TechIn2
1.17K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
ኮቪድ ያላቆመው የፈጠራ ስራ በአለማችን
***************************************
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአዕምሯዊ ንብረት ኤጀንሲ የፈጠራ ስራ ኮቪድ በተስፋፋበት ወቅት እንኳን እድገት እንዳስመዘገበ ገለጸ፡፡ ቴክኖሎጂ፣ የመድሃኒት ቅመማ እና የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ከፍተኛውን እድገት በማስመዝገብ ከአንዳንድ ዘርፎች በተቃራኒው የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎችን እንደሰሩ ታውቋል፡፡

ይህ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማበረታታት፣ በማገዝና የፈጠራ ስራዎቻቸውን በመመዝገብና እውቅና በመስጠት የሚታወቀው የአለም የአእምሯዊ ንብረት ተቋም የፈጠራ ስራ እድገት እያስመዘገበ ቢሆንም አጠቃላይ የፈጠራ ስራ ስነ ምህዳር ግን የሚጠበቅበትን ያክል ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበ እንዳልሆነ አሳስቧል፡፡ በመሆኑም ሀገራት ከወረርሽኙ በኋላ ከዘርፉ ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅም በማሰብ መስራት እንዳለባቸው ምክሩን ለግሷል፡፡

በ2020 የፈጠራ ስራ ደረጃ መሰረት ሲውዘርላንድ፣ ስዊዲን፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው ስራ ያስመዘገቡ ሲሆን ቻይናና ፈረንሳይ ደግሞ ደረጃቸውን በማሻሻል በእስያን፣ በአውሮፓንና በሰሜን አሜሪካ የበላይነት የተያዘውን የዘርፉ ግንባር ቀደምነት ተቀላቅለዋል፡፡

ኮቪድ 19 ብዙ የስራ ዘርፎችን ያቀዛቀዘ ሲሆን እንደ ኮሚኒኬሽን፣ ሀርድዌር፣ አይ.ሲ.ቲ፣ መድሃኒት ቅመማ እና ባዮ ቴክኖሎጂን የመሰሉ ዘርፎች በተቃራኒው ከፍተኛ መነቃቃት ታይቶባቸዋል፡፡

ይህ የ132 ሀገራትን የፈጠራ እንቅስቃሴ የመዘገበው መረጃ ከ2019 ይልቅ ዘርፉ ከፍተኛ እድገት ያስመዘገበ እንደሆነና በመቶኛም 8.5 እድገት ማሳየቱን አመላክቷል፡፡ በአለማችን የሚገኙ እንደ አፕል፣ ማይክሮሶፍትና ሁዋዌ የመሰሉ የቴክሎጂ ካምፓኒዎች ካለፈው አመት በ10 በመቶ ከፍ ያለ የኢንቨስትመንት ስራ መስራታቸው ታውቋል፡፡

ምንጭ techxplore
ተጨማሪ ንባብ https://techxplore.com/news/2021-09-agency-coronavirus-emerged.html
ወድቀው የማይሰበሩበት ምድር
************************
በአለማችን ላይ ከተለመደው ውጭ የሆነ የእሳተ ገሞራ ወይም ቅልጥ አለት ያለባት ሀገር ታንዛኒያ ናት፡፡ በአካባቢው ቋንቋ ‹ኦል ዶይንዮ ሌንጋዪ› ወይም የእግዚአብሔር ተራራ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በአካባቢው ያለው በጣም ዝቅተኛ ሀይል ወይም ንደት ያለው ፍንዳታ አለቶቹ ቢወድቁባቸው ጉዳት የማያደርሱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ቅልጥ አለቱ በአመዛኙ መጨመር በማያሳይ 520 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ባዛልት ከሚሰኘው በብዛት ከሚታወቀው የፍንዳታ አይነት ያነሰ ፍንዳታ ያለው ነው፡፡ ባዛልት የተሰኘው ቅልጥ አለት 1000 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚጠጋ መጠነ ሙቀት የሚፈነዳ የገሞራ አይነት ነው፡፡ በታንዛኒያ ያለው ይህ ገሞራ ከገሞራ ሙቀት አንጻር በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ ምንጊዜም አለቱ ጥቁር ሆኖ ይታያል፡፡ ይህም ማለት ፍህም እንደሚመስል የሚያስችለው ሙቀት የሌለው ነው ማለት ነው፡፡

በ2007 አንድ ሰው በዚህ ቅልጥ አለት ላይ ወድቆ በመጠነኛ ጉዳት ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ለህይወት የሚያሰጋ ጉዳት እንዳልደረሰበት ተነግሯል፡፡ ከዚህ በጣም ዘገምተኛ ከሆነ ገሞራ የሚወጣው ቅልጥ አለት ‹ካርቦንታይት› የሚሰኝ ሲሆን ከአብዛኛው ቅልጥ አለቶች በተለየ የአልካሊ ውህድ የሆኑ ካልሺየምና ሶዲየም የያዘ ነው፡፡ ቅልጥ አለቶች በብዛት የሲልካ እና የኦክስጅን ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡

ምንጭ iflscience
ተጨማሪ ንባብ https://www.iflscience.com/environment/volcano-lava-cold-fall-survive/?fbclid=IwAR0_Y70OKo2zUzfUXC6OLdv2r_7atRA6Mm6Zudde1IL-qO8PH6XrwafhczA
ሁለገቡ የኮንቨርጀንስ ሳይንስ የምርምር እድገት
ሁለገቡ የኮንቨርጀንስ ሳይንስ የምርምር እድገት
======================
ኮንቨርጀንስ ሳይንስ (Convergence science) የሳይንቲፊክ ምርምር አሰራር ሰፊ አስተሳሰብ ሲሆን በአንድ ዘርፍ ላይ ከማተኮር ይልቅ የተቀናጀ የምርምር አሰራር ላይ ያተኩራል። ኮንቨርጀንስ ሳይንስ በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ስፔሻላይዝ ከማድረግ ወይም በአንድ ዘርፍ ላይ ከመብቃት ይልቅ ብዙ መስኮች ላይ ማተኮር የሚፈልግ ሳይንስ ነው። ይህም አንድ የህክምና ባለሙያ የአይሲቲ ባለሙያ፣ መሃንዲስ፣ የኤሌክትሮኔክስ ባለሙያ፣ የፊዚክስ ባለሙያ ወይም ሌላ የኬሚስትሪ ባለሙያ እንዲሆን የሚጠይቅ ዘርፍ ነው።

በርካታ ሰዎች ኮንቨርጀንስ ሳይንስ ለፈጠራ መሰረት ወይም ፈር ቀደጅ ነው ይሉታል። የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ማቴሪያል ሳይንስ፣ ናኖ ቴክኖሎጂ፣ ኦፕቲክስ፣ ኳንተም ፊዚክስ፣ ኮምፒውቲንግ፣ ሲሙሌሽን እና ሞዴሊንግ የመሳሰሉ ዘርፎች በማደጋቸው የተነሳ ሙሉ ለሙሉ የፊዚካል ሳይንስን ሊቀይር ችሏል። ኮንቨርጀንስ ሳይንስ ቴክኒካዊ መሣሪያዎች፣ የተለያየ ሙያዊ ቅርጾች (ምህንድስና፣ ፊዚክስ) በህይወት ሳይንስ ጥናት ላይ ተግባራዊ ይደረጋሉ። የፊዚካል ሳይንስ የህይወት ሳይንስን እየቀየረ እንዳለ ሁላ በተቃራኒው የህይወት ሳይንሱ ፊዚካል ሳይንሱን በመቀየር ላይ ይገኛል። የባዮ ፊውል፣ ባዮ ማቴሪያል እና ቫይራል ሰልፍ አሴምብሊ ፊዚካል ሳይንስን በመቀየር ላይ የሚገኙ ጥቂት የህይወት ሳይንስ ምሳሌዎች ናቸው።

ከኮንቨርጀንስ ሳይንስ ጠቀሜታዎች መካከል ኮንቨርጀንስ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ወይም ለመፍጠር ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የተለያዩ ዘርፎች አንድ ላይ በመጣመር የሚሰሩ ተግባራት ከፍተኛ ጥቅም አላቸው። ጥናትና ምርምር ደግሞ አዲስ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ነገሮችን ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው። የኮንቨርጀንስ ጥናትና ምርምርም ከተለያዩ ዘርፎች የተሰባጠሩ ሙያተኞች/ ምሁራንን በመያዝ ችግር ፈቺና አዲስ የሆኑ ስራዎችን ይሰራል። ኮንቨርጀንስ ጥናት በአንድ ዘርፍ ስፔሻላይዝ ባደረገ ሰው ብቻ መሰራት አይችልም። የኮንቨርጀንስ ጥናትና ምርምርን ለማከናወን ሁለት እና ከዛ በላይ የሆኑ ዘርፎች በአንድ ላይ መጣመር ግድ ይላል። በተለያዩ አለማት ዙሪያ ኮንቨርጀንስ ጥናትና ምርምር አሰራር በርካታ ተመራማሪዎች እየሰሩበት የሚገኝ ዘርፍ ነው።ይህም አለማችንን አዲስ ወደሆነ ምዕራፍ እያሸጋገራት የሚገኝ እና ትኩረት የሚሻ የጥናትና ምርምር አይነት ነው።
https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC5540327/#:~:text=Convergence%2C%20or%20transdisciplinary%20science%2C%20is,problem%2C%20topic%2C%20or%20theme.
ታዳጊ የኢኖቬሽን አምባሳደሮች ተመረቁ
ታዳጊ የኢኖቬሽን አምባሳደሮች ተመረቁ
===============
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ አልሞ ባዘጋጀው የኢኖቬሽን አምባሳደር ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ተማሪዎችን ወላጆች፣ አጋዥ ተቋማትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በትናንትናው ዕለት አስመረቀ፡፡ በዕለቱ በተከናወነው በዚህ የምረቃ መሰናዶ ላይ ለተማሪዎቹ የእውቅና እንዲሁም በሁዋዌይ አማካኝነት የተዘጋጀ የማበረታቻ ስጦታ ሲበረከትላቸው ተማሪዎቹ በቆይታቸው ማጠናቀቂያ የሰሯቸው ፕሮጀክቶች በእንግዶች ተጎብኝተዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ለተገኙት የእንኳን መጣችሁ ንግግር ያሰሙት የቴክኖሎጂ እና ኦኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም ቴክኖሎጂ ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ቢሆንም ከገበያ ገዝቶ ለመጠቀም አስቸጋሪና ከፍተኛ ወጪ ብሎም ዕውቀትን በመጠየቁ ከታችኛው ደረጃ አንስቶ ባሉት ተማሪዎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አጉልተዋል፡፡ ለተመራቂ ተማሪዎቹም ኢኖቬሽንን በሄዳችሁበት ቦታ ሁሉ በማስተዋወቅና ወደፊትም በሰለጠናችሁበት ሙያ ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ ተሳትፋችሁ አኩሪ አስተዋፅዖ እንደምታድርጉ ከፍተኛ እምነት አለኝ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ ሆነው ከሰፊው የህይወት እና ሙያዊ ተሞክሮአቸው ለተመራቂ ተማሪዎቹ ያካፈሉት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታው ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ ተማሪዎቹ ራዕይ እንዲኖራቸውና ያለንበት ጊዜ ምሁራን በብዛት የሚገኙበት እንደመሆኑም እነርሱን ተጠቅመው ራዕያቸውን እንዲያሳኩ ምክራቸውን ለግሰዋቸዋል፡፡ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ እኛን አይመጥነም ያሉት ፕ/ር አፈወርቅ የሰለጠናችሁትን ተጠቅማችሁ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ እንድታስፈነጥሩ ሲሉ አደራ የቀላቀለ ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላኛው የእለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ስሜነው ቀስቅስ በበኩላቸው “ኢኖቬሽን ኢኮሲስተም ኢን ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በሀገራችንም ያለውን የኢኖቬሽን እንቅስቃሴ፣ ዕድል፣ ተግዳሮት፣ ፖሊሲ ብሎም ተቋማቸው ስቴም ፓወር ኢኖቬሽንን በማስፋፋትና የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ ረገድ እየሰራ ስላላቸው ስራዎች ገለፃ አቅርበዋል፡፡ አክለውም እንደተቋም ለወደፊት ከተመራቂ ተማሪዎቹ ጋር ለመስራት ያላቸውን ፈቃደኝነት ገልፀዋል፡፡

ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው ስልጠና እና የሰመር ካምፕ ቆይታቸውን አጠናቀው ትናንት የተመረቁት ተማሪዎቹ በቀጣይ የኢኖቬሽን ባህልን የሚያስገነዝቡ ሁነቶችን በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማዘጋጃ ቦታዎች የማዘጋጀት፣ ሀገርና ዓለም አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኩነቶች ላይ የሚሳተፉ እንዲሁም የኢኖቬሽን ባህል እንዲያድግ የሚሰሩ ይሆናል፡፡
ለተማሪዎች በነጻ የቀረበው የኤሌክተሮኒክ ሲሙሌሽን መተግበሪያ
ለተማሪዎች በነጻ የቀረበው የኤሌክተሮኒክ ሲሙሌሽን መተግበሪያ
========================
የተለያዩ የኢንዱስትሪያ ውጤቶችን በኮምፒውተር የሲሙሌሽን ስርዓት ለማበልፀግ እና አዳዲስ የንድፍ ስልቶችን ለመማር የሚያስስችል የ Ansys መተግበሪያ ለተማሪዎች፣ ለሰልጣኞች እና ለትምህርቱ ፈላጊዎች በነፃ መቅረቡ ተነግሯል፡፡ የኤሌክተርሮኒክ ሲሙሌሽን ወይም በሙሉ ስያሜው ኤሌክትሮኒክ ሰርኪዩት ሲሙሌሽን የሂሳብ ሞዴሎችን በመጠቀም መደበኛ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለማውጣት የሚስችሉ ሲሙሌሽን ወይም አምሳያዎችን በኮምፒውተር አልጎሪዝም አማካኝነት ለማቀናበር እና ለመቅዳት የሚያስችል በምህንድስና ዘርፍ ውስጥ የሚካተት ትምህርት ነው፡፡ በኮምፒውተር ሲስተም አማካኝነት የሚከናወነው ይህ የቴክኖሎጂ መስክ ለዚሁ አገልግሎት ተብለው በበለፀጉ መተግበሪያዎች አማካኝነት ሊተገበር ይችላል፡፡

በቅርቡ Ansys በተባለው የቴክኖሎጂ ኩባንያ በነፃ ያቀረበው አዲስ የኤሌክተሮኒክ ሲሙሌሽን መተግበሪያ ለተማሪዎች እና ለሰልጣኞች አዳዲስ የንድፍ ስልቶችን ለመማር የሚያስችሉ ጠቃሚ የኤሌክተሮኒክ ሲሙሌሽን አሰራሮችን ወይም ቱሎችን በማካትት ከፕሮጀክት እቅድ አንስቶ የሞዴል ፈጠራ እና የኤክስፕርመንቴሽን ትንተና ሂደቶችን በቀላሉ ለማስተማር የቀረበ ነው፡፡ በመተግበሪያው አማካኝነት የሚቀርቡት ጠቃሚ የሲሙሌሽን ክህሎት መማሪያ መሳሪዎች ለማናቸውም የኤሌክትሪካል ምህንድስና አጥኝዎች አልያም እውቀቱን ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ጠቃሚ ትምህርቶችን የሚያስገኙ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ንድፍ ከመስራት አንስቶ ጥራታቸው እጅግ ከፍ ያሉ ሲሙሌሽን ለማበልፀግም የሚረዱ ናቸው፡፡

በምህንድስናው ዘርፍ የኮምፒውተር ሲሙሌሽን ትግበራዎች ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ባሉበት በአሁን ሰዓት የእውነተኛውን አለም ችግር በአነስተኛ ወጪ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለመፍታት የሚስችሉ የሲሙሌሽን ቴክኒኮችን ለመማር በዘርፉ ተቋማት የሚቀርቡ የመተግበሪያ አማራጮችን መጠቀም ትልቅ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፡፡

በዚህ የኤሌክተሮኒክ ሲሙሌሽን የትግበራ ዘርፍ ውስጥ በበይነ-መረብ የሚገኙ ብዛት ያላቸው የኦንላይን ወይም የኦፍላይን መተግበሪያዎች ቢኖሩም ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ኖሯቸው ለሰልጣኞች ወይም ለተማሪዎች አስፈላጊውን የክህሎት ስልጠና የሚሰጡት አማራጮች እጀግ አነስተኛ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ Ansys ያሉ የኤሌክተሮኒክ ሲሙሌሽን መተግበሪያ አማራጮች በሙያው ረዥም ርቀት መጓዝ ለሚፍልጉ ሰልጣኞችና ተማሪዎች ደረጃው እጅግ ከፍ ያለ የሲሙሌሽን ቴክኒክ እና ተያያዥ እውቀቶችን ለማግኘት ትክክለኛው ቦታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ምንጭ፡ techgz
https://techgz.net/2021/09/20/ansys-has-just-released-its-free-desktop-electronics-student/
የመተግበሪያው ሊንክ https://www.ansys.com/academic/students/ansys-electronics-desktop-student?utm_campaign=academic&utm_medium=paid-trade&utm_source=interesting-engineering%20&utm_content=partner_electronics_web-banner-aedt-student_product-page_download_sponsored-content_en_global&campaignID=7013g000000HRcDAAW
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኖቬሽን መለኪያ ደረጃዋን በአንድ አሻሻለች
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኖቬሽን መለኪያ ደረጃዋን በአንድ አሻሻለች
==================
ከቀናት በፊት በወጣው ዓለም አቀፉ የኢኖቬሽን መለኪያ ወይም ኢንዴክስ ኢትዮጵያ አምና ከነበረችበት 130ኛ ደረጃዋን በአንድ በማሻሻል 129ኛ ሆና ተቀምጣለች፡፡ ኢትዮጵያ 18.6 ነጥብ በማምጣት ነው በዚህ ዝቅተኛ ሊባል በሚችል ደረጃ ላይ የተቀመጠችው፡፡

መለኪያው 7 ዓባይት ጉዳዮችን፤ ተቋማትን፣ የሰው ኃይልና ምርምር፣ መሰረተ ልማት፣ የገበያ ልህቀት፣ የቢዝነሶች ልህቀት፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ወጪ ምርት እንዲሁም የፈጠራ ወጪ ምርትን ከግንዛቤ በማስገባት የተቀመጠ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በሦስት ዘርፎች ላይ የደረጃ መሻሻልን በማሳየት የሰው ኃይልና ምርምር ከ128ኛ ወደ 126ኛ፣ በገበያ ልህቀት ከ131ኛ ወደ 130ኛ እንዲሁም በእውቀትና ቴክኖሎጂ ወጪ ምርት ከ87ኛ ወደ 81ኛ ደረጃዋን ማሻሻል ችላለች፡፡ ሆኖም በተቃራኒው በሌሎች ሦስት ዘርፎች ከነበረችበት በማሽቆልቆል በመሰረተ ልማት ከ108ኛ ወደ 121ኛ፣ በቢዝነስ ልህቀት ከ120ኛ ወደ 126ኛ እንዲሁም በፈጠራ ወጪ ምርት ከ119ኛ ወደ 127ኛ ወርዳለች፡፡ የተቀረው የተቋማት ዘርፍ አምና ከነበረችበት ሳይለወጥ 116ኛ ሆና ቀጥላለች፡፡

ከነዚህ ዘርፎች መካከል 6 ደረጃዎችን በማሻሻል ቀዳሚውን እምርታ ያሳየችው በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ወጪ ምርት ዘርፍ ሲሆን በውስጡ ካሉት ሦስት መለኪያዎች መካከል በእውቀት ስርጭት ረገድ መልካም የሆኑ የደረጃ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ ይህም ሲባል ሀገራችን በአዕምሮ ንብረት ምዝገባ፣ ወደውጭ በምትልካቸው የቴክኖሎጂ እና የአይሲቲ ምርቶች ረገድ መልካም መሻሻያዎች ታይተዋል፡፡ በአንፃሩ ደረጃው ካሽቆለቆለባቸው ዘርች መካከል ቀዳሚው በሆነው በመሰረተ ልማት ረገድ ጠቅላላ መሰረተ ልማትን ስናይ ከፍተኛ መሻሻል ቢኖርም ከአይሲቲ ጋር በተያያዙት እንደ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ተደራሽነት፣ የዜጎች ኤሌክትሮኒክሳዊ ተሳትፎ ብሎም የዜጎች አይሲቲ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር ባሉት መለኪያዎች ሲታይ ደረጃዋ ከአምና አሽቆልቁሏል፡፡

132 ሀገራትን በተመለከተው በዚህ መለኪያ ዝቅተኛ የገቢ መጠን ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ የ10ኛ ደረጃን ስትይዝ ኢንዴክሱ ላይ ከተካተቱት ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ውስጥም 23ኛ ላይ ተገኝታለች፡፡ ይህም በኢኖቬሽን ረገድ ብዙ ስራዎች መሰራት አንዳለባቸው የሚያሳይና እጅግ ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡

በአንፃሩ ሞሪሺየስ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬኒያና 35.2፣ 32.7 እና 27.5 ነጥብ በማስመዝገብ ከሰሀራ በታች ካሉት የአፍሪካ ሀገራት ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን እና አሜሪካን 65.5፣ 63.1 እና 61.3 ነጥብ በማስመዝገብ ከፊት ተቀምጠው ይመራሉ፡፡

በዓለም አቀፉ የአዕምሮ ንብረት ድርጅት እና አጋር ተቋማት ቅንጅት በየዓመቱ እየተዘጋጀ የሚወጣው የዓለም የኢኖቬሽን መለኪያ ከአውሮፓውያኑ 2007 አንስቶ ሀገራት በኢኖቬሽን ረገድ የሚያሳዩትን ስኬታማነት በመመልከት ደረጃ የሚያወጣ ነው፡፡
የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ተሸለሙ
*****************************************
ሀገራችን ኢትዮጵያ ካሏት ህዝቦች ውስጥ ከ70 እስከ 80 የሚደርሱት በገጠር የሚኖሩ እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ በገጠር የሚኖሩ አብዛኘዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች የመኖሪያ አካባቢያቸው የመሰረተ ልማት ተደራሽነት እጥረት ያለበት በመሆኑ መንግስት ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ እየሰራ ይገኛል፡፡
በገጠር የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል በብዛት ከሚቸገርባቸው የመሰረተ ልማት ፍላጎቶች መካከል የሀይል አቅርቦት ፍላጎት አንደኛው ነው፡፡ ይህ ፍላጎት በተገቢው ፍጥነትና ጥራት የሚሟላበት መንገድ ካልተፈለገ ይህ የህብረተሰብ ክፍል በሀይል እጦት ምክንያት ከሚደርስበት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና በተጨማሪ ሀገራችን የምትከተለውን የአረንጓዴ ልማትና ሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚቃረኑ እንደ ደን ጭፍጨፋ እና ለአካባቢ ብክለት ተጋላጭ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ መሰማራቱ የማይቀር ነው፡፡
ይህንን ችግር ያስተዋለው የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ አካባቢ ፈንድ (GEF)፣ ከተባበሩት መንግሥታት ልማት ፈንድ(UNDP) እና ከተባበሩት መንግስታት ካፒታል ልማት ፈንድ( UNCDF) ጋር በመተባበር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር በማዘጋጀት አሸናፊ ለሆኑ 19 የሦስተኛ ዙር ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 8000 ዶላር (348 ሺህ 721 ብር)፤ ለ9 የ4ኛ ዙር ውድድር አሸናፊዎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 33,333 ዶላር (1 ሚሊየን 453 ሺህ 8 ብር) ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በሳካይ ላይት ሆቴል የተካሄደውን የሽልማት መርሐ ግብር በንግግር የከፈቱት በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍሬሕይወት ወልደ ሐና ሽልማቱ ዘላቂ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጅዎችን ለማስፋፋት በ2016 ይፋ በሆነውና የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከGEF, UNDP እና UNCDF ጋር በጋራ በመሆን የሚተገብረው ፕሮጀክት አካል መሆኑን ጠቁመው የፕሮጀክቱ ዋና ዓለማ በገጠር የሚኖረው የሕብረተሰብ ክፍል ለቤት ውስጥና ለሌሎች የምርት ሂደቶች ታዳሽ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም፤ በዚህም የዛላቂ የልማት ግቦች ግብ 7 እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ የኢነርጂ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ማሳካት መቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ታዳሽ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ላይ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ኢንተርፕራይዞችና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ገልጸው አሸናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ሽልማትና ለሥራቸውም እውቅና የሚሰጥበት መሆኑን በመጠቆም በውድድሩ አሻናፊ ለሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ዘላቂ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፊያ ፕሮጀክት ታዳሽ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋትና በገጠር የሚኖረው የሕብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀም በማበረታታች የካርቦንዳይኦክሳይድን ልቀትን ለመቀነስና ኢነርጂን ለመቆጠብ በውሃ፣መስኖና ኢንረጂ ሚኒስቴርና በልማት አጋሮች ትብብር በመተግበር ላይ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡
እንዲህ አይነት ፕሮጀክቶች መተግበራቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለፈጠራ ባለቤቶችና ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል እንደሚሰጡ ይታመናል፡፡
ምንጭ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር
በልጆች መጫዎቻ ሰው ሰራሽ ክንድ የሚሰራው ብልሁ የፈጠራ ሰው
========================
ፖሊሽ ሲንድሮም በተባለው ከባድ በሽታ ከልጅነቱ የተያዘው ዴቪድ እንደ እድሜ እኩዮቹ በሁለቱ እጆቹ ያሻውን ለማድረግ አይችልም ነበር፡፡ ገና ወደዚህች ዓለም ሲቀላቀል የቀኝ ክንዱን የተነጠቀው ይህ ህፃን በእድሜ እኩዮቹ የሚደርስበት እንግልትና ማዋከብ በራሱ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርገው ነበር፡፡ በህጻንነቴ ሁሌ ራሴን በመስታዎት ስመለከት እንደሁሉም ሰዎች ሁለት እጆች ይዤ አለመወለዴ በጣም እንድበሳጭ እና እንዳዝን ያደረግኝ ነበር የሚለው ዴቪድ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ብዙ ሃሳቦችን ማውጠንጠን እና ፈጠራዎችን በራሴ ለመስራት ቁጭት አሳደረብኝ ይላል፡፡

ገና ከ9 ዓመቱ ጀምሮ በቤት ውስጥ ለመጫወቻ በተገዛለት የሌጎ ጡቦች ሰው ሰራሽ ክንድ ለመስራት ሲጥር የነበረው ዴቪድ ከብዙ ሙከራዎች በኋላ በቀኝ እጁ ላይ ሊገጠም የሚችል ተጣጣፊ ክንድ መስራት ቻለ፡፡ ዴቪድ የልጆች መጫዎች ከሆኑት የሌጎ ጡቦች ያበለፀገውን ይህን ሰው ሰራሽ ክንድ ይበልጥ እያዳበረ እና እያሳደገ ከመጣ በኋላ ስራውን ከጀመረበት ከዘጠኝ አመታት በኋላ ለተጎዱ ሰዎች በሚገባ ግልጋሎት መሰጥት የሚችል እና አስገራሚ ንድፍ ያለው ሰው ሰራሽ ክንድ ሰርቶ በማቅረብ በ2017 በጊነስ የአለም ሪከርድ ፈጠራውን ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡

ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሌጎ ጡቦች አማካኝነት ለራሱ የሰራውን ሰው ሰራሽ ክንድ በመጠቅም ሙሉ ጊዜውን መስል ችግር ላለባቸው ሰዎች ፈጠራውን ለማቅረብ ሲሰራ የቆየው ዴቪድ፤ ፖሊሽ ሲንድሮም በተባለው በሽታ ሁለት ክንዶችን ላጣው የስምንት አመት ህጻን ፈጠራውን ሰርቶ ማቅረብ ችሏል፡፡ መጀመሪያ ስሰራቸው ከነበሩት ሰው ሰራሽ ክንዶች አሁን ላይ ያሉት ምቾት ያላቸውና በተገጠመላቸው ኮንትሮል ዩኒት በቀላሉ ትዕዛዝ መቀበል እንዲችሉ ተደርገው መሰራታቸውን የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው ዴቪድ ለስምንት ዓመቱ ህፃን ቤንኩር የሰራውም ሰው ሰራሽ ክንድ በቀላሉ ትዕዛዝ ሊቀበል የሚችል እና የህጻኑን ምቾት የማይነሳ ፈጠራ መሆኑን ይናገራል፡፡

የህጻኑ ቤንኩር ወላጀች ዴቪድ የሚሰራቸውን ሰው ሰራሽ ክንዶች በጊነስ የአለም ሪከርድ ዜና ላይ ከተመለከቱ በኋላ ለልጃቸው የሚሆን ሰው ሰራሽ ክንድ ለማሰራት ከሚኖሩበት ፈረንሳይ ዴቭዲ ወዳለበት አንዶራ 1,300 ኪ.ሜትሮችን ተጉዘው አግኝተውታል፡፡ የፈጠራ ባለሙያው አጭር ጊዜ ወስዶበት ለህጻኑ ማቅርብ የቻለው የሌጎ ሰው ሰራሽ ክንድ የህጻኑን ምቾት በጠበቀ መልኩ የተሰራ ከመሆኑም ባለፈ ትዕዛዝን ተቀብሎ የመፈፀም አቅሙ እጅግ የላቀ ነበር፡፡ ዴቪድ ይህን አስገራሚ የፈጠራ ውጤት ለወላጆቹ ሰርቶ ለማቅረብ የተጠቀማቸው የሌጎ ጡቦች እና አንዳንድ የኤሌክተሮኒክስ ቁሶች በጥቅሉ 18 ዶላር ብቻ መፍጀታቸው ብዙዎችን ያስደነቀ ጉዳይ ነው፡፡

ፖሊሽ ሲንድሮም በተባለው በሽታ የአካል ጉድለት ላለባቸው ብዙ ሚሊዮኖች ፈጠራውን ማቅረብና መርዳት የሚፈልገው ዴቪድ በቀጣዮቹ አመታት አሁን ካሉት ስራዎች እጅግ የላቀ እና ልክ እንደተፈጥሮ አካል በቀላሉ መንቃሰቀስ የሚችሉ ሰው ሰራሽ ክንዶችን በመላው ዓለም ለማቅረብ እቅድ እንዳለው ይነገራል፡፡ በኔ የደረሰው የህይወት አጋጣሚ ለብዙ ህፃናት ትልቅ ትምህርት እና መነሳሳት እንደሚፈጥር የሚናገረው ዴቪድ ከተለያዩ የተፈጥሮ ወስንነት አደጋዎች ጋር የሚወለዱ ብዙ ሚሊዮን ታዳጊዎች በሰዎች ላይ ጥገኛ ብቻ ሳይሆኑ ለብዙዎች መትረፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ ክስተት ነው ይላል፡፡
ምንጭ፡ techgz
https://techgz.net/2021/09/21/an-ingenious-inventor-created-a-prosthetic-arm-for-an-8-year-old-lego-child/