TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የክላውድ ኮምፕዩቲንግ መሰረታዊነት
***********************************
በኮምፒውተር ኢንዳስትሪ ማርሽ ቀያሪ ሊባሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በየግዜው ይከሰታሉ። ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ምናልባት ከነዚህ ተጠቃሽ ቴክኖሎጂ ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል። ቃሉን በቀጥታ ወደ አማርኛ ከተረጎምነው ዳመና ላይ ማስላት ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ይህን ዓይነት ትርጉም መስጠት ከቴክኖሎጂው መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ጋር ይበልጥ ስለማይጎዳኝ የእንግሊዘኛውን ስያሜ መጠቀም የተሻለ ነው።

ክላውድ ኮምፒዩቲንግ በአጭሩ ሲገለጽ የኮምፒውተር አገልግሎቶች ማለትም ሰርቨሮች፣ የውሂብ (data) ማጠራቀምያዎች፣ አውታር መረቦች፣ ሶፍትዌሮች እና ሌሎች አገልግሎቶችን ኢንተርኔት (ክላውድ) ተጠቅሞ የሚያቀርብልን ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ማለት ውሂብ ወይም ዳታ የምናስቀምጠው በኮምፒተራችን ሳይሆን፤ ሌሎች ድርጅቶች በሚቆጣጠሩት ኮምፒውተር ነው ማለት ነው። ያስቀመጥነውን ውሂብ ማግኘት ስንፈልግ፣ ኢንተርኔትን ተጠቅመን ወደ የግላችን ኮምፒውተር መገልበጥ ወይም እዛው ክላውድ ላይ እያለ በማሰሻ (browser) ከፍተን ማየት እንችላለን። ይሁንና ክላውድ ኮምፒዩቲንግ ውሂብ ማከማቻ ጎተራዎች ብቻ አይደለም በአገልግሎት መልክ የሚያቀርብልን፤ ማንኛውም ኮምፒውተራችን ላይ ማድረግ የምንችለውን ተግባር በተሻለ ፍጥነት እና ዋጋ ማከናወን የሚይስችለን ቴክኖሎጂ ነው።

ከክላውድ ኮምፕዩቲንግ መምጣት በፊት፤ ሶፍትዌር የሚያመርቱ እና የሚጠቀሙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ብዙ ዓይነት ሶፍትዌር እና ሃርድዌር ገዝተው ይጠቀሙ ነበር። ይህ ውድና ውስብስብ ከመሆኑም በላይ፤ ለአጭር ግዜ ብቻ መጠቀም የምንፈልገውን ሃርድዌር ከመግዛት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ወደ ገበያ ለመግባት የሚፈልጉ ድርጅቶች ከጅምሩ ብዙ ወጪ ማውጣት ግድ ይላቸው ነበር። ድርጅቶች ከጅምሩ ምን ያክል የውሂብ ማጠራቀምያ (storage)፣ የማስያ ጉልበት (processing power) ወዘተ…. እንደሚያስፈልጋቸው በቀላሉ መገመት አይችሉም። ድርጅታቸው ከሚፈልገው በላይ ጉልበት ያላቸው ሃርድዌር ከገዙ ለአላስፈላጊ ወጪ ይጋለጣሉ፤ ካሳነሱት ደግሞ ሲስተማቸው ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራል። ይህንን ዓይነት ችግር ለመፍታት ክላውድ ኮምፒዩቲንግ እጅግ ወሳኝ ቴክኖሎጂ ነው።

እንደ አማዞን፤ ማይክሮሶፍት እና ጉግል የመሳሰሉ ድርጅቶች ብዙ ክፍተኛ አቅም ያላቸውን ኮምፒውተሮችን አዘጋጅተው ለድርጅቶች እና ግለሰቦች ያከራያሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው 100 ኮምፒተሮችን ተጠቅሞ ውስብስብ የሆነ የኮምፒውተር ሲሙሌሽን መስራት ቢፈልግ፤ 100 ኮምፒተሮችን መግዛት አይጠበቅበትም ማለት ነው። ከ አማዞን እነዛን ኮምፒተሮች ተከራይቶ ተገቢውን ሶፍትዌር ኮምፒተሮቹ ላይ በርቀት (ኢንተርኔት ተጠቅሞ) ይጭናል። የፈለገውን ስራ አከናውኖ የተገኘውን ውጤት ወደ ራሱ ኮምፒተር መውስድ ይችላል። ይህ ሰውዬ እንደዚህ በማድረጉ ብዙ ነገር አትርፏል። አንደኛ ስራው መጀመርያ እንዳሰበው በ 100 ኮምፒተሮች ብቻ የማይከናወን ከሆነ በቀላሉ ተጨማሪ ኮምፒተሮችን ማሰማራት ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ ሰውዬው ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ሲጠቀም የሚከፍለው ብር ልክ እንደ ውሃና ኤሌክትሪክ በተጠቀመበት መጠን በመሆኑ እነዛን 100 ኮምፒተሮች ለ አንድ ሰዓት ብቻ ከተጠቀመ የሚከፍለው በዛ ልክ ብቻ ነው። ይህም ክላውድ ኮምፕዩቲንግን እጅግ አስፈላጊ ከማድረጉም በተጨማሪ ተለጣጭ ወይም (elastic) ባህሪ ያለው ቴክኖሎጂ ያደርገዋል።

የክላውድ ኮምፒዊቲንግ ቀላል ምሳሌ ከፈለግን በሞባይላችን ውሂብ መጠባበቅያ (backup) ስናስቀምጥ፤ ኢሜል ስንጠቀም እና ሌሎች ነገሮችን ስናደርግ መረጃችን ያለምንም መጨናነቅ መቀመጣቸው የክላውድ አስፈላጊነትን በሚገባ ያሳዩናል። ስልካችን ቢጠፋም አስፈላጊውን ቅጽ በመሙላት የጠፉብንን ውሂቦች የምናገኘው በክላውድ የተነሳ ነው። ለምሳሌ ፌስቡክን ካየነው ሙሉ በሙሉ ክላውድ መሰረት ያደረገ አፕሊኬሽን በመሆኑ ኢንተርኔት እስካለን ድረስ ማንኛውንም ፌስቡክ ላይ ያደረግነውን እንቅስቃሴ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነን ማየት እንችላለን።
ምንጭ፡ AD. Information Technology እና tech viral
ፍሬያማ ምርት
*****
ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በረሃብ እየማቀቀ ይገኛል፡፡ ምናልባትም ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነን በቂ እህል ማምረት ብቻ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም፡፡ የማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የውሃ እጥረት እና ሰብልን የማሾር(Crop rotation) ልምድ አናሳ መሆን ይህ እውን እንዳሆን እንቅፋት ሆኗል፡፡
ሰብልን ማሾር፡- በአንድ ቦታ ላይ ለረዥም ጊዜ አንድ አይነት ሰብሎችን አለመዝራት እና በዙር በዙር የተለያዩ ሰብሎችን እየዘሩ የአፈሩን ደህንነት የማስጠበቅ ሂደት፡፡
ይህንን በተመለከተም የ Global Landscapes Initiative at the University of Minnesota ተመራማሪ እና ዳይሬክተር ፖል.ሲ ዌስት እና ባልደረቦቹ ሰፊ ጥናት በማካሄድ የዓለምን የምግብ ዋስትና ለመረጋገጥ ያስችላል ያሏቸውን 5 ዋና ነጥቦች በጥናት ፅሁፋቸው ውስጥ ያቀረቡ ሲሆን እኛ ለዛሬ 3ቱን እንካችሁ እያልን ቀሪዎቹን በሌላ ጊዜ የምናቀርባቸው ይናል፡፡
ፖል ለTreeHugger(ዌብሳይት) በሰጠው መግለጫ ላይም እንዳለው ከሆነ በጥናታችን ውስጥ የጠቀስናቸው ጉዳዮች ላይ አፅንዖት ተሰጥቶ ቢሰራበት 3ቢሊዮበን የሚሆንን ህዝብ በስርዓቱ መመገብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ ከባቢውን አዎንታዊ በሆነ መንገድ የመለወጥ ትሩፋት አለው ብለዋል፡፡
1- የምርት ልዩነትን ማጥበብ
እንደ (World Wildlife Fund) ግምት ከሆነ በ2050 120 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ተፈጥሯዊ የመኖሪያ ቦታ ወደ እርሻ ቦታነት ይቀየራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዓለም ላይ ያሉ የእርሻ ቦታዎች ማምረት ከሚገባቸው እና ከሚችሉት በ50 ፐርሰንት ያነሰ እያመረቱ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ምንም ተጨማሪ የእርሻ መሬት ሳንጠቀም የእርሻ መሬቶች ማምረት የሚገባቸውን ያህል ማምረት የሚችሉበትን ሁኔታ ብናመቻች እና ጋፑን/ልዩነቱን ማጥበብ ከቻልን ተጨማሪ 850ሚሊዮን ህዝብ መመገብ ይችላሉ፡፡ ሰለዚህ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ልዩነቱን እንዴት እናጥብብ የሚለው ነው፡፡
2- ማዳበሪያዎችን በብቃት እና በትክክል መጠቀም
ምንም እንኳን እኛ እንደ TreeHugger አርቴፊሻል ማዳበሪያዎችን መጠቀምን ባናበረታታም አሁን ላይ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተጠቃሚነት አለ ፡፡ ይሁንና ይህ ጥናት ማዳበሪያን በተመለከተ ጥሩ ዜና ይዞ ብቅ ያለ ሲሆን እሱም ዓለም ስንዴ፣ሩዝ እና በቆሎ ለማምረት እየጠቀመች ያለችውን የናይትሮጂን እና የፎስፈረስ ማዳበሪያ መጠን ከ13 -29 ፐርሰንት ቀንሳም ቢሆን ከዚህ በፊት የምታመርተውን ያህል ማምረት ትችላለች ፡፡ በተጨማሪም የማዳበሪያ አጠቃቀም እውቀትን በማሳደግ መች እና እንዴት መጠቀም እንዳለብን ካወቅን ትርፋማ የመሆን እድላችን ሰፊ ይሆናል፡፡
3- አነስተኛ ውሃ የሚፈልጉ ምርቶች ላይ ማተኮር
በግብርና ዓለም ውስጥ ውሃ ትልቁ ተግዳሮት ነው፡፡ ይህንን ለመዋጋትም መስኖን መጠቀም እና እምብዛም ውሃ የማይሹ ምርቶችን ማበረታታት እንደ ዓይነተኛ አማራጭ መታየት አለበት ያሉ ሲሆን ለምሳሌ ያህል እንደ ሩዝ እና እንደ ስኳር ድንች ያሉ ምርቶች ከፍተኛ ውሃ የሚሹ ምርቶች በመሆናቸው ትልቅ እክል ይገጥማቸዋል፡፡
ይሁንና የምግብ ምርት የብዙ ነገር ተፅዕኖ የሚያርፍበት ስራ ነው፤ አንድ ገበሬ የሚያመርተው ገበያውን እና ባህሉን ተንተርሶ በመሆኑ በቀላሉ የሚያመርተውን ነገር መቀየር የሚችል አይደለም ይህ ደግሞ አነስተኛ ውሃ የሚሹ ምርቶችን ተመራጭ ላያደርጋቸው ይችላል ሲሉ ተግዳሮቱን ጠቆም አድርገው አልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- TreeHugger
የኢትዮጵያ የሳይንስ ሳምንት በመካሄድ ላይ ነው
##########################
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ለአራት ቀናት የሚቆይ የሳይንስ ሳምንት ከዛሬው ዕለተ አንስቶ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መካሄድ ጀምሯል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ህዳር 10 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ምክንያት በማድረግ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ይህ የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ የፈጠራ ወድድሮችና የአውደ ርዕይ ስነ ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ስነ ስርዓት ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የመጀመሪያ ደረጃ (7ኛ እና 8ኛ) ፣ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው በሚያቀርቡት የፈጠራ ፕሮጀክት የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ መምህራን እና ከተለያዩ ስቴም ማዕከላት የተወጣጡ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በኢንጂነሪንግ፣ ሮቦቲክስ እና ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ ፈጠራቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ውድድር በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ በተማሪዎች ብቻ ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች የሚቀርቡ ሲሆን የመምህራን እና የስቴም ማዕከለት ሲጨመር ደግሞ ከ187 በላይ ፕሮጀክቶች ለውድድር ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተዘጋጀው በዚህ የሳይንስ ሳምንት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ እንዳሉት የተዘጋጀው ይህ የውድድር መድረክ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የቀሰሙትን የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ችግሮችን ሊፈታ ወደሚችል ጠቃሚ ፈጠራ እንዲቀይሩ ከማገዙም ባለፈ በመጪው ጊዜ ለሚኖራቸው የስራ ክህሎት ጥሩ ልምድ እና መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው አንስተዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ የሚከበረው የሳይንስ ሳምንት “Open Scienece, Leaving No One Behined” በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያም በተለያዩ የፈጠራ ውድድሮች እና የአውደ ርዕይ ስነ ስርዓቶች ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚከበር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡
በዓይን የማይታየው ዓለም
********************

የሰው ልጅ በየዘመኑ በፈለሰፋቸው የቴክኖሎጂ አቅሞች በመታገዝ በዙሪያው የሚገኙትን በዓይን የሚታዩ ሕይወት ያላቸውንና የሌላቸውን አካላት አፈጣጠር፣ አኗኗርና ጠቀሜታ ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠት ረገድ ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከተለመደውና ከሚታወቀው ባሻገር ያለውን በዓይን መታየት የማይችለውን የደቂቅ አካላት ዓለም (microbial world) የማወቅ አቅም የፈጠረው ዘግይቶ ነው፡፡

ስለ ደቂቅ አካላት መኖር መነገር የጀመረው ከ5ኛው ክፍለ ዘመን (BC) ጀምሮ ቢሆንም በ17ኛው ክፍለ ዘመን የታዋቂዎቹ ሳይንቲስቶች የሮበርት ሁክና የአንቶኒዮ ቫን ሊቨንሆክ በማስረጃ የተደገፈ አዲስ ግኝት በዓይን የማይታዩ አካለት መኖራቸውን ያበሰረ ነበር፡፡ በ1663 ዓ.ም በሮበረት ሁክ በባለ አንድ ሌንስ ትንሽ ማይክሮስኮፕ በመታገዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከር (Mucor) የተባለውን የፈንገስ ዘር በማግኘት የተጀመረው በዓይን የማይተየውን ዓለም የማወቅ ጅማሬ ከ1677-1678 ዓ.ም ባለው ጊዜ አንቶኒዮ ቫን ሊቨንሆክ ባሻሻለው ማይክሮስኮፕ “little animalcules” በመባል የተጠሩትን ባክቴሪያ ለማየት በመቻሉ የበለጠ ወደ መታወቅ የተሸጋገረበት ወቅት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል::

አሁን ላይ በተደረሰበት ሳይንሳዊ ውጤት መሰረት በዚህ በዓይን በማይታየው የፍጥረት ዓለም ውስጥ የተመደቡት በወል ስማቸው ደቂቅ አካላት1 (microorganisms/microbes) ተብለው የሚታወቁት ፍጥረቶች በየዘርፋቸው ሲዘረዘሩ አርኪያ (Archae)፣ ባክቴሪያ (bacteria)፣ ፈንገስ (Fungus)፣ ማይክሮአልጌ (Microalgae)፣ ፕሮቶዞዋ (Protozoa) እና ቫይረስ (virus) የተባሉት ናቸው፡፡

ደቂቅ አካላት ሕይወት ካላቸው የምድር ፍጥረታት ከ3.5 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ቀድመው የተፈጠሩ የፍጥረት ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በዓይን የማይታዩ የምድራችን ፍጥረታት ከነሱ በኋላ ለመጡት በሕይወት መቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው እንደሆኑ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች ያስረዳሉ፡፡ ዛሬም ቢሆን ካለነዚህ ደቂቅ ፍጥረታት አስተዋጽዖ ሌሎች በሕይወት መቀጠል እንደማይችሉ ሳይንቲስቶች ያምናሉ፡፡ በምድር ላይ ለ3.5 ቢሊዮን ዓመታት ባደረጉት ዝግመተ ለውጥና መላመድ በምድራችን በየትኛውም አካባቢ ለመኖር ችለዋል፡፡፡ በዚህም የተነሳ ሌሎች ፍጥረታት ሊኖሩ በማይችሉባቸው አስቸጋሪ ቦታዎች ምግብ ሳይቸግራቸውና በሕይወት ለመኖር ስጋት ሳይገባቸው ኖረዋል፣ እየኖሩም ነው፡፡ ለእነርሱ በሚኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ምግብ አለ፣ ሕይወት አለ፡፡

የደቂቅ አካላት ልከት (size) በጣም ትንሽ መሆን በዓይን እንዳይታዩ ያደረጋቸው ሲሆን፣ ዛሬም ቢሆን በዘመናዊ ቴክኖሎጂም እንኳን በመታገዝ መታየት የቻሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ያላቸው መጠንና የክብ አጋማሻቸውም ከሰው ህዋስ ጋር ሲነጻጸር በተዋረድ 1/8000ኛ እና 1/100ኛ እንደሆነ ነው የታወቀው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች በድምር ሊኖራቸው የሚችለው መጠን ሲገመትም የስፒል ጭንቅላት ያህል እንደሚሆን ነው፡፡ ብዛታቸውም በቁጥር ለመግለጽ ከሚቻለው በላይም እንደሆነ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል በምድራችን ያሉ የባክቴሪያዎች ቁጥር ብቻ አምስት ኖኒሊዮን (5x1030) እንደሚደርስና የፕላኔታችን አብዛኛው ግዝፈ ሕይወት (biomass) የባክቴሪያ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ያስረዳሉ፡፡ በጥቅል ሲታይ ደቂቅ አካላት በድምር መጠናቸው ከምድር ፍጥረታት አጠቃላይ መጠን የ2/3ኛውን ድርሻ የሚወስዱና 50% የሚሆነውን ፕሮቶፕላዝም የያዙ እንደሆኑ ይገመታል፡፡

በቅርብ ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደቂቅ አካላት ከሰው ጋር ያላቸውን ቁርኝት ስንመለከት በሰው አካል ውስጥ ከሚገኘው ህዋስ 90%ቱን የሚሸፍኑት ባክቴሪያና ፈንገሶች እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡ የሰው አንጀት ብቻ 40 ሺህ የባክቴሪያ ዝርያዎችን፣ 9 ሚሊዮን ልዩ የሆኑ የባክቴሪያ በራሂዎችን (genes) እና 100 ትሪሊዮን የደቂቅ አካላት ህዋሶችን (cells) እንደያዘም ተገምቷዋል፡፡ በአጠገባችን ያለ አንድ ግራም አፈር 40 ሚሊዮን እንዲሁም አንድ ሚሊ ሊትር ንጹህ ውኃ አንድ ሚሊዮን የባክቴሪያ ህዋሶችን እንደያዘ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው በዓይናችን ስለማናያቸው እንጂ ደቂቅ አካላት ከኛ ጋር እና በዙሪያችን በየትኛውም ስፍራና አካባቢ እንደሚገኙ ነው፡፡ ለምን? በአጭሩ ሊጠቅሙን!

ከፍጥረታት እጅግ ጉልበተኛውና ኃይለኛው ማነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ የምድራችን ምላሽ ደቂቅ አካላ
የሰመር ካምፕ ተወዳዳሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተበረከተላቸው
****************************************************************
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ያዘጋጀው እና ከሃምሌ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ሲካሄድ የቆየው የሰመር ካምፕ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በእውቅና እና የሽልማት ስነ ስርዓቶች ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ የሰመር ካምፕ ፕሮግራሙ በዋናነት የመንግስት ተቋማት የአሰራር ስርዓትን የሚያዘምኑ የሶፍትዌር ፕሮጀክቶች ማበልጸግ እና ማቅረብ በሚለው የትግበራ ዘርፍ ላይ አተኩሮ የተሰናደ ሲሆን፣ ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ አመልካቾችም በመነሻነት መሳተፋቸውን በስነ ስርዓቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በተዘጋጀው በዚህ የእውቅና እና ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ የመክፈቻና የአንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ የሰመር ካምፑ መዘጋጀት የሚኖረውን ከፍተኛ ጥቅም አንስተው ወደ ፊት ይበልጥ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል እና ድጋፎችም በሰፊው እንደሚደረጉ ገልፀዋል፡፡ ተቋሙ በአዲስ የመዋቅር መስረታ እና የሽግግር ሂደት ላይ ከመሆኑ አኳያ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ እንደዚህ ያለ ፕሮግራምን በስኬት ማጠናቀቁ ጥሩ መነሻ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

የሰመር ካምፕ ዝግጅቱን አጠቃላይ ሂደት እና የውድድር መስፈርት አስመልክቶ ገለፃ ያደረጉት የኮምፒውቲንግ እና አናሊሲስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብሬ አላምነ በጥቅሉ ከሶስት መቶ በላይ ተማሪዎች ለውድድሩ ማመልከታቸውን ጠቅሰው በተዘጋጀው መስፈርትም 27 የሚሆኑት ተወዳዳሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ እና ፕሮጀክታቸውን እንዲያከናውኑ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተዘጋጀው የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ላይ ምንም እንኳን ጊዜን ጨምሮ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ችግሮች እንደነበሩ ያነሱት አቶ ገብሬ የሚቻለውን ድጋፍ ለተማሪዎቹ በማድረግ የመንግስት ተቋማትን የሚያዘምኑ ችግር ፈቺ ሶፍትዌሮች እንዲሰሩ መደረጋቸው በስኬት ደረጃ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተዘጋጀው የመስፈርት ሁኔታ ሶስት ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ሲሆኑ ፕሮጀክታቸውን በስኬት ያጠናቀቁ 14 ተማሪዎችም የእውቅና ሽልማት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀው ፕሮጀክት በናትናኤል ዘነበ እና ሳምሶን ተከስተ የተሰራው Employe Attendance System የተሰኘው ፕሮጀክት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአላዛር ደምሴ የተሰራው General Safty የተሰኘው ችግር ፈቺ ሶፍትዌር አሸናፊ ሆኗል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ቢታኒያ ናስር እና ናትናኤል ሙሉጌታ የሰሩት Storage Management System የተሰኛው ፕሮጀክት ሲሆን ለሶስቱም አሸናፊች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በስነ ስርዓቱ ማጠናቀቂያ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የኢንቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ሳህለ ማሪያም በተማሪዎቹ የተሰራው ችግር ፈቺ ሶፍትዌር ብዙ የመንግስት ተቋማት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ጠቃሚ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ለወደፊቱም የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ሶፍትዌሮቹ ወደ ተግባር የሚገቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
5G ቴክኖሎጂ እንዴት ይሰራል?
*****************************
የ 5G ቴክኖሎጂ የ አምስተኛው ትውልድ የሞባይል ቴክኖሎጂ ሲሆን የዲጂታል ዓለሙ የሚፈልገውን ፈጣን ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ እርምጃ ያራመደ ቴክኖሎጂ ተደርጎም ይወሰዳል። የ 5G ቴክኖሎጂ የመረጃ መለዋወጫ ፍጥነትን አሁን ካለው የ4G ቴክኖሎጂ ከ10 እስከ 100 የተሻለ እጥፍ እንደሚልቅ ይገምታል። ይህም ማለት የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን እስከዛሬ ከነበረው የm/s ፍጥነት ወደ g/s ያሳድገዋል ማለት ነው።
ኒዮርክ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሃሪሽ ክሪሺናስዋሚ እንዳሉት “ የ 5G ቴክኖሎጂ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም አሁን ባለው የኔትዎርክ ፍጥነት መተግበር ያልቻልናቸውን ከፊተኛ የሆነ የኔትዎርክ አቅምን የሚጠይቁ መተግበሪያዎችን እንዲንጠቀም ያስችለናል ለምሳሌ በ ጊጋ ባይት ደረጃ ያሉ ፊልሞችን በሰከንድ ከኢንተርኔት ማውረድ ያስችለናል እንድሁም እንደ ቨርችዋል ሪያሊቲ መተግበሪያና ሰው አልባ መኪኖችን ላይ ለፈጣን የመረጃ ዝውውር መጠቀም ያስችለናል”። በተጨማሪም ዘመኑ እየፈጠራቸው ያሉ ቴክኖሎጂዎች ማለትም እንደ አጉመንትድ ሪያሊቲ እና ሰው አልባ መኪኖች ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ፍጥነትን ይሻሉ ስለሆነም የ5G ቴክኖሎጂ የመረጃ የመዘግየት ሂደንት ወደ 1 ሚሊ ሴኮንድ ዝቅ ማድረን አላማ አድርጎ ተነስቷል ይህ ማለት ተንቀሳቃች መሳሪያዎች መረጃን የ1 ሴኮንድ 1/1000 ባነሰ መለዋወጥ ያስችላቸዋል።
ባለፉት ትውልዶች ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙት የኤሌክትሮማግኔቲክ ጨረርን እንደ ሬድዮ ሞገድ ባሉ ቴክኖሎጂዎች በመሆኑ የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ በከፍተኛ ሁኔታ የኔትዎርክ መጨናነቅን ይፈጠርበታል፡፡ ስለሆነም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ የሆነ የራድዮ ሞገድ ከመጠየቁም በላይ በ ሴንቲሜትር የሚለካውን ወደ ሚሊሜትር ሞገድ ዝቅ ማድረግ አስፈልጓል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ቀድመን ከምናውቀው ትልልቅ የሆኑ የኔትዎርክ ምሰሶዎች በላይ በማይፈልጉ የህንጻዎች አናት እና በመብራት አስተላላፊ ምሰሶዎች ላይ ሊገጠሙ የሚችሉ በመሆኑ ቴክኖሎጂዎቹ አዲስ የግንኙነት መንገድ የክፈቱ አስብሏቸዋል። ነገር ግን እነዚህ የሞገድ አይነቶች ሌሎች ተግዳሮቶች አጋጥሟቸዋል ከነዚህም መካከል ሞገዶቹ በዛፎችና በህንጻዎች ከመዋጥ አልዳኑም። ነገር ግን እነዚህ በመጠናቸው አንስተኛ የሆኑ የኔትዎክ አስተላላፊዎች ለአዳዲስ የምርምር ስራዎች መፈጠር ጉልህ አስተዋጾ ነበራቸው። የ አምስተኛው ትውልድ ኔትዎርክ የመፈጠር ምክንያትም ናቸው። የአምስተኛው ትውልድ ኔትዎርክ (5G) ቀድሞ በነበሩት የኔትዎርክ አስተላላፊዎች ላይ ቁጥራቸው በርከት ያሉ በመጠን አነስተኛ የሆኑ አንቴናዎችን በመጨመር እንዲሁም የማስተላለፍ አቅማቸውን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ መላላኪያ ፍጥነትን በመጨመር የተፈጠረ ሲሆን የመረጃ መዘግየትን በእጅጉ ቀንሷል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከዚህ በተጨማሪም በፊት ከነበሩት የኔትዎርክ አስተላላፊዎች ያነሰ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀማቸውም ልዩ ያደርጋቸዋል።
ምንጭ:-Live science
የፔቲዲን (Pethidine) ሱስና ህክምናው
*********************
ፔቲዲን መካከለኛና ከፍተኛ ስቃይን ለማስታገስ በመርፌ የሚሰጥ መድሀኒት ሲሆን ህመም ከማስታገስ ባሻገር የደስታ ስሜት ስለሚፈጥር አንዳንድ ሰዎች ላይ ሱስ ሊሆን ይችላል። ፔቲዲን ሱስ ሲሆን ከአእምሮና ከሰውነት ጋር ስለሚለማመድ ህመምን ለመቀነስ ወይም ደስታን ለማግኘት ከፍ ያለ መጠን መውሰድ ይፈልጋል።
የፔቲዲን ሱስ ያለባቸው ሰዎች በተከታታይ የሚወጉት መድሀኒት እየጨመረ ስለሚመጣ በድንገት ብዙ መጠን ወስደው መንቀጥቀጥ ራስን መሳት እንዲሁም ሞት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ብዙ መጠን ለረጅም ጊዜ የወሰዱ ሰዎች በድንገት ሲያቆሙ ከፍተኛ ጭንቀት፣ መቅበጥበጥ፣ እንባ መብዛት፣ ማቅለሽለሽ ...ወዘተ ይታይባቸዋል። በዚህ ምክኒያት በድንገት ማቆም አይመከርም።
የፔቲዲን ሱስ ያለባቸው ሰዎች ሀፍረት ስለሚሰማቸው ችግሩን መቀበል ያስቸግራቸዋል ከዛ ይልቅ ለመሸፋፈን ይሞክራሉ። አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገ ጥናት ፔቲዲንን ጨምሮ በመርፌ የሚወሰዱ መድሀኒቶች ሱስ የሆነባቸው ከ አራት ሺህ በላይ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ብዙዎቹ ህክምና እንዳለው እና ህክምናው የት እንደሚሰጥ ባለማወቅ የህክምና እግዛ ሳያገኙ ይቀራሉ።
ዘውዲቱ ሆስፒታል የሚገኘው የአእምሮ ህክምና ክፍል ፔቲዲንን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ እንዲያቆሙ የሚያግዝ ሲሆን የግልና የቡድን የንግግር ህክምናም ይሰጣል። የፔቲዲን ሱስ ለህክምና ተብሎ በተሰጠ መድሀኒት ተከትሎ የሚመጣ በመሆኑ Center for Disease Control የሚከተሉትን ነጥቦች ለባለሞያዎች እንደመርህ ያስቀምጣል።
*በተቻለ መጠን ፔቲዲን (ኦፒዮይድ) ከመጠቀም ሌሎች አማራጭ መድሀኒቶችን መጠቀም
*ፔቲዲን ማዘዝ አስፈላጊ ሲሆን የሚያስፈልገውን ትንሹን መጠን ለሚቻለው ትንሽ ጊዜ ብቻ ማዘዝ
*ፔቲዲን የሚወስዱ ሰዎች ላይ ሱስ መሆን አለመሆኑን በጥንቃቄ መመልከትና ሱስ ከሆነ የአእምሮ ህክምና እንዲያገኙ ማገዝ ናቸው።
ምንጭ፡ addiction hope እና mental wellness
የፀሃያችንን ድንበር አልፈው የሄዱት ሁለቱ መንኮራኩሮች
*********************
የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ እንደግሪጎሪያኑ በ1977 በተለያየ ወር ልዩነት ያመጠቃቸው ቮዬጀር1 እና ቮዬጀር2 (Voyager 1&2) የተሰኙት አሳሽ መንኮራኩሮች ስለ ፕላኔት ጁፒተር፣ ሳተርን፣ ዩራኑስ እና ኔፕቱን ስሪት አጥንተው እንደጨረሱ ወደ በይነኮከባዊ ህዋ (interstellar space) መላካቸው የሚታወቅ ነው። እነዚህ መንኮራኩሮች ከ37 አመታት የህዋ ውስጥ ጉዞ በኋላ በጁላይ 2012 አካባቢ ሴንሰሮቻቸው የፀሀይ ነፋሳት ፍጥነት ቀንሶ የበይነኮከባዊ ነፋሳት ፍጥነት እንደጨመረ ማረጋገጥ ችለዋል። በመሆኑም ስርአተፀሀያችንን ለቀው ወደ በይነኮከባዊ ህዋ ጉዟቸውን እንዳደረጉ እርግጥ ሆኗል።
ስለ ስርአተፀሀያችን ድንበሮች ያለንን እውቀት በሙሉ ያስጨበጡን ቮዬጀሮች በጥቂት ወራት ተለያይተው የተላኩ ቢሆንም ስርአተፀሀያችንን ከቦ የሚገኝውን እና ከድንኩዋ ፕላኔት ፕሉቶ ምህዋር በእጅጉ ርቆ የሚገኝውን ኢነባራዊ ድንበር ሂልዮስፌር (Heliosphere) አልፈው መሄዳቸው በታሪክ በሰው ልጅ ከተሰሩ አሳሽ መንኮራኩሮች ውስጥ ቀዳሚ ያደርጋቸዋል። መንትያዎቹ አሳሽ መንኮራኩሮች የሚጉዋዙበት አቅጣጫ እንዲሁ የተለያየ ቢሆንም ሁለቱም ግን ስርአተፀሀያችንን ለቀው ወጥተዋል። ቮዬጀር2 አሁን ላይ 'ሳጁታርየስ' ወደተሰኘው ህብረከዋክብት (Constallation) አቅጣጫ በሰኮንድ 16ኪ.ሜ እየገሰገሰች ጉዞዋን ቀጥላለች። በዚህ ፍጥነት ከቀጠለች ከ 296,000 አመታት በሁዋላ ሰማያችን ላይ ደምቃ ከምትታየው 'ሲረስ' ከተሰኘቸው ኮከብ ልትደርስ ትችላለች ተብሎ ይታሰባል።
ይሁንና ሁለቱም መንኮራኩሮች መንቀሳቀሻ ሀይላቸው የሆነው 'ፕሉቶኒየም ተርሞኤሌክትሪክ ጀነሬተር' የተሰኘው ባትሪያቸው ከ5 አመታት በሁዋላ በ 2025 ሙሉ ለሙሉ ተሟጦ የሚያልቅ በመሆኑ መረጃቸውን መላክ ያቆማሉ። ይህ ማለት ግን ጉዟቸውን ያቋርጣሉ ማለት አይደለም። ከሁለቱ መንኮራኩሮች በፊት እንደመጠቀችው ፓዮኔር 10 አሳሽ መንኩራኩር ሁላ መንትዮቹም በውስጣቸው ምድራችንን የሚገልፅ እና መገኛ አቅጣጫዋን የሚጠቁም ካርታ ይዘዋል። እነዚህ አሳሽ መንኮራኩሮች ማረፊያቸው በውል አይታወቅምና ምናልባት ከኛ ውጭ ህይወት ያላቸው ፍጡራን እነዚህን መንኮራኩሮች ቢያገኟቸው ከየት እንደመጡ እና ስለመጡበት ፕላኔት በደምብ የሚያስረዳ ካርታ እና ስእላዊ መግለጫን ይዘው ይጓዛሉ።
አሁን ላይ ከቮዬጀሮች የተላክ መልእክት ምድራችን ለመደረስ ከ16 ሰአታት በላይ የሚፈጅበት ሲሆን አሁን ከደረሱበት የinterstellar medium (ISM) አንፃር መልክቱን ለማድረስ የሚፈጅባቸው ጊዜ በመጠኑም ቢሆን ለውጥ ያመጣል፡፡ መንትዮቹ መንኮራኩሮች ከላይ እንሰተጠቀሰው በ2012 በላኳቸው መረጃዎች የፀሀይ ነፋሳት ፍጥነት ቀንሶ የበይነኮከባዊ ነፋሳት ፍጥነት መጨመር ተከትሎ interstellar medium ላይ መድረሳቸው የሚጠቀስ ሲሆን በቅርቡም በተለይም ቮዬጀር2 የተባለቸው ሞንኮራኩር የላከቸው ሲግናል ስለጥልቁ ህዋ ያላወቅናቸውን እና ስለበይነኮከባዊ ህዋ ሰፊ መረጃን ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡Science Focus እና theguardian
Presentation 2.jpg
1.3 MB
techin weekly seminar
venue: techin hall
date and time nov 14, from 4:30
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ጋራ በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ
***************************
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የአዕምሮ ንብረት ድርጅት እና የአውሮፓ አዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት ጋራ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡ ኢንስቲትዩቱን ወክለው የመግባቢያ ስምምነቱነን የፈረሙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ ሲሆኑ በኢትዮጵያ አዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት በኩል የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሀን ነበሩ፡፡
ስምምነቱን አስመልክተው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ባደረጉት ንግግር ስምምነቱ ከፊርማም ባለፈ በተቋማቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደላቀ ተቋማዊ ደረጃ እንደሚያሻግረውና ለወደፊት ስራዎችም መነሻ እንደሚሆናቸው ገልፀዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በበኩላቸው ስምምነቱ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከአውሮፓ የአዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት ጋራ እንዲሰራ እንደሚያደርገውና ፅህፈት ቤታቸውም በዚህ ትስስር የግንኙነት ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል፡፡ አክለውም ኢንስቲትዩቱ ፓተንቶችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ የሄደባቸውን ርቀቶች አውስተው የአውሮፓ አዕምሮ ንብረት ቢሮ በዚህ እንቅስቃሴ ጉልህ እገዛ እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ አስረድተዋል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ተሳታፊ የነበሩት በአውሮፓ አዕምሮ ንብረት ፅህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ትብብር ክፍል ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት አቶ ኒኮላስ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናን ችረው ስምምነቶቹን ወደ ተግባር የሚለውጡ የጋራ ስራዎችን ከኢንስቲትዩቱ ጋራ እንደሚሰሩ አሳውቀዋል፡፡