ብራና ሚድያ - Birana Media
618 subscribers
1.68K photos
40 videos
4 files
577 links
+ የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት
+ ገዳማትና ታሪካዊ ስፍራዎች
+ የቅዱሳን አበው መንፈሳዊ ተጋድሎና ታሪክ
+ እንዲሁም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ወደ እናንተ ውድ ተከታታዮች መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ በየእለቱ ይቀርባል።
ቻናላችንን Subscribe በማድረግ ይቀላቀሉን።
https://www.youtube.com/c/BiranaMedia
ጥያቄ ካሎት በዚህ ይጻፉልን @birana259
Download Telegram
«ወኢትምጻእ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክከ ዕራቀከ»
በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ራቁትህን አትምጣ
【ዘዳ ፲፮፥፲፮】

በዚህ መጻሕፍት ይተባበሩበታል
✧ "ወኢታስተርኢ ቅድሜየ ዕራቀከ ☞ በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ" 【ዘጸ ፴፬፥፳】
✧ "ወኢትትረአይ በቅድሜየ ዕራቀከ ☞ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። 【ዘጸ ፳፫ ፥፲፭ / ፳፬፥፲፩】
✧ ሲራክም "ኢትባእ ቅድመ እግዚአብሔር ዕራቀከ ☞ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ባዶህን አትግባ" 【ሲራ ፴፪፥፮】

በቅድሜየ ወይም በፊቴ ማለቱ ለእግዚአብሔርስ ሁሉ ቅድሙ ወይም ፊቱ ነው፤ በሁሉ ያለና ከፊቱ የሚሸሸግ የሌለ ሆኖ ሳለ መገለጫ መክበሪያውን ሲያይ ፊቴ ይላል።
☞ በዘመነ ብሉይ በደብተራ ኦሪትና በቤተ መቅደስ በረድኤት ያድር ነበርና
☞ ዛሬም በዘመነ ሐዲስ በሥጋውና ደሙ በቤተክርስቲያን ይገለጽባታልና ከሁሉ አብልጦ ማደርያ ቤቱን ቅድሜየ አላት።

ይህን ራሱ ሙሴ ሲገልጠው «ቅድመ እግዚአብሔር ፥ ውስተ መካን ዘኀርየ እግዚአብሔር አምላክከ ☞ በእግዚአብሔር ፊት ፥ እርሱ አምላክህ በመረጠው ስፍራ» ሲል አስረድቷል፤

ለሰው አካሉን ገልጦና ሰውነቱን አራቁቶ ለመታየት የታወቀ (በቂ) ምክንያት ያስፈልጋል፤ ሠለስቱ ምዕት ለመታከም «የሚተኮስ» «የሚታገም» አካል ቢኖር አልያም ከጸበል ሊነከሩና ሊታጠቡ እንጂ በሌላውስ መንገድ በማንም ፊት እርቃን መታየት ክልክል ነው ብለዋል።

"ወዓዲ ተዐቀብ ከመ ኢትትዐረቅ እምልብስከ ቅድመ መኑሂ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ይረክበከ ምክንያት ለተዐርቆ። ☞ ዳግመኛም በማንም ፊት ከልብስህ ራቁትህን እንዳትሆን ተጠበቅ፤ የምትራቆትበት ምክንያት ቢያገኝህ ነው እንጂ" 【ሃይ አበው ፳፥፲፪】

ራቁትነት በውጭ ያለ (አፍኣዊ) ገላን መክደኛ ነውርን መሸፈኛ ከሆነው ጨርቅ ከመራቆት በላይ በሦስት መንገድ ውሳጣዊ እርቃንን የሚያስረዱ ሦስት መንገዶችን እናስቀምጥ

፩ኛ] ራቁት የሚለው #በኃጢዓት_መመላለስ በበደል መጽናትን ነው። ያንን በንሰሐ ሳያጠሩ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚገባ አይደለምና።

በኃጢዓት ከመውደቃቸው አስቀድሞ የማይተፋፈሩ የነበሩ አዳምና ሴቲቱ ከሕግ ሲወጡ ራቁትነትን አወቁ፤

“የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።” 【ዘፍ ፫፥፯】

ቅዱስ ዳዊት ይህን ድርጊት «እንሰሳትን መምሰል» ብሎታል
【መዝ ፵፰፥፲፪/፳】

አባ ጊዮርጊስም በመጽሐፈ ምሥጢር እርቃን ከመቅረት በላይ እንሰሳትን መምሰል ወዴት አለ? ብሏል
“ምንት ውእቱ ተመስሎ እንስሳ ዘእንበለ ተከሥቶ ዕርቃኑ ማእከለ ዕፀዊሃ ለገነት ሶበ ነፍጸ አጽፈ ብርሃን ዘላዕሌሁ ኀደጎ አጽፈ ብርሃን ⇨ በገነት ዛፎች መካከል ዕርቃኑን ሆኖ ከመተየት በስተቀር እንስሳን መምሰል ምንድ ነው? የብርሃን ልብስ ከበላዩ ላይ በተገፈፈ ጊዜ የብርሃን መጐናጸፊየው ተለየው”

ክዶ ከአምላኩ ተለይቶ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታው በፊቱ በቆመ ሠዓት ለጊዜ እርቃኑን በልብስ ደብቆ ከባህር ጠልቆ መታየቱ ነውን በንሰሐ አርቆ ሥጋን በቅጣት አስጨንቆ ድኅነት እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
“ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ።” 【ዮሐ ፳፩፥፯】

እንደ ወርቅ የተፈተነ ቃሉን በመያዝ ፣ እንደ ነጭ ልብስ የከበረውን ጸጋ ልጅነት ለማጽናት… ከፊቱ ቀርቦ በንሰሐ መመላለስ ይገባል
“ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።” 【ራእ ፫፥፲፰】

፪ኛ) ራቁት ማለት ራስን መግለጥ #ተርእዮን_መሻት እግዚአብሔርን መርሳት አምላከ ቅዱሳንን ማስረሳት ማለት ነው። ራስን ለመስበክና ስለራስ ለማውራት እግዚአብሔር ፊት መቆም ተገቢ አይደለም።
በሰማይ ያሉ አገልጋዮቹ ከመንበሩ ፊት የቆሙ መላእክቱ ፊት እግራቸውን መሸፈናቸው ለዚህ መማርያ ይሆነናል
“ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።” 【ኢሳ ፮፥፪】

ራሱን ሲሰብክ ለዋለው
"ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት” (ዮሐ 12፥2) የሚል መልእክት ልከው
ኋላ ተመልሶ ራሱን ሰውሮ ክብረ ክርስቶስን ቢሰብክላቸው
“ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።” (ዮሐ20፥20) ብለው አመስግነውታል።

፫ኛ) ራቁት ማለት ባዶ እጅ #ምንም_ሳይዙ_መምጣት ማለት ነው፤ መባዕ፣ ስእለት ፣ ምጽዋት ፣ ዐሥራት፣ በኩራት፣ ቀዳምያት እና መስዋእት ሳይይዙ ወደመቅደሱ መምጣት የሚገባ አይደለምና።

“ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” 【ሉቃ ፮፥፴፰】

©️ ዲ/ን ቴዎድሮስ በለጠ መንግስቱ ( ዶ/ር )