ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
35.6K subscribers
908 photos
16 videos
16 files
721 links
በዚህ ቻናል የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች እና የአበው ቀደምት የተናገሯቸው መንፈሳዊ ንግግሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ ትምህርቶችና መልዕክቶች ይተላለፉበታል፡፡
Download Telegram
አንተ ሰው ቃለ እግዚአብሔርን ተማር፤ ባትለወጥም ዝም ብለህ ተማር! ኹልጊዜ ተማር። ላትስተካከል ትችላለህ፤ ላትለወጥ ትችላለህ፤ ግን ተማር። ቢያንስ ቢያንስ ጥሩ ሰው እንኳን ባትኾን ራስህን ለመውቀስ የምትችልበት ዓቅም ታገኛለህ። ካልተማርክ ግን ራስህን እንኳን መውቀስ የምትችልበት ዓቅም አታገኝም። ስለዚህ ተማር! ስትማር ቢያንስ ኃጢአት እንኳን ስትሠራ ራስህን እየወቀስክ ትሠራለህ። ይህች የንስሓ በር ትኾንልሃለች፡፡ አንድ ቀን ወደ ንስሓም ትመራሃለች።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ተወዳጆች ሆይ! አንድ እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ ቤታችንን እንደምን እንደምናሰናዳው ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ሁላችንም እንግዳችንን ደስ የሚያሰኘው ነገር ለማድረግ የምንቻኰል አይደለንምን? ለእንግዳችን የሆነ ነገር ባናደርግለት፥ እንግዳችን በመምጣቱ ደስ ተሰኝተን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ባናደርግለት፥ ግን ደግሞ በመምጣቱ ደስ እንደተሰኘን ብንነግረው እንግዳችን በፍጹም አያምነንም፡፡ በእንግዳችን መምጣት ደስ እንደተሰኘን ከቃላት ባለፈ በገቢር መግለጥ አለብንና፡፡ እንኪያስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን ከመጣ ደስ መሰኘታችንን በገቢር ልንገልጽ ያስፈልጋል፡፡ እንግዳችን ክርስቶስን የሚያስቈጣ ነገር ልንፈጽም አይገባንም፡፡

እንግዳ ሲመጣ ቆሻሻ ልብስ አይለበስም፡፡ እንግዳ ሲመጣ የሚያስጸይፍ ነገር አይነገርም፡፡ ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ስንፈልግም ቆሻሻ ልብሳችንን (ማንነታችንን) አውልቀን ልንጥል ያስፈልጋል፤ አስጸያፊ ነገራችንን ልንተው ያስፈልጋል፡፡ እንግዳ ሲመጣ ቤት ያፈራው ሁሉ ይቀርብለታል፡፡ ክርስቶስ ወደ ቤታችን ሲመጣም የሚበላ ነገር ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለመሆኑ የክርስቶስ መብል ምንድነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጥያቄ ሲመልስልን እንዲህ ብሏል፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ዮሐ.፬፡፴፬፡፡

እንኪያስ ክርስቶስ የራበው ይኸው ነውና እንመግበው፤ ኢየሱስ የጠማው ይኸው ነውና እናጠጣው፡፡ እርሱም ይቀበለናል፡፡ አንዲት ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ብንሰጠው እንኳ ይቀበለናል፡፡ ስለብዛቱ ሳይሆን ስለፍቅሩ ብሎ ይቀበለናል፡፡ እኛን ስለመውደዱ ይቀበለናል፡፡ የምንወደው ሰው የሰጠነውን የሚቀበለን ስለ መጠኑ አይደለም፤ ስጦታው የወዳጅ ስለሆነበት እንጂ፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ሁለት ሳንቲም ብንሰጥ እንኳ ብዙ እንደሰጠን አድርጐ ይቀበለናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታችንን የሚቀበለው ድሃ ስለሆነ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድሃውም የባለጸጋውም ስጦታ እኩል የሚቀበለው ስለ ልቡናችን ኀልዮት (Intention) እንጂ ስለ ስጦታው ትልቅነት ወይም ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን እንደምንወደው ለመግለጽ የግድ ብዙ ወይም በውድ ዋጋ የተገዛን ስጦታ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ስጦታችን እርሱ ወደ እኛ ስለመጣ ደስ የመሰኘታችን መግለጫ ነውና ስለ ስጦታችን መጠን ልንመለከት አይገባም፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ)

@beteafework   @beteafework
@beteafework   @beteafework
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
መልካም ምግባር ሰዎች እንዲያዩልን ብለን አናድርግ፡፡ ብንጾምም፣ ብንመጸውትም፣ ብንጸልይም፣ ሌላም በጎ ምግባር ብናደርግ የተገለጠውንም የተሰወረውንም ሁሉ ለሚያውቅ እግዚአብሔር ብለን የማናደርገው ከሆነ ከሰዎች አንዳች ጥቅም አያስገኝልንም፡፡ እንዲህ በማድረጋችን ሰዎች ቢያመሰግኑን እየጎዱን እንደሆነ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡

እንዲህ ከሆነ ታድያ ለምንድነው ሰዎች እንዲጎዱን ምቹ ሁኔታዎችን የምንፈጥርላቸው? ትክክለኛ ማንነታችን የሚያውቀው፣ የዘለዓለምን ሹመት ሽልማታችንን የሚሰጠን እግዚአብሔር አይደለምን? ታድያ ለምንድነው ጥቅም ከማይሰጠን ይልቁንም ከሚጎዳን አካል ውዳሴን የምንጠብቀው? ስለዚህ በቃላችንም፣ በግብራችንም፣ በሐሳባችንም እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ ልናሰኝ አይገባንም እላችኋለሁ፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ)
ሰውን የሚያረክሱትን ነገሮች የትኛዎቹ እንደኾኑ እንረዳ እና አንዴ ከተረዳንም በኋላ እንራቃቸው፡: በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች የውጫቸው ንጹህ ኾኖ መታየት እንደሚያሳስባቸው እናያለን፤ ነገር ግን ስለ ንጹህ ልብስ እንጂ በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ ልባቸውን ስለማቅረብ አያስቡም፡፡ እጃችሁን ወይም አፋችሁን አትታጠቡ እያልኩ አይደለም ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ በመልካም ተግባርና በጎነት ብትታጠቡ ይሻላል፡፡

ስለሌሎች መጥፎ መናገር፤ ጸያፍ ቋንቋ መጠቀም፤ ተገቢ ባልኾኑ ቀልዶች መሳቅ እነዚህ ነገሮች ልብን ያቆሽሹታል፡፡ እንግዲያው፣ ከእነዚህ ነገሮች አንዱንም ካላደረጋችሁ፤ በቅን ልብ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ትችላላችሁ፡፡ እነዚህን ነገሮች ካደረጋችሁ ግን ጸሎታችሁ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ርኩሰት የተሸከመ ምላስህንም በውኃ ማጠብህ ትርጉም አይኖረውም።

ይህን አስቡ በእጃችሁ ላይ ጭቃ ወይም እበት ቢኖርባችሁ ለመጸለይ ትደፍራላችሁ? በጭራሽ። ነገር ግን የእጅ መቆሸሽ ከልብ መቆሸሽ በላይ የሚያጸይፍ መሆን የለበትም፡፡ ለምንድነው አላስፈላጊ ለኾኑ ነገሮች ትኩረት የምትሰጡት እና አስፈላጊ የኾኑትን ችላ የምትሉት? “አትጸልዩ ነው ወይ የምትለን" ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። አይ፤ መጸለያችሁን ማቆም የለባችሁም፣ ግን በዚህ ቆሻሻ ሁኔታ ውስጥ መሆን የለበትም፡፡

“ሳላውቅ ኃጢአትን ብሰራ፣ ስህተት ካደረኩ ምን ማድረግ አለብኝ?" እራስህን አጽዳ፡፡ እንዴት? ተጸጸት፣ ለድሆች ስጥ፣ የሰደብከውን ስው ይቅርታ ጠይቅ፣ የበደሉህንም ይቅርታ አድርግላቸው፡፡ እግዚአብሔርን አብዝተህ እንዳታስቆጣ አንደበትህን አጽዳ፡፡

በእጆቹ ጭቃ የያዘ ሰው እግርህን ቢይዝና ገንዘብ ቢጠይቅህ፣ አትሰማውም፤ እንዲያውም ልትገፋው ትችላለህ፡፡ ታዲያ ለምን በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር ትቀርባለህ? የሚጸልዩ ሰዎች አንደበት የእግዚአብሔርን ጉልበት እንደሚነካ እጅ ነው፡፡ ስለዚህ አንደበታችሁን አታርክሱ፣ አለዚያ እግዚአብሔር ጸሎታችሁን አልሰማም ይላል፡፡ አንደበት የሕይወትና የሞት ኃይል አለው። ቃላትህ ሊያጸድቁህ ወይም ሊያስኮንኑህም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ምላስህን ከዓይኖችህ የበለጠ በጥንቃቄ ጠብቅ።

አንደበት ለንጉሥ እንደ ፈረስ ነው፤ በእርሱም ላይ ልጓም ቢደረግበት፣ ከተቆጣጠሩት እና ከገሩት ለንጉሡ የታመነ ይኾናል፡፡ ነገር ግን እንዲሁ እንዲሮጥ ከፈቀድክ የዲያብሎስ መሳሪያ ይሆናል፡፡ አንደበትህን አታርክሰው፣ በየዋህነት እና በትህትናም አስጊጠው::

ለእግዚአብሔር የሚገባውን አድርጉ፣ አንደበታችሁ በመልካም ቃላት ይሞሉ፤ መልካም ቃል ከስጦታ ይሻላልና፡፡ ለድሆች በደግነትና በቅንነት መልሱ፡፡ የቀረውን ጊዚያችሁን ስለ እግዚአብሔር ሕግጋትና ትምህርቶች በማሰብ አሳልፉ፡፡ ንግግሮቻችሁ ኹሉ በልዑል እግዚአብሔር ህግጋት የተገሩ ይሁኑ፡፡ ራሳችንን አስጊጠን ወደ ንጉሡ እንውጣና በእግሩ ሥር እንውደቅ፣ በአካል ብቻ ሳይኾን በአዕምሯችንም፡፡ ወደ ማን እንደምንሄድ፣ ለምን ዓላማ እና ምን ማከናወን እንደምንፈልግ እንመርምር፡፡ ሱራፌልና ኪሩቤል በዓይናቸው የማያዩት፤ ግርማውን መሸከም ያቃታቸው፣ መዳረሻ አልባ ብርሃን ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር እንሄዳለን፡፡ ከገሃነም ለማምለጥ፤ ለኃጢአታችን ይቅርታ ለመጠየቅ፤ ከቅጣት ለመራቅ እና ወደ መንግሥተ ሰማያት (እና በረከቶቿ ኹሉ) ለመግባት ወደ እርሱ እንሄዳለን፡፡

ምንጭ፦
(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ - #የነፍስ_ምግብ ገጽ 60-62 #በፍሉይ_ዓለም_የተተረጎመ)

@beteafework    @beteafework
@beteafework    @beteafework
እንደ ጋኔን ቅናተኛ የለም፡፡ ቅናቱ ግን በሰው ልጆች ላይ እንጂ እርሱን በሚመስሉ አጋንንት ላይ አይደለም፡፡ ሰው ግን በገዛ ወንድሙ ላይ ይቀናል፤ በአጋንንት እንኳን በጭራሽ የማይደረግ በገዛ ቤተሰቡ ላይ ይቀናል፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ሰው እንዴት ይቅርታን ያገኛል? እንዴት ምሕረት ቸርነትን ያገኛል?

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ልንናደድ_የሚገባን_ማን_ላይ_ነው?

ብዙ ኃጢአቶችንና ወንጀሎችን የሠራ አንድ ሰው ለሠራው ኃጢአትና ወንጀል ሳይቀጣ ሲቀር አይተን ብዙዎቻችን እንበሳጫለን፡፡ ያ ሰው እንዲጠየቅና እንዲቀጣ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሳይኾን ከቀረ ግን ቅር እንሰኛለን፤ እንናደዳለን፡፡

እንዲህ የምንኾነው ግን የገዛ ራሳችንን ግብር ስለማንመለከት ነው፡፡ መበሳጨትና መናደድ ቅርም መሰኘት የሚገባን በገዛ ራሳችን ላይ ነውና፡፡ እያንዳንዳችን ለራሳችን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ ይገባናል፦ "በሌሎች ሰዎች ላይ ስንት በደል ፈጸምሁ? ለዚህ በደሌስ ስንቴ ሳልቀጣ ቀረሁ?"

በራሳችን ላይ ብዙ ምሳሌዎችን እንደምናገኝ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህን ማወቃችን ደግሞ በሌሎች ሰዎች ላይ የተቆጣነው ቁጣና የተበሳጨነው ብስጭት እንደ ጢስ ተኖ እንደ ትቢያ በንኖ እንዲጠፋ ያደርጓል፡፡ ከዚህም በላይ ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር እንድናዞር ስለ በደልነውም በደል ይቅርታንና ቸርነትን እንድንለምን ያደርገናል፡፡

እንዲያውም እኛ በበደልነው በደልና ሌሎች ሰዎች በሠሩት ኃጢአት ልዩነቱን እናስተውለው ይኾናል፡፡ ምናልባት የእኛ በደል የተሰወረና ለሌሎች ሰዎች የማይታይ ሕቡዕ ይኾናል፤ በአንጻሩ ደግሞ የሌሎች ሰዎች ኃጢአት በግልጽ የሚታይ ይኾናል፡፡

ታዲያ በዚህ ኹኔታ የእኛ በደል ንኡስ፥ የሌሎች ሰዎች ኃጢአት ግን ዐቢይ እንደ ኾነ ልናስብ ይገባናልን? በጭራሽ! ምክንያቱም በስውር የሚሠ'ራና ሌላ ሰው የማያየው በደል ብዙውን ጊዜ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ስርቆትንና ቀማኛነትን የመሳሰሉ በግልጽ የሚታዩ ኃጢአቶች ኃጢአት መኾናቸው በቀላሉ ይታወቃሉ፡፡ መታወቃቸው ብቻም ሳይኾን በቀላሉ ንስሐ ሊገባባቸውና ሊወገዱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ውሸትን፣ ሐሜትንና በስውር ማታለልን የመሳሰሉ በስዉር የሚሠሩ በደሎች ግን በደል መኾናቸውን ለማወቅም ስለ እነዚህ ንስሐ ገብቶ ለማስወገድም እጅግ ክቡዳን ናቸው፡፡

(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ - አምስቱ የንስሐ መንገዶች ገጽ 98-99)
#እውነተኛ_ወዳጅ፥ ወዳጅ መኾኑ የሚታወቀው ጓደኛውን መገሠጽ ሲችል ነው፡፡ ኹላችንም በየጊዜው ኃጢአት እንሠራለን፡፡ አብዛኞቻችን ደግሞ ኃጢአታችንን እንዳላየነው ኾነን ለማለፍ እንጥራለን፡፡ ለራሳችን ይቅርታ እንቸራለን፡፡ ወይም ምንም እንዳላጠፋ ሰው ለመምሰል እንሞክራለን፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰዓት እውነታውን በትክክል እናይ ዘንድ ዓይናችንን የሚከፍት እውነተኛ ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡

አንተ ሆይ! እስኪ ራስህን መርምር፡፡ ጓደኛህ እውነታውን እንዲያይ ታደርጋለህ? ጓደኛህ ኃጢአት ሠርቶ ሲያበቃ ለራሱ ይቅርታ ሲያደርግ ይቅርታው ያደረገው ይቅርታ ትክክለኛ እንዳልኾነ እንዲያውቅ ታደርጓለህን? እንዲህ እውነታውን ስትነግረው ምናልባት ጓደኛህ አለአግባብ ሊቈጣህ ይችላል፡፡ ታዲያ ሲቈጣህ ለመታገሥ ዝግጁ ነህን? ወይስ ከዚህ በተቃራኒ የጓደኛህን ኃጢአት አይተህ እንዳላየህ ነው የምትኾነው?

ጓደኛ ስንመርጥ ከእኛ ጋር እውነተኛ ወዳጅ ሊኾን የሚገባውን መኾን አለበት፤ ስንቈጣው እንኳን ቁጣችንን ታግሦ ስናጠፋ የሚያርመን ሊኾን ይገባል፡፡ እንደዚህ ካልኾነ ጓደኝነት ጥልቀት አይኖረውምና፤ ጓደኞች ነን መባባላችን ጥቅም የለውምና፡፡

ልናውቀው የሚገባን ነገር ግን አለ፡፡ ጓደኛችን በሚያጠፋበት ሰዓት ተግሣጽ አስመስለን እንዲሁ ክብሩን በሚነካ መልኩ ልንናገረው አይገባንም፡፡ ተግሣጻችን ኹልጊዜ እውነቱን ብቻ እንጂ የተጋነነና ሌላውን መልካምነቱን የሚክድ መኾን የለበትም፡፡ ጥፋቱን ስንነግረው ኹልጊዜ በቀና ልብ እንደምንነግረው እርግጠኛ እንዲኾን ማድረግ አለብን፡፡ ይህን የምናደርገው ከፍቅራችን የተነሣ እንጂ ከቅናት ወይም ከንቀት እንዳልኾነ እንዲያውቅ ማድረግ አለብን፡፡ እውነተኛ ወዳጅነት ማለት ይህ ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
አንድ ነዳይ አጥብቆ እየለመነህ በቸልታ ትተኸው ስትሔድ እግዚአብሔርን አጥብቀህ በምትለምን ጊዜ ቢተውህ የሚሰማህን አስብ።"
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

"ክርስቶስን በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ወድቆ በሚለምነው ነዳይ ውስጥ ካላገኘኸው ውስጥ ገብተህ በመንበሩ ላይ ባለው ጽዋ ላይ አታገኘውም።"
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
እውነተኛ ወዳጅ፥ ወዳጅ መኾኑ የሚታወቀው ጓደኛውን መገሠጽ ሲችል ነው፡፡ ኹላችንም በየጊዜው ኃጢአት እንሠራለን፡፡ አብዛኞቻችን ደግሞ ኃጢአታችንን እንዳላየነው ኾነን ለማለፍ እንጥራለን፡፡ ለራሳችን ይቅርታ እንቸራለን፡፡ ወይም ምንም እንዳላጠፋ ሰው ለመምሰል እንሞክራለን፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰዓት እውነታውን በትክክል እናይ ዘንድ ዓይናችንን የሚከፍት እውነተኛ ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡

አንተ ሆይ! እስኪ ራስህን መርምር፡፡ ጓደኛህ እውነታውን እንዲያይ ታደርጋለህ? ጓደኛህ ኃጢአት ሠርቶ ሲያበቃ ለራሱ ይቅርታ ሲያደርግ ይቅርታው ያደረገው ይቅርታ ትክክለኛ እንዳልኾነ እንዲያውቅ ታደርጓለህን? እንዲህ እውነታውን ስትነግረው ምናልባት ጓደኛህ አለአግባብ ሊቈጣህ ይችላል፡፡ ታዲያ ሲቈጣህ ለመታገሥ ዝግጁ ነህን? ወይስ ከዚህ በተቃራኒ የጓደኛህን ኃጢአት አይተህ እንዳላየህ ነው የምትኾነው?

ጓደኛ ስንመርጥ ከእኛ ጋር እውነተኛ ወዳጅ ሊኾን የሚገባውን መኾን አለበት፤ ስንቈጣው እንኳን ቁጣችንን ታግሦ ስናጠፋ የሚያርመን ሊኾን ይገባል፡፡ እንደዚህ ካልኾነ ጓደኝነት ጥልቀት አይኖረውምና፤ ጓደኞች ነን መባባላችን ጥቅም የለውምና፡፡

ልናውቀው የሚገባን ነገር ግን አለ፡፡ ጓደኛችን በሚያጠፋበት ሰዓት ተግሣጽ አስመስለን እንዲሁ ክብሩን በሚነካ መልኩ ልንናገረው አይገባንም፡፡ ተግሣጻችን ኹልጊዜ እውነቱን ብቻ እንጂ የተጋነነና ሌላውን መልካምነቱን የሚክድ መኾን የለበትም፡፡ ጥፋቱን ስንነግረው ኹልጊዜ በቀና ልብ እንደምንነግረው እርግጠኛ እንዲኾን ማድረግ አለብን፡፡ ይህን የምናደርገው ከፍቅራችን የተነሣ እንጂ ከቅናት ወይም ከንቀት እንዳልኾነ እንዲያውቅ ማድረግ አለብን፡፡ እውነተኛ ወዳጅነት ማለት ይህ ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ