TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
TECHIN weekly seminar
For this week Wubishet Begashaw will discuss “design and develop digital traffic light system based on PICMICRO CONTROLLER” and “inventing user-centered technology: the case of BIRR ETHIOPIC” will be presented by Samuel Zeber.
As always we are delighted to have you here tomorrow.
በሀገር ልጆች የተሰሩት የፈጠራ ስራዎች
===
ትናንት በተካሄደው የቴክ-ኢን ሳምንታዊ ሴሚናር ሁለት ተጋባዥ የፈጠራ ሰዎች ተገኝተው ስራቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ የዕለቱ የመጀመሪያ ቴክኖሎጂ ሆኖ የቀረበው የአቶ ሳሙኤል መለሰ ዓለም ስራ የሆነው ብዕር የኢትዮፒክ ነው፡፡ ይህ የሲስተም ሶፍትዌር የግዕዝ ፊደልን ተጠቅሞ መፃፍን ቀላልና ማንኛውም ሰው ያለ ምንም እንግሊዝኛ እውቀት ሊያደርገው በሚችለው መልኩ ከማቅረቡም በላይ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችንም በአማርኛ ለመፃፍ ያስችላል፡፡ ቴክኖሎጂው በሁሉም ኮምፒውተሮች ላይ እንደሚሰራና ሁሉም ሰው በቀላሉ ተምሮ ሊጠቀምበት እንደሚችል አቶ ሳሙኤል የተናገሩ ሲሆን ወደ ተግባር ከተገባበት በሀገር ምጣኔ ሐብት ላይም በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት ጥቅምን ይዞ እንደሚመጣ ገልፀዋል፡፡
በአቶ ውብሸት በጋሻው ተሰርቶ የቀረበው ሁለተኛው ቴክኖሎጂ የትራፊክ መብራት አሰራርን የሚያዘምን ስርዓት ነው፡፡ ስርዓቱ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ እና የትራፊክ ጫናውን በመመልከት የሚያስተናብር ነው፡፡ ይህም ሲባል የትራፊክ መብራቱ ብዙ ተሸከርካሪዎች ያሉበትን አቅጣጫ በሚገጠምለት ሴንሰር አማካኝነት ስለሚረዳ ከሌሎቹ በተሸለ ከዚያ አቅጣጫ ለሚመጡት ተሸከርካሪዎች ሰፋ ያለ የማለፊያ ጊዜን ይፈቅድላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ አቅጣጫ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ሲያልቁ ለአቅጣጫው የተመደበለት የመተላለፊያ ሰዓት ማለቁን ሳይጠብቅ ቀይ መብራትን በማብራት ከሌላ አቅጣጫ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች እንዲያልፉ ያደርጋል፡፡
ቴክኖሎጂው በትራፊክ መብራት ብቻ የማይገደብ እና ለሌሎቸም አገልግሎቶች መዋል የሚችል መሆኑን አቶ ውብሸት አብራርተዋል፡፡
ሁለቱም ባለሙያዎች ስለ ፈጠራቸው ከማብራራትም ባሻገር ከኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እና ታዳሚያን የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ስማርት ቴክኖሎጂ ምንድነው?
===================
ቴክኖሎጂ በተለያዩ የስራና እንቅስቃሴ ምህዳሮች ውስጥ መሰራጨትን ተከትሎ የስማርት ቴክኖሎጂ ባለንበት ዓለም ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል፡፡ አሁን አሁን ስማርት ቴክኖሎጂዎችን በብዙ ቁስ እና ስርዓቶች ላይ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ስማርት ስልክ፣ ስማርት ቴሌቪዥን፣ ስማርት ሰዓት….ብዙ የስማርት ማዕረግን ያንጠለጠሉ መሳርያዎችን በየዕለቱ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከነዚህ ባለፈ ግን ስማርት በጤና አጠባበቅ፣ የመንገድ አገልግሎት፣ ኃይል ስርጭትና ቁጥጥር፣ በመንግስታዊ አስተዳደር፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ መዝናኛና ቱሪዝም በቴክኖሎጂው ተገልጋይ ከሆኑ ስርዓቶች ውስጥ ይገኙበታል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እንኳን ብናይ የስማርት ቴክኖሎጂ የበይነ መረብ እና ሌሎች የግንኙነት መንገዶቻቸው እንዲሰፋ ከማድረጉም በተጨማሪ ስልኮቹ ከዚህ በፊት ተነጣጥለው ይገኙ የነበሩ አገልግሎቶች በአንድ አሰባስበው እንዲሰሩ አስችሎታል፡፡
የተጠቀሱት አገልግሎቶቹ እንዳሉ ሆኖ በስማርት ቴክኖሎጂ ምንነት ላይ ግን የጠራና ሁሉን ያማከለ ትርጓሜ መስጠት አዳጋች ነው፡፡ ለምሳሌ በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ እይታ ስማርት ማለት ማንኛውም አይነት ስርዓት ወይም መሳሪያ (Device) ሆኖ ነገሮችን የመረዳትና (ሴንስ የማድረግ) የመቆጣጠር ብቃት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ትርጓሜ አሰጣጥ ዕይታ ሁሉም የስማርት ቴክኖሎጂዎች ከባቢያቸውን ይረዳሉ፤ አገልግሎቶቻቸውንም የሚሰጡት በዚህ ምልከታ ላይ ተመስርተው በሚያሳልፉቸው ውሳኔና አመራር አማካኝነት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ስማርት አንፖሎች ብርሃንን የሚለቁት አካባቢያቸው መጨለም አለመጨለሙን በማረጋገጥና ያለውን የሰው ልጆች እንቅስቃሴ በመገምገም ነው፡፡
የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) ላይ ስንመጣ የስማርት ቴክኖሎጂ ምንነት በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ እይታ መሰረት ስማርት መሳሪያዎች ዙሪያቸውን ከመረዳትና ከመቆጣጠር ባሻገር ከሌሎች መሳሪያና ስርዓቶች እንዲሁም የግንኙነት መረቦች ጋር ትስስርን መፍጠር መቻል አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ችሎታቸው የስማርት መሳሪያዎችን ምንነት ትርጓሜ ከባቢያቸውን ወደሚያጤኑ፣ ከተጠቃሚዎቻቸው ጋር መስተጋብርን የሚፈጥሩ እና እርስ በእርሳቸው ግንኙነትን ወደሚመሰርቱ ግለሰባዊ ማሳሪያነት (Personal Device) ያሸጋግራቸዋል፡፡ ለዚህ በምሳሌነት በየተጠቃሚው ደጃፍ የሚተከሉትን ስማርት የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣሪዎች ብናይ እንኳን ቆጣሪዎቹ የተቀበሉትን እና በሰዓቱ እየተጠቀሙት ያለውን የኃይል መጠን መዝግበው ለኃይል አቅራቢ ተቋሙ ያሳወቃሉ፡፡ እንዲያደርጉት ሆነው ፕሮግራም ከተደረጉ ደግሞ የሚገባውን ኃይል የመቆጣጠርና የመመጠን ብቃትም ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስማርት ስልኮችን፣ ስማርት ማቀዝቀዣዎችን፣ ስማርት ምስለ መስኮቶችን እንዲሁም ሌሎች መሰል መሳሪያዎችን በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ምሳሌ ሆነው መቅረብ ይችላሉ፡፡
ምንጭ፡ ቴክ ሳይንስ፤ ቅፅ ፲፮
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀም በኢንስቲትዩታችን ጉብኝት አድርገዋል
=======================
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀም በላይ ከአመራር ቡድን አባላቶቻቸው ጋራ በመሆን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት ተቋሙ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ ከተነሳበት ወቅት አንስቶ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንቲትዩት ሆኖ ከቆመ በኋላም በተሰሩ ስራዎች እና ባጋጠሙ ተግዳቶች ዙርያ በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ ገለፃ ቀርቦላቸዋ፡፡ አቶ ሳንዶካን በገለፃቸው ወቅት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸው ዘንድ ጥያቄ ሲያቀርቡ ሚንስትሩ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩ በውይይቱ አስታውቀዋል፡፡
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆኑ ተቋመት አንዱ ሲሆን ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀምም ከቅርቡ ሹመታቸው ወዲህ መሰል ጉብኝትን ወደ ኢንስቲትዩቱ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
የኮሮና ቫይረስ እና መልስ ሊሰጣቸው የሚገቡት ጉዳዮች
*******************************
የኮሮና ቫይረስ ወይም በይፋዊ ስሙ COVID-19 ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሌሎች የአለማችን ክፍሎች እስከተዳረሰበት የአጭር ወራት ጊዜ ውስጥ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ብዙዎችን ሲያነታርኩ እና ሲያከራክሩ የቆዩ ጉዳዮችም ሲሰሙ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም ቫይረሱ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ምልክቶችን በትክክል ለመመልከት ምን ያህል ቀን ይፈጃል የሚለው ጉዳይ እና ምልክቶችስ ከመታየታቸው በፊት ቫይረሱ ወደሌሎች የመተላለፍ እድሉ ምንያህል ነው የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ተገቢ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ተመራማሪዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ከስንት ቀናት በኋላ ምልክቶችን ማሳየት እንደሚጀመር ለመረዳት ሰፊ ጥናት ሲያደርጉ እንደነበር በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ይህ incubation period of a virus በመባል የሚታወቀው ፅንሰ ሃሳብ የትኛውም ቫይረስ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ምልክቶችን ለማሳየት የሚወስድበትን የጊዜ መጠን የሚያሳይ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜም እንደቫይረሱ ዓይነት እና እንደተጠቃው ግለሰብ የአቅም ሁኔታ የተለያየ ውጤት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
ታዲያ SARS-CoV-2 የተሰኘው የቫይረስ በሽታ ሰዎችን ካጠቃ ወይም infected ካደረገ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምልክቶችን በትክክል ማሳየት እንደሚጀምር ለማወቅ በተደረገ ሰፊ ጥናት ብዙዎችን ሊያስማማ የሚችል አዲስ ግኝት በጆንስ ሆፕኪነስ ዩኒቨርስቲ ይፋ ሆኗል፡፡ ጥናቱ የ SARS-CoV-2 ወይም የኮሮና ቫይረስ ኬዝ ያለባቸው 181 የቻይና ዜጎች ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰራ ሲሆን፤ በአማካኝም 97.5 በመቶ የሚሸፍኑት ተጠቂዎች 5.1 በሚሆን ቀናት ውስጥ ምልክቶቹ ሊታይባቸው እንደቻለ የምርምር ቡድኑ አስታውቋል፡፡ ይህም እስካሁን ሲደረግ የነበረውን የአስራ አራት ቀናት የለይቶ ማቆያ ጊዜ (quarantine period) ምክንያታዊ ቢያደርገውም የተቀረው 2.5 በመቶ የሚሸፍነው የቫይረሱ ተጠቂ ግን ሌሎች አከራካሪ ነጥቦች እንዲነሱ ምክንያት የሆነ ነው፡፡
በዚህ ስሌት መሰረት ጥናቱ የተደረገባቸው አብዛኞቹ (97.5%) የቫይረሱ ተጠቂዎች 11.5 በሚሆኑ ቀናት ውስጥ ዋና ዋናዎቹን የትኩሳት፣ የደረቅ ሳል እና የትንፋሽ መቆራረጥ ምልክቶች በየተራ ማሳየት የቻሉ ቢሆንም 2.5 በመቶ የሚሆኑት ግን ከ14 ቀን በላይ ምልክቶች ሳታይታይባቸው እንደቆየ የጥናት ቡድኑ የምርምር ውጤት ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ በሌላ አገላለፅ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡ 10,000 ሰዎች ቢኖሩ እና ቫይረሱ እንዳለባቸው ለማረጋጋጥ 14 ቀን ቢቆዩ፤ ከእነዚህ ውስጥ 101 የሚሆኑት በተገለሉባቸው 14 ቀናት ውስጥ ምንም ምልክት ሳይታይባቸው ከለይቶ ማቆያ ወይም (quarantine) ከወጡ በኋላ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡ ይህም እንደተመራማሪዎቹ ትንተና አሁን እየተሰራበት ያለው የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ጊዜ መቶ በመቶ ውጤታማ ያደርጋል የሚለውን መከራከሪያ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ በጥያቄ ለማንሳት እንደተሞከረው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ምልክቶቹን ከማሳየቱ በፊት ወደ ሌሎች ቫይረሱን የማስተላላፍ እድሉ ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ሌላው ትንታኔ የሚስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በዚህ ሃሳብ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን እና የሃገራት ኬዞችን የሚተነትኑ ባለሙያዎች እንደሚያነሱት ይህ ጉዳይ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው የኮሮና ቫይረስ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ስርጭት ትልቅ አስተዋፆኦ እንዳበረከተ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ፀሃፊዎች በትንታኔያቸው ላይ ለአብነት ያስቀመጡትን የማሳቹሴትስ ጉዳይ ለምሳሌ ብናነሳ በዚህ ግዛት ተመዝግበው የነበሩ 82 ኬዞች የስርጨት መነሻቸው በቫይረሱ የተጠቁና ምንም ምልክት ሳይታይባችው የቆዩ ጥቂት ግለሰቦች እንደነበሩ ከማስረጃ ጋር አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡ ይህ በአሜሪካ አንድ ግዛት የታየ ጉዳይ ቢሆንም በሌሎች ሃገራት የነበሩ ሁኔታዎችን ስንመለከት ቫይረሱ ከሚታሰበው በላይ የስርጭት መጡኑ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ሌሎች ያልተመለሱ ጥቄዎች እንዳሉ ሆነው ይህ ጉዳይም አስፈላጊውን ትኩረት እንዳለገኘ የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም እንደአጥኚዎቹ እና እንደተንታኞቹ መከራከሪያ ከሆነ ለእነዚህ ጉዳዮቹ የተሰጠውን ትኩረት ይበልጥ በማሳደግ የቀረቡ ጥናቶችን ከግምት ውስጥ ባማስገባት እና ትንተናዎችን በመመልከት የጤና መመሪያና ፖሊሲዎችን ከጉዳዮቹ ጋር አጣጥሞ ማስኬዱ ይበልጥ እንደሚበጅ ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
ምንጭ፡ https://edition.cnn.com/2020/03/14/
health/coronavirus-asymptomatic-spread/index.html እና https://bigthink.com/politics-current-affairs/coronavirus-incubation
አስቸኳይ ጥሪ ለፈጠራ ባለሙያዎች በሙሉ
=============================
የኢትዮጵያ ኢኖቬተርስ አሶሴሽን የኮሮና ቫይረስ (COVID -19) ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመግታት የሚያግዝ የፈጠራ ሐሳብ ያላችሁ ሁሉ ኑ በጋራ እንስራ ይላችኋል፡፡ የበለጠ መረጃ በደብዳቤው ላይ በተገለጽት አድራሻዎች የምታገኙ ይሆናል፡፡
COVID-19 የመግደል ምጣኔው ምን ይመስላል?
********************************
ኮቪድ-19 የሚል ስያሜ የተሰጠው ቻይና ውስጥ የተቀሰቀሰው ተላላፊ በሽታ እስካሁን ድረስ 182,000 ሰዎችን ሲያጠቃ 7,100 የሚሆኑትን ደግሞ ህይወታቸውን የነጠቀ ነው፡፡ ቫይረሱ ከአፍንጫ አንስቶ እስከ ሳምባ ያሉትን የመተንፈሻ አካላት የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ውስን ቀናት ከሚታየው ትኩሳት በማስከተል ደረቅ ሳል የሚኖረው ወረርሽኝ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ቫይረሱ ከሳምንት በኋላ የትንፋሽ ማጠርን እንዲሁ የሚያስከትል ሲሆን፤ በዚህም ሳቢያ አንዳንድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል በሀገሪቱ ተመዝግበው በነበሩ የኮሮናቫይረስ ኬዞች ተመርኩዞ በሚያወጣቸው የተለያዩ መረጃዎች መሰረት COVID-19 የከፋ በሚሆንበት ጊዜ እንደነ ኒሞኒያ፣ ሳርስና እና ሌሎች የውስጥ አካላትን ሥራ እንዲያቆሙ በማድረግ በጤናችን ላይ ችግር የሚፈጠሩ በሽታዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ መተንፈሻ አካላትን የሚያዳክም ሲሆን ሌሎች በሽታዎች ሲጨመሩበት ደግሞ ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ቫይረሱ በዕድሜ የገፉ እና እንደአስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም የመሳሰሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ይበልጥ በመጉዳት በህይወት የመቆየት እድላቸውን በእጅጉ ሊያጠበው እንደሚችል ቢገመትም ከነዚህ መረጃዎች ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተረጋገጠ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይነገራል።
ከታች በምስሉ እንደሚታየውም ቫይረሱ አጠቃላይ የሞት ምጣኔው እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ እና ተጨማሪ የጤና ችግር በተመዘገበባቸው ሰዎች ላይ አደገኛ በመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት በሚቻለው አቅም በመቆጣጠር የሞት መጠኑን መቀነስ እንደሚቻል ከማዕከሉ በወጣው መረጃ ማየት ይቻላል፡፡ ቫይረሱ በተለይም ከመተንፈሻ አካል ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸውን እና የካንስር በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ይበልጥ በመጉዳቱ እነዚህ ኬዞች ላይ ትኩረት በማድረግ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መሞከር ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካል ችግርን የሚያመጡ ተህዋሲያን ውስጥ የሚመደብ አንደመሆኑ መጠን በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት የሚያወጧቸው ጥቃቅን ጠብታዎች (droplets) በሽታው ከሰው ሰው እንዲተላለፍ ዋና ምክንያት በመሆናቸው፤ ስናስልና ስናስነጥስ አፍንጫና አፋችንን በሶፍት ወይም በክርናችን በመሸፈን፤ እጃችንን ሳንታጠብ ፊታችንን ባለመንካት እንዲሁም ከታመሙ ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ባለማድረግ በሽታውን በሚገባ መከላከል እንችላለን።
በቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የተሰራውን የምርምር ውጤት በዚህ ቻርት ይመልከቱ
ቢቢሲ
የዓለማችን ፈጣኑ ሱፐር ኮምፒውተር "Summit" የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለማቆም የሚያግዝ አዲስ መላ አግኝቷል
************************
ወቅታዊው የዓለማችን አደጋ COVID-19 የስርጭት መጠኑ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ የምርምር ተቋማትን በእጅጉ ያሳሳበ ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ በእነዚህ የምርምር ተቋማት የሚሰሩ ሳይንቲስቶች በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የሚያደርጉት የምርምር ስራ ቅልጥፍና የታከለበት ቢሆንም ከእነሱ ፍጥነት በላይ ቫይረሱ የሚሰራጭበት ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ብዙዎችን ያሳሳበ ነው፡፡
ይሁንና "Summit" ለተሰኘው ፈጣን ሱፐር ኮምፒውተር ክብር ይግባውና ምናልባት ከዚህ በኋላ ብዙ ወራቶችን ሊወሰድ የነበረው የተሳካ የምርምር ውጤት በዚሁ ኮምፒውተር የተነሳ ሊያጥር ችሏል፡፡ ሱፐር ኮምፒውተሩ በተገጠሙለት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ግብዓቶች አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ማስመሰያዎችን (simulations) በማንቀሳቀስ ቫይረሱ የሚያርፍባቸውን ተጠቂ ህዋሳት በመመርመር የትኞቹ የመድኃኒት ውህዶች (drug compounds) ቫይረሱን ማቆም እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ ነው፡፡ ሱፐር ኮምፒውተሩ ይህን ሰፊ ትንተና ሲያደርግ በጥቅሉ 77 የሚሆኑ ኬሚካሎችን ወይም የመድሃኒት ውህዶችን መለየት የቻለ ሲሆን በጥቅሉም ውጤታማ የሆነ የክትባት መድሃኒት ለመስራት በሚደረገው ጥረት ላይ መልካም ጅምር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ኦክ ሪጅ የተሰኘው ታዋቂ የምርምር ተቋም በአጋርነት የሰራው ይህ ጥናት በፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ በተሰራው የኮሮናቫይረስ spike protein መለያ ጥናት ላይ ተመርኩዞ የተከናወነ ሲሆን፤ ይኸውም ቫይረሱ ሰዎችን በሚያጠቃበት ጊዜ በሚያርፍባቸው ህዋሳት ላይ የሚፈጠረውን የመባዛት እና የመሰረጨት መጠን የሚጠቁም ነበር፡፡ ታዲያ ተመራማሪዎቹ ሱፐር ኮምፒውተሩን በመጠቀም እንደተረዱት የተጠቀሟቸው ብዛት ያለቸው ማስመሰያ ውህዶች በቫይረሱ spike protein ላይ በመጣበቅ ቫይረሱ በማረፊያ ህዋሳት ላይ የሚኖረውን ስርጭት መግታት እንደሚቻልና፤ ከዚህ ውስጥም ከ1 እስከ 77 የሚደርሱት የኬሚካል ውህዶች አስገራሚ ውጤት እንደነበራቸው ለመረዳት የቻሉበት ነው፡፡
በዚህ ፍሬያማ ጥናት ላይ ምርምሩን በበላይነት የመሩት የኦክ ሪጅ ብሄራዊ ላብራቶሪ ዳይሬክተር ጄርሚ ስሚዝ ግኝቱ ኮሮናቫይረስን ማከም የሚችል መድሃኒተ አገኘን ማለት ባይቻልም ክትባቱን ለመስረት በምናደርገው ጥረት ላይ የተሻለ እርምጃ የተራመድንበት ነው ብለዋል፡፡
የምርምር ስራውን ሲያቀላጥፍ የነበረው "Summit" ሱፐር ኮምፒውተር በ2019 በአሜሪካ የኢነርጂ ዲፓርትመንት እና በIBM አማካኘነት የተሰራ የዓለማችን ፈጣኑ ሱፐር ኮምፒውተር ሲሆን፤ በሰኮንድ 200 ኳድሪሊዮን (15 ዜሮዎችን የሚስከትል) ስሌቶችን ኮምፒውት በማድረግ መሰል ጥናቸን የሚያቀላጥፍ ወደር የማይገኝለት ቴከኖሎጂ ነው፡፡ ኮምፒውተሩ 200 petaflops አጠቃላይ አቅም ያለው በመሆኑ ፈጣን ከሚባሉት ላፕሎቶፖች አንድ ሚሊዮን እጠፍ ስራውን ማከናወን እንደሚችል ይነገራል፡፡
ለበለጠ https://edition.cnn.com/2020/03/19/us/fastest-supercomputer-coronavirus-scn-trnd/index.html
የኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሥርዓት በይፋ ስራ ጀመረ
========================
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭት ያለበትን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አዳዲስ መረጃዎች በየጊዜው ይፋ የሚያደርግ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት በማበልጸግ ለኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት አስረክቧል፡፡
ኤጀንሲው ያዘጋጀው “የኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሥርዓት” የበሽታው ምልክት የታዩባቸው ወይም ስጋት ያደረባቸው ዜጎች ጥቆማ የሚሰጡበት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የኮሮኖ ቫይረስ በሽታን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን አሳሳቢ ችግር በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን በቀጥታ እንዲመዘገቡ የሚያስችል መሆኑን የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በርክክቡ ጊዜ ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የመቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ህብረተሰቡ በኮቪድ-19 በሽታ ላይ ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድጉና ወቅታዊ መረጃዎችን የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር የበሽታው ምንነት፣ የበሽታው ምልክቶች፣ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎቹ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያቀርብ ነው ብለዋል፡፡
ፕላትፎርሙ ከችግሩ አንገብጋቢነት አንጻር ኤጀንሲው እንደ ተቋም ምን ማድረግ አለብኝ በሚል በአጭር ጊዜ ውስጥ የበለጸገ መሆኑን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ፕላትፎርሙ በአማረኛ እና በእንግሊዘኛ የቀረበ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች በሲስተሙ እንደሚካተትበት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ተናግራዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በመንግስት እየተወሰደ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት የመከላከል ሥራን ለማገዝ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅቶ ባቀረበው “የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሥርዓት” ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ለህብረተሰቡ በበሽታው ዙሪያ ወቅታዊ መረጃ እና አገልግሎት ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን አስተዋጽ ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትሯ ቫይረሱን ለመግታት ቴክኖሎጂው ጠቃሚ መሆኑ ባያጠያይቅም ውጤታማ መሆን የሚቻለው ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የበሽታው ምልክት የታዩባቸውም ሆነ ማንኛውንም ጥንቃቄ የሚጠይቁ ምክሮችን የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በፕላትፎርሙ የተቀመጠውን የነጻ የስልክ መስመር በመደወል መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ዜጎች በአቅራቢያቸው ስለሚገኙ ሆስፒታል፣ ፋርማሲ ወይም የፖሊስ ጣቢያ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥርአት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ወደ ፕላትፎርሙ ለመግባት ይህን ሊንክ መጫን ይችላሉ
http://www.etwisdom.gov.et/covid-19
ምንጭ፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ