TechIn2
1.16K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችና የሚለቁት ከፍተኛ ሙቀት
==================
በሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተብለው የሚገነቡ ግድቦች ዋነኛ ከሚባሉት የታዳሽ ኃይል ምንጮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ታድያ እነዚህ ኃይል ማመንጫዎች ከብክለት የፀዳ ኃይል በማምረት የዓለም ሙቀት እንዳይጨምር የድርሻቸውን ቢወጡም ቅሉ በግድቦቹ የሚጠራቀመው ከፍተኛ መጠመን ያለው ውሃ ይህን ጥቅማቸውን የሚደመስስ ሙቀት እንደሚለቅ ተመራማሪዎች ገለፁ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በመላው ዓለም ከ3,700 በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በእቅድ አልያም ግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ታድያ እነዚህ የኃይል ማመንጫ ግድቦቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እንዲያስችላቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃን ከኮንክሪት ግርግዳቸው ጀርባ ማጠራቀም ሲኖርባቸው፤ ይህ የተጠራቀመ ውሃ ደግሞ ስፍራው ቀድሞ ግድብ ባልተገነባበት ጊዜ ከነበረው በላቀ ከፍተኛ የፀሐይ ኃይልን ይሰበስባል፡፡

ከኦስትሪያው ዩኒቨርሲቲ አፍ ኢንስብረክ የሆነው ጌኦርግ ዎልፋርት እና ሌሎች የሙያ አጋሮቹ በመላው ዓለም የሚገኙ 724 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣብያዎችን የመረመሩ ሲሆን በግኝታቸው መሰረትም የኃይል ማመንጫ ግድቦቹ ውስጥ የተጠራቀመው ውሃ በዙርያቸው ካለው አንፃር ጨለም ያሉና በዚህም ሳብያ የሚሰበስቡት የፀሐይ ኃይል ከፍ ያለ እንደሆነ ለማወቅ ችለዋል፡፡ የጥናት ቡድኑ ከእያንዳንዱ የውሃ ማጠራቀምያ ግድብ የተገኘውን ተጨማሪ ሙቀት እንዲሁም በካይ የኃይል ምንጮችን ከመጠቀም ይልቅ እነዚህ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን በመጠቀም መቀነስ የተቻለውን የሙቀት ልቀት አስልቷል፡፡ በውጤቱም ግማሽ ያህሉ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች በአራት ዓመታት ውስጥ የአየር ንብረት ጥቅምን እንደሚሰጡ ማወቅ ችለዋል፡፡ 19 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ይህን ዓይነት ጥቅም ለመስጠት 40 ዓመታትን መጠበቅ ሲኖርባቸው ሌሎች 12 በመቶዎቹ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች በበኩላቸው 80 ዓመታትን ቆይተው እንኳን ምንም አይነት የአየር ንብረት ጥቅም ለመስጠት እንዳልቻሉ ተረጋግጧል፡፡

አጥኚዎቹ በኤሌክትሪካ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ የብርሃን ማንፀባረቅን ከግምት ያስገቡ የንድፍ ለውጦች ይኖሩ ዘንድ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ምንጭ፤ Nature
ማርስ ላይ የሚነዱት እጅግ ዘመናዊ ጎማዎች ምድር ላይም ለገበያ ሊቀርቡ ነው
================
ዘ ስማርት የተሰኘው ጎማ አምራች ኩባንያ በህዋ ምርምር ላይ እየዋሉ ያሉት እጅግ የዘመኑ ጎማዎቹን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል፡፡ በናሳው የማርስ ሮቨርስ ተልዕኮ ላይ ያገለገሉት ጎማዎቹ እጅጉን ተለጣጭ የሆነው የኩባንያው ሼፕ ሚሞሪ ራዲያል ቴክኖሎጂ (SMART) የተገጠመላቸው ናቸው፡፡ ይህም በአንድ በኩል ጎማው እንዲለጠጥ ከማድረጉም ባሻገር የስማርት ሚሞሪ ሜታሉ በሚታጠፍበት ሰዓት ሞለኪውላዊ ቅርፁን እንዲቀይርና መልሶ ወደ ቀድሞ ቦታውም መመለስ እንዲችል ሆኖ የተሰራ ነው፡፡ በዚህም ሳብያ ምንም አይነት አየር ከጎማው አምልጦ የማይወጣና የማይተነፍስ ሲሆን ጥንካሬውም ልክ እንደ ታይታኒየም ነው፡፡

ምድራችን ላይ የዚህ አይነት ጎማዎች መኖር ልዩ ልዩ ጥቅሞችን እንደሚሰጥ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ምስሉ ላይ በምንመለከተው መልኩ የእነዚህ ጎማዎች በሳይክሎች ላይ መገጠም ከተለምዶአዊው ጎማ በላቀ ጉዞውን ምቹ የሚያደርጉም ብቻ ሳይሆን መሬቱን ይበልጥ ቆንጥጠው ስለሚይዙም የጉዞ ደህንነትን ያሻሽላሉ፡፡ ጎማዎቹ በማንኛውም የአየር ፀባይ ወቅት መሬቱን በተሻለ ቆንጥጦ ለመያዝ ይረዳቸቸው ዘንድም ፖሊዩረቴኒየም የተሰኙ ሴንቴቲክ ቁሶችን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ማለት ጎማዎቹ ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥማቸውና አንድም ጊዜ መቀየር ሳያስፈልጋቸው ሳይክሉ ማገልገል እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ የሚኖሩ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ጎማዎቹ ከባዱን የማርስ አየር ንብረት እና መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲቋቋሙ ተደርገው የተሰሩ በመሆኑም ነው እንዲህ በማይታመን ደረጃ ጠንካራ ለመሆን የበቁት፡፡

ሌላው ጎማዎቹን ለየት የሚያደርጋቸው ጉዳይ በናሳ የሚመረቱ መሆናቸው ነው፡፡ ከናሳ በተጨማሪ ድርጅቱ ከፎርድ የመኪና አምራች ኩባንያ ጋር ከሚሰራ አንድ ሌላ ድርጅት ጋርም አነስተኛ የኤሌክትሪክ ሳይክሎችን ለማምረት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ትብብር አማካኝነትም ሁለቱ ድርጅቶች ቀላልና ደህንነቱ የተጠየበቀ ማጓጓዣን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ አልመዋል፡፡

እነዚህ በህዋ ምርምር ውስጥ አልፈው የመጡት ጎማዎች ወደፊት በተለያየ መጠን ለሁሉም ተሽከርካሪ ተሰርተው ሲቀርቡ 250 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን ዓለም ዓቀፍ የጎማ ገበያ እንደሚቀይሩት ታምኖባቸዋል፡፡ ለአሁን ግን ለሳይክል ብቻ የሚውሉ ሲሆን እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ ገበያ ላይ እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፤ Tech Xplore
ማርን ያለ ንብ፤ ወተትን ያለ ላም ማዘጋጀት
=====================
እንደአለም አቀፉ የምግብና ግብርና ተቋም (FAO) መረጃ ከሆነ ባለፉት ጥቂት አመታት የስጋና የወተት ውጤቶች በአለማችን የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት ውስጥ 14.5 በመቶ እንደሚሸፍኑ አስታውቆ ነበር፡፡ እንዲሁም በከፍተኛ መጠን በአለማችን ላይ ጥቅም ላይ ከሚውለው የማር ምርት ጋር ተያይዞ ብዛት ያላቸው የንብ ዝርያዎች ከፍትኛ ጉዳት እንደሚደርስባቸው ይነገራል፡፡ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የስጋና የወተት ውጤቶች ከአትክልት በሚገኙ ምግቦች በተወሰነ መልኩ እየተተኩ በሚጡም የምርቶቹ ልዩ ባህርያት በአመጋገገብ ሂደት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ያደርጋቸዋል፡፡
በኢንግሊዟ ዋና ከተማ ለንደን መቀመጫውን ያደረገው ቤተር ዲያሪ የእነዚህን ምግቦች ተፈጥሮኣዊ ይዘት በጠበቀ መልኩ በሁሉም የሞሎኪውል ስርዓታቸው ከተፈጥሮአዊው ማር እና ወትት ጋር ምንም ልዩነት የሌላቸውን የማርና የወተት ውጤቶቸ በመስራት ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን፤ እጅግ ብዛት ያላቸውን ደቂቅ አከላትን በመጠቀም በፈርመንቴሽን ቴክኖሎጂ (fermentation) አማካኝነት የማር እና የወተት ምረቶች በማምርት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የሜታቦሊክ ሂደት በሆነው የፈርመንቴሽን ስርዓት ደቂቅ አካላትን (micro-organisms) በትክክለኛው መጠን በማቀነባበር እና ከእርሾ (yeast) ጋር በማጣጣም ሌሎች የመጠጥ እና የምግብ ውጤቶች እንደሚመረተው የማርና የወተት ወጤቶችም በዚህ መልኩ ማምርት እንደሚቻል ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡
የእንስሳት ተዋፅዖችን መሰረት አድርገው የሚሰሩ የምግብ እና የመጠጥ ውጤቶችን የማይመገቡ (vegans) ሰዎች ይህን በሞሎኪውል ስርዓታቸው ከተፈጥሮአዊው ምርቶች ጋር ምንም ልዩነት የሌላቸው bio-identical ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ ረዥም የምርምር ሂደት የሚስፈልጋቸው ቢሆንም ለአካባቢ ስነምህዳር ከሚሰጡት የጎላ አዎንታዊ አስተዋፅኦ አንፃር ተቀባይነተቻው እጅግ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት እንደ MeliBio እና Clara Foods ያሉ ድርጅቶችም በፈርመንቴሽን ቴክኖሎጂ የተቃኘ የማቀነባበሪያ ስርዓቶችን በመዘርጋት በተፈጥሮ ይዘታቸው ተመሳሳይ የሆኑ ምርቶችን በማዘጋጀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ MeliBio የተባለው የአሜሪካን ድርጅት ከንብ የሚገኘውን የማር ምርት በፈርመንቴሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት ለመተካት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን Clara Foods የተባላው ተቋም ደግሞ ተመሳሳይ ቴክኒኮችን በመጠቀም እስከ 2028 ድረስ ከእንቁላል የሚገኙትን ንጥር ነገሮች በራሱ በማምረት ለአለም ገበያ ለማቅርብ እንደሚሞክር አስታውቋል፡፡
ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የማር ምርት ለሌሎች የምርት ውጤቶች እንደግሪዲየንት ሆኖ ከማገልገሉ አንጻር እነዚህ ድርጅቶች ምርታቸውን ይዘው በሚቀርቡበት ወቅት ወደ ገበያው ለመግባት ቢዝነስ ቱ ቢዝነስ የተባለውን ሞዴል የሚከተሉ ይሆናል፡፡ ይህም በቀጥታ ምርታቸውን ወደተጠቃሚው ከማድረስ ይለቅ የምግብ፣ የመጠጥ፣ ኮስሞቲክ እና የመድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ በመስራት ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማስገባት እቅድ ይዘዋል፡፡ የ MeliBio መስራች ሚስተር ማንዲች እንደሚሉት በአሜሪካ ከሚገኙ 15 ኩባንያዎች ጋር ምርታችንን ለማቅርብ የተስማማን በመሆኑ በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ወደገበያ ለመቅረብ አቅድ አለን ብለዋል፡፡ BBC
ፌስቡክ ተከሰሰ
========
መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረው ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ የተባለ ተቋም ተጠቃሚዎችን ከጥላቻ ንግግር መጠበቅ አልቻለም በሚል ፌስቡክ ላይ ክስ መስርቷል፡፡ ተቋሙ ፌስቡክን “በአሳሳች የንግድ አካሄዱ” ምክንያት ነው በፍርድ ቤት እንደሚከሰው የተናገረው፡፡ ድርጅቱ የማህበራዊ ሚዲያው በገፁ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ንግግር እና የተሳሳተ መረጃ በስፋት እንዲተላለፍበት ፈቅዷል ሲልም ወንጅሎታል፡፡
እንደ ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ አነጋገር ምንም እንኳን ፌስቡክ ደህንነቱ የተጠበቀና ከስህተት የፀዳ አገልግሎት ለማቅረብ ቃል ቢገባም በጥላቻ የተሞሉ ፅሁፎች እና አሳሳች መረጃዎች በገፁ ላይ በስፋት ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡ ክሱ ፈረንሳይ ውስጥ ያለውን ስራ የሚያከናውንባቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት ፌስቡክ ፈረንሳይ እና ፌስቡክ አየርላንድ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ክሱ በተለይም በገፁ ተፖስተው የነበሩት በፈረንሳዩ የሻርሊ ሄብዶ መፅሔት ጋዜጠኞች ላይ የተቃጣው የግድያ ዛቻ እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ላይ አተኩሮ በተሰራውና ሀሰተኛ መረጃን በመያዝ በሚከሰሰው ሆልድ አፕ የተሰኘ ፊልም ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በፈረንሳይ ሕግ መሰረት አሳሳች የሆኑ የንግድ ተግባራትን ያከናወኑ ድርጅቶች 10 በመቶ የሚሆነው ዓመታዊ ገቢያቸውን በቅጣት መልክ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ፌስቡክ በመላው ዓለም የሚገለገልበት የአጠቃቀም ደንቦቹ ተመሳሳይ እንደመሆናቸው መጠንም የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ዓለም አቀፍ ተፅዕንዖ ሊኖረው እንደሚችልና ሌሎች ሀገራትም ይህን በአርዓያነት ወስደው ተመሳሳይ ክሶችን ሊመሰርቱ እንደሚችሉ ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ ተናግሯል፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህ ታላላቆቹ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተደጋጋሚ የሕግ እርምጃዎች በሀገሪቱ እያጋጠሟቸው ይገኛል፡፡ ከሳምንታት በፊትም 14 የሴት መብት ተሟጋቾች በእርሱ ንብረትነት የሚተዳደረው ኢንስታግራም አንዳንድ ፖስቶቻችንን ከገፁ ላይ አንስቶብናል፤ ሌሎች ተጠቃሚዎችም እንዲተናኮሉን ፈቅዷል በሚል ፌስቡክ ላይ ክስ መስርተውበት ነበር፡፡ ሌላኛው ግዘፍ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋም ትዊተርም በሀገሪቱ የተለያያዩ ክሶች ተመስርቶበት ይገኛል፡፡
ምንጭ፤ Tech Xplore
ባለቀለበቷ ኔፕቱን (Neptune)
==================
ፕላኔት ኔፕቱን ከፀሀይ በ 4,509,300,000 ኪሎሜትሮች ርቃ መገኘቱዋ ከምድር ላይ ሆነን ማየት እንዳንችል አድርጎናል። የጥንት ህዝቦችም ማጉያ መሳሪያ ስላልነበራቸው ሊያዩዋት አልቻሉም ነበር። እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ ሴፕቴምበር 23, 1846 ኡርቤን ሊ ቬርየር እና ጆሀን ጋሊ በተባሉ ተመራማሪዎች የመጉላት አቅሙ ከፍተኛ በሆነ ቴሌስኮፕ ለመጀመሪያ ግዜ ታየች። ፕላኔት መሆኑዋን ለማረጋገጥ ሳይንቲስቶቹ ብዙ የሂሳብ ቀመር ማውጣት ነበረባቸው። በቅደም ተከተል ከዩራኑስ ቀጥሎ ከፀሀይ ደግሞ በ 8ኛ ደረጃ ርቃ ትገኛለች። ኔፕቱን ክብደቱዋ የምድራችንን 17.5 እጥፍ ይሆናል። የምድር ወገቡዋ ደግሞ 49,528ኪ.ሜ ይረዝማል። በፀሀይ ዙሪያ 1 ዙር ለማጠናቀቅ 60,190,03 ቀናት ወይንም 164 አመታት ከ 79 ቀናት ይፈጅባታል። በራሱዋ ዛቢያ ላይ ደግሞ 1 ዙር ለመዞር 17 ሰአታት ብቻ ይፈጅባታል። የቅዝቃዜ መጠኑዋ ከዜሮ በታች በአማካኝ -201 ዲግሪ ሴልሽየስ ይደርሳል።
ኔፕቱን እንደሌሎቹ አብዛኞቹ ፕላኔቶች የተሰራችው ከ ሀይድሮጅን ከሂልየም እና ሜቴን ከተባሉ ጋዞች ነው። ሜቴን ጋዝ በተፈጥሮው ቀይ ቀለም ውጦ የምስቀረት ባህሪይ አለው፤ ከፀሀይ በመጠኑ ፕላኔቱዋ ላይ የሚያርፉትን ጨረሮች ከውስጣቸው የሚገኘውን ቀይ ቀለም ውጦ ስለሚያስቀረው ፕላኔቱዋ ላይ ጎልቶ የሚታየው ሰማያዊ ቀለም ነው፤ ስለዚህም ፕላኔቱዋ ደማቅ ሰማያዊ ቀለም አላት። ኔፕቱን ልክ እንደ ሳተርን እና ዩራኑስ ፕላኔቶች ኔፕቱንም በዙሪያዋ ቀለበቶች ይገኛሉ። 5 የሚደርሱት እነዚህ ቀለበቶች የተሰሩት ከ አዋራ፣ከበረዶ ፍርከስካሽ እና ከትናንሽ አለቶች ነው።
ኔፕቱን በአጠቃላይ 14 ጨረቃዎች/ሳተላይቶች አሉዋት። ከነዚህ ውስጥ ታዋቂ የሆነው ትራይቶን የተባለው ጨረቃዋ ነው። ይህ ጨረቃ በብዛት የተሰራው ከ ናይትሮጅን (Nitrogen) ንጥረ ነገር ሲሆን በተጨማሪም የበረዶ አለቶች እና ፍርክስካሽ አለቶች ይዙዋል። ከዜሮ በታች -240ሴልሽየስ ቅዝቃዜን በማስተናገድ የስርአተ ፀሀያችን እጅግ ቀዝቃዛ ጨረቃ በመሆን ቀዳሚ ደረጃን ይዞዋል። እስከዛሬ ኔፕቱንን የጎበኘቻት መንኮራኩር ቮዬጀር 2 ስትሆን ይህች መንኮራኩር እ.ኤ.አ በ 1989 ፕላኔቱዋን ስትጎበኛት በህዋ ሳይንስ እስካሁን ድረስ እጅግ አስደናቂ የሆነውን ፎቶ ለማንሳት ችላ ነበር።
ምንጭ፡ Airtable universe እና E.As
የመጠጥ ውሃ ችግርን እንደሚፈታ የተነገረለት አዲስ የቆሻሻ ውሃ ማጣርያ ቴክኖሎጂ
=========================
ሶላር ስቲል ተብሎ የሚጠራው መሳርያ የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ቆሻሻ ወይም ጨዋማ ውሃን እንዲተን ካደረገ በኋላ ንፁህና ለመጠጥ ወደመሆን የሚያሸጋግር ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሆኖም መሳርያው በመጠኑ ግዙፍና በዋጋ ረገድም ወደድ ከማለቱ ባሻገር ለአነስተኛ ቤተሰብ የሚበቃን ውሃ ብቻ የሚሰጥ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ታድያ አጥኚዎች የትነት ሂቱን በማፋጠን ለአንድ ሙሉ ቤተሰብ የሚበቃ የመጠጥ ውሃን መስጠት የሚያስችል አዲስ ቁስ ማበልፀግ ችለዋል፡፡ ቴክኖሎጂው ረከስ ብሎ መቅረብ የሚችል ከሆነም በመላው ዓለም ድህነት ውስጥ ለሚገኙት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ንፁህ እና ጤንነቱ የተጠበቀ ውሃን ማቅረብ ይችላል፡፡
ባለንበት ዘመን በመላው ዓለም 783 ሚሊዮን ህዝብ ወይም ከ10 ሰዎች ውስጥ አንዱ የንፁህ ውሃ ተደራሽነት እንደሌለው የዩኒሴፍ መረጃ ያሳየናል፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ ራቅ ካለ ቦታ ውሃን ለማምጣት በየቀኑ በድምሩ 200 ሚሊዮን ሰዓታትን ያባክናል፡፡ ምንም እንኳን ቆሻሻ እና ጨዋማ ውሃዎችን አጣርተው የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም ውድ መሰረተ ልማት እና ከፍተኛ ኃይልን የሚጠይቁ መሆናቸው ለእነዚህ ህዝቦች አይቀመሴ አድርጓቸዋል፡፡
ታድያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አጥኚዎች ሶላር ስቲሎችን በማሻሻል ርካሽና ያልተወሳሰበ የቴክኖሎጂ አማራጭ አድርገው ለማቅረብ ሲጥሩ ነበር፡፡ ተለምዶአዊ ሶላር ስቲሎች በውሃ ተሞልተው በንፁህ መስታወት ወይም ፕላስቲክ ክዳን የተሸፈኑ ግዙፍ መሳርያዎች ናቸው፡፡ ጠጠር ያለው የታችኛው ክፍላቸው የፀሐይ ብርሃኑን በማስረፅ ውሃውን የሚያሞቅና ቆሻሻውን ወለሉ ላይ ትተው ወደላይ እንዲተኑ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የተነነው ውሃም ከመሰብሰቢያው በመግባት ወደ መጠጥ ውሃነት ይቀየራል፡፡ ሆኖም የፀሐይ ጨረሩ የተጠራቀመውን ውሃ ከማትነኑ በፊት ሙሉ በሙሉ ማሞቅ ስለሚጠበቅበት የሚሰጠው ንፁህ ውሃ መጠን አነስተኛ ነው፡፡ ገበያ ላይ የሚገኙት መሳርያዎችን ብናይ በሰዓት በአንድ ሜትር ካሬ ላይ ከተጠራቀመ ውሃ (L/h/m2) ማውጣት የሚችሉት የመጠጥ ውሃ መጠን 0.3 ሊትር ብቻ ነው፡፡ መሳርያዎቹ እጅግ ጥሩ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ አድርገን ብናስብ እንኳን በዚህ የቦታ አቅም እና ሰዓት ውስጥ ከ1.6 ሊትር በላይ የማምረት አቅም የላቸውም፡፡ አንድ ሰው በአማካኝ 3 ሊትር ውሃ እንደሚያስፈልገው ከግምት ስናስገባ ደግሞ ለአንድ ቤተሰብ በቂ የሆነ ውሃን ያቀርቡ ዘንድ መሳርያወዎቹ 5 ካሬ ሜትር ላይ የተጠራቀመ ውሃን ይጠይቃሉ፡፡
በአሜሪካኑ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ በማቴሪያል ሳይንስ ተመራማሪነት የሚሰራው ጉዩዋ ዩ እና የስራ አጋሮቹ ይህ በተለምዶዎቹ ሶላር ስቲሎች ላይ የሚታይ ችግርን ይቀርፍ ዘንድ ሀይድሮጄል የተሰኙ ከባለ ሶስት እይታ ውሃ አስተላላፊ ድንጋዮች (Porous) የተወሰዱ ፖሊመሮችን በመጠቀም ውሃን መምጠጫ ስርዓትን ገንብተዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ ጄል መሳይ የሁለት ፖሊመሮች ጥምር ስፖንጅን ተጠቅመዋል፤ አንደኛው ፖሊቫይኖ አልኮል (PVA) የተሰኘ ውሃን አጣብቆ የሚይዝ ፖሊመር ሲሆን ከፀሐይ ትይዩ ሆኖ በውሃው ላይ የሚቀመጠው ሌላኛው ፖሊመር ደግሞ ብርሃንን የሚሰበስብበው ፖሊፓይሮል (PPy) የተሰኘ ፖሊመር ነው፡፡ በጄሉ ውስጥ ያለው ውሃ ከፖሊቫይኖ አልኮሉ ጋር በመጣበቅ ሀይድሮጅን ቦንድ የተባሉ የኬሚካል ጥምረቶችን ይፈጥራል፡፡ ሆኖም የውሃ ሞለኪዎሎቹ ከፖሊቫይኖ አልኮሉ ጋር ባላቸው ልክ እርስ በእርሳቸው መጣበቅ ስለማይችሉ በፍጥነት እንዲተኑ ይገደዳሉ፡፡ ከተነኑ በኋላም በቦታቸው ሎሎች የውሃ ሞለኪውሎችን ወድያው ወዲያው የሚተኩ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት አዲሱ የሶላር ስቲል ከቀድሞዎቹ እጅጉን በላቀ ደረጃ በሰዓት በአንድ ሜትር ካሬ ላይ ከተጠራቀመ ንፁህ ያልሆነ ውሃ 3.2 ሊትር ንፁህ ውሃን ማምረት ይችላል፡፡
አሁን ላይ የጥናት ቡድኑ ውሃን በከፍተኛ ደረጃ የሚስበውን ካይቶሳን የተሰኘ ፖሊመርን በሦስተኝነት በመጨመር ይበልጥ የተሻለ ሀይድሮጄልን መፍጠር ችሏል፡፡ ይህም ከቴክኖሎጂው የሚገኘውን የንፁህ ውሃ መጠን ወደ 3.6 ሊትር የሚያሳድገው ነው፡፡
በየቀኑ እስከ 30 ሊትር ንፁህ የመጠጥ ውሃን መስጠት እንደሚችል የተነገረለት ቴክኖሎጂው በሀይድሮጄሉ ውስጥ የተጠቀማቸው ሦስቱም ፖሊመሮች ርካሽ ከመሆናቸው አንፃር ጠንካራ ሆነው ከተገኙ ንፁህ የመጠጥ ውሃን አጥብቀው ለሚሹ ሁሉ መድህን ሊሆን እንደሚችል በሌሎች ተመራማሪዎች ተመስክሮለታል፡፡
ምንጭ፤ Science
በምሽት የምንሰማው አዋኪ የእንቁራሪት ድምፅ ምስጢር
=====================
ብዙ ግዜ ተደጋግሞ እንደተባለው የተፈጥሮ አሰራር እጅግ ሚስጥራዊ ነው፤ ስለአሰራርዋ ይበልጥ ለማወቅ በተሞከረ ቁጥር የያዘችው እውነታና ሃቅ እጅግ አስደማሚ ሆኖ ይገኛል፡፡ በቅርቡ Cell Press በተባለ አለም አቀፍ ጆርናል በእንቁራሪቶች አለም ስለሚካሄደው በድምፅ የመራባት እንቆቅልሽ እና ሴት እንቁራሪት እንዴት ሳምቧዋን ተጠቅማ የወንዶቹን ድምፅ መለየት እንደምትችል የሚያሳይ አስገራሚ ጥናት በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ወቶ ነበር፡፡
እንደተመራማሪዎች ማብራሪያ ከሆነ በእንቁራሪቶች አለም የድምፅ ሞገድ የመራቢያ ቁልፍ ነው፡፡ ብዙ ግዜ እንደምናስተውለው በምሽት የምንሰማው አዋኪ የእንቁራሪት ድመፅ ወንዱ እንቁራሪት ሴቷን ለመገናኘት ሲፈልግ የሚያወጣው ረዥም የድምፅ ሞገድ ነው፡፡ በመራቢያ ወቅት ሁሉም ወንድ እንቁራሪቶች ይህን አዋኪ ድምፅ ሴቷ ባለችበት ቦታ የሚያሰሙ ሲሆን ሴቷ እንቁራሪትም ሳምባዋን ተጠቅማ ተመሳሳይ ከሆኑት ድምፆች መካከል ዝርያዋን ለይታ ማውጣት ትችላለች፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል
ሴት እንቁራሪቶች በሳምባቸው በሚተነፍሱበት ወይም (inflate) በሚያደርጉበት ጊዜ ለድምፆቹ የሚኖራቸው የታንቡር ስሱነት (eardrum's sensitivity) ቀንሶ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ግን በተወሰነ የፍሪኪዌንሲ ክልል ውስጥ ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው የወንድ አንቁራሪት ድምፆችን በቀላሉ ለይቶ ለማውጣት ያስችላቸዋል፡፡ የሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ይህን ሴት እንቁራሪቶች በሳምባቸው የሚከውኑትን አስገራሚ ድርጊት spectral contrast enhancement ብለው የሚጠሩት ሲሆን፤ ይህም በተለያየ ሞገድ ከሚሰሙ አዋኪ ድምፆች ውስጥ የዝርያቸውን ስፔክተረም በመለየት የመረባት ሂደታቸውን የሚያስጀመር ተግባር ነው፡፡
በጥናቱ ላይ ዋና ተሳታፊ የነበሩት ዶክትር ኖርማን ሊ እንደሚስረዱት ይህ አስገራሚ የሴት እንቁራሪቶች የሳምባ ሚና ከውጭ የሚሰሙ አዋኪ ድምፆችን ለመከላከል እንደምንጠቀመው አላስፈላጊ የድምፅ ማስወገጃ (noise cancelling) መተግበሪያዎች ወይም ስርዓቶች ጋር ተመሳሳይንት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ተመራመሪዎች ይህን ጥናት ለማካሄድ ከዚህ በፊት በተሰሩ ተዛማጅ ምርምሮች እና በቤተ ሙከራ ውስጥ በተገበሩት ሌሰር ቫይብሮሜትሪ (laser vibrometry) በተሰኘ ሳይንሰዊ ቴክኒክ በመጠቀም ምርምሩን ማካሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፡ Sciencetimes
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ላይ ያተኮረው ወርክሾፕ
========================
በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት የሚከናወነው ይህ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ነገ ከጠዋቱ 3 ሰዓት አንስቶ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ ይደረጋል፡፡ በዋናነት ሴቶች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ላይ ያላቸው ተሳትፎ የሚቃኝበት ዝግጅቱ ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ ባለድርሻዎች እና የተቋሙ ተመራማሪዎች ታዳሚ የሚሆኑበት ይሆናል፡፡
በመድረኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሴል ኤንድ ሂዩማን ሳይኮሎጂ ምሁር እና የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ፆታ ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌር የዓለምፀሐይ መኮንን፣ የስቴም ፓወር ዋና ዳይሬክተር ቅድስት ገ/አምላክ እንዲሁም ከ100 በላይ የፈጠራ ስራዎችን ያበረከተው ቢኒያም መንግስቱ ሙያዊ ገለፃዎችን ያቀርቡበታል፡፡
በመድረኩ ልዩ ልዩ አንኳር ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡