ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ Balderas for Democracy
1.67K subscribers
985 photos
14 videos
3 files
138 links
Political party
Download Telegram
#ሰበር_ዜና
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሆነ!!!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የአገር አቀፍ ፓርቲነት የእውቅና ሠርቲፊኬት ሰጠ፡፡

ባልደራስ ፓርቲ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታቸው በማሟላት የሀገር አቀፍ ፓርቲነት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬትን 27/12/2016 ዓ.ም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረከቡን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የምርጫ ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ- ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 64 1/ሀ መሰረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት ሊመዘገብ የሚችለው አስር ሺህ መስራች አባላት ሲኖሩት እና ከመስራች አባላቱ መካከል 40 ከመቶ  የማይበልጡት የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች ሲሆኑ ነው፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ክልላዊ ፓርቲነት በተመዘገበበት ጊዜ ከአራት ሺሕ በላይ መስራች አባላትን ይዞ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

በአዋጁ መሠረት ባልደራስ ከክልላዊ ፓርተነት ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ለመሸጋገር በአራት ክልልሎች የ #ስድስት_ሺህ መስራች አባላት ፊርማን ማቅረብ ሲገባው፣ ፓርቲያችን ግን በስድስት ተጨማሪ ክልሎች ከ #አስር_ሺህ በላይ የመስራች አባላት ፊርማን በማሰባሰብ በአጠቃላይ ከ14 ሺሕ በላይ የመስራች አባላት ፊርማን በማስገባት የሀገር አቀፍ ፓርቲነት ሰርቲፍኬቱን ተረክቧል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በክልል አቀፍ ፓርቲነት ከተመዘገበበት 21/6/1212 ዓ.ም ጀምሮ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ እንዲመዘገብ አስተዋፅዖኦ ላበረከቱ አባላት እና አካላት በሙሉ የከበረ  ምስጋናውን  ያቀርባል፡፡

       የምስክር ወረቀቱ ከታች ተያይዟል፡፡
👏8👍6
የአዲስ አበባ ህዝብ የብልፅግና መንግስት የቤት ፈረሳ ይበቃል ሊል ይገባል

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የኦህዴድ ብልፅግና  የጎጥ ፖለቲካ ወላጅ አባቱን ተክቶ አራት ኪሎን ከተቆጣጠረ ስድስት አመታትን አስቆጥሯል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ከሀሰት ትርክት የተወለደ የጥላቻ ፓለቲካን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች፣ በከፋ መጠንና በተለያየ ስልት ሳያቋርጥ ሲያራምድ ቆይቷል።  እንደ ኦሀዴድ/ብልፅግና ያሉ ጥንፈኛ የነገድ ፖለቲከኞች ፖለቲካቸውን የተቃኜው የዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በፊት በፈጠሩት የሃስት ትርክት ላይ ነው፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና ይዞት ከተነሳው የሀሰት ትርክት መካከል 1ኛው የአማራ ጥላቻ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የአዲሰ አበባን ነዋሪ የስነ ህዝብ (ዲሞግራፊ) ሰብጥር የመቀየር ግቡ ደግሞ ሁለተኛው ነው፡፡ በእርግጥ የህዝብ ስብጥር ለውጥ ፖሊሲው በሁሉም ማህበረሰቦች ላይ እየተተገበረ ቢሆንም፤ በተለይ ግን የአማራውን ህዝብ ዋነኛ ኢላማው ማድረጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ወንበሩ የተደላደለ  እንደመሰለው በቀጥታ የተሸጋገረው የአዲስ አበባ ታሪክ ናቸው ያላቸውን ቅርሶችና ስፍራዎች ወደ ማውደምና በአዲስ አበባ ዳርቻ የሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ቤት ወደማፍረስ ነው። የአዲስ አበባን ዙሪያ ነዋሪ ቤት በማፍረስ የጀመረው በነገድ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተውን ተግባር ወደ መሀል ከተማ በማምጣት ነባር የአዲስ አበባ ሰፈሮችን ወደማጥፋት/erase/ ተሸጋግሯል። በዚህ ሂደትም የነዋሪዎች ህይወት ጠፍቷል፣ አባወራዎች/እማወራዎች ከእነልጆቻቸው ጎዳና ላይ ወድቀዋል፣ ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፣ ማህበራዊ መስተጋብር ፈርሷል፣  በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል እየተፈፀመበት ይገኛል።

ይህ በህዝብ ዝምታ ምክንያት እዚህ የደረሰው መኻል ፒያሳን ነፍስ አልባ ያደረገው የብልጭልጭ መብራትና የኮሪዶር ልማት ከመገናኛ እስከ መሪ ፣ ከፒያሳ እስከ ለግሐር፣ ቄራን እና የተለያዩ የአዲስ አበባን አካባቢዎች አዳርሶ አሁን ደግሞ ካዛንችስን፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮንን እና ሽሮሜዳን ነፍስ አልባና፣ ታሪክ አልባ፣ ባለቤት አልባ አድርጎ ለማፈራረስ ቀጠሮ ይዟል። ከሰሞኑ የአገዛዙ ካድሬዎች በካዛንችስ፣ በፈረንሳይ እና ሽሮሜዳ የሚገኙ ነዋሪዎችን በመሰብሰብ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከሀብት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉና መንደራቸውም እንደሚፈርስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። በስብሰባው ላይ ማናቸዉም መገናኛ ብዙሃን እንዳይገኙ እና ድምፅ ሊቀርፁ ይችላሉ የተባሉ መሳሪያዎች እንዳይገቡ በተደረገባቸው በእነዚህ ስብሰባዎች፣ ነዋሪዎች ተወልደው ካደጉባቸው፣ ለአመታት ከኖሩባቸው ሰፈሮቻቸው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ እንደሚፈናቀሉ መርዶው ተነግሯቸዋል።    

አንድ ዜጋ ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ይቅርና በፈለገው የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ፣ ሀብት ንብረት አፍርቶ የመኖር ህገመንግስታዊ መብቱ  የተጠበቀ ስለመሆኑ ብልጽግና ሲፈለግ ብቻ የሚያከብረዉ ህገመንገስት ይደነገጋል። አገዛዙ እሞትለታለሁ በሚለው በህገመንግስት አንቀጽ 43 ተራ ቁጥር 4 ላይ "የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ የዜጎችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይሆናል"  ይላል።   የብልጽግና አገዛዝ አዲስ አበባ ላይ እያካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ተብዬው በርግጥ የከተማውን ህዝብ መሠረታዊ ፍላጎትቶች ለማሟላት እየተከናወነ ያለ ነው ወይ? ብለን ስንጠይቅ  መልሱ አይደለም ነው።  የህዝብ ጥያቄ የሚመልስ የልማት ሥራ የሚጀምረው መሠረታዊ የሆኑ  አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው ከኖሩ ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው፣ “የአዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ መሆንና በጎጥ ኮታ የሚመደቡ ካድሬዎች ሊያስተዳድሩት አይገባም፤ አዲስ አበባ በራሷ ልጆች ትመራ” የሚለው ዋነኛው ሲሆን፣ በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ነዋሪዎች በሚኖሩበት አካባቢ የመኖሪያ ቤት ችግርን የሚያቃላልሉ በቂ የኮንዶሚኒየም ህንፃዎች እንዲገነቡ፣ የግል ይዞታ ያላቸው በግል ይዞታቸው ላይ የማልማት እድል እንዲሰጣቸው፣  የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ፣ የመብራት አቅርቦት እንዲሻሻል፣ በቂ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር፣ የትራንስፖርት ችግርን የሚፈቱ መፍትሄዎች እንዲቀየሱ፣ ለወጣቱ ትውልድ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እንዲነደፉ የሚሉ ጥያቄዎችም ይገኙበታል። የብልፅግናው አገዛዝ ግን በተቃራኒው  እራሱ ቃል የገባውን "ከእንግዲህ ማንም ከቀዬው አይፈናቀልም" የሚለውን የማዘናጊያ  መሃላውን ሙሉ በሙሉ አጥፎታል።  በህገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 43 ተራቁጥር 2 ላይ "ዜጎች በብሔራዊ  ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማህበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው" የሚለውን አንቀፅ በመተላለፍና የህዝብን ጥያቄ ወደጎን በመተው፤ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ያለው የአዲስ አበባ ህዝብ ማህበራዊ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶቹን በመጠቀም በጉርብትና አንዱ ከሌላው ጋር እየተረዳዳ ችግሩን ለመቋቋም በሚጣጣርበት ወቅት፤ ጭራሽ በኮሪደር ልማት ስም  የከተማውን ህዝብ ቤትና  ንብረት አፍርሶ ፣ ነባሩን የከተማ ማህበረስብ ከቤተ እምነቶቹ አርቆ፣  የደሃ ደሃ ለማድረግና ከተማውን አስለቅቆ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት ባልተዘረጋባቸው ስፍራዎች ለመወርወር እየተጣደፈ ይገኛል።  

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፣ ከዚኽ በፊት የብልጽግናን መንግሥት ከመነሻው  በጎጥ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ አላማውን አውቆና ለይቶ አመራሩ እና አባላቱ ከባድ መስዋእትነቶችን እየከፈሉ ሲታገሉት  መቆየቱ የሚታወስ ነው። ባልደራስ አሁንም  በመሃል ከተማ የድሃው ቤትና ንብረት ፈርሶ ልማት ተብሎ እየተሠራ ያለው የሳርና ዛፍ ተከላ እንዲሁም የብልጭልጭ መብራት ጋጋታና መናፈሻ የከተማውን ህዝብ መሠረታዊ ችግር እንዲፈታ የታለመ ሳይሆን ነዋሪዎችን በማፈናቀል የብልጽግና መንግስትን  የገጽታ ግንባታ ለማድረግ መሆኑን ፓርቲያችን ያምናል።  ይህን አይነት በህዝብ ጥቅምና መብት ላይ  እየተረማመዱ የመሪዎችን ግለሰባዊ ገጽታ የመገንባት ሂደት ፓርቲያችን አጥብቆ ይቃወማል። አብዛኛውን ደሃውንና፣ መካከለኛ ኑሮ ያለውን ማህበረሰብ ተሳትፎና የጥቅም ተጋሪነት ያላረጋገጠ ልማት ፣ ልማት ሊባል አይችልም።   በመኾኑም  ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ በልማት ሰበብ የመፈናቀል አደጋ የብልፅግና መንግሥት  የጋረጠባቸው የሽሮ ሜዳ፣የካሳንቸስና፣ የፈረንሳይ ነዋሪዎች በህገመንግሥቱ የተሠጣቸውን መብት ተጠቅመው በአገዛዙ ከታቀደው የመፍረስ አደጋ እራሳቸውን በህጋዊ መንገድ አንዲከላከሉ እያሳሰበ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫ ለማስተላለፍ ይገደዳል።

ሀ. ለብልጽግና መራሹ አገዛዝ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀረበ ጥሪ፦

1. መንግሥት በማናለብኝነት አካሄድ የአዲስ አበባን  ነዋሪ ሰፈሮች በአጠቃላይ በተለየም ከአዲሱ አመት ወዲህ ደግሞ የሽሮሜዳ፣ የፈረንሳይና፣ የካሳንችስ ማህበረሰብ መኖሪያ ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አፈርሳለሁ በማለት ህዝብን ከማሸበር ተግባሩ በአስቸኳይ እንዲቆጠብና ከህዝብ ጋር ነፃ ውይይት   እንዲጀምር፣
👍3
2. ከዚህ በፊት የብልፅግና መንግሥት "ከእንግዲህ አንድም የሚፈናቀል ሰው አይኖርም" ሲል  ለህዝብ የገባውን   ቃል እንዲያከብርና፣ "እገዛለታለሁ" በሚለው ህገ-መንግሥት አንቀጽ 43 ላይ የተደነገጉትን የህዝብ መብቶች እንዲያከብር፣

3. በህገመግሥቱ አንቀጽ 43 ተራ ቁጥር 4 ላይ እንደተደነገገው  የልማት እንቅስቃሴ ዋና አላማ  የዜጎችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት በመኾኑ፤ ህዝብ መንግሥት የሚያቅዳቸውን የልማት  ፕሮጀክቶች  የማወቅ፣ አስተያየት የመስጠት፣  የመሳተፍ እና የመወያየት መብቱ እንዲጠበቅለት፣

4. ህዝብን ያላማከለ፣ የህዝብን ይሁንታ ያላገኘና በህዝብ መብት ላይ እየተረማመደ የሚከናወን ፕሮጀክት መጨረሻው ውድቀት፣ የንብረት ውደመት እና የገንዘብ  ብክነት እንደሆነ አገዛዙ እንዲገነዘብ እናሳስባለን።

ለ. ከቤት ንብረቱ  ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚፈናቀል ለተነገረው የሽሮሜዳ ፣       የካዛንችስና የፈረንሳይ ነዋሪ የቀረበ ጥሪ፦

1. ማንኛውም የልማት ፕሮጀክት ህዝብን ያማከለና የህዝብን አመኔታና ተቀባይነት ሳያገኝ መከናወን እንደማይችል ህገ-መንግስቱ ስለሚደነግግ፤ ህገመንግሥታዊ መብትህን ተጠቅመህ በየአካባቢህ በመነጋገርና ኮሚቴዎችን በማቋቋም ህጋዊ ጥያቄዎችህን ፔቲሽን በመፈራረም በጽሑፍ ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት   እንድታመለክት፣

2. አገዛዙ የምታቀርበውን ትያቄ አልቀበልም ብሎ ለውይይት የማይጋብዝህ ከሆነ፣ ጥቄዎችህን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በህጋዊ ትግሉ እንዲገፋበት እናሳስባለን፡፡  

3. የሚመለከታችሁ አካላት ሁሉ ከአዲስ አበባ ህዝብ ጎን በመቆም ሙያዊ ትብብር እንድታደርጉ ፓርቲያችን ባልደራስ ይጠይቃል፡፡

በጨረሻም መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ  በኮሪዶር ልማት ስም በርካታ የከተማዉን አካባቢ፤ ሰው አልባ፣ባለቤት አልባ ያደረገው የብልፅግና መንግሥት አሁን ደግሞ ነባር ሰፈሮችኽን አንድ በአንድ በልማት ስም ለማፍረስ እየተጣደፈ ይገኛል። በመኾኑም፤  አሁን የመፍረስ አደጋ ከተጋረጠባቸው  የፈረንሳይ፣ የካሳንችስ እንዲኹም የሽሮሜዳ ነዋሪዎች  ጎን በመቆም፣ በስልጡን አካኼድ ድምፅህን እንድታሰማ። እንደ ማህበራዊ ሚዲያ ያሉ የህዝብ ድምጽ የሚሰማባቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ከተማህን ከመፍረስ አደጋ  አንድታደግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።


የባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
መስከረም 07/ 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ
👍51
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረስዎ!
መልካም የደመራና የመስቀል በዓል!
👏43
በንፁሐን ሞት እና ሰቆቃ የሚተከል አሻራ፣ የሚፀና ወንበር የለም

በንፁሐን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሠጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሶስት አሰርት ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፀሐይ በታች በሰው ልጆች ላይ ያልተፈፀመ ግፍ የለም፡፡ የአማራ ሕዝብ በስርዓት እና በመዋቅር በተደገፈ ሁኔታ የእልቂት ሰለባ መሆኑ የአደባባይ እውነት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ይሁን እንጂ ሰውን እንደ ሰው በማይመልከት የነገድ ስርዓት ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከገዳዮች ሰይፍ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ይህን አውነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ፣ትናንት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸው የተቀጠፈበትን እና በርካቶች አካላቸውን ያጡበትን የሰሜን ኢትዮጵያን እልቂት ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ አምባ ገነን መሪዎች ባሕሪያቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ለራሳቸው ስልጣንና እርካሽ ዝና ሲሉ አንድን ሕዝብ ወይንም ማሕበረሰብን ለአረመኔ ፖለቲካቸው እዳ ከፋይ እንዲሆን ይፈርዱበታል፡፡ ይህ የነገድ ፖለቲካ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ምድር ዛሬም ከትናንቱ የባሰ ዋጋ እያሰከፈለ ነው፡፡ ሁሉም አካል ሊገነዘበው የሚገባ እውነት ቢኖር አንዱን ገድሎ አንዱ ሊኖር አይችልም፡፡እመራዋለሁ የሚለውን ሕዝብ የሚወጋ አገዛዝም ሆነ ነፃ አውጭ ቡድን ንፁሐንን በመግደል የሚተክለውም አሻራ፣ የሚያፀናውም ወንበር አይኖርም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የበርካቶች ዝምታ፣ለገዳዮች መተባበር መምሰሉ ሀዘኑን እና ጥፋቱን መሪር አድርጎታል፡፡ ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እኩያን ሀይሎች በንፁሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ግፍ እያጋለጠ እና ግፈኞችን በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ይገኛል፡፡

‘’በአማራ ክልል’’ በብልፅግና አገዛዝ ከሰማይ በድሮን ከመሬት በታንክ፣በመድፍ፣በዙ23 እና በዘመናዊ መሳሪያ በርካታ ሰዎች በእየ ቀኑ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ አርጌ (ዝብስት) ከተማ ላይ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም የብልፅግና አገዛዝ ከ40 በላይ ንፁሐን ሰዎችን በድሮን ጨፍጭፏል። የድሮን ጥቃቱ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ በመፈፀሙ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ሕፃናት እና አረጋዊያን ተጨፍጭፈዋል፡፡ በድሮን ጥቃት ከሞቱት ንፁሀን በተጨማሪ በርካቶች መቁሰላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጠናል። በተመሳሳይ ቀጠና በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ አዲስ ቅዳም ከተማ ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም የአገዛዙ ሠራዊት ቤት ለቤት በመዞር እና መንገድ ላይ ያገኙትን ከ20 በላይ ንፁሀኖች ገድለዋል፡፡ ከተገደሉት ንፁሐኖች አብዛኞቹ ሕፃናት እና ወጣቶች መሆናቸውን የተጎጅ ቤተሰቦች ለዜና አውታሮች ገልጸዋል።

የአማራን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀው ጠባብ ብሔርተኝነት የተጠናወተው አገዛዝ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ የለን ቀበሌ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም የብልፅግና አገዛዝ በፈፀመው የድሮን ጥቃት አምስት ንፁሀን ተገድለዋል፡፡ በጥቃቱ ከተገደሉት ንፁሀን መካከል የሰባ ዓመት አዛውንት ይገኙበታል። ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ቦራ ወረዳ ቢጢስ ቀበሌ በሰው ደም በሰከሩ ታጣቂዎች ከሰላሳ በላይ ንፁሐን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ በዚህ አረመኔ ቡድን ከተጨፈጨፉት ንፁሀን መካከል ሕፃናት፣አረጋውያን እና እናቶች ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ በሁለት ቦታዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ካራ ከተማ አካባቢ እና ባጮ ፋሉሚ በተባሉ ቦታዎች በርካታ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ተገድለዋል፡፡ በዚህ ጥቃት ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ፓርቲያችን የደረሰው መረጃ አረጋግጧል፡፡

በዚሁ ጥቅምት ወር ከሳምንት በፊት ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ አድዓ መልኬ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የገንዳ አረቡ መስጅድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ መኪን ሀጂ አረፉን ጨምሮ አስራ ሁለት ሰዎች በሽብርተኛ ሀይሎች ተገድለዋል። ኢማሙ እና የኢማሙ አስራ አንድ የቅርብ ቤተሰቦች ከመገደላቸው በተጨማሪ በርካቶች ታግተው መወሰዳቸውን የተጎጅ ቤተሰቦች አብራርተዋል፡፡ይህን አረመኔ ተግባር የፈፀመው ሽብርተኛው የኦነግ ሸኔ ቡድን የገደላቸውን ንፁሐኖች ለመልቀቅ በሚል ሶስት ሚሊዩን ብር ጠይቆ 1.4 ሚሊዮን ብር ተለምኖ ተሰጥቶታል፡፡ ንፁሐን ሰዎችን መግደል ፣ማገትእና መዝረፍ የሽብርተኛው ኦነግ ሸኔ ቡድን የተፈቀደ ደንበኛ ስራ በሚመስል መልኩ ቀጥሏል፡፡ የእርስ በእርስ ግድያ ፣ማፈናቀል እና ዘረፋ የስርዓቱ መርሆዎች ተደርገው የሚተገበሩ ይመስላል፡፡

"ሀዘንሽ ቅጥ ያጣ፣ ከቤትሽ ያልወጣ፤
የሞተው ወንድምሽ ፣የገደለው ባልሽ፤
አሁን እንዴት ብሎ፣ ይወጣል ሀዘንሽ፤’’

ኢትዮጵያን ዘርፈው ሲከብሩ ዞረው መውጋት እና እርስ በእርስ ማጋደልን የእውቀት ጥግ አድርገው የሚቆጥሩ ጎሰኞች የሚፈፅሙትን አረመኔነት ከላይ የሰፈረው ስንኝ በሚገባ ይገልፀዋል የሚል እምነት አለን፡፡

ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት እና ሰቆቃ እንዲቆም በርካታ ጊዜ በመግለጫ አሳስቧል፡፡ ዛሬም ፓርቲያችን በቅርቡ ከሚተገብራቸው የሰላማዊ ትግሎች አስቀድሞ የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፡፡

1. የዜጎቹን ሕይዎት መታደግ ያልቻለው የብልፅግና አገዛዝ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንዲሆን፣

2. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከአርምሞ እና ውዥንብር ወጥቶ ይሕን ግፍ በአደባባይ እንዲቃወም፣

3. የእምነት፣ የሲቪል ተቋማት እና ልዩ ልዩ ማሕበራት ተጎጅዎች ፍትህ እንዲያገኙ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፣

4. ከሀገር ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እርስ በእርስ ከመከፋፈል ወጥቶ አንድነቱን በማጠናከር በሀገር ቤት እየተካሄደ የሚገኘውን ሰላማዊ ትግል በማጠናከር የስርዓቱን ኢ ሰብአዊ ድርጊት የማጋለጥ ስራውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻ በሞቱ ወገኖቻችን የተሰማንን መሪር ሀዘን እየገለፀን በዝምታ ገዳዮችን ከመተባበር ወጥተን ለሀገራችን አንድነት ሁላችን ለሰላማዊ ትግል መነሳሳት እንዳለብን በአንክሮ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

የባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ህዳር 03/ 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ/ ኢትዮጵያ
👍11
#የሀዘን_መግለጫ

የባልደራስ ፓርቲ - የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ ማህበር መስራች አባል የነበሩት እና በኦዲት እና ቁጥጥር በኃላፊነት ያገለገሉት አቶ ወንድወሰን መኮንን በትላንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአቶ ወንድወሰን መኮንን ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ እና ለትግል አጋሮቹ መፅናናትን ይመኛል።

ነፍስ ይማር!
😢16
ከስራቸው የተፈናቀሉ ሰራተኞች በአስቸኳይ ወደ ስራ ገበታቸው ይመለሱ

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአንበሳ አውቶቡስ እና የኢትዮ ፖስታ አገልግሎት ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤት ሰራተኞች በግፍ ከስራቸው እየተባረሩ መሆናቸውን ባልደራስ ከደረስው የህዝብ ቅሬታ አረጋግጧል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንት ብቻ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ከ480 በላይ ሠራተኞች አለ አግባብ ከስራቸው ሲባረሩ ፣ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ደግሞ እንደዚሁ ተመሳሳይ 450 በላይ ሰራተኞች ተባረዋል፡፡ ለፓርቲያችን የሚደርሱት የሕዝብ ጥቆማዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ምን አልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የመንግሥት ሰራተኞች ብሔራቸውን በመጥቀስ ፎርም ሞልተው የብቃት  መመዘኛ በሚል ፈተና መሰጠት ሲጀመር ፣ሆነ ተብሎ  የአማራ ተወላጆችን እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከስራ የማፈናቀል ተግባር መሆኑን አጋልጠናል፡፡‘’የብቃት መመዘኛ‘’እየተባለ የሚሰጠው ፈተና ለዓመታት ብቸኛ መፈተኛ ቋንቋ ሁኖ ሲያገለግል በቆየው  የአማርኛ ቋንቋ ተፈትነው በአንድ መስሪያ ቤት ሲሰሩ የኖሩ ሰራተኞችን ፣በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲፈተኑ የተደረገበት ስልታዊ የማባረሪያ ምክንያት  ነበር፡፡ በተጨባጭ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከስራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉት አብዛኞቹ በአማርኛ ቋንቋ ፈተና የወሰዱት ናቸው፡፡

በነገድ ላይ የተመሰረተው አገዛዝ ሆነ ብሎ የአንድን ማሕበረሰብ አባል ለማጥቃት የሚጠቀምበት መሳሪያውም የብሔር ብረሰቦች እና ሕዝቦች የሚባለውን’’ ሕገ መንግሥት’’ ነው፡የኦሕዴድ/ኦነግ/  ብልፅግና ፖለቲከኖች የፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤት ‘’በአንድ ማሕበረሰብ ተይዟል’’ በሚል ሲለፉት የነበረውን የጥላቻ አካሄድ ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ በዚህ ኢ ህገ - መንግሥታዊ አካሄድ የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨምሮ የአማርኛ ቋንቋ ተናገሪውን  ሕዝብ ግንባር ቀደም የጥቃቱ ሰለባ አድርገዋል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ በሀገር እና በሕዝብ ላይ ከባድ መከራን ከማስከተል እና ሀገርን ከማውደም የዘለለ ለማንም ቡድን ወይንም ግለሰብ የሚሰጠው ዘላቂ ጥቅም አይኖርም፡፡

ባልደራስ ለአውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ለአስርት ዓመታት ያገለገሉ ሰራተኞች እና ቤተሰቦቻቸውን ጎዳና ላይ የሚጥል ውሳኔ በአገዛዙ መሰጠቱን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ፓርቲያችን ባልደራስ በዚህ የግፍ ውሳኔ ተጠቂ የሆኑ ወገኖቻችን ፍትሕ እንዲያገኙ እና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ አሰራሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል።

1. በግፍ ከስራቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ እናሳስባለን፤

2. ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከስራቸው ከተባረሩ ዜጎች ጎን ቁሞ  ሰላማዊ ተቃውሞ እንዲያሰማ ጥሪ እናቀርባለን፤

3.  ከስራቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለሚያደርጉት ማንኛውም ሰላማዊ ተቃውሞ ፓርቲያችን ሙሉ ድጋፉን ይሰጣል፤

4.  የሚመለከታችሁ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ የምትስሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሚዲያ አካላት የመስራት መብት በፈረንጆች አቆጣጠር በ1966 በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የፀደቀው የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (United Nation Universal Declaration of Human Rights) (UNDHR)በአንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ አንድ (1)ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን የዜጎች መብት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ ፣የማሕበራዊ እና ባህላዊ መብቶች (The International Covenant on Economic, Social and Cultural Rights) (ICESCR) ቃል ኪዳን  ውስጥ የተካተተውን መሠረታዊ መብት ግልፅ በሆነ ሁኔታ የሚጥስ በመሆኑ ፣ይህን  ህገ ወጥ ድርጊት ለዓለም በማጋለጥ ለመብቶች መከበር እየተደረገ ላለው ሀገራዊ ትግል የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ እና የሰላማዊ ለውጡ  አካላት በሙሉ የዜጎችን ከስራ መፈናቀል በፅኑ በመቃወም የሰላማዊ ትግሉ አካል እንድትሆኑ  ፓርቲያችን ባልደራስ አበክሮ ይጠይቃል፡፡

የባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ  
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
👍3😢1
በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጥቃት በጥብቅ እናወግዛለን

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይርተሰጠ መግለጫ

በጥር 22/2017 ዓ.ም በአውሲ ራሱ ዞን ኤሊዳር ወረዳ ኪያሩ ቀበሌ በደረሰ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት የሚሆኑ የአፋር ወገኖቻችን መሞታቸው ታውቋል። ጥቃቱ የተፈፀመው  በጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ድሮን መሆኑን የጅቡቲ መንግስት ያመነ ሲሆን፣ ነገር ግን በራሱ ግዛት ላይ እንደተፈፀመ አሳውቋል። እንደ ምክንያት የጠቀሰውም የሽብር ጥቃትን ለመከላከል እንደሆነ ገልጿል። የአፋር ክልል ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ጭምር ግን ጥቃቱ በአፋር ክልል ላይ እንደተደረገ እና በጥቃቱም ንፁሀን እንደተገደሉ እማኝነታቸውን ገልፀዋል።

ሆኖም የኦህዴድ-ብልፅግና አገዛዝ ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም። ይህም አገዛዙ በህዝብ ላይ ለሚደርስ ሞት እና ውዥንብር ደንታ ቢስ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይህ በርሀብ፣ በኑሮ ውድነት፣ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት... ወ.ዘ.ተ ፍዳውን እየበላ የሚገኝ ህዝብ ላይ ተጨማሪ የድሮን ድብደባ ሲደርስበት እጅግ አሳዛኝ ነው። ከደረሰው ግድያ ባልተናነሰ በተለይ አደጋው በሚመለከታቸው ተቋማት ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱ አሳዛኝነቱን ያጎላዋል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ሞት እና ጉዳት እያዘነ  ፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል።  አገዛዙም በአስቸኳይ በንፁሀን ላይ ለደረሰው ግድያ እውቅና እንዲሰጥ እና በአስቸኳይ ግልፅ ማብራሪያ እንዲያቀርብ ፓርቲው ያሳስባል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
👍81
አምስት አመታትን ለህዝብ በመታመን

ከክልል አቀፍ ፓርቲነት እስከ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት!

ድል ለኢትዮያ!
ድል ለዲሞክራሲ!
👍15
ታስረው ፍርድ ቤት ስለማይቀርቡ እና በታጣቂዎች እየታገቱ ስላሉ ዜጎች ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሠጠ መግለጫ

1. ታስረው ፍርድቤት እንዳይቀርቡ ስለተደረጉ ዜጎች

የኦህዴድ/ብልፅግና አገዛዝ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እንዲሁም የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት፣ "ሕገመንግስቱን ማስከበር¡" የሚል የዳቦ ስም በተሰጠው ቅፅል አፈናዎች፣ የኃይል እርምጃዎች እና ግድያዎች ሲፈፅሙ ቆይተዋል አሁንም እያደረጉት ይገኛል። ነገር ግን በእነዚህ 34 አመታት ውስጥ ሕገመንግስቱንም ሆነ ሌሎች ሕጎችን በመጣስ አራት ኪሎን ተቆጣጥረው የቆዩት ኢህአዴግ ቁጥር አንድ እና ሁለትን የሚወዳደር የለም። ለዚህም ከቁጥር በላይ ምስክሮችን ማቅረብ ይቻላል። ለአብነት በቅርቡ ከተለያዩ ቦታዎች የተያዙ እና አድራሻቸው የጠፉ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል።

በአገዛዙ ኃይሎች ከመኖሪያ ቤት፣ ከመንገድ ላይ እና ከስራ ቦታቸው የተወሰዱ እነዚህ ዜጎች ከተያዙ ብዙ ቀናትን ቢያስቆጥሩም እስካሁን ድረስ ግን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። ይህም አገዛዙ 'እመራበታለሁ እና አስከብረዋለሁ' በሚለው ሕገመንግስት አንቀፅ 19 (3) ላይ የተፃፈውን "የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው" የሚለውን አንቀፅ ፍፁም የሚደፈጥጥ ነው።

2. በታጣቂዎች ታግተው አድራሻቸው ስለሚጠፉ ንፁሀን

ባለፉት ከሰላሳ በላይ አመታት አማራን በአማራነቱ ብቻ መግደል፣ ማገት እና ማፈናቀል የተፈቀደ ስራ መስሎ ቀጥሏል፡፡ በተለይም የብልፅግና አገዛዝ በትረ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ እጅግ በከፋ መልኩ ብሶ ቀጥሏል።

በአገዛዙ ደረጃ ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንዳይገባ የተከለከለው የአማር ህዝብ አሁን ላይ ተንቀሳቅሶ እንኳን እንዳይሰራ በህገወጥ ታጣቂዎች እየተገደለ፣ እየታገተና ገንዘብ እየተጠየቀበት ይገኛል። ይህ በአማራው ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው መከራ በተለያየ መጠን በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይም እየተፈፀመ መሆኑን ፓርቲያችን ባልደራስ ይገነዘነባል፡፡
ከአይን እማኞች እንደተገኘው መረጃ፣ በመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ከአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕርዳር መነሻውን ያደረገ በተለምዶ ''ታታ'' ተብሎ የሚጠራ የሕዝብ ማመላለሻ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ በጎሀጽዮን እና ቱሉ ሚልኪ ከተሞች መካከል በሚገኝ ሥፍራ ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ በርካታ ሰዎች ሲገደሉ አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው ግድያ ፣ዘረፋ እና እገታ ተባብሶ መቀጠሉን ከጥቃት የተረፉ የአማራ ተወላጆች አብራርተዋል፡፡ አካባቢው ላይ በርካታ የሚባል የመንግስት ታጣቂ ሀይል ቢኖርም፣ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመውን ግድያ እና እገታ መታደግ አለመቻሉ እንዳሳዘናቸው የተጎጅ ቤተሰቦች ተናግረዋል። "ፅንፈኛ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱበት፣ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የአማራ ተወላጆች መንቀሳቀስ ባለመቻላችን፣ የአውሮፕላን ቲኬት መግዛት የማንችል ሰዎች በሕይታቸው ፈርደን የምንሄድበት የግድያ ቀጠና ሆኖብናል" ብለዋል፡፡

ከቀናት በፊት በዚሁ አካባቢ በታጠቁ ሀይሎች ''ፈለገ ግዮን'' በተባለ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ላይ ተመሳሳይ እገታ ተፈጽሞ ከ50 በላይ የሚሆኑ ተሳፋሪዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ በመግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም።

እንደዚህ ያሉ ተደጋጋሚ ክስተቶች አማራን ከአዲስ አበባ ከተማ የማገድ ሴራ እንደሆነ፣ ሁነቶቹን አትኩሮ ለሚከታተል ሁሉ ግልፅ ነው። ከዚህ ቀደም በአገዛዙ የፀጥታ ሀይሎች ጭምር የአማራ ተወላጆች ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንዳይገቡ ክልከላ ሲደረግባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው። ባልደራስ ፓርቲም ድርጊቱን በቪዲዮ ጭምር ማጋለጡ ይታወቃል። ከዚህ ድርጊት ተቀፅላ በሚመስል መልኩ አሁን ላይ የታጠቁ ሕገወጥ ሀይሎችም ሲያሻቸው እየገደሉ፣ ሲያሻቸው ደግሞ አግተው ገንዘብ በመቀበል የአማራውን ስቃይ እያባባሱት ይገኛሉ። ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ እና የሚደጎሙ ሚዲያዎች ስለ ጉዳዩ አልሰማንም ብለው ማለፋቸው ነው።

ባልደራስ ለእውነተና ዲሞክራሲ ፓርቲ ከላይ በገለፁት ጉዳዮች ላይ የሚከተሉትን አቋሟቹን ያንፀባርቃል።

1. ከተለያዩ ቦታዎች የተያዙ እና ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ዜጎቻችን በአስቸኳይ ፍ/ቤት ቀርበው ሕጋዊ ፍትሕ እንዲያገኙ፣

2. አገዛዙ ተደጋጋሚ እገታዎች በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ላይ ልዩ ስምሪት በማድረግ እንገታዎችን እንዲያስቆም፣ የታገቱ ንፁሀንንም በአስቸኳይ እንዲያስለቅቅ፣

3. ሚዲያዎች ለእንደዚህ አይነት አሳሳቢ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት በመስጠት ለህዝብ ትክክለኛ ድምፅ እንዲሆኑ፣

4. መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትኛውም ሕገወጥ ድርጊቶች ነገ የእያንዳንዳችን ቤት ሊያንኳኳ የሚችሉ መሆኑን አውቀን ካሁኑ ድርጊቶቹን እንዲያወግዝ እና እንዲቆሙ ጫና እንዲያደርግ ባልደራስ ያሳስባል።

ባልደራስ በታጣቂ ሀይሎች ለተገደሉ ንፁሀን ነፍስ ይማር እያለ ለመላ ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡

የባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራአስፈፃሚ ኮሚቴ
👍71😢1
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሁለተኛውን ዙር ውይይት ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የፓርቲ-መዋቅር ተወካዮች ጋር አደረገ።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ማደጉን ተከትሎ፣ በተለያዩ የሀራችን ክፍሎች መዋቅሩን እየዘረጋ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እያከናወነ ያለውን የመዋቅር ዝርጋታ ተከትሎ ከሲዳማ ክልል በመቀጠል ሁለተኛውን ዙር እሁድ ሚያዚያ 5/2017 ዓ.ም የፓርቲው ስራአስፈፃሚ ወኪሎች፣ ከደቡብ እና ደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመዋቅር ወኪሎች ጋር በፓርቲው ፖለቲካዊ እና አደረጃጀት ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

የባልደራስ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አምሀ ዳኜው፣ የፓርቲው ምክትል ፕ/ት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉን ጨምሮ ሌሎች የስራ አስፈፃሚ አባላት ለወኪሎቹ የ"እንኳን ደህና መጣችሁ" መልዕክት አስተላልፈዋል። የባልደራስ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ለተወያዮቹ ፣የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን አስከብሮ የኖረ ጠንካራ ህዝብ ሲሆን ባልደራስም በደቡብ ኢትዮጵያ ትልቅ መሰረት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ የፓርቲው የአደረጃጀት መዋቅር በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚሆን እና በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ለተሳታፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው ላይ የተሳተፉ የፓርቲው አደራጆች በበኩላቸው፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ መንቀሳቀሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ድል  መሆኑን ተናግረዋል። ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የአደረጃጀት መዋቅር መዘርጋቱ  በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ እና ትልቅ ተስፋ መስጡትን ተወያዮቹ አብራርተው ፓርቲው ይዞት የተነሳውን አላማ እንዲሳካ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እውን እንዲሆን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

በዕለቱ የፓርቲው አደረጃጀት እና ፖለቲካ ስራዎች ላይ ከተከበሩ የመዋቅር ወኪሎች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። መርሀ ግብሩ ሙሉ ቀን የቆየ ሲሆን ከውይይት ባለፈም፣ የተለያዩ አደረጃጀታዊ እና ፖለቲካዊ አቅጣጫዎች የተወሰዱ ሲሆን በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና  ደቡብ-ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ያላችሁ ሀገር ወዳድ ዜጎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን በመቀላቀልና በተለያየ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ሰላማዊ ትግሉን እንድታጠናክሩ ባልደራስ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ድል ለዲሞክራሲ!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ!
👏5👍41