ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
32.1K subscribers
811 photos
11 videos
16 files
559 links
በዚህ ቻናል የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች እና የአበው ቀደምት የተናገሯቸው መንፈሳዊ ንግግሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ ትምህርቶችና መልዕክቶች ይተላለፉበታል፡፡
Download Telegram
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ከቅዱሳን_ባሕታውያ_ጋር

በአንድ ወቅት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለ፡-ከዕለታት አንድ ቀን በሀገረ ስብከቴ ሥር በነበሩ በሜዲትራኒያን ባሕር በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩ ምእመናንን ለመጎብኘት አሰብሁ፡፡ ከእኔ ጋር ቀሳውስትንና ዲያቆናትን አስከትዬ በጀልባ ተሳፍሬ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ተጓዝሁ፡፡ በደሴቱ ውስጥ ስንዘዋወር የሰው ዱካ ብንመለከትም ምንም ሰው ማየት አልቻልንም ነበር፡፡ በአሸዋው ላይ ታትሞ የነበረውን የሰው ዱካ ተከትለን ስንጓዝ ካልተፈለፈሉ ዐለቶች የተሠራ ቤተ ክርስቲያን የሚመስል ዋሻ ላይ ደረስን፡፡

ዋሻው በርም ሆነ መስኮት የለውም፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ ልክ እንደ ሰባቱ ደማቅ ከዋክብት እጅግ በጣም አንጸባራቂ ብርሃን ቆመው ከሚጸልዩ ሰባት አባቶች ዘንድ ሲወጣ ተመለከትን፡፡ እኛም ከእነርሱ ጋር ለመጸለይ ባለንበት ቆምን። አባቶች ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ እኛ ዞሩና በፊቴ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሰገዱ። በመቀጠልም ሰላምታ ሰጡን፡፡ እኔ ዮሐንስም ‘እኔ አባታችሁና ፓትርያርካችሁ ዮሐንስ ነኝ’ አልኳቸው፡፡ ቅዱሳኑ እንደገና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በፊቴ ሰገዱ እና እኔን ደካማውን እንዲህ አሉኝ፡- “የምንወደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድትባርከንና እኛም አንተን በማየት እንድንበረታ ወደዚህ አመጣህ” አሉ። እኔም “እባካችሁ ታሪካችሁን ንገሩኝ” አልኋቸው፡፡

ሰባቱ አባቶችም “ከብዙ ዓመታት በፊት ሰባታችንም ከቍስጥንጥንያ ወጥተን በአንድነት ተሰባስበን ሕይወታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና በአምልኮ ብቻ ለማሳለፍ ወደዚህ ደሴት መጣን፡፡ ከዚህ ደሴት በደረስንበት ዕለት ከባሕሩ ከሚመጣው አስቸጋሪ ነፋስ ራሳችንን ለመከላከል ዋሻዎችን ለመገንባት ዐለቶችን ሰበሰብን፤ በሁለተኛው ቀን ደግሞ ይህን ቤተ ክርስቲያን መሥራት ጀመርን፡፡ በዐለቶች መካከል ከሚበቅለው ሣር እንበላለን፤ ውኃም ከባሕሩ እንጠጣለን፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን የከበቡትን እነዚህን የአሸዋ ክምሮች ለማስወገድ ፈልገን ነበር፤ ግን አእምሯችንና አሳባችን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስለተያዘ ጊዜ አጣን” በማለት ታሪካቸውን ነገሩኝ።

እኔም “መንፈሳዊ አባታችሁ የት ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ ይህን ጥያቄ ከመጠየቄ ወዲያውኑ አንድ ሽማግሌ በትሩን ተደግፎ ወደ እኔ ቀረብ አለና “እኔ የአንተ አገልጋይ ነኝ” አለኝ፡፡ አረጋዊው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ ራቁቱን ነበረና “ሰውነትህን የምትሸፍንበት ትንሽ ልብስ ትፈልጋለህ?” ስለው እሱም “ጌታ ከክረምቱ ቅዝቃዜ፣ ከበጋው ሙቀት ይከላከልልናል፤ ይጠብቀናልም” በማለት መለሰልኝ፡፡ “ምግብ ያስፈልጋችኋል?” ብዬ ስጠይቀው እርሱም “የሚበቃንን ያህል ከእነዚህ ዕፅዋት እንመገባለን ከዓለም የሆነ ምንም ነገር አያስፈልገንም” በማለት መለሰልኝ፡፡

እኔም “አባቶቼ እባካችሁ ለእኔ እና ስለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ጸልዩ” አልሁት። የእነዚያን ቅዱሳን ባሕታውያን አባቶች በረከት ከተቀበልን በኋላ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለም ምሥጋና የሚገባውን የምንወደውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያመሰገንን ወደ መጣንበት ተመለስን” ይለናል ቅዱሱ አባታችን ዮሐንስ አፈ ወርቅ።

ምንጭ፦ ግሑሣን አበው
#ግንቦት_12

የመምህር ወመገስጽ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የእረፍቱ ቀን፣ የአባታችን የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ፍልሰተ አጽም እና የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የቃልኪዳን ዓመታዊ ክብረ በዓል ነወ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ባሕረ ምስጢራት የሆነ የሰውን ፊት አይቶ የማያደላ "መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ" (በርሱ ዘንድ ንጉሥ፣ ሐብታም፣ ደሃ፣ ነዳይ እኩል ነውና)፣ አፈ በረከት፣ አፈ መዐር (ማር)፣ አፈ ሶከር (ስኳር)፣ አፈ አፈው (ሽቱ)፣ ልሳነ ወርቅ፣ የዓለም ሁሉ መምሕር፣ ርዕሰ ሊቃውንት፣ ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)፣ የሐዲስ ኪዳን ዳንኤል፣ ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)፣ ጥዑመ ቃል... እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እረፍቱ ነው።

#ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ
ብፅዕት ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ሰይጣንን ከፈጣሪ ጋር ልታስታርቅ በሄደች ጊዜ ከሲኦል ቅዱስ ሚካኤል እየተራዳት ብዙ ነፍሳትን ያወጣችበት የቃልኪዳን በዓል ነው።

#አቡነ_ተክለሃይማኖት
የአባታቸንና የኢትዮጵያ ፀሐይ የፃድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ግንቦት 12 ከደብረ አሰቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ አጽማቸው የፈለሰበት (ፍልሰተ አጽም) ይከበራል።

አምላከ ቅዱሳን በቅዱሳኑ ጸሎት ልመናና ቃልኪዳን ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከጭንቀትና ከመከራ ይጠብቀን።
#ግንቦት_12

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ባሕረ ምስጢራት የሆነ የሰውን ፊት አይቶ የማያደላ "መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ" (በርሱ ዘንድ ንጉሥ፣ ሐብታም፣ ደሃ፣ ነዳይ እኩል ነውና)፣ አፈ በረከት፣ አፈ መዐር (ማር)፣ አፈ ሶከር (ስኳር)፣ አፈ አፈው (ሽቱ)፣ ልሳነ ወርቅ፣ የዓለም ሁሉ መምሕር፣ ርዕሰ ሊቃውንት፣ ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)፣ የሐዲስ ኪዳን ዳንኤል፣ ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)፣ ጥዑመ ቃል... እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እረፍቱ ነው።

ምልጃውና የከበረች ጸሎቱ ከእኛ ጋር ትሁን!

https://youtu.be/CuyWTMtAIYw
https://youtu.be/CuyWTMtAIYw
እግዚአብሔር ሲቀጣን

"አንድ ሐኪም አእምሯቸውን የሳቱ ሰዎች ቢሰድቡት፥ ስድባቸውን ከቁም ነገር አይቆጥረውም፡፡ እንዲህ አእምሯቸውን እንዲስቱ ያደረጋቸውን ምክንያት ያስወግድላቸው ዘንድ ይተጋል እንጂ፡፡ 'ሰድበውኛል' ብሎ የራሱን ጥቅም አያይም፤ የሕሙማኑን እንጂ፡፡ በጥቂቱም ቢኾን ሻል ካላቸውና ራሳቸውን መግዛት የሚችሉ ከኾነም እጅግ ደስ ይሰኝባቸዋል፡፡ ውስጡ በፍጹም ሐሴት ይሞላል፡፡ መድኃኒት መስጠቱን በፊት ከሚያደርግላቸው ይልቅ ተግቶ ይሰጣቸዋል፡፡ 'ከዚህ በፊት ሰድበውኛልና ልበቀላቸው' ብሎ በፍጹም አያስብም፡፡ ይበልጥ እንዲጠቀሙና ወደ ቀድሞ ጤናቸው ይመለሱ ዘንድ ተግቶ ይሠራል እንጂ፡፡

"እግዚአብሔርም እንደዚህ ነው፡፡ ምንም እንኳን እጅግ ጥልቅ በኾነ ኃጢአት ውስጥ ብንወድቅም፥ ኹሉንም ነገር የሚያደርገው እኛን ከመቅጣት አንጻር አይደለም፤ የሚቀጣን ስለ ሠራነው የኃጢአት ዓይነት አይደለም፡፡ ከዚህ ሕመማችን እንድንፈወስ ብሎ ነው እንጂ፤ በዚሁ መንገድ ሊመለሱ ይችላሉ ብሎ በማሰብ ነው እንጂ፡፡"

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፥ ወደ ቴዎድሮስ፥ ገጽ 36)

ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔርን ከማሳዘን ውጪ ምንም ይኹን ምን [አንፍራ፡፡] ሠለስቱ ደቂቅ የሚንበለበል እሳት በፊታቸው ቢያዩም ናቁት፤ ኃጢአትንም ብቻ ፈሩ፡፡ በእሳቱ ቢቃጠሉ ምንም የሚያስፈራቸው ነገር እንደሌለ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ባይገኝባቸው ግን እጅግ የከፋ ጉስቁልና እንደሚያገኛቸው ያውቃሉና፡፡ ምንም ሳንቀጣ ብንቀርም እንኳን እጅግ ትልቁ ቅጣት ግን ኃጢአት መሥራት ነው፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ምንም ያህል ቅጣት ቢያገኘንም እጅግ ትልቁ ክብርና ጸጥታ ግን በተጋድሎና በምግባር ሕይወት መኖር ነው፡፡

እግዚአብሔር ራሱ፡- “በደላችሁ በእናንተና በእኔ መካከል አልለየችምን?” ብሎ እንደ ተናገረ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ይለየናል (ኢሳ.59፡2)፡፡ ቅጣት ግን “እግዚኦ አምላክነ ሰላመ ሀበነ እስመ ኵሎ ወሀብከነ - አቤቱ አምላካችን ኹሉን ሰጥተኸናልና ሰላምን ስጠን” እንደ ተባለ ዳግመኛ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ ያደርገናል (ኢሳ.26፡12)፡፡

እንበልና አንድ ሰው ቁስል ወጣበት፡፡ የሚያስፈራው የትኛው ነው - የሚሰፋው ቁስል ወይስ የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ቢላ? ብረቱ ወይስ እጅግ እየባሰበት ያለው ቁስል? ኃጢአት የሚሰፋ ቁስል (Gangrene) ነው፤ ቅጣት ደግሞ የቀዶ ጥገናው ሐኪም ቢላ ነው፡፡ ያልፈረጠ የሚሰፋ ቁስል ያለው ሰው ሕመሙ እንዳለበትና ለወደፊቱም የማያፈርጠው ከኾነ ሥቃዩ እየባሰበት እንደሚኼድ ኹሉ፥ ቅጣት ያላገኘው ኃጢአተኛ ሰውም ከሰዎች ኹሉ ይልቅ ጎስቋላው ሰው እርሱ ነው፤ ለወደፊቱ ጭራሽ ቅጣትና መከራ የማያገኘው ከኾነ ደግሞ ከአሁኑ ይልቅ እጅግ ጎስቋላው ሰው እርሱ ነው፡፡ የጣፊያ ወይም የሆድ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ብዙ መብል ቢበሉ፣ ቀዝቃዛ መጠጦችን ቢጠጡ፣ የተለያዩ ዓይነት ጣፋጭና ቅመማ ቅመም የበዛባቸው መብሎችንም ቢወስዱ ይህ ድሎት ሕመማቸው እንደሚጨምረውና እንደ ሕክምናው ሕግ ራሳቸውን ከመብሉም ከመጠጡም በመጠኑ ቢወስዱ ግን የመዳን ተስፋ ሊኖራቸው እንደሚችል ኹሉ፥ በክፋት ዓዘቅት የሚኖሩ ሰዎችም ቅጣት ካገኛቸው በጎ ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል፤ ከክፋታቸው ጋር አብረው ዝንጋዔንና ድሎትን የሚጨምሩበት ከኾነ ግን ሆዳቸውን ከሚያማቸው ሰዎች በላይ እጅግ ጐስቋሎች ሰዎች ናቸው - ደዌ ዘነፍስ ከደዌ ዘሥጋ ይልቅ የከፋ ነውና፡፡ ተመሳሳይ ኃጢአት እያላቸው አንዳንዶቹ በማጣትና በብዙ ሕመም ሲሠቃዩ፣ ሌሎቹ ግን እስኪበቃቸው ድረስ እየጠጡና እየተስገበገቡ የሚበሉ እየተመቻቸውም በደስታ የሚኖሩ ሰዎችን ብትመለከት እነዚያ መከራ የሚቀበሉት የተሻሉ እንደ ኾኑ አስተውል፡፡ በእነዚህ መከራዎች የተወገደላቸው የፈንጠዝያ ሕይወት እሳት ብቻ ሳይኾን ሊመጣ ወዳለው ፍርድና አስፈሪ ዙፋን ሲኼዱም ከቀላል ዕረፍት ጋር አይደለምና፤ ስለኾነም እዚያ ሲኼዱ ከኃጢአታቸው የሚበዛውን በዚህ ዓለም ባገኛቸው ሥቃይ አስወግደው ነው፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ወንድሞቼ!
ከእናንተ መካከል አንድ አይነ ሥውር ሰው ወደ ጉድጓድ ገብቶ ሊወድቅ ሲል እጁን ዘርግቶ የማይደግፈው ማን ነው? ታድያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በልቡናቸው ታውረው ወደ ሲዖል ጉድጓድ ለዘለዓለም ሲወድቁ እንደ ምን እጃችንን የበለጠ አይዘረጋም?ወገኖቼ!በነፍስም በሥጋም የታመመ ሰውን ስታዩ "ይህ የእኔ ሥራ አይደለም: የቀሳውስትና የመነኮሳት ሥራ እንጂ፡፡ ምክንያቱም ሚስት አለችኝ: ልጆችንም አሳድጋለሁ" አትበሉ፡፡

እስኪ ምሳሌ መስዬ ልጠይቃችሁ እናንተም መልሱልኝ፡፡ አንድ ትልቅ በወርቅ የተሞላ ሳጥን ወድቆ ብታዩ "ይህ እኔን አይመለከተኝም፡ ሌሎች መጥተው ያንሡት እንጂ" ትላላችሁን? ግራ ቀኛችሁን አይታችሁ በፍጥነት የምታነሡት አይደለምን?

ይህ ወደ ዘለዓለም ጉድጓድ እየወደቀ ያለው ወንድማችሁም ከዚያ ወርቅ በላይ ውድ የእግዚአብሔር ሀብት ነውና አንሡት እንጂ የበለጠ  እንዲወድቅ አትግፋት፡፡ እግዚአብሔር ይህን በተመለከተ በአፈ ያዕቆብ እንዲህ ብሏልና፡- "ወንድሞቻችን ሆይ! ከእናንተ ወገን ከጽድቅ ወጥቶ የበደለ ቢኖር መክሮ አስተምሮ ከበደሉ የመለሰው ቢኖር ራሱን አንድም ወንድሙን ከሞት እንዳዳነ ይወቅ፡፡ የራሱን አንድም የወንድሙን ብዙ ኃጢአቱን እንዳስተሠረየ ይወቅ፡፡ አንድም የወንድሙን ነፍስ እንዳዳነ ይወቅ"(ያዕ.5:19-20)፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

@beteafework    @beteafework
@beteafework    @beteafework
@beteafework    @beteafework
#የንጉሥ_ግብዣ_አለ_ተጠርተሃል_እንዳትቀር

ወደ ቤተክርስቲያን አዘውትራችሁ የምትመጡ ይህን ልመናዬን ስሙ፤ ሰነፍ የኾኑትን ወደ ቤተ ክርስቲያን የመሄድን አስፈላጊነት አስተምሯቸው፡፡ የትምህርቷን ውበት ቀምሳችኋልና እናንተ ያወቃችሁትን ሳያውቁ እንዳይቀሩ፡፡

ቤተክርስቲያን ሀኪም ቤት እንጂ የነፍስ ፍርድ ቤት አይደለችም። የኃጢአትን ስርዬት ትሰጣለች እንጂ ኃጢአትን አትፈርድም፡፡

በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደምናገኘው ምስጋና በሕይወታችን ውስጥ እንደዚህ ያለ አስደሳች ነገር የለም፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ደስተኞች ደስታቸው ይበዛላቸዋል፡፡ የሚጨነቁት፤ ያዘኑት፣ ሰላምን ያገኛሉ፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ፤ የተቸገሩ ሰዎች እፎይታ ያገኛሉ፤ ኹሉም ከተሸከሙት ያርፋሉ፡፡

ቤተክርስቲያን ኹሉን ታቅፋለች፡፡ ውስጥ ከሆንክ ተኩላው አይገባም፣ ብትሄድ ግን አራዊቶች ይይዙሃል፡፡ ከቤተክርስቲያን አትራቅ፣ ከቤተክርስቲያን የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። ቤተክርስቲያን ተስፋህ ናት፡፡ ቤተክርስቲያን መዳንህ ናት፡፡ ቤተክርስቲያን ከሰማያት ከፍ ትላለች፡፡ ቤተክርስቲያን ከድንጋይ ትከብዳለች፡፡ ቤተክርስቲያን ከአለም ትስፋለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን አታረጅም፣ ነገር ግን ሁልጊዜ እራሷን ታድሳለች፡፡

"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ በመከራና በኃጢአታችሁ የከበደ ኹሉ' ወደ እኔ ኑ" ይላል እግዚአብሔር፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡" (ማቴ ፲፩፥፳፰)

ይህንን ድምጽ ከመስማት የበለጠ ምን ደስታን ሊሰጠን ይችላል? ከዚህ ግብዣ የበለጠ ጣፋጭ ምንድነው? ጌታ ወደ ቤተክርስቲያን የሚጠራችሁ ለታላቅ ግብዣ ነው፡፡ ከትግል ወደ እረፍት፣ ከስቃይ ወደ እፎይታ ያሸጋግራችኋል፡፡ ከኃጢአታችሁ ሸክም ያገላግላችኋል፡፡ ጭንቀትን በምስጋና፣ ሀዘንንም በደስታ ይፈውሳል፡፡

ለክርስቶስ ከሚኖረው በቀር በእውነት ነጻ፣ በእውነት ደስተኛ የሆነ ማን ነው? እንዲህ ያለው ሰው ክፋትን ኹሉ ያሸንፋል ምንም አይፈራም!

ቤተ ክርስቲያን ለኹሉም መጠጊያ ሆና ቆማለች፡፡ የአምላክን ትዕዛዝ የምትፈጽም መልካም ሰው ከሆንክ ቅድስናህን ለመጠበቅ ግባ፤ ኃጢአተኛ ከሆንህ መዳንን ለማግኘት እርምጃህን ፈጠን አድርገው:: የቤተክርስቲያንን ትምህርት ሳይሰሙስ እንዴት ነፍስን ወደ መልካም መንገድ መምራት ይቻላል?

የእግዚአብሔር ቃል 'ብርሃን' በመባል ይጠራል፤ ፀሐይ ከምታፈልቀውና እኛም ከምናየው ብርሃን፣ እጅግ በጣም የከበረ ብርሃን፣ የነፍሳችንን ጥልቀት የሚያበራ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ እውነት እንዲህ ሲል መስክሯል፣ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው::"

ከእናንተ መካከል በታማኝነት ቤተ ክርስቲያን የምታገለግሉ፤ 'ስራ በዛብኝ፣ ልመጣ አልችልም' እንዳይሉ ሌሎቹን ምከሩ፡፡ ወደ ንጉሱ ግብዣ የተጋበዙ ግን መምጣት ያልቻሉትን እንደ ምሳሌ እንመልከት፡፡ አንደኛው አምስት ጥማድ በሬዎችን ሊገዛ እንደሄደ ተናገረ፣ ሌላው አዲስ መሬትን ሊገዛ እንደሄደ ሲናገር ሌላው ደግሞ ሚስት ማግባቱን ተናገረ፡፡ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ ንጉሡ ግብዣውን ንቀው ስለቀሩ የሚታገሳቸው ይመስልሃል? እናም ንጉሡን በሰበብ አስባቡ አታናዱት፡፡

ከጊዜህ ላይ አንድ ሰዓት ያህል እንኳን መቆጠብ ያቅትሃል? ቤተክርስቲያንን ከተሳለሙ በኋላ ወደ ሥራ መሄድ በእውነት ይህን ያህል ከባድ ነውን? አንድ ሰው ወርቅ፣ ብር፣ ማር ወይም ወይን በነጻ እየሰጠ ነው ቢባል፤ ማንም ሳይቀድማችሁ ለመድረስ አትቸኩልም? ነገር ግን፣ ከወርቅ የሚበልጥ፣ ከማርም ከወተትም የሚጣፍጠውን የእግዚአብሔርን ቃል ለማድመጥ ወደ ቤተክርስቲያን የምትመጡት አልፎ አልፎ ነው፡፡

ስለዚህም፣ ይህን ችላ ማለታችሁን አውግዣለሁ፤ ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ያላችሁን ግድየለሽነት እቃወማለሁ፡፡ ከመንፈሳዊ ትምህርቶቿ በመራቃችሁ፣ በውስጣችሁ የእግዚአብሔር ፍራቻ የለም፤ እግዚአብሔርን የማትፈራ ነፍስም ለኃጢአት የተገዛች ትሆናለችና ነፍሳችንን እንጠብቃት፡፡

(#የነፍስ_ምግብ
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ እንዳስተማረው - ገጽ 105-107)

@beteafework        @beteafework
@beteafework        @beteafework
#ኃጢአትህን_ኹሉ_በዲያብሎስ_ላይ_አታሳብብ

በንስሐ ተስፋ ከቆረጥክ ዲያብሎስ ይወድሃል፡፡ ግን እርሱ እንዲረካ አታድርግ፡፡ ለድኅነት ቀንም ሁሌም ዝግጁ ሁን፡፡

እነዚህን ኹሉ የተናገርኩት ዲያብሎስን ከነቀፋ ነፃ ለማውጣት ሳይሆን እናንተን ከስንፍና ነፃ ለማውጣት ነው፡፡ ኃጢአታችንን ኹሉ በእርሱ እንዳናሳብብ በእውነት ይስፈልጋል፤ ለሁሉም ክፋታችን ሰይጣንን ተጠያቂ የምናደርግ ከሆነም የራሳችንን ቅጣት እንጨምራለን፤ ጉዳዩን ኹሉ ወደ እርሱ ስላስተላለፍንም ይቅርታ አናገኝም - ልክ ሄዋን ይቅርታን እንዳላገኘች ሁሉ፡፡

ግን ይህን አናድርግ፡፡ እራሳችንን እንወቅ፡፡ ቁስላችንን እንወቅ። ከዚያም መድኃኒቶቹን ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን፤ ደዌውን የማያውቅ ሰው፣ ድካሙን አይፈውስምና፡፡

ብዙ ኃጢአት ሠርተናል፤ ይህን በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ሁላችንም ቅጣት ይገባናል፡፡ እኛ ግን ያለ ይቅርታ አይደለንም፣ ከንስሐ አንቀርም፤ አሁንም በአደባባይ ቆመናል፤ በንስሐም ተጋድሎ ውስጥ ነን፡

አርጅተኻል እና በመጨረሻው የሕይወት ደረጃ ላይ ነህ? አሁን እንኳን ከንስሐ እንደወደቅክ አታስብ፡፡ በራስህ መዳን ተስፋ አትቁረጥ፤ በመስቀል ላይ ነፃ የወጣውን ዘራፊ አስብ፡፡ እርሱ ዘውድ ከተቀዳጀበት ጊዜ የበለጠ ምን አጭር ነገር አለ? ያም ሆኖ ይህ ለእርሱ መዳን በቂ ነበር፡

ወጣት ነህ? በወጣትነትህ አትተማመን፣ ከፊትህ ረዥም ጊዜም እንዳለ አታስብ “የእግዚአብሔር ቀን እንደ ሌባ በሌሊት ይመጣልና" (፩ኛ ተሰ. ፭፣፪) ለዚህም ነው ፍጻሜያችንን የማይታይ ያደረገው፣ ተግተን እንድንጸና።

ማንም ኃጢያተኛ ሊያደርግህ አይችልም ይላል አቡነ ቴዎድሮስ - ዲያብሎስም ቢሆን፡፡ ለኃጢአት የመስማማት ወይም የመቃወም ኃይል ያለው በአንተ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

አሁን እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ክፋት እንዲሆን የፈቀደ እንደሆነ አልያም በሌላ ምክንያት እንደሆነ እንመርምር።

በስንፍና በልቡም ምኞት ወደ ራሱ ኃጢአትን ከሚያስገባ ሰው በቀር፣ ኃጢአት በማንም ላይ ሊጫን አይችልም፡፡ ፈቃደኛ ባልሆነው እና ኃጢአትን በሚቃወመው ሰው ላይ ዲያብሎስ ኃይል የለውምና፡፡

ዲያብሎስ በኢዮብ ላይ ይህን የኃጢአት ክፋት ለመጫን የክፋት ዘዴውን ኹሉ ከተጠቀመ በኋላ ዓለማዊ ንብረቱን ኹሉ ገፍፎት፣ በሞት ሰባቱን ልጆቹን ነጥቆት፣ ከጭንቅላቱ ፀጉር እስከ እግሩ ጥፍር ድረስ የሚያስፈሩ ቁስሎችን፣ የማያባሩ ስቃዮችን ከሰጠው በኋላ የኃጢአት እድፍ በኢዮብ ላይ እንዲጣበቅ ለማድረግ በከንቱ ሞከረ፤ ኢዮብ በዚህ ኹሉ ጸንቶአልና፤ ከቶ አምላኩን ለመሳደብ ፍቃደኛ አልነበረም።

(የነፍስ ምግብ - #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ እንዳስተማረው ገጽ 80-82 #በፍሉይ_ዓለም የተተረጎመ)
የንጉሥ ሥልጣን በሥጋ ላይ ነው፤ የካህን ሥልጣን ግን በነፍስ ላይ ነው፡፡

ንጉሥ ይቅር ቢል የገንዘብን ዕዳ ነው፤ ካህን ይቅር ሲል ግን የበደል የኃጢአት ዕዳን ነው፡፡

ንጉሥ ያዝዛል፤ ካህን ግን ያስተምራል ይዘክራል። ንጉሥ ያስገድዳል፤ ካህን ግን ነጻ ፈቃድን ያያል፡፡

ንጉሥ ቁሳዊ የጦር ዕቃ መሣሪያ አለው፤ ካህን ግን ረቂቅ (መንፈሳዊ) የጦር ዕቃ መሣሪያ አለው፡፡

ንጉሥ የጦር ዕቃ መሣሪያውን ቢሰብቅ አንገዛም ብለው ባመፁት (እንዲሁም ከወራሪዎች፣ ሥጋውያን ደማውያን) ላይ ነው፤ ካህን ግን ውጊያው ከጨለማ አበጋዞች ከአጋንንት ጋር ነው፡፡

ስለዚህ ሥልጣነ ክህነት ከሥልጣነ መንግሥት ይበልጣል፡፡ እንዲህም በመኾኑ ንጉሥ አንገቱን ለካህናት እጅ ያጎነብሳል፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ፣ ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ድርሳን ፬ በተረጎመበት ድርሳኑ)

@beteafework        @beteafework
@beteafework        @beteafework
ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ብነግራችኁ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

ጾመ ሐዋርያት (ሰኔ ጸም) ነገ ሰኔ 17/2016 ዓ.ም
(JUNE 23/2024 G.C) ይገባል፡፡

@beteafework         @beteafework
@beteafework         @beteafework
@beteafework         @beteafework
ይህን ያህል ቀን ጾምኩ አትበሉኝ፡፡ ይህን አልበላሁም ወይም ያንን አልበላሁም፣ የወይን ጠጅ አልጠጣሁም አትበሉኝ።

ይልቁንስ ከግልፍተኝነት ወደ ገርነት፣ ከጭካኔ ወደ ደግነት የተሸጋገርኽ እንደሆነ አሳየኝ፡፡ በአንተ ውስጥ ጥላቻና ቂም ቢኖሩ፣ በወይን ፋንታ ውኃ ብትጠጣ ምን ይጠቅማል? ጾም ብቻውን ስማያዊ ምንዳ አያስገኝምና፤ ትርጉም በሌለው በባዶ የፆም ሥርአት ራስህን አታስገዛ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

@beteafework    @beteafework
@beteafework    @beteafework
"አንተ ራስህ ለገዛ ወንድምህ ጨካኝና ይቅር የማትል ኾነህ ሳለስ እግዚአብሔር እንዲራራልህና እንዲምርህ እንዴት መለመን ይቻልሃል?

"ባልንጀራህ ምናልባት ንቆህ ሊኾን ይችላል፡፡ አዎ! አንተ ግን እግዚአብሔርን ኹልጊዜ እንደናቅኸው ነው፡፡ በባልንጀራና በእግዚአብሔር መካከልስ ምን ንጽጽር አለ? ባልንጀራህ ምናልባት ጉዳት ሲደርስበት ሰድቦህ ይኾናል፤ አንተም በዚህ ተበሳጭተህ ይኾናል፡፡ አንተ ግን ምንም ሳይጎዳህና በአንተ ላይ ክፉ ሳያስብ ይልቁንም ዕለት ዕለት በረከቱን እየተቀበልክ እያለ እግዚአብሔርን ሰድበኸዋል፡፡ እንግዲህ ተመልከት! ነቢዩ፡- “እመሰ ኃጢአተኑ ትትዐቀብ እግዚኦ መኑ ይቀውም - አቤቱ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ ማን ይቆማል?” ብሎ እንደ ተናገረ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የምንፈጽመውን በደል ቢመረምር ኖሮ አንዲት ቀንስ እንኳን በሕይወት መቆየት አንችልም ነበር (መዝ.129፡3)፡፡

እያንዳንዱ በደለኛ ሰው ለራሱ የሚያውቀውንና ሌላ ሰው የማይመሰክርበትን እግዚአብሔር ብቻዉን ግን የሚያውቀውንስ ይቅርና የተገለጠውና ሰው ኹሉ የሚያውቀው ኃጢአታችንን እንኳን እግዚአብሔር ቢቈጣጠር ኖሮ ከእነዚህ ኃጢአቶች በኋላ የምንጠብቀው ምንድን ነው? እግዚአብሔር ንዝህላልነታችንንና ጸሎት ስናደርስ የምናሳየው ግድየለሽነታችንን፣ ሠራተኞች ለአሠሪዎቻቸው ወታደሮችም ለአለቆቻቸው ጓደኛሞች ለጓደኞቻቸው የሚያሳዩትን ፍርሐትና ክብር ያህልስ እንኳን ለጸሎትና ለልመና በፊቱ በቆምን ጊዜ አለማሳየታችንን ቢቈጣጠር ኖሮ ምን ነበር የምንኾነው?

አንተ ከጓደኛህ ጋር ስትነጋገር ለምታደርገው ማንኛውም ነገር ትጠነቀቃለህ፡፡ ስለ በደሎችህ እግዚአብሔርን ስትጠብቀው፣ ለብዙ መተላለፎችህ ይቅርታን ስትጠይቀው፣ ሥርየትን ለማግኘት ስታሳስበው ግን [በፊቱ ላይ] ኹልጊዜ ግድየለሽ ትኾናለህ፡፡ ጉልበትህ በምድር ላይ ተንበርክኮ ሳለ ልቡናህ ግን እዚህም እዚያም፣ በገበያ ሥፍራም፣ በቤት ውስጥም ይዋልላል፤ ከንፈርህ በከንቱና እንዲሁ ያነበንባል፤ ይህን የምንፈጽመው ደግሞ አንዴ ወይም ኹለቴ ሳይኾን ኹልጊዜ ነው።

እንግዲህ እግዚአብሔር ይህን ብቻ እንኳን ቢመረምር ይቅርታን ወይም ምሕረትን እንደምናገኝ ታስባለህን? በእውነት አይመስለኝም!"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

#ትምህርት_በእንተ_ሐውልታት_መጽሐፍ
ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው
አንተ ሰው ቃለ እግዚአብሔርን ተማር፤ ባትለወጥም ዝም ብለህ ተማር! ኹልጊዜ ተማር። ላትስተካከል ትችላለህ፤ ላትለወጥ ትችላለህ፤ ግን ተማር። ቢያንስ ቢያንስ ጥሩ ሰው እንኳን ባትኾን ራስህን ለመውቀስ የምትችልበት ዓቅም ታገኛለህ። ካልተማርክ ግን ራስህን እንኳን መውቀስ የምትችልበት ዓቅም አታገኝም። ስለዚህ ተማር! ስትማር ቢያንስ ኃጢአት እንኳን ስትሠራ ራስህን እየወቀስክ ትሠራለህ። ይህች የንስሓ በር ትኾንልሃለች፡፡ አንድ ቀን ወደ ንስሓም ትመራሃለች።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ተወዳጆች ሆይ! አንድ እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ ቤታችንን እንደምን እንደምናሰናዳው ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ሁላችንም እንግዳችንን ደስ የሚያሰኘው ነገር ለማድረግ የምንቻኰል አይደለንምን? ለእንግዳችን የሆነ ነገር ባናደርግለት፥ እንግዳችን በመምጣቱ ደስ ተሰኝተን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ባናደርግለት፥ ግን ደግሞ በመምጣቱ ደስ እንደተሰኘን ብንነግረው እንግዳችን በፍጹም አያምነንም፡፡ በእንግዳችን መምጣት ደስ እንደተሰኘን ከቃላት ባለፈ በገቢር መግለጥ አለብንና፡፡ እንኪያስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን ከመጣ ደስ መሰኘታችንን በገቢር ልንገልጽ ያስፈልጋል፡፡ እንግዳችን ክርስቶስን የሚያስቈጣ ነገር ልንፈጽም አይገባንም፡፡

እንግዳ ሲመጣ ቆሻሻ ልብስ አይለበስም፡፡ እንግዳ ሲመጣ የሚያስጸይፍ ነገር አይነገርም፡፡ ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ስንፈልግም ቆሻሻ ልብሳችንን (ማንነታችንን) አውልቀን ልንጥል ያስፈልጋል፤ አስጸያፊ ነገራችንን ልንተው ያስፈልጋል፡፡ እንግዳ ሲመጣ ቤት ያፈራው ሁሉ ይቀርብለታል፡፡ ክርስቶስ ወደ ቤታችን ሲመጣም የሚበላ ነገር ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለመሆኑ የክርስቶስ መብል ምንድነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጥያቄ ሲመልስልን እንዲህ ብሏል፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ዮሐ.፬፡፴፬፡፡

እንኪያስ ክርስቶስ የራበው ይኸው ነውና እንመግበው፤ ኢየሱስ የጠማው ይኸው ነውና እናጠጣው፡፡ እርሱም ይቀበለናል፡፡ አንዲት ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ብንሰጠው እንኳ ይቀበለናል፡፡ ስለብዛቱ ሳይሆን ስለፍቅሩ ብሎ ይቀበለናል፡፡ እኛን ስለመውደዱ ይቀበለናል፡፡ የምንወደው ሰው የሰጠነውን የሚቀበለን ስለ መጠኑ አይደለም፤ ስጦታው የወዳጅ ስለሆነበት እንጂ፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ሁለት ሳንቲም ብንሰጥ እንኳ ብዙ እንደሰጠን አድርጐ ይቀበለናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታችንን የሚቀበለው ድሃ ስለሆነ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድሃውም የባለጸጋውም ስጦታ እኩል የሚቀበለው ስለ ልቡናችን ኀልዮት (Intention) እንጂ ስለ ስጦታው ትልቅነት ወይም ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን እንደምንወደው ለመግለጽ የግድ ብዙ ወይም በውድ ዋጋ የተገዛን ስጦታ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ስጦታችን እርሱ ወደ እኛ ስለመጣ ደስ የመሰኘታችን መግለጫ ነውና ስለ ስጦታችን መጠን ልንመለከት አይገባም፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ)

@beteafework   @beteafework
@beteafework   @beteafework