TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ችግኝን እንዴት መትከል እና መንከባከብ ዓለብን
============================
ሰኞ ሐምሌ ፳፪ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ሽር ጉድ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ሆኖም ከመትከል ባለፈ ዘመቻው ውጤት ያመጣ ዘንድ ችግኞቹን በአግባቡ መትከል እና መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ ተከታዮቹን ተግባራት በቅደም ተከተል ማከናወን አለብን፡፡

፩፡ በመጀመሪያ ችግኞቹን የምንተክልበት ጉድጓድ ውስጥ እንደ ድንጋይ እንጨት፣ ቅጠል እና ውሃ ያሉ ባዕድ ነገሮች ካሉ ማውጣት አለብን፤
፪፡ ከጉድጓዱ ተቆፍሮ የወጣውን አፈር ከችግኙ ስሮች ይጣጣም ዘንድ እስከ ጉድጓዱ አጋማሽ ድረስ መልሶ መሙላት ይገባል፤
፫፡ በመቀጠልም ችግኙ ላይ ያለውን ፕላስቴክ አፈሩ ሳይፈስብን በጥንቃቄ በመላጥ ችግኙን እስከ ግንዱ መጀመሪያ ድረስ በጉድጓዱ ማኖር፤
፬፡ ችግኞቹ ተጣመው እንዳይቆሙ በመጠንቀቅ ተቆፍሮ የወጣውን አፈር በፕላስቲክ ተሸፍኖ በነበረው አካል ዙሪያው ጠቅጥቆ መሙላት
፭፡ ከተተከለ በኋላ ውሃ በመጠኑ ማጠጣት (በተለይም አፈሩ ደረቅ ከሆነ)
፮፡ ችግኝ ተሸፍኖባቸው የቆዩትን ፕላስቲኮች በመሰብሰብ በተገቢ ሁኔታ ማስወገድ፡፡

በችግኝ ተከላ ወቅት የሚስተዋሉና መቅረፍ የሚገባን ተደጋጋሚ ስህተቶች
• ችግኝን ከነፕላስቲኩ መትከል፤
• የችግኙ ስር አንዲታይ አድርጎ መትከል፤
• የችግኙን ግንድና ቅጠል ጭምር በጉርጓዱ መቅበር፤
• አፈሩን በትክክል አለመሙላት እና አለመጠቅጠቅ፤
• ችግኙን ሳይተክሉ በጉድጓድ ውስጥ አስቀምጦ ብቻ መሄድ፤
• አጣሞ መትከል፤
• ከአንድ በላይ ችግኝ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ መትከል፤
• የችግኙን ስር አጣሞ መትከል፤
• በውሃ በተሞላ ጉድጓድ ውስጥ መትከል፡፡

ችግኞችንስ ዕንዴት እንንከባከብ?
እንደየ ዝርያ፣ የተተከሉበት አካባቢ እና ወቅት ቢለያይም ችግኞች እስከ ሶስት ዓመታት ድረስ ልዩ እንክብካቤን ይሻሉ፡፡ በዚህም መሰረት ተከታዮቹን መንገዶች ተጠቅመን እንክብካቤን ልንቸራቸው ይገባል፡፡
• ከተተከሉበት ዕለት አንስቶ ችግኞቹን ከሰውና እንስሳት ንክኪ መጠበቅ (ከተቻለ ማጠር)፣ በዙሪያቸው ያለውን አረም፣ ደረቅ ሳር ወዘተ…ማንሳትና ከእሳት መጠበቅ እንዲሁም ከተባይና ነፍሳት ጥቃት በመታደግ ጥበቃ ማድረግ፤
• ብርሃን፣ ውሃና ንጥረ ነገሮችን ስለሚሻሟቸውና ለተባይ መራቢያ ስለሚሆኑ በዙሪያቸው ያለውን አረም ችግኞቹ ከተተከሉ ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ ማንሳት፤
• የሞቱ ችግኞች ካሉ ለይቶ መተካት፤
• ከክረምቱ ማብቂያ አንስቶ መኮትኮት፤
• የተተከሉበት አፈር ለምነት የጎደለው ሊሆን ስለሚችል ጉዝጓዝ፣ ቀልዝ፣ ፍግ ወይም ማዳበሪያ ከበጋው ወቅት ጅማሮ አንስቶ ማድረግ፤
• በበጋው ወቅት ሲገባ ወይም የተተከሉት እርጥበት አጠር ቦታ ሲሆን ውሃ ማጠጣት፤
• መመልመልና ማሳሳት፡፡

መልካም የተከላ ጊዜ እንዲሆንልዎ ተመኘን!!!
ተልዕኮው ተሳካ፤ እኛም የድርሻችንን ተወጣን !!!
==============================
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢኒትቲትዩት ሰራተኞች የችግኝ ተከላን በጋራ አከናወነዋል፡፡ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በስሩ የሚገኙ ሌሎች ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ጨምሮ በተሳተፉበት በዚህ ስነ-ስርዓት ከአዲስ አበባ 75 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የአለልቱ ወረዳ በጠቅላላው 17887 ችግኞች ለመትከል ተችሏል፡፡
አግኝተን ያነጋገርናቸው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታው ዶ/ር ጀማል በሽር ይህ ሐገር ዓቀፍ የችግኝ ተከላተ በጋራ ከተሰራ በሐገር ላይ ዕድገትን ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ሲናገሪ የችግኝ ተከላው የተከናወነበት ስፍራም ከመሐል ከተማ መራቁ የገጠሩን ኑሮ ለመገንዘብ ድርብ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ችግኞቹን ከመትከልም ባለፈ የመንከባከብ ተጋባራት በቀጣይነት አንደሚከናወኑ ጠቁመው አልፈዋል፡፡
ይህ የችግኝ የመትከል ስነ-ስርዓት ከላይ ከተጠቀሱት ተቋማትም በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የተከበረው ምክር ቤታ ዓባላትም ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡
የማርጀት ሚስጥር ታወቀ

በሳውዝ ካሊፎርኒያ ኢንጂነሪንግ ዩኒቨርስቲ በሁለት የኬሚካል እና የማቴሪያል ኢንጂነሪን ረዳት ፕሮፌሰሮች የሚመራው ቡድን አማካኝነት የሴሎችን የማርጀት ሚስጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የማቴሪያል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰሩ ግራሃም እንዳለው የወጣትንትን ምንጭ ለመቅመስ ወጣትንትን እና ሁኔታውን መመርመር የሚመረጥ በሆንም እኛ ግን በተቃራኒው እርጅናን በመመርመር እርጅናን በትክክለኛ መንገድ ማከም መርጠናል፡፡
ይህም ጥናቱ ሴሌች እንዴት እንደሚያረጁ በመረዳት የሚሰራ ሲሆን ሴሎች በምን ምክኒያት እንደሚያረጁ ከታወቀ ያንን ማስቆም እና የተራዘመ እርጅናን ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
ጥናቱ ሴሎች እራሳቸውን መተካት የሚያቆሙበትን እርከን በማጥናት የተጀመረ ሲሆን እዚህ እርከን ላይ እንደ አንጓ ብግነት፣ የአጥንት መሳሳት እና የልብ መድከም የመሳሰሉት የእርጅና ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡
ሴንሴት ሴል በሴል ኡደት ውስጥ የመጨረሻው የሴል ደረጃ ነው፤ ማለትም ሴሎች ሴሎች እራሳቸውን ለመተካት ሲሉ የማይከፈሉበት ደረጃ ማለት ነው፡፡ ይህ የጥናት ቡድን ግን ከዚ አንድ ደረጃ ከፍ በማለት ስለዚህ የሴል ዑደት እርከን አዲስ ነገር ለማወቅ ችሏል እሱም ሴሌች የሴንሴት የሴል ዑደት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ኒውክሎታይድ የተሰኘውን የኬሚካል ዓይነት ማምረት ያቆማሉ፡፡
ኒውክሎታይዶች ለ ዲ.ኤን.ኤ ምስረታ እንደ መሰረተ ዲንጋይ የሚየገለግሉ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ስለዚህ ሴል ኒውክሎታይድን ማምረት ሲያቆም ዲኤንኤ መሰራት ስለሚቆም እርጅና ይከሰታል፡፡ ስለዚህ ትላለች የምርምር ቡድኑ ተጠሪ ዴልፋራህ ሴሎች ኒውክሎታይድን ማምረት እንዳያቆሙ ማድረግ ከተቻለ ሰዎች የሚያረጁበትን እድሜ ወደዛ መግፋት ይቻላል፡፡
ይሁንና ሴንሴት ሴል ባለሁለት ስለት ሴል ነው፤ ማለትም በአንድ በኩል ሰውነታችን በካንሰር እንዳይጎዳ የሚረዳ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እርጅና እንዲከሰት ምክኒያት ነው ያሉት ሳይንቲስቶች ሴንሴት ሴል ሳይጎዳ ኒውክሎታይድን ብቻ ማረት የማያቆምበትን መንገድ ለመፍጠር እንድንችል ዘንድ ከባድ የሆነ ምርምር እና ጥናት ልናደርግ ይገባና ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡- ScienceDaily
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩትን በቴክኖሎጂው መስክ ለማገዝ ቃል ገቡ ***************************************** **********************************
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከአሜሪካ እና ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ከተወጣጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በቴክኖሎጂና መሰል ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስአቶ የሚያስችሉ ውይይቶችን አድርጓል፡፡ በወይይቱ መጀመሪያ ላይ ስለተቋሙ እቅድና አጠቃላይ ዓላማ ገለፃ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዱካን ደበበ፤ በውጭ ሃገር ኑሮቸውን ካደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር መስራት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው አንስተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ የመንግስትን አሰራር የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ እየሰራ ከመሆኑ አኳያ እና የጥናትና ምርምር እንዲሁም የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዋና ስራዎቹ ከመሆኑ አንፃር፤ የትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ እንደሚሆን አበክረው ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኢንስቲትዮቱ አቅሙን ለማጎልበት እንዲችል እና ተልኮውን በሚገባ ለማሳካት እንዲችል ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በትውልደ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው ‘ተስፋ’ የባለሙያውች ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ደረጀ ተሰማ (ዶ/ር) በተለዩትመስኮች ድጋፍ ለማድረግ የሚያግዝ የባለሙያዎች ብድን በማቋቋም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርጉ በውይይቱ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡
አለምአቀፉን የጠፈር ጣቢያ በጥቂቱ
International Space Station (ISS)
********************************
አለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (ISS) እጅግ ውስብስብ እና በታሪክ የሰው ልጆች የሚገርም የላቀ የአስተሳሰብ ጥበባቸውን ተጠቅመው የሰሩት እጅግ ግዙፍ የምህንድስና ውጤት የሆነ ህዋ ላይ የሚንሳፈፍ የምርምር ማእከል ነው። ይሄ በራሪ ሳተላይት አሁን ላይ ሆነን የምንሰማቸውን አዳዲስ የጠፈር ሳይንስ ግኝቶች ያስገኘ እና እያስገኘም ያለ ላቦራቶሪ እና ጂኦሎጂካል ምርምሮች የሚካሄዱበት ግዙፍ ተቋም ነው። ISS በአማካኝ ከምድራችን በ 400 ኪሎሜትሮች ከፍታ ላይ ይጉዋዛል። ምድርንም አንድ ግዜ ዞሮ ለመጨረስ 90 ደቂቃ ብቻ ይፈጅበታል፤ ይህም የሆነው ISS በሰአት 28,163ኪ.ሜ የመብረር ፍጥነት ስላለው ነው።
ማእከሉ በአንድ ቀን ውስጥ የሚጉዋዘው ርቀት ቢደመር ከምድር እስከ ጨረቃ ደርሶ ለመመለስ የሚፈጀውን ርቀት ይሆናል። ይህ የሚያሳየው ISS ህዋ ላይ እጅግ በጣም ፈጣን ጉዞ እንደሚያደርግ ነው። ISS ጥርት ባለ ጨለማ ሰማይ ላይ ከፕላኔት ቬኑስ ይልቅ ደምቆ ያለማጉያ መነፅር ይታያል። ነገር ግን በፍጥነት ስለሚጉዋዝ ወስን ቦታ አይኖረውም፤ በመሆኑም ISSን ሰማይ ላይ ለማየት የረጅም አመት ልምድ እና መቼ የቱ ጋር ማየት እንዳለብን ማወቅ ያስፈልጋል። ይሄን ግዙፍ ማእከል ለመስራት በስራቸው 15 ሀገራትን ያቀፉ 5 ሀገራት ተሳትፈዋል። የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (NASA)፣ የአውሮፓ፣ የካናዳ፣ የሩሲያ እና የጃፓን የጠፈር ምርምር ተቋማት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ሙሉ ማእከሉን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 100 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር ፈጅቱዋል።
ISS በአጠቃላይ 391ቶን ወይንም 391,000ኪ.ግ ይመዝናል። ይህን የሚያህል ክብደት ያለው ነገር ወደጠፈር ይዞ መውጣት አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የማይቻል በመሆኑ ተመራማሪዎች ማእከሉን ወደ 7 ንኡስ በመክፈል ሊወስዱት ችለዋል። በመሆኑም የመጀመሪያውን ንኡስ ማእከል የሆነችውን የሩስያዋን 'ዛራያ' እ.ኤ.አ በ1998 ወደጠፈር እንድትመጥቅ ተደረገ። ዛራያ ለ 2 ሳምንታት ያህል በጠፈር ላይ በምህዋር ስትንሳፈፍ ከቆየች ቡሀላ አሁንም ሩስያ ሰራሹዋ 'የኒቲ' እንድትመጥቅ ተደርጎ ከዛራያ ጋር ጠፈር ላይ በተመራማሪዎች ተገጣጥመው ወጥ ሆኑ። ሁለቱ ብቻ በምህዋር ላይ ለአመት ከመንፈቅ ያክል ሲዞሩ ቆይተው እ.ኤ.አ በ2000 ሌላኛዋ 'ዚቬዝዳ' የተባለችዋ ንኡስ ማእከል ተልካ ተገጥማለች። በመቀጠልም 'ዴስቲኒ' እ.ኤ.አ በ 2001፣ የጃፓን የምርምር ማእከል በ 2009 እና ሌሎችም ንኡሳን ማእከላት ወደጠፈር በመምጠቅ እና እርስ በእርሳቸው በመገጣጠም መሉ ማእከሉ ተሰርቶ ሊያልቅ ችሉዋል።
ማእከሉን በፎቶዎች ስናየው አንሶ ታይቶን ይሆናል። ነገር ግን የፀሀይ ብርሀን መሰብሰቢያ ክንፉን ጨምሮ ስፋቱ አንድ የእግር ኳስ ስታዲየም ይክላል፡፡ ISS በውስጡ ሳሎኖች፣ 2 መታጠቢያ ከፍሎች፣ ጂምናዚየም እና የተመራማሪዎቹ የስራ ቦታ ላቦራቶሪ አለው። ለግዜው በውስጡ መያዝ የሚችለው የተመራማሪዎች ቁጥር 6 ሲሆን ይህ ቁጥር ከግዜ ወደግዜ አዳዲስ ንኡሳን ማእከላት ሲጨመሩ አብሮ ይጨምራል። እነዚህ ንኡሳን ማእከላት በየጊዜው ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይዘው ነው የሚሄዱት። በቅርቡ 3Dprinter፣ የጨረር ግንኙነት መሳሪያ እና ያሉት ማእከሉ ላይ የሚገጠሙ ተወንጫፊ የምርምር ሳተላይቶችን የያዙ ንኡሳን ማእከላት ተልከዋል። እነዚህን ማእከላት በከፊል የሚቆጣጠሩት ISS ላይ ያሉት ተመራማሪዎች ሲሆኑ ገሚሱን ደግሞ ምድር ላይ ያሉ ተመራማሪዎች ይቆጣጠራሉ።
ምንጭ፡ Airtable universe እና E.As
ከቁልቋል ጭማቂ ፕላስቲክ መስራት የቻለቸው ተመራማሪ
*****************************************
**********
አብዛኛውን ጊዜ በቤተ ሙከራ የሚደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች በሚሊዮን እና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘብ የሚፈስባቸው ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን እጅግ ቀላል በሚባል ወጪ አስገራሚ የምርምር ውጤቶች ሲሰሩ ይታያል፡፡ እነዚህ ምርምሮች ቀላል ወጪ ይውጣበቸው እንጂ እጅግ ከፍተኛ የምርምር ሂደት ተከናውኖባቸው የሚሰሩ ናቸው፡፡
ታዲያ በቅርቡ በሜክሲኮ ሃገር በአንዲት ወጣት ተማራማሪ የተሰራው ሳይንሳዊ ግኝት ካላይ ያነሳነውን ሃሳብ የሚደግፍ ይመስላል፡፡ በሃገሪቱ በሚገኘው ቫሊ ኦፍ አቴማጃክ ዩኒቨርስቲ የኬሚካል ምህንድስና ፕሮፌሰር የሆነቸው ይህች ወጣት ተመራማሪ አስገራሚ ሊባል በሚችል የቤተ ሙከራ ምርምር ከቁልቋል ጭማቂ ባዮዲግሬደብል (biodegradable) የሆነ የፕላስቲክ ቁስ ማውጣት ችላለች፡፡
ሳንድራ ፓስኮይ ኦርቲዝ የተባለችው ይህች ተመራማሪ በሃገሪቱ ታዋቂ የሆነውን የቁልቋል ተክል ጭማቂ በመውሰድ glycerol እና colorants ከተሰኙ ውህዶች ጋር በመቀየጥ ከባዮፕላስቲክ የሚመደብ ቁስ ማግኘት የቻለች ሲሆን ግኝቱም ምንም ተቀጣጣይነት የሌለው እና እንደ ዓሳ ያሉ የውሃ ውስጥ ፍጥረታት ቢመገቡት አንዳች የጎንዮች ጉዳት እንደማይኖረው ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ በአለማችን በስፋት በመተግበር ላይ ያለው ነዳጀን መሰረት ያደረገ የፕላስቲክ ምርት ለውቂያኖሶች እና ለተለያዩ የውሃ አካላት ስነ ምህዳራዊ ሚዛን መናጋት ትልቅ ምከንያት ከመሆኑ አኳያ፣ እንደ ባዮዲግሬደብል ያሉ የፕላስቲክ አይነቶች እጅግ አስፈላጊ መሆናቻውን የሚጠቅሱት የዘርፉ ባለሙያዎች ከቁልቋል ጭማቂ የተገኘው ይህ አዲስ የምርምር ግኝትም እጅግ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡
ምንጭ፡ Natural Blaze
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ ከተወጣጡ የቴክኖሎጂ አካላት ጋር በኤይሲቲ እና መሰል ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ አካሄደ
*****************************************
***************
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት በግሉ ዘርፍ ተሰማርተው እንቅስቃሴያቸውን በኤይሲቲ እና መሰል የቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ካደረጉ የተለያዩ ኩባንየዎች እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በአይሲቲ ዘርፍ ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ በተዘጋጃው የውይይት መድረክ ላይ እንደመነሻ ሃሳብ የሚሆኑ ጉዳዮች ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት በመጡ ተወካዮች የቀረቡ ሲሆን፤ በዋናነትም በስራ ዕድል ፈጠራ እና በአይሲቲ እንቅስቀሴ ላይ የውይይት መነሻዎች ቀርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ እጅግ ከፍተኛ ልምድ ካለቸው የዘርፉ አንቀሳቃሾች ጀምሮ እስከ ወጣት የሶፍተዌር አበልፃጊዎች ድረስ የተለያዩ የቴክኖሎጂ አካላት ሲሳተፉ ሰፊ ማብራሪያ የሚስፈልጋቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም ከተሳታፊዎች ሊነሳ ችሏል፡፡ ውይይቱ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው አንኳር ሃሳቦች መካከልም የአይሲቲ ፓርክ ሁኔታ እና በአገር ደረጃ በተደጋጋሚ ሲስተዋል የነበረው የኢንተርኔት መዘጋት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በተጨማሪም የፖሊሲ ማሻሻያ የሚጠይቁ እና የአሰራር ለውጥ የሚያስፈልጋቸው የቢሮክራሲ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡
በተሰጡ አስተያየቶች መሰርትም ከቡር ሚኒስቴሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ጨምሮ የአይሲቲ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ዶክተር አህመዲን መሃመድ ለተነሱ ጥያቄዎችሲሉም ማብራሪያ ለመስጠት የሞከሩ ሲሆን ችግሮቹም እንደሃገር የምንጋራቸው ከመሆናቸው አኳያ ሁላችንም የመፍትሄው አካል ልንሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በወይይቱ መጨረሻ ላይ ከተሳታፊ አካላት የተወጣጡ 11 የኮሚቴ አባላት የግል ዘርፉን በመወከል የትብብር ስራዎችን ለመስራት የተሾሙ ሲሆን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋርም በጋራ በመሆን በፖሊሲ ግብዓቶች እና በማማከር ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ታውቋል፡፡
አዲሶቹ የኢቦላ መድኃኒቶች ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል
**********************************************
የኢቦላ በሽታ ለረዥም ዓመታት መድሃኒት ሳይገኝለት የቆየ እና በገዳይነቱም እጅግ ፈጣን ከሚባሉት የበሽታ አይነቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚሰለፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሽታው ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተስፋፍቶ የብዙ ምስኪኖችን ህይወት ሲያጠፋም እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ2018 ሚያዚያ ወር ላይ ብቻ ተከስቶ ከ1,400 በላይ የሃገሪቱ ዜጎችን የቀጠፈበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡
በሽታው በእነዚህ አመታት ሁላ ከፍተኛ የመከላከል ሂደት ሲደረግበት እና የተለያዩ የምርምር ስራዎች ሲካሄዱበት የቆዩ ቢሆንም በስኬት ደረጃ ይህ ነው የሚባል ግኝት እንዳልነበረ በተደጋጋሚ የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡ ይሁንና በ2018 መጨረሻ ዓመት ላይ ክፍተኛ ምርምር ሲደረግባቸው ከነበሩት አራት የመከላከያ መድሃኒቶች ውስጥ ሁለቱ ትልቅ ተስፋ በማሳየታቸው ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መደረጋቸውን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መቀመጨውን ያደረገ የምርምር ማዕከል ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህ ሁለት የመድሃኒት አይነቶች በዋናነት በደም ውስጥ በሚፈጠር የፀረ ባክቴሪያ ስሪት ወይም (antibodies) አማካኝነት የሚሰሩ የመከላከያ መድሃኒቶች ሲሆኑ Regeneron በሚባለው የመድሃኒት አምራች ድርጅት እና በሃገሪቱ በሚገኝ የብሄራዊ ጤና ኢኒስቲትዩት አማካኝነት መሰራታቸው ታውቋል፡፡
እንደሚታወቀው በኢቦላ ቫይረስ የተያዘ ሰው በፍጥነት ህክምና ካለተደረገለት 75 በመቶ ህይወቱን እንደሚያጣ በተደረጉ ምርምሮች ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አኳያ እነዚህ ሁለት መድሃኒቶች በሽታው ብዙም ባልፀናበት ሰው ላይ ከ80 እስከ 90% በሽታውን ለመከላከል በመቻላቸው እስከዛሬ ከተሰሩት እንደ ZMapp ካሉ የመድሃኒት አይነቶች ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ነግር ግን ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃው ሰው መድሃኒቶቹን እየተጠቀመ እንኳን 30 በመቶ የመሞት እድል እንደሚኖረው የምርምሩ አካላት አስታውቋል፡፡
ይሁንና እስካሁን ከነበረው የመከላከል አቅም አንፃር ከፍተኛ ስኬት መታየቱን የተናገሩት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሄራዊ የጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጃኪዩስ ሙዬምቤ የብዙ ሺዎችን ህይወት የሚታደግ የኢቦላ መድሃኒት አግኝተናል ማለት ይቻላል ብለዋል፡፡
ምንጭ፡ big think.com
የ8 ዓመቷ ህፃን በአስገራሚ ፈጠራዋ መነጋገሪያ ሆናለች
*****************************************
********
የሜክሲኮ ተወላጅ የሆነቸው የስምንት ዓመት ህፃን ሾቺየል ክሩዝ የሶላር ኢነርጂን በመጠቀም የሰራቸው የውሃ ማሞቂያ ቴክኖሎጂ አለምን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ይህች ህፃን ገና ከአራት ዓመቷ ጀምሮ ለሳይንስ ያላት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ በሃገሪቱ በሚገኝ ልዩ ችሎታ ያላቸው የህፃናት ማሳደጊያ እንድትገባ ተደርጋለች፡፡
ህፃኗ በዚህ የማሳደጊያ ፕሮግራም ከታቀፈች በኋላ ከሷ ሊጠበቁ የማይችሉ ፈጠራዎችን ስትሰራ የ የቆየች ሲሆን ለማበረታቻ የሚሆኑ የተለያዩ ሽልማቶችንም ከተቋሙ አግኝታለች፡፡ ሾቺየል ይህን የፈጠራ አቅሟን አሳድጋ በ8 ዓመቷ የሰራቸው የውሃ ማሞቂያ ቴክኖሎጂ ደግሞ ከማሳደጊያ ተቋሙ አልፎ በሀገሪቱ በሚገኝ የኒውክለር ሳይንስ ኢኒስቲትዩት ውስጥ ሽልማት እና አውቅናን አስገኘቶላታል፡፡
ቺያፓስ ተብሎ በሚጠራ በደቡባዊ ሜክሲኮ በሚገኝ ትንሽ የድሃ መንድር የምትኖረው ሾቺየል ቴክኖሎጂውን ለመስራት ምን አነሳሳሽ ተብላ ለቀረበላት ጥያቄ አንዳለቸው “በሰፈራችን የሚኖሩ ሰዎች የውሃ ማሞቂያ ቴክኖሎጂ ስለሌላቸው ብቻ ዛፎችን በመቁረጥ የከባቢ አየር ሁኔታን መጉዳታቸው ስለቴክኖሎጂው እንዳስብ አድርጎኛል ስትል ተደምጣለች፡፡” ቴክኖሎጂውን ለመስራት አባቴ ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል ያለቸው ሾቺየል ለወደፊቱም ትልልቅ ፈጠራዎችን ለማበርከት እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡
በሶላር ሃይል የሚሰራው የውሃ ማሞቂያ ቴክኖሎጂ መልሶ መላልሶ ጥቅም ላይ በሚውል የተለያየ ቁስ ተዋቅሮ የተሰራ ሲሆን ለሙከራ እንዲሆን በማሰብም በቤታቸው ጣራ ላይ ተገጥሞ ቀዝቃዛ ውሃን ወደ ሙቅ ውሃ በመቀየር እየተገለገሉበት ይገኛል፡፡
ምንጭ፡ Truth Theory

እውቀቶን የሚያሳድግ፣ የሚያስተምር እና የሚያዝናና መሰል የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ለማግኘት እንዲችሉ የዩቲዩብ እና የፌስቡክ አድራሻችንን ይጎብኙ
https://www.youtube.com/channel/
UC6jvUOLRSkVEQtc5Annfwvg

https://m.facebook.com/TechinEthiopia/?ref=opera_speed_dial&_ft_=mf_story_key.2364169170357821%3Atop_level_post_id.2364169170357821%3Atl_objid.2364169170357821%3Acontent_owner_id_new.563821287059294%3Athrowback_story_fbid.2364169170357821%3Apage_id.563821287059294%3Aphoto_id.2364154333692638%3Astory_location.4%3Astory_attachment_style.photo%3Apage_insights.%7B%22563821287059294%22%3A%7B%22page_id%22%3A563821287059294%2C%22actor_id%22%3A563821287059294%2C%22dm%22%3A%7B%22isShare%22%3A0%2C%22originalPostOwnerID%22%3A0%7D%2C%22psn%22%3A%22EntStatusCreationStory%22%2C%22post_context%22%3A%7B%22object_fbtype%22%3A266%2C%22publish_time%22%3A1566461596%2C%22story_name%22%3A%22EntStatusCreationStory%22%2C%22story_fbid%22%3A%5B2364169170357821%5D%7D%2C%22role%22%3A1%2C%22sl%22%3A4%2C%22targets%22%3A%5B%7B%22actor_id%22%3A563821287059294%2C%22page_id%2C2%3A563821287059294%2C%22post_id%22%3A2364169170357821%2%22role%22%3A1%2C%22share_id%22%3A0%7D%5D%7D%7D%3Athid.563821287059294&__tn__=%2Cg