Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
11.4K subscribers
5.09K photos
76 videos
20 files
861 links
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት
Download Telegram
ታሕሣሥ 20፣ 2017 ዓ.ል | ጁማዱል ሳኒ 28፣ 1446 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ለሙስሊም ወጣት አመራሮች እና ሴቶች የስነ-ምግባር ሥልጠና ተሰጠ።
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ |
በወጣት አደረጃጀት ኃላፊነት ላይ ላሉ ወጣቶች፣ ሴቶች እና መምህራን በእስልምና ስነ-ምግባር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጠ።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሴቶችና የወጣቶች ዘርፍ ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የወጣቶች ሊግ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ የአንድ ቀን ሥልጠና ላይ ሁለት የጥናት 'ማኑዋሎች' ቀርበዋል።

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሴቶችና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊዋ ዑስታዛ ፋጡማ ሑሴን ወጣቶችና ሴቶች በማኅበረሰብ ግንባታ ውስጥ ሰፊ ቁጥር ያላቸው እና ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው መኾናቸውን ተናግረዋል።

ኃላፊዋ አክለውም በስነ-ምግር የታነፀ፣ ከሱስ የፀዳ እና ራዕይ ያለው ትውልድ ለማፍራት የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሴቶችና የወጣቶች ዘርፍ ከባለድርሻ አካት ጋር ሀሉ አብሮ ይሠራል ብለዋል።

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሥራ አሰፈጻሚ አባል እና የሴቶችና የወጣቶች ዘርፍ ተጠሪ ሸይኽ አብዱልሐሚድ አሕመድ የወጣትነት ተልዕኮን ብርቱነት አስመልክተው ቁርኣንና ሐዲስን ዋቢ ያደረገ ምክራቸውን ለግሰዋል።

"ወጣትነታችሁን አላህን በማላቅ፣ የራሳችሁንና የወላጆችን ሐቅ በመወጣት፣ በታታሪነት እና በስነ-ምግባር ለመወጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባችኋል ሲሉ አደራ ብለዋል።

በሥልጠናው መርኃግብር ላይ በእንግድነት የተገኙት የአገር አቀፉ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዚደንት ዑስታዝ ሐይደር ከድር አብዱልቃድር ወጣትነትን አስመልክቶ ከእስልምና አኳያ ሰፋ ያለ ትምህርታዊ ንግግር አቅርበዋል።

ሙስሊም ወጣቶች እንደ ማኅበረሰብም ሆነ እንደ አገር ሚናችን የጎላ እንዲሆን ኃላፊነትን ለመሸከም ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል ብለዋል።

ወጣቶች በችግር ጊዜ በግንባር ቀደምነት ተሰልፈን ዋጋ እንደምንከፍለው ሁሉ በመዋቅሮችም ውስጥ በንቃትና በብቃት ኃላፊነት የመሸከም ሚናችንን የማላቅ፣ ተቋማችንን ከፍ የማድረግ እና የለውጥ ሠራዊት መሆን ይገባናል ሲሉ የሥልጠና ተሳታፊውን አነቃቅተዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሙስሊም ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ወጣት ሙሐመድ አሕመድ በበኩሉ ሊጉ ከተመሠረተ ጀምሮ የከተማውን ወጣቶች በማደራጀትና በማንቃት ሰፊ ሥራ መሥራቱን ተናግሯል።

ወጣትነት ለትልቅ ኃላፊነት የሚታጩበት መሠረት በመሆኑ የከተማውን የወጣት ሊግ አመራር አቅም ለማሳደግ ይህን መሰል የስነ-ምግባር ሥልጠና ትልቅ ግብዓት የሚገኝበት መሆኑን ተናግረዋል።

በሥልጠናው ላይ በዶክተር ዱረቲ ቃሲም "የዘመኑ የወጣቶች ፈተና" በሚል ርዕስ ጽሑፍ የቀረበ ሲኾን፣ ወጣቶች ለሱስ ተጋላጭ የሚሆኑበት ገፊ ምክንያት፣ የባህሪ ለውጥ፣ የዕድገት ሂደት፣ ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫና መሠረት ያደረጉ ሳይንሳዊ የግንዛቤ ማብራሪያዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዑስታዝ አሕመድ ሙስጠፋ "ስነ-ምግባር በሁለቱ ዓለም፣ ለማኅበረሰባዊ ግንባታ - እስላማዊ ዕይታ" በሚል ርዕስ ስነ-ምግባር ለማኅበረሰብ ግንባታ ያለውን እሴት ከግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ እና ከሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ አሳታፊ የሆነ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ከሱስ የፀዳ ትውልድ እና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ለወጣቶችና ለሴቶች ትኩረት በማድረግ መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተነግሯል።

••••••••••••
የኢት/እ/ጉ/ጠ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት።
ይከታተሉን | Follow us፡
ፌስቡክ | Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
ቴሌግራም | t.me/eiasc1
ትዊተር | https://x.com/eiasc13
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የሚፈፀሙትን የመብትና የሃይማኖት ጥሰቶችን በሚመለከት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ታሕሣሥ 24፣ 2017 ዓ.ል |  ረጀብ 2፣ 1446 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
7 ሺህ 500 የልብ ህሙማን የቀዶ ሕክምና ለማግኘት ተራ እየጠበቁ ነው።
• የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ የልብ ህክምና ማዕከልን ጎበኙ።
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ |

በአሁኑ ጊዜ 7 ሺህ 500 የልብ ህሙማን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ የልብ ሕክምና ማዕከል የቀዶ ሕክምና ለማግኘት ተራ እየጠበቁ እንደሚገኙ የማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ ተናገሩ።

የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ሰላሃዲን ኸሊፋ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የክብር ዶክተር ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እና የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ማዕከሉን በጎበኙበት ጊዜ ነው።

ታካሚዎች በማዕከሉ ሐኪም ጋር ለመቅረብ ከአንድ እስከ ሁለት ቀናት ብቻ እንደሚጠብቁ የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢው፣ የቀዶ ሕክምና ለማግኘት ግን እስከ 32 ወራት እንደሚጠብቁና ይህን ረጅም ጊዜ ለማሳጠር ማዕከሉ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ የልብ ሕክምና ማዕከል ዓላማው በኢትዮጵያ አስተማማኝ የልብ ሕክምና መስጠት እንደኾነ የተናገሩት አቶ ሰላሃዲን፣ ሕክምናው በአገር ዉስጥ በሰፊው ባለመስፋፋቱ ሳቢያ ታክመዉ መዳን እየቻሉ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው አክለውም፣ ምንም እንኳ ወደውጪ ሀገር ሄደው የሚታከሙ አንዳንድ ሰዎች ቢኖሩም፣ ለከፍተኛ ወጪ እና እንግልት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።

ማዕከሉ በዓመት 110 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ነፃ የቀዶ ሕክምና፣ ከ12 ሺህ በላይ የተከታታይ ሕክምና ምርመራ እና ከ390 በላይ ደረት ሳይከፈት ሕክምና እየሰጠ መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል።

በየዓመቱ ከ1 ሺህ 300 በላይ የልብ ህሙማን ከመላው ኢትዮጵያ ሕክምና ለማግኘት ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡም ሰብሳቢው ተናግረዋል።

ማዕከሉ ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን ከ40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚያወጣ ነፃ ሕምና መስጠቱን የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል።

ክቡር ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በማዕከሉ እየተሰጡ ያሉ የነፃ ሕክምና አገልግሎቶችን ከጎበኙ በኋላ፣ በማዕከሉ በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎችን አመስግነዋል።

በማዕከሉ በነፃ እየተሰጠ ያለውን የልብ ሕክምና አገልግሎት ምክር ቤቱ እንዲጎበኝ በመጋበዙ ክቡር ፕሬዚደንቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የሰው ልጅ የፈጣሪያችን የአሏህ (ሱ.ወ.) ክቡር ፍጡር መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ፕሬዚደንቱ፣ "የአንድን ሰው ህይወት ማዳን፣ ዓለምን ማዳን እንደሆነ" በቁርኣን መወሳቱን ተናግረዋል።

ክቡር ሼይኽ ሐጂ ኢብራሒም ጠቅላይ ምክር ቤቱ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ የልብ ሕክምና ማዕከልን ለመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ምክር ቤቱ የዓሊሞች ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሼይኽ ሙሐመድዘይን ዘኽረዲን በተቋሙ የሚሰጠውን  አገልግሎት ሲያውቁ፣ ከአሥራ ስድስት ዓመት በላይ መኾኑን ተናግረዋል።

በዉጪ አገር መሰል የልብ ሕክምና አገልግሎት በክፍያ እንደሚሰጥ የተናገሩት ሼይኽ ሙሐመድዘይን፣ በማዕከሉ  ለመታከም ተራ የሚጠብቁ ህሙማን ክፍያን ለመሸፈን ተቋሙን መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ የልብ ህክምና ማዕከል በተካሄደው ጉብኝት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚደንት እና የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪው ሼይኽ አብዱልዓዚዝ አብዱልወሊን ጨምሮ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል።

••••••••••••
የኢት/እ/ጉ/ጠ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት።
ይከታተሉን | Follow us፡
ፌስቡክ | Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
ቴሌግራም | t.me/eiasc1
ትዊተር | https://x.com/eiasc13
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት #የዑለማ ጉባኤ ሶላትንና #ሂጃብን አስመልክቶ የተሰጠ ፈተዋ!
ታሕሣሥ 24፣ 2017 ዓ.ል | ረጀብ 3፣ 1446 ዓ.ሒ
بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
የሃይማኖት አባቶች በትግራይ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚፈፀመውን የሃይማኖታዊ መብት ጥሰትና ወከባ እንዲያወግዙ ጥሪ ቀረበ።

• ለቀድሞው የሰላም ሚኒስትር የሽኝት መርኃግብር ተካሂዷል።
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
አዲስ አበባ |

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የክብር ዶክተር ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት በአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሒጃብ ምክንያት እየደረሰባቸው ያለውን የመብት ጥሰት የሃይማኖት አባቶች እንዲያወግዙ ጥሪ አቀረቡ።

ክቡር ፕሬዚደንቱ በትግራይ ክልል በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ በሒጃብ ምክንያት የሚደርሰውን የመብት ጥሰት የሃይማኖት አባቶች በአንድ ቃል እንዲያወግዙ ጥሪ ያቀረቡት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች ለቀድሞው የሰላም ሚኒስትር አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም ባዘጋጁት የምሥጋናና የሽኝት መርኃግብር ላይ ነው።

በጉባዔው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የምሥጋና እና የሽኝት መርኃግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም በትግራይ ክልል ሴት ተማሪዎችና ወላጆቻቸው በእስልምና ሃይማኖት ግዴታ (ዋጂብ) የኾነውን ሒጃብ እንዲያወልቁ የመንግሥት ሥልጣንን ተገን በማድረግ እየተፈፀመ የሚገኘው ሕገወጥ ወከባ በአስቸኳይ እንዲቆም ሁሉም የእምነት አባቶች ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

በሽኝቱ መርኃግብር ላይ የበላይ ጠባቂ አባቶች ሲናገሩ፣ አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በኃላፊነት በመሩበት ወቅት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት እና በክብር ማገልገላቸው ተነግሯል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ኾነው የተሾሙት ብናልፍ አንዱዓለም ሚኒስቴሩን በኃላፊነት በመሩበት ጊዜያት እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎችን በትዕግስትና በፅናት በማለፍ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን እንደሠሩ የእምነት አባቶቹ ተናግረዋል።

አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው በተሾሙበት አሜሪካ ሥራቸው የተሳካ እንዲሆን የእምነት አባቶቹ ፀሎት እንደሚያደርጉላቸው የእምነት አባቶቹ ተናግረዋል።

አምባሳደር ብናልፍ የእምነት አባቶቹ ያደረጉላቸው የሽኝት መርኃግብር ለእርሳቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው፣ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር መሥራት ታላቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።


••••••••••••
የኢት/እ/ጉ/ጠ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት።
ይከታተሉን | Follow us፡
ፌስቡክ | Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council
ቴሌግራም | t.me/eiasc1
ትዊተር | https://x.com/eiasc13