TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ኢትዮጵያዊው የአዕምሮ ጤና ምሁር በሀርቫርድ ተሸለሙ
====================
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይካትሪ ምሁር ሆነው እያገለገሉ ያሉት ፕሮፌሰር አታላይ አለም የ2019 የሀርቫርድ Psychiatric Epidemiology and Biostatistics አዋርድ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ይህ ሽልማት የተበረከተላቸው በሳይካትሪ ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ባበረከቷቸው በጎ አስተዋፅዖዎች አማካኝነት ነው፡፡
ፕሮፌሰር አታላይ የቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ በሳይካትሪስት እና ሜዲካል ዳይሬክተርነት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ኮሌጅ በዋና ዳይሬክተርነት እና ሌሎች ኃላፊነቶች ላይ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ መሰል እውቅናና ሽልማቶችን ለመጎናፀፍ አዲስ ያልሆኑት እኚህ ኢትዮጵያዊ ምሁር ከአሜሪካኑ የቴዎዶር እና ቫዳ ስታንሌይ ፋውንዴሽን ሰርተፊኬት ሲበረከትላቸው በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ላከናወኑት የትምህርት፣ አገልግሎት ብሎም ጥናትና ምርምር ተግባራት ደግሞ የሮበርት ግሬል አዋርድን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ይህ አዋርድ በህይወት ዘመናቸው በሳይካትሪክ ኤፒዲሚዮሎጂ ወይም ባዮስታትስቲክስ ዙሪያ ከፍተኛ አበርክቶዎችን ላደረጉ የዘርፉ ምሁራን በየዓመቱ የሚሰጥ ሲሆን አሸናፊዎችም ወደ ቦስተን በማምራት ለሳይንሱ ዓለም ታዳሚዎች ሌክቸር እንዲያቀርቡና በተለያዩ ዝግጅቶችም ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
የኢትዮጵያን 50 በመቶ የዘይት ፍላጎት ያሟላል የተባለው ፋብሪካ ሊጠናቀቅ ነው
****************************************************
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለምርት የሚቀርበው የቅባት ዘር እና የምግብ ዘይት አቅርቦት በሃገሪቱ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት ጋር ያልተመጣጠነ በመሆኑ በየጊዜው ቀላል ሊባል የማይችል የውጭ ምንዛሬ ወደ ሌሎች ሃገራት በግዢ መልክ እንደሚወጣ ይታወቃል፡፡ በሃገሪቱ ያሉት አብዛኞቹ የምግብ ዘይት ማቀናበሪያ ፋበሪካዎች በአነስተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸውና የግብዓት አጠቃቀም ሰንሰለታቸው በሚገባ ያልተጠናከረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጥራት ችግር እንዲነሳባቸው እና ለሌሎች ተያያዥ እክሎችም በር እንዲከፍቱ አስገድዷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በየጊዚያቱ ወደ ዘርፉ የሚቀላለቀሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች በአንስተኛ ደረጃም ቢሆን ቁጥራቸው እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን ከሰሞኑም በአማራ ክልል በመጠናቀቅ ላይ ያለው የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ከእነዚህ ውስጥ እንደአንዱ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ይህ አዲስ ፋብሪካ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ ውስጥ በ30 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን ከ2,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ እድል እነደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ሙሉ ለሙሉ እየተጠናቀቀ መምጣቱን እና የተለያዩ የማሽነሪ ግብዓቶች እየተሟሉለት እንደሚገኝ የሚናገሩት የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዳኛቸው ዋሴ በጠቅላለውም ለኢንቨስትመንት ወጪው ከ2.1 ቢሊዮን ብር ባላይ መፍጀቱን ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካው የዘይት ምርቱን ለማስኬድ የሱፍ አበባ እና የሶያ ቢን ግብዓቶችን በዋናነት እንደሚጠቀም የተናገሩት ኢንጅነሩ፤ እንደመነሻም 1,400 ቶን የሚጠጋ የምግብ ዘይት በየቀኑ ለማምረት የሚስችል አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካው ምርታማነትን በማሳደግ እና የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማዘመን በኩል በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ከ50 በመቶ በላይ ለሚሆነው የሃገሪቱ ህዝብ በቂ የምግብ ዘይት ለማቅረብ የሚስችለውን አቅም እንደፈጠረ ተነግሯል፡፡

ፋብሪካው በአግሮቢዝነስ እና ሌሎች ተያያዥ የስራ ዘርፎች ላይ በሰፊው እየሰራ በሚገኘው ቢ.ኬ ቢዝነስ ግሩፕ የሚከናወን ሲሆን በጥቂት አመታት ውስጥም በምግብ ዘይት አቅርቦት ዙሪያ የሚወጣውን ከፍተኛ የወጪ ምንዛሬ እንደሚያድን ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡ SNV እና New Business Ethiopia
የሳይንስ ማዕከል በአዲስ አበባ ተከፈተ
=================
ህፃናት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ያላቸውን አቅም የሚያሳድግ ማዕከል በኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ተገንብቶ ዛሬ ተመርቋል፡፡ ከስቴም ሲነርጂ ጋር በመተባበር የተገነባው ማዕከሉ የተለያዩ የሳይንስ ዘርፎችን ያካትታል፤ ለጊዜውም ሁለት የኤሌክትሮኒክስ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራዎችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡
በምርቃት ስነ-ስርዓቱ የኢትዮያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማስረሻ እንዲሁም የሳይንስ ማዕከለሉ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንግዳወርቅ በሳይንስ አካዳሚው እና የሳይንስ ማዕከላት ዙሪያ ለእንግዶች ገለፃ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የክብር እንግዳው ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ሳይንስን ከንባብ በዘለለ ወደ ተግባር ስራ እንደሚለውጥ በማመላከት ማዕከሉን ግንባታ አድንቀዋል፡፡
መሰል የሳይንስ ማዕከላት በስቴም ሲነርጂ አማካኝነት በመላው ሐገራችን 14 ስፍራዎች ተከፍተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አብዛኛው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተያይዘው የተገነቡ ናቸው፡፡ በቀጣዮቹ ጊዜያትም ሀረማያ እና ቀብሪደሃርን ጨምሮ በሰባት የሐገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ማዕከላቱን እንደሚገነባ የስቴም ሲነርጂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ለገሰ ተናግረዋል፡፡
ዛፍን መትከል እንደዋነኛ የመፍትሄ አማራጭ መውሰድ ይገባል፤ ጥናት። =======================
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የዛፍ ተከላዎች በመረግ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን እንኳን ብናይ ከሁለት ዛፍ ለሁለት ሺህ አንስቶ እስከ አሁኑ የአራት ቢሊዮን ዕፅዋት ተከላ መርሀ ግብር ያለውን እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሆኖም በግቡ ውጤታማነት ላይ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆየተተዋል፡፡
ከቀናት በፊት የወጣው ጥናት ለዚህ በጎ ምላሽ የሚሰጥ ሆኗል፡፡ እንደጥናቱ ከሆነ ዕፅዋት በተገቢው አፈር ላይ ከተተከሉ 205 ጊጋ ቶን የሚሆን የሚሆን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በሚቀጥሉት ከ40 እስከ መቶ ዓመታት ውስጥ መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ ይህን አሀዝ ለንፅፅር ስናቀርበው የሰው ልጆች ከኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት አንስቶ ካመነጨነው ሁለት ሶስተኛው ጋር የሚስተካከል ነው፡፡ በተጓዳኝም በእጅጉ እየተጎዳ የሚገኘውን የዓለማችን ስነ-ምህዳር ይጠገናል፡፡
ጥናቱ 80,000 የሳተላይት ምስሎችን በመሰብሰብ የመረመረ ሲሆን ምድራችን ምን ያህል ዕፅዋትን፤ በየትኛው ስፍራና የአየር እንዲሁም አፈር ሁኔታ ማቀበል እንደምትችልም ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የተገለጸውን ውጤት ያስገኝ ዘንድ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ቆዳ ስፋት ዘጠኝ እጥፍ በሚበልጥ መሬት ላይ ዕፅዋትን መትከል እንደሚቻልና እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም ተከላው ከወዲሁ መቀላጠፍ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ እየጨመረ በሚመጣው የዓለም ሙቀት አማካኝነት የሚከሰቱት ድርቅ እና የዛፎች አተነፋፈስ ለውጥ የዛፎቹን ዕድገት ሊገታ ይችላል፡፡
ሆኖም መንገዶች አልጋ በአልጋ አይሆኑም፡፡ ወደፊት እንደሚያጋጥሚ ከሚጠበቁ ችግሮች ውስጥ አንዱ የዋጋው ጉዳይ ነው፡፡ ዛፎችን በዚህ መጠን መትከል በትንሹ 300 ቢሊዮን ዶላርን ይጠይቃል፤ ምንም እንኳን እንደቡድኑ ግምት ከሌሎች የካርበን መምጠጫ መንገዶች አንፃር ርካሽ እንደሆነ ቢነገርም፡፡
ታድያ እርስዎስ ስንት ዛፎችን በዚህ ክረምት ስንት ዛፎችን ተክለዋል፤ ስንረትስ ለመትከል ዕቅድ ይዘዋል፡፡
ምንጭ፡ Scientific American
ክፍት የሥራ መደብ ማስታወቂያ
=================
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በሥሩ በሚገኙት ሦስት ማዕከላት ላሉ የምርምር ዳይሬክቶሬቶች ከዚህ ቀጥሎ በተዘረዘሩት የስራ መስኮች ላይ ባለሙያዎችን አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለሙያዎች እንዲያመለክቱ ይጋብዛል፡፡
ማሳሰቢያ፡-
• ተወዳዳሪዎች ማሟላት ያለባቸው፡-
• ለሚወዳደሩበት የሥራ መደብ ማመልከቻ/Application Letter/፣ካሪኩለምቪቴ(CV)፣ የተሟላ የትምህርትና የሥራ ልምድ የThesis/Dissertation እና የሌሎች ሕትመቶች Abstract፣ አያይዘው መላክ ይኖርባቸዋል፤ በተጨማሪም ስልክ ቁጥር እና ኢሜይል በማመልከቻቸው ላይ መግለጽ ይኖርበታል፡፡
• የምዝገባ ሁኔታ በOnline http://www.techin.gov.et/am/web/sticsite/techin12
ብቻ ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በኢሜል Vacancy@techin.gov.et አያይዘው መላክ ይኖርባቸዋል፤
• ሴት ተወዳዳሪዎች እንዲያመለክቱ ይበረታታሉ፤
• ለፈተና የሚቀርቡትን ተወዳዳሪዎች በአድራሻቸው የምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን::
• ተቋሙን የተመለከቱ ተጨማሪ መረጃ ቢያስፈልግ የፌሥቡክ አድራሻችን Technology and Innovation Institute, Ethiopia ወይም የኢንስቲትዩቱን ድረ-ገፅ
www.techin.gov.et በመጠቀም ማግኘት የሚቻል መሆኑን እንገልፃለን::
መልካም ተስፋ ለኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞች
============================
ናትናኤል ታከለ ይባላል፤ ወጣት የፈጠራ ባለሙያ ሲሆን እጅግ ለአጠቃቀም ቀላል እና ዘርፈ ብዙ ጥቅምን የምትሰጥ የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪን ሰርቶ ያቀረበ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ተሸርካሪዋን በራሱአቅም ሰርቶ ያቀረባት ሲሆን እስከ 80 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደትን ተሸክማ ከፀሐይ በምታገኘው ኃይል አማካኝነት ትንቀሳቀሳለች፡፡ በተለያየ አቅጣጫ ይመራት ዘንድ ጆይስቲኮች ተገጥመውላታል፡፡ እነዚህን ጆይስቲኮች ተጠቅመው መገልገል ለማይችሉም ቢሆን በብሉቱዝ አማካኝነት ካሉበት ቦታ ሆነው በስልካቸው ሊቆጣጠሯት ይችላሉ፡፡ የተሰራላት የአንድሮይድ መተግበሪያ (አፕ) ታድያ ይህን በማስተናበር ረገድ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ተሸከርካሪዋ በሰዓት እስከ 20 ኪ.ሜ መጓዝንም ትችላለቸው፡፡ በህዝብ ጎዳናዎች ላይም ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ አሳፍራ ለመንቀሳቀስ በሚያስችሏት መሳሪያዎች የተሞላች ናት፡፡

ስለ ወጣቱ እና አስደናቂ ፈጠራው ሙሉውን ለማወቅ በመቅርጸ ምስላችን ካስቀረነው ተንቀሳቃሽ ምስል እንካችሁ ብለንዎታል፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=Oh-7QdiCEUQ&t=29s
ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!!
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ሰራተኞች ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበርን ጎበኙ
***************************
የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ሰራተኞች በዛሬው ዕለት ሽሮ ሜዳ በሚገኘው ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር በአካል በመገኘት ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡ የተቋሙ ሰራተኞች ይህን ድጋፍ ያደረጉት የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን በሚያከናውነው የሶሻል ኮሚቴ አማካኘነት ሲሆን፤ ይህም ኮሚቴው ከሚሰራቸው መሰል ተግባራት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡
የኢኒስቲትዩቱ ሰራተኞች ይህን ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት የማህበሩ አባላት ስለጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር አንዳንድ ገለፃዎችን ያደረጉላቸው ሲሆን በድጋፍ ሂደቱም በአጠቃላይ ለዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚውሉ የተለያዩ ቁሳ ቁሶችን ረድተዋል፡፡
ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት ከ2003 ጀምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኘ ማህበር ሲሆን በስሩም እጅግ ብዛት ያላቸው የአእምሮ ህሙማን እንደሚረዱ ይታወቃል፡፡
“ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል
በማለት ሰለሞን ቀድሞ ተናግሮታል
ሳትደፈር ኖራ ጨረቃም እርቃ
በሰው ተፈተነች ጊዜዋን ጠብቃ”
======================

የትዝታው ንጉስ ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ይህን ስንኝ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ባቀነቀነው ዘፈኑ ውስጥ አካቶ ተጫውቶት ነበር፡፡ ታድያ ይህ የጊዜን ሃያልነት የሚያወሳው የታላቁ ሰው ስራ ለአድማጭ ጆሮ ከመብቃቱ ጥቂት ዓመታትን አስቀድሞ የሰው ልጅ ሚሊኒየሞችን በሚዘልቀው የስልጣኔ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን በእግሮቹ ለመርገጥ ችሎ ነበር፡፡ አሜሪካዊያኑ የህዋ ተመራማሪዎች ኒል አርምስትሮንግ፣ ኤድዊን ኢ. አልድሪን ጁኒየር እና ሚካኤል ኮሊንስ በሚመሩት የአፖሎ 11 ተልዕኮ አማካኝነት የሆነ ነበር፡፡ አርምስትሮንግ ጨረቃን በእግሮቹ የረገጠው የመጀመሪው ሰው ለመሆን ሲበቃ ከእርሱ ሃያ ደቂቃን ዘግይቶ ከመጓጓዣቸው የወጣው አልድሪን ሁለተኛው ሰው ለመሆን በቅቷል፡፡ እንሆ ይህ በህዋ ሳይንስ ውስጥ እንደ ትልቅ እርምጃ የሚወሰድ ተግባር የተከናወነበትን 50ኛ ዓመት ከሁለት ቀናት በፊት ደፍኗል፡፡

የሃምሳኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ሂውስተን፤ ቴክሳስ በሚገኘው የናሳ ጎብኚዎች ማዕከል የአዲስ ዓመት አቀባበል በሚመስል መልኩ በኮንሰርት ታጅቦ ሲከበር በዋሽንግተን መታሰቢያ ላይም የጨረቃን ምስል የሚያሳዩ ምስሎችን ለ16 ደቂቃዎች በማንፀባረቅ ተከብሯል፡፡ ሌሎች የአሜሪካን ከተሞችም በተመሳሳይ በድምቀት አክብረውት ሲያልፉ በተቀረው ዓለምም ከማክበር አልቦዘነም፡፡ ከነዚህ ውስጥ በፓሪሱ ግራንድ ፓላሲስ ጨረቃን የሚወክል ቅርፅ በማንጠልጠልና ሌሎች ትዕይንቶችን በማከናወን የተካሄደው አውደ ርዕይ ይጠቀሳል፡፡

ይህ ዓለምን ለሃምሳ ዓመታት ያስደነቀ ሁነት ከሳይንስ ስኬትነቱ በተጨማሪ ለጥርጣሬዎችም መነሻ ከመሆን አልዳነም፡፡ ለዚህ ተጠቃሹ የተልዕኮውን ዕውነተኛነት የሚጠይቀው ነው፡፡ በዋናነት የጨረቃን ጉዞ በሐሰትነት በሚወነጅሉ ሰዎች የሚራመደው ይህ ሐሳብ ጅማሬውን ያደረገው የአሜሪካን አየር ኃይል ባልደረባ የነበረው ቢል ካይሲንግ “We Never Went to the Moon: America’s Thirty Billion Dollar Swindle” በሚል ስያሜ ከ33 ዓመታት በፊት ካሳተመው አወዛጋቢ መፅሐፍ በኋላ ነበር፡፡ የመፅሐፉ ማጠንጠኛ ናሳ ፕሬዘዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዴ የሰጡትን የሰው ልጅን እ.አ.አ በስልሳዎቹ መባቻ ጨረቃ ላይ የማሳረፍ ተልዕኮን ማሳካት ባለመቻሉ ሰዎችን ወደ ምድራችን ምህዋር ብቻ መላኩን እና ለዚህም የቅርብ ዕውቀት እንዳለው ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የተነሳው ይህ ፅንሰ ሐሳብ የኋላ ኋላ የሐገሪቱ የስለላ ተቋማት ገብተውባቸው የነበሩትን የሐሰት ተግባራት በመንተራስ በመላው ዓለም ቁጥራቸው የበዛ ተከታዮችን ሊያፈራ በቅቷል፡፡

ውዝግቦችን ለጊዜው ወደጎን በመተው ተልዕኮውን የተመለከትን እንደሆነ ይህ ጉዞ በተለያዩ አስገራሚ ዕውነታዎች የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፤

• አርምስትሮንግ ከመሬት ከተነሳበት ቅፅበት አንስቶ ጨረቃ ላይ ደርሶ ከመንኮራኩሯ በመውጣት የጨረቃን ምድር እስከረገጠባት ቅፅበት ድረስ 109 ሰዓታት ከ42 ደቂቃ ፈጅቶበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው በጉዞ የጠፋ ነው፡፡
• ከጨረቃ ወደ ምድር የተደረገው የመልስ ጉዞ በበኩሉ 195 ሰዓታት፣ 18 ደቂቃ እና 35 ሰኮንዶችን ወስዷል፡፡
• ተጓዥ ቡድኑ ከጨረቃ ወደ ምድር ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት 106 የተለያዩ ቁሳቁሶችን እዚያው ጨረቃ ላይ ትቶ የነበረ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ጉዞውን የሚያከብሩ የ74 ሐገራት መሪዎችን መልዕክትን የያዘ የሲልከን ዲስክ፣ በወርቅ የተሰራች አነስተኛ የዘንባባ ቅጠል፣ ሁነቱን ለዓለም ያስተላለፉት ካሜራዎች፣ ሽንትና ሰገራ እንዲሁም ባንዲራ ይገኙበታል፡፡
• ሚካኤል ኮሊንስ ከሌሎቹ ተመራማሪዎች ጋራ አብሮ ወደጨረቃ ቢጓዝም ቅሉ ሁለቱ ባለደረቦቹ ጨረቃን ሲረግጡ እርሱ ግን ከላይ በመሆን እስከ ጥልቅ ክፍሏ ድረስ በጨረቃ ሰማይ ላይ በምህዋሯ እንዲሽከረከር ተገዶ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለ45 ደቂቃዎች እዚሁ መሬት ላይ ከነበረው የናሳ መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንኙነቱ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የዓለማችን ብቸኛው ሰው የሚል ተቀፅላ ስምን ሸምቷል፡፡
• አፖሎ ጋይዳንስ ኮምፒውተር (AGC) በመባል የምትታወቀው እና በአፖሎ 11 ውስጥ ተገጥማ ጉዞውን ያስተናበረችው ኮምፒውተር የራም (Random Access Memory) አቅሟ አሁን ካሉት ስማርት ስልኮች ሲነፃፀር ከአንድ ሚሊዮን እጥፍ በላይ ያነሰ ሲሆን ይህን ንፅፅር ወደ ሮም (Read Only Memory) ያመጣነው እንደሆነ ወደ 4.4 ሚሊዮን እጥፍ ይጠጋል፡፡ በተጨማሪም የኮምፒውተሯን ፕሮሰሰር ከዘንድሮዎቹ ስማርት ስልኮች አንፃር ሲታይ 100,000 እጥፍ ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
• ይህ ሁነት በመላው ዓለም በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የተላለፈ ሲሆን ከ600 ሚሊዮን የላቁ ሰዎችም በቴሌቪዥን መስኮቶቻቸው በቀጥታ ተከታትለውታል፡፡

ምንጭ፡ bbc፣ የናሳ ድረ-ገፅ እና ሌሎችም