Daily Wisdom ደይሊ ዊዝደም
299 subscribers
83 photos
6 videos
2 files
93 links
በጊዜውም አለጊዜውም ቃሉን ስበክ።
#ትምህርት
#ስብከት
#ታሪክ
#መፅሐፍት
#ይከታተሉን።
አጋር @ws_youth
Download Telegram
#የልባችሁ አይኖች ይብሩ!

ድንቆች ሆይ ሳምንታችሁ ድንቅ እየሆነ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ! ድንቅ ሆናችሁ ዋሉ! ቃሉን አንብቡ ጥቂት ደቂቃም ቢሆን ፀልዩ! ይሄን የዕለቱ መልዕክት ደግሞ አስተውሉት:- እነሆ የማለዳው ማዕድ :-

ሐዋሪያው ጳውሎስ ለኤፌሴዎን ሰዎች በመልዕክቱ እንደሚፀልይላቸው እንዲህ አሰፈረላቸው:-

ኤፌሶን 1 (አዲሱ መ.ት)
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ እንዲሁም በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
¹⁹ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኀይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣

ድንቆች ሆይ የሐዋሪያው ናፍቆት የእኔም ናፍቆት ነው ፣ የእናንተም ናፍቆት እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ! ፀሎቱ ያማረ ለብሰው የተራቆቱትን እንዲያሳቅቁ አይደለም(ያማረ መልበስ መጥፎ ባይሆንም) ፣ የተገፋበት ጊዜ አልፎ ሰውን እንዲገፋ አይደለም ፣ ታዋቂ ሁነው ብዙ ሺህ ህዝብ እያጋፋ የሚከተላቸው እንዲሆኑ አይደለም ፣ አግኝተው ያጣውን እንዲንቁ አይደለም የፀለየላቸው ይልቁንስ የፀለየው አንድ ነገር ነው እርሱም የልቦናቸው አይኖች እንዲበሩ ነው።

ድንቆች ሆይ ፦ የልቦናችን አይኖች እንዲበሩ እንፀልይ! በአለም ላይ ብዙ የከፋ ጨለማዎች አሉ የልብ ጨለማ ግን አስፈሪ ነው። እጅግም ከባድ ነው። አባይን ገድበን ብርሃን ለከተሞቻችን መስጠት እንችላለን የልብ ብርሃን ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው የሚሰጠው ፣ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማሳለፍ ነው የሚመጣው።

ልበ ጨለሞች ጥላቻ በውስጣቸው አለ። የአንተ ውድቀት ለእነርሱ ድግስ ነው። ልበ ጨለሞች የክርስቶስ ልብ የላቸውም። ለሚጠፋው ከመማለድ ይለቅ የዳነውም ቢጠፋ ደንታ የላቸውም። ጳውሎስ ኤፌሶንያዊያን የልብ ብርሃን እንዲያገኙ ይፀልያል። ልባቸው ላይ የፍቅር ፀኃይ ፣ የደሙ ኃይል እንዲያበራ ፣ የልባቸውን አይን ቻርጅ አድርጎ እንዲሞላው ይፀልያል።

ድንቆች ሆይ የውጫዊው ሰውነታችን እያየ የውስጣችን ከጨለመ ብርቱ ፀሎት ያስፈልገናል። ክርስቶስን ለማየት የታወረ ሰው ራሱን ፃድቅ ሌላውን ኩነኔ አድርጎ ይመለከታል። ክርስቶስን በማየት የተሞላ ልበ ብርሃን ግን በምህረቱ ተደግፎ ለሌላው ምህረትን ይናፍቃል።

ማየት የተሳነው ሰው ሆኖ መፈጠርም አለማየትም ኃጢያት አይደለም። የልብ ዕውርነት ግን የጨለማው መንግስት አገልጋይነት እና ኃጢአት ነው። አይን አልባዎች በመለኮት ተዓምር ይፈወሱ ይሆናል የልብ አይን ግን በቃሉ ብርሃን እና በትምህርት ብቻ ነው የሚበራው!

የልባችሁ ዓይኖች መብራቱ የሚታወቀው
   - ሙሉ በሙሉ ለቃሉ አክብሮት ሲኖራችሁ
   - እግዚአብሔር ለሰጣችሁ ምህረትና ዕድሜ እውቅና ስትሰጡ
   - ተንኮልና ሴራን ትታችሁ ፍቅርንና እውነትን መውደድ ስትጀምሩ!
   - ሰውን ማክበር  !
    - ስለእኔ ማለትን ስታስወግዱ!
   - የልድያን ልብ ስትይዙ
   - ለመማር ልብ ሲኖራችሁ
   - ወዘተ

ድንቆች ሆይ ራስን መመርመር ጥሩ ነው። የቤተ ክህነት መሪዎች የሆኑትን ፈሪሳዊያንን ጌታ አግኝቶ "ዕውር ዕውርን ቢመራው" ብሎ ከባድ ንግግር እንደተናገረ ስናስተውል እያየን እየመሰለን ታውረን እንዳይሆን መጠንቀቅ ጥሩ ነው። ፈሪሳዊያን እኛን እንዴት እውር ይለናል ብለው ተቆጥተዋል ሆኖም ግን ጌታ የሚያወራው ስለልባቸው መታወር ነበር። ጳውሎስ እኮ ልቡ ብርሃን ከማግኘቱ በፊት ለእግዚአብሔር ቀንቶ ሰው ያስገድልና ያሳስር ነበር። ልባችን ብርሃን ካላገኘው መግደል ፅድቅ ነው እንላለን ፣ ማሳደድ ትክክል ነው እንላለን። ግና ብርሃን ሲያገኝን ገዳይ ሳንሆን ለወንጌል ተገዳይ ፣ አሳዳጅ ሳንሆን ለስሙ ተሰዳጅ እንሆናለን።

ጳውሎስ የተደረገለትን ያውቃል ስለዚህም ለዳኑት ሰዎች ያለው ፀሎት የልብ አይናችሁ ይብራ ብሎ ነው።

ፀሎቴ በዛሬው ማለዳ እግዚአብሔር የልቦናችንን አይኖች ያብራው ነው። የልብ አይን ሲበራ ለውጥ ይሆናል ፣ መስቀሉንና በመስቀሉ ላይ የተሰራውን ማየት ይሆናል። ልባችን የነፍሳት ፍቅር ፣ የሰው ፍቅር ይሞላዋል!

ኦ ድንቆች ሆይ ዛሬ የልቦናዬን አብራው አንተን ልይህ ፣ አንተን ማየት እወዳለሁ እንበለው! ጥቂት ደቂቃ ወስዳችሁ ፀልዩ! እውነት እላችኋለሁ እግዚአብሔር የልባችሁን አይን ይዳስሰዋል። ጥላቻ ካለባችሁ በፍቅር ይሞላችኋል ፣ ከጨለመባችሁ ያበራላችኋል ፣ ድንግዝግዝ ካለባችሁ ጥርት ያደርግላችኋል!

የተወደዳችሁ ሆይ ፦ የልቦናችሁ ዐይኖች ይብሩላችሁ! አሜን አሜን!

መልካም ዕለተ ዕረቡ!
እወዳችኋለሁ!
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናቸሁ!
ጥቅምት 16/2015 ተከተበ!
❤❤❤
👍1
#ኩኒስ ኒደርባ!

ድንቆች ሆይ እንዴት አደራችሁ ? እኔና ቤቴ እግዚአብሔር ይመስገን ድንቅ ነን! ምህረቱን ያስታዋለ ፣በመስቀል ላይ የተሰራለትን የተገነዘበ ፣ በፈጣሪ እጅ እንደተሰራ የሚያውቅ ፣ ፈጣሪ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን አባቱ እንደሆነ የተረዳ ድንቅ ነኝ ይላል ምክንያቱም የድንቅነቱ ምንጭ አምላኩ ፣ ፈጣሪውና አባቱ ስለሆነ..ድንቅ ናችሁ! አሜን

ይሄን ታሪክ ካነበብኩት ወይም ከሰማሁት ቆይቷል ግን በጣም አስተማሪ ስለሆነ ትጠቀሙበት ዘንድ እነሆ ፦

"አንድ በድህነት ውስጥ የሚኖር ገበሬ ነበር። ይህ ገበሬ የሚያርስበት በሬ እንኳን የሌለው አንዲት በሬ ብቻ ነበረችው ስለዚህ ራሱን ከበሬው ጋር ጠምዶ ያርስ ነበር። ታዲያ አንድ የውጭ ሀገር ጎብኚ ሰው ሲያልፍ ያየውና ቀረብ ብሎ " ምን እያደረክ ነው?" ይለዋል። ገበሬውም ያለበትን ጥልቅ ችግር በመንገር ከበሬው ጋር ተጠምዶ ለማረስ መገደዱን ይነግረዋል። የውጪው ጎብኚ ያዝንለት ጀመረ ገበሬው ግን መልሶ እንዲህ አለው " አትዘን "ኩኒስ ኒደርባ" አለው ትርጉሙም "ይህም ያልፋል" ማለት ነው።

ከተወሰነ አመታት በኋላ ያ የውጭ ሀገር ጎብኚ ተመልሶ መጥቶ ስለዚያ ገበሬ ያጠያይቃል። "ያ ገበሬ እንዴት ሆኖ ይሆን ? ተጨማሪ በሬ አግኝቶ ይሆን ? ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይሆን ?" እያለ የአከባቢውን ሰው ሲጠይቅ "እሱ እኮ ቤተመንግስት ገብቷል" ይሉታል።

የውጭ ዜጋውም በደስታ ተሞላ "ይሄን ቤተመንግስት የገባውን ገበሬማ ማየት አለብኝ" አለ ቤተመንግስት ሄዶ ሲያጠያይቅ እውነትም ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ገበሬው ንጉስ መሆኑን ይሰማል። ይሄማ ለማመን ይከብዳል ብሎ ጭንቅላቱን ያዘ ገበሬ የነበረውን የአሁኑን ንጉስ አግኝቶ ሲያወራው "አትደነቅ ፤ ኩኒስ ኒደርባ "ይሀም ያልፋል" " አለው።የውጭ ዜጋው ተደነቀ፣ ተገረመ!

ከብዙ ቆይታ በኋላ እንደገና ያ የውጭ ዜጋ" ያ ገበሬ ንጉስ ሆኖ የነበረው ሰው እንዴት ሆኖ ይሆን? ወንበሩ ፀንቶለት ይሆን ? ብሎ እያሰላለሰለ ሰዎችን መጠየቅ ሲጀምር "ውይ ወዳጄ አልሰማህም እንዴ ? ሞተ'ኮ" አሉት! አዘነ! ከዚያ "እባካችሁ አስክሬኑ ያረፈበትን ስፍራ ውሰዱኝና ልሰናበተው አሳዩኝ" ይላል! የመቃብር ስፍራ ከብዙ ሐውልቶች መካከል የእርሱን ሃውልት አሳዩት ወደዚያ ቀረብ ሲል አንድ ፁህፍ ተፅፏል " ኩኒስ ኒደርባ" ይህም ያልፋል ይላል።

ድንቆች ሆይ ሁሉም ያልፋል! ለሁሉም ጊዜ አለው። አሁን ያለንበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን እኛም እናልፋለን። በምድር ላይ ፀንቶ የሚኖር ምንም ነገር የለም። ገበሬው ስለገባው ከታች እስከ ከፍታው "ይህም ያልፋል" በማለት ተመላለሰ!

እንደዚህ መኖር ምን ጥቅም ይሰጣል?

- በየትኛውም ሁኔታ በማግኘት በማጣት ጊዜ ትሁት እንድትሆን ያደርግሃል።
- በቅጡ መኖርን ፣
- ትላንትና የነበርንበትን አለመርሳትን ያሳያል
- ተስፋ መቁረጥና ጭንቀት ውስጥ እንዳንገባ ያግዘናል።
- በአግባቡ ማገልገልን እንደሚያልፍ እያሰብን ተስፋ ማድረግን መልካም መስራትን እንማራለን።

ድንቆች ሆይ ፦ ሁሉም ያልፋል። ስናጣ ምናገኝ አይመስለንም ፣ ስናገኝ ምናጣ አይመስለንም፣ ስንታመም ምንድን አይመስለንም ፣ስንድንም ምንታመም አይመስለንም ፣ ወንበር ስልጣን ስናገኝ ምንወርድ አይመስለንም ግን ሁሉም ያልፋል። ስንስቅ ምናለቅስ አይመስልም ስናለቅስ ምንስቅ አይመስልም ግን ይህም ያልፋል።

የተወደዳችሁ ሆይ ፦ ሁሉ እንደሚያልፍ ስናስብ ዕውቀታችንን ለማካፈል አይገደንም ፣ የተቸገረን ለመርዳት ለገንዘባችን አንሳሳም ፣ ህይወታችንን ለማካፈል አንቆጠብም ፣ ባገኘነው ስልጣን ሰው ለመጉዳትና ለማንቋሸሽ አንሰራም ፣ ዛሬ ያለን ነገ እንደሚጠፋ ስናስብ ተንኮልና ሴራ አናስብም ፣ ለጥላቻ ሳይሆን ለፍቅር እንኖራለን

ድንቆች ሆይ ፦ ሁሉ ቢያልፍም ሁሉን የሚያሳልፍ ጌታ በዙፋኑ ላይ መኖሩን አንረሳም። እርሱ ራርቶልናልና ለሌሎች እንራራ ፣ ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደተተወልን አስበን ሌሎችን ይቅር እንበል! ከእግዚአብሔር እጅ የጎረስን ነን እና ከገበታችን ለምስኪኖች እናጉርስ፣ ሰዎች የሚያደርጉብንን ትክክል ያልሆነ ነገር "ይህም ያልፋል" ብለን እንለፍ።

ጠቢቡ ሰለሞን "ለሁሉም ጊዜ አለው" ማለቱ ለዚያም ነው። ዛሬ የሚሆነው ነገ በሚሆነው መተካቱ አይቀርም። ከፍቅር በቀር ሁሉም ያልፋል ፣ ለሁሉም ጊዜ አለው በማለት እንኑር ! አንዳንድ ነገሮችና ጊዜዎች ማለፋቸው ላይቀር አቅማችሁን ቅንነታችሁን መልካም አስተሳሰባችሁን እና ትጋታችሁን ይዘውባችሁ እንዳይሄዱ ተጠንቀቁ!

ለዛሬው ግን "ኩኒስ ኒደርባ" ብያለሁ።

እናንተም ላላችሁበት ለማንኛውም ሁኔታ "ኩኒስ ኒደርባ" "ይሀም ያልፋል" በሉ!

መልካም ዕለተ ሐሙስ!
እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ
ቡሩካን ናችሁ!
ጥቅምት 17/2015 ዓ.ም ተከተበ
❤❤❤
👍1🔥1
#የልቦና አይን መብራት
(ክፍል ሁለት)

ድንቆች ሆይ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ! በዕለተ ዕረቡ ስለልብ ዓይን መብራት አንስቼ ነበር። ዛሬም የጳውሎስን ፀሎት እየፀለይን እንድናየው አበረታታለሁ!

በታምራት ኃይሌ መዝሙር "ጌታቸው ሲመጣ ሲተጉ የሚያገኛቸው" ከሚለው መዝሙር አንደኛው አንጓ!

"ቀጠሮ ፡ አፍራሽ ፡ የጊዜ ፡ ሌባ ፡ መምሸቱን ፡ አውቆ ፡ ቤቱ ፡ ማይገባ ከዘመን ፡ ኋላ ፡ ኋላ ፡ ተጎታች ፡ የሁሉም ፡ ጭራ ፡ ከሁሉም ፡ በታች
ከቶ ፡ የማይገባኝ ፡ የህይወት ፡ ነገር ፡ እንዳልሆንብህ ፡ እንዳትቸገር
እግሬ ፡ መራመድ ፡ እንዳያቅተው ፡ የሩቁን ፡ እንዳይ ፡ አይኔን ፡ ክፈተው"

ታምራት በዝማሬው የፀለየው ፀሎት "አይኔን ክፈተው" ነው። ለምን የልብ ዓይን ካልበራ መንፈሳዊ ጉዞን መጓዝ ከባድ ነው። መንፈሳዊ አለም ብዙ ትግል አለው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ለገላቲያ ሰዎች "ክርስቶስ በፊታችሁ ተስሎ ነበር ለክርስቶስ እንዳትገዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?" ይላቸዋል። ለምን አይኖቻቸው ክርስቶስን ማየት ስላቃተው ፣ በአዚም ተመተው ከክርስቶስ ስራ ፈጥነው ዞር ያሉበት የልብ መታወር ውስጥ ስለገቡ!

ድንቆች ሆይ፦ የልብ ብርሃን በቃሉ እውነት እየተጠበቀ ፣ ከክርስቶስ ጋር እየተጣበቅን ከእርሱ ጋር እየተሰፋን ካልሄድን መንፈሳዊ ጉዞ አሰልቺ ነው። አስደሳች አይደለም።

የልብ ዓይን መታወር አሳባችን ምድራዊ ፤ ኑሯችንም ሆነ አገልግሎታችን ሰውን ለማስደሰት ፤ ሰው ተደስቶ እግዚአብሔር ቢያዝን ምንም መስሎ አይሰማንም! ምክንያቱም መንፈሳዊ አይኖቻችን ማየት ስለማይችሉ!

ልድያ የምትባለው ሴት የሀር ነጋዴ ነች! የሞላላት ሴት ነች ነገር ግን ጳውሎስ ቃሉን ሲሰብክ ስትሰማ የልቦና ዓይኖቿ ተከፈቱላት ነገሩን ማስተዋል ሆነላት! በጳውሎስ አገልግሎት ውስጥ ትልቁን ሚና የተወጣች የአገልግሎቱ ደጋፊና አበረታች ከመሆኗም አልፋ የመጀመሪያዋ የፊሊጲሲዮስ ቤተክርስቲያን እርሷ ቤት ነው የተመሰረተው! ምክንያት የዓይን መብራት!

የተወደዳችሁ ሆይ ፦ ጳውሎስ የልብ ዓይን ሲበራ የሚሆኑ ነገሮችን ዘርዝሯል በጥቂቱ እነሆ ፦

1.የመጥራቱ ተስፋ ታላቅነት መረዳት እንችላለን!

ድንቆች ሆይ ፦ ክርስትና በተስፋ የተሞላ ህይወት ነው። ያ ተስፋ ደግሞ የተረጋገጠ ተስፋ ነው። ተስፋውን ሰጪ የካርዱ አከፋፋይ ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ነው። በተስፋ ውስጥ ፀጋን ፣ በፀጋ ውስጥ መፅናትን ፣ በመፅናት ውስጥ መውረስን የሚሰጠን የልብ ዓይን መብራት ነው። ሰው የመጥራቱ ተስፋ ካልገባው ተስፋ ይቆርጣል! ራሱን ከመንፈሳዊ ነገር ያርቃል። ምድሩን ብቻ እያሰበ ይዝላል።

ሁሉን ከሚገዛው ከሰማዩ ቤተመንግስት ታላቅ የእራት ግብዣ ጥሪ ያለብን ሰዎች ሆነን ለመኖር የዓይን መብራት ያስፈልገናል።  የእራት ግብዣው ጥሪ ግን በተሳታፊነት ብቻ ሳይሆን የበጉ ሙሽራ ሆነን ታጭተን መሆናችን ሲገባን ድንቅ የሚለን የልብ ዓይናችን ሲበራ ነው። ምፅዓቱን ተስፋ የማድረግ ህይወት ፣ ሞትን ያለመፍራት ማንነት የሚጀምረው ከአይን መብራት ነው።

2.በቅዱሳን ዘንድ ያለውን የርስት ባለጠግነት መረዳት ነው።

ድንቆች ሆይ ፦ የልባችን አይኖች በርተው የገባንበት "የባለጠግነት" ልክ ቢገባን ለአፍታም እግዚአብሔርን ከማመስገን ባልተቆጠብን ከምናልፍበት አስቸጋሪ ህይወት ባሻገር ማየት በቻልን ነበር። ይሄ ባለጠግነት በስርቆት የመጣ አይደለም በመስቀል ላይ በተገኘ ድል የመጣ ነው።

በዚህ ምድር ላይ ብዙ ብልጥግና የያዙ ሌቦች አሉ። ከእግዚአብሔር አገኝተው ሳይሆን ከደሆች ቀምተው! በሌላው ሞት ላይ ቤታቸውን የገነቡ እልፍ አላፋት ናቸው። ታዲያ የያዙትም ሀብት ጥለውት ይሄዳሉ እርሱም ጥሏቸው ይሄዳል። የእግዚአብሔር ርስት ባለጠግነትን የተካፈለ ሰው ግን ኦ ማንም ምንም ሊወስድበት አይችልም። ጳውሎስ የልባችሁ ዓይን በርቶ ይሄን ብትረዱልኝ ደስታዬ ወደር የለውም የሚል ይመስላል።

ድንቆች ሆይ አይኖቼን አብራ እንበል!

3.ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ማወቅ ነው።

የተወደዳችሁ ሆይ የእግዚአብሔር የኃይሉ ታላቅነት የታየው በሽተኛን በመፈወስ ፣ ዕውር በማብራት ሙታን በማስነሳት አይደለም የእግዚአብሔር የኃይሉ ታላቅነት የታየው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን በማስነሳት ነው። የትኛውንም ኃይለኛ የተባለን ሰው አይታችሁ ልባችሁ አያርፍም ምክንያቱም ኃይላቸው ገደብ አለው። የክርስቶስን የኃይሉን ታላቅነት ማየት ግን ልብን ያሳርፋል። ኃይል የእግዚአብሔር ነው ብሎ ማረፍ የሚችል ሰው አይኑ የበራለት ብቻ ነው። የተወደዳችሁ ሆይ አይናችንን መድሐኒያለም ይክፈትልን።

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ነው የፀለየላቸው እኔም ይሄን መልዕክት ለምታነቡ በየትኛው ጠርዝ ለምትኖሩ "የልባችን ፣ የልቦናችን ፣ የልቦቻችሁ" ዓይኖች እንዲበሪ ፀሎቴ ነው

ጌታ ሆይ የልቦናችንን ዓይኖች አብራልን! አሜን!

መልካም ዕለተ ዓርብ!
እወዳችኋለሁ
❤❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ
ቡሩካን ናችሁ!
❤❤❤❤
ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም ተከተበ!
😍😍
❤2🥰2
#የጥበብ_ቃል_ሰባት/7/

ድንቆች ሆይ እንኳን ወደ ዕለተ ቅዳሜ በሰላም መጣችሁ! ማለዳችሁ ቡሩክ ቀናችሁ ብሩህ ይሁንላችሁ! እነሆ ይሄንን የጥበብ ቃል አስተውሉት ደግሞ አሰላለስሉት "ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብ ይጨምራል" እንደሚል ቃሉ ጥበብን ትጨምሩ ዘንድ እኚህን አስተውሉ!

1.መንገድህን ዕወቀው!

ድንቆች ሆይ መንገድን ማወቅ ህይወትን ቀላል ያደርገዋል። መንገዳችንን አለማወቅ ግን ህይወታችንን ያደክመዋል። ለምሳሌ ወደ ድሬዳዋ የሚሄደውን መንገድ አዋሳ ብትደርሱ መንገዱን ሄዳችኋል ግን ውጤታችሁ ላይ አልደረሳችሁም ይልቁንስ ርቃችኋል። መንገድን አለማወቅ አቅምን ይጨርሳል ፣ ህይወትን ያጎሳቁላል ፣ ያላችሁን ኃይል ሁሉ ይበላል።መንገድን ባለማወቅ የሚወጣው ኃይል ብዙ ነው አንድ ጊዜ ግን መንገድህን ካወቅከው በትንሽ ኃይልና አቅም ወደምትፈልገው ትደርሳለህ።

መንገድ ሲጠፋ
- ጥርጣሬ ህይወታችን ላይ አለ
- መንከራተታችን ይበዛል
- በከንቱ እንደክማለን

የተወደዳችሁ ሆይ ላለመንከራተት መንገዳችሁን ዕወቁ። መንከራተት ከመጓዝ የተለየ ምዕራፍ ነው። የሚንከራተቱ ሰዎች ቃዴስ በርኔ ጋር 38 ዓመታት የተጓዙት አይነት ሰዎች ናቸው ይሄዳሉ ግን እዛው ናቸው። ይደክማሉ ግን ፈቅም አይሉም። ይሮጣሉ ግና አይደርሱም። ግባቸውና መንገዳቸው አልተገጣጠመም። ይሄን የጥበብ ቃል አስተውል "መንገዴን እንዳውቅ" እርዳኝ አይኖቼን ክፈት ብለህ ፀልይ! ከመነሻህም ከመድረሻህም እንዳትሆን የሚያደርግህ የመንከራተት ህይወት መንገድን ያለማወቅ ህይወት ከህይወት እንዲወገድ ፀሎቴ ነው።

2.መሪ አላማ ይኑርህ!

ውዶች ሆይ ፦ መንገድን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው ግን ደግሞ መሪ አላማህ ምንድን ነው ? በመንገዱ ልታሳካ የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው ? መንገዷን የያዘች ጀልባ መሪ ከሌላት ምን ምትሆን ይመስልሃል ? የሚወዘውዛት መዓበሉ ነው። ተመልሳ መንከራተቱ ውስጥ መግባቷ አይቀርም። የነፋሱ አቅጣጫ ይመራታል ወደፊት ወደኋላ ፣ ወደግራ ወደቀኝ ስትወዘወዝ ትኖራለች ! እየህደች ነው ግን አትደርስም ምክንያቱም መሪ የላትም። ወዳጄ ህይወትህ ዓላማ ከሌለው የሚወዘውዝ ብዙ ነው።

በቀን ውስጥ የሚወራው የወሬ ብዛት ፣ የሚፈበረከው ውሸት ህይወትህን ይወዘውዘዋል ፣ የሳምንቱ ሰበር ዜና ፣ የወሩ ምርጥ ፊልም ፣ የአመቱ ምርጥ ጨዋታ ወዘተ ከመዳረሻ ያስቀሩሃል። ግና ከመዳረሻ የቀረህው መድረስ ስለማትችል ሳይሆን አላማ ስለሌለህ ነው። ለቤትህ ለቤተክርስቲያንህ አላማ ይኑርህ አላፊ አግዳሚ ፣ የተረዳህ ያልተረዳህ ፣ የሚወድህ የሚጠላህ የሚያወራው "ፋብሪኬትድ" ወሬ ላይ አታተኩር ይልቁንስ መድረስ ከፈለግህ አላማ ላይ አተኩር።

ድንቆች ሆይ ክርስቶስ የመጣበትን የመንገዱን ፍፃሜ ያሳካው አላማው ላይ ትኩረት ስላደረገነው ከህይወቱ ጅማሬ ጀምሮ እስከ ህየወቱ ፍፃሜ እርሱን ለማጥፋት ያልተሞከረ የጠላት ዕቅድ የለም። ግን ያንን አልፎ የመድሐኒትነትን ስራ ለአለም ሁሉ በመስቀል ላይ ሰራልን።

ውዶች ሆይ ፦ ለመድሐኒትነት መፈለግ የሚቻለው አላማ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው። መንገዳችሁን ዕወቁ አላማችሁን ለዩ!

3.ለመንግስቱ ስራ አትስነፍ!

ድንቆች ሆይ ፦ ከዲያቢሎስ ከራሱ የምንማረው ነገር  እንዳለ ታውቃላችሁ ? ዲያቢሎስ ሰዎች የገሃነም አብረውት ወራሽ እንዲሆኑ ሳይታክት እንደሚሰራ እናውቅ ይሆን? ሰንፎ አያውቅም። የስንፍና ቫይረስን በሰዎች ህይወት ይለቃል በዚያም ለራሱ መንግስት ያዘጋጃቸዋል እንጂ ዲያቢሎስ ሰነፍ አይደለም። ሰነፍ ቢሆንማ በምን ዕድላችን ይሄን ሁሉ የቤት ስራ አይሰጠንም ነበር ከቤት እስከ ሀገር ፣ ከመስራቤት እስከ ቤተክርስቲያን "አሳይመንት" የሚሰጥን እሱ አይደል ? አዎ!

እርሱ ለመግደል ያን ያህል ከተጋ ስንፍናን ካስወገደ እኛ ለምን የመንግስቱን ስራ ለመስራት እንሰንፋለን ? እያንዳንዳችን እጅ መክሊት አለ! መነገጂያ ማትረፊያ ለሰዎች የሚተርፍ ህይወትን የሚሰጥ የወንጌል እውነት አለ። ያንን እውነት ለምን አንመነዝረውም ? ከስንፍና ርቀን ለምን አንተጋም በዚህች ቅፅበት ሚሊዮኖች ወደ ሲኦል እየፈጠኑ እንደሆነ ገብቶን ባለንበት ቦታ ለአንድ ሰው ወንጌል ለምን አንሰብክም ?

ውዶቼ ሆይ ሰይጣንን በአዳራሽ ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን በገባንበት ባለንበት በየትኛውም ስፍራ ኢየሱስን በመስበክ ልናሸንፈው ይገባል። አዎ ከዛሬ የተሻለ ምቹ የስራ ቀን የለም። በምድር ላይ ያለው ቀውስ ምን ቢበረታ ወንጌል ለመስበክ ጥሩ ሜዳ እንደሚሆንልን አንርሳ!

ውዶች ሆይ ! ድንቆች ሆይ ! እነዚህን የጥበብ ቃላት በማሰላሰል ወደ ህይወታችሁ ትተረጉሟቸው ዘንድ ፀሎቴ ነው። በየማለዳው ደጃችሁን የምቆረቁረው ለእግዚአብሔር መንግስት አትራፊ ሰራተኛ ትሆኑ ዘንድ ካለኝ ጥልቅ ፍላጎትና ከወደቀብኝም የሰማይ ጥሪም አንፃር ነው። ዛሬ ሚዲያውን ለብዙ ውድመት የሚጠቀሙበት ሰዎች አሉ እኛ ግን ለመልካም እንጠቀምበት ዘንድ በልባችሁ መበረታትንም ለመፍጠር ነው። እያንዳንዷ መልካም ዘር ትርፋ እንደምታደርገኝ አምኜ ነው። ሁሌም በመልዕክቱ ተጠቃሚ ከሆናችሁ ለወዳጅ ዘመዳችሁ ሼር በማድረግ "ንቃትን" ፍጠሩ!

ድንቆች ሆይ ቅዳሜ ላይ ደምቃችሁ ከፍ ብላችሁ ዋሉልኝ! ሀሳባችሁ ይስመርላችሁ! ፀሎታችሁ ይመለስላችሁ! ሰላምና ዕረፍት ይሁንላችሁ!

የልቤ ደጆች ለሁላችሁም ፍቅርን ያስተጋባል።

እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ጥቅምት 19/2015 ተከተበ!
❤❤❤❤
#የዕለቱ ባርኮት

በዚህ በዳዊት መዝሙር ልባርካችሁ!

መዝሙር 6 (አዲሱ መ.ት)
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ፤ ከእኔ ራቁ፤ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ድምፅ ሰምቶአልና።
⁹ እግዚአብሔር ልመናዬን አድምጦአል፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ይቀበላል።
¹⁰ ጠላቶቼ ሁሉ ያፍራሉ፤ እጅግም ይደነግጣሉ፤ በመጡበት ይመለሳሉ፤ ድንገትም ይዋረዳሉ።

🙏🙏 ዐመፃ የሚያደርጉተን ከህይወታችሁ ያርቅላችሁ🙏🙏
🙏🙏እግዚአብሔር የለቅሶችሁን ቃል ይስማላችሁ🙏🙏
🙏🙏እግዚአብሔር ፀሎታችሁን ይቀበላችሁ🙏🙏
🙏🙏 ጠላታችሁ ከፊታችሁ ያስወግድላችሁ🙏🙏
🙏🙏እግዚአብሔር መስዋዕታችሁን የአምልኮ ዕጣናችሁን ይቀበልላች🙏🙏

- ዕሁድን በእግዚአብሔር ፈቃድ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ተገዝታችሁ ዋሉ
- ዕረፍታችሁን ይባርክላችሁ
- ቤታችሁን የሳቅና የደስታ ያድርግላችሁ
- ሀዘን እና ጉስቁልናን ይገስፅላችሁ
- ተባርካችሁ ለበረከት ሁኑ!

አሜን!
አሜን!

ዕሁድ የቤተክርስቲያን ቀን የህብረት ቀን ነው። ወደ ቤተክርስቲያን መሄድን አትርሱ ለመሄድም አትስነፋም! አሸንፋችሁ ሂዱ ! እግዚአብሔር እዚያም ሊያያችሁ እና ሊያገኛችሁ ይፈልጋል!

ድንቆች ሆይ መልካም ዕለተ ሰንበትና የአምልኮ ቀን ይሁንላችሁ!

ልቤ በፍቅር ሆኖ❤❤❤
እወዳችኋለሁ
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ
ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም
ቡሩካን ናችሁ
❤❤❤
❤1🥰1👏1
#ሳምንታችሁን_እና_እናንተን_እንዲህ ባረኳችሁ!

ድንቆች ሆይ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ!

❤️ክርስቶስን ከሚጋርድ አዚም የሆነባችሁ ነገር ከአይናችሁ ላይ ያንሳላችሁ! ክርስቶስን የምታሳዩ እርሱን የምትኖሩ የህይወት ባለቤት ያድርጋችሁ!

❤በ30 ብር ከሸጠው ጋር ማዕድ የሚቀመጥ ፣ ትተውት ለሚበተኑት እንጀራ የሚቆርስ ፣ የሚያዋርዱትን ዝቅ ብሎ እግር የሚያጥብ ክርስቶስ የሆነው ኢየሱስ ከፊታችሁ የፍቅርን ገበታ ይዘርጋላችሁ ፤ ደጆችን ይክፈትላችሁ ፤ በዕቅፍ እንዳለ ልጅ ዕቅፍ ድግፍ አድርጎ ይንከባከባችሁ ፣ አቧራችሁን አራግፎ ሞገስ ያልብሳችሁ ፤ ኃጢያታችሁን በደሙ ይጠብላችሁ!

❤ወደ ስራ ቦታችሁ ስትገቡ በረከትና ድል እንጂ መከራ ና ስቃይ አብሯችሁ መግባት አይሁንለት! ለመበለድና ለስንፍና ደከማ ያድርጋችሁ ፣ ለመስራትና ለመውደድ ያጎብዛችሁ ፣ ለመጥላት ሩቅ ለመውደድና ለማፍቀር ቅርብና ትዕግስተኛ ያድርጋችሁ!

❤ሰውን በተንኮልና በሴራ ለመጣል የምትፀየፋ ፣ የሚሰራን ለመግፋት የማትተባበሩ ይልቁንስ የወደቀን ለማንሳት የበረቱ እጆች ይስጣችሁ፣ የሚሰራን በርታ የሚል የአሮንና የሆርን ደጋፊ እጆች ያድላችሁ!

❤ተዘግቷል አብቅቷል ባላችሁት ጉዳይና በር ላይ የመለኮት የተዓምራት ብርሃን ይግባላችሁ ፣ ሰላምና ክንውን ያግኛችሁ ፣ በመሰቀል ላይ የቆሰሉት እጆቹ ህመማችሁን ይፈውስላችሁ ፣ ህይወታችሁ ይጠገን ፣ መራብን በመጥገብ ማጣትን በማግኘት ይተካላችሁ!

❤ ጥያቄያችሁ መልስ ያግኝላችሁ ፣ ሰላማችሁ አይሙትባችሁ ፣ ደስታችሁና ሳቃችሁ እንደቀን አጭር ሳይሆን እንደዘመን ረጅም ይሁንላችሁ ፣ እንጀራ ከመሶባችሁ ገንዘብ ከኪሳችሁ ሰላም ከቤታችሁ ሰቅ ከአፋችሁ አይጥፋባችሁ ፣ በቁጥቁጥ ሳይሆን በመትረፍረፍ የሚያኖር ጌታ ጉብኙትን ይላክላችሁ!

❤ህይወታችሁን ከእጃችሁ ወስዶ እጁ ላይ ያኑርላችሁ ፣ እናን እጅ ቆይታ ከመበላሸት ጠብቆ እሱ እጅ ላይ ልምላሜ ይስጥላችሁ፣ እያታገላችሁ ያለውን ነገር እንደጎልያድ በአፍጢሙ ይገንድስላችሁ ፤ ብቸኝነት አንገላታኝ ላላችሁ እግዚአብሔር አለው ይበላችሁ እርሱ ሳቅና ጨዋታችሁ ይሁንላችሁ!

❤መላዕክቶች ይከበቧችሁ ፣ የተዘጋውን ደጅ ይክፈቱላችሁ ፣ የሰማይን መልዕክት ያምጡላችሁ ፣ የሰማይ ሐሳብ ሳይከለከል ያግኛችሁ!

❤ድንቆች ሆይ ደስ የምትሰኙበት ቀንና ሳምንት ይሆንላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም መረቅኳችሁ ! የመለኮት ክንድ ይደግፋችሁ ፣ ክፋና ክፋዎችን ያርቅላችሁ! መለኮት ይጠጋችሁ!

አሜን
አሜን!

ድንቆች ሆይ ፍቅሬ ከልቤ በልቤ ለእናንተ ወደእናንተ ነው።

እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ጥቅምት 21/2015 እነዚህ የባርኮት ቃል ለማስተላለፍ ተከተበ!
❤❤❤❤
#የጥበብ_ቃል_ሰምንት(8)

ድንቆች ሆይ እንዴት አድራችኋል ? ፀጋና ሰላም በያላችሁበት ይብዛ!

#ሦስቱን ምክር እናስተውል!

ድንቆች ሆይ ፦ አንድ ታሪክ አንብቢያለሁ ይሄንን ታሪክ የማካፍላችሁ ለህይወታችሁ ጠቃሚ ምክሮች ናቸው እናም በማስተዋል አንብቡት!

በአንድ ወቅት በጣም የሚፋቀሩ ባልና ሚስት ናቸው። ፍቅራቸው ድንቅ ነው። በምሳሌነትም የሚነሳ ነው። ሁለት የሚያማምሩ ወንድ ልጆች ወልደዋል። ነገር ግን ድህነትን ማሸነፍ አልቻሉም የከፋ ችግር ውስጥ ገቡ ስለዚህ ባልና ሚስት ይስማሙና ባል ለስራ ወደሩቅ ሀገር ሄዶ ስራ መስራት ጀመረ። ነገር ግን እንዳሰበው ነገር አልቀና ብሎት 16 ዓመታትን በስራ አሳለፈ። አሁንስ በቃኝ ብሎ ወደናፈቁት ቤተሰቦቹ ለመሄድ ሲነሳ ያልጠበቀው ነገር ከቀጣሪው ተነገረው እስከአሁን የሰራህው 3000 ብር ብቻ ነው ብሎ በተለያየ ምክንያት ቆራርጦ ሰጠው። የተሰጠውን ተቀብሎ በመንገዱ ላይ የሚያገኘው ስራ ካለ እየሰራ እያጠራቀመ ለመሄድ መንገድ ወደ ቤተሰቡ ጀመረ

ጉዞ ላይ ሳለ አንድ በዕድሜ የሸመገሉ አባት አገኙት "ልጄ ወዴት እየሄድክ ነው አሉት ? ከየትስ ነው አመጣጥህ ?" ብለው ቢጠይቁት ያሳለፈውን ህይወት ሁሉ ከ-እስከ ድረስ ተርኮ ነገራቸው። እርሳቸውም "ልጄ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት በጣም ቀላል ነው ?" ይሉታል

እሱም "እንዴት አባቴ?" አለ ለመስማት ጆሮውን አሰግጎ

ሽማግሌው "በል አንድ ሺህ ብር አምጣና እነግርሃለሁ"
እርሱም ከችግሩ ለመውጣት ፍላጎት አለውና አንድ ሺ ብር ሰጣቸው ሽማግሌውም " አቋራጭ ነው ብለህ በማታውቀው መንገድ አትሂድ" ይሄ ምክር አንድ ነው ይሉታል!

ሁለተኛውን ሺ አምጣና ሁለተኛውን መንገድ ልንገርህ ይሉታል። ሰውዬውም በየዋህነት ሁለተኛውን ሺ ያለማመንታት ሰጣቸው "በማያገባህ አትግባ" ይሄ ሁለተኛው ምክሬ ነው አሉት!
ደነገጠ "በቃ ይሄው ነው" አለ
ሽማግሌውም "አዎን ልጄ ሶስተኛውን አምጣና በጣም አስፈላጊውን የመጨረሻ ምክሬን ልለግስህ" አሉት ። ምንም ማድረግ አይችልምና ሰጣቸው።

ሽማግሌውም "ክፋ ለማድረግ አትቸኩሉ" ብለው በባዶ ኪሱ ከሶስቱ ምክራቸው ጋር አሰናበቱት! ይሄ ታሪክ ብዙም ለማንበብም የማይመስጥ ነው። ሰውዬውም በስጨት እያለ ከ16 ዓመት በኋላ ባዶ ኪሱን መመለሱን እያሰበ ተጓዘ። አሁን ታሪኩ ጀመረ

1 "አቋራጭ ነው ብለህ በማታቀው አትሂድ!"

በጉዞ ላይ ነጋዴዎችን አግኝቶ አብሯቸው እየተጓዘ ሳለ መሸ ለምን በአቋራጭ አንሄድም በማለት ጉዞ ጀመሩ እሱም አብሯቸው ጉዞ እንደጀመረ የሽማግሌው ምክር ትዝ አለው "አቋራጭ ነው ብለህ በማታውቀው መንገድ አትሂድ" ስለዚህ እነሱን ትቶ በሚያውቀው መንገድ ብቻውን በጨለማ ወደ ከተማ ገባ!

2.በማያገባህ ነገር አትግባ

የመሸበት እንግዳነኝ እባካችሁ አሳድሩኝ ብሎ ሰዎችን ቢጠይቅ እዚያ ከተማ አንድ ሰው የሚያሳድር ሰው አለ ነገር ግን እዛ ቤት ሰው ሲገባ እንጂ ሲወጣ አላየንም ግን ዕድሌን ልሞክር ካልክ ግባ አሉት። መሽቶበታል ምርጫ የለውም ሄዶ አንኳኳ "ቤት የእንግዳ ነው" ብለው በሞቀ ፈገግታ ተቀበሉት።

እና ከቤቱ ባለቤት ጋር ጨዋታን ጨዋታ ሲያነሳው ከየት እንደመጣ ለባለቤቱ ሳያወራው የቤቱ ባለቤት ተገርሞ "እንዴት ተረፍክ ፣ ባልከው መስመር ይመጡ የነበሩ ነጋዴዎች ሁሉ ተዘርፈው እንዲሁም ተገድለዋል። ከተማዋ ጩኸት በጩኸት ሆናለች" ሲለው። ያቺ በአንድ ሺብር የተገዛች ምክር በብር የማትገዛ ህይወቱን እንዳተረፈችለት ሲያስብ ለአምላኩ ምስጋና አቀረበ።

የሰውዬው ሚስት ለእንግዳው ምግብ ልታቀርብ ከወጥ ቤት ብቅ ስትል እንግዳው ደነገጠ የሚያየውን ማመን አልቻለም። ሴትየዋ የተወሰነ አካሏ ብቻ ነው ሰው የሚመስለው በዚያ ላይ በጣም ታስፈራለች። መውጣት አማረው ግን ወዴት መሽቷል እሷ ቶሎ ገብታለት ለማውራት ቸኮለ። ገባች

"ከዚህች ጋር እንዴት ነው የምትኖረው"ብሎ ሊጠይቅ ሲል አንድ ነገር ትዝ አለው። "በማያገባህ ነገር አትግባ" መጠየቅ እየፈለገ እሱ አብሯት ለሚኖረው እኔ ምንቤት ነኝ ? ምን አገባኝ ?ብሎ ራሱን ገዝቶ አደረ።
የቤቱ ባለቤት ከመሄድህ በፊት የማሳይህ ነገር አለ ብሎ ወደጓሮ ወሰደውና የሰው አፅም የሞላበት ቦታ አሳየው "ይሄ ምንድን ነው?" ብሎ ሊጠይቅ ብሎ በማያገባህ አትግባ ብሎ ራሱን መክሮ ዝም አለ። የቤቱ ባለቤት በዚህ ሰውዬ ተደንቆ "በእውነት አንተ የምትገርም ሰው ነህ ፤ ይህ የምታየው ሰው ሁሉ በእንግድነት መጥተው ስለሚስቴ የማያገባቸውን አስተያየት ስለሰጡ የተገደሉ ናቸው ፤ አንተ ግን ታላቅ ሰው ነህ የሀብቴን አንድ አራተኛ ሰጥቼሃለሁና ይዘህ ሂደ አለው።

በአንድ ሺ ብር ብዙ ሀብት ተካፍሎ ወደ ቤቱ ሄደ። በደስታ እዛች ደሳሳ ጎጆ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ነበር።

3.ክፋ ነገር ለማድረግ አትቸኩል

ሁሉም ነገር በአከባቢው ላይ ለውጥ ቢያመጣም እርሱ ያቺ ደሳሳ ጎጆው አልጠፋችበትም። በትልቅዬ እንጨት የተዘጋችውን ቤት ገፋ አድርጎ ሲከፍተው አይኑን ማመን የማይችለው ነገር አየ፣ ሚስቱ ከሁለት ጎረምሶች መሃል ተኝታለች በንዴት ጦፈ እኔ ስለፋ እርሷ ትማግጣለች ብሎ ድንጋይ አንስቶ ወደ ውስጥ ሊገባ ሲል "ክፋ ለማድረግ አትቸኩል" የሚለው ትዝ ቢለው ዛፍ ላይ ወጥቶ አደረ። ሚስት በጠዋት ስትነሳ ደፋ ቀና ለማለት ድንገት ባሏን ስታይ ዕልልታዋን አቀለጠችው ፣ ዘላ ተጠመጠመችበት ፤ በድንጋጤ ከእንቅልፋ እየነቃ ሳለ እጆቹን ይዛ ወደ ቤት ገብታ ሁለቱን ጎረምሶች አስተዋወቀችው " ይህ የመጀመሪያ ልጅህ ፣ ይህ ደግሞ ሁለተኛው" ስትለው ወድቆ አምላኩን አመሰገነው! የአንድ ሺ ብሩ የመጨረሻው ምክር የልጆቹን ነፍስ ከማጥፈት ሚስቱን ከማጣት ታደገለት። ሰውዬው ሶስቱ የሽማግሌው አባት ምክሮች ከቤተሰቡ ጋር አቀላቀለው።

ድንቆች ሆይ ይህቺ ታሪክ ዕውነት ትሁን አፈታሪክ ቁምነገሩ እርሱ አይደለም ይልቅ የሰጡን ምክሮች ድንቅ ናቸው።

የተወደዳችሁ ሆይ ፦ ይሄ ሰውዬ እነዚህን ምክሮች በሶስት ሺ ብር ገዝቷችኋል በነፃ ትቋደሳቸው ዘንድ የጋበዝኳችሁ እነዚህን የጥበብ ቃላት በህይወታችሁ በመተርጎም ተግባራዊ ብታደርጓቸው።

በአቋራጭ ከሚመጣ ስኬት ይልቅ በትከክለኛ መንገድ መጓዝን ውደዱ! ሁሉ ነገር እንደሚመለከታችሁ አታስቡ የማይመለከታችሁ ነገር እንዳለ በማሰብ "በማያገባችሁ አትግቡ" ፣ ክፋ ስራ በመስራት ምንም ጥቅም አይገኝም። በንዴት በብስጭት ወዘተ ሆናችሁ የምታደርጉት ክፋ ነገር የገዛ የራሳችሁን ነገር ሊያሳጣችሁ ስለሚችል ተጠንቀቁ!

ይሄ የጥበብ ቃል የህይወት ስንቅ ይሁናችሁ!

የምሳሌ መፅሐፍ የአዲሱ መደበኛ ትርጉም ሸንሻኝ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 8-19 ላለው ክፍል እንደዚህ ርዕስ ሰጥቶታል "ጥበብን ገንዘብ ለማድረግ የተሰጠ ምክር"

መልካም ዕለተ ዕረቡ!
እወዳችኋለሁ
❤❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ጥቅምት 23 / 2015 ዓ.ም ተከተበ
👍1
#ሻሎም! ሻሎም!
ሰላም! ሰላም!

ድንቆች ሆይ እንኳን ለዚህች ለተወደደች የሐሙስ ቀን በሰላም አደረሳችሁ!

ይህቺ ቀን ጥቅምት 24 ሁለት አጋጣሚያዊ ክስተቶችን አስተናግዳለች። የጦርነት ፊሽካ የተነፋባት አሳዛኝ ቀን ነበረች። ዛሬ ደግሞ የሰላም ዕወጃ የታወጀባት ቀን ሆነች። በመሃል ግን ሁለት አመታት አልፈዋል። እኛ ተንበርክከን በፀሎት አለቀስን ብዙዎች ግን አየሞቱና እየተፈናቀሉ አለቀሱ እግዚአብሔር የሁላችንን ጩኸት በመስማት "በቃ" የሚል አዋጅ ከሰማይ ያወጣልን ይመስላል የምናየው አውንታዊ ነገር አበረታቶናል ግን የተወደዳችሁ ሆይ ዛሬም ፀሎት ያስፈልጋል።

ዛሬም የበለጠ በፀሎት መጋደል ያስፈልጋል። ሰላም ጠባቂ ያሻታል እኛ ደግሞ የምንጠብቃት በፀሎት ነው። የሰላማችን ጠላት ከእግራችን በታች እንደተጣለ በማመን ዛሬም መሰዊያችን ስር ሆነን እንዋጋ ድሉ የሁላችን ነው የሰላሙ ጥቅም ለሁላችን ነው።

ሀገራችን ኢትዮጲያ በብዙ የእርስ በእርስ ጦርነት የጨቀየ ታሪክ አላት ያን ታሪክ የሚዘጋ የእግዚአብሔር ሻሎም ብቻ ነው።
በ1968-1969 በነበረ አስከፊ የዕልቂት ጊዜ ስለነበር እንዳህ ተብሎ ተገጥሞ ነበር
"ካጠገቧ ሳልርቅ ከፊቷ ሳልጠፋ
ካይኗ ሳልሰወር
ልጄ ጠፋ እያለች እናቴ መሸበር
ያ ሁሉ መጨነቅ
ካንቺ እንዳልለይሽ እንዳታጪኝ ነበር
እማዬ ምን በጀሽ እንደወጣሁ ስቀር"
የእናት ጭንቀትና ለቅሶ ጠርዙን አልፎ ይታይ ነበር። ልጃቸው 14 ዓመት ሲደርስ የነበረው ጭንቀት አይጣል ነው ይላል ታሪክ ልጇን ማሰሮ ውስጥ ግባ ብላ ትታገል የነበረች እናት ልጇን አላስገባ ብሎ ማሰሮ እየተተረተረባት ጭንቀቷ ወደ ዕብደት ተለውጦባት ነበር። ደርግም ሲወድቅ እንዲሁ የዕልቂት ታሪክ ነበር ! አሁን ግን ጌታ ከአርያም በቃ ይበለን ! የእናት እንባ ፣ የአባት ጭንቀት ፣ የልጆችን ለቅሶ ፣ የወጣቶችን ደም መገበር ይብቃን! ይሄን ሰማይ ያድርግልን!

የተወደዳችሁ ሆይ

ዛሬ የዕብራይስጡ ቃል "ሻሎም" የተሰኘውን በእኛ "ሰላም" የተባለውን ቃል ከነትርጉሙ እየተመለከትን የኢትዮጲያን ሰቆቃ ፀጥ ዝም የሚያሰኘውን ይሄን "ሻሎም" እንድናውጅ ብዬ ነው።

ሻሎም "Abundance of peace" "የተትረፈረፈ ሰላም"የሚል ትርጉም ሲይዝ ዕብራዊያኖቹ ሲጠሩት "የእግዚአብሔር ሰላም" ይሉታል።

ልብ በሉ የእግዚአብሔር ሰላም ማለት ከራሱ ከእግዚአብሔር የሚመነጭ "ሰላም" ማለት ነው። ወይም ስለኢየሱስ ነብዩ ኢሳያስ እንዲህ ብሎ ተንብዮ ነበር "ስሙ ድንቅ መካር፣ የሰላም አለቃ.." ሰላምን የሚያስተዳድረትና የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ራሱ ሲናገር "እኔ የምሰጣችሁ ሰላም አለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም" ብሎ ብራንድ የሆነ ሰማያዊ ሰላም የሚሰጠው እርሱ ብቻ መሆኑን አውጆ ነበር።

ሰላም የሚለው ቃል በፖለቲካዊ ፍቺው "የጦርነት አለመኖር የሚል ነው" ነገር ግን ሻሎም የሚለው ቃል ግን ከዚያ ያልፋል የሁኔታዎች መቀያየር ላይ የሚመሰረት አይደለም። ሁኔታዎች ጥሩ ቢሆኑሙ ባይሆኑም የማይወሰድ ጥልቅ ሰላም ነው።

"ሻሎም" የሚለው ቃል የሚከተሉትን አራት ነገሮች ይነካል።
    1.በህይወት ላይ ያለን ስምምነትን
     2.በህይወት ያለ ምሉዕነትን
      3.በህይወት ያለ ስኬትን
       4. በህይወት ያለ ደህንነትን ነው

ድንቆች ሆይ ፦ "ሻሎም" የሚለው ቃል ሙሉ ሰላም ነው። ተስማሚ የሆነ ህይወት ፣ ሙላት ያለበት ፣ የበለፀገች ፣ እና አስተማማኝ ጥበቃ ውስጥ የገባን ህይወት ያሳያል።

ቤተክርስቲያን የምትተነፍሰውን የሰላም አየር አለም ትተነፍስ ዘንድ ማድረግ የሚጠበቅባት "የሰማይ የሰላም አምባሳደር ነች" ፣ እውነተኛውን ሰላም አውጥታ ገብያው ላይ ማከፋፈል ያለባት እርሷ ነች። "የሰላም ሚኒስተር " የሚባለው የመንግስት ቢሮ ከሚሰራው በላቀ እሷ የሰማይ የሰላም ሚኒሰተር ቢሮ ሆና የበለጠ ታበረክት ነበር። ቤተክርስቲያን እኮ ያላትን ሰማያዊ አቅም ብታውቅ የአለም መልክ በብዙ በተቀየረ ነበር። ግን ቤተክርስቲያን የጠላትን የቤት ስራ ስትሰራ ትውልድ የሰላም ያለህ እያለ ይጮኻል። ይርዳን! ከማለት ውጪ ምለው የለኝም።

ይሄ አመት ሲነጋ/ሲጀምር የሚከተለው ጥቅስ ለእኔና ለቤቴ ተሰጠኝ፦

“ ይሁን እንጂ፣ ፈውስንና ጤንነትን እንደ ገና እሰጣታለሁ፤ ሕዝቤንም እፈውሳለሁ፤ በብዙ ሰላምና በርጋታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ።”
  — ኤርምያስ 33፥6 (አዲሱ መ.ት)

ድንቅ ቃል ነው። አጠናነው! በማይመች ሁኔታ አስተማማኝ ነገር በሌለበት ጊዜ ለኤርሚያስ የመጣ ቃል ነው። ጩኸ ብሎ በምላሹ ግን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ "ፈውስን ፣ ጤኔነትን ፣ በሰላምና በርጋታ መኖርን" የሚሰጥ አምላክ መሆኑን ገለጠ። 

ዛሬ ይሄ እውነተኛው ሰላም እንዲሆን በመሰዊያችሁ ስፍራ ሆናችሁ

"ሻሎም" ለኢትዮጲያ በሉ።

ተሳትፎ አደርጋለሁ ካላችሁ ደግሞ

ከታች "ሻሎም ለኢትዮጲያ" ብላችሁ ፃፉ!

ብልፅግና ኖሮ የውስጥ ሰላም(ኢየሱስ የሚሰጠው) በሰው ዘንድ ከሌለ "ሻሎም" የለም ማለት ነው። የጦርነት መቅረት መረጋጋትን ያመጣል እውነተኛው ሻሎም ግን ክርስቶስ የሚሰጠው ነው። ዛሬ ትልቅ የቤት ስራ ተቀብለናል በጦርነት መቆም ማግስት ይሄ ሻሎም በሰው ሁሉ ልብ እንዲገዛ መፀለይ እና መስበክ። መፅሐፋም "የሰላም አምላክ ዲያቢሎስን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል" እንደሚል ይሄ ፊርማም እንዲፀና ሰላሙም እንዲቀጥል ፣ የሰላማችን ጠላት የሆነውን ዲያቢሎስን ልንቀጠቅጠው ይገባል። አንድም እናት አታልቅስ! በቃ ብለን በቁጣ እንውጣ እንዝመት እንዋጋ!

"እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ ፤ ይራራልህም ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደአንተ ያንሳ ሰላምንም ይስጥህ" ብሎ እስራኤልን እንደባረከ እግዚአብሔር ሰላምን በቤታችሁ ፤ ሰላሙን ለሀገራችን አብዝቶ ይስጥልን። ይሄ ባርኮት "ሻሎም" የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም በህይወት ስለመገለጥ የሚያወራ ነው።

ኢትዮጲያዬን የእግዚአብሔር ሰላም ይጥለፋት ፣ ይቀፋት ፣ ይያዛት ፣ ይንካት ! አሜን !

"በልቤ ደስታን ጨመርህ ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ። በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም ፤ አቤቱ አንተ ብቻ በእምነት አሳድርህኛል" እንደሚል ቃሉ

"የሰላም አየርና እረፍት" በኢትዮጲያ ጎጆዎች ላይ ይግባ ፣ መኝታዎች የሰላም እንቅልፍ ያለባቸው እንጂ የድንግጤ ቦታ አይሁኑ። ነፍስ በዚህ ሻሎም ከመቅበዝበዝ ትረፍ! አራቱም ማዕዘናት በሰላም ይሞሉ!

መለዓኩ ገብርኤል ያወጀውን አዋጅ ላውጅና ላብቃ!

"መላዕኩም እንዲህ አላቸው እነሆ ለህዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ እነግራችኋለሁ አትፍሩ....ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”
  — ሉቃስ 2፥10-14

ድንቆች ሆይ ፦ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን ፣ ሰላም ደግሞ ለእኛ ይሁንልን።

ሻሎም በአዕምሮ ፣ በአካልና በሁለንተና የተረጋጋ መሆን ነው። ጌታ በዚህ ይባርካችሁ!

ሰላም ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ከእኛ በላይ የሰላምን ጥቅም የሚያውቅ ሰው የለም። ምክንያቱም በክርስቶስ ያገኘነው ሰላም ስለምናውቀው!

ሻሎም ለኢትዮጲያ ፣ ሻሎም ለምድር ሰው ሁሉ! አሜን!

እንኳን ደስ አላችሁ! አለን!

በኢየሱስም ሰላሙ ይፅና!
እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ
ቡሩካን ናችሁ!
❤❤❤
ጥቅምት 24/2015 በሀገር ደረጃ የመጣውን የሰላም ንግግር ታሳቢ በማድረግ "ሻሎምን" ለማስታወስ ተከተበ!
Daily Wisdom ደይሊ ዊዝደም pinned «#ሻሎም! ሻሎም! ሰላም! ሰላም! ድንቆች ሆይ እንኳን ለዚህች ለተወደደች የሐሙስ ቀን በሰላም አደረሳችሁ! ይህቺ ቀን ጥቅምት 24 ሁለት አጋጣሚያዊ ክስተቶችን አስተናግዳለች። የጦርነት ፊሽካ የተነፋባት አሳዛኝ ቀን ነበረች። ዛሬ ደግሞ የሰላም ዕወጃ የታወጀባት ቀን ሆነች። በመሃል ግን ሁለት አመታት አልፈዋል። እኛ ተንበርክከን በፀሎት አለቀስን ብዙዎች ግን አየሞቱና እየተፈናቀሉ አለቀሱ እግዚአብሔር…»
#ሰው_ይቃወመኛል_ብለህ_ትክክል_ከመስራት_አትቆጠብ!

ድንቆች ሆይ እንደምን አደራችሁ ? የሳምንቱ መጀመሪያ የወሩ መጨረሻ ሰኞ ላይ ነን! ጌታ ስሙ ይባረክ! ዛሬም ኑሩ ያለን እሱ ነው ለእርሱ ያልተቋረጠ ክብር ይሁንለት !

(ፌስቡክ ላይ በ2011 የለጠፍኩትን ልጥፍ ዛሬ በዚህ ገፅ ላጋራችሁ ወደድኩ)

ድንቆች ሆይ ፦ ትክክለኛ ነገር ማድረግ ዋጋ ያስከፍላል ግን ደግሞ ያሸልማል!

ግን ደግሞ ሰዎች ይቃወሙኛል ብሎ ትክክለኛ ነገር ከማድረግ እንደመቆጠብ ያለ ኪሳራ የለም።
ሉቃ 6:6-11
ኢየሱስ በሰንበት በሙክራብ ገብቶ ያስተምር ነበር። በዚያ መሓል አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበር። አስተውል ቀኑ ሰንበት ነው። ቢፈውሰው ትክክለኛ ስራ ነው ግን በፈሪሳዊያን ክስ ያመጣበታል። ስለዚህ ከሁለት አንዱን የመምረጥ አጣብቂኝ ውስጥ ነው። ትክክሉን ሰርቶ ይከሰስ ወይስ ክሱን ፈርቶ ትክክለኛውን ነገር ከማድረግ ይቆጠብ።

ይሄ ለብዙዎቻችን የቀን ተቀን ቻሌንጃችን ነው።

ድንቆች ሆይ ዛሬ በስራ ቦታችሁ ፣ በማህበራዊ መስተጋብራችሁ፣ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችሁ የሚገጥማችሁ ነገር ይህው ነው።የቱን ትመርጣላችሁ ?

ትክክለኛውን ነገር አድርገን የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል የቆረጥን በጣም ጥቂት ሰዎች ነን። ብዙዎቻችን ዋጋ መክፈልን እንፈራለን።

እኔ ግን የምልህ በዚህ የሳምንት መጀመሪያና ማለዳ ትክክለኛውን ነገር ብቻ አድርግ ነው።

ኢየሱስ የእነሱ ቁጣ ይነዳል ብሎ ሰውዬው ከነበሽታው እንዲቀጥል አልፈቀደም።

የተወደዳችሁ ሆይ ትክክለኛ ነገር ከማድረግ ምንም ነገር አያስቁማችሁ! የሚያሸልመንን ትክክለኛ ነገር እናድርግ! ዳንኤል አንበሳ ጉድጓድ የተጣለው ትክክለኛ ያልሆነ ነገር አድርጎ ቢሆን አንደነቅም ነበር ግና አይደለም! ዋጋ የከፈለው ለትክክለኛ ድርጊቱ ነው።

ኢየሱስም ያደረገውን ነገር ስናስታውለው የሚፈወሰው ሰውዬ ፈውሱን ካገኘ በኋላ ምንም የሚደርስበት ነገር የለም ፈዋሹ(ኢየሱስ) ግን ዋጋ ይከፍላል።

ድንቆች ሆይ

እኔ ምላችሁ ይሄን ነው ለሰዎች መልካም ማድረግ ዋጋ የሚያስከፍልህ ብቻ ሳይሆን ህይወትህን እንኳን የሚያሳጣህ ቢሆን ያንን ከማድረግ ወደ ኋላ አትመለስ።

ዋጋ ለሚያስከፍል እውነተኛ ነገር መኖር መታደል ነው።

መልካምና የተባረከ ሰኞ እና የሳምንት መጀመሪያ ይሁንላችሁ!

በዚህ የወሩ የመጨረሻ ቀናት በጎነቱ ይጎብኛችሁ፣ ፀሎታችሁ ይመለስላችሁ! የምትፈሩት ሳይሆን የገባላችሁ ቃል ያግኛችሁ!

እወዳችኋለሁ!
❤❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ
ብሩካን ናችሁ!!
28/2/11 የተለጠፈ በ2015 እዚህ የተለጠፈ
#ትክክለኛ_ነገር_ዋጋ_ቢያስከፍልም_አድርገው።
❤❤❤
#እግዚአብሔር ሌሊታችሁን ያነጋዋል!

ድንቆች ሆይ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ!

በማለዳው የፈነጠቀችውን ፀኃይ እያስተዋልኳት ብዙዎች ወደ ሰራቸው ሲሮጡ ፣ ረዥጅም ሰልፎችን ፣ የመኪናው ትርምስ ፣ የተማሪዎች ትመት ፣ የቀኑ መጀመሪያ የንጋቱ ፊሽካ መሆኑን ያወሳል። ሰው ሁሉ በገባው "በቀኝ አውለኝ" ብሎ ፀልዮ ይወጣል። በዚያ መሃል የጠወለገ ፊት ፣ ተስፋ የቆረጠ ፊት ፣ ፈገግ ያለ ውስጡን የደበቀ ፊት ፣ ደማቅ ፈገግታ ያለበት ውስጡም ውጩም ያማረበትን ታስተውላለህ !

ምሽቱ እየመጣ ባለበት በ11 ኛው ሰዓት አከባቢ ደግሞ ሌላ ትርምስ ፤ ወደቤት የሚደረግ ሩጫ አንዳንዱ ቤቱን ናፍቆ ፣ ሚስቱን ልጆቹን ወላጆቹን አሊያም ራሱ ቤቱ ራሱ ናፍቆት ይሮጣል። ደስታ የተሞላበት ፊት ማግኘት ይቸግራል ፣ ድካም ያጠላበት መቼ ቤቴ ደርሼ ባረፍኩ የሚል አሊያም ደግሞ የታመመ ልብ ኖሮት እግዚአብሔርን "ወይ ውረድ ወይ ፍረድ" በሚል ስሜት ገንትሮት እያብሰለሰለ ይጓዛል! ከዚያ ሁሉም ነገር ወደ እንቅልፍ አለምና ወደ ፀጥታ ይገባል።

ድንቆች ሆይ እግዚአብሔር ግን ሌሊት የለበትም ለልጆቹ ድንቅና ተዓምራት ለማድረግ በእኛ ሌሊት ለእኛ ንጋት ይሰራል።

ሌሊት ላይ የነገሮች መዘጋት ብቻ ሳይሆን የሌቦችም የዝርፊያ ሰዓት ነው።ወንጀለኞች ሊያስለቅሱ ሊገድሉ የሚወጡበት ሰዓት ነው። ሆኖም እግዚአብሔር ግን በሌሊት ብዙ ተዓምራትን ሰርቷል። ባህር የተከፈለው በሌሊት ነው ፣ መርደኪዮስ ያመለጠው በሌሊት ነው ፣ ጴጥሮስ የተፈታው በሌሊት ነው ፣ ብዙ ድንቅ የሆነባቸው ሌሊቶች አሉ።

ድንቆች ሆይ ሌሊታችሁን ፣ ሌሊታችንን የሚያነጋ ባህሩን የሚከፍል እግዚአብሔር በስራ ላይ ነው። እስራኤል ባህር አፋፍ ላይ ናቸው ከኋላ ደግሞ የሚከተላቸው የወቅቱ ሜካናይዝድ ጦር የግብፅ ሠራዊት አለ። ኮቴው ከመሰማት አልፎ ቀሮቧችዋል! በእነሱ ቦታ ከሆናችሁ ያስደነግጣል !

እኔ ግን እላችኋለሁ ሌሊቱ ንጋት ይሆናል ፣ ባህሩም ድርምስ ብሎ ይከፈላል ! አሜን!

ወደኋላ ዞራችሁ የጠላትን ጉምጉምታና ሜካናይዝድ ጦሩን አትመልከቱ ይልቁንስ ከፊታችሁ የተዘጋጀውን ተዓምራት ተመልከቱ! እንመልከት ! ለሀገሬም ቢሆን ከፊት ለፊቷ ያለውን ተዓምራት ማየት ያዋጣናል።

ድንቆች ሆይ ትላንትንና ኋላን በማየት አትደንግጡ ይልቁንስ ዛሬን የሰጠን አስደሳች ተዓምራት ከፊታችን እንዳዘጋጀ እንመን!

ድንቆች ሆይ እግዚአብሔር በፈረቃ ሰርቶ አያውቅም ፣ ፀኃይ አትረዳው ሌሊት አይከለክለው ፣ ደመና አይጋርደው መናፍስታት አይዙትም እርሱ ከሁሉ በላይ የሆነ የጊዜ ክበብ የማይዘው እውነተኛ ሰራተኛ አምላክ ነው። ሌሊታችሁን ያነጋዋል ፣ ቀናችሁን ያደምቀዋል! ፍርሃታችሁን ይገድለዋል።

ድንቆች ሆይ ከፊቴ ገደል ነው አልሻገርም ብትሉ ድልድይ ይሆንላችሁል! ጨለማ ስትሉ ብርሃን ይሰጣችኋል። አይታለፍም የተባለውን ሰንጥቃችሁ የምታልፋበት ተዓምራት ያገኛችኋል።

እኔ አምናለሁ ነገርን ሁሉ በጊዜ ውብ አድርጎ ሰራው የሚለው ቃል አካል ለብሶ ሌሊታችን ይነጋል ፣ እንባችን ይታበሳል።

መልካም የደስታና የእምነት ማክሰኞ ይሁንላችሁ!

እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ጥቅምት 29/2015 ተከተበ!
❤❤❤
#ምክንያት ፈልገን እናመሰግናለን! ምክንያት ሳንፈልግም እናመሰግናለን!

ድንቆች ሆይ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ! ይህ የጥቅምት ወር የመጨረሻዋ ቀን ነች! በዚህች ቀን ተመስገን እንበል ለማለት ነው።

የዚህችን አለም ሰዎች እዩቸው ዳንኪራ ለመደለቅ የሚፈልጉት ትንሽ ምክንያት ነው ፣ ከዚያ ጭፈራው ዳንሱን ወዘተ ላባቸው ጠብ እስኪል ያስነኩታል ምክንያት ስትሏቸው ልጄ Kg ተመረቀ ብለው...መለስተኛ ሰርግ አዘጋጅተው ይሉታል...ልደት ነው ፣ ምርቃት ነው ፣ የተጠመቀበት ቀን ነው ፣ ሰርግ ነው ፣ ወዘተ እያሉ የዘፈንና የጭፈራ አራራቸውን ይወጡበታል።

ጳውሎስ ደግሞ ለእኛ "በሁሉ አመስግኑ" ብሎ መልዕክት ፅፎልን አልፏል! ለነገሩ ጳውሎስ በሁሉ አመስግኑ ያለው ሳይኖር አይደለም ኖሮት ነው፣ ለህይወቱ በሚያሰጋበት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ነው።

ድንቆች ሆይ ለምስጋና ምክንያት መፈለግ መጥፎ ባይሆንም ግን መኖራችን መዳናችን ከምክንያት በላይ ነው። ለማመስገን ከበቂ በላይ ነው። እንደው ግን ለማመስገን የሚበቃ ምክንያት ከቤታችሁ እስከ አደባባይ ፈልጋችሁ ታጣላችሁ ? አንድ ሁለት እያላችሁ የምትቆጥሩት የምስጋና ምክንያትስ የለምን ? እረ እልፍ ነው ! እጅግ በጣም እልፍ ነው።

ድንቆች ሆይ አንድ ምክር ልለግሳችሁ ምክንያት ፈልጋችሁ አታጉረምርሙ ፣ አታልቅሱ ፣ አትተክዙ ይልቁንስ አመስግኑ! የምናለቅስበትን ምክንያት ከፈለግን አናጣም በዚያ ግን ሰይጣንን ነው ደስ የምናሰኘው። እንባችሁን በምልጃና በፀሎት ሰዓት ለሚሰማችሁ ለአምላካችሁ አቅርቡ ከዚያ በተረፈ ግን ሰበበ ፈላጊ አልቃሽ ፣ አጉረምራሚ ሳትሆኑ ሰበብ ፈላጊ አመስጋኝ ሁኑ!

የተወደዳችሁ ወይ ፦ በሁሉ አመስግኑ ማለት የምስጋና ሀብታሞች የለቅሶና የማጉረምረም ደሆች ሁኑ ማለቱን እንደሆነ አንዘንጋ! ሲመችም ሳይመችም ፣ ሲሳካም ሳይሳካም ፣ ቢደላም ባይደላም ፣ ቢገኝም ቢታጣም ፣ ብንፈወስ ባንፈወስ ፣ ብንታመም ጤነኛ ብንሆን በሁሉ አንደበታችን በተመስገን ልባችን በውዳሴና በሐሴት መሞላት አለበት ማለት ነው።

ድንቆች ሆይ ለማመስገን የሚሆን ምክንያት ከመተንፈሳችሁ ጀምራችሁ ብትፈልጉ እልፍ ነው። ማመስገን የህይወት መርሃችን ይሁን!

ማጉረምረም ሰይጣንን ማምለክ ነው። እግዚአብሔርን መበደል ነው። ወዳጆቼ እንደዚህ ለማለት የታመሙት ወገኖቼ ቢያሳዝኑኝም ግን እውነታ ነው እነሱ ኩላሊታቸውን ለማሳጠብ በሌሊት ተመስገን ብለው ሲነሱ እኛ ፊታችንን ለመታጠብ ስንነሳ ተመስገን አለማለታችን የሚደንቅ አሳዛኝ ነገር ነው። ሰው በጠዋት ብዙ ኪኒኒን እየዋጠ ተመስገን ሲል እኛ እጃችንን ታጥበን ቁርስ ለመብላት እየቀረብን ተመስገን አለማለት የሚደንቅ ነው።

ድንቆቼ ሆይ ፦ እንደበደላችንና እንደስንፍናችን ቢሆን ቀን ሊጨመርልን የማይገባንን ይህው ከ2015 እንኳን ሁለት ወራት ጨምሮልናል ፣ ወራቶችን እንደቀላል እያሳለፈን አመታትን ለጨመረልን እንዴት እንሰለቻለን ተመስገን ማለት ይቀድማል ይበልጣልም። የጠላታችንን ክፋ የሌሊት ምክር አፍርሶ የቀኑ ጅማሬ ላይ ስለደረሰን ተመስገን ማለት ይቀድማል ይገባልም!

ሁልጊዜ ይመከርባችኋል ! ታውቃላችሁ ይሄን ? በሰይጣን ብቻ ሳይሆን በክፋ ሰዎች ፣ በጠሏችሁ ሰዎች ፣ በስራ ባልተግባቧችሁ ሰዎች ነገረ ግን ምክራቸውን ከንቱ እያደረገ መውጣት መግባታችሁን በሙሉ ጥበቃው ስር ሲሆን በጥንቃቄዬ ተጠበቅኩ ብለህ ከምትታበይ በምህረት ተከለልኩ ብለህ ትሁት ሆነህ በርከክ ብለህ አወድሰው ፣ ተመስገን በለው!

ድንቆች ሆይ፦ ዙሪያችሁን ለምስጋና የሚሆን ምክንያትና ርዕስ እንደንፁህ አየር ከቦሃል ያንን እየማግህ አመስግነው። ምድር መሰረቷ እስኪናወጥ ሰማያት በከባድ ደመና እስኪሞሉ ድረስ በምስጋና ተሞላ!

ድንቆች ሆይ እግዚአብሔርን በማመስገን የሚሰራ ስህተትም የሚፈጠር ፀፀትም የለም። መርጣችሁ አመስጋኝ ሳትሆኑ በሁሉ አመስጋኝ ሁኑ! ምስጋና ለእግዚአብሔር ልንሰጠው የምንችለው ብቸኛ ነገር ነው።

እና ምክንያት ብዙ ነው! ምክንያት አጣሁ ለምስጋና አይሰራም! በጌታ በኢየሱስ ስም መረቅኳችሁ ለማልቀሻ ለማጉረምረሚያ የሚሆን ምክንያት እጡ! ለምስጋና የሚሆን ምክንያት ግን አትጡ!

መልካም ዕለተ ዕረቡ!

እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ጥቅምት 30/2015 ለምስጋና ምክንያት ብዙ ነው ለማለት ተከተበ!
❤❤❤
👍2
Daily Wisdom ደይሊ ዊዝደም pinned «#ምክንያት ፈልገን እናመሰግናለን! ምክንያት ሳንፈልግም እናመሰግናለን! ድንቆች ሆይ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ! ይህ የጥቅምት ወር የመጨረሻዋ ቀን ነች! በዚህች ቀን ተመስገን እንበል ለማለት ነው። የዚህችን አለም ሰዎች እዩቸው ዳንኪራ ለመደለቅ የሚፈልጉት ትንሽ ምክንያት ነው ፣ ከዚያ ጭፈራው ዳንሱን ወዘተ ላባቸው ጠብ እስኪል ያስነኩታል ምክንያት ስትሏቸው ልጄ Kg ተመረቀ ብለው...መለስተኛ ሰርግ አዘጋጅተው…»
#የጥበብ_ቃል_ዘጠኝ(9)

ድንቆች ሆይ! ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ! እንኳን ለዚህች የተወደደች ቀን አደረሳችሁ !

እነዚህን ተያያዥነት ያላቸውን ሶስት የጥበብ ቃላት አስተውሉ!

እመቤታችን ድንግል ማርያም በቃና ዘገሊላ በነበረው የሰርግ ስነ-ስርዓት ያስተላለፈችው ድንቅ መልዕክት "የሚላችሁን አድርጉ ነው።"

1.የህይወት ስኬትና ውድቀት ክርስቶስን ከመታዘዝና ካለመታዘዝ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው አንርሳ!

ህይወት ቁልፍ አላት ዋነኛው እምነት ነው። እምነት ሌላኛው ስሙ ግን እግዚአብሔር ላዘጋጀው የመድሐኒትነት መንገድ መታዘዝን የሚያሳይ ነው። ያለመታዘዝ እምነት የለም። አመነ ቃሉን ማለት ታዘዘ ቃሉን ማለት ነው። ቃሉን ማክበራችን የሚታወቀው በመታዘዛችን ነው። ህይወት የምትቀነጭረው ፣ አሊያም አለመርካትና የውስጥ ሰላም የሚጠፋው ባለመታዘዝ ህይወት ሲኬድ ነው። አዳምና  ሄዋን የህይወት መናጋት የገጠማቸው ባለመታዘዛቸው ነው። ኑሮውን ማስቀጠል ያልቻሉት እግዚአብሔርን መታዘዝ ቀላል ነገር ስለመሰላቸው ነው።

ህይወት የቃና ዘገሊላው አይነት ገጠመኝ ይገጥማታል ፣ የነገር መሟጠጥ ፣ የችግር መደራረብ ፣ እጥረትና ውጥረት ፣ በህይወታችን ሊበዛ ይችላል ፣ ፍቅር ከልባችን ማህደር ፣ ትግስት ከባህሪያችን መንደር ፣ ሰላም ከጎጆችን ፣ ደስታ ከውስጣችን ፣ ጉድለትና ማጣት ከቤታችን ማጀት ሊገባ ይችላል! ከዚህም የተነሳ ምን ላድርግ የሚል የመፍትሄ ያለህ ጩኸት ላይ ልንሆን እንችላለን! ግን ቃና ዘገሊላ የሚሰጠን መልስ "የሚላችሁን አድርጉ ነው"  መታዘዝ ነው።

2. በልምድህ ሳይሆን በሚሰጥህ ምሪት ተጓዝ!

ሰርግ ቤቱ የቆየ ዝግጅት አድርጓል! የወይን አዘገጃጀት ክህሎታቸው የላቀ ሰዎች አዘጋጅተውታል! ሆኖም ሊብቃቃ አልቻለም! ነገሩ አልቆ ሙሽራውም ቤተሰቡም ውርደትን እየጠበቁ ነው። እዚህ በአጭሩ እንደምፅፍልህ እንዳይመስልህ በአይሁድ ባህል ትልቅ ውርደትን የሚያመጣ ጉዳይ ነው። የኢየሱስ ትዕዛዝ ታዲያ ..."ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው" የሚል ነው። ልምድ ላለው ሰው ፣ ወይን በማዘጋጀት ጥርሱን ለነቀለ ሰው ይሄ የአመቱ ምርጥ ቀልድ ነው።

ድንቆች ሆይ እግዚአብሔር ሲሰራ ልምዳችሁን አይፈልገውም ፣ ልምዳችሁ የሚጠቅምበትና የጠቀመበት ቦታ አለ ግና አሁን ላይ ያ አስፈላጊ ሰዓት ላይ አይደለም። ያልተመደ ልምምድና የተዓምራት መንገድ ላይ ለመግባት ትክክለኛው መንገድ ምሪቱን መከተል ነው። የሰማይን ምሪት አለመናቅ ነው። አገልጋዮቹ ይሄንንማ አናደርግም ቢሉ አንዳች የሚሆን ተዓምር የለም።

የተወደዳችሁ ሆይ "በራስ ማስታዋል እንዳንደገፍ" መፅሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል።

ችግር መከራ እንደገጠመን አውቀን ደግሞም ጌታን አንሰማም ብለን የሚሆን ጉዳይ አይደለም። ችግራችን ዕድሜ የሚያስቆጥረው እኛ በለመድነው ካልፈታነው ብለን በተለይ ልምዳችንና ዕውቀታችንን መከታና መታመኛ ስናደርግ ነው። ልምድም ዕውቀትም የማይሰሩበት ቦታ እንዳለ ካልተረዳህ የህይወት መሪ የሆነውን ጌታን መከተል ተራራ መውጣት ነው የሚሆንብህ!

3.እያወቅከው ፣ሳትከራከር  መራመድ ጀምር !

ውሃ መሆኑን ያውቃሉ ግን ቀድተው መስጠት ሲጀምሩ ያረጀ የወይንጠጅን የሚያስንቅ በልምድ የተሰራውን መናኛ የሚያሰኝ ተዓምራት መሆን ጀመረ! ለምፃሞቹን ኢየሱስ ሄዳችሁ ራሳችሁን ለካህን አሳዮ ሲላቸው ለምፃቸው አልነፃም ግና ለማሳየት ሲሄዱ ነፁ ይላል! ኢየሱስ ሲያዝህ ክርክርም መቆምም አይፈቀድም ዝም ብለህ በዕምነትና በመታዘዝ መራመድ ነው። አምስቱን የገብስ እንጀራና ሁለቱን አሳ አከፋፍሏቸው ስጧቸው ሲል ምንም የተፈጠረ ነገር አልነበርም ሆኖም ግን መስጠት ሲጀምሩ ፣ መራመድ ሲጀምሩ ከ20- 25 ሺ የሚሆን ህዝብ በልቶ ጠግቦ 12 መሶብ ትራፊ ተነሳ!

ይሄን ህዳር ወር እስቲ እነዚህን ሶስት የጥበብ ቃላት በማስታዋል እንኑራቸው!

- ቃሉን መታዘዝ
- ከልምዳችን ይልቅ ምሪቱን መከተል
- ሳንከራከር እርምጃ መውሰድ!


ድንቆች ሆይ፦

ህይወታችንን ውብ የሚያደርገው ለቃሉ መታዘዛችን ነው። ለመታዘዝ እኛ የምንፈልገው ሁኔታ መሟላትን አንጠብቅ! ምቹ ሁኔታ ወይም የምንፈልገው ሁኔታ መምጣት ቃሉን ለመታዘዝ የሚፈይደው ነገር የለም። ምክንያቱም ኤደን ገነትም ሆነው ያልታዘዙ ምሳሌዎች አሉና። የቃና ዘገሊላ ሰዎች ግን የታዘዙት ችግሩ እየጨመረ ፣ ትርምሱ እየበረከተ ፣ ውርደት ሊመጣ በደጅ ባለበት ጊዜ ነው።

ሞትን ያመጣው አለመታዘዝ ነው ! ደስታና ህይወትን የሚያመጣው መታዘዝ ነው።

የሚለንን የምናደርግበት ጥዑም የህዳር ወር ይሁንልን!

መልካም ዕለተ ሐሙስ ይሁንላችሁ!

እወዳችኋለሁ
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ
ህዳር 1 /2015 ዓ.ም ተከተበ
❤❤❤❤
#የጠራንን_እግዚአብሔርን_እንከተል!

ድንቆች ሆይ ፦ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ!

ሐዋሪያው ጳውሎስ "ያዳነን በቅዱሰሰ አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና.." ብሎ በ1ኛ ጢሞቲዎስ 1:9 ላይ ይናገራል።

የተወደዳችሁ ሆይ ፦ መለኮታዊ የሆነ ጥሪ እና ተልዕኮ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጥ ስጦታ ነው። ያንን ጥሪ ተግባራዊ ለመፈፀም የሰው ፈቃድ እና ፈገግታ መጠበቅ የለብንም። እግዚአብሔር እኛን ሲጠራን ማንንም አማክሮ አይደለም። በነገራችን ላይ የመዳናችን ጥሪ በተመለከተ እያወራው ነው። የመዳናችን ጥሪ ውስጥ መለኮታዊ ተልዕኮዊ ጥሪ አለ። የተላከ እና ያልተላከ የሚባል የለም። የዳነው ማህበረሰብ ሰማይን ወክሎ በምድር የሚንቀሳቀስ የሰማይ እንደራሴና መልዕክተኛ ነው።

ድንቆች ሆይ ፦ ስሙኝማ ሲጠራችሁ የልባችሁን ፈቃድ እሺ ይሁን ብላችሁ ተቀብላችኋል አይደል! ደግሞስ እንዴት እንደሳበን እንዴትስ የልባችንን አለታማ ድንጋይስ በፍቅሩ መዶሻ እንደሰበረውስ የሚገባን ነገር ይኖር ይሆን ? በአደባባይ ተሰቅሎ ባሳየን ፍቅሩ በልባችን በማይገባን መልኩ በተሰራው የፍቅሩ ስራስ እንደተገነባን ይገባን ይሆን ?

ድንቆች ሆይ ፦ ሰውን ለማስደሰት ጎንበስ ቀና አትበሉ። ሰው ሰው ነው። እግዚአብሔርን መታዘዝና ለእግዚአብሔር መገዛት ብቻ ነው ከኪሳራ የሚያወጣን ፣ ዘላለማዊ ትርፍ የሚሰጠን አለቀ! ሰው ማለት እንደጤዛ ነው ዛሬ አይተህው ነገ የለም። እግዚአብሔር ግን ዘላለማዊ ነው።

ጳውሎስ “ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።”
— ገላትያ 1፥10

የተወደዳችሁ ሆይ ፦ በልባችሁ ፅላት የደመቀውን የመስቀሉን ፍቅር ፣ የታተመውን የመስቀሉን ተልዕኮ ለመፈፀም ትጉ! እግዚአብሔር የልቦናችን አይኖች በርቶ በመንግስቱ ውስጥ ያለንን መለኮታዊ ድርሻ እንድንወጣ ይፈልጋል! የእኔ ድርሻ የቱ ጋር ነው ? ጌታ ሆይ እንድወጣ የምትፈልገው ነገርስ ምንድን ነው ? ያየህውን አሳየኝ ! ያሰብከውን አሳስበኝ ብሎ መፀለይ ተገቢ ተግባር ነው።

ኢሳያስ የመለኮቱ አጀንዳ ሲገባው "እኔን ላከኝ አለ? " ዙሪያውን ሳይሆን መለኮትን አየ! የሚያታግለውን ነገር ሳይሆን ሰማይ የሚሰጠው አጀንዳ ላይ አተኮረ!

አብርሃም እሺ ብሎ ባይታዘዝ ለዓለም ሁሉ የመዳን ተስፋ የሆነው የክርስቶስ ዘር በእርሱ ዘር ባልመጣ ነበር! ምንም በሌለበት ከሰማይ ለተገለጠለት ድምፅ "እሺና አሜን" ሲል የሰማይ በሮች ተከፈቱለት ፣ የሰማይ አጀንዳ በእርሱ ብቻ አይደለም በትውልዱ ተነደለ !

ዳዊት የአባቱን ትዕዛዝ ተከትሎ ስንቅ ሲያደርስ ወንድሞቹ የነቀፋትን ነቀፈ "የልብህን ክፋትና ትዕቢትህን" እናውቃለን ብለው የማያውቁትን ሲዘባርቁ ፣ በቅናትና በተንኮል የስድብ ናዳ ሲያወርዱበትና ሲንቁት ተስፋ ቆርጦ ወይም ተናዶ ሰማይ ከሰጠው ተልዕኮ ዞር ቢል ለእስራኤል መራና ንጉስ ጎልያድን የሚገነድስ የቅባት ሰው መሆን ይችል ነበርን ? ወዳጄ! በየፌርማታው እየቆምክ ለሰዎች ማብራሪያ አትስጥ ! ተልዕኮህ ላይ ትኩረት አድርግ! ልቡን አውቀዋለው የሚሉትን ሁሉ ከሰማህ ልብህ ውልቅ ነው የሚለው ይልቁንስ ልብህን ብቻውን ማወቅ የሚችል ከእርሱ ምንም የተደበቀ ነገር የሌለውን እግዚአብሔርን ተከተለው!

መቅደላዊት ማርያምስ ብትል የለፋችበትን የአንድ አመት ደሞዝ የሚያወጣውን ክቡር ሽቶ ኢየሱሴ እግር ላይ ስታፈሰው ፣ ለእግሩ ውሃ ያላቀረበ በተቀመጠበት ስፍራ እርሷ በከበረ ነገር ስታጥበው ፣ የሴት ልጅ ክብር ነው በሚባለው በፀጉሯ ስታብሰው...ልቧ ውስጥ ለተተከለው ፍቅር ነው። ደቀመዛሙርቱና የቤቱ ባለቤት ግን ተፀይፈው ያጉረመርሙ ነበር።

የተወደድክ ሆይ ምን ሆነሃል ? ሰው ምን ይለኛል ብለህ በልብህ ያለውን የተልዕኮ ተግባር ከመፈፀም ወደኋላ አትበል። ሰው እንደሆነ ስትሰራም ይተችሃል ባትሰራም ይተችሃል። ሽቶ ስትሰብርም ለንስሃ እግሩ ስር ስትወድቅም ይተቿታል ስትዘሙትም ይተቿታል ! አጃኢብ ነው!

ኢየሱስ ግን "ይህ ወንጌል በተነገረበት ስፍራ ሁሉ" የእርሷ ስም እንደሚነሳ ተናገረላት! ስማኝማ ሰማይ የሚናገርልህን ለመስማት ሰማይ የሚወደውን አድርግ!

ድንቆች ሆይ አስተውሉኝ ከሰዎች ከልምዳቸውም እንዲሁም መልካም ምክሮቻቸውን መስማትና መቀበል ጥሩ ነው ደግሞም አስፈላጊ ነው። ፍፁም የሆነ ምክርና ትዕዛዝ ግን ከሰማይ አምላክ ከመለኮት የሚመጣ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል!

ሐዋሪያትን ከዚህ በኋላ ብለው በህግ ማነቆ ሊያስሯቸው ፈልገው ከዚህ በኋላ እንዲህና እንዲህ እንዳታደርጉ ብለው "የክልከላ" ህግ አወጡባቸው "ጴጥሮስና ሐዋሪያትም መልሰው አሉ፦ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል" ሐዋ 5:29

ድንቆች ሆይ ሰው እስትንፋስን መንጠቅ አይችልም ፣ ሰው ተልዕኮን መንጠቅ አይችልም ይልቁንስ እግዚአብሔርን በመታዘዝ የሰው ባሪያ ከመሆን ነፃ ልንወጣ ይገባል። ሰዎች የመጨረሻው አቅም በህግ ማስፈራራት ነው አለቀ! የእግዚአብሔር ዘላለማዊን አጀንዳ እንደተሸከም ከገባህ ግን እንደነዳንኤል አንበሳ ጉድጓድ እየተጣልክ ! እንደነሲድራቅ እሳት ውስጥ እየተወረወርክ መድመቅህ አይቀርም። ከስራ ያባሩኛል ፣ ደሞዜን ይነጥቁኛል ብለህ የሰማይ እንድራሴነትህን እንዳትጥል!

የመዳን ጥሪ ለሌሎች የመድረስ ጥሪም ጭምር ነው።

“ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥”
— ገላትያ 1፥15-16

መልካም ዕለተ ቅዳሜ!

እወዳችኋለሁ!
❤❤❤
መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ህዳር 3/2015 ተከተበ!
❤❤❤
❤3🔥1
#እግዚአብሔርን_በማክበር_መኖር!

ድንቆች ሆይ ! ሁሉን የሚችል አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ይባረክ! ሁላችሁም በያላችሁበት በጌታዬ በመድሐኒቴ ጥበቃ ስርና በረከት ውስጥ እንደሆናችሁ አምናለሁ። እኔና ቤቴም በእግዚአብሔር ሞገስና ፀጋ ውስጥ ባልተቋረጠው የምህረቱ ዝናብ እየረሰረስን አለን!

ድንቆች ሆይ ዛሬ ማለዳ እግዚአብሔርን ስለማክበር እንዳወራችሁ መንፈስ ቅዱስ ልቤ ላይ አመላክቶኛል።

የማናውቀውን ማክበር ይቸግረናል። ማወቅ ከማክበር ይቀድማል። የዛሬው ፀሎቴ ይሄን ልናከብረው የተገባውን ጌታ ታውቁት ዘንድ ነው።አውቃችሁትም ታከብሩት ዘንድ ነው።

ጳውሎስ “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።”
  — ፊልጵስዩስ 3፥10-11

ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የመረጃ ባለቤት ያደርግሃል ፤ እግዚአብሔርን ማወቅ ግን የማክበርን እና የህብረትን ምንነት ያስረዳሃል።

ማወቅ ጥሩ ነው ማክበር ደግሞ ማወቃችን የሚፈጥረው ድምር ውጤት ስለሆነ እጅግ በጣም ጥሩ ነው።

የእግዚአብሔር ፍላጎት

“ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤”
  — ራእይ 21፥3

ወዳጆቼ የእግዚአብሔር ፍላጎት በመሐከላችን መሆን ነው። በአንተ ውስጥ ማደር ነው። ለሙሴ ምን እንዳለው እናስተውል ይሆን ?
“በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ።”
  — ዘጸአት 25፥8

የእግዚአብሔር ፍላጎቱ በእኛ ውስጥ ማደር ነው። ኤደን ገነት ላይ የነበረው ኑሮ በመገኘቱ ውስጥ ነው። ሊፈልጋቸው የመጣው እርሱ እግዚአብሔር ነበር።  ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የላከው ማደሪያ መቅደሱን ሊሰራ ነው። ከመስቀሉ ስራ በኋላ በአማኞች ልብ ውስጥ የሚያድር መኖሪያውን እኛ ጋር ያደረገ መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል።

ወዳጆቼ ሆይ ፦ ፈፅሞ አትዘንጉ የእግዚአብሔር ፍላጎት ከእኛ ጋር ህብረት ማድረግና በእኛ ውስጥ መኖር ነው።

እናክብረው!

የእግዚአብሔር ፍላጎት እኛ ውስጥ ማደር ከሆነ ከእኛ የሚጠበቀው ደግሞ እርሱን ማክበር ነው። ልናከብረው የተገባ ፣ ስግደታችን ፣ አምልኮታችን እና ምስጋናችን የሚገባው ብቸኛው አምላክ እርሱ ብቻ ነው።

እርሱ ታማኝ ነው! እርሱ የማንም ጥገኛ አይደለም ፣ ራስ ገዝ ነው ፣ እውነተኛ ነው ፣ ክብርን የተሞላ ነው ፣ መሃሪ ነው እርሱ መቼም ወድቆ አያውቅም አይወድቅምም!

እርሱን እናክብረው ፣በዜማዎቻችን እናመስግነው! በሰጠን ጊዜ እና በአገልግሎታችን እናክብረው።

ባለን ነገር እናክብረው ፣ በሁሉ ነገር ቅድሚያ ለእርሱ እንስጥ!

ድንቆች ሆይ ፦ ወደቤታችን ና ኑርበት እንበለው ፣ ወደ ትዳራችሁ ጋብዙት ፣ ወደ ስራችሁ ፣ ወደ አገልግሎታችሁ ና ኑርበት በሉት እንበለው። በሁለንተናችን አስበንበት ልናከብረው ይገባል።

በጌታ በኢየሱስም እግዚአብሔር የማይቆጣጠረውና የማይከብርበት ምንም አይነት የህይወት ክፍል እንዳይኖራችሁ እፀልያለሁ!

#የሚያከብሩትን ያከብራል

እናስታውስ ፣ እናስታውል ፦ "የሚያከብሩኝን አከብራለሁ" ያለው ራሱ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔርን ስናከብረው እርሱ የማንጠብቃቸውን ማክበሮችን በህይወታችን ያደርጋል።

ጠቢቡ ሰለሞን ከመላው አለም ከአፍሪካ ጭምር ብዙ ክብርን የተቀበለው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ? በመፅሐፍ ቅዱስ መዝገብ ውስጥ የሰለሞንን ያህል እግዚአብሔርን የማክበር መስዋዕትነትን የሰዋና ያቀረበ የለም። ስለዚህም በምላሹ ክብርን ተጎናፀፈ።

ኤልሳ እግዚአብሔርን ሲያከብር በሱናማይቷ ሴት ሆኖ አከበረው!

እግዚአብሔርን ለምታከብሩ ተዘጋጁ እግዚአብሔር እናንተን ማክበርን ይጀምራል። ይሄ ማነቃቂያ ንግግር አይደለም መፅሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው።

#እርሱ_ከፍ_ያደርጋችኋል!

እግዚአብሔር ሁልጊዜ በዙፋኑ ላይ ነው! ከፍ በል ብለን ከፍ አናደርገውም ግና የማክበሪያ ቃሎችን ፣ ዝማሬዎችን ተጠቅመን ለእርሱ ያለንን አክብሮት እንገልፃለን ሆኖም በዚያ ሰዓት እኛን ከፍ እያደረገን ይመጣል። ወደራሱ ክብር ያስጠጋናል ፣ ወደደረቱ ይጎትተናል የከፍታችንና የመክበራችን ምስጢር ይጀምራል።

ይሄ ቀን ፣ ይሄ ወር ፣ ይሄ ሳምንት የክብር ፣ የሰላም ፣ የተዓምራት ቀንና ወር በኢየሱስ ስም ይሁንላችሁ! አሜን!

❤እወዳችኋለሁ❤
ፓስተር ቢኒ
ህዳር 7/2015 ዓ.ም.
❤❤❤❤
👍2😁1
ግሩምና ድንቅ ሆነን ተፈጥረናል!

ድንቆች ሆይ ፦ ዕለተ -ዕሁድ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የምትሰሙበት ፣ ከሐሳቡም ጋር የምትስማሙበት ቀን ይሁንላችሁ!

ሰው የተፈጠረው ፣ ወይም ፈጣሪ ሰውን የፈጠረው ብቸኝነት ተስምቶት አጀብ ግርግር ፈልጎ አይደለም። ድካም አስቸግሮት አጋዥ ጧሪ ቀላቢም ሽቶ አይደለም።እርሱ የማይኖርበት ጊዜ ስለሚኖር እንዲተካው አስቦም አይደለም። ምክንያቱም እርሱ ብቻውን ሆኖ ብዙ ነው ፣ ያለማንም መኖር የሚችል ፈጣሪ ነው ፣ ድካም የማያውቀው ሰራተኛ ነው ፣ አጋዥ የማይፈልግ የሁሉ ደጋፊና አጋዥ ነው። ዘላለም በእርሱ ላይ የሚኖር መጀመሪያም መጨረሻም የሌለው ፣ ከ - እስከ የሚበል የመነሻ ፊደልም ቁጥርም መደምደሚያም የሌለው መለኮት ነው።

እግዚአብሔር በባሕሪው ድካም ፣ በመንግስቱ ሽረት ፣ በህልውናውም ህልፈት ፣ ለማንነቱም መጀመሪያም መጨረሻም የሌለው ነው።

አንተን ፣ አንቺን ፣ እኔን (እኛን) እንዲፈጥር ያስገደደው ውስጣዊ ብቸኛ ምክንያት ፍቅር ነው። በፍቅር ምክንያት ፈጠረን በፍቅሩ ምክንያት አንድያ ልጁን ላከልን ፣ በፍቅር ምክንያት አዳነን!

"አላማው በእኔ ላይ ፍቅር ነው" የሚል መዝሙር አለ። እውነት ነው እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ብቸኛው አላማ ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው።

ግሩምና ድንቅ ሆነን ተፈጥረናል የምልበት ምክንያት ምን እንደሆነ ታውቃለህ የእግዚአብሔር የፍቅር ስሪቶች ስለሆንን ነው። መቼም ይገባሃል እኛ ባልታመንበት እና እግዚአብሔርን በምንበድልበት ወቅት እንኳን እርሱ ለራሱ የታመነ ስለሆነና የፍቅር አምላክ በመሆኑ ብዙ ዘመን የማይገባንን መልካምነት እንዳደረገልን ልንዘነጋው አይገባም።

ግሩምና ድንቅ ነህ! ለምን ? አልከኝ ልበል ! እግዚአብሔር አምላክ ከሙሉ ነፃነት ጋር ፈጥሮሃልና! ነፃ ፈቃድህን ማንም ሊገፍህ አይችልም። ይሄን ነፃነት የሰጠህን ጌታ አክብረው። ነፃነት የስልጣኔ ወለድ ስጦታ የሚመስላቸው ፣ የሆነ የጫካ ትግል አድርገው ነፃነትን በስጦታ መልክ የሰጡህ የሚመስላቸው ነገስታትም እንዳሉ የምታስብ ከሆነ ተሳስተሃል የነፃነትት አባት "ኔልሰን ማንዴላ" አይደሉም ራሱ እግዚአብሔር ነው።

እኛ እኮ የተወደድን እንደሆንን ቢገባን እርሱን ለማምለክ ደስ ብሎን እንጂ ተገደን አንመጣም። እግዚአብሔርን የምናመልከው መርጠነው ነው እንጂ አማራጭ አጥተን አይደለም። ግና ከማንም ሊወዳደር የማይችል ፣ ብንከተለው የሚያኮራ ፣ ብንሰማው የሚያሳርፍ ፣ ብንወደው የሚወደድ ፣ ብናመልከው የሚገባው አምላክ እንደሆነ ገብቶን ነው።

ድንቅ ነኝ የምለው የሆነ የስነልቦና መምህር አውጀው ስላለኝ አይደለም። ድንቅ አድርጎ የፈጠረኝ ድንቅ አምላክ እንዳለኝ ስለምረዳ ነው። ድንቅና ግሩም መሆናችንን መቀበል ለእግዚአብሔር ፍቅር ተገቢውን ቦታ መስጠት መሆኑን ልንመለከት ይገባል።

ዛሬ ማለዳ ወደ ቤተክርስቲያን ስትሄድ በእውነት በደስታ ሂድ ፣ ማንም ስለሚለውና ከጀርባህ ስለሚወራው ነገር አትጨነቅ አንተ ግሩምና ድንቅ የሆነውን ጌታ ለማምለክ ግሩምና ድንቅ ሆነ የተፈጠርክ መሆንህን እያወጅክ ሂድ !

ጥያቄ ቤቴ ሆኜስ ባመልከው የምትል አትጠፋም!

ድንቁ ወዳጄ እኛ በህብረት ልንኖር በህብረት ልናመልክ የተፈጠርን ሰዎች ነን። ሐዋሪያትም መምህራቸው ኢየሱስም ወደቤተመቅደስ መሄድ ያዘወትር ነበር። በህብረት የሚገኝ በረከት በግል ከምታገኘው በረከት የሚልቅበት ጊዜ እንዳለ መረዳት ጥሩ ነው።

እና አልፈህ ሂድና አምልክ ፣ ከቅዱሳን ጋር ህብረት አድርግ ከአምልኮ በኋላም ይሁን ፊት አንድ የማታውቀውን ሰው በጌታ ፍቅር ሰላምታ ስጠው! ፍቅርህን ግለፅለት !

የምታቃቸውን ደግሞ ጠበቅ አድርገህ ሰላም በላቸው! ለአንተ መጥፎ ስሜት እንዳላቸው የምታውቃቸውም ሰዎች ካሉ የክርስቶስ ግሩምና ድንቅ ፍጥረት መሆናቸውን አስበህ ሰላምታ ለግሳቸው።

ከምንም በላይ በህብረት ፈጣሪህን ለማምለክ ያገኘህውን የዚህች ቀን ዕድል አታባክን በደንብ ተጠቀምበት! ነገ የሚባል የማንወዳት አንድ ቀን መምጣቷ አትቀርም።ስለዚህ "Enjoy and worship God on this day!"

መልካም ዕለተ ሰንበት!

በመንፈስ አለም በዮንቨርሳሏ ቤተክርስቲያን ላይ በአምልኮ አለም እንድንገናኝ ቀጠሮ ሰጠው!

እወዳችኋለሁ
❤❤❤

መጋቢ ቢኒያም ኃይሉ!
ቡሩካን ናችሁ!
ህዳር 11/2015 ግሩምና ድንቅ መሆናችንን በማስታወስ በህብረት እናመልከው ዘንድ ለማነሳሳት ተከተበ
❤❤❤
❤2
የአዲስ አመት ስጦታ
👇👇👇👇
Subscribe
👇👇👇👇
https://youtube.com/@salemtvethiopia?si=fYByc3V5xGARlwKO

ሳሌሞች Congratulation❤❤❤