Ethio Fm 107.8
20.4K subscribers
7.52K photos
16 videos
4 files
2.3K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
የጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት ሶስት ወራት ከ27 ቢሊዮን በላይ ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት 27 ነጥብ 54 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 26 ነጥብ 62 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 27 ነጥብ 58 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጿል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም
ጡረተኛው ዲፕሎማት የጆርዳን ንጉስ አብደላህ በአዲሱ መንግስት ስም ቃለ መሀላ ፈጸሙ።

ጡረታ ወጥቶ በነበረው አርበኛ ዲፕሎማት በሽር አል ክሀስዋኔህ በሚመራው አዲስ መንግስት ስም የጆርዳን ንጉስ አብደላህ መሀላ መፈጸማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ይሄ አዲስ መንግስት በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚደገፈውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በፍጥነት እንዲተገብር ይጠበቃል፡፡ ለአስርታት ተኮማትሮ የኖረው የጆርዳን ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቀውስ ውስጥ ገብቷልና፡፡

የ 51 አመቱና ብሪታንያ የተማሩት ክሀስዋኔህ ፤ ኦማር አል ራዛዝን ተክተው ዕሮብ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በከፋ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ሀገሪቱ ባለችበት እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ተብሎ የህዝቡ ነፃነት በተገደበበትና ህዝቡ በመንግስት ደስተኛ ባልሆነበት ጊዜ ነው የመጡት፡፡

በሔኖክ አስራት
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
የአሜሪካዉ ግዙፋ የህክምና መሳሪያዎች አምራች ኩባንያ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በኮቪድ 19 ላይ ሲያደርገዉ የቆየዉን ሙከራ እንዲያቀም ታዘዘ፡፡

ድርጅቱ ለቫይረሱ ይሆናል ያለዉን ክትባት አዘጋጅቶ ካሳለፍነዉ መስከረም ወር ጀምሮ በፍቃደኝነት ባሰባሰባቸዉ ወደ 60 ሽህ የሚሆኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች ላይ የክትባቱ ዉጤታማነት ላይ ሙከራ ሲያደርግ ነበር፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የተዉጣጡ ሲሆኑ ክትባቱ ህመም እንደፈጠረባቸዉ መናገራቸዉን ተከትሎ ነዉ ለጊዜዉ ሙከራዉን እንዲቆም የተወሰነዉ፡፡

ድርጅቱ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ላይ የፈጠረዉን የህመም ስሜት ለይቻለሁ፤ቀጣይ በሚደረጉ ሙከራዎች አይከሰቱም ቢልም የሃገሪቱ መንግስት ግን ሙከራዉን እንዲያቆም ትዕዛዝ ማስተላለፉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ክትባቶች ጊዜያዊ እገዳ ሲጣልባቸዉ የመጀመሪያዉ አለመሆኑን የገለጸዉ ዘገባዉ ቀደም ሲልም በዩናይትድ ኪንግደም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ አስትራ ዜኔካ ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት እገዳ ተጥሎበት እንደነበር አስታዉሷል፡፡

ሁለቱም ድርጅቶች በዋናነት ለጉንፋን መንስኤ የሆነዉን ቫይረስ በማሻሻል የሰዉ ልጅ የኮቪድ ቫይረስን ለመከላከል እንዲችል አቅም መፍጠር ላይ ያተኩራል፡፡

ባሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 180 የሚሆኑ የኮኒድ 19 መከላከያ ክትባቶች ላይ ሙከራዎች እየተደረጉ ሲሆን ሙከራዉን ግን በአስተማማኝ ሁኔታ ያለፈ አንድም ክትባት አለመኖሩን ዘገባዉ ጠቁሟል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ልደቱ አያሌው ክስ መዝገብ ምስክሮችን ፖሊስ በቀጠሮ ቀን ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጠ።

ዛሬ አቃቤ ህግ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች ቃል ለመስማት በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው ውሳኔ ሳያገኙ ተመልሰዋል፡፡

የአቶ ልደቱ ጠበቃ የሆኑት አቶ አብዱል ጀባር ሁሴን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ፍርድ ቤቱ ለምን አቃቤ ህግ ምስክሮቹን እንዳላቀረበ ሲጠይቅ ሁለቴ ቀርበው ስለተመለሱብኝ ዛሬ አልመጡም ሲል መልሷል ብለውናል ፡፡

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ልደቱ የዋስትና መብታቸው ሳይከበር ቀርቷል፤ ይህም በእጅጉ አሳዛኝ ነው ብለዋል ጠበቃው ፡፡

እናም ፖሊስ እና አቃቤ ህግ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያከብሩ ዘንድ ፍርድ ቤቱ በአጽንኦት እና ከማስጠንቀቂያ ጋር ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀናል ነው ያሉት አቶ አብዱል ጀባር ፡፡

ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹ መጥሪያ እንዲሰጣቸው እና እንዲቀርቡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢሾፍቱ ወረዳ ፖሊስ መምሪያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማዘዙን አስረድተዋል፡፡

የምስክሮቹን ቃል ለመስማትም ለጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል ፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
ከቻይና ጋር ከፍተኛ ዉዝግብ ዉስጥ የገባችዉ አሜሪካ ለታይዋን 3 ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ ማረጋገጫ ሰጠች፡፡

ቀደም ሲል አሜሪካ ለታይዋን የመሬትና የአየር ላይ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ጨምሮ፣ 7 ዘመናዊ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እንደምትሸጥ ገልጻ የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ ዉስጥ 3ቱን ለታይዋን ለመሸጥ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡

አሁን ለሽያጭ ዝግጁ የሆኑት አንድ ክሩዝ ሚሳኤል፣ኤፍ 16 የጦር ጀትና እስከ 190 ማይል ድረስ ጠላትን ማጥቃት የሚችል ሮኬት ናቸዉ፡፡

በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ የትራምፕ አስተዳደር የያዘዉን ለታይዋን መሳሪያ የመሸጥ እቅድ እንዲሰርዝ ጠይቋል፡፡

ቻይና በሉዓላዊነቴ ላይ የተቃጣ ጣልቃ ገብነት ነዉ በሚል ይህን የአሜሪካን ድርጊት ስትኮንን ብትቆይም ከአሜሪካ በኩል ግን ሰሚ አላገኘችም፡፡

ታይዋን አሁን ለሽያጭ ዝግጁ ናቸዉ ለተባሉ የጦር መሳሪያዎች ምን ያህል እንደምትከፍል ባይገለጽም ቀደም ሲል ተዋጊ ጀቶችን ለመግዛት ከአሜሪካ ጋር የ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ማድረጓ ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ ዉሳኔ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ዉጥረት ዉስጥ እንዳይከተም ስጋት መፍጠሩን ሮይተርስ ዘግቧል።

በዳንኤል መላኩ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
የአዉሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል 9 ሚሊዮን ዩሮ ሰጠ፡፡

ድጋፋ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተዉን የበርሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል ለምታደርገዉ ጥረት የሚዉል ነዉ ተብሏል፡፡

ይህን ያሉት የህብረቱ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦሬልና የህብረቱ የአደጋዎች መከላከል ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናሬክ በሶማሊያ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ነዉ፡፡

ሌናሬክ አክለዉም የተደረገዉ ድጋፍ ህብረቱ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያለዉን ጠንካራ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ በቀጣይም በጎርፍ፣በድርቅና በተለያዩ አደጋዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ድጋፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታዉቋል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በ887 ሺህ ዶላር ወጪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና የዜጎች ተሳትፎ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን ሁለቱ ተቋማት ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላኩት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ በጤና መረጃ ላይ የተመሰረተና ለዜጎች ኮቬድ-19 የተመለከተ ምላሽ የሚሰጥ፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና መረጃ ድረ-ገጽ ለማልማትና የጥሪ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል ነው ተብሏል።

ይህ ድረ-ገጽ አንደ አንድ ወጥና የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት የሚያገለግል ሲሆን መንግስት በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን የመከላከሉ ጥረት አካል የሆኑ መረጃዎች የሚወጡበት ነው።

በተጨማሪም የመንግስት የኮቪድ 19 ምላሽ መረጃዎችን ዜጎች እንዲያገኙ የሚያሳልጥም ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ከዜጎች ለሚመጡ ጥሪዎች ወዲያውኑ መረጃ መስጠት የሚያስችልና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አጫጭር መልእክቶችን በጽሁፍ፣ በድምጽና በተመረጡ የመረጃ አድራሻዎች መረጃ የሚያደርስ ቴክኖሎጂ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አህመዲን መሐመድ ፕሮጀክቱ ዜጎች የተቀናጀ ሥርዓት ባለው ድረ-ገጽ አማካኝነት መንግስት የኮቪድ -19 ወረርሽኝን በተመለከተ መንግስት እየወሰዳቸው ስላሉ እርምጃዎች መረጃው እንዲኖራቸው የሚያደርግ ብለዋል፡፡

ዶክተር አህመዲን አክለውም ኅብረተሰቡ ስለ ኮሮና ቫይረስ ያላውን ግንዛቤ ያሳድጋል ብለዋል።

ይህንን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና የዜጎች ተሳትፎ ፕሮጀክት ለማበልጸግ 887 ሺህ ዶላር የፈጀ ሲሆን ወጪው በማስተርካርድ ፋውንዴሽን መሸፈኑ ተገልጿል።

በዳንኤል መላኩ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
ሮናልዶ በኮቪድ 19 ተያዘ።

የፖርቱጋል እና ጁቬንቱስ አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ተረጋገጠ፡፡

ይህንን ያለው የፖርቱጋል እግር ኳስ ፌደሬሽን ነው፡፡

የ35 ዓመቱ ተጫዋች ምንም ዓይነት ምልክት ያላሳየ ሲሆን ራሱን አግልሎ እንዲቆይ ወደ ከብሄራዊ ቡድኑ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡

ፖርቱጋል ነገ ምሽት በኔሽንስ ሊግ ጨዋታ ስዊዲንን ትገጥማለች፡፡

የፈርናንዶ ሳንቶስ የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን ቀሪዎቹ አባላት በሙሉ ከኮቪድ ነጻ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ባሳለፍነው እሁድ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር 0ለ0 የተለያየው የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን ከዓለም ሸምፒዮኖቹ ጋር በነጥብ እኩል ቢሆኑም ምድባቸውን በበላይነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡

በአቤል ጀቤሳ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮችን መደገፍ የሚያስችል የ300 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት መቅረጹን አስታወቀ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ በአፍሪቃ ሃገራት ላይ ተጽዕኖው ጎልቶ ታይቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (IFAD) እጅግ ተጋላጭ የሆኑ አርሶ አደሮችን ለመርዳት እና ለማጠናከር በ305.7 ሚሊየን ዶላር አዲስ ፕሮግራም ይፋ ማደረጉን አፍሪካ ቢዝነስ ሪቪው በድረገጹ አስፍሯል፡፡

በኢትዮጲያ ልማት ባንክ የሚሰጠው አገልግሎት አርሶ አደሮች የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ያመቻቻል፡፡

ድጋፉ አርሶ አደሮች ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እና ገቢ የሚያገኙባቸውን አማራጮች እንዲያሰፉ ያግዛል፡፡

የተሸለ አመጋገብ እንዲኖራቸው እና በአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ውስጥ በወደቁ ገጠራማ አካባቢዎች ችግሮችን ተቋቁመው መኖር እዲችሉም ያግዛል፡፡

በፕሮጀክቱ የምረቃ ስነስርዓት የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች ፣የመንግስት ባለስልጣናት ፣የተባበሩት መንግስታት እና የሌሎች ተቋማት የስራ ባልደረቦች ፣የኢትዮጲያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ደስታ ፣የኢትዮጲያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃንስ አያሌው እና የ IFAD የኢትዮጲያ ዳይሬክተር ኡላክ ደሚራግ ታድመዋል፡፡

80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጲያ ህዝብ የሚተዳደርበት የግብርና ዘርፍ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰት ተደጋጋሚ ድርቅ መከራ ማየቱን ቀጥሏል፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት የእህል ምርት በመቀነሱ እና የቀንድ ከብቶች በማለቃቸው ወደ 8.5 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አስፈልጎት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
የኣዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማሀበራዊ ጉይይ ቢሮ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ 3 ሺህ 500 የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንደሚያነሳ አስታወቀ።

የቢሮ ሐላፊ አቶ ተፈራ ሞላ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት እስካሁን ከ9 ክፍለ ከተሞች 1 ሺህ 148 የጎዳና ተዳዳዎች ተነስተው ቃሊቲ ማቆያ እና ማገገሚያ ማእከል እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

የተሱትን የጎዳና ተዳዳሪዎች ተገቢውን የስነልቦና ትምህርት ስልጠና በመስጠት በከተማው ዉስጥ ባሉ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ዉስጥ በማስገባት እንደየፍላጎታቸው ሰልጥነው ወደ እንደሚገቡም ተገልጿል።

ባለፉት አመታት ከጎዳና ላይ ከሰበሰባቸው በኋላ በተለያየ ችግሮቺ ምክንያት መልሰው የመውጣት ችግሮች ያጋጠመው መሆኑን የነገሩን አቶ ተፈራ ይሄን ችግር ለመቅረፍ በቅድሚያ ግንዘቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን እና በሚፈልጉበት የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡

ሃላፊው አክለውም ባብዛኛው ከጎዳና ላይ እየተነሱ ያሉ ሰዎች ዲግሪ እና ከዛ በላይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው እንደሚገኙበትም ነግረዉናል፡፡

በመጨረሻም ይህ ፕሮጅክት ለማከናወን የሚውል ከአለም ባንክ 270 ሚሊየን ብር ድጋፍ መገኘቱንም ተናግረዋል።

በሁሉሀገር አተሮ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ምርጫውን እንዳያሸንፉ እየጸለዩ መሆኑን የፍልስጤም ጠቅላይ ሚንስትር ተናገሩ።

የፍልስጤማዊን ጠቅላይ ሚኒትር ሙሀመድ ሺታያህ ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ የህዳሩን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ መጪው ጊዜ ለአሜሪካም ሆነ ለአለም ከባድ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ከአውሮፖ ህብረት ህግ አውጪዎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ነው ይህንን አስተያየት የሰጡት፡፡

ባለፉት አራት አመታት የትራምፕ አስተዳደር ፍልስጤማዊንን በእጅጉ ጎድቷል ብለዋል በንግግራቸው፡፡

ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ሌላ አራት አመት የምንኖር ከሆነ ፈጣሪ ይርዳን …..ፈጣሪ ይርዳችሁ…..እና ፈጣሪ መላው አለምን ይርዳ ብለዋል፡፡

ይህንን አስተያያታቸውንም በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል፡፡

ነገሮች በአሜሪካ ውስጥ የሚለወጥ ከሆነ ይህ በእስራኤልና በፍልስጤም ላይም ይሆናል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የህዳሩን ምርጫ የዲሞክራቱ እጩ ተወዳዳሪ ጆ ባይደን ቢያሸንፉ እንደሚመርጡ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርሱ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ጥሩ መረዳት አለው ያኔ የፍልስጤም-አሜሪካ ግንኙነት ይሻሻላል ብለን እናምናለን ሲሉም አክለዋል፡፡

በያይኔአበና ሻምበል
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
የካራባክ ጦርነት ንጹሃን ዜጎችን ለአስከፊ ህይወት መዳረጉን እንደቀጠለ ነው።

ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የናጎርኖ ካራባክ ግጭት እልባት አላገኘም፡፡

አርሜኒያ እና አዘርባጃን እንደ ጎርጎሮሲያውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1990 በኋላ በአስከፊነቱ ቀዳሚ ወደ ሆነ ከባድ ግጭት አምርተዋል፡፡

የሩሲያ የአደራዳሪነት ሚናም እስካሁን የፈየደው ነገር የለም፡፡

አዘርባጃን አወዛጋቢውን ግዛት የመጠቅለል ውጥኗን ገና እንዳልፈጸመች ትናገራለች፡፡

ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የሚያውቀው አካባቢው በአዘርባጃን ግዛት ውስጥ እንደሚገኝ ነው፡፡

አርመኒያ በበኩሏ ናጎርኖ-ካራባክ የአርሜቢያ አካል ሆኖ ለብዙ ክፍለ ዘመናት መቆየቱን ትናገራለች፡፡

አዘርባጃን ጋንጃ ወደ ተባለው የሰላማዊ ዜጎች መኖሪያ መንደር አርሜኒያ ሚሳዔሎችን ታስወነጭፋለች ብላ ትከስሳለች፡፡

አርሜኒያም ሰላሚዊ ዜጎች ላይ የሮኬት ጥቃት ታደርሳለች ስትል ባኩን ተወነጅላለች፡፡

በመካከል ግን ከሁለቱም ወገን ሰላማዊ ዜጎች የተለመደ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን መግፋት ተስኗቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በርካቶች ለሞት እና ስቃይም ተዳርገዋል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው፡፡

በመቅደላዊት ደረጀ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
ጥራት የጎደላቸው ምርቶችን ያስተላለፉ አራት የብዙሀን መገናኛ 23 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት ተላለፈባቸው።

በብሮድካስት ባለስልጣን የህግና ማስታወቂያ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ፋንታዬ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በኢትዮጵያ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን 4 መገናኛ ብዙሀን ላይ የገንዘብ ቅጣት እንደተላለፈባቸው ተናግረዋል፡፡

ቅጣቱ የተላለፈባቸው ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት ማስታወቂያ በመልቀቃቸው ሲሆን ሀላፊነታቸውን ተወጥተው ባለመገኘታቸው በሚል በማስታወቂያ አዋጁ መሰረት ከ10 እስከ 23 ሚሊየን ብር እንዲቀጡ ተደርጓል፡፡

በተመሳሳይም ማስታወቂያውን በግድየለሽነት በመስራት ለመገናኛ ብዙሀኑ ሰጥተዋል የተባሉት የማስታወቂያ ድርጅቶችም ላይ ቅጣት እንደተፈጸመባቸው ለማወቅ ችለናል፡፡

ይሁንን ዳይሬክተሩ ቅጣቱ የተላለፈባቸውን መገናኛ ብዙሃን ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

የብሮድካሰት ባለስልጣን የንግድ ወድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመሆን በማስታወቂያዎች በኩል ወደ ህብረተሰቡ የተሳሳተ መረጃ እንዳይሰራጭ ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

የተቀመጠውንም መመሪያ ተላልፎ የተገኘ የመገናኛ ብዙሀን አስመጪ ድርጅቶችም ይሁን የማስታወቂያ ድርጅቶች ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ እስከ ፍቃድ መሰረዝ አይነት እርምጃዎች ይወሰዳሉ ሲሉ አቶ ዮናስ ነግረውናል፡፡

የማስታወቂያ አዋጅ በሀገራችን ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመቅደላዊት ደረጃ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሴቶች ድምጽ መጽሔት በየወሩ እየታተመ ለንባብ መብቃት ጀመረ፡፡

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሴቶች ድምጽ መጽሔት ለንባብ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

መጽሔቱ በዋነኝነት የሴቶች ልሳን ሆኖ የምታገለግል ሲሆን ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የሚገጥማቸውን ችግሮች፣ በየዘርፉ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

እንዲሁም በተለያየ መስክ ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን በአርአያነት የሚያቀርቡበት እንደሆነም ተገልጻል፡፡

መጽሔቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እየተዘጋጀ የሚቀርብ ሲሆን ይህ የሆነበት ዋና ዓላማም ተቋሙ በዘርፉ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በቅርበት እየሰሩ የሚገኙ የልማት አጋራት የሚያደርጉትን እገዛና ድጋፍ ወደፊትም በበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡

መጽሄቱ በመጀመርያ እትሙ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሰላም እሴት ግንባታ፣ እንዲሁም አለምን እያስጨነቀ ከሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች ይዞ ብቅ ብሏል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው 845 ማሽኖች ማስወገዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ህንጻና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ መወገድ የነበረባቸው ነገር ግን ሳይወገዱ ለረጅም ዓመታት ተቀምጠው የተገኙ 845 ያገለገሉ ማሽኖች እና ኤሌክትሮኒክሶችን ማስወገዱ ነው ያስታወቀው፡፡

እነዚህ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ማሽኖች መወገድ የነበረባቸው በከተማ አስተዳደሩ ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በመንግስት ህንጻና ንብረት አስተዳደር በኩል እነደተወገዱ ነው የተገለጸው፡፡

ባለስልጣኑ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው ከዚህ በተጨማሪም በክፍለ ከተሞች ደረጃ በትርፍነት የተያዙ 84 ሞተር ሳይክሎችን ለፋናንስ ቢሮ አስተላልፏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከሦስት ክፍለ ከተሞች ባለቤት የሌላቸው 12 ሞተር ሳይክሎች አገልግሎት የማይሰጡ ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችም ለፋይናንስ ቢሮ ማስተላለፉን ገልጿል።

በየውልሰው ገዝሙ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
የአለም ባንክ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት የሚዉል 12 ቢሊዮን አሜሪካን ዶላር በጀት አጸደቀ፡፡

የአለም ባንክ በዛሬው እለት በማደግ ላይ ላሉ አንድ ቢሊዮን ለሚሆኑኑ የተለያዩ ሀገታት ዜጎች፤ በተለይ ለኮሮናቫይረስ ክትባት የሚውል 12 በሊዮን ዶላር በጀት መድቧል፡፡ ባንኩ እስካሁን ድረስ ለ111 ሀገራት ገንዘቡ ደርሷል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የአለም ባንክ ፕሩዘዳንት የሆኑት ዴቪድ ማለፓስ እንደተናገት አሁን በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ፍተሃዊ የሆነ የኮሮና ቫይረስ የክተትባት ስርጭት እና አቅርቦት እንዲኖረቸው እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ አያይዘውም በተለይም በኢኮኖሚ በማደግ ለይ ያሉ ሀገራት ትልቅ ትኩረት እንደሚሻቸው በመግለፅ፤ ድህንነቱ የተጠበቀና ወጤታማ የሆነ ክትባት እንዲመረት በሎም ወቅቱን የጠበቀ ስርዐጭትም በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ዋና የአለም ባንክ አበዳሪ የግል ተቋም ሲሆን፤ በ 4 ቢሊዮን ብር በጀት የኮሮና ቫይረስ በሽታ መከላከያ፤ መቆጣጠሪያ እና ክትባትን ለማምረት ኢንቨስት እያደረገ ይገኛል፡፡

ተቋሙ እንገለጸው በዚህ ሰአት በአለም ዙሪያ ለ 1 ሚሊዮን ሰዎች ሞት፤ ከ 38 ሚሊዮን በላይ ለሞሆኑ በበሽታ ለለከፈው እና ሚሊዮኖችን ስራ አልባ በማድረግ ለድህነተ ለዳረጋቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤
ክትባት ማምረት እጅግ ወሳኝ ነው ብሏል፡፡

በጅብሪል ሙሀመድ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
ሳውዲ አረቢያ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መቀመጫ አጣች

ሳውዲ አረቢያ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መቀመጫ ስታጣ ቻይና እና ሩሲያ ብዙም ተቃውሞ አልገጠማቸውም ተብሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ባካሄደው ሚስጥራዊ ድምጽ 15 አገራት 47 አባላት ላሉት ምክር ቤት መመረጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በእስያ-ፓስፊክ ምድብ ውስጥ አራት መቀመጫዎች ብቻ የተገኙ ሲሆን ሳውዲ አረቢያ በቻይና ፣ በፓኪስታን ፣ በኔፓል እና በኡዝቤኪስታን ተሸንፋለች፡፡

ሩሲያ እና ኩባ እንዲሁ ያለምንም ተፎካካሪ ከምድባቸው በምክር ቤቱ መቀመጫ ማግኘታቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት ከ412 ሚሊዮን በላይ ብር ተመዝብሮ የነበረ ገንዘብ ማስመለሱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አስታወቀ።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ ባለፉት ሶስት ወራት በተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ላይ ናቸው።

አቃቢ ህጉ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የህግ ማስከበር እና የወንጀሎችን ህግ ማስከበር በ3 ወራት ውስጥ 12 ሺህ 37 ክሶች ላይ አቃቢ ህግ ውሳኔ ሰጥቷል።

የኢኮኖሚ ወንጀሎችን በተመለከተ በተለያዩ ምክንያቶች ተመዝብረው ከነበሩ የህዝብ ሀብቶች ከ412 ሚሊየን በላይ የሚገመት ብር ማስመለስ ተችሏል ብለዋል።

የህግ ማዐቀፍን በተመለከተም የንግድ ህግ ፣ የወንጀል ህግ ስርዓት እና የማስረጃ ህግ እና የግልግል ዳኝነት ህግ ዝግጅትን በተመለከተ ጠንካራ ስራ መስራቱን ጠቅላይ አቃቡ ህጉ ተናግረዋል።

በዳንኤል መላኩ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
በኪሊ ማንጃሮ ተራራ የተነሳው እሳት ለማጥፋት 500 ያህል የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተሰማሩ፡፡

ከሁለት ቀናት በፊት ታንዛኒያ ውስጥ በሚገኝው የአፍሪካ ረጅሙ ተራራ ኪሊ ማንጃሮ ተራራ የተነሳው የእሳት አደጋ ከፍተኛ ቦታ እየሸፈነ መምጣቱን ነው የተነገረው፡፡

በዚህም የሀገሪቱ መንግስት ከተለያዩ መስራቤት የተውጣጡ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ወደ ተራራው እንዳሰማራ ነው የተገለጸው፡፡

የታንዛኒያ ብሔራዊ ፓርክ እንዳስታወቀው የእሳት አደጋ ሰራተኞቹ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ አስታውቆ እሳቱን በቁጥጥር ስር እያዋሉት ይገኛሉ ብሏል፡፡

የፓርኩ ዳይሬክተር ፓስካል ሺሉቴት ለአልጀዚራ እንደተናገሩት የአደጋው መንስኤ ምን እንደ ሆነ እስካሁን አልታወቀም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኪሊ ማንጃሮ በአፍሪካ ትልቁ ተራራ ሲሆን ከመሬት ጠለል በላይ 19 ሺህ 443 ሜትር ርቀት አለው፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ባሰማራቸው የትራፊክ ስምሪት ባለሙያዎች በሚጠይቁት ጉቦ መማረራቸውን አስተያየታቸውን ለኢትዮ ኤፍ ኤም የሰጡ የታክሲ ሾፌሮች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ታክሲ ስራ ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች ፣መንግስት ያውጣው የቅጣት እርከኑ የመንገድ ትራስፖርት ስምሪት ባለሙያዎች እንደልባቸው እንዲፈነጩብን እድል ሰጥቷቸዋል ብለውናል።

ሹፌሮቹ እንዳሉን ከሆነ ቀላል በሆኑ ጥፋቶች እየተከሰስን ነው፣ በጥቃቅን ጥፋቶች አንድ ሺህ እና ሁለት ሺህ ብር ነው እየተቀጣን ነው ብለዋል።

አዲሱ የስምሪት ስርዓተ ህግ የትራስፖር ስምሪት ባለሙያዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ፣ ትራፊክ መቶ ብር እና ሁለት መቶ ብር እየከሰሰ ለእነሱ በተለየ መንገድ እንዲቀጡ ህጉ መፍቀዱ ኞፌሮች ከስምሪት ባለሙያዎች ጋር እንዲደራደሩ ያስገድዳል ይህ መሆኑ ደግሞ ለስምሪት ባለሙያዎች እንዲያስፈራሩን እድል የሚሰጥ እና ለጉቦ ይዳርጋል ብለዋል።

የመንገድ ትራስፖርት ክስ ከአቅማችን በላይ ነው ፣አንድ ሺህ ብር ሁለት ሺህ ብር ተከሰን ከፍሉ ከምንባል ሙሉ ቀን ለምነን 300 ብር ጉቦ ብንከፍል ይሻላል ፣ ህጉ ለብልሹ አሰራር የሚገፋፋ ነው፣ እነሱም ህጉን ተገን አድርገው እኛን በሆነው ባልሆነው ያስፈራሩናል ሲሉም ሾፌሮቹ ቅሬታቸውን ነግረውናል፡፡

ሾፌሮቹ አክለውም የትራፊክ ፖሊስ ቅጣት ሚዛናዊ እና ተገቢው ነው የመንገድ ትራስፖርት እንደዛው ተመጣጣኝ ክስ ቢሆን አሸከርካሪም አይጎዳም መንግስትም ተገቢውን ገቢ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበበ ትራስፖርት ቢሮ የስነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ዳይሬክተሩ አቶ አምባላይ ዘራይ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን ተከትሎ የቅጣት ማሻሻያዎች ተደርጓል ነገር ግን ህጉ ለመንገድ ትራስፖርት ስምሪት ባለሙያዎች ያደላነው መባሉ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በእንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ መረዳዳት ያለብን እና የመጀመሪያው ጥያቄ መሆን ያለበት ለምን ያጠፋሉ? የሚለው እና አጥፍተው ህጉ ለእነሱ ያደላ ነው ማለት ምን አይነት አመክንዮ ነው? በሚል ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል አቶ አምባላይ ፡፡

ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት መሰራት ያለበት በጋራ ነው አሽከርካሪውም ሆነ የስምሪት ባለሙያዎች መገዛት ያለባቸው ለህግ እና ስርዓት መሆን አለበት ሲሉም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

በዳንኤል መላኩ፡፡
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
ጋዜጠኛ ተመስገን ታስሮ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገባ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ተናገረ።

ታሪኩ ደሳለኝ እንዳለው

"ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መታሰሩን በር ላይ ያሉት ፖሊሶች ነግረውናል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቢሮ መወሰዱን እንደሰማን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያመራን ሲሆን እዛ በር ላይ ያሉት ፖሊሶች ተመስገንና የመፅሔቱ አዘጋጅ ምስጋን ዝናቤ ተይዘው መግባታቸውን ገልፀውልናል።

ከዚያ ውጪ ምንም ዓይነት መረጃን ያላገኘን ሲሆን ምናልባት ምግብና ልብስ ካመጣን ለማስገባት እንደሚተባበሩን ነግረውናል።" ማለቱን የጀርመን ድምጽ ሬድዮ DW ዘግቧል።

ጋዜጠኛ ተመስገን በፖሊስ ለምን እንደታሰረ እስካሁን የትኛውም መንግስታዊ ተቋም ያለው ነገር የለም።

ይሁንና ጋዜጠኛ ተመስገን ባሳላፍነው ቅዳሜ በፍትህ መጽሄት ከብር ቅያሬው ጋር ተያይዞ ባወጣው የትንታኔ ዘገባ ምክንያት ለእስር ሳይዳረግ እንዳልቀረ በርካቶች ግምታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው።

ጋዜጠኛ ተመስገን ለረጅም አመታት በእስር ቤት ቆይቶ በምህረት ከተፈታ ገና ሁለት አመቱ ነበር።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም