የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
287 subscribers
885 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
"ወእንዘ ትጸውሙ - ስትጾሙ" ማቴ፮፥፲፮
➥[ከሳምንት የቀጠለ]➥
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ወእንዘ ንጸውም - ስንጾም ጾማችንን በመቀደስ ነው

በዘወረደ "ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም" ብሎ ሃይማኖትን ሰብኮን ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት - ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ[ምስባክ መዝ ፪፥፲፩] እያለ የሚመክረን ዓቢይ ጾም በሁለተኛው ሳምንት ስለ መቀደስ ይነግረናል- #ቅድስት!

❖ በዘወረደ ያልጀመረ ቅድስት፣ ቅድስት ያልተከተለው ዘወረደ እንደሌለ ሃይማኖት እንበለ ምግባር፣ ምግባር እንበለ ሃይማኖት ህልው አይሆንም ምውት ነው! አይጠቅምም [ያዕ ፪፥፲፬]

❖ የቅ/ዮሐንስ መጥምቅ ደቀ መዛሙርት የነበሩት ቅ/ዮሐንስ[ወንጌላዊ] እና ቅ/እንድርያስ ጌታችንን "አይቴ ተኃድር? - በየት ታድራለህ?" ብለው ጠየቁት። ጌታም "ንዑ ትርአዩ- ኑና እዩ" ማለት እመኑብኝ በሚያምንብኝ ሰውነት አድራለሁ አላቸው። "ወሖሩ ወርእዩ - ሄዱና አዩ" ማለት አመኑ። ከዚህ በኋላ "ወወአሉ ኀቤሁ እስከ ዓሥሩ ሰዓት" ይላል እስከ አሥረኛው መዓርገ ቅድስና ደረሱ ሲል [ዮሐ፩፥፴፰-፴፱ ትርጓሜ ተመልከት] በሃይማኖት የተከተለ በቅድስና ይውላል!

❖ ቸሩ እግዚአብሔር በባሕርይው ቅዱስ ሆኖ ሳለ እኛን ቅዱሳን ሁኑ ይለናል [ዘሌ፲፱፥፪]
❖ በምናችን ነው የምንቀደሰው የምንል ከሆነ ቅ/ጴጥሮስ እንዲህ ይለናል
" እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ #በኑሮአችሁ_ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ" ፩ኛ ጴጥ፩፥፲፭-፲፮

❖ የኛ የክርስቲያኖች ኑሮአችን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ [የተቀደሰ] ሊሆን ይገባዋል ይኸውም ሁል ጊዜ በሁሉም ቦታ በሀሳባችን፣ በንግግራችን፣ በተግባራችንም ነው

ለዚህ ደግሞ ዘወትር መታገል ሥጋንም መጎሰም ያስፈልጋል።

ከቅድስና ተለይተን እንዳንጣል ሥጋችንን እየጎሰምን ከምናስገዛበት መሣሪያዎች ዋነኛዋ ጾም ናት! [፩ኛ ቆሮ፱፥፳፯]

❖ ለጸሎት እናት ለአርምሞ እህት ለመልካም ሁሉ ምግባራት ምንጭ የሆነች ይህቺ ጾም ወደ ቅድስና እንድትመራን ልንቀድሳት ይገባናል
" በጽዮን መለከትን ንፉ፥ #ጾምንም_ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ" እንዲል ኢዮኤል ፪፥፲፭

❖ ጌታችን እንደነገረን ጾማችን ከግብዞች ጾም መለየት[መቀደስ] አለበት [ማቴ፮፥፲፮]

ብዙዎች መጾምን ይጾማሉ የጾማቸው ዓላማ ግን ይለያያል
● ለግብዝነት የሚጾሙ አሉ [ማቴ፮፥፲፮]
● ሰውን ለመግደል ብለው የሚጾሙ አሉ [ሐዋ ፳፫፥፲፬]
● በጤና ማጣት ምክንያት ተገደው የሚጾሙ አሉ
● ለሥጋዊ ውበታቸው ብለው የሚጾሙ እንዳሉም ግልጥ ነው

የእኛ ጾም ለግብዝነት ያይደለ ለትህትና፣ ለመግደል ያይደለ ለማዳን፣ ተገደን ያይደለ ወደን፣ ለሥጋዊ ያይደለ ለነፍሳዊ ውበታችን ሊሆን ይገባል

ደግሞም ሆዳችንን ከምግብ ማጾም ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ያሬድ እንዳስተማረን በዓይናችን ክፉ ከማየት በጆሮአችን ክፉ ከመስማት፣ በአንደበታችንም ክፉ ከመናገር መጾም ይገባል

❖ ይህ ካልሆነ "እኔ የመረጥሁት ጾም ይኽ ነውን?" የሚል ተግሳጽ ይከተለናል

❖ ጾማችንን በሚገባ ቀድሰን የጾምነው እንደሆነ "ዘጾመ ወጸለየ ወሰአለ እሙነ ይነስዕ እሴቶ - የጾመ የጸለየ የለመነ በእውነት ዋጋውን ይቀበላል" እንዲል በጎ ዋጋችንን እንቀበላለን

❖ ያን ጊዜ ብርሃናችን እንደ ንጋት ያበራል...ያን ጊዜ እንጣራለን እግዚአብሔርም ይሰማናል... ጨለማችን እንደ ቀትር ይሆናል፤... እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይመራለናል፤... እንደሚጠጣ ገነት ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ እንሆናለን፤... ከድሮ ዘመን ጀምሮ የፈረሱት ሥራዎች ይሠራሉ፤.... እኛም ሰባራውን ጠጋኝ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ እንባላለን [ኢሳ፶፰፥፭-፲፪]

✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

በሃይማኖት መሠረትነት [ዘወረደ] ጸንተን በኑሮአችን ተቀድሰን [ቅድስት] ከተነኘን የጌታችንን ትምህርት እያደመጥን፣ ቤተ መቅደሱን ሲያጸዳ እየተመለከትን በአማናዊቷ ምኩራብ እንኖራለን - ለአማናዊቷ ሙክራብ የበቃን ያድርገን! ይቆየን!