ASD AJ LAH
754 subscribers
1.79K photos
197 videos
3 files
511 links
ካነበብኩት…
Download Telegram
ለሶላት የውጭ ድምፅ ማጉያ መጠቀም
~
ሶላት ዒባዳ ነው። ዒባዳችን ከእልህና መሰል አጉል ስሜቶች ፀድቶ በኢኽላስና በንፁህ መንፈስ ሊፈፀም ይገባል። ድምፅን በሶላት ከፍ ማድረግ በቦታው ሲሆን የተወደደ ነው። አልፎ በእንቅልፍ ሰዓት ሰዎችን እስከሚረብሽ ሊደርስ አይገባም። አንዳንድ አካባቢ ከሶላትም አልፎ መዝሙር ከፍተው እንደሚያውኩ ሰዎች መንዙማ ለቀው የሚያውኩ አሉ። ኢስላም ይህንን አይፈቅድም። "እነሱስ እንዲህ እያደረጉ አይደል?" የሚል ማመሀኛ እልህ እንጂ ማስረጃ አይደለም። ደግሞም እነሱ አይደሉም ምሳሌዎቻችን። በረመዷን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ሌሊት ለተሀጁድ የሚነሱ ወገኖች የውጭ ድምፅ ማጉያዎችን ሲጠቀሙ ሰፈሩን እንዳለ ነው የሚያውኩት። ጉዳዩ አላህን በመፍራት ሰከን ብሎ ማጤን ይሻል። ሰፈር ጎረቤት ቢታወክም እንጮሃለን እያስባለን ያለውን ምክንያት ረጋ ብለን እናዳምጠው። ምናልባት አንዳንዶች ጋር "በዚያ ሰዓት እተኛለሁ የሚል ይረበሽ። ሙሉ የሰፈሩ ህዝብ ተነስቶ ይስገድ" የሚል ስሜት ወለድ ሙግት ካለ ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ ከማለት ውጭ ይሄ ምላሽም የሚግገባው አይደለም። ብቻ ደጋግሜ የምለው አላህን እንፍራ። የታመመ ይተኛ። መተኛት የፈለገም ይረፍ። አሁን ያለው ግን ሌላው ቀርቶ መስጂዶች በሚቀራረቡባቸው አካባቢዎች ባጎራባች ያሉ ሰጋጆች ሶላታቸው እስከሚረበሽ እየደረሰ ነው።
ከዚህ በፊት አንዳንዶች "ቁርኣን እንዴት ይረብሻል?" የሚል የህፃን ክርክር ሲያስነሱ ነበር። የሚረብሸው ለከት ያለፈው ድምፅ ነው። መስገዳችንን አገር እንዲያውቅልን ማወጅ የለብንም። ለኢኽላስ የቀረበው በልክ የሆነው ስራ ነው።

እንዲያውም በተሀጁድ ብቻ ሳይሆን #በሌሎችም ሶላቶች የውጭ ድምፅ ማጉያዎችን መጠቀም ክልክል ነው ይላሉ ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ። ይሄውና:

ጥያቄ:- “ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የመስጂድ ኢማሞች የውጭ ድምፅ ማጉያዎችን መጠቀም አብዝተዋል። ድምፅ ማጉያዎቹ በአብዛኛው ሚናራ ላይ የሚሆኑ ሲሆን በጣም ከፍ ያለ ድምፅ ይጠቀማሉ። በዚህ ድርጊት የተነሳ ድምፅ ከፍ በሚደረግባቸው ሶላቶች ጊዜ ከፊል መስጂዶች በቁርኣን ንባብ ጊዜ ድምፅ ማጉያዎችን ስለሚጠቀሙ ሌሎቹን ይወሰውሳሉ። እና ድምፅ ከፍ በሚደረግባቸው ሶላቶች ጊዜ የድምፅ ማጉያዎችን መጠቀም ብይኑ ምንድነው?

የሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር:-

ድምፅ ከፍ በሚደረግባቸው ሶላቶች ጊዜ ድምፅ ማጉያዎችን ከሚናራ ላይ መጠቀም ክልክል ነው። ምክንያቱም በአቅራቢያ ባሉ ነዋሪዎች እና መስጂዶች ላይ መረበሽ አለበትና። ኢማሙ ማሊክ ረሒመሁላህ በዘርቃኒይ ሸርሕ ላይ እንደሚገኘው ሙወጦእ (178) ላይ በ (باب العمل في القراءة) የአላህ መልእክተኛ ﷺ እየሰገዱ ከነበሩ ሰዎች ዘንድ ወጡ። በቁርኣን ድምፃቸው ከፍ ብሏል። በዚህን ጊዜ እንዲህ አሉ:-
"إن المصلي يناجي ربه فلينظر بما يناجيه به ولا يجهر بعضكم على بعض بالقرآن"
“ሰጋጅ ከጌታው ጋር ነው የሚንሾካሾከው። ስለዚህ የሚንሾካሾክበትን ይመልከት። አንዳችሁ በሌላው ላይ በሶላት አይጩህ። አቡ ዳውድ (1332) (رفع الصوت بالقراءة في صلاة الليل ) በሚል ርእስ ስር ከአቡ ሰዒድ አልኹድሪይ ረዲየላሁ ዐንሁ በዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ﷺ በመስጂዳቸው ኢዕቲካፍ አድርገው ነበር። በቁርኣን ሲጮሁ በሰሟቸው ጊዜ መጋረጃውን ገልጠው እንዲህ አሉ:-
"ألا إن كلكم مناج ربه فلا يؤذين بعضكم بعضاً، ولا يرفع بعضكم على بعض في القراءة ، أو قال في الصلاة"
“ንቁ! እያንዳንዳችሁ ከጌታው ጋር ነው እየተንሾካሾከ ያለው። ስለሆነም አንዳችሁ ሌላችሁን አያስቸግር። በቁርኣን ንባብ / በሶላት አንዳችሁ ሌላችሁ ላይ አይጩህ።” [መጅሙዑ ፈታዋ ኢብኒ ዑሠይሚን: 13/74-96]

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል:-

“ሶላቶችን ከሚናራዎች ላይ በድምፅ ማጉያዎች ማስተላለፍ ጠያቂው እንዳለው በየቤታቸው ያሉ ሰዎችን መወስወስ ነው። የግል ዚክሮቻቸውንና ተስቢሖቻቸውን ማናጋት ነው። ምናልባትም ከዚህ ጊዜ ውጭ ማረፊያ ያጡ የተኙ ሰዎችንና ህመምተኞችን መረበሽ ሊኖርበትም ይችላል።
በተጨማሪም ከዚህ ድምፅ ባጎራባች ላሉ መስጂዶች መረበሽና መወስወስ አለበት።” [ኑሩን ዐለ ደርብ:176]

የሁለቱንም ፈትዋዎች ይዘት ሙሉውን ስላላቀረብኩ የፈለገ ምንጩን ተከትሎ ያንብብ።

(ኢብኑ ሙነወር፣ ረመዳን 19/1442፤ ሚያዚያ 23/2013)