TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚያዘምን የኮምፒውተር ስርዓት ሊተገበር ነው
===============================
የኢትዮጵያን የሎጅስቲክስ ዘርፍ የሚያዘምን የተቀናጀ የሎጅስቲክስ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት እና የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መካከል ተደረሰ፡፡ የኮምፒውተር ስርዓቱ ሐብት የት እንዳለ በአግባቡ ተረድቶ ለመጠቀም እና የክትትል ስራዎችን ለመስራት ጠቃሚ አንደሆነ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ያስረዱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ዘርፉን በICT በማገዝ የትራንስፖርት ስራዎችን እንደሚያስተሳስር እና የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ እንደሚጠቅም ጠቁመው አልፈዋል፡፡
አዲሱ ስርዓት የሎጅስቲክስ ዘርፉን ውጤታማ እና ወጪ ቆጣቢ ከማድረጉም በተጨማማሪ በተለይ ወደ ወደብ የሚደረጉ ጉዞዎችን የሚያሻሽል ይሆናል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ መረጃ አስተዳደር፣ የስራ ቅንጅት እና የጉዞ አስተዳደር ረገድ ማሻሻያዎችን እንደሚያመጣ ሲታመንበት ከዚህ በፊት በተተገበሩ ስርዓቶች ላይ ይስተዋል የነበረውን የቅንጅት ጉድለት እንደሚቀርፍ ስርዓቱን አስመልክቶ በቀረበው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም ባለፈ ግን ይህ ብዙ ክፍተቶችን የሚሸፍን ስርዓት ባክኖ እንዳይቀር ዘላቂ ድጋፎች እንደሚያደረጉና ተቋማቸውም በከፍተኛ ኃላፊነት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል መሆኑን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትን ወክለው የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሳንዶካን ደበበ ተናግረዋል፡፡
በመግባቢያ ሰነዱ ፊርማ ላይ የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዲሁም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትሩ ዶ/ር አብረሀም በላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የለውጥ አመራሩ የለያቸው የህብረተሰብ ጥያቄዎችን ከመመለስም ባሻገር የሎጅስቲክ ስርቱን እንደሚያዘምን ወሮ ዳግማዊት የገለጹ ሲሆን ዶ/ር አብረሀም በበኩላቸው ብዙ ባለድርሻዎች እንደሚሳተፉበት በማወቅ ስራዎች በጥራት እና ደህንነታቸው ተጠብቆ ይከናወኑ ዘንድ አሳስበዋል፡፡
እጅን መታጠብ ያድናል !!!

ተመራማሪዎች አሁንም ቢሆን የኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ መንገድን ለመረዳት በጥረት ላይ ናቸው፡፡ ቢሆንም ሁሉንም የሚያስማማ አንድ እውነታ አለ፤ እጅን መታጠብ እና ፊትን አለመነካካት በእጅጉ እንደሚጠቅመን፡፡ እጅን መታጠብ ለኮሮና ብቻም ሳይሆን አይነታቸው ለበዛ ሌሎች ቫይረሶችም ሁነኛ መከላከያ መፍትሄ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ታድያ አለኝታነቱ በበሽታው ላለመያዝ ለሚታትሩት ብቻ አይደለም፤ ተይዘው ከአልጋ ለዋሉትም እንጂ፡፡ በበሽታው የተጠቃን እንደሆነ እጃችንን በመታጠባችን ብቻ ከእኛ ወደ ሰዎች እንዲሁም ሰዎች ሊነኳቸው ወደሚችሏቸው ቁሳቁሶች እንዳይተላለፉ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለ “20 ሴኮንድ” በሳሙና መታጠብ እራስን፣ ቤተሰብን እና ማህበረሰብነ ለመጠበቅ ቀዳሚው አማራጭ ነው፡፡
ኮሮናንም ሆነ ሌሎች በሽታዎችን የሚያመጡ ተህዋሲያን በዙርያችን እና አዘውትረን በምንነካቸው ቁሶች ላይ ሰፍረው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ የእጅ መታጠብ እነርሱን የመከላከል ኃይሉን እንዲያገኝ ያደረገው ተህዋሲያኑን ከእጃችን ማስለቀቅ በመቻሉ ነው፡፡ ይህም በምንታጠብበት ሰዓት ሳሙናው በእጃችን ላይ የተከማውን ዘይት እና ቆሻሻ አጥቦ ስለሚያወርዳቸውና ተህዋሲያኑም በዚህ እንቅስቃሴ ታጥበው ስለሚርዱ ነው፡፡ ስንታጠብ እጃችንን በምናሽበት ሰዓትም ዘይቱን ለማስለቀቅ የሚያበቃ ፍትጊያ እንፈጥራለን፡፡ በባዶ ውሃ መታጠብ በትንሹ ሊረዳን ይችላል፤ ካለመታጠብም የተሸለ ነው፡፡ ሆኖም ውጤታማነቱ በእጅጉ የወረደ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
እዚህ ላይ ግን ዋናው ችግር ከእኛ ዘንድ ያለው ግድ የለሽነት ነው፡፡ እጅን መታጠብ ያለው ኃይል ለመቶዎች አመታት ሲነገር ነበር፡፡ ብዙ ሃይማኖቶችም እጅ መታጠብን ሲያበረታቱ ቆይተዋል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ብቅ ያለው በጀርም ላይ የሚያውጠነጥን የበሽታ ትንተናን ተከትሎ በህክምናው ዓለምም ያለው ስፍራ ሊጨምር ችሏል፡፡ ሆኖም በጉዳዩ ዙርያ ዕውቀት መኖሩ እና የማንቂያ ስራዎች ለዓመታት መሰራታቸው ከመፀዳጃ ቤት መልስ እንኳን እጃችንን የምንታጠብ ሰዎች የዓለማችን ህዝብ ብዛት አንድ አምስተኛው እንኳን ሊያልፍ አልቻለም፡፡ ይታጠባሉ የሚባሉትም ቢሆን እንደነገሩ ከመታጠብ ባሻገር ሁሌም በስነ ስርዓት ለ20 እና 30 ሴኮንድ ሲታጠቡ አይስተዋልም፡፡
“እጃችንን በአግባቡ እንታጠብ” !!!
“ፊታችን ከመንካት እንቆጠብ” !!!
ምንጭ፡ Popular Science
TECHIN weekly seminar
For this week Wubishet Begashaw will discuss “design and develop digital traffic light system based on PICMICRO CONTROLLER” and “inventing user-centered technology: the case of BIRR ETHIOPIC” will be presented by Samuel Zeber.
As always we are delighted to have you here tomorrow.
በሀገር ልጆች የተሰሩት የፈጠራ ስራዎች
===
ትናንት በተካሄደው የቴክ-ኢን ሳምንታዊ ሴሚናር ሁለት ተጋባዥ የፈጠራ ሰዎች ተገኝተው ስራቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ የዕለቱ የመጀመሪያ ቴክኖሎጂ ሆኖ የቀረበው የአቶ ሳሙኤል መለሰ ዓለም ስራ የሆነው ብዕር የኢትዮፒክ ነው፡፡ ይህ የሲስተም ሶፍትዌር የግዕዝ ፊደልን ተጠቅሞ መፃፍን ቀላልና ማንኛውም ሰው ያለ ምንም እንግሊዝኛ እውቀት ሊያደርገው በሚችለው መልኩ ከማቅረቡም በላይ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችንም በአማርኛ ለመፃፍ ያስችላል፡፡ ቴክኖሎጂው በሁሉም ኮምፒውተሮች ላይ እንደሚሰራና ሁሉም ሰው በቀላሉ ተምሮ ሊጠቀምበት እንደሚችል አቶ ሳሙኤል የተናገሩ ሲሆን ወደ ተግባር ከተገባበት በሀገር ምጣኔ ሐብት ላይም በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት ጥቅምን ይዞ እንደሚመጣ ገልፀዋል፡፡
በአቶ ውብሸት በጋሻው ተሰርቶ የቀረበው ሁለተኛው ቴክኖሎጂ የትራፊክ መብራት አሰራርን የሚያዘምን ስርዓት ነው፡፡ ስርዓቱ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ እና የትራፊክ ጫናውን በመመልከት የሚያስተናብር ነው፡፡ ይህም ሲባል የትራፊክ መብራቱ ብዙ ተሸከርካሪዎች ያሉበትን አቅጣጫ በሚገጠምለት ሴንሰር አማካኝነት ስለሚረዳ ከሌሎቹ በተሸለ ከዚያ አቅጣጫ ለሚመጡት ተሸከርካሪዎች ሰፋ ያለ የማለፊያ ጊዜን ይፈቅድላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ አቅጣጫ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ሲያልቁ ለአቅጣጫው የተመደበለት የመተላለፊያ ሰዓት ማለቁን ሳይጠብቅ ቀይ መብራትን በማብራት ከሌላ አቅጣጫ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች እንዲያልፉ ያደርጋል፡፡
ቴክኖሎጂው በትራፊክ መብራት ብቻ የማይገደብ እና ለሌሎቸም አገልግሎቶች መዋል የሚችል መሆኑን አቶ ውብሸት አብራርተዋል፡፡
ሁለቱም ባለሙያዎች ስለ ፈጠራቸው ከማብራራትም ባሻገር ከኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እና ታዳሚያን የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ስማርት ቴክኖሎጂ ምንድነው?
===================
ቴክኖሎጂ በተለያዩ የስራና እንቅስቃሴ ምህዳሮች ውስጥ መሰራጨትን ተከትሎ የስማርት ቴክኖሎጂ ባለንበት ዓለም ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል፡፡ አሁን አሁን ስማርት ቴክኖሎጂዎችን በብዙ ቁስ እና ስርዓቶች ላይ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ስማርት ስልክ፣ ስማርት ቴሌቪዥን፣ ስማርት ሰዓት….ብዙ የስማርት ማዕረግን ያንጠለጠሉ መሳርያዎችን በየዕለቱ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከነዚህ ባለፈ ግን ስማርት በጤና አጠባበቅ፣ የመንገድ አገልግሎት፣ ኃይል ስርጭትና ቁጥጥር፣ በመንግስታዊ አስተዳደር፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ መዝናኛና ቱሪዝም በቴክኖሎጂው ተገልጋይ ከሆኑ ስርዓቶች ውስጥ ይገኙበታል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እንኳን ብናይ የስማርት ቴክኖሎጂ የበይነ መረብ እና ሌሎች የግንኙነት መንገዶቻቸው እንዲሰፋ ከማድረጉም በተጨማሪ ስልኮቹ ከዚህ በፊት ተነጣጥለው ይገኙ የነበሩ አገልግሎቶች በአንድ አሰባስበው እንዲሰሩ አስችሎታል፡፡
የተጠቀሱት አገልግሎቶቹ እንዳሉ ሆኖ በስማርት ቴክኖሎጂ ምንነት ላይ ግን የጠራና ሁሉን ያማከለ ትርጓሜ መስጠት አዳጋች ነው፡፡ ለምሳሌ በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ እይታ ስማርት ማለት ማንኛውም አይነት ስርዓት ወይም መሳሪያ (Device) ሆኖ ነገሮችን የመረዳትና (ሴንስ የማድረግ) የመቆጣጠር ብቃት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ትርጓሜ አሰጣጥ ዕይታ ሁሉም የስማርት ቴክኖሎጂዎች ከባቢያቸውን ይረዳሉ፤ አገልግሎቶቻቸውንም የሚሰጡት በዚህ ምልከታ ላይ ተመስርተው በሚያሳልፉቸው ውሳኔና አመራር አማካኝነት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ስማርት አንፖሎች ብርሃንን የሚለቁት አካባቢያቸው መጨለም አለመጨለሙን በማረጋገጥና ያለውን የሰው ልጆች እንቅስቃሴ በመገምገም ነው፡፡
የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) ላይ ስንመጣ የስማርት ቴክኖሎጂ ምንነት በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ እይታ መሰረት ስማርት መሳሪያዎች ዙሪያቸውን ከመረዳትና ከመቆጣጠር ባሻገር ከሌሎች መሳሪያና ስርዓቶች እንዲሁም የግንኙነት መረቦች ጋር ትስስርን መፍጠር መቻል አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ችሎታቸው የስማርት መሳሪያዎችን ምንነት ትርጓሜ ከባቢያቸውን ወደሚያጤኑ፣ ከተጠቃሚዎቻቸው ጋር መስተጋብርን የሚፈጥሩ እና እርስ በእርሳቸው ግንኙነትን ወደሚመሰርቱ ግለሰባዊ ማሳሪያነት (Personal Device) ያሸጋግራቸዋል፡፡ ለዚህ በምሳሌነት በየተጠቃሚው ደጃፍ የሚተከሉትን ስማርት የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣሪዎች ብናይ እንኳን ቆጣሪዎቹ የተቀበሉትን እና በሰዓቱ እየተጠቀሙት ያለውን የኃይል መጠን መዝግበው ለኃይል አቅራቢ ተቋሙ ያሳወቃሉ፡፡ እንዲያደርጉት ሆነው ፕሮግራም ከተደረጉ ደግሞ የሚገባውን ኃይል የመቆጣጠርና የመመጠን ብቃትም ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስማርት ስልኮችን፣ ስማርት ማቀዝቀዣዎችን፣ ስማርት ምስለ መስኮቶችን እንዲሁም ሌሎች መሰል መሳሪያዎችን በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ምሳሌ ሆነው መቅረብ ይችላሉ፡፡
ምንጭ፡ ቴክ ሳይንስ፤ ቅፅ ፲፮
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀም በኢንስቲትዩታችን ጉብኝት አድርገዋል
=======================
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀም በላይ ከአመራር ቡድን አባላቶቻቸው ጋራ በመሆን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት ተቋሙ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ ከተነሳበት ወቅት አንስቶ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንቲትዩት ሆኖ ከቆመ በኋላም በተሰሩ ስራዎች እና ባጋጠሙ ተግዳቶች ዙርያ በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ ገለፃ ቀርቦላቸዋ፡፡ አቶ ሳንዶካን በገለፃቸው ወቅት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸው ዘንድ ጥያቄ ሲያቀርቡ ሚንስትሩ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩ በውይይቱ አስታውቀዋል፡፡
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆኑ ተቋመት አንዱ ሲሆን ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀምም ከቅርቡ ሹመታቸው ወዲህ መሰል ጉብኝትን ወደ ኢንስቲትዩቱ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
የኮሮና ቫይረስ እና መልስ ሊሰጣቸው የሚገቡት ጉዳዮች
*******************************
የኮሮና ቫይረስ ወይም በይፋዊ ስሙ COVID-19 ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሌሎች የአለማችን ክፍሎች እስከተዳረሰበት የአጭር ወራት ጊዜ ውስጥ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ብዙዎችን ሲያነታርኩ እና ሲያከራክሩ የቆዩ ጉዳዮችም ሲሰሙ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም ቫይረሱ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ምልክቶችን በትክክል ለመመልከት ምን ያህል ቀን ይፈጃል የሚለው ጉዳይ እና ምልክቶችስ ከመታየታቸው በፊት ቫይረሱ ወደሌሎች የመተላለፍ እድሉ ምንያህል ነው የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ተገቢ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ተመራማሪዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ከስንት ቀናት በኋላ ምልክቶችን ማሳየት እንደሚጀመር ለመረዳት ሰፊ ጥናት ሲያደርጉ እንደነበር በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ይህ incubation period of a virus በመባል የሚታወቀው ፅንሰ ሃሳብ የትኛውም ቫይረስ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ምልክቶችን ለማሳየት የሚወስድበትን የጊዜ መጠን የሚያሳይ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜም እንደቫይረሱ ዓይነት እና እንደተጠቃው ግለሰብ የአቅም ሁኔታ የተለያየ ውጤት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
ታዲያ SARS-CoV-2 የተሰኘው የቫይረስ በሽታ ሰዎችን ካጠቃ ወይም infected ካደረገ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምልክቶችን በትክክል ማሳየት እንደሚጀምር ለማወቅ በተደረገ ሰፊ ጥናት ብዙዎችን ሊያስማማ የሚችል አዲስ ግኝት በጆንስ ሆፕኪነስ ዩኒቨርስቲ ይፋ ሆኗል፡፡ ጥናቱ የ SARS-CoV-2 ወይም የኮሮና ቫይረስ ኬዝ ያለባቸው 181 የቻይና ዜጎች ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰራ ሲሆን፤ በአማካኝም 97.5 በመቶ የሚሸፍኑት ተጠቂዎች 5.1 በሚሆን ቀናት ውስጥ ምልክቶቹ ሊታይባቸው እንደቻለ የምርምር ቡድኑ አስታውቋል፡፡ ይህም እስካሁን ሲደረግ የነበረውን የአስራ አራት ቀናት የለይቶ ማቆያ ጊዜ (quarantine period) ምክንያታዊ ቢያደርገውም የተቀረው 2.5 በመቶ የሚሸፍነው የቫይረሱ ተጠቂ ግን ሌሎች አከራካሪ ነጥቦች እንዲነሱ ምክንያት የሆነ ነው፡፡
በዚህ ስሌት መሰረት ጥናቱ የተደረገባቸው አብዛኞቹ (97.5%) የቫይረሱ ተጠቂዎች 11.5 በሚሆኑ ቀናት ውስጥ ዋና ዋናዎቹን የትኩሳት፣ የደረቅ ሳል እና የትንፋሽ መቆራረጥ ምልክቶች በየተራ ማሳየት የቻሉ ቢሆንም 2.5 በመቶ የሚሆኑት ግን ከ14 ቀን በላይ ምልክቶች ሳታይታይባቸው እንደቆየ የጥናት ቡድኑ የምርምር ውጤት ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ በሌላ አገላለፅ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡ 10,000 ሰዎች ቢኖሩ እና ቫይረሱ እንዳለባቸው ለማረጋጋጥ 14 ቀን ቢቆዩ፤ ከእነዚህ ውስጥ 101 የሚሆኑት በተገለሉባቸው 14 ቀናት ውስጥ ምንም ምልክት ሳይታይባቸው ከለይቶ ማቆያ ወይም (quarantine) ከወጡ በኋላ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡ ይህም እንደተመራማሪዎቹ ትንተና አሁን እየተሰራበት ያለው የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ጊዜ መቶ በመቶ ውጤታማ ያደርጋል የሚለውን መከራከሪያ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ በጥያቄ ለማንሳት እንደተሞከረው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ምልክቶቹን ከማሳየቱ በፊት ወደ ሌሎች ቫይረሱን የማስተላላፍ እድሉ ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ሌላው ትንታኔ የሚስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በዚህ ሃሳብ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን እና የሃገራት ኬዞችን የሚተነትኑ ባለሙያዎች እንደሚያነሱት ይህ ጉዳይ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው የኮሮና ቫይረስ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ስርጭት ትልቅ አስተዋፆኦ እንዳበረከተ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ፀሃፊዎች በትንታኔያቸው ላይ ለአብነት ያስቀመጡትን የማሳቹሴትስ ጉዳይ ለምሳሌ ብናነሳ በዚህ ግዛት ተመዝግበው የነበሩ 82 ኬዞች የስርጨት መነሻቸው በቫይረሱ የተጠቁና ምንም ምልክት ሳይታይባችው የቆዩ ጥቂት ግለሰቦች እንደነበሩ ከማስረጃ ጋር አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡ ይህ በአሜሪካ አንድ ግዛት የታየ ጉዳይ ቢሆንም በሌሎች ሃገራት የነበሩ ሁኔታዎችን ስንመለከት ቫይረሱ ከሚታሰበው በላይ የስርጭት መጡኑ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ሌሎች ያልተመለሱ ጥቄዎች እንዳሉ ሆነው ይህ ጉዳይም አስፈላጊውን ትኩረት እንዳለገኘ የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም እንደአጥኚዎቹ እና እንደተንታኞቹ መከራከሪያ ከሆነ ለእነዚህ ጉዳዮቹ የተሰጠውን ትኩረት ይበልጥ በማሳደግ የቀረቡ ጥናቶችን ከግምት ውስጥ ባማስገባት እና ትንተናዎችን በመመልከት የጤና መመሪያና ፖሊሲዎችን ከጉዳዮቹ ጋር አጣጥሞ ማስኬዱ ይበልጥ እንደሚበጅ ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
ምንጭ፡ https://edition.cnn.com/2020/03/14/
health/coronavirus-asymptomatic-spread/index.html እና https://bigthink.com/politics-current-affairs/coronavirus-incubation
አስቸኳይ ጥሪ ለፈጠራ ባለሙያዎች በሙሉ
=============================
የኢትዮጵያ ኢኖቬተርስ አሶሴሽን የኮሮና ቫይረስ (COVID -19) ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመግታት የሚያግዝ የፈጠራ ሐሳብ ያላችሁ ሁሉ ኑ በጋራ እንስራ ይላችኋል፡፡ የበለጠ መረጃ በደብዳቤው ላይ በተገለጽት አድራሻዎች የምታገኙ ይሆናል፡፡
COVID-19 የመግደል ምጣኔው ምን ይመስላል?
********************************
ኮቪድ-19 የሚል ስያሜ የተሰጠው ቻይና ውስጥ የተቀሰቀሰው ተላላፊ በሽታ እስካሁን ድረስ 182,000 ሰዎችን ሲያጠቃ 7,100 የሚሆኑትን ደግሞ ህይወታቸውን የነጠቀ ነው፡፡ ቫይረሱ ከአፍንጫ አንስቶ እስከ ሳምባ ያሉትን የመተንፈሻ አካላት የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ውስን ቀናት ከሚታየው ትኩሳት በማስከተል ደረቅ ሳል የሚኖረው ወረርሽኝ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ቫይረሱ ከሳምንት በኋላ የትንፋሽ ማጠርን እንዲሁ የሚያስከትል ሲሆን፤ በዚህም ሳቢያ አንዳንድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል በሀገሪቱ ተመዝግበው በነበሩ የኮሮናቫይረስ ኬዞች ተመርኩዞ በሚያወጣቸው የተለያዩ መረጃዎች መሰረት COVID-19 የከፋ በሚሆንበት ጊዜ እንደነ ኒሞኒያ፣ ሳርስና እና ሌሎች የውስጥ አካላትን ሥራ እንዲያቆሙ በማድረግ በጤናችን ላይ ችግር የሚፈጠሩ በሽታዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ መተንፈሻ አካላትን የሚያዳክም ሲሆን ሌሎች በሽታዎች ሲጨመሩበት ደግሞ ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ቫይረሱ በዕድሜ የገፉ እና እንደአስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም የመሳሰሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ይበልጥ በመጉዳት በህይወት የመቆየት እድላቸውን በእጅጉ ሊያጠበው እንደሚችል ቢገመትም ከነዚህ መረጃዎች ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተረጋገጠ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይነገራል።
ከታች በምስሉ እንደሚታየውም ቫይረሱ አጠቃላይ የሞት ምጣኔው እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ እና ተጨማሪ የጤና ችግር በተመዘገበባቸው ሰዎች ላይ አደገኛ በመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት በሚቻለው አቅም በመቆጣጠር የሞት መጠኑን መቀነስ እንደሚቻል ከማዕከሉ በወጣው መረጃ ማየት ይቻላል፡፡ ቫይረሱ በተለይም ከመተንፈሻ አካል ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸውን እና የካንስር በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ይበልጥ በመጉዳቱ እነዚህ ኬዞች ላይ ትኩረት በማድረግ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መሞከር ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካል ችግርን የሚያመጡ ተህዋሲያን ውስጥ የሚመደብ አንደመሆኑ መጠን በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት የሚያወጧቸው ጥቃቅን ጠብታዎች (droplets) በሽታው ከሰው ሰው እንዲተላለፍ ዋና ምክንያት በመሆናቸው፤ ስናስልና ስናስነጥስ አፍንጫና አፋችንን በሶፍት ወይም በክርናችን በመሸፈን፤ እጃችንን ሳንታጠብ ፊታችንን ባለመንካት እንዲሁም ከታመሙ ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ባለማድረግ በሽታውን በሚገባ መከላከል እንችላለን።
በቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የተሰራውን የምርምር ውጤት በዚህ ቻርት ይመልከቱ
ቢቢሲ