DW Amharic
50.4K subscribers
3.73K photos
857 videos
69 files
14.4K links
ይህ የዶይቼ ቬለ ይፋዊ የቴሌግራም ገፅ ነው። ትኩስ ዜና፣ በአበይት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ትንታኔ ያቀርባል።
Download Telegram
ባለፉት ሁለት ቀናት በሶማሊያ መንግሥት ኃይሎችና በአሸባብ ሚሊሽያዎች መካከል ሰሜን ምዕራብ መቅዲሾ ውስጥ በተካሄደ ውጊያ በርካታ ወታደሮች መገደላቸው ተዘገበ። የሶማሊያ መንግሥት ዜና አገልግሎት መንግሥት 50 ይደርሳሉ ያላቸው የአሸብብ ሚሊሽያዎች በውጊያው ተገድለዋል ብሏል። ከሚሊሽያዎቹ በኩል ግን የተባለ ነገር የለም።አንድ የዓይን እማኝ እንዳሉት በሁለት ቀናቱ ውጊያ በሁለቱም ወገኖች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል። ገበሬው ሁሴን አሊ የሶማሊያ መንግሥትም ሆነ አሸባብ በርካታ አስከሬኖችን መሰብሰባቸውን ገልጸዋል። ከሁለቱም ወገን ቢያንስ 20 አስከሬን መቁጠራቸውንም ተናግረዋል። ርሳቸውና ሌሎች ሲቪሎችም በተኩስ ልውውጡ ምክንያት ከአካባቢያቸው መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ በኮሮና ተሕዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ700,00 በላይ ሆነ። በአፍሪካ በተህዋሲው ክፉኛ ከተጠቁ ሃገራት ቀዳሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ 18,370 ሰዎች ከኮሮና በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሃገሪቱ በተለይ ባለፉት የሐምሌ እና ነሐሴ ወራት የተሕዋሲው ስርጭት ጫፍ ደርሶ የነበረበት ጊዜ እንደነበር የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታውቋል። በእነዚሁ ወራት በየዕለቱ በአማካይ 12,000 ሰዎች በተሕዋሲው ሲያዙ እንደነበር ማዕከሉ ጠቁሟል። በሀገሪቱ ተህዋሲውን ለመከላከል ተጥለው የነበሩ ጥብቅ ክልክላዎች ለተሕዋሲው ስርጭት መጠናከር አይነተኛ አስተዋጽዖ እንደነበራቸው ተገልጿል። በኢትዮጵያ በተሕዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ 87,169 ሲደርስ ከኮሮና በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 1325 ደርሷል። በተመሳሳይ በመላው ዓለም በኮሮና ተሕዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ39 ሚሊዮን ሲሻገር ። ከኮሮና ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ ገደማ ደርሷል።
የአድማጮች ማሕደር https://p.dw.com/p/3k4Z6 ?maca=amh-RED-Telegram-dwcom
በጀርመን የኮሮና ተህዋሲ ስርጭት ማሻቀቡን ተከትሎ ሕዝቡ በተቻለ መጠን ከቤት ባለመውጣት ኮሮናን እንዲከላከል መራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጥሪ አቀረቡ ። በጀርመን እንደገና ያገረሸው የተህዋሲው ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የሀገሪቱ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታውቋል። መራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በየሳምንቱ ለንባብ በሚቀርብ አንድ መጽሔት «አሁን ማድረግ ያለብንን ነገር ሳናደርግ ብንቀር ኋላ ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችል ችግር ሊያስከትል ይችላል» ብለዋል። የተሕዋሲውን ስርጭት በጀርመን አሁን ወደ አሳሳቢ ደረጃ ከፍ እያለ ነው ያሉት መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ሕዝቡ በተቻለ መጠን ከአላስፈላጊ ጉዞ እንዲቆጠብ እና ሰዎችን የሚያሰባስቡ ዝግጅቶችን ከማዘጋጀት እንዲቆጠብም ጠይቀዋል። በጀርመን ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 7,830 ሰዎች በተሕዋሲው መያዛቸው መረጋገጡን የጀርመን ዜና ምንጭ ዘግቧል። የኮሮና ተህዋሲ በጀርመን መከሰቱ ከተነገረበት ዕለት ጀምሮ 356,387 ሰዎች በተሕዋሲው መያዛቸው ሲረጋገጥ 9,767 ሰዎች ደግሞ ከኮሮና በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።
የኪሊማንጃሮ ተራራ በሰደድ እሳት መያያዝ እና የአካባቢው ስነምህዳር
ባለፈው እሁድ ምሽት የታንዛንያ ብሔራዊ ፓርክን የሚያስተዳድረው ባለ ሥልጣን በዓለማችን በትልቅነቱ አንዱ ስለሆነው የኪሊማንጃሮ ተራራ አስደንጋጭ ምስል በትዊተር ገጹ ላይ አወጣ። በእርግጥ ነው በትዊተር ገጹ ላይ የሰፈረው ምስል ዝርዝር ጉዳይ አልያዘም ። https://p.dw.com/p/3k4rv ?maca=amh-RED-Telegram-dwcom
በፈረንሳይ አንገቱን ተቀልቶ የተገደለው መምሕር በእስላማዊ ጽንፈኛ አሸባሪዎች የተፈጸመ ድርጊት መሆኑን የሀገሪቱ መንግስት አስታወቀ። ሳሙኤል ፓቲ የተባለው መምህር በስለት የተገደለው በአንድ የፓሪስ ጎዳና አጠገብ በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት አካባቢ ትናንት ምሽት ላይ ነበር። ፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮ የመምህሩን መገደል ተከትሎ «መምህሩ ሃሳብን በነጻነት መግለጽን በማስተማሩ የጥቃቱ ሰለባ ሆኗል» ብለዋል። በጥቃት አድራሾቹ ላይ ፈጣን እርምጃ እንደሚወስዱም ዝተዋል። የፈረንሳይ ፖሊስ በበኩሉ ከጥቃት አድራሹ ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀርም ያላቸውን ዘጠኝ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ካስቴክስ ዛሬ ጠዋት በቲዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት «መምህሩ የጽናት ተምሳሌት ነው» ብለዋል። « በእስላማዊ ጽንፈኛ አሸባሪዎች የሚደረጉ መሰል ጥቃቶች ፈረንሳይን አያንበረክኩም» በማለትም ገልጸዋል። ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመቶ ተገድሏል። ሟቹ መምሕር የነቢዩ መሐመድን የካርቱን ስዕሎችን ለተማሪዎቹ እያሳየ ያስተምር እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
የኮትዴቩዋር ምርጫ እና የተቃዋሚዎች ጥሪ
ሁለቱ ዋነኛ የኮትዴቩዋር ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ተቀናቃኞች እጎአ ከፊታችን ጥቅምት 31 ቀን ሊደረግ በታቀደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል። በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሄንሪ ኮናን ባዴይ እና አፊ ንጉዌሳን የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ቆርጠው የተነሱትን አላሳን ዋታራን እየተገዳደረ ነው።https://p.dw.com/p/3k4vK?maca=amh-RED-Telegram-dwcom
ቱርክ በጥቁር ባሕር ውስጥ ተጨማሪ የ85 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋስ ክምችት ማግኘቷን አስታወቀች። የጋስ ክምችቱ መገኘቱ የታወቀው በጥቁር ባህር ላይ ቱና-1 የሚል መጠርያ የተሰጠው እና 4,775 ሜትር ጥልቀት ያለው ቁፋሮ በስኬት መጠናቀቁ ከተረጋጋጠ በኋላ መሆኑን ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶሃን ተናግረዋል። ቱርክ ባለፈው ነሐሴ ወር በዚያው የጥቁር ባህር ዳርቻ ላይ 320 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋስ ክምችት ማግኘቷን አስታውቃ ነበር። ምንም እንኳ ክምችቱ ቱርክ የቀጣናው የተፈጥሮ ሀይል ክምችት ቋት ለመሆን ለምታደርገው ጥረት በቂ አለመሆኑን ተንታኞች ቢያሳውቁም። ቱርክ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋስ ክምችት እጎአ ከ2023 ጀምሮ በማውጣት ጥቅም ላይ ለማዋል ማቀዷን የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል። የጋስ ክምችቱ ሀገሪቱ ቀደም ሲል በውጭ ሃገራት ላይ የነበራትን ጥገኝነት እንደሚያስቀርላት ከወዲሁ ተገምቷል። ባሳላፍነው ሳምንት ቱርክ ከግሪክ እና ቆጵሮስ ጋር ስትወዛገብበት በነበረው የምስራቃዊ የሜዲትራንያን የባህር ክፍል ተሰማርቶ የነበረ መርከቧን መመለሷን አስታውቃለች። በሃገራቱ መካከል የተፈጠረው ውዝግቡ ግን አሁንም ድረስ ከአንዳች መቋጫ አልደረሰም።
በአዛርባጃን የጋንጃ ከተማ በደረሰ የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት 13 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ መንግሥት አስታወቀ። ለጥቃቱም አርመንን ተጠያቂ አድርጓል። በጥቃቱ ከሞቱት ባሻገር 50 ሰላማዊ ሰዎች ቆስለዋል። በናጎሮኖ ካራባህ ግዛት ጉዳይ በሁለቱ ሃገራት መካከል ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ከመርገብ ይልቅ አይሎ ለሰላማዊ ሰዎችን ሞት እያባባሰው መምጣቱን ዘገባዎች እያመለከቱ ነው። አዛርባጃን ዛሬ ያቀረበችውን የሚሳኤል ጥቃት ክስ አርመን አጣጥላዋለች። የናጎሮኖ ካራባህ ተገንጣይ ቡድን ባለስልጣናትም በበኩላቸው በአዛርባጃኗ የጋንጃ ከተማ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ከመዘርዘር ባለፈ ለጥቃቱ ኃላፊነት መውሰድ አልፈለጉም። እንደ የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ በጋንጃ ከተማ ላይ ትናንት ሌሊት በተተኮሰ ሶቭየት ሰራሽ ስኩድ ሚሳኤል 20 የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በህይወት የተረፉ ሰዎችን ከፍርስራሹ ውስጥ ለማውጣት ዘለግ ያለ ጊዜ ወስዶባቸው እንደነበር የከተማዋ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ሁለቱ ሀገራት በገቡበት ደም አፋሳሽ ጦርነት ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃት እንደማያደርሱ በየፊናቸው ቢያሳውቁም ። ከሁለቱም ወገን በየዕለቱ የሚሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ዘገባው አመልክቷል።
ዛሬ ረፋዱ ላይ በፖላንዷ ጊዲኒያ በተካሔደ የኦለም ግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን የወከሉ አትሌቶች ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል። በውድድሩ በሴቶች ምድብ ኬኒያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ቀደም ሲል በራሷ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረወሰን በማሻሻል አሸናፊ ሆናለች። የገባችበት ሰዓትም 1 ሰዓት 05 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጤታማነቷን እያስመሰከረች የምትገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊት ጀርመናዊት ሜላት ይስሓቅ ሁለተኛ ሆና ገብታለች። ኢትዮጵያዊቷ የዓለም ዘርፍ የኋላ ሶስተኛ ሆናለች። በውድድሩ የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረው አባበል የሻነህ በሶስተኛው ዙር ላይ ተጠልፋ በመውደቋ ሳይሳካላት ቀርቷል። ውድድሩን አምስተኛ ሆና ለመጨረሰም ተገዳለች። በወንዶች መካከል በተደረገ ተመሳሳይ ውድድር ዑጋንዳዊው ጃኮች ኪፕሊሞ አሸናፊ ሆኗል። 58 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ የገባበት ሰዓት ሆኗል። ኬኒያዊው ካንዴ ሁለተኛ ሲሆን ኢትዮጵያዊው አምደወርቅ ዋለልኝ ሶስተኛ ሆኖ መግባት ችሏል። በውድድሩ ከ1ኛ እስከ ሶስተኛ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች የ30 ሺ 15 ሺ እና የ10ሺ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ። የዓለም ክብረ ወሰን ያሻሻለችው ኬኒያዊቷ ጄፕቺርቺር የ50 ሺ የአሜሪካ ዶላር ተሸልማለች። TD/EB
“ እናስታውሳችሁ!” በሚል መሪ ሀሳብ በባሕር ዳር ከተማ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ኮሜዲያን የኮሮና መከላከል ቅስቀሳ አካሂደዋል፡፡
የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ኮሜዲያን ህብረተሰብ ከመዘናጋት ወጥቶ ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው እንዲከላከልም ተማፅነዋል፡፡
ባለሙያዎቹ በተለያየ መንገድ የመከላከያ መንገዶችን በከተማው እየተዘዋወሩ ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ አርፍደዋል፣ የአማራ ክልል የሙዚቃ ማርሽ ባንድም ለቅስቀሳው ድምቀት ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ በስነስርዓቱ ከፍተኛ የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡
(የቪዲዮ ዘገባ፦ ዓለምነው መኮንን) https://www.facebook.com/dw.amharic/videos/418849512850649
የዕለቱ ዜና በድምጽ
• የዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ በዳርፉር ግጭት የጦር ወንጀል እና የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው በሚፈለጉ ሹማምንት ጉዳይ ለመምከር ሱዳን ገቡ።
• የጊኒ ዜጎች በአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምጽ ሲሰጡ ዋሉ። ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩበት ይኸው ምርጫ በአገሪቱ የጎሳ ውጥረት ፈጥሯል።
• የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የግል ጠባቂያቸው በኮሮና መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን ማግለላቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አስታወቁ። ፕሬዝዳንቱ ራሳቸውን ያገለሉት ከትናንት ቅዳሜ ጀምሮ ነው።
• ጣልያን በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ 179 የሕክምና ዶክተሮችን ዛሬ አስባ ዋለች።
• ሳዑዲ አረቢያ ዜጎቿ እና በግዛቷ የሚኖሩ ሰዎች በመካ በሚገኘው ታላቅ መስጂድ ለሰባት ወራት ተቋርጦ የቆየውን ዕለታዊ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲያካሒዱ ፈቀደች።
https://p.dw.com/p/3k6eB?maca=amh-RED-Telegram-dwcom
በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች መደጋገፍ ማህበር የበጎ ተግባር እንቅስቃሴ!
በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች መደጋገፍ ማህበር የበጎ ተግባር እንቅስቃሴ!
በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆች መደጋገፍ ማህበር በተለያየ ዘርፍ ለከተማዋ በጎ ተግባር ላከናወኑ አካላት ድጋፍና የምስጋና ፕሮግራም አካሄዷል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በመከላከል ረገድ ለአረጋውያን መርጃ ድርጅቶች እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የቀድሞ ስፖርተኞች በውጭ ከሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆች እና ወዳጆች ያገኘውን ድጋፍ ሰቷል።
በደርግ ዘመን ከተማዋን በከንቲባነት ለመሩት አቶ አበበ እሸቴ በዚህ ዝግጅት ምስጋና ተሰቷል። አቶ አበበ ለከተማዋ እድገት ካበረከቱት አስተዋጽኦ ባለፈ ወጣቶች የቀይ ሽብር ሰለባ እንዳይሆኑ በመከላከል የሰሩት ስራ በመልካም ስም ይነሳላቸዋል። https://www.facebook.com/dw.amharic/videos/650954632459541
የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የግል ጠባቂያቸው በኮሮና መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን ማግለላቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አስታወቁ። ፕሬዝዳንቱ ራሳቸውን ያገለሉት ከትናንት ቅዳሜ ጀምሮ ነው። የፕሬዝዳንት ሽታይንማየር የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት ኔጌቲቭ ቢሆንም ራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል። በመጪዎቹ ቀናት ፕሬዝዳንቱ ተጨማሪ ምርመራ ይደረግላቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዛሬው ዕለት ሊሳተፉበት ከታቀደው የፍራንክፉርት የመጻሕፍት አውደ ርዕይ በዚሁ ሳቢያ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሐይኮ ማስ ባለፈው መስከረም በተመሳሳይ ጠባቂያቸው በኮሮና መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን ለማግለል ተገደው ነበር። ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ በተደረገላቸው ምርመራ በኮሮና አለመያዛቸው ተረጋግጧል።
የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በወረርሽኙ ከተያዘ የሕክምና ዶክተር ከተገናኙ በኋላ በመጋቢት ወር ለሁለት ሳምንታት በመኖሪያ ቤታቸው ተነጥለው ቆይተዋል። ሜርክል እንደ ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ሁሉ ኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ነጻ ሆነዋል።
እስካሁን ድረስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የብራዚሉ አቻቸው ዣየር ቦልሶናሮ እና የብሪታኒያው ጠቅላይ ምኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮና ተይዘው ነበር። 👉🏾 @dwamharicbot
የጊኒ ዜጎች በአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምጽ ሲሰጡ ዋሉ። ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩበት ይኸው ምርጫ በአገሪቱ የጎሳ ውጥረት ፈጥሯል። በዋና ከተማዋ ኮናክሪ ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት ተሰልፈው ታይቷል። የ82 አመቱ ፕሬዝዳንት ለሶስተኛ ጊዜ ለምርጫ እንዲቀርቡ የተፈቀደላቸው ጊኒ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ካደረገች በኋላ ነበር።

ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንቱን ተገዳድረው ለምርጫ የቀረቡት የተቃዋሚ መሪ ሴሉ ዳሌይን ዲያሎ ባቀረቡት ክስ አልፋ ኮንዴ በሥልጣን ለመቆየት ምርጫውን ያጭበረብራሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የጊኒ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነትን የሚወክሉት ሴሉ ዳሌይን ዲያሎን ጨምሮ አስር ፖለቲከኞች ለፕሬዝዳንትነት ይወዳደራሉ። ዛሬ በተካሔደው ምርጫ ኹከት ይቀሰቀሳል በሚል ሥጋት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ለጥበቃ መሰማራታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የድምፅ አሰጣጡ እስካሁን እንደተፈራው ግጭትም ሆነ ኹከት አልገጠመውም።

ምርጫው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን በሚደግፉት የማሊንኬ ጎሳ አባላት እና ሴሉ ዳሌይን ዲያሎን በሚደግፉት የፉላኒ ሰዎች መካከል አደገኛ ውጥረት ፈጥሯል። ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በምርጫ ምክንያት የተፈጠረ ቅራኔ "እጅግ አደገኛ ነው" ሲል አስጠንቅቆ ነበር። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ባለፈው አንድ አመት ኮንዴ በድጋሚ ለምርጫ ለመቅረብ መወሰናቸውን በመቃወም በተደረጉ ሰልፎች በትንሹ 50 ሰዎች ተገድለዋል።
መቀመጫውን በኔዘርላንድስ ዘ-ሔግ ከተማ ያደረገው ዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ከምርጫው ጋር የተያያዘ ኹከት በጊኒ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት አለው። የፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሶዳ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሒቃን በምረጡኝ ዘመቻው ወቅት አሰምተውታል ያሉትን ጠብ ጫሪ ንግግር አውግዘዋል።
👉🏾 @dwamharicbot
ጣልያን በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ 179 የሕክምና ዶክተሮችን ዛሬ አስባ ዋለች። መርሐ-ግብሩ የተካሔደው በሰሜናዊ ጣሊያን ዱኖ በተባለች ከተማ ሲሆን በወረርሽኙ ክፉኛ በተጠቃው የሎምባርዲ ግዛት በኮሮና ምክንያት ሕይወታቸን ያጡ የሕክምና ዶክተሮች ለመታሰቢያ በተዘጋጀ እብነ በረድ ላይ ስማቸው ሰፍሯል።
ባለፉት ቀናት በጣልያን በኮሮና መያዛቸው በምርመራ የሚረጋገጥ ሰዎች ቁጥር ከ10,000 ሺሕ በልጧል። ይኸ ወረርሽኙ በከፋባቸው የመጋቢት እና የሚያዝያ ወራት ከነበረውም የላቀ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ወረርሽኙ ያሰጋው የአገሪቱ መንግሥት ተጨማሪ ጥብቅ ገደቦች ለመጣል እያሰበ ነው።
የጣልያን መንግሥት ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ምጣኔ ሐብታዊ ዳፋ ለመቀነስ 40 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 47 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ አጽድቋል። የኮሮና ወረርሽኝ ዳግም ያሰጋው ግን ጣልያንን ብቻ አይደለም።
ፈረንሳይ በወረርሽኙ ሳቢያ የጣለችው የሰዓት ዕላፊ የአገሪቱን ከተሞች ጸጥ ረጭ አድርጓቸዋል። የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በትናንትናው ዕለት እንዳለፈው ጸደይ ሁሉ ዜጎች በወረርሽኙ ላይ እንዲያብሩ ጥሪ አቅርበው ነበር። በኮሮና የሚያዙ እና በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በሩሲያ ጭማሪ ቢያሳይም የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ቅሬታ የሚያሳድር የእንቅስቃሴ ገደብ ገቢራዊ ከማድረግ ተቆጥቧል።
ሬውተርስ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት በመላው ዓለም 39.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ተይዘዋል። አንድ ሚሊዮን 105 ሺሕ 938 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውና አጥተዋል። አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ እና አርጀንቲና ኮሮና እጅግ የበረታባቸው ቀዳሚ አምስት አገሮች ናቸው።
ኢትዮጵያ ጃፓንን ተከትላ ሖንዱራስን አስከትላ በ49ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እስከ ትናንት ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 88 ሺሕ 434 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ያወጡት መግለጫ ይጠቁማል። በወረርሽኙ ሳቢያ 1346 ሰዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
👉🏾 @dwamharicbot
ሳዑዲ አረቢያ ዜጎቿ እና በግዛቷ የሚኖሩ ሰዎች በመካ በሚገኘው ታላቅ መስጂድ ለሰባት ወራት ተቋርጦ የቆየውን ዕለታዊ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲያካሒዱ ፈቀደች። በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጠው አል-ሐራም መስጂድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው ዕለታዊ ጸሎት እንዲካሔድ መፈቀዱን የአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ዛሬ ማለዳ ዘግቧል።
አገሪቱ ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት በመካ እና በመዲና የአገሪቱ ዜጎች እና በዚያው በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ሰዎች የኡምራ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲያከናውኑ ፈቅዳለች። ባለፈው መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በተጀመረው የመጀመሪያ ዙር የኡምራ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሳተፉ የተፈቀደላቸው ስድስት ሺሕ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ሳዑዲ አረቢያ ደሕንነታቸው ከተረጋገጠ አገሮች ከጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በኡምራ መንፈሳዊ ጉዞ ለመሳተፍ የሚጓዙ መንገደኞችን መቀበል እንደምትጀምር የሳዑዲ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።👉🏾 @dwamharicbot
የዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ በዳርፉር ግጭት የጦር ወንጀል እና የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው በሚፈለጉ ሹማምንት ጉዳይ ለመምከር ሱዳን ገቡ። ትናንት ኻርቱም የደረሱት ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሶዳ እና የዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ሌሎች ሹማምንት እስከ ረቡዕ በሱዳን እንደሚቆዩ የጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በመግለጫው መሠረት ልዑካኑ ዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ባወጣባቸው ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ከሱዳን መንግሥት ጋር ይወያያሉ። የጠቅላይ ምኒስትሩ ጽህፈት ቤት የተጠርጣሪዎቹን ማንነት በስም አልዘረዘረም።
በፍርድ ቤቱ ከሚፈለጉ መካከል ባለፈው አመት ከሥልጣን ወርደው በርከት ያሉ ክሶች ከቀረቡባቸው በኋላ እስር ቤት የገቡት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሺር ይገኙበታል።
በዳርፉር ግዛት ግጭት የተቀሰቀሰው አረቦች የሚበዙበት የኻርቱም መንግሥት ይፈጽመዋል የተባለውን ጭቆና በመቃወም አማፂያን ከአስራ ሰባት አመታት በፊት የትጥቅ ትግል ከጀመሩ በኋላ ነበር።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የኦማር አል-በሺር መንግሥት በጦር አውሮፕላኖች ድብደባ እና የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል በሚል የሚከሰሱትን የጃንጃዊድ ታጣቂዎች በአካባቢው በማሰማራት ምላሽ ሰጥቷል። በዚህ ግጭት እስከ 300,000 የሚደርሱ ሰዎች ሲገደሉ 2.7 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት የ76 አመቱን አል-በሺር በዳርፉር የተፈጸመውን ጥቃት በማስተባበር እና በጦር ወንጀል ከሷቸዋል። የሱዳን ዐቃቤ ሕጎች ባለፈው ሳምንት በዳርፉር ግጭት ላይ የራሳቸውን ምርመራ ጀምረዋል።
ከአል-በሺር በተጨማሪ ግጭቱ በበረታበት ወቅት የሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳይ እና የመከላከያ ምኒስትር ሆነው የሰሩት አብደል-ራሒም ሙሐመድ ሑሴይን እና የጸጥታ ኃላፊ ኋላም የገዢው ፓርቲ መሪ የነበሩት አሕመድ ሐሩን ላይ ተመሳሳይ ክስ መስርቶባቸዋል። ሁለቱም ባለሥልጣናት አሁን በእስር ላይ ይገኛሉ።
ፍርድ ቤቱ የዳርፉር አማፂያን መሪ የነበሩት አብዱላ ባንዳ እና የጃንጃዊድ ሚሊሺያ መሪ የነበሩት አሊ ኩሻይብ ላይ ክስ መስርቷል። አብዱላ ባንዳ የት እንዳሉ ባይታወቅም አሊ ኩሻይብ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የ ዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት መቀመጫ ወደ ሆነችው ዘ-ሔግ ከተማ ተወስደዋል።
👉🏾 @dwamharicbot