ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA
354 subscribers
1.3K photos
11 videos
146 files
169 links
Download Telegram
#በደብተራ_በአማን_ነጸረ
መሠረተ እምነት (ዶግማ) ለምን?
--
የምናምነውን እንጸልያለን፤ የምንጸልየውን እናምናለን የሚል ይዘት ያላት ጥቅስ በቀሲስ መብራቱ በኩል ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ጸሎተ ሃይማኖት ትልቁ ጸሎታችን ነው፡፡ በምሥጢሩ የአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አምላክነት፣ አንድነትና ሦስትነት፣ የጌታ ከድንግል ሰው ሆኖ ዓለምን ማዳን፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፣ ነገረ ቤተ ክርስቲያን ያለበት የእምነት መግለጫ ነው፡፡ የእምነታችን መግለጫ ጸሎታችንም ነው፡፡ አበው እንዲህ አድርገው አሠረጹብን፡፡ እምነታችን ዝርው እንዳይሆን መሰብሰቢያ ሠርተው ጸሎትም የእምነት መግለጫም በአንድ ላይ አቀበሉን፡፡ ይህ እምነትና ጸሎት በአንድ የተገለጡበት ድንጋጌ አማንያን በነጻ ፈቃድ የሚታሠሩበት የሚኖሩበት የሚገዙበት መንፈሳዊ ሕግ፣ ዘለዓለማዊ እውነት ነው፡፡
የቃል ሥጋ መሆን፣ የሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ መሆን፣ ያለወንድ ዘር በድንግልና ፀንሶ በድንግልና መውለድ እንዲሁ እንብለ ተኀሥሦ (ያለመመራመር) በእምነት የሚቀበሉት ምሥጢር ነው፡፡ ምሥጢሩን ለማወቅ ጭላንጭል የሚገኝ ተቀብለውት ሲያበቁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ኢምክንያታዊ አምላክ አይደለም፡፡ ሆኖም በእርሱ ያለን እምነት በአመክንዮ የሚደረስበት አይደለም፡፡ እምነት ግላዊ ምናብና አስተያየት አይደለም፡፡ እምነት ተቀብለው የሚኖሩት ሕይወት ነው፡፡ ለማወቅ የሚሞከር ካመኑ በኋላ ነው፡፡ የማይመረመረውን ምሥጢር በድንግዝግዙ ለመግለጥ ሰብአዊ ቋንቋ እንጠቀማለን፡፡ የእምነታችን ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ቢሆንም ዝርውነት እንዳይኖር የመጽሐፉን ተርጓሚነት ሥልጣን በየግላችን አንቧጨቀውም፤ ሉዐላዊ የትርጓሜ ሥልጣኑ የቤተ ክርስቲያን እንደሆነ እናምናለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባሰመረችው መስመር፣ አበው ባኖሩት የዶግማ ቅጽር እንፀናለን፡፡ ለምን?
--
1.እንዲህ እናምናለን ብሎ ለመቆም!
ደጋግሜ እንደምለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካሄዳችን አጸፋዊ (reactive) የሆነ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በሚቀረጽልን አጀንዳ ዙሪያ ብቻ መሽከርከር፡፡ አልፎ አልፎም በተጋነነ ቀናዒነት በሚሰጥ የደም ፍላት ምላሽ ከመጽሐፍ እስከ መጋጨትና መሠረታዊ ዶግማን እስከ ማድ እንደርሳለን፡፡ ‹‹እንዲህ እናምናለን›› ማለትን ሳያስቀድሙ ‹‹እንዲህ ይሉናል፣ እንዲህ ይላሉ›› ከሚል ደመ ነፍሳዊ ስሜት የሚነሣ የአፀፋ አካሄድ ማነፁ ያጠራጥራል፡፡ ዕቅበተ እምነት (እምነትን መጠበቅ/መከላከል) አስቀድሞ እምነትን ማወቅን ይፈልጋል፡፡ የተጻፈ የተተረጐመ ዶግማ አለን፡፡ ክብ … ድ አድርገን በ‹‹ፊዚክስ›› ዐይን አንየው፤ ቅል …ል አድርገንም በደመ ነፍስ የሚነበነብ ጸሎት አናድርገው፡፡ ጊዜ ሰጥተን፣ ከቀልባችን ሆነን ዶግማውን እንወቀው፡፡ ‹‹እንዲህ እናምናለን፣ እንታመናለን›› እስክንል ድረስ፡፡
--
2.የኅብረትና አንድነታችንን መሠረት ለማወቅ!
አንድ ምዕመን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን ሲባል ወደ አንድ ዐቢይ መንፈሳዊ ኅብረት እየተጨመረ ነው፡፡ ዕድር፣ ዕቁብ፣ አክሲዮን ስንገባ መተዳደሪያ ሕጉን እናውቃለን፡፡ ያሰተሳሰረንን አንድነት እናውቀዋለን፡፡ የእምነታችን መጠሪያ የሆነውን ‹‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› ትርጓሜ ማወቅ እየተቻለን ዕውቀትን ለካህን ብቻ የተሰጠ ግብር ማድረግ ስንፍና ነው፡፡ ያስጠይቃል!
--
3.እንዲህ ነን ለማለት!
‹‹እንዲህ ናችሁ›› ባዩ ብዙ ነው፡፡ የእምነቱን መሠረታውያን ያወቀ ሰው ‹‹አይ እንዲያ ሳይሆን እንዲህ ነን›› ለማለት አያፍርም፡፡ በማይጠራበት ስም ሲጠሩት በስሜ ጥሩኝ ይላል፡፡ ራሱን መግለጥ በሚገባው ቦታ ይገልጣል፤ ይመሰክራልም፡፡ አውቆ መመስከር ያጸድቃል፡፡
--
4.እምነቱን ለልጅ ለማውረስ!
‹‹እምነት እንደ ፍሻሌ ሽጉጥ አይወረስም›› የሚልህን ዝርው ቧልተኛ እርሳው፡፡ ይወረሳል፡፡ የይስሐቅ እምነት ከአብርሃም የተወረሰ ነው፤ ከነግዝረቱ ነዋ! በነሐሴ 3 ስንክሳር የምትዘከረውን የሶፍያ ንግሥት ደናግል ልጆች እምነት ታውቃለህ! ቅዱስ ያሬድ ‹‹መተወት ደቂቃ ለስምዕ›› የሚላት እርሷን ነው፡፡ በየትም አገር ልጅ የአባቱን እምነት ተቀብሎ አብዛኛው በዚያው እምነት ኖሮበት ያልፋል፡፡ ብልጣብልጡ እንኳ ልጁ እምነቱን እንዳይወርስ ያደርጋል ብለህ እንዳትገምት፡፡ አራዳውን እርሳው! ሕገ መንግሥቱም ወላጅ ልጁን በሚያምንበት እምነት አንጾ የማሳደግ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖተ አበውን መጠበቅ ግዴታችን ነው፡፡ ቄርሎስን እንደ ቄርሎስ እንዲሠራ አጎቱ ቴዎፍሎስ ደክሟል፡፡ ቈስጥንጢኖስ የእናቱ ልጅ ነው፡፡ ከአባትህ የተቀበልከውን ለልጅህ ማቀበል ግዴታህ ነው፡፡ የምታቀበልው እንዳታጣ የቤተ ክርስቲያንህ ዶግማ ሰንቅ! ልጅህን በእምነትህ ቅረጸው! ቢላዋ የሚሳል ለራ ባልተሳለ ሞረድ ነው ብለህ ግን እንዳትዘናጋ፡፡ ማወቅና ማሳወቅ እየቻሉ አለማወቅና አለማሳወቅ አያጸድቅም!
--
5.አፈንጋጮችን ትቈጣጠርበታለህ!
ዐውደ ምሕረት ላይ እምነት የሚያጎድፍ፣ ምሥጢር የሚያፋልስ ሰብከት ቢሰበክ፣ በመጻሕፍት ተጽፎ ብታገኝ፣ በግል ውይይት ሲነገር ብትሰማ ጋላቢው ላይ ልጓም ትስብበታለህ፡፡
--
6.ማን፣ ለምን፣ ከምን፣ በምን፣ እንዴት እንዳዳነህ ትረዳበታለህ!
ቤተ ክርስቲያን አንዲት ዘለላ የድኅነት ፎርሙላ አትሰጥህም፡፡ ‹‹አመንክ ጸደቅህ›› ብላ አታዘናጋህም፡፡ ነገረ ድኅነት ጌታ ከፅንሰት እስከ ምጽአት ያለው ጉዞ የሚካተትበት፣ የምግባርና የምሥጢራትም ጉዳይ ያለበት ሁለንተናዊ ጉዞ መሆኑን ትረዳበታለህ፡፡ ዝርዝር ጥያቄዎችህ በዚያ ሂደት መልስ ያገኛሉ፡፡ ያመንከውን ለማወቅ አንብብ፣ ጠይቅ፣ ተረዳ፣ የተረዳሀትን ለመኖር ጣር፣ በምሥጢራት ተሳተፍ፣ ቸርነቱን በእምነት ተስፋ አድርግ፡፡
--
ንባብህን እንደ #ኦርያሬስ ካሉ የጉባኤን ምሥጢር ሳይገድፉ የዘመንህን ቋንቋ የዋጀ አቀራረብ ካላቸው የነገረ ሃይማኖት መጻሕፍት አታርቅ፡፡ ያንጊዜ ባለፀጉረ ጉንጉን ሐሳዊም ሆነ የፌርማ አወናባጅ አያወናብድህም፡፡ እምነትህ እንደ መገበሪያ ሰንዴ የተለቀመች ናት፡፡ አትሰነፍ! የጉባኤ ሰዎች ቸርነት ሳይነጥፍ፣ ያንተም የጉብዝና ወራት ሳያልፍ፣ ኦርያሬስ ሳትጠልቅ (ጀምበር ኦርያሬስ/ ሳለች ሩጥ እንዲሉ አበው) ምሥጢሯን አስስ! ኦርያሬስ ከሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ #ተንከተም ና ከእነ መ/ር ገብረ መድኅን #ምሥጢረ_ምሥጢራት በኋላ የመጣ ግሩም የነገረ ሃይማኖት መጽሐፍ ነው፡፡ የብሔራውያኑን ሊቃውንት ረቂቅ የነገረ ክርስቶስ ተዋሥኦ ካሻህ እንዳቅማችን በአማተራዊ ብርዕ የደከምንባት #ጽንዐ_ተዋሕዶ መስፈንጠሪያ ትሆንህ ይሆናል፡፡

#ኦርያሬስ_በአርጋኖን_መጽሓፍት_መደብር_እየተከፋፈለነው