትኩረት እንሰራን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

በዛሬው እለት እየተካሄደ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምስረታ ስነ ስርዓት ላይ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ በከተማዋ የምንሰራቸው ሁሉም ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች በከታማችን ነዋሪዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥን እንዲያመጡ እንሰራን ብለዋል፡፡

በከተማችን ላይ ምርትና አገልግሎት አቅርቦቶችን ለማሻሻል ሲባል በጥናት ለመለየት ይሰራል ያሉት ወ/ሮ አዳነች የከተማዋን የመልማት አቅም ለማጎልበት በትብብር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች ይህንን የከተማዋን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጣን ደግሞ የመንግስት የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ የማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡

በተለይም ደግሞ የከተማዋ የመሰረተ ልማቶች ተደራሽነት ላይ በትኩረት የሚሰሩባቸው ዘርፎች መኖራቸውንም እንዲሁ ጠቁመዋል፡፡

ከነዚህም መካከል፤ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል፤ የውሃ፤ የመብራትና የኮምንዩኬሽን እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፎችን ለማሳለጥ በልዩ ትኩረት የምንሰራባቸው ዘርፎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች አክለውም ደሃ ተኮር መርሃ ግብሮቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ወጣቶችና ሴቶች ላይ የስራ እድል እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ የኢንዱስትሪን ልማት እድገትና የሰራ ፈጠራ ዘርፎችን ለመደገፍ ሲባል አንዱ የትኩረት አቅጣጫችን ይሆናል ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወሮ አዳነች የሌብነትና የዝርፊያ ስራዎችን ለመከላከል ሲባልም አዳዲስ የስነ ምግባር እንዲሁም ተጠያቂ ለመሆን የሚያስችሉ ደንቦችን እንዲወጡ እናደርጋንም ብለዋል፡፡

በጅብሪል ሙሃመድ
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም