ልዩ ኦፕሬሽን ስልጠና የወሰዱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ተመረቁ
አዳይቱ፣ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም (ኢፌፖሚ):-
ልዩ ኦፕሬሽን ስልጠና የወሰዱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት በአፋር ክልል አዳይቱ ልዩ የኦፕሬሽን ስልጠና ማዕከል በድምቀት ተመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፡ ምረቃው በሀገራችን አዲስ መንግሥት በተመሰረተበት ማግስት የተካሄደ በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፣ ለዚህች ታላቅ ሀገር፣ ሕዝብና ትልቅ ርዕይ ላለው መንግሥት የሚመጥን የፖሊስ ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝና በተለይም የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በብቃት መመከት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከለውጥ ወዲህ የሀገራችንን ፖሊስ ለማዘመን እየሰራ ባላቸው ስራዎች አንዱና ዋናው የኦፕሬሽን አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ የስፔሻላይዜሽን ስልጠናዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና የመሬት አቀማመጥ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ፖሊሳዊ ግዳጅ ለመወጣት የሚያስችል በተግባር የተደገፈ ስልጠና ውስጥ ያለፉ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደረጀ አስፋው ስልጠናው ለሰልጣኞቹ የእውቀት፣ የስነ-ምግባር፣ የተቋማዊ ክብር እና የጽናት አቅም የፈጠረ በመሆኑ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ግዳጅ በከፍተኛ በብቃት ለመወጣት የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
❤2
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 19ኛውን ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በታላቅ ድምቀት አከበረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ):
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 19ኛውን ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በዋና መሥሪያ ቤት በታላቅ ድምቀት አክብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ለሠራዊቱ የሥራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ሠራዊታችን አሁን ላይ በተሠማራባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት፣ በዲሲፕሊን እና በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እየፈጸመ ባለበት ወቅት የምናከብረው ስለሆነ ይህ ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብር መገለጫ ከመሆኑም በላይ ለሠራዊቱ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈያ ዋና መለኪያ መሆኑን ገልፀው ለታላቋ ሀገራችን የሚመጥንና በዲሲፕሊን የታነጸ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በመጨረሻም ሰንደቅ ዓላማችን ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ትልቅ ትርጉም ያለው የሀገራችን መገለጫ በመሆኑ ለሰንደቅ ዓላማችን መስዋዕትነት የመክፈል እውነታ በመለዮ ለባሹ ዘንድ በተግባር እየተረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረው፤ በመላው ሀገራችን ስምሪት ወስደው ግዳጃቸውን በጀግንነት እየተወጡ ያሉ የፖሊስ አመራርና አባላት ይህንኑ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ መመሪያ ሰጥተዋል።
❤3
የሰንደቅ ዓላማ እና የፖሊስ ቁርኝት በምስል
❤56👍26👏21