TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የከንፈር ቁስለት
==========
የከንፈር ቁስለት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን የሚያውክ የጤና እክል ነው፡፡ ሲከሰትም እንደ ምግብ መመገብ እና ጥርስን መፋቅ የመሳሰሉ ተግባራትን ያከብድብናል፡፡ ብዙውን ጊዜ ከንፈር ቁስለት ንክሻን በመሳሰሉ ቀላል ምክንያቶች ሊከሰት ቢችልም እንደ ካንሰር እና ሌሎች ቀላል እና ከበድ ያሉ የጤና እክሎችንም ተከትሎ ሊመጣ ይችላል፡፡ እነዚህ የአፍ ቁስለቶች ተላላፊ እና የህክምና እርዳታን የሚሹም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአፍ ቁስለትን ያመጣሉ ከሚባሉ ሌሎች ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
• ያልተመጠነ የጥርስ ተከላ
• ሹል ወይም የተሰበረ ጥርስ
• ብሬስ እና መሰል ቁሶች
• ትኩስ ምግብ እና መጠጥ
• ሲጋራ (ማጨስም ማቋረጥም)
• አንዳንድ ህክምናዎች
• ከፍተኛ የአሲድ መጠን ያላቸው ምግቦች
• ጭንቀት
• የቫይታሚን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች እጥረት
ህክምና
***
አብዛኛውን ጊዜ የከንፈር ቁስሎች በራሳቸው ይድናሉ፡፡ ለምሳሌ በቀላል ጉዳቶች አማካኝነት የሚመጡ ቁስለቶች ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ድህነታቸውን ይጨርሳሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቁስሉን ለማጥፋት የሚከተሉት መንገዶች ይመከራሉ፤
• በጨው ውሃ ማጠብ
• ትኩስ እና የሚያቃጥሉ ምግቦችን አለመመገብ
• ሲጋራን ከማጨስ መቆጠብ
• ከአልኮል መራቅ
• እንደ ብርቱካን እና ሎሚ ያሉ ፍራፍሬዎችን አለመመገብ
ሆኖም በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይሻለን አሊያም የኢንፌክሽን ምልክት ካሳዩ፣ ከነጡ እና ህክምናን ተከትለው የተከሰቱ ከሆኑ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መታከም ይኖርብናል፡፡
ምንጭ፡ Medical News Today
ኢትዮጵያና ሩሲያ የኒውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የኒውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ስምምነት በሩሲያ ሶቺ ተፈራረሙ።

የሁለትዮሽ ስምምነቱ በሩሲያ ሶቺ እየተካሄደ ካለው የአፍሪካ ሩሲያ የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ነው የተፈረመው፡፡

የስምምነቱን ፊርማ በኢትዮጵያ በኩል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በዛሬው ዕለት ፈርመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን፥ በቀጣይ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሃይል ምንጭነት መጠቀም የሚያስችላትን ተጨማሪ ፕሮቶኮል ፊርማ መፈረሟ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ኒውክሌርን ለማናቸውም ሰላማዊ ጥቅም በተለይም ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ እና የኤሌክትሪክ ሃይልን ለማመንጨት ጭምር እቅድ አላት።

Source.........FBC
ሳይጠጡ መስከርን ምን ይሉታል?
=====================

የ46 ኣመቱ ጎልማሳ አሜሪካዊ ምንም ዓይነት አልኮል በምላሱ ሳይዞር ይሰክራል፤ የቁጡነት ባህርይንም ያሳያል፡፡ ጠጥቶ በማሽከርከርም ተይዞ ወህኒ ከመግባት ቢሆን አላመለጠም፡፡ ምክንያቱም ምርመራዎች በደሙ መኖር ካለበት ሁለት እጥፍ የአልኮል መጠን መኖሩን በመናገራቸው፡፡ አለመጠጣቱን በየፖሊስ ጣቢያው እና ሆስፒታሉ ደጋግሞ ቢናገርም ማንም ሊያምነው አልቻለም፡፡ ግን ይህ ቀልድ ሊመስል ቢችልም አውቶ ብሪወሪ ሲንድረም (ABS) በተባለ በሽታ ከመጠቃት የሚመጣ ነው፡፡

አውቶ ብሪወሪ ሲንድረም በአንጀት ውስጥ ያለው ባክቴሪያ ካርቦሀይድሬትን ወደ ስካር አምጪ አልኮልነት እንዲለውጥ የሚያደርግ የጤና እክል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ታማሚዎቹ ስኳር ወይም ካርቦሀይድሬት የበዛባቸውን ምግቦች በሚመገቡበት ወቅት አረቄ ወይም ቢራ እንደጠጣ ሰው ሁሉ ወደ ስካር መንፈስ ይወረውራቸዋል፡፡ ከላይ የጠቀስነው ሰውም ታድያ ምግቡን ከተመገበ በኋላ መንቀሳቀስ ያቅተው እንደነበር ጉዳዩን የተከታተሉት ዶ/ር ፋርሀድ ማሊክ ገልፀዋል፡፡ ታማሚው ይህ ሁኔታ ያጋጥም የጀመረው እጁ ላይ ለደረሰበት የተወሳሰበ ጉዳት ይሆንለት ዘንድ በፈረንጆቹ 2011 የፀረ ባክቴሪያ መድሀኒት መውሰድ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ሆኖም ይህ መድሀኒት ከተወሰደበት ዓላማ ጎን ለጎን በአንጀቱ ውስጥ ያሉትን ባክቴሪያ፣ ፈንገስ ወይም ሌሎች ጥቃቅን ህዋሳትን ተግባር ረብሾ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ይህ ሰው ህመሙ ባመጣበት ጦስ ታስሮ ሳለ አንድ ግለሰብ በተመሳሳይ ህመም ህክምናውን እንደተከታተለ የሰማችው የዚህ ሰው አክስት ህክምናውን እንዲከታተል ነገሩ ወደተሰማበት ጤና ተቋም ትወስደዋለች፡፡ እዚያ ባከናወነው የሰገራ ምርመራ ሀኪሞቹ የቢራ እርሾ የመሰለ ነገርን በማግኘታቸው በተገለፀው በሽታ ለመጠቃቱ ይጠቁማቸዋል፡፡ ከስምንት ሰዓታት በኋላ ግን በሰውየው ደም ውስጥ ያለው የአልኮል ምጣኔ ወደ 0.05 በመቶ ሊያድግ ቻለ፡፡ ይህን ተከትሎ የምግብ እና ፀረ-ፈንገስ ህክምናን ብሎም ሳይካትሪስት እና ኒሮሎጂስቶችን ጨምሮ በተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ቢሰጠውም ከመስከር ሊድን አልተቻለውም፡፡ በአንድ አጋጣሚም በደሙ ውስጥ ያለው የአልኮል መጠን እጅጉን አሻቅቦ ለሞት ሊያበቃ በሚችል 0.4 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ሁኔታውን የተመለከቱት ሀኪሞች መጠጥ አለመጠጣቱን መናገሩን ከውሸት ቆጠሩበት፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር በሪችሞንድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል ባለሙያዎች ዕርዳታን ለማግኘት ወደዚያው ያቀናው፡፡ የማዕከሉ ሀኪሞች ታማሚውን ለሁለት ወራት በቅርበት ሲመረምሩት ቆይተው በአንጀቱ ውስጥ ያሉትን ተህዋሲያን ማስወገድ ቻሉ፡፡ ሀኪሞቹ በማስከተል ታማሚውን የሚረዱ ባክቴሪያዎችን እንዲያሳድግለት መድሀኒት የተሰጠው ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ወደጤነኝነት ሊመለስና ያማረውን አማርጦ ለመብላት በቅቷል፡፡ መቼስ አጃይብ ነው!!!

ምንጭ፡ Live Science
በማቴሪያል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈርቀዳጅ የሆነችው ኢትዮጵያዊት ተመራማሪ፡ ፕሮፌሰር ሶስና ሃይሌ
==================================
ፕሮፌሰር ሶስና ሃይሌ እ.ኢ.አ በ 1958 ከአዲስ አባባ የተገኘች ኢትዮጵያዊት ሳይንቲስት ናት፡፡ በ1967 በሃገሪቱ የመንግስት ለውጥ መምጣት ተከትሎ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ለመሰደድ የተገደደችው ፐሮፌሰር ሶስና አብዛኛውን የህይወት ጊዜዋንም በዚህ አንድታሳልፍ ሆናለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከቤተሰቦቿ ጋር አብራ በመሆን የልጅነት ጊዜዋን በሚኒሶታ ሃገረ ግዛት ገጠራማ አካባቢ ካደረገች በኋላ በ1986 የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በማቴሪያል ሳይንስና በኢንጂነሪንግ ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ማሳካት ችላለች፡፡

ፐሮፌሰር ሶስና በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት የፒችዲ ትምህርቷን ለመማር እንዲያስችላት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘችበት የማሳቹሴትስ የቴክኒሎጂ ኢኒስቲትዩት ያቀናች ሲሆን፤ በዚህም እንዲሁ በምትወደው የማቴሪያል ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ መመረቅ ችላለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከዚህ የተሳካ የትምህርት ጉዞዋ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኘችበት የካልቴክ ፋካልቲ ከማምራቷ በፊት ሲያትል በሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት የሰራች ሲሆን በዚህ የሶስት ዓመት ቆይታዋም ሀገሯን የሚያኮራና አፍሪካንም የሚያስጠራ ትልልቅ የምርምር ስራዎችን ለመስራት በቅታለች፡፡

ፐሮፌሰር ሶስና ድምራቸው ከ150 በላይ የሆነ የጥናትና ምርምር ፅሁፎችን በግል እና ከሌሎች ምሁራን ጋር በጋራ በመቀናጀት ሰርታ ለህትመት አብቅታለች፡፡ በስሟ የተመዘገቡላት ፓተንቶችም ቢሆን አስራ አምስትን ተሻግረዋል፡፡

ከነዚህ የህትመት እና ምርምር ውጤቶች ውስጥ ብዙሃኑ በጠጣር የአዮን ቁስ እና መሳሪያዎች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚያጠነጥኑት የፕሮፌሰር ሶስና ስራዎች መካከል ደግሞ ከዓመታት በፊት የሰሩት አዲስ ዓይነት የፊውል ሴል ከሌሎች ፈጠራዎቿ ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ሶስና ኬሚካሎችን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል በመቀየር ለመኪኖች፣ ሃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች ሃይልን ለሚጠይቁ ተግባራት ንፁህ የሃይል ምንጭ በመሆን እንዲያገለግለ፤ በማሰብ የፊውል ሴሎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል ቁስን ለመስራት አልማ ተነሳች፡፡ ይህ ሃሳቧም በአይነቱ አዲስ የሆነ የኃይል ማመንጫን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ የሚችል የሱፐርፕሮቶኒክ ቅንብር መስራትን ያጠቃልላል፡፡ ሆኖም ይህ ሃሳቧን ተቀብለው የአሰራር ስርዓታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ከመቀየር የታቀቡት የፊውል ሴል አምራቾች የራሷን ቤተ-ሙከራ ተጠቅማ በዓለም የመጀመሪያውን ጠጣር የአሲድ ፊውል ሴል ቁስ አካል እንድትፈበርክ ምክንያት ሆኗት፡፡ ኋላ ላይ ይህን አዲስ ፈጠራዋን የቀድሞ ተማሪዎቿ በንግድ ሰርቶ ማሳያነት የተጠቀመበት ሲሆን ለተመራሪዋም በአረንጓዴ የሃይል ልማት ዘርፍ ዕውቅናን እንድትሸምትበት አስችሏታል፡፡

ፕሮፌሰር ሶስና በአሁኑ ሰዓት ጠጣር ፊውል ሴሎችን በተለይም ለከባቢ ተስማሚ የሃይል ምንጭ መሆን በሚችሉት ላይ አተኩሮ የሚሰራን የምርምር ቡድን በሃላፊነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ቡድን የተለያዩ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ሲገኝ ከቅርብ ስኬቶቹ መካከልም ውሃና ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በቴርሞ ኬሚካል ሂደት አማካኝነት በመጠቀም የፀሐይን ኃይል ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሌላ ምዕራፍን የከፈተ ነበር፡፡ በፕሮፌሰር ሃና እና ቡድኗ እየተሰራባቸው ካሉት ስራዎች ውስጥ ፕሩቶንን አስተላላፊ ጠጣር አሲድ እና ፐሮቭስካይት ኤሌክትሮይቶች፣ የኤሌክትሮን እና ኦክስጅን ድብልቅን አስተላላፊ ፍሎሪት እና ፐሮቭስካይት እንዲሁም ኢ-ስቶይኪዮሜትሪክ ኦክሳይዶችን ማበልፀግ ይገኝበታል፡፡

ይህች ኢትዮጵያዊት እንቁ ተመራማሪ በትልቁ ስሟን ከሚያስጠሩ ስራዎቿ አንዱ ከሆነው የፊውል ሴል ፈጠራዋ በተጨማሪ በሴራሚክ ሳይንስ፣ በኤሌክትሮኬሚካል እና በፋንክሽናል ሶሊድ (electrochemical and functional solids) የደረገቻቸው ምርምሮች እና ያሳተመቻቸው ፅሁፎች በተሰማራችበት የሳይንስ ዘርፍ ከሚኖረው አበርክቶት ባለፈ ለብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ሴት ተመራማሪዎች የሚኖረው ጠንካራ መልእክት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ፐሮፌሰር ሶስና ለሰራቸው ስራና ላበረከተችው የምርምር ውጤት እውቅና የሚሆን ሽልማቶችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያገኘች ሲሆን ከእንዚህ ውስጥም በ1989 በማቴሪያል ሳይንስ ባደረገችው ሰፊ ምርምር ያገኘችው የሃርዲ አዋርድ፣ በ2002 በፊውል ሴል ፈጠራዋ ያገኘችው የኬሚካል ፖይነር አዋርድ እንዲሁም በ2004 በሴራሚክ ሳይንስ ምርምሯ ያገኘቸው የዓለም አቀፍ የሴራሚክ ፕራይዝ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የእውቅና ሽልማቶቿ ናቸው፡፡

ምንጭ፡ ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 15 (ሙሉ መፅሐፉን በዚህ ሊንክ ያገኙታል=http://library.techin.gov.et/web/dl-site/stic-resources/-/document_library/Y9QR0tiVPdYe/view_file/4710001?_com_liferay_document_library_web_portlet_DLPortlet_INSTANCE_Y9QR0tiVPdYe_redirect=http%3A%2F%2Flibrary.techin.gov.et%2Fweb%2Fdl-site%2Fstic-resources%3Fp_p_id%3Dcom_liferay_document_library_web_portlet_DLPortlet_INSTANCE_Y9QR0tiVPdYe%26p_p_lifecycle%3D0%26p_p_state%3Dnormal%26p_p_mode%3Dview%26p_r_p_categoryId%3D672548)
የወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ
******************************************************************
የአሜሪካን የኬሚካል ሶሳቲ የሴቶችን ሸክም ለመቀነስ ሌት ተቀን እሰራን ነው ሲል ተደምጧል፡፡ ሴቶች ለዘመናት ወሊድ የመቆጣጠር ጣጣን ለብቻቸው ሲወጡት የነበረ ሲሆን ይህ ጤናቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ከመሆኑም ባሻገር አሁን አሁን የጡት ካንሰር እና የደም መርጋት ችግሮች በስፋት እየታየ በመሆኑ ለረዥም ጊዜ የሚወሰድ እርግዝና መከላከያ እንክብል ለጤና የሚመከር እድዳይሆን እያረው ነው፡፡

ምንም እንኳን ወንዶች ወሊድ ለመቆጣጠር እንዲችሉ ባንድ በኩል ኮንዶምን በሌላ በኩል ደግሞ vasectomyን(የዘር መተላለፊያ ቱቦን መዝጋት) ለዘመናት እንደ አማራጭ እየተወሰደ የነበረ ነገር ቢሆኑም ሁለቱም አስተማማኝ የወሊድ መቆጣጠሪያ አይደሉም ሲሉ የአሜሪካን የኬሚካ ሶሳይቲ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡

ኮንዶም በበኩሉ ሊቀደድ እና እክል ሊገጥመው የሚችል በመሆኑ እና በሌሎች አንዳንድ ምክኒያች ተመራጭ ማይሆንበት በርካታ ምክኒያት አለ ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል የዘር ቱቦን ማቋረጥ ደግሞ ዘላለማዊ የሆነ እና መመለሻ የሌለው በመሆኑ ከባድ ውሳኔን የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ልክ ሴቶች እንደሚጠቀሙት ዓይነት ባለብዙ አማራጭ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ያሉ በርካታ የወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ሊበጁ ይገባል የሚሉ ድምጾች እየተስተጋቡ ነው፡፡ እንደ የአሜሪካን የኬሚካል ሶሳይቲ ያሉ የምርምር ተቋማትም ሌት ተቀን ይህንን እውን ለመድረግ እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በተደጋጋሚም በተለያየ መልኩ ለወንዶች የሚሆን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች እየሞከሩ ያሉ ሲሆን በቅርቡም የኬሚካል ድርብርቦሽን በመስራት እና በማህጸን ውስጥ ግርዶሽ በመፍጠር እርግዝና እንዳይፈጠር ሊረዳ የሚችል አዲስ ግኝትን ለማጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቶኛል ያለው የአሜሪካን የኬሚካ ሶሳይቲ ተመራማሪ ቡድን አየሩን ተቆጣጥሮታል፡፡

ይሁንና በሌላ በኩል የወሊድ መቆጣጠሪያ በራሱ ችግር ያለበት እና ተጠያቂነት የጎደለው አብዮት ነው የሚሉ ሳይንቲስቶች እየተደመጡ ነው፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪያ የማይታወቅ አብዮትን በሴቶች ሰውነት ውስጥ የፈጠረ ሲሆን በተለያየ መንገድ ጤናቸውን አደጋ ውስጥ እየከከተ ያለ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

የወሊድ መቆጣጠሪያ የሴቶችን ጤና እየጎዳ ባለበት ሁኔታ መልሶ ወንዶችንም የገፈቱ ተቃማሽ ማድረግ መፍትሄ አይሆንም ያሉ ሲሆን ያልተገባ ጾታዊ ግንኙነቶችን መቀነስ እና ትዳርን ማበረታታት የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ምክር ሰጥተዋል አክለውም በአሜሪካን በትዳር ውስጥ ካሉ ይልቅ በትዳር ውስጥ ያልሆኑ ሴቶች 90 በመቶ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚወስዱ በመሆኑ ሰዎች እንዲህ ያለ ያልተገባ የጾታዊ ግንኙነቶችን መግታት ቢችሉ ከወሊድ መቆጣጠሪያ ጋር ያለ የጎንዮሽ ጉዳትን ማስቀረት ይቻላል ብለዋል፡፡
ምንጭ፡- Science daily and Guttmacher Institute
ሳይሞቱ መሞት
*****************************************************************
ድካም ሲደጋገምቦት እና ማረፍ ሲያሰኞ ምናለ ለአንድ ሳምንት ያህል ለጥ ባልኩ አልያም ደግሞ ምናለ ምግቡም መጠጡም ቀርቶብኝ ለተከታታይ ቀናት በተኛሁ ብለው ያውቃሉ? እንግዲያውስ ከወደ ኮሎቢያ አከባቢ ስለተከሰተው ነገር ሹክ እንበሎት የ17 ዓመቷ ታዳጊ ከቀናት እና ከሳምንታትም አልፋ ለወራት ሳትነቃ ለጥ እንዳለች ናት፡፡

ሻሪክ ቶቫር ትባላለች ከሚሊዮኖች ቢያንስ 5 ሰዎች ብቻ ሊጠቁበት ይችላሉ ተብሎ በሚታወቀው Kleine-Levin syndrome ወይንም የተኛችው ቆንጆ ሲንድረም ተጠቅታለች፡፡ ምናልባትም እንደ National Organization for Rare Disorders ገለጻ ከሆነ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ከተኛችው ቆንጆ ታሪክ የሚለዩት በሆነ ጊዜ መሀል ላይ እየተነሱ ሽንት ቤት ሊጠቀሙ አልያም ሊመገቡ ይችላሉ፡፡

በታሪክ በዚህ በሽታ ተጠቅተው የሚያውቁ 500 ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የህክምና መዛግብቶች የሚያስረዱ ሲሆን ሃኪም ቤት ያልደረሱ እና ያልታወቁ ሊኖሩ እንደሚችል ይጠረጠራል፡፡

ይህ ሲንድረም ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ላይ የሚበዛ ቢሆንም በተለያየ እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴቶች ላይም አልፎ አልፎ ታይቷል፡፡ የታቮር እናት እንዳስረዱት ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ታቮር ይህ ነገር ያጋጠማት የ2ዓመት ህጻን ልጅ እያለች ሲሆን ለተከታታይ 2 ወራት ተኝታለች፡፡ በተኛችበት ወቅትም እንዳትጎዳ በማለት በየሁለት ሰዓት እየጠበቁ ይመግቧት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ተጠቂዎቹ ከተኙበት ሲነቁ አደገኛ ውዝግብ ውስጥ የሚገቡ ሲሆን መብራት እና ድምፅ እንደሚረብሻቸው ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ሙሉ ለሙሉ አቅም ማጣት እና ስሜት አልባ መሆን ይስተዋልባቸዋል፡፡ በሚነቁበት ሰዓት ትውስታቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚያጡ ሲሆን ታቮር የእናቷን ፊት እንኳን መለየት አልቻለችም ነበር፡፡

ሀኪሞች እንደሚሉት ከሆነ ይህ ሃይፖታለመስ የተሰኘው የአዕምሮ ክፍል መጎዳት ውጤት ነው ያሉ ሲሆን ይህ የአዕምሮ ክፍል እንቅልፋችንን የሚቆጣጠረው ክፍል ነው፡፡
ምንጭ፡Live Science
አበባ እስክትሆን ድረስ ዘር ነህ
****************************************************************
"ማንም ሁን ፤የትም ሁን፤ በየትኛው እድሜ ክልል ውስጥም ተገኝ አንተ ሁሌም የተግዳሮት ሰለባ ነህ " ሲሉ የሳይኮሎጂው ታለቅ ሰው ፕሮፌሰር በርን በርንሰቴን የስነልቦና ምክራቸውን ጀምረዋል፡፡

የምትወደው ሰው ህይወት አደጋ ውስጥ እንደገባ ሰምተሃል፣ ከመስራቤትሽ ያልጠበቅሽው ደብዳቤ ደርሶሻል፣ የምርመራ ውጤትህ አስደሳች ዜና ይዞ አልመጣም፣ ይዘህ መምጣት የሚኖርብህን ሰነድ ረስተሃል ፣ትራንስፖርት አጥተህ ተሰቃይተሃል ወይንም ሌላ ብዙ እንዲሆን ማትፈልገው ነገር እንዲሆን ተገደሃል እናም እንዲህ ያለው ነገር በየስንት ጊዜው ሂወትህ ውስጥ የሚከሰት ይመስልሃል? ብትባል መልሱ ሁሌም በየቀኑ የሚለው እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች ሁሌም አብረውህ ያሉ ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው ምናልባትም ተጋፍጠሃቸው እያሸነፍክ መሻገር አልያም እያየሃቸው ወንዙ ዳር ተገትሮ መቅረት የግል ምርጫህ እና ውሳኔ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተግዳሮቶች የቀን ተቀን ፈተናዎችህ ናቸው፡፡
ምናልባትም የህይወት ዓለማ ምንድነው ብለህ ጠይቀህ ታውቅ ይሆን? የህይወት ዓለማ ደስታ፣ ስኬት አልያም እርካታ እና የመሳሰሉትን በጎ ምኞቶች እንደሆኑ የሚዘረዝሩ የተለያዩ ሰዎች ይኖራሉ ለእኔ ግን ይላሉ ፕሮፌሰሩ "የህይወትህ ዓለማ በየቀኑ የሚገጥሙህን ፈተናዎች ማለፍ ነው፡፡" መሆን የምትፈልገው ምንም ይሁን ፤ መድረስ የምታልመውም የትም ይሁን ፊት ለፊትህ ሁሌም ፈተና አለ ያንን ማለፍ ካልቻልክ የትም መድረስ አትችልም፡፡

ህይወት ታላቁን አንተነትህን ትሆን ዘንድ የተሰጠችህ ፈተና ናት!
እቤትህ ውስጥ አበባ ለመትከል እና ለማሳደግ አስበህ ከሆነ እንኳን በቀላሉ ሊሆን የሚችል እንዳልሆነ ልብ ማለት አለብህ ዘር ከማምጣት አንስቶ ቦታ ማዘጋጀት ፣ውሃ ማጠጣት፣ በየቀኑ መንከባከብ እና አንዳንዴም ከዚህ ሁላ ድካም በኋላ የሚደርቅ ካለ ተስፋ ሳይቆርጡ ቀሪውን በህይወት ማቆየት የራሱ የሆነ ፈተና ነው፡፡

አንተ ውስጥ ያንተን ሙሉ ምስል የያዘ ዘር አለ ፤ ይህንን ዘር ወደ አበባነት መቀየር ቀላል አይደለም በመንገዱ ላይ ቀላል ያልሆኑ ችግሮች ይገጥማሉ እነዚህን ችግሮች እየተጋፈጡ እና ከሁኔታው እየተማሩ ማለፍ ካልተቻለ እርከኑን መሻገር የሚቻል አይሆንም ይህ መንገድ ሙሉውን አበባነትህን እንድትተዋወቀው ይረዳሃል፡፡

አበባ አበባ ሁኖ ለመውጣት በብዙ ነገሮች ውስጥ ያልፋል የትናንት ዘርነቱን አይቶም ዛሬ እንዲህ ያለ መልክ ይኖረዋል ብሎ የሚገምት አይኖርም ፤ነገር ግን አበባ ስሩን ከመሬት ውስጥ በመስደድ እና ለራሱ የማይነቃነቅ መሰረትን በመያዝ ከላይ ደገሞ ርቀቷ ሳይገድበው እና እራሱን ዝቅ አድርጎ ሳይመለከት ከፀሃይ ማግኘት የሚኖርበትን ሁሉ ለማግኘት በመጣር አበባነቱን ያውጃል፡፡

ስለዚህ እኛም በዚህ ምድር ላይ በሚኖረን ቆይታ የራሳችንን ቦታ መፈለግ ይኖርብናል በዚህ ውስጥ አካላዊ እና ስነልቦናዊ የሆኑ ፈተናዎች የሚገጥሙን መሆኑ እሙን ቢሆንም ችግሮቻችን የማስቀረት ስልጣን የለንም፡፡ እኛ ችግሮቻችን ላይ ያለን ስልጣን እንዴት አድርገን እንደምንጋጠማቸው እና እነርሱን እንዴት እንደምናያቸው መወሰን ላይ ነው፡፡

ደብርት እና አዘቅጥ ውስጥ ከተውን እንዲሄዱ እንፈቅድላቸዋልን ወይስ ተምረንባቸውና አሸንፈናቸው ጉዞዋችንን እንቀጥላለን? ችግርን በትክክለኛው ሰዓት እና በትክክለኛው መንገድ መጋፈጥ ለትልቁ እኛነታችን ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በስተመጨረሻም ፕሮፌሰሩ እንዲህ ሲሉ አጠቃለዋል፡- ችግሮች ከጠላትነታቸው ይልቅ ጓደኝነታቸው ያመዝናል ከእነሱ ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ካሳመርን እና በትክክለኛው መንገድ ካስተናገድናቸው እኛ ውስጥ ያሉ እና የማይታዩ ድብቅ ችሎታዎቻችን ለማውጣት ዓይነተኛ አቅም አላቸው፡፡

ስለዚህ ህይወትን እንደፈተና እራሳችንን ደግሞ እንደ ዘር በመቁጠር ቆንጆውን አበባችንን በትዕግስት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡
ምንጭ፡ Psychology Today
የክላውድ ኮምፕዩቲንግ መሰረታዊነት
***********************************
በኮምፒውተር ኢንዳስትሪ ማርሽ ቀያሪ ሊባሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በየግዜው ይከሰታሉ። ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ምናልባት ከነዚህ ተጠቃሽ ቴክኖሎጂ ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል። ቃሉን በቀጥታ ወደ አማርኛ ከተረጎምነው ዳመና ላይ ማስላት ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ይህን ዓይነት ትርጉም መስጠት ከቴክኖሎጂው መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ጋር ይበልጥ ስለማይጎዳኝ የእንግሊዘኛውን ስያሜ መጠቀም የተሻለ ነው።

ክላውድ ኮምፒዩቲንግ በአጭሩ ሲገለጽ የኮምፒውተር አገልግሎቶች ማለትም ሰርቨሮች፣ የውሂብ (data) ማጠራቀምያዎች፣ አውታር መረቦች፣ ሶፍትዌሮች እና ሌሎች አገልግሎቶችን ኢንተርኔት (ክላውድ) ተጠቅሞ የሚያቀርብልን ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ማለት ውሂብ ወይም ዳታ የምናስቀምጠው በኮምፒተራችን ሳይሆን፤ ሌሎች ድርጅቶች በሚቆጣጠሩት ኮምፒውተር ነው ማለት ነው። ያስቀመጥነውን ውሂብ ማግኘት ስንፈልግ፣ ኢንተርኔትን ተጠቅመን ወደ የግላችን ኮምፒውተር መገልበጥ ወይም እዛው ክላውድ ላይ እያለ በማሰሻ (browser) ከፍተን ማየት እንችላለን። ይሁንና ክላውድ ኮምፒዩቲንግ ውሂብ ማከማቻ ጎተራዎች ብቻ አይደለም በአገልግሎት መልክ የሚያቀርብልን፤ ማንኛውም ኮምፒውተራችን ላይ ማድረግ የምንችለውን ተግባር በተሻለ ፍጥነት እና ዋጋ ማከናወን የሚይስችለን ቴክኖሎጂ ነው።

ከክላውድ ኮምፕዩቲንግ መምጣት በፊት፤ ሶፍትዌር የሚያመርቱ እና የሚጠቀሙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ብዙ ዓይነት ሶፍትዌር እና ሃርድዌር ገዝተው ይጠቀሙ ነበር። ይህ ውድና ውስብስብ ከመሆኑም በላይ፤ ለአጭር ግዜ ብቻ መጠቀም የምንፈልገውን ሃርድዌር ከመግዛት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ወደ ገበያ ለመግባት የሚፈልጉ ድርጅቶች ከጅምሩ ብዙ ወጪ ማውጣት ግድ ይላቸው ነበር። ድርጅቶች ከጅምሩ ምን ያክል የውሂብ ማጠራቀምያ (storage)፣ የማስያ ጉልበት (processing power) ወዘተ…. እንደሚያስፈልጋቸው በቀላሉ መገመት አይችሉም። ድርጅታቸው ከሚፈልገው በላይ ጉልበት ያላቸው ሃርድዌር ከገዙ ለአላስፈላጊ ወጪ ይጋለጣሉ፤ ካሳነሱት ደግሞ ሲስተማቸው ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራል። ይህንን ዓይነት ችግር ለመፍታት ክላውድ ኮምፒዩቲንግ እጅግ ወሳኝ ቴክኖሎጂ ነው።

እንደ አማዞን፤ ማይክሮሶፍት እና ጉግል የመሳሰሉ ድርጅቶች ብዙ ክፍተኛ አቅም ያላቸውን ኮምፒውተሮችን አዘጋጅተው ለድርጅቶች እና ግለሰቦች ያከራያሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው 100 ኮምፒተሮችን ተጠቅሞ ውስብስብ የሆነ የኮምፒውተር ሲሙሌሽን መስራት ቢፈልግ፤ 100 ኮምፒተሮችን መግዛት አይጠበቅበትም ማለት ነው። ከ አማዞን እነዛን ኮምፒተሮች ተከራይቶ ተገቢውን ሶፍትዌር ኮምፒተሮቹ ላይ በርቀት (ኢንተርኔት ተጠቅሞ) ይጭናል። የፈለገውን ስራ አከናውኖ የተገኘውን ውጤት ወደ ራሱ ኮምፒተር መውስድ ይችላል። ይህ ሰውዬ እንደዚህ በማድረጉ ብዙ ነገር አትርፏል። አንደኛ ስራው መጀመርያ እንዳሰበው በ 100 ኮምፒተሮች ብቻ የማይከናወን ከሆነ በቀላሉ ተጨማሪ ኮምፒተሮችን ማሰማራት ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ ሰውዬው ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ሲጠቀም የሚከፍለው ብር ልክ እንደ ውሃና ኤሌክትሪክ በተጠቀመበት መጠን በመሆኑ እነዛን 100 ኮምፒተሮች ለ አንድ ሰዓት ብቻ ከተጠቀመ የሚከፍለው በዛ ልክ ብቻ ነው። ይህም ክላውድ ኮምፕዩቲንግን እጅግ አስፈላጊ ከማድረጉም በተጨማሪ ተለጣጭ ወይም (elastic) ባህሪ ያለው ቴክኖሎጂ ያደርገዋል።

የክላውድ ኮምፒዊቲንግ ቀላል ምሳሌ ከፈለግን በሞባይላችን ውሂብ መጠባበቅያ (backup) ስናስቀምጥ፤ ኢሜል ስንጠቀም እና ሌሎች ነገሮችን ስናደርግ መረጃችን ያለምንም መጨናነቅ መቀመጣቸው የክላውድ አስፈላጊነትን በሚገባ ያሳዩናል። ስልካችን ቢጠፋም አስፈላጊውን ቅጽ በመሙላት የጠፉብንን ውሂቦች የምናገኘው በክላውድ የተነሳ ነው። ለምሳሌ ፌስቡክን ካየነው ሙሉ በሙሉ ክላውድ መሰረት ያደረገ አፕሊኬሽን በመሆኑ ኢንተርኔት እስካለን ድረስ ማንኛውንም ፌስቡክ ላይ ያደረግነውን እንቅስቃሴ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነን ማየት እንችላለን።
ምንጭ፡ AD. Information Technology እና tech viral
ፍሬያማ ምርት
*****
ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በረሃብ እየማቀቀ ይገኛል፡፡ ምናልባትም ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነን በቂ እህል ማምረት ብቻ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም፡፡ የማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የውሃ እጥረት እና ሰብልን የማሾር(Crop rotation) ልምድ አናሳ መሆን ይህ እውን እንዳሆን እንቅፋት ሆኗል፡፡
ሰብልን ማሾር፡- በአንድ ቦታ ላይ ለረዥም ጊዜ አንድ አይነት ሰብሎችን አለመዝራት እና በዙር በዙር የተለያዩ ሰብሎችን እየዘሩ የአፈሩን ደህንነት የማስጠበቅ ሂደት፡፡
ይህንን በተመለከተም የ Global Landscapes Initiative at the University of Minnesota ተመራማሪ እና ዳይሬክተር ፖል.ሲ ዌስት እና ባልደረቦቹ ሰፊ ጥናት በማካሄድ የዓለምን የምግብ ዋስትና ለመረጋገጥ ያስችላል ያሏቸውን 5 ዋና ነጥቦች በጥናት ፅሁፋቸው ውስጥ ያቀረቡ ሲሆን እኛ ለዛሬ 3ቱን እንካችሁ እያልን ቀሪዎቹን በሌላ ጊዜ የምናቀርባቸው ይናል፡፡
ፖል ለTreeHugger(ዌብሳይት) በሰጠው መግለጫ ላይም እንዳለው ከሆነ በጥናታችን ውስጥ የጠቀስናቸው ጉዳዮች ላይ አፅንዖት ተሰጥቶ ቢሰራበት 3ቢሊዮበን የሚሆንን ህዝብ በስርዓቱ መመገብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ ከባቢውን አዎንታዊ በሆነ መንገድ የመለወጥ ትሩፋት አለው ብለዋል፡፡
1- የምርት ልዩነትን ማጥበብ
እንደ (World Wildlife Fund) ግምት ከሆነ በ2050 120 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ተፈጥሯዊ የመኖሪያ ቦታ ወደ እርሻ ቦታነት ይቀየራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዓለም ላይ ያሉ የእርሻ ቦታዎች ማምረት ከሚገባቸው እና ከሚችሉት በ50 ፐርሰንት ያነሰ እያመረቱ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ምንም ተጨማሪ የእርሻ መሬት ሳንጠቀም የእርሻ መሬቶች ማምረት የሚገባቸውን ያህል ማምረት የሚችሉበትን ሁኔታ ብናመቻች እና ጋፑን/ልዩነቱን ማጥበብ ከቻልን ተጨማሪ 850ሚሊዮን ህዝብ መመገብ ይችላሉ፡፡ ሰለዚህ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ልዩነቱን እንዴት እናጥብብ የሚለው ነው፡፡
2- ማዳበሪያዎችን በብቃት እና በትክክል መጠቀም
ምንም እንኳን እኛ እንደ TreeHugger አርቴፊሻል ማዳበሪያዎችን መጠቀምን ባናበረታታም አሁን ላይ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተጠቃሚነት አለ ፡፡ ይሁንና ይህ ጥናት ማዳበሪያን በተመለከተ ጥሩ ዜና ይዞ ብቅ ያለ ሲሆን እሱም ዓለም ስንዴ፣ሩዝ እና በቆሎ ለማምረት እየጠቀመች ያለችውን የናይትሮጂን እና የፎስፈረስ ማዳበሪያ መጠን ከ13 -29 ፐርሰንት ቀንሳም ቢሆን ከዚህ በፊት የምታመርተውን ያህል ማምረት ትችላለች ፡፡ በተጨማሪም የማዳበሪያ አጠቃቀም እውቀትን በማሳደግ መች እና እንዴት መጠቀም እንዳለብን ካወቅን ትርፋማ የመሆን እድላችን ሰፊ ይሆናል፡፡
3- አነስተኛ ውሃ የሚፈልጉ ምርቶች ላይ ማተኮር
በግብርና ዓለም ውስጥ ውሃ ትልቁ ተግዳሮት ነው፡፡ ይህንን ለመዋጋትም መስኖን መጠቀም እና እምብዛም ውሃ የማይሹ ምርቶችን ማበረታታት እንደ ዓይነተኛ አማራጭ መታየት አለበት ያሉ ሲሆን ለምሳሌ ያህል እንደ ሩዝ እና እንደ ስኳር ድንች ያሉ ምርቶች ከፍተኛ ውሃ የሚሹ ምርቶች በመሆናቸው ትልቅ እክል ይገጥማቸዋል፡፡
ይሁንና የምግብ ምርት የብዙ ነገር ተፅዕኖ የሚያርፍበት ስራ ነው፤ አንድ ገበሬ የሚያመርተው ገበያውን እና ባህሉን ተንተርሶ በመሆኑ በቀላሉ የሚያመርተውን ነገር መቀየር የሚችል አይደለም ይህ ደግሞ አነስተኛ ውሃ የሚሹ ምርቶችን ተመራጭ ላያደርጋቸው ይችላል ሲሉ ተግዳሮቱን ጠቆም አድርገው አልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- TreeHugger
የኢትዮጵያ የሳይንስ ሳምንት በመካሄድ ላይ ነው
##########################
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ለአራት ቀናት የሚቆይ የሳይንስ ሳምንት ከዛሬው ዕለተ አንስቶ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መካሄድ ጀምሯል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ህዳር 10 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ምክንያት በማድረግ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ይህ የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ የፈጠራ ወድድሮችና የአውደ ርዕይ ስነ ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ስነ ስርዓት ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የመጀመሪያ ደረጃ (7ኛ እና 8ኛ) ፣ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው በሚያቀርቡት የፈጠራ ፕሮጀክት የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ መምህራን እና ከተለያዩ ስቴም ማዕከላት የተወጣጡ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በኢንጂነሪንግ፣ ሮቦቲክስ እና ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ ፈጠራቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ውድድር በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ በተማሪዎች ብቻ ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች የሚቀርቡ ሲሆን የመምህራን እና የስቴም ማዕከለት ሲጨመር ደግሞ ከ187 በላይ ፕሮጀክቶች ለውድድር ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተዘጋጀው በዚህ የሳይንስ ሳምንት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ እንዳሉት የተዘጋጀው ይህ የውድድር መድረክ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የቀሰሙትን የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ችግሮችን ሊፈታ ወደሚችል ጠቃሚ ፈጠራ እንዲቀይሩ ከማገዙም ባለፈ በመጪው ጊዜ ለሚኖራቸው የስራ ክህሎት ጥሩ ልምድ እና መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው አንስተዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ የሚከበረው የሳይንስ ሳምንት “Open Scienece, Leaving No One Behined” በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያም በተለያዩ የፈጠራ ውድድሮች እና የአውደ ርዕይ ስነ ስርዓቶች ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚከበር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡