የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
287 subscribers
885 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
ነነዌ_፳፻፲፭_ዓም
©ሄኖክ_ኃይሌ

ቤተ ክርስቲያናችን እንደወትሮው ሁሉ አሁንም መከራ አልተለያትም:: በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እየተቀበልን ጸንተን መቆም የሚጠበቅብን ሲሆን በሚከተለው መንገድ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችንን እንድናግዛት በአክብሮት እጠይቃለሁ:: (መቼም ጸልዩ ማለት የዲያቆን ሥራ ነው)

የክርስቲያኖች ትልቁ መሣሪያችን እጃችንን ለጸሎት ወደ ሰማይ መዘርጋት ነው:: ዕንባችንም እንደ ራሔል ዕንባ ባሕርን ይከፍላል:: ራሳችንን በንስሓ ካዋረድንና ካለቀስን የማንቀለብሰው ነገር የለም::

የፊታችን ሰኞ የሦስት ቀናቱ ጾም ጾመ ነነዌ ይገባል:: 

ጾሙ ከመግባቱ አስቀድሞ ኦርቶዶክሳውያን ሁላችን ንስሓ እንግባ::  በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ይህንን ያያችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሁላችሁ ንስሓ አባቶቻችሁን ምስክር አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ:: "ጌታ ሆይ ይህ የሆነው በእኔ በደል ነውና ኃጢአቴን ይቅር በለኝ" ብለን አብረን አምላካችንን እንማጸነው::

ከዚህ ንስሓ ጋር የታወጀውን የየነነዌ ጾም ጠዋት በኪዳንና ከሰዓት በቅዳሴ ማታ ደግሞ በጸሎተ ምሕላ በየአጥቢያችን እየተገኘን አምላካችንን እንማጸነው::
የቻልን ሦስቱን ቀናት እስከ ማታ እየጾምንና እየሰገድን የፈጣሪያችንን ምሕረት እንለምን::

በሦስት ቀን ጾም የነነዌን መዓት የመለሰ : በሦስት ቀን ጾም የግብፅን ተራራ ያፈለሰ የነስምዖን አምላክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመጣ ያለውን እሳት ሁሉ በቸርነቱ ይመልስልን ዘንድ በልባችን ጉልበት እንስገድ::

ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የተለዩትን እንዲመልስልን!
በዚህ ምክንያት የሚጠፉ ነፍሳትን እንዲጠብቅልን!
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መናወጽ የሚሻውን ሁሉ እንዲያስታግሥልን ወደ ፈጣሪያችን በጋራ እንጩኽ::

በየጊዜው ለችግራችን ስእለት እንደምንሣለው አንድ ጧፍ እንኩዋን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ስእለት አድርገን እንጸልይ:: አርከ መሀይምናን (የምእመናን ወዳጅ) ለቤተ ክርስቲያንም ቅን መሪን የሚሠጥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ በፊቱ ስለሚማልሉ የዋሃን ብሎ ሰላማችንን ይመልስልን::

"እግዚአብሔር እንዳይቀየማቸው ከመዓትም ተመልሶ ፍጹም ዕረፍትን ይሠጣቸው ዘንድ ስለ በደሉ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን እንማልዳለን" በእንተ ቅድሳት

#ነነዌ_ኢትዮጵያ
#ንስሓ_ግቡ
#ትጉና_ጸልዩ
#አንዲት_ቤተ_ክርስቲያን
#አንድ_ሲኖዶስ
#አንድ_ፓትርያርክ
#eotc_one_holy_synod
#one_church
#one_patriarch
#his_holiness_abune_mathias
#oriental_orthodox
#ጾመ_ነነዌ

#ነነዌ «ታላቋ ከተማ»

ነነዌ በጤግሮስ ወንዝ ዳርች በአሁኑ ኢራቅ አከባቢ የምትገኝ፤ በሃያሉ ናምሩድ የተመሰረተች የአሥራውያን ዋና ከተማ ነበረች (ዘፍ 10፡11)። በጊዜው ዓለም ላይ ከነበሩ ታላላቅ ከተሞች አንዷ የነበረች ነነዌ፤ ውብ ቅጥሮች ያሏት፣ ሃያላን ነገስታትን የማረከች፣ ብዙ መንግስታትን የተፈታተነች ነበረች። በሰሎሞን ልጅ በሮበዓም ዘመን ሰሜን (እስራኤል) እና ደቡብ (ይሁዳ) ተብላ ከሁለት በመከፈሏ ብርታት ያጣችውን የእስራኤልን መንግሥት ስትፈታተን እና ስትወጋም ትኖር ነበር።

ነነዌ 120ሺ ህዝብ የሚኖርባት የቅጥሯ ስፋት ወድ 12ኪ.ሜ ገደማ የሚሆን ከተማ ነበረች። ምንም እንኳን ነነዌ በዓለም ዘንድ ቁንጮ ብትሆንም፣ በእግአብሔር ዘንድ ግን ሃጢያቷ የበዛ፣ ከአምላክ መንገድ የወጣች፣ ተመዝናም ቀላ የተገኘች ነበርች። ሳይመክር ሳያስመክር የማይጣላዉ እግዚአብሔርም ቃሉን ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል ላከ፤ «ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ» አለ (ዮናስ 1፡1)።

#ከእግዜብሔር_የሸሸው_ነብይ

ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፤ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ከሞት ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃንም፣ ይህ ልጅ እንደ ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል (1ኛ ነገ 17፥19)፡፡ የዚህ ነብይ ስሙም «ዮናስ» ትርጓሜውም "ርግብ" ማለት ነው። የእግዚአብሔር ቃልም «ተነስተህ ወደ ነነዌ ሂድ፣ እንዲህም ብለህ ስበክ "ነነዌ እስከ ሶስት ቀን ትጠፋለች"» ሲል ወደሱ መጣ (ዮና 1፡1)። ዮናስ ግን «አንተ መሐሪ ነህ፣ በእሳቱ ፋንታ ምህረትን ብታወርድ፤ አንት መሐሪ፣ እኔ ደሞ ነቢየ ሐሰት እባላለው» ብሎ ከጌታ ፊት ሽሽት ጀመር።

ነብዩ ዳዊት «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።» (መዝ 139፡7)። ያለውን እግዚአብሔር፤ ከደቂቀ ነብያት አንዱ የሆነው ዮናስ ግን እሱን ሽሽት ወድ ተርሴስ ኮበለለ። {ነብየ እግዚአብሔር ዮናስ ሆይ? ከእግዜር ወዴት ትሸሻለህ? ተርሴስ ከእግዜር ትሰውረሃለችን? በእግረ ዳዊት የተተካህ ነብይ ሆይ፣ ዳዊት «ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ» ያለውን አላስተዋልክምን?}። ምንም እንኳን ነብዩ ከእግዜር ሽሽት ወደ ቴርሴስ በመርከብ ቢጓዝም፣ አምላክ ግን በዓሳ አንባሪ ሆድ ወደ ነነዌ ወሰደው። በዚህም በዓሳ አንባሪ ሆድ ዉስጥ ሶስት ቀን እና ሶስት ለሊት ቆይቶ ነነዌ ደረሰ። ይህም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሶስት ቀን ሶስት ለሊት የመቃብር ስለመቆየቱ እና ከሙታን ተለይቶ ስለ መነሳቱ ምሳሌ ሆነን (ሉቃ 11፡30)።

#በሦስት_ቀን_ውስጥ_ነነዌ_ትገለበጣለች

ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ገባ፤ ጮኾም፦ «በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች» አለ (ዮናስ 3፡4)። እንዴት የሚጨንቅ፣ የሚከብድ ቃል ነው። የዮናስ ስብከት ምህረት የለውም፣ 'ንሰሃ ግቡ' ብሎ ለንሰሃ አይጋብዝም። እንድ ነብዩ ኤርሚያስ «ስለ ሕዝብ ስለ መንግሥትም እነቅል አፈርስም አጠፋም ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ» ብሎ ተስፋ የሚሰጥ ቃልም አይደለም።

የነነዌ ህዝብ ከአህዛብ ወገን ናቸው፣ ዮናስን አያቁትም የሱን አምላክ አያመልኩትም፤ ብቻ ለሃገሩ እንግዳ የሆን አንድ ዕብራዊ ወድ ከተማዋ ገብቶ «ነነዌ ትገለበጣለች» አለ። የነነዌ ሰዎች እንዴት በኛ ላይ ታሟርታለህ ብለው ዮናስን አልሰቀሉትም (አይሁድ ሊያድናቸው የመጣውን መሲህን ሰቅለውታልና)፣ በመጋዝም አልሰነጠቁትም (አይሁድ የእግዚአብሀሄርን የምህረት_ቃል ሊያቀብላቸው የመጣውን ልዑለ ቃል ኢሳያስን በመጋዝ ሰንጥቀውታልና)። የነነዌ ሰዎች እንደ ኖህ ዘመን ሰዎች በሀጥያት ውስጥ ሆነው የቀራቸውን ጊዜ አልቆጠሩም፣ ይልቁንም በደላቸውን ለመቁጠር ተፋጠኑ እንጂ።

#የምህረት_አዋጅ

ነነዌ ከቤት መንግስት እስከ ቤተ ከህነት፣ ከነጉስ እስከ አሽከር፣ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሰው እስከ እንስሳ ማቅ ለበሰች። ሃያላን መንግስታትን ያንበረከከች ነነዌ፣ በአንድ ዕባራዊ ተብረከረከች። ሊቁ ቀዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው እንዲህ ይላል ‹‹የነነዌ ንጉሥ ወታደሮቹን ሰብስቦ እንዲህ አላቸውም፣ ይህ ድል እንደተጎናጸፍንባቸው ውጊያዎቻችን አይደለም ፤ ከባዕድ ሀገር በተሰማው ዜና ኃያላኖቻችን ሳይቀሩ ተብረክርከዋል ፤ አንድ ዕብራዊ መጥቶ በቃሉ አብረከረከን፡፡የጀግኖች እናት ነነዌ አንድን ለብቻው የመጣ ደካማ ሰው ቃል ፈርታለች፡፡ ስለዚህ ወገኖቼ ፤ የማይፈርስ አጥር እንገንባ ፤ ይህች አጥር ንስሓ ናት ፤ ሥውር ጦርነት ታውጆብናልና ራሳችንን ሥውር መሣሪያ እናድርግ››። ነነዌ ለሶስት ቀን ነሰሃ ገባች። እግዚአብሄርም በምህረት ከእሷ ተመለስ በነብዩ ኤርሚያስ እንደተናገረውም ሊያደርግባቸው ካሰበው ተጸጸተ።

#እኛስ?

ወገኖቼ! እኛስ? በደላችን ከነነዌ ሰዎች አልባሰምን? ክፋታችን በእግዚአብሄር ፊት አልወጣምን? እግዚአብሔርስ እንድ ዮናስ ነብይ አስነስቶ አልገሰጸንምን? እንደ ምህረቱ ባይሆን ኖሮ እንደ ስራችን ቢሆን ይሄኔ በእሳት አንጠፋም ነበር?

ወዳጆቼ እንደ ነነዌ ሰዎች፣ እኛም ማረን እንበለው፣ መሃሪ ነውና ይምረናል፣ በእንባ ወደሱ እንመለስ። የቀረንን ዘመን ሳይሆን በደላችንን እንቁጠር። የመዳን ቀን ዛሬ ነው ይላል መጽሐፍ፣ ዛሬን ወድሱ እንመለስ። ወዳጆቼ! ይሄን ጾም ነነዌ ስንጾም፣ በግብርም በህሊናም እነሱን እንምሰል።

📜በ፭ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ትምህርት ክፍል ትምህርታዊ ሥነ-ጽሑፍ ንዑስ ክፍል የተዘጋጀ

የካቲት 18, 2016