Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
31.7K subscribers
16.3K photos
66 videos
16 files
8.66K links
ዜና ከምንጩ
Download Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ምልዓተ ጉባኤው ሳይሟላ ስብሰባውን ያካሄደው ፓርላማው ለ60 ዓመታት የዘለቀውን የወንጀል ህግ ሥርዓት አሻሽሎ አጸደቀ

ሐሙስ፣ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም(#አዲስ_ማለዳ)

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርአት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅን በዛሬው ዕለት ምልዓተ ጉባኤውን ባይሟላም አጸደቀ።  

የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የህጉን መሻሻል አስፈላጊነት ወሳኝነት ያብራራ ሲሆን የተቃውሞ ድምጽም ግን ተሰምቶበታል።

በዚህ ጉባኤ የተገኙት 255 እንደራሴዎች ብቻ ናቸው።

ህጉ ለ60 ዓመታት ሳይሻሻል የዘለቀ ቢሆንም ምክር ቤቱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በረቂቅ ደረጃ ሲወያይበት እና ይዞት እንደቆየ ተነግሯል።

የጸደቀው ህግ 195 ማሻሻያዎች ተደርጎለታል የተባለ ሲሆን ከዚህ ቀደም  በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ሲነሱ የቆዩ ጉዳዮችን መልስ የሚሰጥ ነው ተብሎለታል። የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት፣ እውነታን ለማግኘት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ ህጎችን እንዳካተተ ተገልጿል።

ህጉ በ253 ድጋፍ ቢጸድቅም ሁለት የተቃውሞ ድምጾችም ግን ገጥሞታል። የፓርላማ አባሉ አበባው ደሳለኝ “ምልዓተ ጉባኤ ሳይሟላ” መጽደቅ የለበትም ያሉ ሲሆን በተጨማሪም ይህንን የሚያህል ህግ ብዙ ተወካዮች እና የትግራይ እንደራሴዎች በሌሉበት ማጽደቅ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ፓርላማው ከዚህ ቀደም ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ስብሰባውን ሰርዞ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ባይሟላም ህጉን አጽድቋል።

በሌላ በኩል ተቃውሞ የተነሳበት ለሁለት አካል ተመሳሳይ ስልጣን ይሰጣል በሚል ሲሆን እሱም የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን ክልላዊ መንግስት የተመለከተው ነው።

ከፓርላማ አባላት በኩል “የአዲስ አበባን የፍርድ ቤት ስልጣን ለኦሮሚያ ይሰጣል፤ ፍትህ ደግሞ  በመሬት ወሰን ላይ የተመሠረተ ነው፣ በአዲስ አበባ የሚፈጠሩ ማናቸውም ወንጀሎች መታየት ያለባቸው በአዲስ አበባ ነው” የሚል ሙግት ቀርቧል።

“ይህም የፌደራል ስርዓትን ይጎዳል” ቢሉም ቋሚ ኮሚቴው ኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ይዳኝ ያልነው በ ከተማዋ በሚገኙ መስሪያ ቤቶቹ ቅጥር ግቢ የሚፈፀም ወንጀል ነው፤  ይህም “ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አፈ ጉባኤው ታገሰ ጫፉ  ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ለስድስት ዓመታት በጥንቃቄ የታየ ህግ ነው፤ ችግር የለበትም ያለ ሲሆን “ለአንዳንድ ጥያቄዎች ደግሞ አያስፈልጉም” ያሉ ሲሆን መልሱንም በተመሳሳይ ገልጸዋል።

አፈጉባኤው “ይህ ህግ ብዙ ተለፍቶበታል” ያሉ ሲሆን  መጽደቁ ተገቢ ነውም ብለዋል። የፓርላማ አባሉ አበባው ደግሞ በቀጣዩ ምርጫ በሚዋቀረው ምክር ቤት ቢተላለፍና ተሟልቷ ቢጸድቅ የሚል ምክረሃሳብ ሰንዝረዋል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
17👎6😢3🥰1
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ምርጫ ቦርድ የመራጮች የምዝገባ ቀነ ገደብን አራዘመ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 26 ቀን 2018(#አዲስ_ማለዳ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ማራዘሙን ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

አስቀድሞ የተያዘው የመራጮች የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ የተያዘለት እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ነበር።

ቦርዱ የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳውን ያራዘመው በሦስት ምክንያቶች መሆኑን አስታውቋል። ቀዳሚው ምክንያት በተያዘው ዕቅድ መሠረት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ “የመራጮችን ምዝገባን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የኔትዎርክ አቅርቦት እና በምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በፍተሻ ሥርዓት እየለዩ ሲስተሙን አስተማማኝና ቀልጣፋ ለማድረግ ሂደቱ የጠየቀውን ጊዜ ማካካስ በማስፈለጉ ነው” ብሏል።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ “የኔትዎርክ አቅርቦታቸው አስተማማኝ ነው” ተብለው የቀረቡ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የኔትዎርክ አቅርቦት አለመኖሩ በተጨባጭ በመታየቱ ወደ ማንዋል በመቀየር ሂደት “ለባከነ ጊዜ” ማካካሻ በማስፈለጉ መሆኑን አስገንዝቧል።

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ በተወሰኑ ባላቸው ነገር ግን ብዛታቸውን ባልጠቀሳቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በትራንስፖርት አቅርቦት ምክንየት የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ በወቅቱ ባለመድረሱ የተፈጠረውን የመራጮች ምዝገባ መዘግይት ማካካስ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብሏል።

በዚህም ቦርዱ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳን እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. አራዝሟል።

ይሁንና ከሁለት ቀናት በፊት “ተስተውለዋል” ያላቸው “የህግ ጥሰቶች” ቀነ ገደቡን በመራዘም ውሳኔ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለማሳደራቸው ያለው ነገር የለም።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ወሳኝ” ሲል በጠራው የቅድመ ምርጫ ተግባራት ወቅት “ቤት ለቤት በመዘዋወር ካርድ ውሰዱ ከሚል ሕግን ከሚተላለፍ ተግባር አንሥቶ አግባብነት የሌለው መራጭነትን ከማኅበራዊ አገልግሎት ጋር ማግኘት እና ከደሞዝ መቁረጥ ጋር በማያያዝ በዜጎች ላይ ተፅዕኖ እስከማድረስ ያሉ ተግባራት መፈጸማቸውን የሚጠቁሙ ሪፖርቶች” መመልከቱን ገልጾ ነበር።

ቦርዱ ደርሶኛል ባለው “ጥቆማ” መነሻነት “በሁሉም የክልል መንግሥታት እና በሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ሥር በተዋረድ ያሉ አስፈጻሚዎቻቸው የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፤ በመራጭነት መመዝገብን እንደ ግዴታ የሚያደርግ ያልተገባ ተፅዕኖ አንዲያስቆሙ” በጽሑፍ አሳውቄያለሁ ማለቱ አይዘነጋም።

በዚያው መግጫ ቦርዱ አክሎም “ማንኛውም አካል ሕግን በመጣስ በየቤቱ በመሔድ ተመዝገቡ ማለትና በየመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በመራጭነት እንዲመዘገቡ ማስገደድ አይችሉም” በማለት አጽዕኖት ሰጥቷል።

“የመራጭነት ካርድ ካልወሰዳችሁ ደሞዛችሁ ይቆረጣል በማለት ማስፈራራትም ሕገ-ወጥ ድርጊት” ቦርዱ አጥብቄ እቃወማለሁ ማለቱ ይታወሳል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ያልተገባ ቅስቀሳ የሚደረግባቸውን ምርጫ ክልሎች እና ምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት ምርጫ አንዳይካሄድ የሚያደርግ ዕርምጃ እስከመውሰድ” እንደሚገደድ አስጠንቅቆ ነበር።

እሰከ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው መረጃ መሠረት፣ ቦርዱ ሠላሳ ስድስት ሚሊዮን፣ ዘጠኝ መቶ ሰባ አንድ ሺህ፣ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አንድ (36,971,981) መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብና ቤት ቆጠራ ከተካሄደ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ እንደ የተባበሩት መንግስታት ያሉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛትን አንድ መቶ ሠላሳ ሚሊዮን ያደርሱታል።

[ በዚህ ዜና ላይ ተጨማሪ መረጃዎች ከደቂቃዎች በኋላ ታክለውበታል ]

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
16👎2😁1
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ

እሁድ፣ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም(#አዲስ_ማለዳ)

ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ለምርጫ የሚወዳደርበትን ማኒፌስቶ በዛሬው ዕለት ባዘጋጀው መርሀግብር ይፋ ማድረጉን አስታወቀ።

“ሰላምና ብሔራዊ እርቅ እንፈጠር ማድረግ፤ የዲሞክራሲና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስራት፤ ዜጎችን የማህበራዊ ጥበቃና ደህንነት እንዲያገኙ ማስቻል፤ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት፣ ተጠያቂነት እና ግልጽነትን ማስፈን የጥምረቱ ዋና ዓላማዎች” መሆናቸውን በማኒፌስቶው አመላክቷል።

የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱ የቡና ተክል የሆነው ጥምረቱ በሀገሪቱ ይስተዋላሉ ያላቸውን ችግሮች ለመፍታት እንዳቀደም ገልጿል።

“አለመረጋጋቶችንና ግጭቶች፣ የዲሞክራሲ
ተቋማት መዳከም፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣  ማህበራዊ ቀውስ፣ ጥራቱን የትምህርትና የጤና ሥርዓት አለመኖር፣ የሙስና መንሰራፋትና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የፌደራል ሥርአቱ አተገባበር ላይ አሉ” ያላቸውን ችግሮች ጨምሮ ሌሎች በሀገሪቷ ይታያሉ ሲል የዘረዘራቸውን ተግዳሮቶች መሰረት በማድረግ ማኒፌስቶውን እንዳዘጋጀም ተመላክቷል።

ጥምረቱ ያዘጋጀው ማኒፌስቶ፣ የሰላምና ደህንነት ፣ የሲቪል ሰርቪስ፣  የውጪ ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የሥራ እድል ፈጠራና የመሬት ፖሊሲዎች በዋናነት በሰነዱ ተጠቅሰዋል።

“ተመጣጣኝ ህብረ ብሔራዊ የፌደራል ሥርአት” ለመከተል ያቀደው ጥምረቱ “የዞን የአስተዳደር ሥርአትን እንደሚያስቀር” ተናግሯል።

ጥምረቱ ከፍተኛ ዕጩዎችን በማስመዝገብ ረገድ ከብልጽግና፣ ኤዜማ፣ ከትብብር፣ ነእፓ፣ ቀጥሎ እንደተቀመጠ የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመላክታል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
6👍2👏1
#አዲስ_ማለዳ_በሳምንቱ

እሁድ፣ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም

#ከሀገር_ውስጥ

1] የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የነዳጅ እጥረት አልገጠመኝም” አለ

አየር መንገዱ በጦርነቱ ሳቢያ “በረራዎችን አካሂዶ የሚያስፈልገውን ነዳጅ ለማግኘት አስቸጋሪ” ቢሆንበትም “ከተለያዩ” ካላቸው አማራጮች ነዳጅ እያገኘ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

አየር መንገዱ ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ዕለት በአህጉሪቱ የአውሮፕላን እድሳትና ጥገና የማካሄድ  (ኤም.አር.ኦ.)  ያለው አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ የዘርፉን አቅም መገንባት  በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ ዋና ስራ አስፈጻሚው መስፍን ጣሰው በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

2] የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ህገወጥ የነዳጅ ግብይትን መቆጣጠር አሁንም ድረስ “እጅግ አዳጋች” መሆኑን ተናገረ

ለመቆጣጠር አዳጋች እያደረገ ያለውም “የመንግስት አካላት እና የማደያ ባለቤቶች ተሳትፎ” መሆኑ ተጠቁሟል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት አብዛኞቹ ህጋዊ ሽፋንን በመጠቀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። ሚኒስቴሩ ጥቅማችን ተነክቶብናል ካሉ ተቋማት ጋር መተናነቁን የገለጸ ሲሆን ይህም ቢሊዮን ብሮችን የሚመለከት ስለሆነ ነው ብሏል።

ሚኒስቴሩ ረቡዕ ዕለት ለንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስምንት ወራት ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ህገወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያለ ሲሆን 658 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጧል፡፡

3] ምልዓተ ጉባኤው ሳይሟላ ስብሰባውን ያካሄደው ፓርላማው ለ60 ዓመታት የዘለቀውን የወንጀል ህግ ሥርዓት አሻሽሎ አጸደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርአት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅን ባለፈው ሐሙስ ዕለት ምልዓተ ጉባኤውን ባይሟላም አጸድቋል።  

የጸደቀው ህግ 195 ማሻሻያዎች ተደርጎለታል የተባለ ሲሆን ከዚህ ቀደም  በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ሲነሱ የቆዩ ጉዳዮችን መልስ የሚሰጥ ነው ተብሎለታል።

4] ምርጫ ቦርድ የመራጮች የምዝገባ ቀነ ገደብን አራዘመ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ማራዘሙን በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አስቀድሞ የተያዘው የመራጮች የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ የተያዘለት እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ነበር።

5] በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የስደተኛ መጠለያዎች የጎርፍ አደጋ ስጋት እያየለ መሆኑ ተገለጸ

በምስራቅ አፍሪካ የስደተኛ ካምፖችና ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ የጎርፍ አደጋ እያደገ የመጣና ቀጣይነት ያለው ተግዳሮት መሆኑን ዓለምአቀፍ ተቋማት አስታወቁ። ተቋማቱ ይህ ሁኔታ ካልተቀለበሰ እና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉም ተጓዳኝ ችግር ይዞ በመምጣት ለህይወታቸውም አደጋ የሚጥል ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እ.አ.አ. በ2025 በኢትዮጵያም ሆነ ሱዳን ባለው ጣቢያ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ የተከሰተባቸው ነው የተባለው የዴልታሬስ  እና የዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. አዲስ ጥናት ላይ ነው።

#ከውጭ

1] እስራኤል በፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ የሞት ቅጣት የሚደነግገውን አወዛጋቢ ሕግ አጸደቀች

የእስራኤል ፓርላማ “በሽብርተኝነት” የተከሰሱ የፍልስጤም እስረኞች በሞት እንዲቀጡ የሚፈቅደውን አዲስና አወዛጋቢ ሕግ ባለፈው ሰኞ  በ62 ድምጽ ድጋፍና በ48 ተቃውሞ አጽድቆታል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ የሕጉ ዋና ዋና ነጥቦች በቀኝ ዘመሙ የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር ፓርቲ የቀረበውና በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋፍ የተቸረው ይህ ሕግ ከአስገዳጅ የሞት ቅጣት እስከ ስቅላት የሚደርስ ነው።

2] ባቤል መንደብ እንደ ሆርሙዝ ሁሉ “የመዘጋት ዕጣ ፈንታ እንደተጋረጠበት”  ተሰማ

የዓለም የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የሆነው የሆርሙዝ ስርጥ የመከፈት ተስፋ እየመነመነ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሌላኛው ወሳኝ መተላለፊያ ባብል መንደብ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦበታል።

የየመኑ ሁቲ ወደ እስራኤል ሁለት ባልስቲክ ሚሳኤሎችን መተኮሳቸውን ተከትሎ፣ ቀይ ባህርን ከኤደን ባህረ ሰላጤ ጋር የሚያገናኘው፣ እስያና አውሮፓን በስዊዝ ካናል በኩል የሚያስተሳስረው የባቤል መንደብ መስመር ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ተደግኖበታል።

እነዚህ ዘገባዎች ባለፈው ሳምንት በአዲስ ማለዳ የፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ሊንክዲንና ዩቱብ ገጾች ከተጋሩት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የተዘረዘሩትን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ ትንታኔዎች፣ ጥንቅሮችንና ቃለመጠይቆችን ደግሞ በይፋዊ የዩቱብ አድራሻችን ተጋርተዋል። አዲስ ማለዳን ሰብስክራይብ፣ ላይክና ሼር እንድታደርጉ በትህትና እንጋብዛለን።

ዜናን ከምንጩ!

የአዲስ ማለዳ ዩቱብን በዚህ ማስፈንጠሪያ ያገኙታል፦
t.ly/vSgS
18
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ኢራን የአሜሪካ አየር ኃይል አባልን ለማዳን አደረግሁት ያላችው ዘመቻ “ዩራኒየምን ለመስረቅ” የተደረገ ሽፋን ሊሆን ይችላል አለች

ሰኞ፣ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የወደቀውን የአየር ኃይል አባል ለማዳን የተካሄደው የአሜሪካ ዘመቻ ከአገሪቱ “የበለጸገ ዩራኒየምን ለመስረቅ” የተደረገ ሽፋን ሊሆን ይችላል ሲል አስታወቀ።

ትናንት እሁድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ዓርብ ዕለት በኢራን ላይ የወደቀውን የኤፍ-15- ኢ(F-15E) ተዋጊ አውሮፕላን ሁለተኛውን የበረራ አባል “ደፋር” ባሉት የፍለጋ እና የማዳን ዘመቻ ማግኘት መቻሏን ተናግረዋል። የኢራን ጦር በበኩሉ ድርጊቱን “የማታለል እና የማምለጥ ተልዕኮ” በማለት የጠራው ሲሆን፣ ተልዕኮውም “መክሸፉን” ገልጿል።

ሰኞ ዕለት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባቃይ ስለ ዘመቻው “ብዙ ጥያቄዎች እና ጥርጣሬዎች” እንዳሉ ተናግረዋል።

አክለውም፣ “የአሜሪካው ፓይለት ይገኝበታል የተባለው በኮጊሉየህ እና ቦየር-አህመድ ግዛት ውስጥ ያለው ቦታ፣ ኃይሎቻቸውን ለማሳረፍ ከሞከሩበት ወይም ለማሳረፍ ካሰቡበት በመካከለኛው ኢራን ከሚገኘው ቀጠና በጣም ርቆ የሚገኝ ነው” ብለዋል።

“ይህ የበለጸገ ዩራኒየምን ለመስረቅ የተደረገ የማታለል ዘመቻ ሊሆን የሚችለውን ዕድል በፍጹም ችላ ሊባል አይገባም” ብለዋል። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ቃል አቀባዩ ዘመቻው ለአሜሪካ “ውርደት” መሆኑን ገልጸዋል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
17😁4
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ህወሓት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት ላይ ያለውን ተቃውሞ ገለጸ፤ “የትግራይ ጉዳይ የሚወሰነው በትግራይ ህዝብ ብቻ ነው” ሲልም አስታወቀ

ሰኞ፣ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ስም እያካሄደ ያለውን ሂደት እንደማይቀበልና በሂደቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም በትግራይ ህዝብ ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው አስታወቀ። ድርጅቱ በመግለጫው የትግራይ ህዝብ ጉዳይ በትግራይ ምድርና በራሱ በህዝቡ ብቻ ሊወሰን እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ የጀመረውን የህልውና አደጋ አጠናክሮ ቀጥሏል ሲል የከሰሰው ህወሓት፣ ይህንን ድርጊት ለመሸፈንና ለማደናገርም የትግራይ ህዝብ ሙሉ በሙሉ በተገለለበት ሁኔታ በተለያዩ ተቋማት አማካይነት የህዝቡን ሉዓላዊነት የሚጋፉ ውሳኔዎች እየተላለፉ መሆኑን ገልጿል። በተለይም ከሰሞኑ በምክክር ኮሚሽኑ የተከናወነው ተግባር የትግራይ ህዝብ ተሳትፎና እውቅና የሌለው በመሆኑ ዛሬም ሆነ ነገ ተቀባይነት እንደማይኖረው ድርጅቱ አስገንዝቧል።

በተጨማሪም በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው፣ ምክክር ኮሚሽኑ በትግራይ ስም ያካሄደው መድረክ ጥቂት “ለጊዜያዊ ጥቅም የተታለሉ” ግለሰቦችን የሰበሰበና የመንግስትን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም ያለመ ነው ብሎታል።

ትግራይ በምክክር ሂደቱ ላይ የማትሳተፍባቸው ምክንያቶች ለኮሚሽኑ ቀደም ብለው በግልጽ መነገራቸውን ያስታወሰው ህወሓት፣ ህዝቡ በአሁኑ ወቅት በረሃብና በበሽታ እየረገፈ ባለበት፣ መሬቱ በኃይል ተወሮ በሚገኝበትና የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ባለበት ወቅት እንዲህ አይነት አጀንዳዎች ትርጉም የለሽ ናቸው ብሏል።

መንግስት የትግራይን ህዝብ ግልጽ ጥያቄዎች ወደ ጎን በመተው “ትግራይ በምክክር ሂደቱ መክራለች” የሚል የፕሮፓጋንዳ ስራ እየሰራ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ ማንኛውም ወዳጅም ሆነ ጠላት የትግራይ ህዝብ ያልመከረባቸውና ያልተወከለባቸው ውሳኔዎች በምድር ላይ ተግባራዊ እንደማይሆኑ ሊያውቀው ይገባል ብሏል።
በመጨረሻም፣ የትግራይ ህዝብ ከመሰረታዊ የህልውና ጥያቄው ትኩረቱን የሚከፋፍሉ እንዲህ ያሉ “ተንኮሎችን” በመገንዘብ፣ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥና ህልውናውን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደራጅቶ ትግሉን እንዲቀጥል ህወሓት ጥሪ አቅርቧል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
13😁6👎1
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ሰሜን ኮሪያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት እየቀነሰች መሆኑ ተገለጸ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም(#አዲስ_ማለዳ)

የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ለሀገሪቱ ህግ አውጪዎች ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ሰሜን ኮሪያ ለረዥም ዘመናት የቆየውን የቅርብ ወዳጅነቷን ከኢራን ጋር ሆነ ብላ ርቀቷን በመጠበቅ ላይ ነች ብሏል።

ምንም እንኳን በሁለቱ ሀገራት መካከል በታሪካዊ ሁኔታ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ ረገድ ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ቢሆንም ፒዮንግያንግ አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ ያላትን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ገድባለች ስትል ሴዑል በስለላ ድርጅቷ በኩል ማስታወቋን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

እርምጃው ሰሜን ኮሪያ ወደፊት ከአሜሪካ ጋር ሊኖራት ለሚችለው ዲፕሎማሲያዊ ንግግር በር ከፋች ለማድረግ ካላት ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሩቅ ሁና ሂሳቧን እያሰላች ነው ተብሏል። ኪም ጆንግ ኡን ጦርነቱ እንደተጀመረ በምን እንደሚቀላቀሉ ተቸገረዋል፤ ምክንያት አጥተዋል በሚል በሰፊው የተዘገበ ሲሆን በመጨረሻም አንድ የሃገራቸው ዜጋ ኢራን ውስጥ አደጋ ከደረሰበት እርምጃ እንደሚወስዱ መዛታቸው አይዘነጋም።

የስላለ መረጃው እንደሚያመላክተው ከሆነ በኢራን እና በእስራኤል መካከል ከፍተኛ ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ሰሜን ኮሪያ ለኢራን ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያም ሆነ ወታደራዊ አቅርቦቶችን አልላከችም ያለችው ተቀናቃኟ ደቡብ ኮሪያ ናት።

በተለይም የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ በአየር ጥቃት በመገደላቸውም ሆነ ልጃቸው አዲሱ መሪ ሆነው ሲመረጡ ፒዮንግያንግ የተለመደውን እንኳን ደስ አላቸሁም ሆነ የሐዘን መግለጫ ከመስጠት ተቆጥባለች። ይህም ሰሜን ኮሪያ በአካባቢው ካለው ጦርነት እጇን በማውጣት ዓለም አቀፋዊ ገጽታዋን ለማስተካከልና ከዋሽንግተን ጋር አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ስልታዊ ጥንቃቄ እያደረገች መሆኑን ያሳያል ተብላል።

የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሰጣቸው መግለጫዎች እጅግ አነስተኛ እና የቀዘቀዙ መሆናቸው ተስተውሏል ያለው ዘገባው ሀገሪቱ በተለይም የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጥታ ከመንቀፍ እየተቆጠበች ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ውጥረት ለማርገብ እንደ አንድ ምልክት የተወሰደ ነው ተብሏል።

የደቡብ ኮሪያ የደህንነት ተንታኞች እንደሚሉት ኪም ጆንግ ኡን የቀጣናው ጦርነት እስኪረግብ ድረስ ሆን ብለው ድምጻቸውን በማጥፋት ከአሜሪካ ጋር ለሚደረግ ድርድር ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው። ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ወዳጅ ነን ብለው መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸውም መገናኘታቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል፣ ሰሜን ኮሪያ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ጦርነት ምክንያት ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና መጋለጧም ተጠቁሟል። በጦርነቱ ሳቢያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማግኘት የተቸገረችው ፒዮንግያንግ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር እና የውጭ ምንዛሬ ተመን መናር በሀገሪቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ተዘግቧል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የነዳጅ ፍላጎቷን ለማሟላት ፒዮንግያንግ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረች ሲሆን የክሬሚሊንን ድጋፍ በማግኘት የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቋቋም ጥረት እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
18🥰4
የኢራን ጦርነት ስድስተኛ ሳምንቱ ይዟል፤ በየአፍታውም አዳዲስ ጉዳዮች እየተሰሙበት ቀጥሏል

ይሁንና በዚህ ጦርነት ስር ብዙ መመርመር የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከዕለታዊ የውግያ ዜናዎች ባሻገር እነዚህን ልዩ ምልከታ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በተመለከተ አዲስ ማለዳ የአፍሪካ ቀንድና መካከለኛው ምስራቅ ተንታኝ የሆኑትን አብዱራሕማን ሰይድን ከብሪታንያ፣ ለንደን አነጋግራ ሰፊ ቆይታ አድርጋለች፡፡

በዚህ ወቅት አስርሺዎች እየተመለከቱት የሚገኘውን ጥልቅ ትንታኔ እንድትከታተሉት ጋብዝናችኋል

https://www.youtube.com/watch?v=a71w1i1DuBc&t=4685s
7👏1
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
ኢሕአፓ ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄድ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

ረቡዕ፣ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

ኢሕአፓ አስቻይ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት የሚካሄድ ምርጫ “አምባገነንነትን እንደሚያጠናክር” በመግለጽ ለሚያዝያ 30 የተቃውሞ ሰልፍ ጠራ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለው ነባራዊ ሁኔታ “ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም” ሲል አስታውቋል።

ፓርቲው የሥልጣን ሽግግር በሕዝብ ፈቃድና በነፃ ምርጫ መከናወን እንዳለበት በጽኑ ቢያምንም፣ አሁን ያለው ሁኔታ ግን የገዥው ብልጽግና ፓርቲ “የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የሚጠቀምበት የመሸወጃ ትርዒት” እንጂ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሂደት አይደለም ሲል ወቅሷል።

ምርጫ “በአንድ ጀምበር ድምፅ በመስጠት ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት፣ የፖለቲካ ኃይሎች አማራጭ ሃሳብ የሚያቀርቡበት ሰፊ ምኅዳርና ነፃ የምርጫ አስፈጻሚ አካል የሚጠይቅ ሂደት መሆኑን” ኢሕአፓ በመግለጫው አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በጠፋበት፣ ንጹሐን ዜጎች በድሮንና በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ባለበት እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብና በድህነት እየማቀቁ በሚገኙበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አደገኛ መሆኑን ፓርቲው አስገንዝቧል።

በተለይም በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጦርነት ወላፈንና የዜጎች መፈናቀል ሳይቆም የሚደረግ ምርጫ “የአገር አንድነትን ከመሠረቱ የሚንድና አምባገነንነትን የሚያነግሥ እንደሆነም” አክሎ ገልጿል። በተጨማሪም ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ታስረው በሚገኙበት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማትና ሚዲያዎች በመንግሥት ጫና ሥር በወደቁበት ወቅት የምርጫው ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚወድቅ ፓርቲው አስታውቋል።
ኢሕአፓ ከዚህ ቀደም ትክክለኛ ምርጫ ሊካሄድ ይችል ዘንድ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላታቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ያለ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችና ያለ እውነተኛ ብሔራዊ ድርድር የሚካሄድ ሂደት “ለሕዝብ ስቃይ መቀጠል ምክንያት” እንደሚሆን ገልጿል።

በመሆኑም “የንጹሐን ጭፍጨፋና አፈና በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና የኑሮ ውድነትን የሚገቱ እርምጃዎች እንዲወሰዱ” ፓርቲው ጠይቋል።

እነዚህን ጥያቄዎች ለማስተጋባትና አምባገነንነትን ለመቃወም በሚልም፣ ኢሕአፓ ልክ ለዛሬ ወር ዓርብ ሚያዝያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በሐዋሳ፣ በአሶሳ፣ በአዳማ፣ በአምቦ፣ በድሬዳዋና በሐረር ከተሞች ታላቅ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱን በማሳወቅ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪውን አስተላልፏል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
27👏11😁7😢1
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
Photo
እንግሊዝ በባህር ስር ባሉ መሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ የነበሩ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦችን አደጋ ማክሸፏን ገለፀች

ሐሙስ፣ ሚያዚያ 01 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር የሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይሎች በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ የሚገኙ የኢንተርኔት ገመዶችን እና የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን አደጋ ላይ ሊጥሉ የነበሩ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦችን ለሳምንታት በመከታተል አደጋ እንዳያደርሱ አደርጊያለሁ አለ።

ሚኒስትሩ ጆን ሂሊ በለንደን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሩሲያ የዓለም ትኩረት በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ላይ ባረፈበት ወቅት ይህንን ድብቅ ኦፕሬሽን ለማካሄድ መሞከሯን የተናገሩ ሲሆን ይህም አደገኛ እንደነበር ገልጸዋል። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ የሩሲያ አካሄድ አደገኛ እንደነበር አመልክተዋል።

በዚህ ወታደራዊ ክትትል አንድ የሩሲያ ጥቃት አድራሽ ሰርጓጅ መርከብ እና ሁለት ልዩ የሆኑ የስለላ ሰርጓጅ መርከቦች ተለይተው ታውቀዋል ብሏል። የእንግሊዝ ባህር ኃይል መርከቦች እና የጦር አውሮፕላኖች ከኖርዌይ እና ከሌሎች የኔቶ አጋሮች ጋር በመተባበር የሩሲያ መርከቦችን ለ24 ሰዓታት ሲከታተሉ መቆየታቸው ተገልጿል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ፣ “እያየናችሁ ነው፤ በኬብሎቻችን እና በቱቦዎቻችን ላይ የምታደርጉትን እንቅስቃሴ ሁሉ እናውቃለን” በማለት በእነዚህ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት እንደማይታገሱና አስከፊ መዘዝ እንደሚኖረው አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ቀደም የሩሲያ የንዳድጅ ማስተላለፊያ መስመር የዩክሬን ጦር ጋር በተያያዘ በኔቶ አባሎች እንደተቆረጠባት መናገሯ ይታወሳል።

ለወራት ክትትል ሲደርግባቸው ነበር የተባሉት የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ካወቁ በኋላ አካባቢውን ለቅቀው ወደ ሰሜን ተመልሰዋል ተብሏል። እስካሁንም በባህር ስር መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ሩሲያ ቀደም ሲል በባህር ስር ኬብሎች ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡባትን ክሶች ውድቅ ስታደርግ የቆየች ሲሆን ለዛሬው የእንግሊዝ መግለጫ እስካሁን በይፋ የሰጠችው ምላሽ የለም።

በዚሁ ሳምንት የእንግሊዝ ስም በሩሲያ የተነሳ ሲሆን ይህም ዩክሬን በእንግሊዝ የተሰሩ የድሮን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሩሲያ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተገልፆ ነበር። በተለይም ማሎይ ቲ 150 የተሰኙ የጭነትና የጥቃት ድሮኖችን በመጠቀም በደቡባዊ ዩክሬን ለሩሲያ ጦር አቅርቦት ወሳኝ የነበረን ድልድይ ማውደሟ ተዘግቧል። ይህም ክስተት በዘመናዊ የጦርነት ታሪክ ዉስጥ ድሮኖችን በመጠቀም ድልድይን የመሰለ ግዙፍ ግንባታ በማፍረስ ረገድ የመጀመሪያው ስኬታማ ኦፕሬሽን ተብሎ የተገለፀለት እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።

በሌላ በኩል በዛሬ ዕለት በወጣው መረጃ መሠረት ሩሲያ በጦርነቱ የተገደሉ የአንድ ሺህ ዩክሬናውያን ወታደሮችን አስከሬን ያስረከበች ሲሆን በምትኩ የአርባ አንድ ሩሲያውያን አስከሬን ለሀገራቸው ተመልሷል። ይህ ልውውጥ የተከናወነው በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስተባባሪነት በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
28👍8👎4🥰1😁1
መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ፤ አዲስ ማለዳ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ ትመኛለች
👍132
#አዲስ_ማለዳ_በሳምንቱ

እሁድ፣ ሚያዝያ 04 ቀን 2018 ዓ.ም

#ከሀገር_ውስጥ

1] ህወሓት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት ላይ ያለውን ተቃውሞ ገለጸ፤ “የትግራይ ጉዳይ የሚወሰነው በትግራይ ህዝብ ብቻ ነው” ሲልም አስታወቀ

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ስም እያካሄደ ያለውን ሂደት እንደማይቀበልና በሂደቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም በትግራይ ህዝብ ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው አስታወቀ።

ድርጅቱ በመግለጫው የትግራይ ህዝብ ጉዳይ በትግራይ ምድርና በራሱ በህዝቡ ብቻ ሊወሰን እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል።

2] ኢሕአፓ ሚያዝያ 30 የሚካሄድ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

ኢሕአፓ አስቻይ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት የሚካሄድ ምርጫ “አምባገነንነትን እንደሚያጠናክር” በመግለጽ ለሚያዝያ 30 የተቃውሞ ሰልፍ ጠራ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ረቡዕ ዕለት ባወጣውና ለአዲስ ማለዳ በላከላት መግለጫ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለው ነባራዊ ሁኔታ “ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም” ሲል አስታውቋል።

3] መቀጮው ካለው ኢኮኖሚ አንፃር አነስተኛ በመሆኑ  ኮንትሮባንድ የያዘ ተሽከርካሪን መውረስ አግባብ ነው ተባለ

የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ኮንትሮባንድ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ለመውረስ የሚፈቅድ እና ይህ የተወረሰው ገንዘብ ደግሞ ለተቋሙ ገቢ የሚሆንበት ሁኔታ አግባብነት አለው ሲል የጉምሩክ ኮሚሽን ገልጿል።

ተሽከርካሪዎች በኮንትሮባንድ ተሳትፈው ሲገኙ አንድ መቶ ሺህ ብር ቅጣት አሁን ካለው የኢኮኖሚ አንፃር በጣም አነስተኛ በመሆኑ መወረሱ አግባነት አለው ነው የተባለው። ይህም ማለት ተሽከርካሪዎችን ማደን ሳይሆን ኮንትሮባንድን ለመቀነስ እጅጉን ይረዳል ሲል የገንዘብ ሚንስቴርም ተናግሯል። 

4] ሲ.ፒ.ጄ. በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠየቀ

ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ጋዜጠኛ ገነት አስማማው የታሰረችበትን ሦስተኛ ዓመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው ይህን ጥሪውን ያቀረበው፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት፤ መጋቢት 28  ጋዜጠኛ ገነት አስማማው በአማራ ክልል ስለተከሰተው ግጭት በመዘገቧ ምክንያት በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ቀርቦባት መታሰሯን ድርጅቱ አስታውሷል፡፡

ድርጅቱ አድርጌዋለሁ ባለው ቆጠራ እ.አ.አ. በ2025 የታሰሩ አምስት ጋዜጠኞች በተመሳሳይ በአማራ ክልል ስለተነሳው ግጭት በመዘገባቸው በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው መታሰራቸውን አመልክቷል፡፡

#ከውጭ

1] ሰሜን ኮሪያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት እየቀነሰች መሆኑ ተገለጸ

የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ለሀገሪቱ ህግ አውጪዎች ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ሰሜን ኮሪያ ለረዥም ዘመናት የቆየውን የቅርብ ወዳጅነቷን ከኢራን ጋር ሆነ ብላ ርቀቷን በመጠበቅ ላይ ነች ብሏል።

ምንም እንኳን በሁለቱ ሀገራት መካከል በታሪካዊ ሁኔታ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ ረገድ ጥብቅ ግንኙነት  ያላቸው ቢሆንም ፒዮንግያንግ አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ ያላትን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ገድባለች ስትል ሴዑል በስለላ ድርጅቷ በኩል ማስታወቋን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

2] እንግሊዝ በባህር ስር ባሉ መሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት ሊሰነዘሩ የነበሩ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦችን አደጋ ማክሸፏን ገለጸች

የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር የሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይሎች በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ የሚገኙ የኢንተርኔት ገመዶችን እና የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን አደጋ ላይ ሊጥሉ የነበሩ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦችን ለሳምንታት በመከታተል አደጋ እንዳያደርሱ አደርጊያለሁ አለ።

ሚኒስትሩ ጆን ሂሊ በለንደን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሩሲያ የዓለም ትኩረት በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ላይ ባረፈበት ወቅት ይህንን ድብቅ ኦፕሬሽን ለማካሄድ መሞከሯን  የተናገሩ ሲሆን ይህም አደገኛ እንደነበር ገልጸዋል።

እነዚህ ዘገባዎች ባለፈው ሳምንት በአዲስ ማለዳ የፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ሊንክዲንና ዩቱብ ገጾች ከተጋሩት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የተዘረዘሩትን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ ትንታኔዎች፣ ጥንቅሮችንና ቃለመጠይቆችን ደግሞ በይፋዊ የዩቱብ አድራሻችን ተጋርተዋል። አዲስ ማለዳን ሰብስክራይብ፣ ላይክና ሼር እንድታደርጉ በትህትና እንጋብዛለን።

ዜናን ከምንጩ!

የአዲስ ማለዳ ዩቱብን በዚህ ማስፈንጠሪያ ያገኙታል፦

t.ly/vSgS
22