የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
304 subscribers
886 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
"ወእንዘ ትጸውሙ - ስትጾሙ" ማቴ፮፥፲፮
➥[ከገብርኄር የቀጠለ #ዘኒቆዲሞስ]➥
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ወእንዘ ንጸውም - ስንጾም አባቶቻችንን በማሰብ [እንደአባቶቻችን] ነው
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

❖ ታላቁ ጾማችን በሃይማኖት ስለመጽናት፣ በቅድስና ስለማደግ፣ በቤተክርስቲያን ስለመኖር፣ ቢወድቁ በንሰሀ ስለመነሳት አስተምሮን እንዳስተማረን ሆነን ጌታን መጠበቅ እንዳለብንና እርሱ ጌታችን ሲመጣ ዋጋን እንደሚከፍለን ከዘወረደ እስከ ገብርኄር ባሉት ሳምንታቱ አስረድቶናል።

"እንደዚህ ሆኖ መኖር እንደምን ይቻላል?" የሚል ካለ በወንጌል የተነገረንን ትምህርት ኖረው በተግባር ያሳዩንን አበው መመልከት እንደሚገባ የዓቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት ይጠቁመናል - #ኒቆዲሞስ!

❖ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቅዱሳን እንድንመለከት፣ እነርሱንም እንድንመስል ያስተምረናል

✟ "ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ" ኢሳ ፶፩፥፪
✟ " እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ" ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩

❖ ቅዱሱ መጽሐፍ "ወሀሎ አሀዱ ብእሲ ... - ... አንድ ሰው ነበረ" እያለ ስለቅዱሳኑ የሚነግረንም እንድናዘክራቸው /እንድናስባቸው/ እና የእምነታቸውን ፍሬ እየተመለከትን በእምነት እንድንመስላቸው ነው [ዕብ፲፫፥፯]

ወንጌልን በተግባር ካሳዩን እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን ቅዱሳን አንዱ ኒቆዲሞስ ነው!
"ወሀሎ አሀዱ ብእሲ...ዘስሙ ኒቆዲሞስ - ...ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ" ዮሐ፫፥፩
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ኒቆዲሞስ በዓቢይ ጾም ሳምንታት

ኒቆዲሞስ #በዘወረደ - ኒቆዲሞስ በዘወረደ ሃይማኖት ጸንቶ የኖረ ነው። የጸናበትንም ሃይማኖት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተምሯል ጌታም አምስቱን አዕማደ ምሥጢራት እንደወርቅ አንከብሎ እንደሸማ ጠቅልሎ አስተምሮታል (ዘርዝሮ ለማየት ቦታው አልፈቀደም)

ኒቆዲሞስ #በቅድስት - ኒቆዲሞስ ሊቅ፣ ባለጸጋ፣ ባለሥልጣን ቢሆንም እነዚህ ሁሉ እሾኽ ሆነው ሳያንቁት በትህትና ሆኖ የመምህሩንም ተግሳጽ ታግሶ ተምሯል። አይሁድ ስህተታቸውን ሲገልጥባቸው "መርምር፣ እይ" ሲሉት ታገሳቸው እንጂ ክፉ የሆነ የትዕቢትን መልስ አልመለሰላቸውም [ዮሐ፯፥፶፪]
ትህትና፣ ትዕግስት፣... የመሳሰሉ ዕንቁዎች የተገኙበት ኒቆዲሞስን እየተመለከትን በቅድስት እንኑር

ኒቆዲሞስ #በምኩራብ፦ ኒቆዲሞስ በዘወረደ ሃይማኖት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በገባበት ጸንቶ የኖረ ነው።
ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን ህብረት ናትና ኒቆዲሞስን ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በኅብረት ሆኖ እናገኘዋለን
ዛሬም በሃይማኖት ጸንተው በምግባር አሸብርቀው በአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ፤ ዘወትር "ቅዱሳነ ሰማይ ወምድር ማኅበረ ሥላሴ አንትሙ..." እያልን ከምንማጸንባቸው ቅዱሳን መካከል ነው- ኒቆዲሞስ!

ኒቆዲሞስ #በመጻጉዕ፦ አስቀድሞ በሌሊት መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ ፍርሃት የተባለ በሽታ ነበረበት። በዚህ ህመሙ ግን ተስማምቶ መጻጉዕ እስኪባል አልጠበቀም። እነ ቅ/ጴጥሮስን ሳይቀር ከማስካድ አድርሶ የነበረውን ይህንን ክፉ በሽታ ፍርሀትን ከራሱ አራቀው ነፍሱንም ከመጻጉነት አተረፋት
በዮሐ፫ ፍርሃት አይሎበት የነበረው ኒቆዲሞስ በዮሐ፯፥፶ ተሻሽሎ በዮሐ፲፱፥፴፱ ፍርሀቱን ፍጹም አስወግዶ እናገኘዋለን
ኒቆዲሞስ #በደብረዘይት፦ ኒቆዲሞስ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተማረው አምኖ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የተወለደ ነውና የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ ሊገባም ደብረ ዘይትን ይጠብቃል።

ኒቆዲሞስ #በገብርኄር፦ ኒቆዲሞስ ደብረ ዘይት(ዳግም ምጽአት)ን የሚጠብቀው በሀዘንና በጭንቀት አይደለም። እርሱ በጥቂቱ የታመነ ገብርኄር ነውና በብዙ ሊሾም በተስፋ የሚጠብቅ ነው። ኒቆዲሞስ በረከትን የሚሰጥ የህግ መምህር ስለሆነ ከኃይል ወደ ኃይል እየሄደ በጎ አገልግሎትን አገልግሏል። አገልጋዮች በሸሹባት በዚያች በዓርብ ቀን ነፍስ የተለየችው መለኮት የተዋሃደውን የጌታችንን ሥጋ ከመስቀል አውርዶ ገንዞ በመቅበር ያገለገለ በእውነት ታማኝ አገልጋይ- ኒ ቆ ዲ ሞ ስ!

❖ በአርአያ ኒቆዲሞስ ተጉዘን ሆሳዕና እያልን ከህጻናቱ ጋር ለመዘመር ያብቃን። ይቆየን።

✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥