የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
304 subscribers
886 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
"ወእንዘ ትጸውሙ - ስትጾሙ" ማቴ፮፥፲፮
➥[ ከምኩራብ የቀጠለ #ዘመጻጉዕ]➥
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ወእንዘ ንጸውም - ስንጾም ከደዌ ነፍስ በመፈወስ ነው

❖ የዓቢይ ጾም ሳምንታት እንዳስተማሩን በዘወረደ ሃይማኖቱ የጸናለት በቅድስት ምግባሩ የቀናለት በምኩራብ መኖሪያውን ያደረገ ሰው በዚህ አኗኗሩ ለመጽናት መታገል አለበት
❖ የትግሉ ምክንያት በዚህ አይነት ሕይወት እንድንኖር  የማይወድ ጠላት አለብንና ነው። እርሱም ዲያብሎስ ነው።
" መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ" እንዲል ኤፌ ፮፥፲፪

❖ ጠላት እኛን ሲያደክመን ስለሚገጥመን ደዌ የሚያስተምረን የታላቁ ጾማችን ክፍል - #መጻጉዕ ነው!

❖ ደዌ ዘሥጋ ደዌ ዘነፍስ አለ - የሥጋ የነፍስ ህመም/በሽታ።

ደዌ ዘሥጋ በልዩ ልዩ መንገድ ይመጣል [ዮሐ ፭- ትርጓሜ]
◎ እንደ ጢሞቴዎስ ለንጽሕና የሆነ ደዌ ዘንጽህ አለ [፩ኛ ጢሞ፭፥፳፫]
◎ እንደ እዮብ ለዋጋ የሆነ ደዌ ዘዕሴት አለ [ኢዮ፪]
●ሄሮድስ እንደደረሰበት ያለ ደዌ ዘመቅሰፍት አለ
●እንደመጻጉዕ ያለ ደዌ ዘኃጢአትም አለ [ዮሐ፭፥፲፬]

➥ ደዌ ዘሥጋ ለንጽህና ለዕሴት ከሆነ ቢታገሱት ዋጋን ያሰጣል
ቅዱስ ጳውሎስ የሚለውን ተመልከቱ "የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ" ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፯-፱

➥ የመቅሰፍት ኃጢአት ከሆነም በንሰሀ ይርቃል በምስጢረ ቀንዲል ይፈወሳል።

"ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል" ይላል ያዕ፭፥፲፬-፲፭

ከደዌ ሥጋ ይልቅ የሚከፋው ደዌ ዘነፍስ ነው።
ሥጋችን በባዕድ (Bacteria ወይም Virus) ሲወረር ህመምተኛ እንደሚሆን ነፍሳችንን የዲያብሎስ ግሳት ሲወራት ህመምተኛ ትሆናለች

ተወዳጆች! መዝሙር ማድመጥ ሰልችቶናል? ቃለ እግዚአብሔር የመመገብ ፍላጎታችን ቀንሶብናል? ወደ ቤተ እግዚአብሔር ለመሄድ አቅቶናል? የአገልግሎት ሙቀታችን ቀንሶ ብርድ ብርድ ብሎናል? እንግዲህ ነፍሳችን ታማለችና ምን እንጠብቃለን?!

ለሥጋችን ምግብ ከዘጋን፣ ብርድ ብርድ ካለን፣ እንደልባችን መንቀሳቀስ ካቃተን ታመናልና ፈጥነን ወደ ሆስፒታል እንደምንሄድ የነፍሳችን ጤንነቷ ሲታወክብንም ወደ አማናዊቷ ሆስፒታል ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሄደን ከነፍሳችን ዶክተሮች ካህናት ጋር በመገናኘት እነርሱ በሚሰጡን ህክምና ወደ ጤንነታችን መመለስ ይኖርብናል

ነፍሳችን ከልዩ ልዩ ደዌያት የራቀች እንደሆነ ብዙ ነገራችን ይስተካከልልናል

በማቴ ፱፥፳፯ የተጠቀሱት ሁለቱ ዕውሮች የለመኑት ልመና #ማረን የሚል ነበር ጌታችን ግን ዓይናቸውን አበራላቸው ለነፍሳችን ምህረትን የለመንን እንደሆነ የቀረው ዳረጎት መሆኑን ይህ ታሪክ በግልጥ ያስረዳናል።

❖ምንጩን/የነፍሳችንን/ ካስተካከልን ከዚያ በኋላ ያለው የሚያስጨንቅ አይሆንም ይልቅ ከሐዋርያው ጋር "እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን" እያልን የመንዘምርበት ምክንያት ይሆነናል [ሮሜ፰፥፳፰]።

❖በእኛ ተገብቶ የተናገረ ደራሲ "ወስክኒ ክራማተ እስከ እገብር ጽድቀ - ጽድቅን እስክሠራ ዕድሜን ጨምሪልኝ" እንዳለ ዕድሜን ለጽድቅ ስራ እንለምን በተሰጠንም ዕድሜ ከደዌ ነፍስ እንፈወስበት [መልክዐ ማርያም - ለክሳድኪ]።

ያን ጊዜ ከአቡቀለምሲስ ጋር "አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና" እንላለን [ራእ ፳፪፥፳]

"ሰው የሚፈልገውን ከሠራ የሚጠብቀው ሞቱን ነው" እንዲሉ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ለነፍሳችን የሚገባትን ካደረግን #ደብረ_ዘይትን በተስፋ እንጠብቃታለን - ይቆየን!
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥