የአዳማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
1.11K subscribers
1.77K photos
24 videos
22 files
227 links
ይሄ የቴሌግራም ገፅ በምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የመንበረ ጵጵስና ርዕሰ ከተማ ወረዳ ቤተክህነተ በሰ/ት/ቤቶች አንድነት የተከፈተ ሲሆን በዚህ ቻናል መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ዜና ቤተክርስቲያንና ወቅታዊ ጉዳይ የምንዘግብበት ነው። እርሶም ለኦርትዶክሳውያን ሁሉ ቻናሉን በማጋራት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ድምጽ ይሁኑ።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
Download Telegram
በአዳማ ናዝሬት ደብረ ታቦር ምስራቀ ፀሀይ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የፈለገ ብርሃን ሰንበት ትምህርት  ቤት  የነዳያን ምገባ መርሃግብር አከናወነ፦   ሰንበት ትምህርት  ቤቱ በየአመቱ የትንሳኤ ዕለት እንደሚያደርገው ዘንድሮም ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖች  ሰብስቦ  በአጥቢያው ያሉ ነዳያንን፣ እስረኞችን፣ በግቢው የሚገኙ ፀበልተኞችን እና ሌሎችንም የተቸገሩ የታመሙ ወገኖችን የምገባ መርሃግብር አዘጋጅቷል።
በናዝሬት ደብረ መድሃኒት መድሃኒዓለም ገዳም እና ካቴድራል የፈለገ ጥበብ ሰንበት ትምህርት  ቤት  የነዳያን ምገባ መርሃግብር አከናወነ፦   ሰንበት ትምህርት  ቤቱ በየአመቱ የትንሳኤ ዕለት እንደሚያደርገው ዘንድሮም በአጥቢያው ያሉ ነዳያንን እና ሌሎችንም የተቸገሩ የታመሙ ወገኖችን ምግብ በማዘጋጀት የምገባ እና የትምህርት መርሃ ግብር አከናውኗል።
👍4🥰1
ወቅታዊ መልእክት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ (ሀገር አቀፍ) የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከውጪና ከውስጥ የሚቃጡባትን ፈተናዎች በመቋቋም ከውጭ የሚቃጡባትን ፈተናዎች ሰማዕትነትን በሚቀበሉ ልጆቿ ምስክርነት፣ ምንፍቅናን በቃል የመጣውን በቃል በመጻሕፍት የመጣውን በመጻሕፍት በመመከት ሐዋርያዊ ቅብሎሿን ጠብቃ መሠረተ እምነቷን፣ ዶግማና ቀኖናዋን ቅዱስ ትውፊቷን ለትውልዱ እያስተማረች ጸንታ ቆይታለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ በልዩ ልዩ ውጫዊ ፈተናዎች ዋጋ እየከፈለች ያለች ቢሆንም ከሁሉ የከፋው ግን ከክብር በላይ የላቀ ክብር ባጎናጸፈቻቸውና እረኛና ጠባቂ እንዲሆኑ ባሰማራቻቸው ልጆቿ በተደጋጋሚ እየገጠማት ያለው የቀኖና ጥሰት ነው። የጥር ፲፬ ጳጳሳት ሹመት፣ የትግራይ ሲኖዶስ፣ የቅባት ጳጳሳት ሹመት ፤ ፖለቲካን ተጠግቶ ቤተክርስቲያንን የማጥቃት ክፉ ግብር ሳያንሳት ፤በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ የምንፍቅና ትምህርቶች የሚያስተላፉትን  በዝምታ መመልከት እየበዛና በዚህም በጎቿን ከበረቷ ለማስነጠቅ ለሚሠሩ ሁሉ ተባባሪ በመሆን የሚኬድበት ርቀት ቤተክርስቲያኒቱን ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ በቃ ሊባል ይገባዋል፡፡ ለማሳያ ይሆን ዘንድ በአቡነ በርናባስ መባልእትንና ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ፤ በአቡነ ፊልጶስ እመቤታችንና ሥላሴን አስመልክቶ የተናገሩትን የስሕተት ትምህርቶች ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ የሊቃውንት ጉባኤ በወቅቱ ማስጠንቀቂያም ሆነ የእርምት እርምጃ ባለመውሰዳቸው ዛሬ በአቡነ ገብርኤል እመቤታችንንና ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ ያውም በዐውደ ምሕረት፣ እንዲሁም በዕለተ ስቅለት በተደረገ የአዳራሽ ጉባኤ ለተናገሩት የኑፋቄ  ትምህርት አድርሶናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን ገፊ እንደሆነች እና ስለክርስቶስ የሚዘምሩትን እንደምታባርር እርሷም ስለ ክርስቶስ እንደማትዘምር በአደባባይ በጉባኤ ያለምንም ፍርሀት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያን ጨምሮ የተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳት በኑፋቄ ትምህርት ማስፋፋት ላይ የተሰማራውን “ፍኖተ ጽድቅ” ማኅበርን በገንዘቡ በሚሠራቸው የስቱዲዮ ግንባታ፣ የመጽሐፍ ኅትመት እና የመሳሰሉት ተግባራት በመማረክ የቤተክርስቲያንን ክብር አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ አንዳንድ መምህራን እና ማኅበራትም ተሳታፊ መሆናቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡

ይህ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል የሚከተሉት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።

1. የአስተዳደር ብልሹነት የወለደው  ዘርፈ ብዙ ችግር
በእኛ መረዳት አሁናዊው ፈተና እና ችግር ከውጪያዊው የዝግጅት ጥቃትና ፈተናም በላይ የበረታው የውስጥ ችግር ነው። ለዚህም ዋናውና አንደኛው የሁለንተናዊ ድካማችን ምክንያት የቤተ ክህነቱ ብልሹ አስተዳደር  ነው።
አሁን ላይ ያለው የቤተ ክህነት  አስተዳደር ዘመኑን በመዋጀት  የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተልዕኮ  በማስፈፀም  ነፍሳትን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ለማብቃት  የሚያስችል  ቁመና እና ብቃት ላይ አይገኝም ።  ሕግ አውጪ፣ ሕግ ፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ አንድ አካል በመሆን፣ ተጠቅልሎ በተያዘ ሥልጣን ቤተ ክርስቲያኒቱ እጅ ተወርች ተቀፍድዳ  ወደ ትውልዱ እንዳትደርስ እየተሠራ ይመስላል።

ቤተ ክርስቲያን በማይመጥናት ደካማ አስተዳደር ምክንያት ከተመሠረተችበት ነፍስ የማዳን መንፈሳዊ ተግባር ተናጥባለች። አስተዳደሩ ምእመናንን ለመንፈሳዊ ፍሬ ከማብቃት ይልቅ   ለውድቀታቸው ምክንያት ሆኗል። በተለያዩ ጊዜያት ተጠንተው የቀረቡ ልዩ ልዩ የአስተዳደር ማሻሻያዎች እየተኮላሹ ጉዞው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል:: በ ፳፻ወ፬ ዓ.ም ለሲኖዶስ የቀረበው የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጥያቄ ፲፫ ዓመታት ሲገፋ ቆይቶ አሁንም ቦታ ተነፍጐታል። አስተዳደራዊ ለውጥ ጠልነቱ ተባብሶ ቀጥሏል። እኔ ብቻ በሚሉ ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግል ተቋማቸው በሚያዩ አካላት ተወራለች:: በሃይማኖት ችግር ፣ በቀኖና ጥሰት እና በሙስና ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አካላት የተሻለ ሹመትና ሽልማት ይሰጣቸዋል፡፡

2. ለሊቃውንት ጉባኤ ትኩረት መነፈጉ
የሊቃውንት ጉባኤ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው በመቅረቱ ፣ እንዲሁም ሊቃውንት ክብራቸው ባለመጠበቁ እና ከውሳኔ ሰጪነት ድርሻ በመገለላቸው ፤ ለስሑት ትምህርት በሚገባው መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ሆኗል:: እንዲሁም በቤተክርስቲያኒቱ ስም ለሚታተሙና ለሚሰራጩ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ የምስልና የድምፅ እንዲሁም የኅትመት ውጤቶች የመገምገምና ዕውቅና የመስጠት ሥልጣኑ ተነጥቋል። የአደረጃጀትና የመከላከል አቅሙ   በመዳከሙ፤ በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ  ሐሰተኛ መምህራን በአፍም በመጽሐፍም  ስሁት ትምህርታቸውን  በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት እያሰራጩ ይገኛሉ።

ትናንት አባቶች ያቆዩትን ሀብት መንዝሮ መጠቀም እንጂ የራሳቸውን አሻራ የማያኖሩ፣ ሀብት ንብረቷን ጠብቀው ከማቆየት ይልቅ ለግል መዝብረው ቀሪውን ለዘራፊ አሳልፈው የሰጡ ከመንፈሳዊ ክብር በጐደሉ፣ በሥጋ ሐሳብ ጨርሶውኑ በተወሰዱ፣ ምግባር በጎደላቸው ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ባሉ አገልጋዮች እየተፈተነች ትገኛለች።
ያለ ዋጋ ከሚሰጠው መንፈሳዊ ሹመት ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚጎዳ  እኩይ ተግባር በእጅ መንሻ የሚፈጽሙ አካላት በሁሉም መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን  ዓላማ እንዳታሳካ ሳንካ ሆነውባታል።

ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሕግ እና በሥርዓት ዝግጅቷ እንከን አይወጣላትም። ነገር ግን ከሕግና ከሥርዓት ባፈነገጡ፣ ሐሰተኛ ትምህርት በሚያሰራጩ እና ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ ሕይወት ወስጥ በሚመላለሱ በተለይ በሁሉም መዋቅር ወስጥ በሚገኙ አገልጋይ ሠራተኞች ላይ ተግባራዊ ርምጃ አለመወሰዱ ለምእመናን ተስፋ መቁረጥ እና ፍልሰት ምክንያት ሆኗል ።
3. በሕግ ከተሰጣቸው መብት ውጪ በማስተማር የሚሰማሩ ማኅበራትን በሕግ አግባብ ወደ መስመር አለማስገባት
የሰሞኑ ስሁት ትምህርት በሕጋዊ ዕውቅና ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት እኩይ ተግባር ከትናንት የቀጠለ የብልሹ አስተዳደር መገለጫ ነው። የማኅበራት አስተዳደር ደንብ ፀድቆ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ደንቡ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስረጃ በማስደገፍ የማሻሻያ ሐሳብ  ብናቀርብም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በመሆኑም የፈራነው ደርሶ ፤ ደንቡን ለማስፈፀም የተቀመጠው የማኅበራት ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር  መምሪያ፤ በማኅበራት አስተዳደር ደንብ አንቀጽ ፲ ላይ የማኅበራት ዓለማ "ለትምህርት ተጠሪ ተቋማት ድጋፍ መስጠት ነው" በሚል የተደነገገ ቢሆንም  እንደ ‹‹ፍኖተ ጽድቅ›› ያለ ማኅበር ድጋፍ ሰጪ ሳይሆን ፈፃሚ ሆኖ፣ ማኅበሩ ከተመሠረተበት ዓላማ ውጭ ትምህርተ ወንጌልን በአዳራሽ ውስጥ  ሲሰጥ፤ በሚዲያ ትምህርት ሲያስተላልፍ አልፎ ተርፎ የቤተ ክርስቲያን መዝሙሮቿን ከሥርዓቷና ከቀኖናዋ ውጪ በሆነ ሁኔታ በሚዲያ እያቀናበረ ሲያስተላልፍ ተገቢው አስተዳደራዊም ሆነ ቀኖናዊ  እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ ይልቅ በማኅበርነት በመመዝገብ እንዲሁም በደንቡ የተሰጠውን የመቆጣጠር ሓላፊነት የማኅበራት ማደራጃ ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ ባለመወጣቱ ዛሬ ለደረሰው ስሑት ትምህርት ዝግጅትና ስርጭት አብቅቶናል፡፡
👍1
ይኽ ማኅበር ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተህምሮ ውጪ ስሑት ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም እንደሆነ  በተጨባጭ እየታወቀ እና በአካል ቀርበው  አረጋግጠው  እንኳን ቅዱስ ፓትርያርኩን በዚያ ሥፍራ እንዲገኙ በማድረግ  ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው የሰጡ  የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መኖራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡

በመሆኑም ከዚህ በታች የዘረዘርናቸው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጣቸው እና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው  እናምናለን። 

1. የሊቀ ጳጳሱ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ብናምንም በሚገባ እና በትኩረት ጉዳዩ እንዲታይና መፍትሔ እንዲሰጠው፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይም ስሑት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ እና ያስተማሩ ሌሎች ጳጳሳት እና መምህራን  ጉዳይም አብሮ እንዲታይ፣ ይኽን አጋጣሚ ተጠቅሞ የሊቃውንት ጉባኤም በስሑት አስተምህሮዎች ላይ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ቢደረግ፡፡

2. ሓላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣው የማኅበራት ምዝገባና ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ ከሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሓላፊዎች  እንዲጠየቁ፡፡

3. የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ የዕውቅና ሰርተፊኬት ከመቸርቸር ወጥቶ፣ ደንቡና አሠራሩን ዳግመኛ በመፈተሽ፣ የዕውቅና አመዘጋገብ፣ ክትትልና ቁጥጥር ሒደቱም ንጥር ያለ እና መስፈርቶች የወጡለት እንዲሆን፡፡

4. ቅዱስ ፓትርያርኩን በማሳሳት " ፍኖተ ጽድቅ " በተባለው ማኅበር ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ያደረጉ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊና የፖትርያርኩ የፕሮቶኰል ሹም እንዲጠየቁ፡፡

5. ‹‹ፍኖተ ጽድቅ›› የተሰኘው ማኅበር በቤተክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለውን የተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ባለማረሙ ምክንያት ማኅበሩ የምዝገባ ፈቃዱ ተሰርዞ ባስተላለፈው ትምህርቶች በቀኖና እንዲጠየቅ እና በዚሁ አጋጣሚ ከመምህራን እስከ ሊቃነ ጳጳሳት “ፍኖተ ጽድቅ” ከተባለ ማኅበር ጋር የጀመሩት በነዋይ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲደረግ። እንዲሁም በቤተ ክህነቱ የበላይ ሓላፊዎች በኩል  እናት ቤተ ክርስቲያናችን አንዳች ሳይጎድልባት ባልተገባ መሻት ከባለ ጸጋ እጅ ለማኝ በማድረግ ቅድስት ቤተክርስቲያንን የማዋረድ እና አሳልፎ የመስጠት  እኩይ ተግባር እንዲቆም።

6. የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎቷን እንዳታሰፋ እጅ ተወርች ቀፍድዶ የያዛት ደካማ፣ ብልሹ አስተዳደር እንዲስተካከል በልጅነት መንፈስ በተደጋጋሚ የችግሮቹን ማሳያና መፍትሔዎቹን፣ ሥርዓተ መዋቅርን  በመጠበቅ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ  ጉባኤ ድረስ ቢያቀርብም ተጨበጭ ምላሽ አልተሰጠውም ። ይህም ጉዳይ ከግንዛቤ ገብቶ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል።

ነገር ግን አሁንም እንደ ቀድሞው ተሸፋፍኖ የሚታለፍ  እና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ታላቋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስትያን  የማይመጥነው ብልሹ አስተዳደር የሚቀጥል ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ሊቃውንት፣ ምእመናን፣ እና የሰንበት ት/ቤት አባላት ጋር በመሆን የምንረከባትን እና ለትውልድ የምናሰረክባትን እናት ቤተ ክርስቲያን የምንታደግበትን መንገድ የምንከተል መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
ሚያዚያ ፳፩ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)
5
ቋሚ ሲኖዶስ ልዩልዩ ውሳኔዎችን አስተላለፈ።

ሚያዚያ ፳፪/ ፳፻፲፯ ዓ.ም

ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከቤተክርስቲያናችን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጪ በፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር አዳራሽ የሰጡትን ትምህርትና በማኅበሩ ሚዲያ የተላለፈበትን ሁኔታ በተመለከተ በዛሬው መደበኛ ጉባኤው በሰፊው ተወያይቶ ለመወሰን በያዘው ቀጠሮ መሰረት በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

1. ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማህበር በተለያዩ ጊዜያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጪ በሚዲያው ያስተላለፈው የስሕተት ትምህርት የቤተክርስቲያናችንን አባቶች፣ሊቃውንቱንና መላው ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነ በመሆኑ በማህበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ በኩል ጊዜያዊ የእገዳ ደብዳቤ እንዲደርሰው እና በመምሪያው በኩል አስፈላጊው ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ሆኖ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ይቻል ዘንድ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲቋቋም አድርጓል።

በዚህም መሰረት ቋማ ሲኖዶስ ያቋቋማቸው አጣሪ ልዑካን አጠቃላይ የማህበሩን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እና በሚዲያው ያስተላለፋቸውን የስህተት ትምህርቶች በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ከማህበራት ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ክትትል መምሪያ ጋር በመነጋገር በሚገባ መርምርውና አጣርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያቀርቡ፣
2. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ማርያም ቤዛዊተ ዓለም” አትባልም በማለት ከቤተ ክርስቲያናችን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጪ የሰጡት ሕጸጽ ያለበት ትምህርት በሊቃውንት ጉባኤ በኩል በሚገባ ተመርምሮና ተጣርቶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ለቋሚ ሲኖዶስ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ብፁዕነታቸውም ጉዳዩ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተአቅቦ እንዲቆዩ፣

3. ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና ብፁዕ አቡነ በርናባስ የደቡብ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፏቸው የስሕተት ትምህርቶችና በሌሎችም መምህራን የተላለፉ ነቀፋ ያለባቸው ትምህርቶች ካሉ የሊቃውንት ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አንጻር በሚገባ መርምሮና አጣርቶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያቀርብ፣

4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኝ ብዙኃን ስርጭት ድርጅት ለፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማህበር ሚዲያ የአየር ሰዓት የሰጠበትን ዝርዝር ሁኔታና ከማኅበሩ ጋር በተያያዘ አየር ላይ ያዋላቸውን ትምህርቶች የሚያሳይ ሪፖርት እንዲያቀርብ ይደረግ በማለት ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖ የዕለቱን ጉባኤ በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ አጠናቋል።

ምንጭ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
👍4
በመንበረ  ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት በሊቃውንት ጉባኤ አዘጋጅነት ለሦስት ተከታታይ ቀናት በዘርፈ ብዙ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ሲመክር  የቆየው  የሊቃውንት  የምክክር ጉባኤ ባለ 14 አንቀጽ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት  ተጠናቋል። የመግለጫው ሙሉ ሐሳብ   እንደሚከተለው ይነበባል።

============================
ሚያዚያ 22 ቀን 2017ዓ.ም አዲስአበባ 

እኛ ሊቃውንት እንደምንረዳው ጉባኤ ኒቅያ በምንልበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አነጋገር  ጉባኤ ተደረገ ሲባል ሰዎች ተሰብስበው ይህን ማመን አለብን ያንን መተው አለብን ብለው በድምጽ ብልጫ ተስማምተው የጋራ መግለጫ አወጡ ማለት ሳይሆን ሰፊ እርሻ /ሁዳድ/ ያለው ገበሬ በአዝመራው መሐል እህሉን መስሎ አዝመራውን የሚጎዳ የሚያበላሽ አረም ሲበቅልበት ከእህሉ መካከል አረሙን በጥንቃቄ ነቅሎ እንደሚጥል ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም ክርስቶስን በዓይኗ ዓይታ ትምህርቱን በጆሮዋ ሰምታ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን በአባቶቻችን በሐዋርያት አማካይነት የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ዓይታ በምታውቀውና በምታምነው እውነተኛ ሃይማኖት መሐል የራሷን እምነት ሳይሆን ተመሳስሎ የሚጎዳትን የመናፍቃን የአስተሳሰብ አረም ነቅላ ለመጣል አረሙን ነቅላ ትምህርት አዝመራዋን ትከላከላለች፡፡በኒቅያ ጉባኤም የተደረገው ይኸው ነው አረም አርዮስ ተነቀሎ የክርስቶስ አምላክነት በምላት በስፋት ተነገረ የሃይማኖት መግለጫ የሆነው ጸሎተ ሃይማኖት ጸደቀ ፡፡ እኛም የሠለስቱ ምዕት የልጅ ልጆች የኢትዮጵያ ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የበቀለውንና እየበቀለ ያለውን አረም በትምህርት የአረም ማጥፊያ መድኀኒትነት ለመንቀል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ምእመናንን ለማጽናት በዚህ በመንበረ ፓትርያርክ ቅጽረ ግቢ ተሰብስበን መክረን ተወያይተን-

1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በጉባኤው መክፈቻ የሰጡትን ቃለ ምእዳን አባታዊ መመሪያና ቡራኬን በመቀበል የሰጡትን አባታዊ መመሪያ በየመጣንበት ጉባኤ ቤት ሥራ ላይ ለማዋል ቃል እንገባለን፡፡

2. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጉባኤው መክፈቻና በየመርሐ ግብሩ መካከል ያስተላለፉትን የሥራ መመሪያ ወቅቱ በሚጠይቀው ቤተ ክርስቲያን በምትፈልገው ምእመናን ለሚጠይቁት ጥያቄ ሁሉ ምላሽ ለመስጠት በየጉባኤ ቤታችን ከማስተማር ከማገልገል ባሻገር እንደአባቶቻችን ለሃይማኖታችን አለኝታና ጠበቃ ሆነን ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

3. ጥንታዊት ሐዋርያዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም ታሪኳ ውስጥ ባሳለፈቻቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ያካበተችውን የእቅበተ እምነት (ሃይማኖት) ልምድ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያሉትን የዐቃብያነ ሃይማኖት ተጋድሎዎች በመረዳት ቅብብሎሹን ለማስቀጠል ቃል እንገባለን፡፡

4. አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን ከሚከሠቱት አሉታዊ ግድፈቶችና ሥርዋጾች መካከል በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በገድላት፣በድርሳናትና በታአምራት የቤተ ክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍት በመከለስ በመሸቀጥና በመበረዝ መንፈሳዊነታቸውን ለቀው የተዛባ ሐሳብ እንዲኖራቸው ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሐሳብ እንዲወጡ የሚደረገው ሴራ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ስለሆነም ጥንታውያን በቀኖና መጻሕፍት የተሠፈሩና የተመዘኑ መጻሕፍቶቻችን ባሉበት ሁኔታ ተጠብቀው ይቀጥሉ ዘንድ እኛ የጉባኤ መምህራን የመጻሕፍቱ ጠበቃ በመሆን  በሊቃውንት ጉባኤ በኩል ያላለፉ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት አሳታሚነት ያልታተሙ መጻሕፍት ባለመጠቀም ደቀ መዛሙርትና ምእመናን እንዳይገለገሉባቸው ለማስተማር ቃል እንገባለን፡፡

5. የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥዕላት፣መስቀል፣ሥነ ሕንፃና ኪነ ጥበብ ይዘትና ቅርጽ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተለካ ሃይማኖታዊ ምሳሌነታቸው እንደ መጻሕፍት የሚነበብ እንደሰው የሚናገሩ እንደ መምህራን የሚያስተምሩ ንዋያት ናቸው፤ስለሆነም እነዚህን ንዋያተ ቅድሳት በየዘመኑ የሚነሱ የውስጥና የውጭ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የተለያየ ስሜት እንዲፈጥሩ የሚሰጡት ትርጉም እንዲዛባ ለማድረግ የሚያደርጉት ሙከራ እጅግ ብዙ ነው አባቶቻችን በብዙ ውጣ ውረድ ያቆዩልንን የስገኙልንን  እነዚህን ንዋያተ ሃይማኖት ጠብቀን በማስጠበቅ ጥቅማቸውን በማስተማር ባሉበት ሁኔታ ለትውልድ ለማስተላለፍ ምትክ የሌለውን ድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

6. አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱን የውስጥ ሁኔታ በማጤን ራሳቸው በሚሰጡን አጀንዳ በሚፈጠር  የተዛባ የፖለቲካ አመለካከት የመሪዎችን አቋምና ትከሻ በመለካት በሚገኝ አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ሠርጎ በመግባት ኑፋቄን በመዝራት በቀኖና፣በታሪክና በትውፊት በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በዜማ በቅዳሴ በትርጓሜ በበዓላት አከባበር ላይ ሁሉ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑ እንግዳ ነገሮችን ሊያሸክሙን እንደሞከሩና አንዳንዶቹም አዳዲስ ትርክት እንደጫኑብን ታሪክ እንደቀየሩብን በማኅበረሰቡ ውስጥ ቅራኔ እንደፈጠሩብን ከቀረቡት ጥንታዊ ጽሑፎች ተረድተናል፡፡ስለሆነም የደረሱብን ችግር የቀኖና የትውፊት የታሪክ ተፋልሶ ስህተቶችን በማኅብረሰቡ ውስጥ ሠርጎ የገባ የትርክት አረሙን ከስንዴው በጥንቃቄ በመለየት ወደ ጥንታዊ ማንነታችን ለመመለስ የሚጠበቅብንን ሁሉ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ጀምሮ መከፋፈል ያልገጠማት    የተማከለ የአስተዳደር መርሕ ስለምትከተልና ወጥ በሆነ የአሰራር መዋቅር ስለምትመራ መሆኑ የታወቀ ነው፤ስለሆነም ከቤተ ክርስቲያናችን ኣንጻር የተማከለ ኣሰራር የተሻለ ውጤት እንዳለው ለቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖትና ሥርዐት መጠበቅ ጠቃሚ መሆኑን ስለተገነዘብን  ማእከላዊ መዋቅራችንን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ተስማምተናል፡፡

8. በአምስት ሊቃውንት ቅዱሳን ስም በቡድን ተከፋፍሎ በየርእሱ የተደረገው ውይይትና  የመፍትሔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ቡድኑ የተወያየበት ሠነድ የዚህ ቃለ ጉባኤ አካል በማድረግ ጥቅል ሠነዱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ የሚድረግ ሆኖ ለማሳያ ያህል በክብዙ በጥቂቱ በአቋም መግለጫ እንዲወጣበት አድርገናል፡፡በዚህም መሠረት

ሀ. በነገረ ማርያምንና በነገረ ክርስቶስን ዙሪያ በጉባኤው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በዚህ ዙሪያ ውይይት ያደረገው ቡድን ለሚነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽ የሚሰጡ ከቅዱሳት ማጻሕፍት በማጣቀስ የውይይቱን ውጤት አቅርቧል በዚህም መሠረት፡- እመቤታችን በተመለከተ ጊዜውን ተደራሽ ያደረጉ ጥያቄዎች ጥንተ አብሶን፣ ቤዛዊተ ዓለም፣ አማላጅነት፣የጌታችን ወንድሞችና የእመቤታችን ትንሣኤና ተያያዝ ጥያቄዎች በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሰፊ ውይይትና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል ስለሆነም ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ አባቶቻችን ነቢያት፣ አባቶቻችን ሐዋርያት ቀደምት ሊቃውንት ያቆዩልንን የነገረ ማርያም ትምህርት ዛይበረዝ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጠንክረን እናስተምራለን፡፡
ለ. በነገረ ክርስቶስ ዙሪያ በውስጥና በውጭ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ወልድ ፍጥር በሥጋው ይባላል ወይ? ሊቀ ካህናት ቤዛ አስተራቂነት ነገረ ድኅነት ነገረ ቅብዓት በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሰፊ ውይይትና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል ስለሆነም ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ቀደምት ሊቃውንት ያቆዩልንን የነገረ ክርስቶስ ትምህርት ዛይበረዝ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጠንክረን  እናስተምራለን፡፡

ሐ. አንድምታ ትርጋሜን በተመለከተ ጉባኤው በስፋትና በምልዓት ውይይት አድርጓል በመሆኑም ትርጋሜው ዘሩን ሳይለቅ መሻሻል እንዳለበት በመጀመሪያ በመምህር ኤስድሮስ ከዚያም በአዓጼ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ማስፋፍያ እንደተደረገበት ታሪክ ያስረዳል። በሀገሪቱ ያሉ የመጻሕፍት ትርጋሜ ሊቃውንት የሚስተካከሉ አካባቢያዊ ቃላትን ለማስተካከልና ለማዘመን  የትርጋሜውን የማሻሻል ሥራ የሚሠሩ ሰዎች በእውቀት ፥ በእምነትና በሥነ ምግባር የጎለበቱ ፥ ከእኔነት ሥሜት ወጥተው የቤተ ክርስቲያን ሐሳብ ብቻ የሚከተሉ ርቱዓን መምህራን መሆን እንዳለባቸው ጉባኤው በአጽንዖት ያሳስባል።

11. በሢመተ ክህነት እና በሥርዐተ ምንኩስና ላይ የሚታዩ ጉልህ ጉድለቶችን በሚመለከት በርካታ ችግር መኖሩ በቡድን ውይይቱ በስፋት ተገልጧል ይህን ችግር ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ ለክህነት አገልግሎት የሚያበቃ የትምህረት ዝግጅትና ሥነ ምግባር የእድሜ ወሰን ታይቶ እንደ ቀኖና ቤ/ክ/ መሠረት ከሚኖርበት አጥቢያ ቤ/ክ በቂ ማረጋገጫ ተሰጥቶ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብቻ እንዲሰጥ እንዲደረግ እንጠይቃለን። በተጨማሪም ሥርአተ ምንኩስና ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሥርዐተ አበውን ጠብቆ መሥፈርቱን አሟልቶ በየቦታው የሚሠጠው ምንኩስና ቀርቶ በታወቁና በጥንታውያን የምንኩስና ገዳማት  ብቻ እንዲሆን አበክረን እንጠይቃለን፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የሊቃውንት ጉባኤን በየአህጉረ ስብከቱ ማደራጀት እና በማዕከል ካለው የሊቃውንት ጉባኤ ጋር ተናቦ መሥራት እንዲቻል ምን ቢደረግ ይሻላል? ለሚለው የሊቃውንት ጉባኤው በየ አህጉረ ስብከቱና በየወረዳው ቢደራጅ እጅግ መልካም በመሆኑ በቡድን ውይይቱ በስፋት ስለተገለጠ ሁለገብ ሙያ ባላቸው ሊቃውንት ተደራጅቶ የሚመሰገንበትና የሚወቀስበት የተሰፈረ የተቆጠረ የሥራ መዘርዝር ተዘጋጅቶለት እንዲሠራና በዚህ ዘርፍ የሊቃውንት ጉባኤ ሐላፊነቱን እንዲወጣ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

12. ሀ.  አዋልድ ቅዱሳት መጻሕፍትን በተመለከተ አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡ መፍትሔው ምን መሆን አለበት) እንዴት ይታረም) አርትዖትስ እንዴት ይፈጸም) የሚለው የውይይት ሐሳብን በተመለከተ ፡-አዋልድ መጻሕፍት በተለይም ገድላትና ድርሳናት ብዛት ያላቸው የተለያዩ ቅጂዎች ስላሉአቸው ቅጂዎቹ ተሰብስበው በሊቃውት ሊመረመሩና እውነተኛው ሊለይ እንደሚገባ፤በመጻሕፍቱ ውስጥ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር ሊያጋጩ የሚችሉ፣ በተለይም ክርስቲያኖች በቁጥር አንሰው በሚታዩባቸው አካባቢዎች አገልጋዮች ካህናትንና ምእመናንን ለጉዳት የሚዳርጉ ሐሳቦችን የያዙ መጻሕፍት መኖራቸው የሚሉ በርካታ ነጥቦችን በማንሳት ቡድኑ በስፋት ተወያይቷል ከዚህ በመነሳት በመፍትሔ ሐሳብ ደረጃ የተቀመጡትንና ጉባኤው የተስማማባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች፣ምእመናን ባለመረዳት እንዳይደነጋገሩ አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸው መጻሕፍትን ለይቶ ለማሳወቅ አስቀድሞ በተጻፉ የብራና ቅጂዎች ውስጥ ሳይኖሩ በኋላ በስርዋጽ የገቡ ጤናማ ያልሆኑ ሐሳቦች ከጥንት ቅጂዎቻቸው ጋር በማመሳከር እና እውነተኛውን በመለየት ለማረም፣ከገድላት ከድርሳናት ከዜማ መጻሕፍትም ሆነ ከሌሎች አዋልድ መጻሕፍት ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን ለይቶ ማብራራት፣ ማስማማት፣ ማስታረቅ የሚስፈልጋቸውንም ማስታረቅ፣ በስርዋጽ የገባውን በበቂ ጥናት ተለይተው እንዲታረሙ አስፈላጎውን ጥረት እናደርጋለን፣

ለ. የቤተ ክርስቲያን የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍትና ሌላ ማንኛውም ነገር ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ያሉ አካላት እንዳያሳትሟቸውና እንዳይጠቀሙባቸው እንዴት እንከላከል) የሚለውን ሐሳብ በተመለከተ የተነሱ ጭብጦች፡- የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት ግለሰቦች በስማቸው እያሳተሙ ቤተ ክርስቲያን ባለ ቤትነቷን እያሳጧት መሆኑን፣ የትርጓሜና የዜማ መጻሕፍት የየቤታቸው ባህል ስላላቸው ወጥ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ ፣ አሳታሚዎችም ያለቤተ ክርስቲያን ፈቃድ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን እያሳተሙ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ መሆኑ፣በትንሣኤ  የማተሚያ ድርጅት ብቻ ይታተምልን በማለት ቡድኑ በስፋት ተወያይቷል ። ከዚህ በመነሳት የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት ግለሰቦች በስማቸው ሊያሳተሙ ስለማይገባ የመጻሕፍቱ ባለቤት ቤተ ክርስቲያን ሆና ለግለሰቦች ሳይሆን ለምስክር ጉባኤ ቤቶቹ፣ ለመንፈሳዊ ኮሌጆቹና ዩንቨርስቲዎች እውቅና እየተሰጠና በሊቃውንት ጉባኤ ሰሰእየታረመ የየቤቱ ባህል ተጠብቆ እንዲታተም የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፣ አሳታሚ ድርጅቶችም የቤተ ክርስቲያን ሀብቶች የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት  ያለቤተ ክርስቲያን ፈቃድ እያሳተሙ ለግል ጥቅማቸው እንዳያውሉ፣ ቢያትሙም ተጠያቂዎች የሚሆኑበትን አሠራር መፍጠር ፣የቤተ ክርስቲያን ሀብቶች የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያለቤተክርስቲያን ፈቃድ እያሳተሙ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ግለሰቦችም እንዲታረሙ ጥብቅ መመሪያ ከማስተላለፍም በተጨማሪ ምእመናን በማዕከል ያልታተሙ መጻሕፍትን እንዳይገዙ መመሪያ ቢተላለፍ፣የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን።

13. ዕቅበተ እምነትን በተመለከተ የሚታዩ ጉድለቶች ምን ምን ናቸው? የመፍትሔ   ሐሳቦችስ?ምንም ሳይማሩ ሥልጣነ ክህነት የሚቀበሉና በአስተዳደር ሥልጣን የሚሾሙ አሉ፤ በቂ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ሳይኖራቸው ክህነት የተቀበሉ በሥልጠና ቢያስታካክሉ፤ ወደፊት የሚቀበሉ ዐውቀው እንዲቀበሉ ቢደረግ የሚሉና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ቡድኑ ተወያይቶባቸዋል። ስለሆነም ይህም ችግር እንዲስተካከል የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡

14. ሀ. በማኅበራዊ ሚድያ የሚሠራጩ የሃይማኖት ትምህርቶችን እንዴት እንከታተል? የሚፈጠሩ ችግሮችንስ እንዴት እንፍታ? እንዳያሻው የሚስተምርን እንዴት እንከላከል ስለሚለውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚዲያ በማጠናከር ለሁሉም ተደራሽ መሆን የሚቻልበት አሠራር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተጠንቶ ተግባራዊ እንዲሆን እየጠየቅን ምእመናንም ከእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ ትምህርቶችን እንዲከታተሉ እናስተምራለን፡፡

ለ. የቤተ ክርስቲያን አንድነትንና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና መጠበቅ የሚቻለው በምን ዘዴ ነው? ማእከላዊነት መጠበቅ፣ ጠንካራ የሕግ አስተዳደር እንዲኖረን ማድረግ፣ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ሕግ የሚከበርበትን ሁኔታ ማጠናከር፣ ልጆቻችን በመላው ዓለም ስለሚገኙ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ሕልውና፣ ልዕልና እንደ ሌሎች አብያት ክርስቲያናት ዓለም አቀፍ ሥራ መሥራት፡ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡
ሐ. በአብነት ት/ቤቶች፣ መምህራን፣ እና ተማሪዎችን እንዴት እንከባከብ? ተጨማሪ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥልጠናዎች እንዴት ይካተቱ? የአብነት ትምህርትን ቤቶች የሊቃውንት መገኛ፣ የቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የአገልጋዮቿ ሁሉ ምንጭ በመሆናቸው ለአብነት ትምህርት ቤት ልዩ የሆነ ትኩረት መስጠት ስለሚያስ ፈልግ፤ በየአጥቢያው የሚደራጁበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ ለአብያተ ጉባኤ በየደረጃው ልዩ መተዳደሪያ/ሥርዐት እንዲዘጋጅ፣ እንደሚገኙበት ቦታ በገጠር፣ በከተማ፣ በገዳምና በአድባራት ተሳቢ ያደረገ ድጋፍ፣ ክትትል፣ እንክብካቤ፣ ዋስትና፣ ዘላቂ የሕልውና ድጋፍ እንዲደረግ ጠንካራ መመሪያ እንዲወርድ እየጠየቅን እኛም የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

በመጨረሻም፡-
ይህ በሀገር ደረጃ እንዲህ ባማረ ሁኔታ ሊቃውንት ተሰባስበን እንድንመካከር እንድንወያይ በታሪካችን የዚህ እድል ተቋዳሽ እንሆን ዘንድ ለፈቀዱልን ጉባኤያችንን ተገኝተው የባረኩልልን የተቀደሰ ቡራኬያቸውን ለሰጡን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከፍ ያለ ምስጋናችንን ከአክብሮት ጋር እናቀርባለን።

በጉባኤው ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ለተከታተሉን ጉባኤያችንን ለመሩልን መመሪያና ትምህርት ለሰጡን ለብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤የባሕርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከፍ ያለ ምስጋና ከአክብሮት ጋር ስናቀርብልዎ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ይህ ዝክረ ኒቅያ የተሰኘው ሀገር አቀፍ ጉባኤ እንዲካሔድ ከመጀሪያው ጀምሮ ሐሳብ በመስጠት ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን በቅርበት ላደረገው አስተዋጽኦና ሁለንተናዊ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

ሃይማኖት የጸናበትን ርእሰ መናፍቅ የተባለ አርዮስ የተወገዘበትን በኒቅያ ጉባኤ ስያሜ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ድንቅ ጉባኤ እንዲዘጋጅ እኛ የጉባኤ ቤት መምህራን በማዕከል እንድነገናኝ እንድንመካከር እርስ በእርሳችን እንድንተዋወቅ እድሉን ያመቻቸልንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ ዋና ኃላፊ ክቡር መጋቤ ብሉይ ዕዝራ ለገሠ እና የሥራ አጋሮቻቸው ከልብ በመነጨ ምስጋናና አድናቆታችንን ስንገልጽ በታላቅ አክብሮትና በፍጹም ትህትና ነው፡፡ ለወደፊቱም እንደ አመቺነቱ ዛሬ በዚህ ዐቢይ ጉባኤ የተረከብነውን የቤት ሥራ ለመገምገም ለተጨማሪ ሥራና ኃላፊነት ለመዘጋጀት ይህ ጉባኤ በየዓመቱ ከግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በፊት እንዲዘጋጅ በአክብሮት እንጠይቃለን ።

ዝክረ ኒቅያ በሚል የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ ሊቃውንት የተሳካ ይሆን ዘንድ በገንዘብ በሐሳብ ለተባበሩን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ስም ምስጋናችንን እያቀርብን ይህ ባለ 14 ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ ከዝርዝር የውይይት ሰነዱ ጋር ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት በአክብሮት እንጠይቃለን ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን!!!
                                    ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም
                                              አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ


(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)
👍2
ለሁሉም ሼር አርጉት
2