የአዳማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
1.12K subscribers
1.76K photos
24 videos
22 files
227 links
ይሄ የቴሌግራም ገፅ በምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የመንበረ ጵጵስና ርዕሰ ከተማ ወረዳ ቤተክህነተ በሰ/ት/ቤቶች አንድነት የተከፈተ ሲሆን በዚህ ቻናል መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ዜና ቤተክርስቲያንና ወቅታዊ ጉዳይ የምንዘግብበት ነው። እርሶም ለኦርትዶክሳውያን ሁሉ ቻናሉን በማጋራት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ድምጽ ይሁኑ።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
Download Telegram
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ መግለጫ መልእክት የሚከተለው ነው፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተላለፈ የምህላ ሱባዔ፡-

‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ አስተጋብኡ ሕዝበ ሊቃውንተ ሕዝብ፤ ጾምን ቀድሱ፣ጉባኤውንም አውጁ፤ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ኣምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ (ኢዩ ፩÷፲፬)

ሁላችንም እንደምናውቀው ያለንበት ዓለም የመከራ ዓለም ነው፣መከራው በኛ ስሕተትና ክፋት የመጣና እየሆነ ያለ መሆኑም ይታወቃል፤ እኛ የምንፈጽመው ጥቃቅንና ትላልቅ ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን እንደሚያስቈጣ በቅዱስ መጽሐፍ ተረጋግጦ ያደረ ነው፣ለዚህም ከነነዌ ነዋሪ ሕዝብ የበለጠ ማስረጃ የለንም፣የነነዌ ከተማ ነዋሪዎች በፈጸሙት ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን አስቈጥተዋል፣ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ቢሆንም እሱ ምሕረቱን ማስቀደም ስለፈለገ በዮናስ በኩል አስጠንቅቆአቸዋል፣የነነዌ ነዋሪዎችም በዮናስ በኩል የደረሳቸውን የንስሓ ጥሪ ወዲያውኑ ተቀብለው በምህላ፣በጾም፣በጸሎት ንስሓ ስለገቡ እግዚአብሔር ፍጹም ይቅርታ አድርጎላቸዋል፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን

እኛ ሰዎች ዛሬም በየሰዓቱ ብቻ ሳይሆን በየደቂቃው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ አበሳ እንደምንፈጽም ማወቅ አለብን፣አበሳውና ኃጢኣቱ ሲበዛ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነውና ወደ ዳኝነት ተግባሩ ይገባል ይህ ደግሞ በሰብአ ትካት በሰዶምና በጎሞራ ያስተላለፈውን ዳኝነት ያስታውሰናል፣አሁን ያለንበት ዘመን ዓመተ ምሕረት በመሆኑ እግዚአብሔር ለጊዜው ቢታገሠንም በኃጢኣታችን የምንጠየቅበት ጊዜ አዘጋጅቶአል፣ዛሬም ቢሆን የማናስተውለው ሆነን ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔር ተግሣጹን ማስተላለፍ አላቆምም፣ በምድራችን ላይ በምናደርሰው የተዛባ ተግባር በጐርፍ፣በድርቅ፣በመሬት መንቀጥቀጥና በአየር መዛባት እየገሠጸን እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡

እግዚአብሔር ከጥንቱ ከጠዋቱ ጀምሮ ምድርን እንድንከባከባት፣እንድናበጃት፣እንድናጠብቃትና እንድናለማት አዞናል፣ሆኖም ይህን ትእዛዙን ገሸሽ አድርገን በኬሜካልና በመርዛም ጋዝ ምድርን በመበከል፣ደንዋን በመመጠርና ራቁቷን በማስቀረት በምናደርገው ድርጊት አበሳ እየፈጸምን እንደሆነ ያወቅነው አይመስልም፤ በዚህም ምክንያት በጐርፍ፣በድርቅ ለሰው ልጆች በማይመች የኣየር ፀባይ ወዘተ... ስጋት ውስጥ እየወደቅን ነው፡፡

በሌላም በኩል በምናወሳስበው የአስተዳደር ርእዮትና መሳሳብ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ያላስፈላጊ አደጋ ላይ እንድወድቅ እያደረግን ነው በዚህም ጠንቅ ሰላም እየደፈረሰ፣ ፍቅርና አንድነት እየላላ የሃይማኖት ክብርና ልዕልና እየተነካ ራሳችንንም እየጐዳን ነው፣በዚህ ሁሉ ተግባራችን  እግዚአብሔርን እያሳዘንን ነው፣ይህ ሊገባንና ሊቈረቁረን ይገባል፡፡
 
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔውም የሚገኘው ከእግዚአብሔርና ከእኛ ነው፤ ከእኛ በንስሓ ተመልሰን ከልብ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅና ከክፉ ተግባራችን በእውነት መጸጸት ይጠበቃል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን ዓይነቱ ንስሓ ከኛ መኖሩ ሲመለከት ምሕረትና ይቅርታን ይለግሰናል፣በዚህም መፍትሔና ፈውስ ይገኛል፣ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችንና ለዓለማችን ስጋት የሆኑ የጦርነት ክሥተቶች፣የመሬት መንቀጥቀጥ፣የአየር መዛባት፣የድርቅ መከሠት፣የጎርፍ መጥለቅለቅ የሰላም መደፍረስ፣ የሰላማውያን ወገኖች መጎዳት፣የፍቅርና የአንድነት መላላት ወዘተ.... ከምድራችን ተወግደው ፍጹም ምሕረትና ሰላም እናገኝ ዘንድ በኃጢኣታችን ተጸጽተን በምህላ ንስሓ መግባት አለብን፣ከዚህ አኳያ ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ የሚጾመው ጾመ ነነዌ ለዚህ አመቺ ጊዜ ስለሆነ ከየካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ  ለሦስት ቀናት ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም ጠዋትና ማታ በየቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት እየተገኘን በንስሓ በዕንባ በጸሎት በምህላ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ እንድንጠይቅ፣እንደዚሁም በሀገራችንና በውጭ ያላችሁ ሊቃውንተ ሕዝብ ቀኖናውን ጠብቃችሁ ይህንን በማስፈጸም ምህላውን በቀኖናው መሠረት እንድታከናውኑ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን ይቅርታውንና ሰላሙን ለሀገራችንና ለዓለማችን ይስጠን፣ምህላችንንም ይቀበልልን፡፡

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!“
  
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
👍61
እንኳን ለጾመ ነነዌ በሰላም አደረሳችሁ!

ጾሙ የዲያብሎስ ድል መንሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ይሁንልን!

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)
👍7🔥1
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል እንዲሁም  የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ የአዳማ ናዝሬት ደብረ ሰላም ካቴድራል አስተዳደር ሰበካ ጉባኤ በ 2.5 ሚሊዮን ብር  ( በሁለት ሚሊዮን አምስት  መቶ ሺህ ብር )  ወጪ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪ ለሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን  ተጀራሽ ለመሆን ያስገነባውን ዘመናዊ ስቱዲዮ ባርከው መርቀዋል።
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል እንዲሁም  የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ለአዳማ ናዝሬት ደብረ ሰላም ካቴድራል የፈለገ ሰላም ዘመላዕክት ሰንበት ትምህርት ቤት የሚገነባውን ህንፃ የመሰረት ድንጋይ ጥለዋል።
👍1
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የመንበረ ጵጵስና ወረዳ ቤተ ክህነት ሰ/ት/ቤቶች አንድነት የ2017 ዓ/ም አንደኛ መንፈቅ ዓመት ማጠቃለይ ፈተና በሃያ አምስት (25) አጥቢያ ሰ/ት/ቤት ከስድስት ሺ ስምንት መቶ ዘጠና ሶስት(6893) በላይ ሥርዓተ ትምህርቱን ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎችን ለማስፈተን ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ፈተና የሚሰጠው በሀገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሲሆን ቀድሞ ከአጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች የትምህርት አፈጻጸም እና ስልጠና ክፍሎች ጋር የፈተና ዝግጅትና እና አሰጣት ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በሁሉም አጥቢያ ሰ/ት/ቤት ከ1ኛ ክፍል እስከ 5ኛ ክፍል  የካቲት 23/2017 ዓ/ም ከጠዋት 4፡00 ጀምሮ የሚሰጥ ሲሆን ከ6ኛ ክፍል እስከ 9ኛ ክፍል የካቲት 30/2017 ዓ/ም ከጠዋት 4:00 ጀምሮ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ሥርዓተ ትምህርቱ በሁለት ቋንቋ እየተሰጠ ሲሆን በአማርኛ ቋንቋ፡-
1ኛ ክፍል……….1532 
2ኛ ክፍክ…………884
3ኛ ክፍል………..560
4ኛ ክፍል………..792
5ኛ ክፍል………..346
6ኛ ክፍል…………455
7ኛ ክፍል…………942
8ኛ ክፍል………….611
9ኛ ክፍል………….403
በአጠቃላይ 6525 ሲሆን እንዲሁም በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ፡-
1ኛ ክፍል………112
2ኛ ክፍል………..46
6ኛ ክፍል………..19
7ኛ ክፍል………191
የሚፈተኑ ሲሆን በአጠቃላይ 368 ተማሪዎች በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ይፈተናሉ፡፡
ስለሆነም የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ካህናት አባቶች፣ሰባኪያን ወንጌል መምህራኖች እና የተማሪ ወላጅ ቤተሰቦች ይህንን የፈተናው መርሐ ግብር በተሳካ ሁኔታ እንዲሰጥ ከሰ/ት/ቤቱ ጎን በመሆን እንድታግዙ ስንል ሰ/ት/ቤት አንድነቱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
👍62🤔1
👍5