TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
☞ ይህንን ያውቁ ኖሯል?
********************
በፕላኔት ሜርኩሪ ላይ አንድ ቀን ማለት ከመሬት 59 ቀን ጋር እኩል ነው። ይህም ማለት መሬት በራሷ ዛቢያ ላይ አንድ ጊዜ ለመዞር 24 ሰአት ሲፈጅባት ፕላኔት ሜርኩሪ ግን በራሷ ዛቢያ ላይ አንድ ጊዜ ለመዞር 1416 ሰአት ይፈጅባታል።
በሌላ አነጋገር በፕላኔት ሜርኩሪ ላይ አንድ ቀን ማለት 1416 ሰአት ማለት ነው። ይህም ማለት 708 ሰአት ጨለማ፣ 708 ሰአት ብርሐን ማለት ነው። ከስር የምትመለከቱት የሜርኩሪ ፎቶ ነው።
“ወደ ሃብት ሊቀየሩ የሚችሉ ብዙ መረጃዎች ቢኖሩንም አልተጠቀምንባቸውም”
*******************************************************
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ከዜናይሲስ (ZENYSIS) ቴክኖሎጂስ ጋር በትብብር ያዘጋጀው እና ዋና ትኩረቱን በግዙፍ የመረጃ ትንተና (big data analysis) እና አድቫንስድ ኮምፒዊቲንግ (advanced copmputing) ላይ አድርጎ የተሰናዳው ወርክሾፕ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ጥናትና ምርምሮችን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ያከናወኑ ምሁራንም ተሳትፈውበታል፡፡
በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ የመክፈቻና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ ሃገራችን ሌላው ዓለም እየሄደበት ያለውን የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን አድራጊ እና ፈጣሪ ልትሆን ቢገባትም የመረጃን ወሳኝነት በሚገባ ካለመረዳታችን እና ካለመገንዘባችን የተነሳ ብዙ ወደ ውጤት ልንቀይራቸው የሚገቡ ሃብቶች ሳንጠቀምባቸው እንደቀሩ አንስተዋል፡፡ መረጃ የቀጣዪ ጊዜ ወርቅ እና ነዳጅ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ይህንን መሰረታዊ ሃቅ በመረዳት በግዙፍ የመረጃ ትንተና እና አድቫንስድ ኮምፒውቲንግ ላይ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በግዙፍ መረጃ እና ምጡቅ ትንተና ላይ ሰፊ ንግግር ያደረጉት የዜናይሲስ ቴክኖሎጂስ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ካሳ የዘርፉን ታሪካዊ አጀማመር ጨምሮ አጠቃላይ ሂደት ካስረዱ በኋላ የግዙፍ መረጃ ትንተና ሊመሰረትባቸው በሚገቡ ወሳኝ ግብዓቶች ላይ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ከእርሳቸው ቀጥለው መድረኩን የተረከቡት የዜናይሲስ ቴክኖሎጂሰ የሃገር ውስጥ ምርትና ቴክኒካል ትግበራ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንተነህ መኩሪያው የቴክኖሎጂ እና የግዙፍ መረጃ ትንተና በመንግስት ተቋማት ውስጥ በሚለው ርዕሳቸው የሃገራችን የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የግዙፍ መረጃ ትንተና በመጠቀም ወሳኝ የሆኑ የፖሊሲ ክፍተቶች ለመሙላት እንደሚችሉ ከድርጅታቸው ተሞክሮ በመነሳት ገልፀዋል፡፡ አቶ አንተነህ በተለይም ድርጅታቸው በተሳተፈበት የጤና ዘርፍ ላይ ዋና ትኩረታቸውን አድረገው በየተቋማቱ የሚገኙትን ብዛት ያላቸው መረጃዎች እንዴት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚኖርብን በሰፊው አስረድተዋል፡፡ ወርክሾፑ ከከሳዓትም ሲቀጥል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውቲሽናል ዲፓርትመንት ዋና ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ሰለሞን በመረጃ ሳይንስ፣ ሃይ ፐርፎርማንስ ኮምፒዊቲንግ እና በኮምፒውቲሽናል ሳይንስ መሰረታዊ እሳቤዎች ሰፊ ትንተና እና ተሞክሮን አጋርተዋል፡፡
ቢግ ዳታ
************
በዓለማችን ላይ ያለ ነገር ሁሉ ዳታ የማመንጨት ዐቅም አለው፡፡ ሰውነታችን መኪናችን ከባቢያችም ሆነ በዙሪያችን ያለ ቁስ ሁሉ ስለ ብዙ ነገር ብዙ መረጃ ይሰጣል፡፡ እያንዳንዱ እርምጃችን ፣ንግግራችንም ሆነ አኗኗራችን በዘፈቀደ የሚታለፍ አይሆንም ሁሉም ነገር ይቀዳል ይጠራቀማል ትርጉም እንዲሰጥም ይደረጋል፡፡

ይህ ሁኔታ ዓለማችን የተበታተነ ሰውነቷን የሚሰበስብላት የነርቭ ሲስተም ማበጀት እንድትችል የሚረዳት ሲሆን እያንዳንዳችን ደግሞ እንደ ህዋስ በመሆን እናገለግላታለን፤ ይህም ዓለማችን እንደኛው ሁሉ ማስታወስ፣ማጠራቀም እና ማስተንተን እንድትችል ያደርጋታል፡፡ይህ የቢግ ዳታ ቴክኖሎጂ ትልቁ ግብ ነው፡፡

ማንኛውም የምንጠቀመው ማሽን ስልክም ሆነ ኮምፒውተር ትልቁ የመረጃ ምንጭ ነው እያንዳንዱ የጉግል ፍለጋችንም ሆነ ማንኛውም እንቅስቃሴያችን የዲጂታል ፋናን እየጣለ ያልፋል፡፡

ይሁንና ይህ ቁጥር ስፍር የሌለው መረጃ ማለትም ቢግ ዳታ ብቻ ነው፡፡ ጥቅም ላይ መዋል እስካልቻለ እና ትርጉም እንዲሰጥ ተደርጎ ካልተቀናበረ ምንም ነው፡፡ ባለሞያዎቹ እንደተነበዩት ከሆነም በ2020 ዓለም ላይ ያለው መረጃ 40 ዜታባይ ይደርሳል፡፡ ይህም ማለት ዓለማችን ላይ ያለን አሸዋ ሰብስበን በ75 እንማባዛት ነው ሲሉም የመረጃውን ብዛት ይገልጻሉ፡፡

ባለሞያዎቹ እንደሚሉት ከሆነም ባለፉት 3 ዓመታት የተደረገው የዳታ አናላይሲስ ስራ ከዛሬ 3000 ዓመት ገደማ ከተደረገው ይበልጣል፡፡

ታዲያ ቢግ ዳታ ለምን ይጠቅማል;
*****************************************
ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ ብዙ መረጃ በኖረን ቁጥር ብዙ ችግሮችን መፍታት ይቻለናል፤ ይሁንና ምንም ነገር ባለ ሁለት ሰይፍ ነው ችግር መፍታት የሚችለውን ያህል ችግር መፍጠር የማይችል እውነት የለም በመሆኑም መረጃዎችን በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ካልፈቀድን ከባባድ ቀውሶችን መፍጠር እንደምንችለው ሁሉ በተቃራኒው ከግርዶሽ ወዲያ ያሉ የዓለም ችግሮችን እና እንከኖቸን በመዋጋት ባለ ብዙ መፍትሄ የመሆን ዐቅም ይኖረናል፡፡

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ትርጉም እንዲሰጥ ተደርጎ የተተረጎመው መረጃ የአስትሮኖሚ መረጃ ነው ከህዋ የተገኙ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በማቀናበር ስለፍጥረተዓለማችን ብዙ መረዳት እንድንችል የረዳን ሲሆን ከዛም ውስጥ ዛሬ ትንሽ የሚመስለንን ትልቁን እውነት የተዋወቅነው ያኔ ነው ይህም ፀሀይን የምንዞራት እኛ እንጂ እሷ አለመሆኗን መሆኑ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ቀጠለ የሰው ልጅም ማየት ያልቻላቸውን ነገሮች ማየት የሚችልበትን 4ኛ ዓይን አበጀ፤ የማይክሮስኮፕ ግኝት ሴሎች ባክቴሪያዎችን እና ጥቃቅን ነገሮችን በማጋለጥ የሚሊዮኖችን ህይወት ታደገ፡፡ ዓለም በዚህ አላቆመችም ሳይንቲስቶች ወደ ሌላ ክፍታ አሻገሩን በ1650ዎቹ እና በ1660ዎቹ አከባቢ ያገኘናቸው ማይክሮስኮፖች ሊያዩዋቸው የማይችሏቸው ሌላ ረቂቅ እውነታዎች እንዳሉ ታወቀ ያኔም ኤሌክትሮኖች፣ ኒውክለሶች ፣ አተሞችን እና የመሳሰሉትን ታላላቅ ሚስጥሮች በማወቅ የአቶሚክ ዓለም ምዕራፍ ተከፈተ፤ የመብራት እና የኤሌክትሪክ ዘመን መባቻም ተበሰረ፡፡

ቢግዳታን እንደዚህ ያለ ማይክሮስኮፕ እንደሆነ መረዳት እንችላለን ፤በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፈጣን መረጃዎችን አጉልቶ የሚያሳየን አጉሊ መነፅር፡፡በምናየው መረጃ ውስጥ እውነትን እና ሚስጥራትን በመፈለግ የሂወትን እከሎች ከስር እና ከጅምሩ መቅጨት ይቻላል፡፡

መረጃዎችን ከማሰባሰብ አልፎ ማቀናበር የሚቻልበት መንገድ ከተበጀ በጤና ፣ በግብርና፣ በኢንደስትሪና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ የማይታመን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ዳታ/መረጃ እንደ ተጨማሪ ህዋስ በማገልገል ለብዙ ችግሮች ፈጣን እና ብዙ መፍትሄዎችን እንካችሁ ይላል፡፡

በህክምናው ዘርፍ ብናይ አንድ ሰው ከታመመ በኋላ በመታከም ሊድን ይችላል፡፡ ይህ የህክምና መንገድ ግን ከፍተኛ ለሆነ ለመድሃኒት ወጪ እንዲሁም ከመድሃኒት ጋር ለተያያዙ አላስፈላጊ በሽታዎች ሊያጋልጠን ይችላል ስለዚህ ህክምና ሌላ ተጨማሪ መፍሄ ይዞ መጣ እሱም የቀድሞ መከላከል እና ሳይባባስ በጊዜ ቀላል በሆነ መንገድ የማከም ሂደት ይህም የህብረተሰብ ጤናን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ሊረዳ ችሏል፡፡

ነገር ግን አሁንም ትንሽ ከዛ ጠለቅ ብለን እንይ ፋታ የማይሰጡ እና ምልክት የማይተው በሽታዎች ሲከሰቱስ ምን እናደርጋለን? ለምሳሌ ያለጊዜያቸው በመወለዳቸው ምክኒያች ለደቂቃዎች የሚቆይ ኢንፌክሽን ህይወታቸውን ለሚቀጥፋቸው ጨቅላ/አራሶችስ እንዴት እንድረስላቸው? ይሄኔ የቢግዳታ አናላይሲስ ጥቅም ጎልቶ ይወጣል ችግሩ ከመከሰቱ በፊት በጣም ቀድሞ ያሉ የማይታዩ ስስ ለውጦችን በመዘገብ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ በመሆኑ በሽታው ገና በሽታ የሚል ስያሜ ሳይሰጠው በፊት እንዲቀጭ ይሆናል፡፡

እንግዲህ በዚህ ትንሽዬ የቴሌግራም ግድግዳ ላይ ስለቢግ ዳታ ፋይዳ አውርተን መጨረስ የምንችል ባይሆንም ቢግዳታ በአጠቃላይ ለሰው ልጅ እምርታ ያለውን ታላቅ አስተዋፅዖ በሌላ ጊዜ በሰፊው እንደምናነሳ ቃል እየገባን ለዛሬ በዚህ ላይ እናብቃ፡፡
የአፍሪካ ሶፍትዌር አበልፃጊዎች ጉባዬ እየተካሄደ ነው
*****************************************
AFRICAN DEVELOPERS CONFERENCE በማባል የሚታወቀውና በዋናነት በገበያ (Gebeya) የቴክኖሎጂ ኩባንያ እና በተባባሪነት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኢን ቴክ (Ethiopians in Tech) ጋር የሚዘጋጀው የአፍሪካውያን ደቨሎፐርስ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መካሄድ ጀምሯል፡፡
ለሁለት ቀን የሚዘልቀው ይህ ጉባዬ የዲጂታል ኢንዱስትሪን ዋና ትኩረቱ አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የተወጣጡ ሶፍትዌር ኢንጂነሮች፣ ቴክኖሎጂስቶች፣ የSTEM ተማሪዎች እና ስራ ፈጠሪዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡
በጉባዬው ላይ ተጽዕኖ ፈጠሪ የሚባሉ እና በዘርፉ ስኬት ያስመዘጉ ድርጅቶች በተወካዮቻቸው በኩል የፓናል ውይይት እና የልምድ ልውውት ያደረጉ ሲሆን በዋናነትም በሳይበር ደህንነት፣ ክላውድ ኮምፒዊቲንግ፣ ዳታ ሳይንስ እና የሞባይል ቴክኖሎጂ በመሳሰሉ የዲጂታል ዘርፎች ላይ ሰፊ ገለፃ እና ምክክር አድርገዋል፡፡
ጉባዬው በነገው ዕለትም በተለያዩ የፓናል ውይይቶች፣ የስልጠና መርሃግብሮች እና የአውደ ርዕይ ትዕይንቶች ሲቀጥል በዘርፉ ስኬታማ ተብለው የሚጠሩት እንደ Orbithealth፣ ዜናይሲስ፣ አይኮ ግላብስ እና ሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ልምዳቸውን እና እይታቸውን ለተሳታፊዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለአፍሪካ ኢኖቬሽን ሳምንት ተዘጋጅተዋል?
የከንፈር ቁስለት
==========
የከንፈር ቁስለት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን የሚያውክ የጤና እክል ነው፡፡ ሲከሰትም እንደ ምግብ መመገብ እና ጥርስን መፋቅ የመሳሰሉ ተግባራትን ያከብድብናል፡፡ ብዙውን ጊዜ ከንፈር ቁስለት ንክሻን በመሳሰሉ ቀላል ምክንያቶች ሊከሰት ቢችልም እንደ ካንሰር እና ሌሎች ቀላል እና ከበድ ያሉ የጤና እክሎችንም ተከትሎ ሊመጣ ይችላል፡፡ እነዚህ የአፍ ቁስለቶች ተላላፊ እና የህክምና እርዳታን የሚሹም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአፍ ቁስለትን ያመጣሉ ከሚባሉ ሌሎች ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
• ያልተመጠነ የጥርስ ተከላ
• ሹል ወይም የተሰበረ ጥርስ
• ብሬስ እና መሰል ቁሶች
• ትኩስ ምግብ እና መጠጥ
• ሲጋራ (ማጨስም ማቋረጥም)
• አንዳንድ ህክምናዎች
• ከፍተኛ የአሲድ መጠን ያላቸው ምግቦች
• ጭንቀት
• የቫይታሚን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች እጥረት
ህክምና
***
አብዛኛውን ጊዜ የከንፈር ቁስሎች በራሳቸው ይድናሉ፡፡ ለምሳሌ በቀላል ጉዳቶች አማካኝነት የሚመጡ ቁስለቶች ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ድህነታቸውን ይጨርሳሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቁስሉን ለማጥፋት የሚከተሉት መንገዶች ይመከራሉ፤
• በጨው ውሃ ማጠብ
• ትኩስ እና የሚያቃጥሉ ምግቦችን አለመመገብ
• ሲጋራን ከማጨስ መቆጠብ
• ከአልኮል መራቅ
• እንደ ብርቱካን እና ሎሚ ያሉ ፍራፍሬዎችን አለመመገብ
ሆኖም በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይሻለን አሊያም የኢንፌክሽን ምልክት ካሳዩ፣ ከነጡ እና ህክምናን ተከትለው የተከሰቱ ከሆኑ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መታከም ይኖርብናል፡፡
ምንጭ፡ Medical News Today
ኢትዮጵያና ሩሲያ የኒውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የኒውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ስምምነት በሩሲያ ሶቺ ተፈራረሙ።

የሁለትዮሽ ስምምነቱ በሩሲያ ሶቺ እየተካሄደ ካለው የአፍሪካ ሩሲያ የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ነው የተፈረመው፡፡

የስምምነቱን ፊርማ በኢትዮጵያ በኩል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በዛሬው ዕለት ፈርመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን፥ በቀጣይ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሃይል ምንጭነት መጠቀም የሚያስችላትን ተጨማሪ ፕሮቶኮል ፊርማ መፈረሟ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ኒውክሌርን ለማናቸውም ሰላማዊ ጥቅም በተለይም ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ እና የኤሌክትሪክ ሃይልን ለማመንጨት ጭምር እቅድ አላት።

Source.........FBC
ሳይጠጡ መስከርን ምን ይሉታል?
=====================

የ46 ኣመቱ ጎልማሳ አሜሪካዊ ምንም ዓይነት አልኮል በምላሱ ሳይዞር ይሰክራል፤ የቁጡነት ባህርይንም ያሳያል፡፡ ጠጥቶ በማሽከርከርም ተይዞ ወህኒ ከመግባት ቢሆን አላመለጠም፡፡ ምክንያቱም ምርመራዎች በደሙ መኖር ካለበት ሁለት እጥፍ የአልኮል መጠን መኖሩን በመናገራቸው፡፡ አለመጠጣቱን በየፖሊስ ጣቢያው እና ሆስፒታሉ ደጋግሞ ቢናገርም ማንም ሊያምነው አልቻለም፡፡ ግን ይህ ቀልድ ሊመስል ቢችልም አውቶ ብሪወሪ ሲንድረም (ABS) በተባለ በሽታ ከመጠቃት የሚመጣ ነው፡፡

አውቶ ብሪወሪ ሲንድረም በአንጀት ውስጥ ያለው ባክቴሪያ ካርቦሀይድሬትን ወደ ስካር አምጪ አልኮልነት እንዲለውጥ የሚያደርግ የጤና እክል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ታማሚዎቹ ስኳር ወይም ካርቦሀይድሬት የበዛባቸውን ምግቦች በሚመገቡበት ወቅት አረቄ ወይም ቢራ እንደጠጣ ሰው ሁሉ ወደ ስካር መንፈስ ይወረውራቸዋል፡፡ ከላይ የጠቀስነው ሰውም ታድያ ምግቡን ከተመገበ በኋላ መንቀሳቀስ ያቅተው እንደነበር ጉዳዩን የተከታተሉት ዶ/ር ፋርሀድ ማሊክ ገልፀዋል፡፡ ታማሚው ይህ ሁኔታ ያጋጥም የጀመረው እጁ ላይ ለደረሰበት የተወሳሰበ ጉዳት ይሆንለት ዘንድ በፈረንጆቹ 2011 የፀረ ባክቴሪያ መድሀኒት መውሰድ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ሆኖም ይህ መድሀኒት ከተወሰደበት ዓላማ ጎን ለጎን በአንጀቱ ውስጥ ያሉትን ባክቴሪያ፣ ፈንገስ ወይም ሌሎች ጥቃቅን ህዋሳትን ተግባር ረብሾ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ይህ ሰው ህመሙ ባመጣበት ጦስ ታስሮ ሳለ አንድ ግለሰብ በተመሳሳይ ህመም ህክምናውን እንደተከታተለ የሰማችው የዚህ ሰው አክስት ህክምናውን እንዲከታተል ነገሩ ወደተሰማበት ጤና ተቋም ትወስደዋለች፡፡ እዚያ ባከናወነው የሰገራ ምርመራ ሀኪሞቹ የቢራ እርሾ የመሰለ ነገርን በማግኘታቸው በተገለፀው በሽታ ለመጠቃቱ ይጠቁማቸዋል፡፡ ከስምንት ሰዓታት በኋላ ግን በሰውየው ደም ውስጥ ያለው የአልኮል ምጣኔ ወደ 0.05 በመቶ ሊያድግ ቻለ፡፡ ይህን ተከትሎ የምግብ እና ፀረ-ፈንገስ ህክምናን ብሎም ሳይካትሪስት እና ኒሮሎጂስቶችን ጨምሮ በተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ቢሰጠውም ከመስከር ሊድን አልተቻለውም፡፡ በአንድ አጋጣሚም በደሙ ውስጥ ያለው የአልኮል መጠን እጅጉን አሻቅቦ ለሞት ሊያበቃ በሚችል 0.4 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ሁኔታውን የተመለከቱት ሀኪሞች መጠጥ አለመጠጣቱን መናገሩን ከውሸት ቆጠሩበት፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር በሪችሞንድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል ባለሙያዎች ዕርዳታን ለማግኘት ወደዚያው ያቀናው፡፡ የማዕከሉ ሀኪሞች ታማሚውን ለሁለት ወራት በቅርበት ሲመረምሩት ቆይተው በአንጀቱ ውስጥ ያሉትን ተህዋሲያን ማስወገድ ቻሉ፡፡ ሀኪሞቹ በማስከተል ታማሚውን የሚረዱ ባክቴሪያዎችን እንዲያሳድግለት መድሀኒት የተሰጠው ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ወደጤነኝነት ሊመለስና ያማረውን አማርጦ ለመብላት በቅቷል፡፡ መቼስ አጃይብ ነው!!!

ምንጭ፡ Live Science
በማቴሪያል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈርቀዳጅ የሆነችው ኢትዮጵያዊት ተመራማሪ፡ ፕሮፌሰር ሶስና ሃይሌ
==================================
ፕሮፌሰር ሶስና ሃይሌ እ.ኢ.አ በ 1958 ከአዲስ አባባ የተገኘች ኢትዮጵያዊት ሳይንቲስት ናት፡፡ በ1967 በሃገሪቱ የመንግስት ለውጥ መምጣት ተከትሎ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ለመሰደድ የተገደደችው ፐሮፌሰር ሶስና አብዛኛውን የህይወት ጊዜዋንም በዚህ አንድታሳልፍ ሆናለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከቤተሰቦቿ ጋር አብራ በመሆን የልጅነት ጊዜዋን በሚኒሶታ ሃገረ ግዛት ገጠራማ አካባቢ ካደረገች በኋላ በ1986 የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በማቴሪያል ሳይንስና በኢንጂነሪንግ ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ማሳካት ችላለች፡፡

ፐሮፌሰር ሶስና በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት የፒችዲ ትምህርቷን ለመማር እንዲያስችላት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘችበት የማሳቹሴትስ የቴክኒሎጂ ኢኒስቲትዩት ያቀናች ሲሆን፤ በዚህም እንዲሁ በምትወደው የማቴሪያል ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ መመረቅ ችላለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከዚህ የተሳካ የትምህርት ጉዞዋ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኘችበት የካልቴክ ፋካልቲ ከማምራቷ በፊት ሲያትል በሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት የሰራች ሲሆን በዚህ የሶስት ዓመት ቆይታዋም ሀገሯን የሚያኮራና አፍሪካንም የሚያስጠራ ትልልቅ የምርምር ስራዎችን ለመስራት በቅታለች፡፡

ፐሮፌሰር ሶስና ድምራቸው ከ150 በላይ የሆነ የጥናትና ምርምር ፅሁፎችን በግል እና ከሌሎች ምሁራን ጋር በጋራ በመቀናጀት ሰርታ ለህትመት አብቅታለች፡፡ በስሟ የተመዘገቡላት ፓተንቶችም ቢሆን አስራ አምስትን ተሻግረዋል፡፡

ከነዚህ የህትመት እና ምርምር ውጤቶች ውስጥ ብዙሃኑ በጠጣር የአዮን ቁስ እና መሳሪያዎች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚያጠነጥኑት የፕሮፌሰር ሶስና ስራዎች መካከል ደግሞ ከዓመታት በፊት የሰሩት አዲስ ዓይነት የፊውል ሴል ከሌሎች ፈጠራዎቿ ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ሶስና ኬሚካሎችን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል በመቀየር ለመኪኖች፣ ሃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች ሃይልን ለሚጠይቁ ተግባራት ንፁህ የሃይል ምንጭ በመሆን እንዲያገለግለ፤ በማሰብ የፊውል ሴሎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል ቁስን ለመስራት አልማ ተነሳች፡፡ ይህ ሃሳቧም በአይነቱ አዲስ የሆነ የኃይል ማመንጫን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ የሚችል የሱፐርፕሮቶኒክ ቅንብር መስራትን ያጠቃልላል፡፡ ሆኖም ይህ ሃሳቧን ተቀብለው የአሰራር ስርዓታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ከመቀየር የታቀቡት የፊውል ሴል አምራቾች የራሷን ቤተ-ሙከራ ተጠቅማ በዓለም የመጀመሪያውን ጠጣር የአሲድ ፊውል ሴል ቁስ አካል እንድትፈበርክ ምክንያት ሆኗት፡፡ ኋላ ላይ ይህን አዲስ ፈጠራዋን የቀድሞ ተማሪዎቿ በንግድ ሰርቶ ማሳያነት የተጠቀመበት ሲሆን ለተመራሪዋም በአረንጓዴ የሃይል ልማት ዘርፍ ዕውቅናን እንድትሸምትበት አስችሏታል፡፡

ፕሮፌሰር ሶስና በአሁኑ ሰዓት ጠጣር ፊውል ሴሎችን በተለይም ለከባቢ ተስማሚ የሃይል ምንጭ መሆን በሚችሉት ላይ አተኩሮ የሚሰራን የምርምር ቡድን በሃላፊነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ቡድን የተለያዩ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ሲገኝ ከቅርብ ስኬቶቹ መካከልም ውሃና ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በቴርሞ ኬሚካል ሂደት አማካኝነት በመጠቀም የፀሐይን ኃይል ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሌላ ምዕራፍን የከፈተ ነበር፡፡ በፕሮፌሰር ሃና እና ቡድኗ እየተሰራባቸው ካሉት ስራዎች ውስጥ ፕሩቶንን አስተላላፊ ጠጣር አሲድ እና ፐሮቭስካይት ኤሌክትሮይቶች፣ የኤሌክትሮን እና ኦክስጅን ድብልቅን አስተላላፊ ፍሎሪት እና ፐሮቭስካይት እንዲሁም ኢ-ስቶይኪዮሜትሪክ ኦክሳይዶችን ማበልፀግ ይገኝበታል፡፡

ይህች ኢትዮጵያዊት እንቁ ተመራማሪ በትልቁ ስሟን ከሚያስጠሩ ስራዎቿ አንዱ ከሆነው የፊውል ሴል ፈጠራዋ በተጨማሪ በሴራሚክ ሳይንስ፣ በኤሌክትሮኬሚካል እና በፋንክሽናል ሶሊድ (electrochemical and functional solids) የደረገቻቸው ምርምሮች እና ያሳተመቻቸው ፅሁፎች በተሰማራችበት የሳይንስ ዘርፍ ከሚኖረው አበርክቶት ባለፈ ለብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ሴት ተመራማሪዎች የሚኖረው ጠንካራ መልእክት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ፐሮፌሰር ሶስና ለሰራቸው ስራና ላበረከተችው የምርምር ውጤት እውቅና የሚሆን ሽልማቶችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያገኘች ሲሆን ከእንዚህ ውስጥም በ1989 በማቴሪያል ሳይንስ ባደረገችው ሰፊ ምርምር ያገኘችው የሃርዲ አዋርድ፣ በ2002 በፊውል ሴል ፈጠራዋ ያገኘችው የኬሚካል ፖይነር አዋርድ እንዲሁም በ2004 በሴራሚክ ሳይንስ ምርምሯ ያገኘቸው የዓለም አቀፍ የሴራሚክ ፕራይዝ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የእውቅና ሽልማቶቿ ናቸው፡፡

ምንጭ፡ ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 15 (ሙሉ መፅሐፉን በዚህ ሊንክ ያገኙታል=http://library.techin.gov.et/web/dl-site/stic-resources/-/document_library/Y9QR0tiVPdYe/view_file/4710001?_com_liferay_document_library_web_portlet_DLPortlet_INSTANCE_Y9QR0tiVPdYe_redirect=http%3A%2F%2Flibrary.techin.gov.et%2Fweb%2Fdl-site%2Fstic-resources%3Fp_p_id%3Dcom_liferay_document_library_web_portlet_DLPortlet_INSTANCE_Y9QR0tiVPdYe%26p_p_lifecycle%3D0%26p_p_state%3Dnormal%26p_p_mode%3Dview%26p_r_p_categoryId%3D672548)