Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
33.5K subscribers
15.9K photos
61 videos
15 files
8.21K links
ዜና ከምንጩ
Download Telegram
"ቦርዱ ከፌዴራል መንግስት ጋር የጀመርነውን ተከታታይ ውይይት ከማደናቀፍ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን" - ህወሓት

ቅዳሜ የካቲት 08 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ)  በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ( ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ምርጫ ቦርድ ላስተላለፈበት እግድ ምላሽ የሰጠ ሲሆን "ቦርዱ ከፌዴራል መንግስት ጋር የጀመርነውን ተከታታይ ውይይት ከማደናቀፍ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን" ብሏል።

ከተመሰረተ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ አንጋፋ ፓርቲ መሆኑን የገለፀው ህወሓት  በመግለጫው " ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካዋ የፕሪቶሪያ ከተማ የሰላም ውል ከተፈራረመ ጀምሮ ህጋዊነቴ የተመለሰ ነው " ብሏል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ከነሃሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ህወሓትን በአዲስ ህግ እንደ አዲስ ፓርቲ " መዝግቤዋለሁ ማለቱን " አስገራሚ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡

"የምርጫ ቦርድ አካሄድ በመሰረቱ ተቀባይነት የሌለው ፤ ህግን መሰረት ያላደረገ ፣ትርጉም አልባ ውሳኔ ነው" ብሎታል።

"ህወሓት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ተሰጥቶ የሰላም ውል የፈረመ ፓርቲ ነው " ያለው ህወሓት ፤ " ከኢፌዴሪ መንግስት ተከታታይ የፓለቲካ ውይይት በማካሄድ ላይ በመሆኑ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰላማዊ ውይይቱን ከማደናቀፍ እንዲቆጠብ " ሲል አቋሙን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጊዜ አንሥቶ ባሉት 6 ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ ይጠበቅበት የነበር  ቢሆንም ይህንን ባለማድረጉ ለሦስት ወር ከፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ፤ በሦስት ወራት የዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር የፖርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኾነው ተመረጡ

ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ( አዲስ ማለዳ) ጅቡቲን ለበርካታ ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ ቀጣዩ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኾነው ተመርጠዋል።

ኮሚሽኑን እንዲመሩ በሊቀመንበርነት የተመረጡት የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተካሔደውና ብርቱ ፉክክር በታየበት፣ እንዲኹም እስከ ሰባተኛ ዙር ድረስ በዘለቀ ምርጫ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ በማግኘት ነው።

ከሳምንት በፊት 60ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩት ዩሱፍ፣ የኬንያውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶን በማሸነፍ ኮሚሽኑን በቀጣይ አራት ዓመታት እንዲመሩ ተመርጠዋል።

አዲሱ የኅብረቱ ተመራጭ ከአውሮፓውያን 2005 ጀምሮ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ በአፍሪካ አህጉር ለረጅም ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የገለገሉም ናቸው።
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊዬነር አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የምዋዕለንዋይ ፍሰት በእጥፍ እንደሚያሳድጉ አስታወቁ

አዲስ ማለዳ - የካቲት 09፣ 2017 – የአፍሪካ ግንባር ቀደም ባለሃት ናይጄሪያዊው ቱጃር አሊኮ ዳንጎቴ፣ በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ማስፋፊያ እንደሚሰሩ አስታወቁ። በማስፋፊያው በኦሮሚያ ክልል ሙገር የሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማምረት አቅሙን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት አምስት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርት ተነግሯል፡፡ በለሃብቱ በስኳር እና ማደባሪያ ዘርፍ ያካበቱትን ልምድ መሠረት በማድረግ በዘርፉ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል፡፡

የዳንጎቴ ግሩፕ ሊቀመንበር እና ዋና ስራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ በሚኖረኝ ጉብኝት ሁሌም ደስተኛ ነኝ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረግኩት ጉብኝት እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በነበረኝ ውይይት፣ በሃገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦች ስላበረታቱኝ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ተነሳስቻለሁ ብለዋል።

“ውጣ ውረዶች ቢያጋጥመንም በሲሚንቶ ላይ ባደገነው ኢንቨስትመንት በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” ፋብሪካውን ለመገንባት የተበደርነውን ብድር ሙሉ ለሙሉ የመለስን ከመሆኑም ባሻገር፣ ሰርተን ያተረፍነውን ትርፍም ሙሉ ለሙሉ በተሳካ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡

አሊኮ ዳንጎቴ በአፍሪካ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ‘የዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ’ን በሃገራቸው ሥራ ካስጀመሩ በኋላ ትልልቅ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለማቆም አቅደው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱ አመለከታቸውን እንደለወጠው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ የዳንጎቴ ግሩፕ ያቀዳቸውን የማስፋፊያ እና አዳዲስ እንቨስትመንቶችን በደስታ መቀበላቸውን ተናግረው ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ እድገትን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለስራ እድል ፈጠራ ቅድሚያ የሚሰጥ የኢኮኖሚ ለውጥ እያስመዘገበች ነው። ይህን ተከትሎ ዳንጎቴ ግሩፕ በሃገራችን አሻራውን ሲያሰፋ በማየታችን ተደስተናል፤ ይህ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ የንግድ ከባቢ ላይ የመተማመን ምልክት ሲሆን ለመሰረተ ልማት እና ለኢኮኖሚ እድገታችን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል” ብለዋል።

ዳንጎቴ ግሩፕ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች ግዙፍ አምራች ኢንዲስትሪዎችን በማስፋፋት ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያም 2.5 ሚሊዮን ቶን የሚያመርት የሲሚንቶ ፋብሪካ ከአስር አመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያ ደሳለኝ አስመርቆ ሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን በወቅቱ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ገበያን ያረጋጋ ኢንቨስትመንት ነበር፡፡ ፋብሪካው በኦሮሚያ በተቀጣጠለው ግጭት ምክንያት በሥራው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል የደረሰበት ከመሆን አልፎ ህንዳዊው የድርጅቱ አስኪያጅ እና ሁለት ሰራተኞቹም ግንቦት 2009 ከአማፂዎች በተተኮሰ ጥይት የተገደሉበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለው ትርፍ በውጭ ምንዛሬ ለማስወጣት ከገጠመው ችግር አንፃር የኩባንየው በኢትዮጵያ የሚኖረው ቆይታ ላይ አጠራጣሪ ሆኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እነዚህ ችግሮች ሁሉ አልፈው አሁን ላይ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ባደረጉት ኢንቨስትመንት በጣም ደሥተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

በተለይ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይት እና አጠቃላይ የሃገሪቱ የኢንቨስትመንት ከባቢ ላይ ባዩት ተስፋ፣ ሙገር በሚገኘው የሲሚንቶ ፋብሪካቸው ላይ ከፍተኛ የማስፋፊያ ሥራ እንደሚያደርጉ እና የፋብሪካውን የማምረት አቅም በዕጥፍ በማሳደግ በአመት ወደ አምስት ሚሊዮን ቶን ሲሚኒቶ እንደሚያመርቱ ተናግረዋል። በተጨመሪም በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ አዳዲስ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው እና የኦሞ ኩራዝ ስኳር ኩባንያ እንደሚያለሙ ተነግሯል። የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳው የሀገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከተፈጠረ በኋላ በኢትዮጵያ የዩሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ለመትከልም እቅድ እንዳላቸው ተናግረወል።

ዳንጎቴ የአፍሪካን እድገት ለመምራት “የአፍሪካ የንግድ መሪዎች” ያላቸው ሚና ላይ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ “አፍሪካ የምትለማው በአፍሪካውያን ነው። የፖለቲካ መሪዎቻችን የአፍሪካ ህብረትን ለማጠናከር በሚሰሩበት ወቅት፣ እኛ ደግም የንግድ መሪዎች እንደመሆናችን በአህጉሪቱ ያለውን የንግድ ትስስራችንን በማጠናከር ጥረታቸውን መደገፍ አለብን” ብለዋል።
#አዲስ ማለዳ_ማስታወቂያ

ሶስት ቀን ብቻ ቀረ!

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው 9ኛው የጤና ኤግዚቢሽን እና ዓለምአቀፍ ኮንግረስ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሊከፈት ሶስት ቀናት ብቻ ቀርተዋል፡፡ ከየካቲት 13 – 15 በሚደረገው ሁነት በጤና እና ህክምናው ዘርፍ ዓለም የደረሰችበትን ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ አሰራር ይመለከታሉ፣ የመድሃኒት አቅርቦት እና አሰራር የደረሰበትን ያያሉ፤ እርሶ ብቻ እንዳይቀሩ! ብዙ ነገር ይቀስማሉ፣ የንግድ እና የሥራ ግንኙነቶችን ለማዳበርም ሁነኛ አጋጣሚ ነው፡፡

ምን እሱ በብቻ!

አሉ የተባሉ የጤና እና ህክምና ባለሙያዎች በዘርፉ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችን እና አገልግሎቶችን፣ እንደዚሁም የቴክኖሎጂ ግኝቶች እና ተሞክሮዎችን የሚያካፍሉበት እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት ዓለምአቀፍ ኮንግረስም ተዘጋጅቷል፡፡

ይምጡ!

• አዳዲስ የንግድ እድሎችን እና የሥራ ግንኙነቶችን መሥርተው ይሄዳሉ!
• ለህክምና ማዕከልዎ አስተማማኝ እና ደረጃቸውን የጠበቁ አቅራቢዎችን ይተዋወቃሉ!
• አዳዲስ እና ዘመናዊ አሰራሮች አይተው ተቋምዎትን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል!
• የገበያ አድማስዎን ለማስፋት ሊከተሉት ስለሚገባ ስትራቴጂ እና ዘመናዊ አሰራር ተሞክሮ ይቀስሙበታል!

ይህ መልካም አጋጣሚ እንዳያመልጥዎ ፈጥነው ይመዝገቡ! ይህን ሁሉ ሸምተው ምንም ክፍያ አይከፍሉም!

https://bit.ly/ethio-health-registration

ለበለጠ መረጃ
+251929 30 83 63/64
www.ethio-health.com
“የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንዳናካሂድ መከልከላችን የገዢ ፓርቲውን አንባገነንነት ያሳያል” - ኢሕአፓ

ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ የካቲት 9 እና 10 2017 ዓ.ም የማዕከላዊ ኮሚቴውን ስብሰባ በሆቴል ለማካሄድ የተያዘው ፕሮግራም በገዢው ፓርቲ ሹማማንት ተከልክሎብናል ብሏል፡፡ በመሆኑም በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት አዳራሽ ስብሰባውን ማስቀጠሉን የገለጸ ሲሆን የተወያየባቸውን የአቋም መግለጫ አስፍሯል፡፡

የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የፓርቲው የ6 ወራት የሥራ ሪፖርት በማድመጥና በመወያየት፣ በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በህብረትና በትብብር ለመስራት የሚያስችል ሰነድን መርምሮ በማፅደቅ፣ የተጓደሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ መጠናቀቁን ገልጿል።

ፓርቲው በአማራ፤ በኦሮሚያ ፤ በቤንሻጉል ጉሙዝ ፤ በጋምቤላ፣ በደቡብ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም እጦት መቋጫ ሊበጅለት ይገባል ብሏል፡፡

በመግለጫው መንግሥት የህግ የበላይነትን የማክበር፣ የማስከበርና፣ የዜጎችን ህይወት የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ ፓርቲው በአጽንዖት አሳስቧል፡፡

“ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ከመጥበቡ የተነሳ እስር ፤ እንግልት፣ከስራ የመፈናቀል፣ ከፍ ሲልም ግድያ ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ ሲገደዱ እያስተዋለ” መሆኑን ፓርቲው ኮንኗል፡፡

“ከዚህ አንጻር ገዢው ፓርቲ እጁን በማስረዘም የፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በኃይል መጨፍለቁን እንዲያቆምና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ሕገመንግስታዊ ግዴታውን ይወጣ” ብሏል፡፡

“የገዢው ፓርቲ ሹማማንት የፓርቲዎችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማኮላሸትና መሪዎቻቸውን ለማሸማቀቅ የሚያደርጉትን ጥረት አጥብቀን እናወግዛለን” ሲል ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ አፈፃፀምን እያዳመጠ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ባካሄደው 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመት የስራ አፈፃፀምን አያዳመጠ ይገኛል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሀገራዊ የምክክክር ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ያከናወናቸው ተግባራት እንደሚቀርቡ እና ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አስረድተዋል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ በስፋት ተወያይቶ ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክር ቤቱ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን “የስራ ዘመን ያራዝማል” ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በታህሳስ 2014 ዓ.ም የጸደቀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ሶስት ዓመት እንደሆነ ይደነግጋል።

የኮሚሽኑ የስራ ዘመን የሚቆጠረው፤ በአዋጁ መሰረት የሚመረጡ ኮሚሽነሮች በፓርላማ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዕጩነት የቀረቡ 11 ኮሚሽነሮችን ሹመት ያጸደቀው የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር።
ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበት ቀንሷል ቢልም ተቃራኒ ሪፖርት መውጣቱ ተገለጸ

ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ባወጣው የእስታትስቲክስ ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ይህም በባለፈው አመት ጥር ወር ከነበረበት 29.4 በመቶ ወደ 15.5 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን ይህም 13.9 በመቶ ማሽቆልቆሉን የሚያመለክት መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡

እንዲሁም የምግብ ግሽበት በ16.6 በመቶ እና በምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በ10.2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል።

ይሁን እንጂ ትሬዲን ኢኮኖሚክስ ተደረገ ባለው ጥናት ከብሄራዊ ባንክ ሪፖርት ጋር ተቃራኒ የሆነ ቁጥር መመዝገቡን ገልጿል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አመታዊ የዋጋ ግሽፈት 17 በመቶ እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን የብሄራዊ ባንክ ካወጣው ቁጥር ጭማሪ የሚያሳይ ነው፡፡

ሁለቱም ሪፖርቶች የቁጥር ልዩነት ቢኖራቸውም የዋጋ ግሽበት እንደ አጠቃላይ ከነበረበት መቀነሱን አመላክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ ዓመት አራዘመ

ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017(#አዲስ_ማለዳ)

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ አመት አራዝሟል።

የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፤ በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ በአብላጫ ጽምጽ ጸድቋል።

መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች “ወሳኝ ምክንያቶችን የመለየት” እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ በአዋጅ የተቀመጠለት የስራ ዘመን ሶስት ዓመት እንደነበር ይታወቃል።

ፓርላማው ኮሚሽኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በስራ ላይ እንዲቆይ ውሳኔ ከማሳለፉ አስቀድሞ፤ የተቋሙን የሶስት ዓመታት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት በንባብ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ የምክክር፣ የአጀንዳ መለየት እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎችን በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

አባላቱ ኮሚሽኑ በተሰጠው ተጨማሪ የስራ ዘመን ተጠባቂ ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል።
ለቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራሮች ሹመት ተሰጠ።

ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017(#አዲስ_ማለዳ)

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ጥሪ ለተቀበሉ የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ሹመት ሰጥቷል፡፡

በዚህ መሰረት፡-

1. አቶ ያደሳ ነጋሳ
በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ

2. አቶ ኦሮሚያ ረቡማ
የኦሮሚያ ክልል ዓቃቤ ሕግ ምክትል ኃላፊ፣

3. አቶ ቶሌራ ረጋሳ
የኦሮሚያ ክልል ጸጥታና አሥተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው መሾማቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ከባድ ድንጋጤን የፈጠረ በሬክተር ስኬል 5.3 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 (#አዲስ_ማለዳ)

በኢትዮጵያ በሬክተር ስኬል 5.3 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ እሁድ ሌሊት 8 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ መከሰቱን የአውሮፓ ሜዲትራንያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል አስታውቋል፡፡

ዘለግ ላሉ ሰከንዶች የቆየው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት መዲናዋ አዲስ አበባ ድረስ ተሰምቷል።

የመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳቀውከጭሮ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ሲሆን በአዋሽም “ቀላል” የሆነ ንዝረት ማስከተሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን የሚመዘግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ገልጿል።

ንዝረቱም በድሬዳዋ፣ ሂርና፣ በዴሳ፣ ገለምሶ፣ ደደር፣ አቦምሳ፣ ገዋኔ፣ መተሐራ፣ አዳማ፣ ወንጂ፣ ሞጆ እና ቢሾፍቱ ከተሞችን ማዳረሱን እንዲሁም ተመሳሳይ መጠን ያለው ንዝረት በደብረሲና፣ ደብረ ብርሃን፣ ከሚሴ፣ ባቲ፣ ኮምቦልቻ እና ደሴ ድረስ መሰማቱንም ተመላክቷል፡፡
የእንቁላል ዋጋ ጭማሪ እጅግ እያሻቀበ በመሆኑ መንግስት ሊቆጣጠረው ይገባል - ነዋሪዎች

ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 (#አዲስ_ማለዳ)

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ የሚገኘው የእንቁላል ዋጋ ጭማሬ የተጋነነ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

አስር ብር እና ከዛ በታች ስንገዛ የቆየነው እንቁላል አሁን ሀያ ብር እና ከዛ በላይ እየተሸጠ ነው፤ ይህን ያህል የዋጋ ልዩነት በወራት ውስጥ መምጣቱ ከማህበረሰቡ የመግዛት አቅም በላይ ነው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት የእንቁላል ዋጋ እንደየ አካባቢው የሚለያይ ሲሆን ከ16 ብር እስከ 20 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዋጋው አሳሳቢ ነው ያሉት ነዋሪዎች፤ እንቁላልን እንኳን የዘወትር ምግብ ልናደርገው፣ የበዓል ዕለት ለማከተትም ተቸግረናል ይላሉ፡፡ ዋጋው ህብረተሰቡ ከሚያገኘው ገቢ ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ መንግሥት ቁጥጥር እንዲያደርግበት አሳስበዋል፡፡
የዋጋው መናር መንስኤ ምንድነው ስትል አዲስ ማለዳ ዶሮ እና የዶሮ ተዋጽኦ አቅራቢዎችን አነጋግራለች፡፡

በመሆኑም ከአቅራቢው እስከ ተጠቃሚው እጅ እስኪደርስ ብዙ ውጣውረዶች መኖራቸውን ገልጸው ነገር ግን የዶሮ መኖ የዋጋ ጭማሬ እንደ አንድ ምክንያት ሊታይ እንደሚችል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የእንስሳት እርባታ እና የዶሮ ተዋጽኦ አቅራቢ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ከአቅራቢው ወይም ከዶሮ አርቢው ተረክቦ እስከሚያከፋፍሉት ከዛም ለተጠቃሚው እስከሚያደርሱት ድረስ የሚታይ የዋጋ ለውጥ መኖሩን፤ እንዲሁም የትራንስፖርት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ አንዱ በሌላው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ነጋዴው ከአላስፈላጊ ትርፍ መሰብሰብ ቢቆጠብ እና ምርቶቹን በተገቢው ዋጋ ቢያቀርብ የራሱ የሆነ ለውጥ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በነገው ዕለት 60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለጨረታ ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ

ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 (#አዲስ_ማለዳ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ነገ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡

በዚህም ጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ጨረታው ለሁሉም ባንኮች ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።

እንዲሁም ከቅርብ ወራት ወዲህ ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበረታች መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር የሪፎርሙ ጥሩና አዎንታዊ ውጤት ቢሆንም የማዕከላዊ ባንኩን ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲና የዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር እንደሚገ አሳስቧል፡፡

በመሆኑም ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማገናዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ባንኩ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሁኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ሽያጮችን እንደሚያካሂድ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በተለይም የወጪ ንግድ፣ ሐዋላና የካፒታል ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት 13 ኢትዮጵያውያን ተገደሉ

ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 (#አዲስ_ማለዳ)

በኢትዮጵያ እና በኬንያ አሳ አጥማጆች መካከል በተፈጠረ የድንበር ግጭት 13 ኢትዮጵውያን ሲገደሉ፣ ሶስቱ ቆሥለዋል፤ በተጨማሪም ሁለት ዜጎች የገቡበት አልታወቀም፣ በአንፃሩ 22 ኬንያውያን የገቡበት መጥፋቱን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡ ዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታሩ መረጃውን የሁለቱም ሀገራት ባለስልጣናት አረጋግጠውልኛል ብሏል።

ግጭቱ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በኦሞ ወንዝ አካባቢ በሁለቱ ሀገሮች ድንበር ላይ መከሰቱን የኬንያ ቱርካና ካውንቲ አስተዳዳሪ ኤርሚያስ ሎሞሩካይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ስየስ ቀበሌ ነዋሪዎች ነገሩኝ ብሎ አዲስ ስታንዳርድ እንደዘገበው፣ የኬንያ ታጣቂዎች “ስድስት ጀልባዎችን ጨምሮ 130 የሚደረሱ የአሣ ማጥመጃ መረቦች፣ እስከ 500 ሺህ የሚደርሱ ደረቅ አሣዎች እና በርካታ ንብረቶችን” መወሰዳቸውን ጽፏል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ዋና የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት መሳይ ሊበን፤ “የኬንያ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ለሚመጡ ታጣቂዎቹ ከተሽከርካሪ አንስቶ እስከ ተተኳሽ የጦር መሣሪያዎች ድጋፍ ማድረጉን” ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮመን እሁድ ዕለት በኤክስ ገፃቸው ላይ እንደፃፉት፣ መንግሥት በድንበሩ ላይ ተጨማሪ ጥበቃ ማሰማራቱን እና "በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል ሰላም ለመፍጠር" ከአዲስ አበባ ጋር እየተገናኘ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡

ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም ያለው የድንበር ግንኙነት ከኬንያ ጋር ያላት ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኬንያ በኩል የእርሻ እና ግጦሽ መሬትን በሃይል ለመንጠቅ እንደዚሁም ውሃ ፍለጋ የሚደረጉ መተናኮሶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶቹ በአካባው ሽማግሌዎች፣ አለፍ ሲልም የአካባቢ የመንግሥት አስተዳደሮች እልባት ሲሰጡት መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ ከጅቡቲ የተነሳ ድሮን በኢትዮጵያ አፋር ክልል ጥቃት ማድረሱ በሃገር ውስጥ የተለያዩ አካላት ዘንድ ቁጣ የቀሰሰ ክስተት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ብሄር ጥቃት እና ተደጋጋሚ ትንኮሳም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን፣ አልፋሽጋን እንደምክንያት በመጥቀስ የሱዳን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ወደኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው እንደሚገቡ እና የፀጥታ ሥጋት እንደሚፈጥሩም ይታወቃል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ያለውን የፖለቲካ፣ የጸጥታ ችግሮችን እና ሰብዓዊ ቀውሶችን  ለመፍታት በሚል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ፣የኦረሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ እና በኦሮሚያ ክልል ከ16 በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎች የአራት ቀናት ምክክር አድርገዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በዚህ ምክክር ላይ የተሳተፉትን የኦፌኮ ሊቀመንበርና አንጋፋ ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጋር አዲስ ማለዳ ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡ ሙሉ ቃለመጠይቁን ከስር ባለው ማስፈንጠሪያ በመጫን ይከታተሉ

https://youtu.be/NlI3-vcUY1g?si=z4JdudWUGnxse2Re
ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ጨረታ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአማካይ 135 ብር ዋጋ መሸጡ ተገለጸ

ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 (#አዲስ_ማለዳ)

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ በልዩ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአማካይ 135 ብር ዋጋ መሸጡ ተገልጿል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በዛሬው ዕለት ያካሄደው የ60 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ልዩ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታ መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በዚህ ልዩ ጨረታ ውጤት መሰረትም የአንድ የአሜሪካ ዶላር አማካይ የምንዛሪ ዋጋ 135 ነጥብ 6185 ብር መሆኑን ይፋ አደርጓል።

ጨረታው ላይ 27 ባንኮች መሳተፋቸውን የገለጸው ብሄራዊ ባንኩ፤ የውጭ ምንዛሪ ጨረታው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳትፎ የታየበት ነበር ብሏል።

በቀጣይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ከዋጋና ከውጭ ምንዛሪ መረጋጋት ጋር በሚስማማ መልኩ ተጨማሪ ጨረታዎችን እንደሚያካሂድ ባንኩ አስታውቋል።