Arba Minch University
20.7K subscribers
18.6K photos
66 videos
1.14K files
932 links
The official telegram channel of Arba Minch University
Download Telegram
ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ፣ ልማትና ኢንኩቤሽን ማዕከል ከ‹‹Innovation for Peace (I4P)›› ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የቢዝነስ ሀሳብ ውድድር አዘጋጅቷል።

ስለሆነም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በዚህ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር ላይ እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል።

ለመመዝገብ ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ተጭነው ይመዝገቡ

https://docs.google.com/forms/d/e/1FAIpQLSc0ax9mjkg1aWtaxooJShBOTfD2XkHLPBzBRqYV6V8xpSnH9w/viewform
ፕሮጀክቱ ከትንንሽ ወንዞች ኃይል በማመንጨት ከዋናው መስመር የራቁ አካባቢዎችን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት መሆኑ ተመላከተ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ክርስቲያን ኤይድ ትብብር የተገነባው የዲንጋሞ ፒኮ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ምርምርና ሳይንስ ወደ መሬት የወረዱበትና ከትላልቅ ወንዞች ባሻገር ትንንሽ ወንዞችን ተጠቅሞ ኃይል በማመንጨት ከዋናው መስመር የራቁ አካባቢዎችንና ማኅበረሰቦችን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ከካምባ ዙሪያ ወረዳ አመራሮች ጋር በመሆን የፕሮጀክቱን የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒል የግንባታ ሳይቶችን፣ የመብራት ተጠቃሚ የሆኑ መኖሪያ ቤቶችን እንዲሁም ተቋማትን ሚያዝያ 19/2017 ዓ/ም የጎበኙ ሲሆን የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይት አካሂደዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደ ሀገር ካለን የውኃ ሀብት 45 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ቁጥር በሀገሪቱ የሚገኙ ትንንሽ ወንዞችን ያማከለ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዲንጋሞ ፒኮ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ከትላልቅ ወንዞች ባሻገር ትንንሽ ወንዞችን ተጠቅሞ ኃይል በማመንጨት ከዋናው መስመር የራቁ አካባቢዎችን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት እንዲሁም እንደ ሀገርም ሞዴል መሆን የሚችል ሥራ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በቀጣይ መሰል ሥራዎችን ለመስራት የሚያስችል ልምድ የተገኘበት ነው ያሉት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ የግንባታ ሥራው ከጥናትና ዲዛይን ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች የተመራ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በውኃ መስክ ቀዳሚ እንዲሁም በመስኩ የልኅቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ለሚገኝ ተቋም የዚህ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቅ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው በክፍል ውስጥ በጽነሰ ሃሳብ ደረጃ የሚያስተምረውን ሳይንስ መሬት ላይ በተግባር ሰርቶ ያሳየበት መሆኑን ገልጸው በመስኩ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎችም የተግባር ትምህርት የሚማሩበት እንዲሁም ምርምር የሚሰሩበት ቤተ-ሙከራ በመሆን ማገልገል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የዲንጋሞ ፒኮ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የሚሰራቸው ሥራዎች ብዛት፣ ዓይነትና ጥራት እያደገ መምጣጡን የሚያሳይና ዲንጋምን ከጨለማ ያወጣ የተለየ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ምርምርን መነሻ በማድረግ የተሰራ መሆኑ አዲስ የተቀየረውን የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተሳሰብ በተግባር ያሳየንበት ሲሆን በቀጣይ የሚሰሩ መሰል የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች በምን አግባብ መመራት እንዳለባቸው ትምህርት የተወሰደበት መሆኑንም ዶ/ር ተክሉ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ስኬት ውስጥ የክርሰቲያን ኤይድ ሚና በትልቁ የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ በትብብር መሥራት ከተቻለ በተለየ ሁኔታ ማኅበረሰብን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደሚቻል የታየበት ፕሮጀክት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ኢንስቲትዩቱ በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል አማካኝነት በጋሞና ጎፋ ዞኖች ገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችንና ትምህርት ቤቶችን የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የ24 ሰዓት መብራት አገልግሎት እንዲገኙ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ የዲንጋሞ ፒኮ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ሃሳብ ከዚሁ ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የመነጨ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሙሉነህ መሰል ማኅበረሰቡን የሚጠቀሙ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ኢንስቲትዩቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ይሰራል ብለዋል፡፡

የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በበኩላቸው የዲንጋሞ ፒኮ ሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክት መነሻው በ8 ወንዞች ላይ የተካሄደ ጥናት መሆኑን ጠቅሰው በዩኒቨርሲቲው ምርምርን መነሻ አድርገው ከተሰሩ ውጤታማ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ባለፉት ሶስት ዓመታት ይህንን ፕሮጀክት ለመጨረስ በርካታ ውጣ ውረዶች መታላፋቸውን ጠቅሰው ሥራው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ክርስቲያን ኤይድ ለዘመናት የሚቆይ ስማቸውንና አሻራቸውን የተከሉበት ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቶሌራ በሀይድሮ ፓወር መስክም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ተግባራትን ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የካምባ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓለሙ ጎንችሬ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በዋናው የኤለሌትሪክ መስመር ያልደረሰባቸውን አካባቢዎች መብራት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና ያለውና የማኅበረሰቡን የቆየ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዲንጋሞ እንዲገነባና ማኅበረሰቡ ብርሃን እንዲያገኝ ላደረጉት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ክርስቲያን ኤይድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ኢ/ር በየነ ፈየ ፕሮጀክቱ 15 ኪሎ ዋት ኃይል በማመንጨት አራት መቶ አባወራዎችንና በአካባቢው የሚገኙ የትምህርት፣ የጤና፣ የሐይማኖትና የንግድ ተቋማትን የኤሌትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡ መብራት ከመስጠት ባሻገር ፕሮጀክቱ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች አሉት ያሉት ኢ/ር በየነ ሥራው ዲንጋሞን ከገጠር ቀበሌነት ወደ ከተማነት የቀየር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት