የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
304 subscribers
886 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
"ወእንዘ ትጸውሙ - ስትጾሙ" ማቴ፮፥፲፮
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ጾም ቀዳማዊ ትዕዛዝ ናት [ዘፍ፪፥፲፮] ይህቺ ቀዳማዊት ትዕዛዝ ህይወታቸው ሙሉ የጾም ህይወት ከሆነ ከመላእክት ጋር የምታስተባብረን አንድ የምታደርገን ናት! በእርግጥ የክርስቲያኖች የመጨረሻ ሕይወትም  እንደመላእክት ያለ ነው። [ማቴ፳፪፥፴] 

ጾም፦ ሙሴ ህግን ተቀብሎባታል [ዘፀ፴፬፥፳፰ ] ፤ የነነዌ ሕዝቦች ታወጀባቸውን መቅሰፍት አስመልሰውባታል [ዮና፫፥፯-፲]፤ አይሁድ በሐማ ተንኮል ከተሴረባቸው የሞት ሴራ ተርፈውባታል [አስቴር ፬፥፲፮ ] ፤ ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ ሕይወታቸው አድርገዋት የጥበብ ባለቤቶች ሆነውባታል [ዳን ፩፥፰ ፤ ፲፥፫]፤... ያለ ጾም የኖረ ነቢይ የለም!

እስራኤል የጾም ወራታቸውን የደስታ በዓል አድርገው አክብረዋል [ዘካ፰፥፲፱ ]

✥ ጌታችን ሐዋርያት እንደሚጾሙ ነግሮናል[ማቴ፱፥፲፭]፤ ሲጾሙም አይተናል [ሐዋ፲፫፥፪ ]፤ የጾም ወራትም በሐዋርያት ዘንድ የታወቀ ነው [ሐዋ፳፯፥፱]

ጾም በነቢያትም በሐዋርያትም የተኖረች ሕይወት ናት!

✥ጌታችን በተራራው ስብከቱ ስለጾም ሲናገር "ወእንዘ ትጸውሙ - ስትጾሙ" ብሎ እንዴት መጾም እንዳለብን ነገረን። [ማቴ ፮፥፲፮] ይኽም ጾም ያስፈልጋል አያስፈልግም ከሚል ጥያቄ ማለፍ እንዳለብን ያመለክተናል።

✥ እኛ ክርስቲያኖች ጾም ያስፈልጋል አያስፈልግም ከሚለው አልፈን ስንጾም እንዴት እንጹም የሚለው ላይ እናተኩራለን፦
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ወእንዘ ንጸውም - ስንጾም ከምግብ እንከለከላለን

✥ በጾማችን ወራት ለተወሰኑ ሰዓታት ከሁሉም ምግብ እንከለከላለን፤ የጾሙ ወራት እስኪያልፍ ደግሞ ከጥሉላት መብሎች እንከለከላለን።

✥ የጾማችን ወራት እስኪያልፍ በምግብ ጊዜ ጾሙን የምናልፍበት ማለፊያ እንጀራን እንመገባለን። የበረቱት ግን ይህንንም በመተው ጾምን ጀምረው ይፈጽሟታል [ዳን፲፥፫ ]

✥✥✥   ✥✥✥   ✥✥✥   ✥✥✥

ወእንዘ ንጸውም - ስንጾም በሃይማኖት ሆነን እንጾማለን

"አሚንሰ መሠረት ይእቲ ወካልዓኒ ህንጻ ወንድቅ እሙንቱ" እንዲል ዮሐንስ አፈወርቅ የሁሉም ነገር መሠረት ሃይማኖት ነው።

✥ ሃይማኖት ያለው ምግባር ከሌለው ከንቱ እንደሆነ ምግባር ያለውም ሃይማኖት ከሌለው ከንቱ ነው። [ያዕ፪፥፲፬]

✥ የዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት የሚያስረዳንም ይህንኑ ነው - #ዘወረደ!

✥ እነየንታ ቅዱስ ያሬድን አብነት አድርገው "ዘወረደ እም ላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ - ከላይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት" በማለት ነገረ ክርስቶስን ይሰብኩናል።

✥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴ ላይ የምታነብልን ወንጌል " ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።"ይላል [ዮሐ ፫፥፲፫]

✥ እኛ ታላቁን ጾማችንን የምንጀምረው ይኽንን እየመሠከርን ነው 'ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም'!

"ምነው እነ ሄኖክ እነ ኤልያስ ወደ ሰማይ ወጥተው የለምን?" የሚለን ካለ እነሱ መች ከሰማይ ወረዱ? እንለዋለን። ደግሞስ ወደ ብሔረ ሕያዋን ተወሰዱ እንጂ መች ወደ ዘባነ ኪሩብ ወጡ? ቢወጡ ቢወጡ ወደ ጸጋ አምላክነት እንጂ[ዘፀ፯፥፩ መዝ፹፩(፹፪)፥፮ ] መች ወደ ባሕርይ አምላክነት ወጡ?

እግዚአብሔር ወልድ ከአምላክነቱ ሳይለይ ከሰማይ ወረደ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ሆነ[ዮሐ፩፥፲፬] ሰው በሆነ ጊዜም ከአምላክነቱ ያልተለየ እርሱ እግዚአብሔር ነው

ከእመቤታችን የተወለደው እርሱ በእርሷ ማህጸን በድንግልና ሰው ሆኖ የተጸነሰው ነው[ማቴ፩፥፳፫ ]።

በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ያየነው በባሕርይ አባቱ የባሕርይ ልጅነቱ የተመሰከረለት እርሱ[ማቴ፫፥፲፯] ከእመቤታችን በድንግልና የተወለደው ነው።

በመስቀል ላይ አይሁድ የሰቀሉት እርሱ[ማር፲፭፥፳፬] በዮርዳኖስ የተጠመቀው ነው።

ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ የለየው እርሱ[ሉቃ፳፫፥፵፮] አይሁድ በመስቀል ላይ የሰቀሉት ነው።

ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ ገንዘው የቀበሩት እርሱ[ማቴ፳፯፥፷] በመስቀል ላይ በፈቃዱ የሞተው ነው።

ከህቱም መቃብር የተነሳው እርሱ[ሉቃ፳፬፥፭] በአዲስ መቃብር የተቀበረው ነው።

ወደ ሰማይ ሲወጣ ያየነው እርሱ[ሐዋ፩፥፱] በራሱ ሥልጣን ከሙታን የተነሳው ቀድሞ ከሰማይ የወረደው ነው።

ስለዚህም ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም!

ከሰማይ የወረደው አማላጅ አይደለምና ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ አይደለም

ከሰማይ የወረደው ነቢይ ስላይደለ ወደ ሰማይ የወጣው እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይ አይደለም።

ከሰማይ የወረደው እግዚአብሔር ነውና ወደሰማይ የወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት እግዚአብሔር ነው።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ሐዋርያት አድርጋ የሾመችው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ስንለው አለን በዚሁ ጸንተን እንኖራለን [ማቴ፲፮፥፲፮  ሐዋ፰፥፴፯ ]

ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽማ በተሰጠች በዚህች ሃይማኖት ሆነን ቅድስናንን እንጠባበቃለን።

ለቅድስቱ ያብቃን.....።
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥