የጊንር ጽጌ ተዋህዶ ሰ/ት ቤት
287 subscribers
885 photos
16 videos
12 files
19 links
ይህ ቻናል ዓላማውን የሰንበት ት/ ቤቱን ጠቃሚ መረጃዎች እና መልእክት ማስተላለፍ አድርጎ ጥር 19/2012ዓም ሌሊት 6:50 ላይ ተከፈተ፡፡
Download Telegram
"ወእንዘ ትጸውሙ - ስትጾሙ" ማቴ፮፥፲፮
➥[ከቅድስት የቀጠለ #ዘምኩራብ]➥
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥

ወእንዘ ንጸውም - ስንጾም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለብን በማሰብ ነው

❖ ታላቁ ጾማችን በዘወረደ ሃይማኖትን አስረድቶን፤ በተረዳች ሃይማኖት እንዴት መኖር እንደሚገባን በቅድስት ሰብኮን፤ በሃይማኖት ጸንተን በምግባር በርትተን የምንኖርባትን መኖሪያ ደግሞ በሦስተኛው ሳምንቱ ይነግረናል - #ምኩራብ!

❖ በአንዲት ሃይማኖት ሆኖ በምግባር ጎልምሶ [ክርስቲያን ሆኖ] መኖር የሚፈልግ ሰው እንዲህ ያለው ህይወት የት እንደሚኖር ካላወቀ በከንቱ ይባዝናል እንጂ ክርስቲያናዊ ህይወትን መኖር አይቻለውም

◎ ከበረቷ ውጪ የምትባዝን በግ የተኩላ ሲሳይ ትሆናለች እንጂ አትጠቀምም ስለዚህ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በወንጌል " ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ" አለን [ዮሐ ፲፥፲፮]

◎ዛሬ በቅዳሴ ላይ በንፍቁ ካህን የተነበበው የመጽሐፍ ክፍል ይሄንኑ ያስረዳናል -ሐዋ ፲፥፩-፱
"...ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ"
ቆርኔሌዎስ ምንም እንኳን እንዲህ ባለ የተመሰገነ ሕይወት ቢኖረውም ይህ አኗኗሩ ትርጉም የሚኖረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ሲጨመር ነውና መልአኩ ጴጥሮስን አስጠርቶ እንዲጠመቅ ነገረው።
ቆርኔሌዎስ በምኩራብና በቅድስት ያለ በግ ነበረና እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ወደ በረቲቱ ምኩራብ አመጣው

❖ በቤተ ክርስቲያን ስንኖር ብዙ አይነት አኗኗር አለና እንዴት ሆነን በምን አይነት አኗኗር መኖር እንዳለብን ልናውቅ ያስፈልገናል
" ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው" ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፭

● ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናትና በመከፋፈል ልንኖርባት አይገባም

● ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናትና በርኩሰት ሆነን ልንኖርባት አይገባም

●  ቤተ ክርስቲያን ኩላዊት ናትና ዘረኞች ሆነን ልንገኝባት አይገባም

● ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናትና ከሐዋርያትና በእነርሱ እግር ከተተኩ አበው ከተቀበልነው ወግ ውጪ ልንሆንባት አይገባም

● ቤተ ክርስቲያን የበጎች በረት ናትና የተኩላ፣ የጅብ፣...... የአራዊት ጠባይ ይዘን በውስጧ መገኘት አይገባም

❖ የጸሎት ቤት በሆነች በእግዚአብሔር ቤት
◎  #ሀና_ወለተ_ፋኑኤል_በጾምና_በጸሎትም_ሌሊትና_ቀን_እያገለገለች_ከመቅደሱ_ሳትለይ_ኖረች [ሉቃ፪፥፴፯]

#ስምዖን_አረጋዊ_ትንቢቱን_በመጠባበቅ_ኖረ [ሉቃ፪፥፳፭-፴፪]

● አይሁድ ግን የጸሎቷን ቤት በንግድ ተሰማሩባት ለቤቱ የሚቀናው ጌታችንም እየገረፈ አስወጥቶ "ወኢትረስዩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ - የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጓት" አለ [ዮሐ ፪፥፲፮]

❖ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን "መንፈሳዊት ዓውድ መዝገበ ሥርናይ እንበለ ክርዳድ - መንፈሳዊት መመላለሻ እንክርዳድ የሌለባት የስንዴ መሰብሰቢያ" ይላታል

◉ በመንፈሳዊቷ መመላለሻ በዘረኝነት፣ በዓለማዊነት፣ በትዕቢት ለተመላለስን- ወዮ!
◉ የስንዴ መከማቻ በሆነችዋ ጎተራ እንክርዳድ ሆነን ለተገኘን ለኛ - ወዮ!

እግዚአብሔር የቤቱ ቅናት ይበላዋል ከማንም በላይ እርሱ ስለቤቱ ይቀናል። እስካሁን ጅራፉን ያላነሳብን ምን አልባት ከነፍሳችን በሽታ እንድንፈወስ መጻጉነታችንን እየታገሰን እንጂ ኃጢአታችንን ወድዶልን አይደለም! ይቆየን!
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥